Tuesday, September 30, 2014

Statement from Ginbot 7 Regarding the Horrific Video of Murdered Civilians in the Ogaden Region

September 28, 2014

Ginbot 7, Movement for Justice, Freedom and Democracy is deeply saddened and outraged by the recent leaked video of barbaric killings of civilians suspected of supporting the Ogaden National Liberation Front (ONLF). Anyone with a conscience should be disturbed by the brutal scenes and sounds of hundreds of civilians whom the regime’s security forces have raped, tortured and killed.

Once again this video is a stark reminder to all Ethiopians, irrespective of their ethnic background and religious affiliation, that Ethiopia is ruled by a savage, blood-thirsty regime carrying out a reign of terror in all parts of Ethiopia.

There are no words of condolence that can adequately convey our sorrow, our sympathy for the victims and their families. The unfathomable brutality of the Tigrai People’s Liberation Front (TPLF) security forces dragging the dead corpses of alleged ONLF supporters in an act of coward savagery is an insult to the moral values of the Ethiopian people, and humanity in general

We affirm our just revulsion over these heinous crimes and call on those responsible for such a heinous crime to be held accountable.

Sunday, September 28, 2014

ህወሃቶች “አቅም ግንባታ” የሚሉት፤ እኛ ደግሞ “አቅም አድክም” የምንለው ሂደት

ህወሃት የመምህራንን፤ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተማሪዎችንና የመንግስት ሠራተኞችን ”አቅም እገነባለው” ብሎ ተነስቷል። ለዚህ “አቅም ግንባታ” እያሉ ለሚጠሩት አሰለቺ እና አደንቋሪ አቅም አድክም ፕሮፖጋንዳ እየወጣ ያለው ወጪ ለሌላ ተግባር ውሎ ቢሆን ኑሮ የተሻለ ይሆን ነበር። የተሻለ ነገር በህወሃቶች መንደር ይሠራል ብሎ መጠበቅ ግን ሞኝነት ነው። ህወሃት የተፈጠረው አገርን ለማፍረሰና ህዝብን ለማስጨነቅ እንጂ የተሻለ ሥራ ሠርቶ ህዝብን ለማስደስት አይደለም።

ህወሃቶች በአፍቅሮተ ንዋይ አብደው አቅላቸውን የሳቱ፤ ለእውቀትና ከእነርሱ በተሻለ ደረጃ ለሚያውቅ ቅንጣትም ታክል ክብር የሌላቸው፤ ውሸት የመኖሪያቸው ድንኳን ሁኖ ለብዙ ዘመን ያኖራቸው ቡድኖች ናቸው። በዚህ ሁኔታ ራሳቸውን የገነቡ ቡድኖች የሌሎችን አቅም እንገነባለን ብለው የመነሳታቸው ነገር አገራችን የገባችበትን የውርደት አዘቀት ፍንትው አድርጎ የሚያሳየን ነው።

የንዋይ ፍቅር የክፋቶች ሁሉ መሠረት ነው። ህወሃቶች በዚህ በክፋት ሁሉ መሠረት በሆነው በንዋይ ፍቅር ያበዱ በመሆናቸው ህወሃቶችን ከክፋት፤ ክፋትን ደግሞ ከህወሃት ለይቶ ለማየት የማይቻልበት ደረጃ ላይ ተደርሷል። እነዚህ ቡድኖች በአፍቅሮተ ነዋይ አብደው ለእብደታቸውም መድሃኒት ጠፍቶ እኛ ከሌለን አገሪቷን እንበትናታለን በሚል ቅዥት ውስጥ እንደሚኖሩም የታወቀ ነው። ህወሃቶች ገንዘብ ሊያሰገኝ የሚችለውን ማንኛውንም ዓይነት ወንጀል ለመፈፀም የሚያቅማሙ አይደሉም። ህዝቡን በሙሉ በገንዘብ የሚገዛ ቢያገኙ ህዝቡን በሙሉ ለመሸጥ ወደ ኋላ ይላሉ ብሎ ማሰብም አይቻልም። ይህን በመሰለ የሞራል ውደቀት ውስጥ የሚገኙ ህወሃቶች የህዝቡን አቅም እንገነባለን ሲሉ ትንሽም አለማፈራቸው አገራችን ከደረሰችባቸው የሞራል ውደቀቶች መካከል አንዱ ሁኖ ሊጠቀስ የሚችል ዓቢይ ጉዳይ ነው።

ህወሃቶች ለእውቀትና ከእነርሱ በተሻለ ደረጃ ማሰብ ለሚችል ሰው ያላቸው ጥላቻ ወደር የለውም። ለዚህም ነው ከእነርሱ መካከል ይሄ ነው ተብሎ ሊጠቀስ የሚችል የተመሰገን የተማረ ሰው የማይገኘው። ለህወሃቶች የተማረ ማለት ሲጠሩት አቤት ሲልኩት ወዴት እያለ ለሆዱ ያደረ እንጂ ለአገሬ፤ ለህዝቤ፤ ለወገኔ ምን በጎ ተግባር ልፈፀም የሚል አስተሳሰብ ያለው ሰው አይደለም። የህወሃቶች ዋነኛው ችግር የተማረ ሰው መጥላታቸው ብቻ ሳይሆን ሁሉንም እኛ እናውቃለን ማለታቸውም ጭምር ነው።ሁሉን እኔ አውቃለሁ ማለት ደግሞ የድንቁርና ታላቅ ምልክት ነው። ከዚህ ድንቁርና ራሱን ማላቀቅ ያልቻለ ቡድን የዜጎችን አቅም እገነባለው ብሎ መነሳቱ ከአስገራሚ በላይ ሁኖብናል።

ስልጠና የሚያስፈልገው ላልሰለጠነው የወያኔ ጉጅሌና ሎሌዎቹ ነው!

አምባገነኖች በውድም በግድም ህዝብ ስብሰባ ጠርተው ህዝቡ ፊት በቆሙ ቁጥር ሌት ከቀን የሚያባንናቸውን የተመረረ ህዝብ የነጻነት አመጽ የሚያስቀሩ ይመስላቸዋል። የህዝብ ሃብትና ጊዜ በከንቱ እንዳሻቸው እያባከኑ፣ ነጋ ጠባ ስብሰባ፣ ግምገማ፣ “ስልጠና” ወዘተ የሚጠሩት ህዝብ የነሱን ፍላጎትና ውሳኔ የኔ ነው ብሎ የሚቀበላቸው፣ የሚሰማቸው እና ፍርሃታቸውን ያቀለላቸው እየመሰላቸው ነው።

የወያኔ ጉጅሌና ሎሌዎቹ ሰሞኑን ተማሪዎችን፣ መምህራንን፣ ሰራተኞችንና መላውን ለፍቶ አዳሪ ተሰብሰብና እናሰልጥንህ የሚሉት በአገዛዛቸው የተንገፈገፈው ህዝብ ምሬቱ ወደ አመጽ እንዳይገነፍል ያደረጉ እየመሰላቸው ነው። ዲሞክራሲንና የህዝብ ወሳኝነትና ልእልናን በተቀበሉ ሀገሮች እንደወያኔና ቀደም ብሎ እንደነበረው የደርግ ስርአት የመንግስት ስብሰባ የማይዘወተረው ለዚህ ነው። የህዝቡን ፍርድ በስብሰባ እና በስልጠና እንደማያቆሙት ስለሚያውቁ ህዝብን ስለሚያከብሩ ነው።

ሰሞኑን በመላ ኢትዮጵያ እየተካሄደ ያለው ወያኔዎች ‘ስልጠና’ ብለው የሚጠሩት፣ በይዘቱ አያቶቻችንን ድሮ ላውጫጪኝ ይጠቀሙበት የነበረውን አፈርሳታ የመሰለ የመደናቆሪያ ስብሰባ አላማው ግልጽ ነው።

አላማው ህዝብ ሰጥ ለጥ ብሎ እንዲገዛ ቢቻል ለማደንዘዝ ካልተቻለም ለማስፈራራት ነው። ግፍን፣ ፍትህ ጥፋትን ልማት፣ ጭካኔን፣ ርህራሄ ለማስመሰል አፈጮሌ ነኝ ያለ ካድሬ ሁሉ የምላስ ጂምናስቲክ የሚሰራበት ጉባኤ ነው። ከተሰብሳቢው ህዝብ ከረር ያለ ጥያቄ በመጣ ቁጥር መላ ቅጡ የሚጠፋቸውም ለዚህ ነው። እነሱ የተዘጋጁት የህዝብ ጥያቄ ለመመለስ አይደለማ! የህዝቡን ጥያቄ እንደማይመልሱማ ያውቁታል።

