Friday, July 19, 2013

መድረክ በመቀሌ በሚያደርገው ህዝባዊ ስብሰባ እንዳይቀሰቅስ ተከለከለ

የኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዴሞክራሲያዊ አንድነት ግንባር(መድረክ) የፊታችን እሁድ ሐምሌ 14 ቀን 2005ዓ.ም. ከጠዋቱ 2 ሰዓት ጀምሮ በመቀሌ ከተማ ማጋጃ ቤት አዳራሽ ውስጥ ለሚያካሂደው ህዝባዊ ስብሰባ በመኪና ቅስቀሳ እንዳያደርግ መከልከሉን ከስፍራው የዓረና ትግራይ እና የአንድነት/መድረክ አመራሮች ገለፁ፡፡ መድረክ በሀገራዊ አንገብጋቢ ጉዳዮች ዙሪያ ከመቀሌና አካባቢዋ ነዋሪዎች ጋር ለመወያት ዝግጅቱን ያጠናቀቀ በመሆኑ ህዝቡ በነፃነት ይመክር ዘንድ በተዘጋጀው መድረክ ላይ እንዲገኝ በድምፅ ማጉያ እና በመኪና ቅስቀሳ ማድረግ እንደማይችሉና ለዚህም እውቅና እና ጥበቃ እንደማያደርጉ የከተማው ፖሊስ መምሪያ ኃላፊ ኮማንደር ገ/ህይወት ካሳዬ መናገራቸውን የስብሰባው አስተባባሪ ከሞቴዎች ከመቀሌ በተለይ ለፍኖተ ነፃነት ገልፀዋል፡፡


የዓረና ትግራይ/መድረክ ምክትል ሊቀመንበር አቶ ብርሃኑ በርሄ ስለጉዳዩ ጠይቀናቸው መድረክ ሐምሌ 7 ቀን 2005ዓ.ም. ከጠዋቱ 2 ሰዓት ጀምሮ በማዘጋጃ ቤት አዳራሽ ህዝባዊ ስብሰባ እንደሚያደርግ ለሚመለከተው አካል ብናሳውቅም በድምፅ ማጉያና በመኪና ቅስቀሳ ማድረግ አትችሉም ተባልን፤ ነገር ግን ለህወሓት/ኢህአዴግ ጠቅላላ ሰላማዊ ሰልፍና ስብሰባ በየጊዜው በድምፅ ማጉያና በመኪና ቅስቀሳ ይደረግ የለም ወይ? የሚል ጥያቄ ስናነሳ ህወሓት/ኢህአዴግ ሰላማዊ ሰልፍ ስለሚያደርግ ነው የፈቀድነው፣ አሁን ግን የመቀሌ ህዝብ ድምፅ ማጉያ እየረበሸን ነው በማለቱ በከተማው ምክር ቤት ተወስኗል የሚል አሳዛኝ ምላሽ ተሰጥቶናል ሲሉ ገልፀውልናል፡፡ ሌላው የስብሰባው አስተባባሪ ኮሜቴ አባል በትግራይ የአንድነት/መድረክ ዋና ፀሐፊ አቶ ክብሮም ብርሃነ በበኩላቸው የከተማው ፖሊስ አዛዥና ሌሎች የሚመለከታቸው አካላት ቅስቀሳ እንዳናደርግ ቢከለክሉንም ህዝባዊ ስብሰባው መካሄዱ ስለማይቀር በየቤቱና በየአካባቢው እየተንቀሳቀስን  በራሪ ወረቀት  እየበተንን እና እያሳወቅን ነው፣ ህዝቡም እየተባበረን በመሆኑ የበለጠ ጥንካሬ ሆኖናል ሲሉ በተለይ ለፍኖተ ነፃነት አስታውቀወዋል፡፡

የዝግጅት ክፍሉም በጉዳዩ ዙሪያ በቀጥታ የሚመለከታቸው የከተማውን ፖሊስ ኮሚሽንና ከንቲባውን ለማናገር ጥረት ቢያደርግም አልተሳካም፡፡ መድረክ የፊታችን እሁድ ለማድረግ ያዘጋጀውን ህዝባዊ ውይይት ከጠዋቱ 2 ሰዓት ጀምሮ በመቀሌ ከተማ ማዘጋጃ ቤት እራሽ ለማድረግ መወሰኑንና ጅግጅቱን ማጠናቀቁን መረዳት ተችሏ፡፡

መድረክ እሁድ ከመቀሌና አካባቢዋ ነዋሪዎች ጋር ለመወያየትን የመፍትሄ ሐሳቦች ዙሪያ ሊመክርባቸው ያሰባቸው ዋነኛ ጉዳዮች፡-የመልካም አስተዳደር እጦት፣ የአብዛኛው ወጣቶች አሰቃቂ ስደትና ሞት፣ ኢ-ፍትሃዊ የግብር አወሳሰን ፣ የኃይማኖት ነፃነት፣የዜጎች መፈናቀል፣የአባይ ግድብ ጉዳይ፣ የትምህርት ጥራትና ልማት ችግር፣ የሊዝ አዋጅና የካሳ አወሳሰን ችግር እንደሚገኙበት ከአስተባባሪዎቹ መረዳት ተችሏል፡፡  

Source: Finote netsanet

No comments:

Post a Comment