Sunday, July 7, 2013

ሰበር ዜና:ኢህአዴግ ደንግጧል!! በአዲስ አበባ የአንድነት አባላትን ማሰር ተጀምሯል

በአዲስ አበባ የፀረ ሽብር ህጉ እንዲሰረዝ የሚጠይቅ በራሪ ወረቀት የበተነ የአንድነት አባል በአደራ ታሰረ፡፡

አንድነት ፓርቲ ‹‹የሚሊዮኖች ድምፅ ለነፃነት›› በሚል መሪ ቃል የጀመረውን ህዝባዊ ንቅናቄ አጠናክሮ መቀጠሉን ተከትሎ መንግስት የማደናቀፍ ተግባሩን በአዲስ አበባም ጀምሯል፡፡ የአንድነት ፓርቲ አመራሮች ለፍኖተ ነፃነት እንደገለፁት ሙሉጌታ ተፈሪ የተባለውን የአንድነት ፓርቲ የወረዳ 15 አባል ካዛንችስ አካባቢ በህገወጥ መንገድ በፖሊስ ታስሯል፡፡ ሙሉጌታ ካዛንችስ አካባቢ የፀረ ሽብር ህጉ እንዲሰረዝ የሚጠይቅ በራሪ ወረቀት ሲያሰራጭ መታሰሩን ፖሊስ ተናግሯል፡፡

የአባሉን መታሰር የሰሙት የአንድነት ከፍተኛ አመራሮች አቶ ግርማ ሰይፉና አቶ በላይ ፍቃዱ ካዛንችስ አካባቢ ፖሊስ ጣቢያ ተገኝተው ሙሉጌታ በህገወጥ መንገድ መታሰሩን በማስረዳት ተከራክረዋል፡፡ የጣቢያው ፖሊሶች ግን “ሙሉጌታን ያሰረው ፖሊስ ስለሌለ እሱ ሳይመጣ አይፈታም” በማለት “የአደራ እስር” ከጎንደር በተጨማሪ በአዲስ አበባም መኖሩን አረጋግጠዋል፡፡ አመራሮቹም “እኛም ወረቀቱን እየበተንን በመሆኑ እሰሩን” በማለት ተሟግተዋል፡፡

ዘግይቶ በደረሰን ዜና የአንድነት አመራሮች የታሳሪውን ጉዳይ መከታተላቸውን ተከትሎ ሙሉጌታ ተፈሪ ክቤ በተባለች ፖሊስ “ተመርምሮ” ወደ 6ኛ ፖሊስ ጣቢያ ሊወሰድ መሆኑን የፍኖተ ነፃነት የፖሊስ ምንጮች አስታውቀዋል፡፡

የአንድነት ፓርቲ አዲስ አበባ ዞን አባላት ዛሬ ጠዋት በፓርቲው ዋና ጽ/ቤት በመገኘት ከፓርቲው ከፍተኛ አመራሮች ህዝባዊ ንቅናቄውን በአዲስ አበባ ተደራሽ የማድረግ ተልዕኮ ተቀብለው ከቀኑ 7 ሰዓት ጀምሮ በእንቅስቃሴ ላይ ይገኛሉ፡፡ ከ100ሺ በላይ የሆነ በራሪ ወረቀትም በማሰራጨት ላይ ይገኛሉ፡፡

‎#millionsofvoicesforfreedom ‎#Ethiopia ‎#udj

No comments:

Post a Comment