ነገሩ መልከ ጥፉን በስም ይደገፉ ሆነና ይህንን ቧልት ‘ስልጠና’ ብለው ይጠሩታል። እነዚህ ራሳቸው መሰረታዊ ስልጣኔ የሌላቸው አሰልጣኞች መምህራኑን ስለትምህርት ጉዳይ ሊያሰለጥኗቸው ሲንጠራሩ አይፍሩም። ባለሙያውን ሁሉ በሙያው ካላ ሰለጠንህ ብለው ግዳጅ ስብሰባ ያጉሩታል። ይህ የወያኔ ተግባር እውቀትና ስልጣን ከተምታታባቸው የወያኔ ጉጅሌዎች ስለመጣ ብዙ ላያስገርም ይችል ይሆናል። እንደ ህዝብና እንደ ዜግነታችን ግን በያንዳንዳችን ላይ እየደረሰ ያለ ውርደት ነው። ወያኔ ካላዋረደንና ሰበአዊ ክብራችን ካላሳነሰ የሚገዛን አልመሰለውም።

Sunday, September 21, 2014

የኦጋዴን ኡኡታ

ዘረኞቹ የወያኔ መሪዎች በወጣትነታችን ብረት አንስተን ጫካ እንድንገባ አደረገን ብለዉ የሚናገሩት በወቅቱ ኢትዮጵያ ዉስጥ ተንሰራፍቶ ይታይ የነበረዉ በብሄር ብሄረሰቦች ጭቆና ነበር። ወያኔዎች በለስ ቀንቷቸዉ አዲስ አበባን ከተቆጣጠሩ በኋላም ቢሆን ለእነሱ ለራሳቸዉ የሚመች ህገ መንግስት ጽፈዉ ትልቁን የኢትዮጵያ ችግር ፈታን ብለዉ የሚናገሩት ይህንኑ ዛሬም ድረስ እናት አገራችንን ኢትዮጵያን እንደ ነቀርሳ በሽታ ቀስፎ ይዞ የሚቆጠቁጣትን የብሄር ብሄረሰቦች ችግር ነዉ። ወያኔ በ1994 ዓም ህገመንግስቱን አጽድቆ የፌዴራል ስርዐት ከመሰረተ በኋላ ድምጹን ከፍ አድርጎ የጮኸዉ ማንም መፍታት ቀርቶ ሞክሮት አንኳን የማያዉቀዉን የኢትዮጵያን ብሄር ብሄረሰቦች ችግር እኔ ፈታሁት የሚል ለሱና ለደጋፊዎቹ ብቻ የሚሰማ ጩኸት ነበር። ወያኔ የኢትዮጵያን ብሄር ብሄረሰቦች ከታሰሩበት ሰንሰለት ፈትቼ “ነፃ” አወጥቼ እራሳቸዉን በራሳቸዉ እንዲመሩ መንገድ ከፈትኩላቸዉ ብሎ ከተናገረ ከሃያ አመታት በኋላ ዛሬም ኢትዮጵያ ዉስጥ የትኛዉም ብሄረሰብ እራሱን በራሱ ማስተዳደር ቀርቶ የአገሪቱ ዜጎች ባሰኛቸዉ ቦታ መኖር እንኳን አይችሉም። የሚገርመዉ ነጻነትና እኩልነት የሠላም ጠላቶች የሆኑ ይመስል ዛሬ ወያኔ ነጻ ወጡ የሚላቸዉ ብሄረሰቦች በሚኖሩበት አካባቢ ሁሉ የሚታየዉ የአገራችንን አንድነት ከፍተኛ አደጋ ላይ የሚጥል ብጥብጥ፤ ግጭትና ክልሌን ለቅቀህ ዉጣ የሚል ወያኔ ይዞብን የመጣዉ መፈክር ነዉ።

ወያኔ ጫካ ዉስጥ እያለ ደርግን በተደጋጋሚ በዘር ማጥፋት ወንጀል ይከሰስ እንደነበር ያኔ ወያኔ ምን ይዞልን ወይም ይዞብን ይመጣ ይሆን እያልን እንከታተለዉ ለነበርን ኢትዮጵያዊያን የቅርብ ግዜ ትዝታችን ነዉ። ከወያኔ ዉንጀላዎቹ አንዱና ዋነኛዉ ደግሞ ወያኔ እራሱ አቀነባብሮና አዘጋጅቶ ሐዉዜን ዉስጥ በቪድዮ እየተቀረጸ የተካሄደዉ ዉጊያ ነበር። በዚህ ዉጊያ ላይ ደርግ በአዉሮፕላንና በታንክ እየታገዘ መንደሮችን በመደምሰስ ብዙ ሰላማዊ ዜጎችን እንደጨረሰ ወያኔ ዛሬም ድረስ የሚነግረን ዉንጀላ ነዉ። የወያኔ መሪዎች የኢትዮጵያ ህዝብ እንዲያዉቀዉ የማይፈልጉትና እነሱም በፍጹም የማይነግሩን እዉነት ቢኖር ደርግን አሸንፈዉ አዲስ አበባን ሲቆጣጠሩ ከደርግ የወረሱት እነሱ እንደሚሉት ባዶ ካዝና ብቻ ሳይሆን የደርግን ክፋት፤ ጭካኔና ጭፍጨፋ ጭምር መሆኑን ነዉ።

ዘረኞቹኦ የወያኔ መሪዎች ባለፉት ሃያ ሦስት አመታት በኢትዮጵያ ህዝብ ላይ የፈጸሙትን ወንጀል መዘርዘር እራሱን የቻለ ትልቅ ፕሮጀክት ነዉና ዛሬ ወደዚያ አንሄድም፤ ሆኖም ይህ ዘረኛ ቡድን ነኝ ብሎ የሚናገረዉን አለመሆኑን ለማሳየት ስንል ብቻ ሁለቱን ትላልቅ የወያኔ የሰዉ ዘር ማጥፋት ወንጀሎች መናገሩ ፍሃዊ ይመስለናል። የወያኔ ዘረኞች በኢትዮጵያ ህዝብ ላይ ከፈጸሟቸዉ ወንጀሎች አንዱና ትልቁ በታህሳስ ወር 1996 ዓም በአኝዋክ ህዝብ ላይ የፈጸሙት የሰዉ ዘር ማጥፋት ወንጀል ሲሆን ሌላዉ ደግሞ አሁንም ድረስ እልባት ያላገኘዉና ምስራቅ ኢትዮጵያ ዉስጥ በሶማሌ ወገኖቻችን ላይ የሚፈጽሙት አይን ያወጣ ጭፍጨፋ ነዉ። ፋሺስቱ ደርግ በአዉሮፕላንና በጦር ሂሊኮፕተሮች እየታገዘ ህፃን፤ አዋቂ፤ ሴትና ወንድ ሳይለይ ህዝብ ይጨፈጭፋል እያለ ሲከስ የነበረዉ ወያኔ ዛሬ እሱ እራሱ ከደርግ በከፋ ሁኔታ ኦጋዴን ዉስጥ እንዲህ ነዉ ተብሎ በቃላት ለመናገር የሚያዳግት ሰቆቃ በኦጋዴን ህዝብ ላይ እየፈጸመ ነዉ። ደርግን – ደርግ ለመሬቱ እንጂ መሬቱ ላይ ስለሚኖረዉ ህዝብ ደንታ የለዉም እያለ አምርሮ ይኮንን የነበረዉ ወያኔ የሱም ጉዳይ አጋዴን ዉስጥ አገኛለሁ ብሎ ከሚተማመነዉ የነዳጅ ኃብት ጋር እንጂ ከኦጋዴን ህዝብ ጋር እንዳልሆነ በተደጋጋሚ በዚህ ህዝብ ላይ በፈጸማቸዉና ዛሬም ድረስ በሚፈጽማቸዉ አረመኔያዊ የጭካኔ እርምጃዎች በተግባር አረጋግጧል። የሰላም፤ የፍህና የነጻነት ጠላት የሆነዉ ወያኔ ኦብነግን ከኦጋዴን ምድር አጠፋለሁ በሚል ሰበብ በክልሉ በየቀኑ በሚወስዳቸዉ ፀረ ህዝብ እርምጃዎች የብዙ ሠላማዊ ዜጎችን ደም እያፈሰሰ ነዉ።

የወያኔውን የከፋፍለህ ግዛ ስርዓት ለመጣል በአንድነት እንነሳ!!!

ዛሬም እንደ ትናንቱ ምንም የማያውቁ ህጻናት ዋይታ!!! የሴቶችና አረጋዊያን ሌላ ዙር መፈናቀል! ሌላ ዙር የጅምላ ስደት መራር መርዶ ከወደ ጋምቤላ

የግጭቱ ስረ መሰረት እንዲህ ነው። የህወሓት አገዛዝየአካባቢውን ማኅበረሰብ በማፈናቀልና ለም መሬታቸውን ቀምቶ በኢንቨስትመንት ስም ባብዛኛው ካንድ አካባቢ ለመጡ የወያኔ አባላት ቀደም ሲል ለሰሩት ወንጀል ማካካሻ እንዲሆን ታስቦ ካቅማቸው በላይ ቸራቸው። እነሱም ያለምንም ይሉኝታና ያካባቢውን ማኅበረስብ ያኗኗር ሁኔታ በጭራሽ ከግምት ሳያስገቡ ጌታዋን እንደተማመነች በግ ያካባቢው ማኅበረሰብ ለዘመናት ሲወርድና ሲዋረድ ጠብቆ ያቆየውን ጥብቅ ደን እየመነጠሩ የጣውላና የከሰል ንግድ ላይ ተሰማሩ።

የአካባቢው ማኅበረሰብ ግን የበይ ተመልካች ሆነ፣ ቅሬታውን ለባለስልጣናት አቤት ቢልም ሰሚ አላገኘም። ጭራሽ ይባስ ብለው በቀየው የተገኘውን ሴት ወንድ ሳይመርጡ በፌደራል ፖሊስ በመቀጥቀጥ ብዙዎችን ለሞት ሲዳርጓቸው ሌሎችን ደግሞ ቁስለኛ አድርገዋል። ከሞትና ከመቁለት የተረፉትም ተፈናቅለው ዱር ገደሉን ቤታቸው አድርገዋል። በሌላም በኩል የግጭቱ ሰለባ የሆኑት ከሌላ ክልል መጥተው ለረዝም ጊዜ ባካባቢው ኑዋሪ የሆኑ ኢትዮጵያዊን ዜጎችም የግጭቱ ሰለባ ከመሆነ አልተረፉም ፣እነሱም ሞትና ቁስለኛ ሆነዋል። ከሞትና ከመቁሰልም የተረፉት በቴፒ ከተማ አውላላ ሜዳ ላይ ተበትነው ምንም የማያውቁ ሴቶችና ህጻናት ቀን በጸሀይ ሌሊት በቁር እየተጠበሱ ይገኛሉ። እጅግ የሚያሳዝነው ግጭቱን የሚባብሱትና በዋና ተዋናይነት የሚተውኑት የወያኔው ቅጥረኞች የሆኑ የአካባቢ ካድሬዎችና መሬቱን ያላግባብ የቀሙ ያንድ አካባቢ ተወላጆችና ያንድ አካባቢ የፌደራል ፖሊስና የመከላከያ የበላይ ሹማምንት መሆናቸው ነው።

እንዲህ ዓይነቱ የወያኔ ሴራ ዛሬ የተጀመረ አዲስ ክስተት አይደለም። ህወሓት ገና ከመጀመሪው ሲፈጠር አብሮት የነበረና ላለፉት ሃያ ሶስት ዓመታት የቀጠለ እዳ ነው። ይህ ህወሓት ኢትዮጵያዊያንን እርስ በራስ በማጋጨት ለዘመናት ለመግዛት አስቦና አልሞ የተነሳበትና ከኢጣሊያን ቅኝ ገዝ የተማረው ስልት ነው፤ ይህ የህወሓት ባንዳነት ውጤት ነው።

Friday, September 19, 2014

የቀድሞው “የአብዮት አድናቂ” ኑዛዜ (“Confession of the Ex-Revo” )

በፍቃዱ ዘ ኃይሉ

ርዕሱን  አላስታውሰውም ‘ንጂ እ.ኤ.አ በ2011 Arab Uprising በመባል የሚታወሰውን አብዮትተከትሎ፣ ኢትዮጵያውያን ፌስቡከኞችም (በተለይ ዲያስፖራ የሚገኙ) ግንቦት 20 ላይ (ልክ በኢሕአዴግ የ20ኛ አገዛዝ ዕድሜ)   “Anger day” በሚል በፌስቡክ አብዮትመጥራታቸውን ተቃውሜ አንዲት ጽሑፍ ጽፌ ነበር፡፡ በዓመቱ ደግሞ ‹‹ አብዮት ወረት ነው›› በሚል ርዕስ በፌስቡክ አብዮት ለማስነሳት ፍላጎት ያላቸው በርካቶች እንዳሉ ገልጬ ነገር ግን ይጎድላቸዋል የሚባሉትንነገሮች ዘርዝሬ ጽፌ ነበር፡፡ በነዚህ ሁለት ጽሑፎች ላይ፣ ላዩን አብዮትን የተቃወምኩ ቢመስልም እውነታው ግን ጽሑፎቹ በተጻፉበትወቅት ሕዝቡም፣ ተቃዋሚ ልሂቃኑም፣ ሁኔታዎቹም ለአብዮት ዝግጁ አይደሉም የሚል ዝንባሌ ማሳየቱ ነበር፡፡

ከሌላ ዓመት በኋላደግሞ ‹‹ስለለውጥ›› በሚል ርዕስ ተከታታይ ጽሑፎችን በ‹‹ዞን 9›› ላይ በግል ተነሳሽነት ማስፈር ጀምሬ ነበር፡፡ ጽሑፉን የጀመርኩት ‹‹ኢሕአዴግ ሥልጣኑን በምርጫ ይለቃል?›› በሚል ጥያቄ ነበር፡፡ ‹‹አይለቅም›› የምልባቸውን ምክንያቶች ካስቀመጥኩ በኋላ የለውጥ አማራጭ የምላቸውን (አብዮት፣ሰላማዊ አለመታዘዝ /civil disobedience/ የመሳሰሉትን) በየዘርፉ እየቀነጫጨብኩ ለማሳየት ነበር ዓላማዬ ከዚያም ‹‹የለውጥ ፍርሃት››፣ ‹‹የሥርዓት ለውጥ እና ሃይማኖት››፣ ‹‹የ1966ቱ የኢትዮጵያ አብዮት እና የማኅበራት ሚና››  የሚሉ ርዕሶችን በማንሳት በሐሳቦቹ ላይ በሐቀኝነት ለመከራከር ጥረት አድርጌያለሁ (ከዚህ በላይ አልገፋሁበትም እንጂ)፡፡ በበኩሌ ስለአብዮት በደንብ ያነበብኩትም፣ ያሰብኩትም፣ የጻፍኩትም፣ የተረዳሁትም ያኔ ነበር፡፡ ያኔ በአብዮት ላይ የነበረኝ እምነት ተሸርሽሮ ግማሽ ደርሶ ነበር፡፡ ተንጠፍጥፎ ያለቀው ግን አሁንም በዓመቱ (በ2006 አጋማሽ) ነው፡፡ አንባቢ ከአብዮት አድናቂነት ወደ ዝግመተ ለውጥ አራማጅነት (በ ‹‹ያ ትውልድ›› ሰዎች አጠራር ከRevo ወደ Sabo) የተሸጋገርኩበትን የሐሳብ ዳገት (ከፈለጋችሁ ቁልቁለት በሉት) ይረዳ ዘንድ በመጠኑ ዘርዘርአድርጌ ማስረዳት አለብኝ፡፡ (ታዲያ አብዮት አድናቆቱም ቢሆን ከወረቀት እንዳላለፈ ልብ በሉልኝ)፡፡

እነዚያን ተከታታይጽሑፎች በጻፍኩበት ሰሞን  ‹አብዮት ‹‹እቆጣጠረዋለሁ›› ብለው ያሰቡትንነገር ግን ድንገት ከቁጥጥር ውጭ ሊሆን የሚችል እሳትን መለኮስ› እንደሆነ እያሰብኩ ባለሁበት ሰሞን ግብጻውያን ሙርሲን ለመጣል ያምጹ ጀመር፡፡ የግብጹ ድጋሚ አመጽ (አብዮት) በጣም የተዘበራረቀ ስሜት ፈጥሮብኝ ነበር፡፡ ሙርሲ እኔ በግሌ ከማምንባቸውና ቋሚም ከሆኑ የዲሞክራሲ መርሆች እያፈነገጠ ነበር፡፡ ስለዚህ የግብጾች ማበይ ምክንያታዊ ነው ብዬ አምኛለሁ፤ እንዲያውም ሕዝብ አንዴ ‹ከነቃ አይሆንም ዕቃ› ብዬ ነበር፡፡ የግብጽ ሕዝብ የሚፈልገውን ዓይነት ሥርዓት እስከሚያገኝ እያበየ ይቀጥላል የሚል ግምት ነበረኝ- ልክ እንደ ፈረንሳዮቹ ተከታታይ አብዮቶች፡፡  ነገር ግን የግብጽ ሕዝብ እያበየ ቢቀጥልም እንኳን የፈለገውን ላያገኝ እንደሚችል የተረዳሁት ወታደራዊ ክንፍ ቀስ በቀስ አገሪቱን በአብዮቱ ተከልሎ ሲጠቀልላት ስመለከት ነበር ፡፡ ከአገራችን የደርግ አመጣጥ አልለይ ብሎኝ ‹አብዮቶች ሁሉ አንድ ናቸው እንዴ?› እስከሚያስብል ድረስ ተመሳስሎብኝም ነበር፡፡

በህወሓት አገዛዝ በኦጋዴን ሕዝብ ላይ እየተፈጸመ ያለውን የጅምላ ግድያ በጽኑ እናወግዛለን!!!





መስከረም 7 ቀን 2007 ዓ.ም.

የአገራችን የኢትዮጵያን በትረ ሥልጣን በጠመንጃ ኃይል የተቆጣጠረው ዘረኛው የወያኔ አገዛዝ የሥልጣን እድሜውን ለማራዘም በኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ እየወሰደ ያለውን እሥራትና ግድያ አጠናክሮ መቀጠሉን የሚያጋልጡ ማስረጃዎች በየጊዜው ከራሱ ከአገዛዙ እየሾለኩ በመውጣት ላይ ናቸው።

መስከረም 5 ቀን 2007 ዓም በኢትዮጵያ ሳተላይት ቴለቪዥን በምስል ተደግፎ የቀረበው በኦጋዴን ወገኖቻችን ላይ የተፈጸመው ጭፍጨፋ ከነዚህ ማስረጃዎች አንዱ ነው ።

የወያኔን አገዛዝ ይቃወማሉ የተባሉና በኦጋዴን ክልል ከሚንቀሳቀሱ ተቃዋሚዎች ጋር ንኪኪ አላቸው የተባሉ እነዚያ የጅምላ ጭፍጨፋ ሰለባ የሆኑ ምስኪን ዜጎች አስከሬን መሬት ለመሬት እየተጎተተ አንድ ቦታ እንዲከማች ሲደረግ፤ አስከሬኑን ለመሰብሰብ ከታዘዙት የአካባቢው ነዋሪዎች አንዱ የገዛ ወንድሙ አስከሬን ከሚጎተተው መሃል እንደነበረ መስማት ህሊናን የሚሰቀጥጥና የወያኔ የጭካኔ እርምጃ አቻ የሌለው ደረጃ ላይ መድረሱን የሚያመላክት ነው።

በደርግ ዘመን ቤተሰብ የተገደለበትን ሰው አስከሬን ለማግኘት የጥይት ዋጋ ለመክፈል ይገደድ ነበር በማለት ሥርዓቱን በነጋ በጠባ የሚወነጅል አገዛዝ ከሚወነጅላቸው ሥርዓት በባሰ በኦጋዴን የገደለውን ንጹህ ዜጋ አስከሬን የገዛ ወንድሙ መሬት ለመሬት እንዲጎትተው አድርጓል። በዚህም ህወሓት በሰብዓዊነት ላይ ከቀደምቶቹ ሁሉ የከፋ የሚሰቀጥጥ ወንጀል ፈጽሟል። ቀደም ሲል በበደኖ፤ በአርሲ፤ በአርባ ጉጉ፤ በሃዋሳ ፤ በጋምቤላ እና ድህረ ምርጫ 97 በአዲስ አበባና ሌሎች የአገሪቱ ከተሞች ነዋሪዎች ላይ በወያኔ ልዩ ትዕዛዝ ተመሳሳይ የጅምላ ጭፍጨፋዎች ተካሂደዋል። ይህ ሁሉ ወንጀል እየተፈጸመብን አስከዛሬ ወያኔን በጫንቃችን ተሸክመን ለመኖር የተገደድነው እነዚሁ ጥቂት ዘረኞች ሕዝባችንን በዘር፤ በቋንቋና በሃይማኖት በመከፋፈላቸው አንዱ የኅብረተሰብ ክፍል ሲጠቃ ሌላው በዝምታ የሚመለከትበት ሁኔታ በመፈጠሩ ነው።

Wednesday, September 17, 2014

“ነጻነትነታችን እንደ ዕርዳታ እህል ከምዕራባውያን የሚለገሰን አይደለም!”

ለአዲሲቷ ኢትዮጵያ የጋራ ንቅናቄ በኢትዮጵያ ለሚገኙ የፖለቲካ መሪዎች ያስተላለፈው ግልጽ መልዕክት

የተወደዳችሁ በኢትዮጵያ የምትገኙ የፖለቲካ ፓርቲ መሪዎች፤

በቅድሚያ ለአዲሲቷ ኢትዮጵያ የጋራ ንቅናቄ (አኢጋን) የአክብሮት ሰላምታ በማቅረብ በትግሉ መስክ የምትከፍሉትን መስዋዕትነት የሚያደንቅ መሆኑን ይገልጻል፡፡ በተለይ በአሁኑ ጊዜ የፖለቲካ ምህዳሩ እጅግ ጠብቦ የለም የሚባልበት ደረጃ በደረሰበት ወቅት በምታገኙት ስንጥቅ ሁሉ እየተጠቀማችሁ ለህዝባችሁ የብርሃን ጭላንጭል ስለምትፈነጥቁ አኢጋን ሥራችሁን ያደንቃል፤ ያከብራል፡፡ እኛ በሥራችሁ ስኬት የምንመኘው ለቆማችሁለት የፖለቲካ ዓላማ ብቻ ሳይሆን ከህወሃት/ኢህአዴግ አገዛዝ ራሳቸውን ነጻ ለማውጣት አቅቷቸው መፈናፈኛ ላጡትም የመወሰን ኃይል እንደምትሰጧቸው በማመን ነው፡፡

አገራችን ካለችበት ወቅታዊ ሁኔታ አኳያ የበርካታዎች ጥያቄ “ህወሃት/ኢህአዴግን በምን ዓይነት የተሻለ አስተዳደር እንዴት መለወጥ ይቻላል የሚለው ነው?” ይህ ጥያቄ “እኛ ኢትዮጵያውያን የዘርና የጎሣ ትንንሽ አጥሮቻንን አፍርሰን ሁሉን አቀፍ ትግል ለማድረግ ተዘጋጅተናል ወይ?” ብለን ራሳችንን መልሰን አንድንጠይቅ የሚያደርገን ነው፡፡ እንዲሁም ከጎሣ ይልቅ ለሰብዓዊነት ቅድሚያ በመስጠት ሁሉም ነጻ ሳይወጣ ራሳችንን ነጻ ለማውጣት እንችላለን ወይ? ብለንም እንድንጠይቅ የሚያስገድደን ነው፡፡ …

ሽንፈት ላይ እያተኮሩና የጠላትን ኃይለኛነት እየሰበኩ ድል አይገኝም፡፡ ልዩነትን እያራመዱ ኅብረትና አንድነት ተግባራዊ መሆን አይችልም፡፡ ለአገራዊ ዕርቅ እንሰራለን እያሉ በፓርቲ መካከል ከዚያም በታች በግለሰብ ደረጃ መተራረቅ ካልተቻለ ብሔራዊ ዕርቅ ከቀን ቅዠት አያልፍም፡፡ እያንዳንዳችሁ የፖለቲካ ፓርቲዎች መድረክ፣ መኢአድ፣ አንድነት፣ ሰማያዊ፣ ኦህኮ፣ አረና፣ እና ሌሎች እጅግ በርካታ ፓርቲዎች የተቋቋማችሁትና ዓላማ ያደረጋችሁት ኢህአዴግን እየተቃወማችሁ ለመኖር እንዳልሆነ የፓርቲ ፕሮግራማችሁ ይመሰክራል፡፡ ወይም ዓላማችሁ የራሳችሁን የፓርቲ ምርጫ የማድረግና ፕሬዚዳንት (ሊቀመንበር)፣ ምክትል፣ ሥራ አስፈጻሚ፣ … በመምረጥ አዙሪት ውስጥ ራሳችሁን ላለማሽከርከር እንደሆነ ከማንም በላይ ራሳችሁ ታውቁታላችሁ፡፡ ከዚህ አንጻር በጥንቃቄና በብዙ ጥናት የተቀመጠው የፓርቲያችሁ ፕሮግራምና ዓላማ ለአገራችን አንዳች ለውጥ ሳያመጣ እንደዚሁ እንዳማረበት ቢቀመጥ ለሕዝብ የሚያመጣው ትርፍ ምንድርነው? እናንተንስ ለመቃወም ብቻ የምትሰሩ አያደርጋችሁምን? …

(ሙሉውን መልዕክት ለማንበብ እዚህ ላይ ይጫኑ)

Monday, September 15, 2014

በዶ/ር ብርሃኑ ነጋ አዲሱን ዓመት አስመልክቶ ለኢትዮጵያ ህዝብ የተላለፈው መልዕክት ጽሑፍ

እንደምን አመሻችሁ!

በዚህች መላዉ የኢትዮጵያ ሕዝብ ከቤተሰቦቹና ከወዳጆቹ ጋር ሆኖ አዲሱን አመት ለመቀበል በሚዘጋጅባት ምሽት በግንቦት 7 የፍትህ፤ የነጻነትና የዲሞክራሲ ንቅናቄ ስም እንኳን ለአዲሱ አመት በሠላም አደረሳችሁ ስል ከፍተኛ ክብርና ትልቅ ደስታ ይሰማኛል። መቼም በባህላችን ለሠላም ያለን ቦታ ከፍተኛ ስለሆነ አዲስ አመት በመጣ ቁጥር እንኳን በሠላም አደረሳችሁ እንባባላለን እንጂ ኢትዮጵያ ዉስጥ ሠላም ከጠፋ ብዙ አመታት ተቆጥረዋል።

ዉድ የአገሬ የኢትዮጵያ ሕዝብ-

እኛን ለመሰለ ከሁለት አስርተ አመታት በላይ በዘረኛ አምባገነኖች ለተረገጠ ሕዝብ የአዲስ አመት ዋዜማ አሮጌዉን አመት ሸኝተን አዲሱን የምንቀበልበት የሆታና የጭፈራ ምሽት ሆኖ ማለፍ የሚገባዉ አይመስለኝም። ይልቁንም በዚህ አሮጌዉን 2006ትን ተሰናብተን አዲሱን 2007ትን በምንቀበልበት ምሽት ባሳለፍነዉ የትግል አመት የገጠሙንን ችግሮችና መሰናክሎች መርምረንና ከድክመታችን ተምረን በ2007 ዓም ለምናደርገዉ ወሳኝ ትግል እራሳችንን ማዘጋጀት ያለብን ይመስለኛል።

እኛ ኢትዮጵያዉያን ረጂም የነጻነት ታሪክና በየዘመኑ የዘመቱብንን ወራሪዎች በተከታታይ ያሸነፍን የጥቁር ሕዝብ የነጻነትና የአልበገር ባይነት ተምሳሌቶች ነን። ያለፉት ሃያ ሦስት አመታት ታሪካችንን ስንመለከት ግን እነዚህ አመታት እፍኝ በማይሞሉ የአገር ዉስጥ ጠላቶቻችን ተሸንፈን ክብራችንንና ፈጣሪ ያደለንን ነጻነታችንን ተቀምተን የኖርንባቸዉ አሳፋሪ አመታት ናቸዉ። በ1983 ዓም አምባገነኑን ደርግ በትጥቅ ትግል ያስወገዱት የወያኔ መሪዎች እነሱ እራሳቸዉ ከደርግ የከፉ አምባገነኖች ሆነዉ አሁንም ድረስ አገራችን ኢትዮጵያን እየገዙ ይገኛሉ።

የወያኔ ስርዐት በየቀኑ በአገርና በሕዝብ ላይ የሚፈጽመዉን ግፍ፣ በደልና ሰቆቃ ስርዐቱን አምባገነን ነዉ ብሎ በመጥራት ብቻ መግለጽ የሚቻል አይመስለኝም። አገራችን ኢትዮጵያን ጨምሮ አለማችን ብዙ አምባገነን መንግስታትን አስተናግዳለች ዛሬም እያስተናገደች ነዉ። ወያኔ ግን እመራዋለሁ የሚለዉን ሕዝብና የሚመራዉን አገር በግልጽ የሚጠላ ከሌሎች አምባገኖች ለየት ያለ አምባገነን ነዉ። ወያኔ ሥልጣን ይዞ በቆየባቸዉ አመታት ሁሉ ኢትዮጵያዊነትን ሽንጡን ገትሮ ተዋግቷል፤ የኢትዮጵያን ደሃ ገበሬ አፈናቅሎ መሬቱን የኔ ለሚላቸዉ ታማኞቹና ለዉጭ አገር ቱጃሮች በርካሽ ዋጋ ሽጧል።ደቡብ ኢትዮጵያ ዉስጥ ለረጂም አመታት ከአካባቢዉ ሕዝብ ጋር ተግባብteዉ ይኖሩ የነበሩትን የአማራ ተወላጆች ይህ የእናንተ አገር አይደለም ብሎ ከገዛ አገራቸዉ ተፈናቅለዉ እንዲወጡ አድርጓል። በ 2005ና በ2006 ዓም በኦሮሚያ፤ በአማራ፤ በአፋርና በሶማሌ ክልሎች ከመሬታችን አታፈናቅሉን ብለዉ የመብት ጥያቄ ያነሱ አያሌ ሠላማዊ ዜጎችን በግፍ ጨፍጭፎ ገድሏል። ባጠቃላይ ወያኔ በዘር የተደራጀ፤ ሕዝብን በዘር የሚከፋፍልና የሚቃወመዉን ሁሉ በጅምላ እያሰረ በጅምላ የሚገድል ድርጅት ነዉ።

ይህም ሁሉ ሆኖ የወያኔ መሪዎች ከሕዝብና ከራሳቸዉ ጋር ታርቀዉ፤ በአገርና በሕዝብ ላይ የፈጸሙት ዝርፊያና ያደረሱት በደል በይቅርታ ታልፎ በኢትዮጵያ ዉስጥ እዉነተኛ ዲሞክራሲያዊ ስርዐት የሚገነባበትን መንገድ እንዲያመቻቹ የኢትዮጵያ ሕዝብ ተደጋጋሚ ዕድል ሰጥቷቸዉ ነበር። ለምሳሌ ከ1997ቱ ምርጫ በኋላ ተቃዋሚ ድርጅቶች የምርጫዉ ዉጤት እንደተጭበረበረ እያወቁ የወያኔ አገዛዝ አገሪቱን ለሚቀጥሉት አምስት አመታት ያለምንም ተቀናቃኝ እንዲመራና እነዚህን አምስት አመታት የተራራቀ ሕዝብን ለማቀራረብ፤ የዲሞክራሲ ተቋሞች መሠረት ለመጣልና አገራችን ዉስጥ መሪዎች በሀቀኛ ህዝባዊ ምርጫ ብቻ ወደ ስልጣን የሚመጡበትን መንገድ ለማመቻቸት እንዲጠቀምበት ዕድል ተሰጥቶት ነበር። ከዚህ በተጨማሪ ተቃዋሚ ድርጅቶች እራሳቸዉም በዚህ አገርን የማዳን ጥረት ዉስጥ ሙሉ በሙሉ ከወያኔ ጎን በአጋርነት እንደሚቆሙና እንደሚተባበሩት ቃል ገብተዉለት ነበር። ሆኖም የወያኔ መሪዎች አስተዋይነትን እንደ በታችነት፤ ትዕግስትን እንደ ፍርሃት መቻቻልን ደግሞ እንደ ሞኝነት በመቁጠር በወዳጅነት ላቀረብንላቸዉ የአገራችንን እናድን ጥሪ ምላሻቸዉ እስር፤ ግድያና ከአገር እንድንሰደድ ማድረግ ብቻ ነበር።

Thursday, September 11, 2014

2007 ወሳኝ የትግል ዓመት!!!

ሁለት ሺህ ስድስት ዓመተ ምህረት ለኛ ለኢትዮጵያዊያን በአብዛኛው በመጥፎ የሚታወስ ዓመት ነው። 2006፣ በመካከለኛው ምስራቅም ሆነ በአፍሪቃ በስደት ላይ የሚገኙ ወገኖቻችን ላይ የሚደርሰው ስቃይ ከፍተኛ ደረጃ ላይ የደረሰበት ዓመት ነበር። 2006፣ ቀደም ባሉ ዓመታት አገራቸዉን ለቅቀዉ የተሰደዱ ሳይደላቸው በርካታ አዳዲስ ስደኞች ከአገር ወጥተው በበረሃዎችን ቀልጠው፤ በባህር ሰጥመው ያለቁበት አሳዛኝ ዓመት ነው። 2006፣ ጥንቃቄ በተሞላበትና በተቆጠበ መንገድም ቢሆን የተቃውሞ ድምጽ ያሰሙ ወገኖቻችን ወደ እስር ቤቶች የተጋዙበት ዓመት ነው። 2006፣ በአምቦ፣ በለቀምት፣ በጅማ በሀረር በርካታ የዩኒቨርስቲ ተማሪዎች የተገደሉበት፤ በአስር ሺዎች የሚገመቱት ደግሞ የታሰሩበት ዓመት ነው። 2006፣ በአፋር፣ በኦሮሚያ፣ በደቡብ፣ በቤንሻንጉል፣ በጋምቤላ፣ በአዲስ አበባና አካባቢው በ100 ሺዎች የሚገመት ኢትዮጵያዊ የተፈናቀለበት ዓመት ነው። 2006 ቁጥራችው ቀላል ያልሆኑ የነፃነት ታጋዮች ከጎረቤት አገራት ታፍነው ወደ እስር ቤቶች የተጋዙበት ዓመት ነው። 2006 የንቅናቄዓችን ዋና ፀሐፊ አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ በጉዞ ላይ እያለ በትራንዚት አውሮፕላን ለመቀየር ባረፈበት በየመን ዋና ከተማ ሰንዓ በየመን መንግሥት ወንበዴዎች ታፍኖ ለሸሪካቸው ህወሓት በህገወጥ መንገድ አስተላልፈው ለስቃይ እንዲዳረግ የተደረገበት ዓመት ነው። በእነዚህ ሁሉ ምክንያቶች ነው 2006 “ጥቁር ዓመት” የሚል ስያሜ ያገኘው።

ጭንቅላት የሚባል ነገር ያልፈጠረባቸው ድኩማን ሰላዮችና ፈንጋዮች የመጨረሻውን የመንግሥት ሥልጣን የያዙበትና ውሳኔያቸው “እሰረው፣ ክሰሰው፣ ግረፈው፣ ግደለው …” ብቻ የሆነበት ዓመት መሆኑ የ2006 ልዩ መታወቂያው ሆኖ ይቆይ ይሆናል። ይሁን እንጂ በ2006 ጨለማ ውስጥ የታዩ የብርሃን ጨረሮችም እንደነበሩና እንዳሉም መርሳት አይገባም።

በሁለት ሺህ ስድስት ዓመተ ምህረት የኢትዮጵያ ሕዝብ ከመቸውም በላይ በህወሓት አገዛዝ አምርሯል፤ በሁለገብ ትግል የህወሓትን አገዛዝ ለመፋለም የቆረጡ ወገኖች ትብብር ተጠናክሯል። በ2006፣ ኢትዮጵያ ዉስጥም ከኢትዮጵያም ውጭም የንቅናቄዓችን የግንቦት 7 ድርጅታዊ መዋቅር ተጠናክሯል። በ2006፣ ከህወሓት አገዛዝ ጋር ያለው መፋጠጥ ከሯል። እነዚህ ሁኔታዎች 2007 አገራችን በለውጥ ማዕበል የምትናጥበት ዓመት ሊሆን እንደሚችል ያመለክታሉ።

Sunday, September 7, 2014

የግንቦት 7 የፍትህ፤ የነፃነትና የዲሞክራሲ ንቅናቄ አለማቀፍ ህዝባዊ ስብሰባዎች ተሳካ ሁኔታ ተካሄዱ

ግንቦት 7: የፍትህ፣ የነፃነትና የዲሞክራሲ ንቅናቄ በመላው ዓለም ከሚገኙ አባላት፣ ደጋፊዎቹና በአጠቃላይ ከኢትዮጵያውያን ጋር በወቅታዊ አገራዊ ሁኔታዎች ላይ ለመመካከር በ 30 ታላላቅ ከተሞች ካሰናዳቸው ህዝባዊ ስብሰባዎች መካከል አብዛኞቹ ባሳለፍነው እሁድ ኦገስት 31 ቀን 2014 አ.ም በድምቀ በመካሄዳቸውን ዘጋቢዎቻችን ያደረሱን መረጃ ያመለክታል። በእነዚህ በአምስት አህጉራት፤ በዘጠኝ አገሮችና 17 ከተሞች በተካሄዱት ህዝባዊ ስብሰባዎች ላይ ኢትዮጵያውያን በነቂስ በመውጣት የታደሙበት እንደነበር ያደረሱን ዘጋቢዎቻችን አገር ወዳድ ኢትዮጵያኑ ከንቅናቄው ከፍተኛ አመራሮች ጋር ሰፊ አገራዊ ውይይት ያካሄዱበት እንደነበር ለማወቅ ተችሏል። ኢትዮጵያውያን በዘር በሃይማኖት በጎሳ ሳይለያዩ በአንድነት በመሰባሰብ በአገራቸው ጉዳይ ላይ በሰፊው የመከሩበት፤ ኢትዮጵያዊነት እጅግ አምሮና አሸብርቆ የታየበት በአይነቱ ልዮ የሆነ ህዝባዊ ስብሰባ እንደነበር በርካቶች ምስክርነት እንደሰጡም ዘጋቢዎቻችንን አመልክተዋል። የንቅናቄው ከፍተኛ አመራሮች በክብር እንግድነት በተገኙባቸውና በስካይፒ በመሩዋቸው ህዝባዊ ስብሰባዎች ላይ ከተሳታፊው የደመቀ አቀባበል እንደተደረገላቸውም ለማወቅ የተቻለ ሲሆን አመራሮቹ ከተሳታፊዎች ለቀረበላቸው በርካታ አገራዊ ጥያቄዎች ምላሽ ሰጥተዋል። በህዝባዊ ስብሰባዎቹ ላይ በክብር እንግድነት የተገኙት በአሜሪካ የዋሽንግተን ዲሲ ግዛት የንቅናቄው ዋና ሊቀመንበር ዶ/ር ብርሃኑ ነጋ፤ በአትላንታ አቶ ነአምን ዘለቀ፤ በቦስተን የንቅናቄው የህዝብ ግንኙነት ተጠሪ አቶ ኤፍሬም ማዴቦ፤ በካናዳ ቶሮንቶ አቶ አንድነት ሃይሉ፤ በጀርመን ሙኒክ አቶ ብዙነህ ጽጌ በኖርዌይ ኦስሎ የንቅናቄው ም/ ሊቀመንበር አቶ አበበ ቦጋለ ሲሆኑ በስካፒ የተደረጉትን ስብሰባዎች የመሩት በደቡብ አፍሪቃ ደርባን፡ ጆሃንስበርግና ቬሪኒንገን ዶ/ር ታደሰ ብሩ፤ በሩስተምበርግ አቶ ቸኮል ጌታሁንና በአውስትራሊያ ፐርዝ የተካሄደውን አቶ ብዙነህ ጽጌ መሆናቸውን ለማወቅ ተችሏል።

በህዝባዊ ስብሰባዎች ላይ በየመን የፀጥታ ሃይሎች ተይዘው አለማቀፍ ህግን በጣሰ አካሄድ ለጉጅሌዎቹ ተላልፈው የተሰጡት የንቅናቄው ዋና ፀሐፊ የአቶ አንዳርጋቸው ጽጌ ሥራዎች በምስልና በቪዲዮ ተቀናብረው ለእይታ የቀረቡ ሲሆን የነፃነት አርበኛው የአቶ አንዳርጋቸው ጽጌ ስራዎችና አሁን ላይ በጠላት እጅ መውደቃቸው ኢትዮጵያውያኑን በቁጭት አስነብቷል፤ በበለጠ ትግሉ ለሚጠይቀው ማንኛውም መስዋዕትነት በእልህና በቁጣ ያነሳሱዋቸው እንደነበሩም ለማወቅ ተችሏል።

የለውጡ አካል መሆኛው ግዜው አሁን ነው!

እኔም አንዳርጋቸው ነኝ የሚል ድምፅ ከአጥናፍ እስከ አጥናፍ እያሰተጋባ ነው። ይሄን ድምፅ የሚያቆመው አንዳችም ምድራዊ ኃይል አልተገኘም። ኢትዮጵያዊ ባለበት ሥፍራ ሁሉ ይሄ ድምፅ ከፍ ብሎ እየተሰማ ነው። ይህንንም ተከትሎ “ላንቺ ነው ኢትዮጵያ፤ ላንቺ ነው ኢትዮጵያ” የሚለው መዝሙር በኢትዮጵያ ተራሮች እናት ላይ እየተዘመረ ነው። ፍትህ ተዋርዳለች፤እኩልነት ጠፍቷል፤ ነፃነት የለም ያሉ ምርጥ ኢትዮጵያዊያን ሳያቅማሙ አያቶቻቸው በተመላለሱበት ተራሮች ላይ ተሠማርተዋል። ሞትንም ንቀው ጋሻ አንስተዋል፤ ሰይፋቸውንም መዘዋል። ለፍትህ፤ ለዕኩልነት እና ለነፃነት የተመዘዘው ሰይፍ ከእንግዲህ ወደ ሰገባው እንደማይመለስ ህወሃቶች እንዲያውቁት እንፈልጋለን።

በኢትዮጵያችን ፍትህ ከጠፋ ብዙ ዘመን ሁኖታል። ከሁሉም ዘመን የህወሃቶች ዘመን ግን የተለየ ነው። ህወሃቶች ህግን ዜጎችን የማጥቂያ መሣሪያ አድርገው መጠቀማቸው ከሌሎች እንዲለዩ ያደርጋቸዋል። እነዚህ ቡድኖች ሥፍር ቁጥር የሌላቸው ቂም መወጣጪያ ህጎችን አውጥተዋል። እንዲህ በማድርጋቸውም ሠላም እናገኛለን ብለው ያስባሉ። የህወሃቶች አስተሳሰብ ደካማና እርባና ቢስ መሆኑን ከሚያሳዩ ተግባሮቻቸው መካከል አንዱ ይሄው በፍትህ ሳይሆን በህግ ብዛት ሠላም እናገኛለን ብለው ተስፋ ማድረጋቸው ነው። የህግ ብዛት ሠላምን አያስገኝም፤ ፍትህንም ማስፈን አይችልም። እንዲያውም ህግ በበዛ ቁጥር ፍትህ እየጎደለች እንደምትሄድ የህወሃቶች ድርጊት ደህና ምስክር ነው። እነርሱ ዜጎችን ለመበቀያ ብለው የሚያወጧቸው ጥቃቅን ህጎች እነርሱ “ህገ መንግስት” ብለው የሚጠሩትን የሚንዱ እና ፍትህን ዋጋ የሚያሳጡ ሁነው እያየናቸው ነው። የፀረ ሽብር ህጉ በህገ መንግስቱ የተቀመጠውን የዜጎችን የመናገር የመደራጀትና በሰላማዊ መንገድ የመንግስትን እኩይ ተግባራት የመቃወምን መብት የገፈፈ ነው። የፀረ ሙስና ህጉም ቢሆን እንዲሁ ነው። በፀረ ሙስና ህጉ የሚጠየቁ በህወሃት የተጠሉ ብቻ ስለመሆናቸው በሙስና የተጨማለቁት የህወሃት ሹማምንት ህያው ምስክሮች ናቸው። በህወሃቶች ህግ ሁሉም ዜጎች እኩል አይደሉም። ህወሃቶች ከሌሎች ይበልጣሉ። የህወሃቶች ምኞት እነርሱ ከህግ በላይ፤ ሌላው ህዝብ ከህግ በታች ሁነው ህወሃትን ተሸክመው እንዲኖሩ ነው። እንዲህ ዓይነቱን ኢ-ፍትሃዊነት መታገል ግዜው የሚጠይቀው ታሪካዊ ግዴታ ነው። መሪያችን አንዳርጋቸው ፅጌ የተነሳውም ህወሃቶች መሣቂያ መሳለቂያ ያደረጓትን ፍትህ ወደ ሚገባት ክብር ለመመለስ ነው። በአገራችን የህግ የበላይነት ሠፍኖ ጥቂቱ ብዙሃኑን ሳይጫን፤ ማንም ማንንም ሳይሸከም ሁሉም በህግ እና በፍትህ እኩል ሁኖ የሚኖሩባት ሠላም የበዛላት ሥፍራ እንድትሆን የመሪያችን የአንዳርጋቸው ምኞት ነው። ይሄን ምኞት ሚሊየኖች አንግበው ተነስተዋል።

ህዝባዊ እንቢተኝነት ለነፃነት እና ለፍትህ !

በይድነቃቸው ከበደ 

በአገራችን የፖሊቲካ ሥርዓት ሄደት ውስጥ ስልጣን በሰላማዊ መንገድ ከአንዱ ወደሌላው የተሸጋገረበት አጋጣሚ እጅግ በጣም አናሳነው፡፡ አብዛኛው የስልጣን ሽግግር ጉልበትና ብረትን መሰረት ያደረገ ነው፡፡ እንዲህ ዓይነቱ የስልጣን ሽግግር ጉልበተኞች ሁሌም አሸናፊ የሚሆኑበት ጉልበቱ አናሳ የሆነ ከስልጣን የሚርቅበት ዓይነተኛ መንገድ ነው፡፡ይህም በመሆኑ በህዝብ ፍቃድ እና ምርጫ ወይም በህዝባዊ እንቢተኝነት የመንግስት የአስተዳደር የስርዓት ለውጥ ወይም ጥገናዊ ማስተካከያ ለውጥ ከዚህ ቀደም እንዲሁም ባሁን ወቅት በአገራችን ስለ መደረጉ ምስክርነት ለመስጠት የሚያስችል አጋጣሚ ስለመኖሩ ያጠራጥራል፡፡ ለዚህም ነው ሰላማዊ ትግል በአገራችን ተስፋ አስቆራጭ እና የማይሞከር መስሎ የሚታየው፡፡

እርግጥነው በሰላማዊ ትግል ሂደት ውስጥ ውጣ ውረዶ የበዛ ነው፡፡ በዓለማችን ላይ የተካሄዱት ሠላማዊ ትግሎች ውጤት ያስመዘገብት መተኪያ የሌለውን የሰውልጅ ሕይወትን እስከመንጠቅ በመድረሰ ነው፡፡ ይበልጥ ደግሞ ትግሉ አስቸጋሪ የሚያስመስለው ውጤቱ የሚፈጀው ጊዜ ነው፡፡ ሠላማዊ ትግል ማለት ታጋዩ የሚታገልለትን ውጤት ሣይመለከት በትግሉ ሂደት የሚሰዋበት ነገር ነው እስከመባል ይደርሳል፡፡ እንዲህ ዓይነቱ ደረጃ ለመድረስ ከሌላ ጋር ሣይሆን ከእራስ አስተሳሰብ ጋር ይህ ቀረሽ የማይባል ትግልን ማካሄድ ይጠይቃል፡፡ ይሁን እንጂ እንዲህ-አይነቱ የአስተሳሰብ ልዕልና ለመድረስ ገፊ ምክንያቶች ካሉ፣ ምክንያቶችሁ በስትራቴጂ ከተነደፉ፣ የገዥው ስርዓት ደካማ ጎኖ በሚገባ ከታወቀና ከተለየ፣ ተምሳሌታዊ እንዲሁም ደረጃ በደረጃ የሚያድግ ሰላማዊት ግሉን የሚመራ ጠንካራ ተቋም ካለ የሰላማዊ ትግል የአስተሳሰብ ደረጃ ማሳያ የሚሆን በአመርቂ ውጤት የተደገፈ ተግባር እውን ሆኖ ማያት የማይቻልበት ምንም ምክንያት የለም ፡፡ በመሆኑም የሠላዊ ትግል መገለጫዎች ከሆኑት ውስጥህ ዝባዊ እንቢተኝነት ከአምባገነን አገዛዝ ወደ ዲሞክራሳዊ ስርዓት ለመሸጋገር አይነተኛ መንገድ ነው፡፡ ስለዚህም ህዝባዊ እንቢተኝነት ወንጀልም አጢያትም አይደለም! ህዝባዊ እንቢተኝነት በተለያዩ አገሮች በተለያየ ወቅት የተተገበር እና ውጤት የታየበት ከአምባገነናዊ ስርዓት የመላቀቂያ ቀጥተኛ መንገድ ነው ብሎ መደምደም ባይቻልም ተመራጭ የሰላማዊ ትግል ስትራቴጂ ነው፡፡ ሁላችንም ሊያስማማን የሚችለው ጨቋኝ የመንግስት ሥርዓት ባለበት ህዝባዊ እንቢተኝነት የቅንጦት ጉዳይ ሣይሆን የህልውናምርጫ ይሆናል፡፡ በዚህም ምክንያት ህዝባዊ እንቢተኝነት የትኛውም አይነት ስም ቢሰጠው ተጨቋኝ እና ጨቋኝ እስካለ ድረስ አይቀሬነቱ እርግጥ ነው፡፡

Friday, September 5, 2014

ወጣቱን ለማደንቆር ያለመው ስልጠና ህወሓትን ለመቅበሪያነት ይዋል!

ህወሓት፣ ከሶስት መቶ ሺህ በላይ የመንግሥት ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተማሪዎችን በየቦታው ሰብስቦ እያሰለጠነ ነው። ይህ ሲያልቅ የግል ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተማሪዎች ስልጠና ይቀጥላል ተብሏል። በድምሩ ወደ ግማሽ ሚሊዮን የሚጠጋ ወጣት አንድ አይነት ሰነድ አንብቦ ለ2007 ትምህርት ይዘጋጃል ማለት ነው። ስልጠናው ወደ መንግሥት ሠራተኞችና ሌሎች የኅብረተሰብ ክፍሎችም ይስፋፋል ተብሎ ይገመታል።

ግንቦት 7: የፍትህ፣ የነፃነትና የዲሞክራሲ ንቅናቄ በዚህ ሥልጠና ላይ ያለውን እይታ በነሐሴ 16 ቀን 2006 ዓም ቁጥር 328 ርዕሰ አንቀጹ መግለጹ ይታወሳል። ግንቦት 7 የዩኒቨርስቲ ተማሪዎች በወያኔ ስልጠናዎች ላይ ተቃውሞ ለማሰማት መድፈራቸው ወጣቱ ለለውጥ የተዘጋጀ እንደሆነ አመላካች መሆኑን ተገንዝቦ ይህ የለውጥ ፍላጎት በድርጅት እንዲታገዝ ወጣቱ በትናንሽ ሕዋሶች ራሱን እንዲያደራጅ መክሯል። ሆኖም ግን ህወሓት ለስልጠናው የሰጠው ትኩረት ቀድሞ ከታሰበው በላይ በመሆኑ ንቅናቄዓችን በዚህ ርዕሰ ጉዳይ ላይ እንደገና ሊመለስበት ወስኗል።

ህወሓት፣ ይህንን ያህል መጠነ ሰፊ ስልጠና ማድረግ ለምን አስፈለገው? የዲሞክራሲ ኃይሎችስ ይህንን ስልጠና እንዴት ለራሳቸው ጥቅም ሊያውሉት ይችላሉ?

ህወሓት ይህንን ትርጉም የለሽ ስልጠና በአሁኑ ሰዓት ለመስጠት የፈለገበትን በርካታ ምክንያቶች ማቅረብ ቢቻልም የሚከተሉት ሁለቱ ግን ዋነኛዎቹ ናቸው ብለን እናምናለን።

አንደኛውና ዋነኛው ምክንያት ህወሓት የተከታዮች ድርቅ የደረሰበት መሆኑ አድርባይ መሪዎቹን ማሳሰቡ ነው። በሚሊዮን ይቆጠራሉ የሚባሉት የኢህአዴግ አባላት ልባቸው ከህወሓት ጋር አለመሆኑ ግልጽ እየሆነ መጥቷል። በተለይ ደግሞ በተላላኪዎቹ ብአዴን፣ ኦህዴድ እና ደህዴግ የተሰባሰቡ አባላት በግልጽ ህወሓትን መቃወም እየጀመሩ ነው። ህወሓት የራሱን መጥፊያ እያደራጀ መሆኑ የተሰማው በመሆኑ አዳዲስ “ምዕመናንን” ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት አካባቢ መመልመል ይፈልጋል። የመንግሥት ንብረትና መዋቅር ለፓርቲ ስልጠና የሚጠቀም በመሆኑ ከብዛት የሚገኝ ትንሽም ቢሆን ጥቅም የሚያገኝ ከሆነ የወጭው ጉዳይ ህወሓትን አያሳስበውም። ስለሆነም ይህ ስልጠና በተቻለ መጠን ብዛት ያላቸዉን የተማተሩ ወጣቶች በአድርባይነት ለህወሓት ማሰለፍን አላማዉ አድርጎ የተነሳ ስልጠና ነዉ።

Tuesday, September 2, 2014

ኑና እንወያይ

የወያኔ ዘረኞች የግንቦት 7 የፍትህ፤ የነጻነትና የዲሞክራሲ ንቅናቄ ዋና ጸሐፊ የሆኑትን አቶ አንዳርጋቸዉ ጽጌን ፍጹም ህገወጥ በሆነ መንገድ አስሮ ማሰቃየት ከጀመሩ እነሆ ሃምሳ ቀኖች ተቆጥረዋል። ሠላማዊ ዜጎችን ሽብርተኛ ብለዉ ካሰሩ በኋላ የፈጠራ ታሪክ እየጻፉ የቴሌቪዥን ድራማ መስራት የለመዱት ዘረኞቹ የወያኔ መሪዎች በአቶ አንዳርጋቸዉ ላይም በዉሸት የተቀነባበረ ድራማ ሰርተዉ የዚህን ጀግና ሰዉ ተክለሰዉነት ጥላሸት ለመቀባት ሞክረዋል። ሆኖም ቆሻሻ ፈብራኪዎቹ የወያኔ ፕሮፓጋንዳ ተቋሞች ያሻቸዉን ድራማ ቢሰሩም በአለም ዙሪያ የሚኖሩ ኢትዮጵያዉያን በአንድ ድምጽ “እኔም አንዳርጋቸዉ ነኝ” እያሉ ትግሉን በመቀላቀል ግንቦት 7 የዕልፍ አዕላፍት ድምጽ አንጂ የአንድና የሁለት ሰዎች ድርጅት አለመሆኑን በተግባር ለወዳጅም ለጠላትም አሳይተዋል። በእርግጥም ግንቦት 7 ወያኔ አንዳርጋቸዉን ካሰረ በኋላ ህዝብን ለማታለል እንደሞከረዉ ያበቃለት ድርጀት ሳይሆን ወያኔና ቆሻሻ ስርዐቱ ተጠራርገዉ ቆሻሻ መጣያ ዉስጥ እስካልገቡ ድረስ በየቀኑ እያደገ የሚሄድ ህዝባዊ መሠረት ያለዉ ድርጅት ነዉ።

ዛሬ ኢትዮጵያን ጨምሮ በየአህጉሩ የሚኖሩ ኢትዮጵያዉያን በአካል ሲገናኙም ሆነ በማህበራዊ ሜዲያዎች ሲሰባሰቡ አንድነታቸዉን የሚገልጹበትና የትግል ቃልኪዳናቸዉን የሚያድሱበት ቃል “እኔም አንዳርጋቸዉ ነኝ” የሚል ቃል ነዉ። ባለፉት ሃምሳ ቀኖች በዚህ መልኩ በወያኔና በተላላኪዎቹ ላይ ቁጣዉን ሲገልጽ የሰነበተዉ በዉጭ አገሮች የሚኖረዉ ኢትዮጵያዊ ወያኔን ባስቸኳይ ለማስወገድ በሚቻልበት መንገድ ለመምከርና ለእናት አገሩ ኢትዮጵያ ያለዉን ፍቅር በተግባር ለማሳየት ከፊታችን እሁድ ነኃሴ 24 ቀን እስከ መስከረም 4 ቀን ባሉት ሦስት ተከታታይ እሁዶች በ26 ታላላቅ የአለም ከተማዎች ዉስጥ በአይነቱ ልዩ የሆናና ከዚህ ቀደም ተደርጎ የማያዉቅ ታላቅ ህዝባዊ ስብሰባ ያደርጋል። የእነዚህ “እኔም አንዳርጋቸዉ ነኝ” በሚል መሪ ቃል የተጠሩ ስብሰባዎች ዋና አላማ አንዳርጋቸዉና ከሱ በፊትም ሆነ ከሱ በኋላ ለእናት አገራቸዉ ኢትዮጵያ አንድነት፤ ሠላምና ብለጽግና ሲሉ የታሰሩና የህይወት መስዋዕትነት የከፈሉ ኢትዮጵያዉያን የቆሙለትን አላማ ከግብ ለማድረስ ምን ማድረግ አለብን የሚለዉን ትልቅ ጥያቄ በጋራ ለመመለስ ነዉ። የኢትዮጵያ ህዝብ ለመብቱና ለነጻነቱ የሚያደርገዉ ትግል ወደመጨረሻዉና ፈታኝ ወደሆነዉ ወሳኝ ምዕራፍ ዉስጥ መግባቱን ሁሉም ኢትዮጵያዉ የተገነዘበዉ ይመስለናል፤ ሆኖም በጋራ ለሚደረግ ህዝባዊ ትግል ህዝብ ቁጭ ብሎ በጋራ ካልመከረበትና ተስማምቶ ለድል የሚወስደዉን ጎዳና በጋራ ካልቀየሰ ትግላችን ወሳኝ ደረጃ ላይ መድረሱን መገንዘቡ ብቻ በራሱ ፋይዳ ይኖረዋል ብለን አናምንም። ስለሆንም በአነዚህ ብዙዎችን አቀራርበዉና አወያይተዉ ለህዝባዊ ትግሉ የሚበጁ ጠቃሚ ሀሳቦችን ያፈልቃሉ ብለን በምናምንባቸዉ ስብሰባዎች ላይ የአገሬ ጉዳይ ከግል ጉዳዬ በላይ ነዉ ብሎ የሚያምን ኢትዮጵያዊ ሁሉ ተገኝቶ የበኩሉን አስተዋጽኦ አንዲያደርግ የዝግጅት ክፍላችን በዚህ አጋጣሚ አገራዊ ጥሪ ያደርጋል።