Sunday, July 21, 2013

አክሰስ ሪል ስቴት መንግሥት አቶ ኤርሚያስን በማግባባት ወይም በኢንተርፖል እንዲያስመጣለት ሊጠይቅ ነው

-    ከ200 ሚሊዮን ብር በላይ የተከፈላቸው ኮንትራክተሮች እየተከራከሩ ነው
-    የቤት ገዢዎች ዓብይ ኮሚቴና አዲስ የቦርድ አመራሮች ተመረጡ

በውጭና አገር ውስጥ ከሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ለመኖሪያ ቤት ግንባታ ከ1.4 ቢሊዮን ብር በላይ ከሰበሰቡ በኋላ፣ በኪሳራ ምክንያት ከአገር የወጡትን የአክሰስ ሪል ስቴት የቀድሞ ሥራ አስኪያጅና የቦርድ ሰብሳቢ አቶ ኤርሚያስ ጠቅል አመልጋን፣ መንግሥት በማግባባት ወይም በኢንተርፖል አማካይነት እንዲያስመጣለት ሰኔ 9 ቀን 2005 ዓ.ም. የተመረጠው አዲሱ የሪል ስቴቱ ቦርድና የቤት ገዢዎች በጋራ ሊጠይቁ ነው፡፡

ከ650 በላይ ባለአክሲዮኖች የሚገኙበት አክሰስ ሪል ስቴት አክሲዮን ማኅበር፣ ሰኔ 9 ቀን 2005 ዓ.ም. ባደረገው አጠቃላይ ስብሰባ፣ ቀደም ሲል በአቶ ኤርሚያስ ሰብሳቢነት ተሰይሞ የቆየውንና ምንም ዓይነት እንቅስቃሴ ሳያደርግ የቆየውን ቦርድ በመበተን አዲስ ቦርድ የሰየመ ሲሆን፣ ለሪል ስቴቱ ሙሉ፣ ግማሽና ሲሶ ክፍያ በመፈጸም መኖሪያ ቤት የገዙ 2,034 ግለሰቦች መካከል ከተመረጡ ዓብይ ኮሚቴ ጋር የሥራ ውል መፈራረማቸው ታውቋል፡፡  

በቀጣይ በጋራ ሊሠሩ ያሰቡት አክሰስ ሪል ስቴት በቀድሞው ሥራ አስኪያጅና ቦርድ ሰብሳቢ ተፈጽመዋል የተባሉትን ችግሮች ለመፍታት፣ የመንግሥት ጣልቃ ገብነት ወሳኝ በመሆኑ ለጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝና ለሌሎች ለሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት ደብዳቤ ማስገባታቸውን፣ የአዲሱ ቦርድ ሰብሳቢ አቶ መኩሪያ ደጉ፣ የዓብይ ኮሚቴው ተጠሪ አቶ አክሎግ ሥዩምና የኮሚቴው አባል አቶ ደመክርስቶስ ዘመነ ለሪፖርተር አስረድተዋል፡፡ 


ሰብሳቢውና ተወካዮቹ እንደገለጹት፣ አቶ ኤርሚያስ በማወቅም ይሁን ባለማወቅ በፈረሙዋቸው ደረቅ ቼኮች ምክንያት ፈርተው ከአገር ወጥተዋል፡፡ አሁን ዱባይ ሆነው ስለአክሰስ ሪል ስቴት ጉዳይ በሚታወቁ፣ በማይታወቁና የሳቸውን ቃል አስመስለው በተለያዩ መንገዶች በሚያስተላልፉ ግለሰቦች እየተከታተሉ ነው፡፡ ምንም ይሁን ምንም አቶ ኤርሚያስ ወደ አገራቸው መጥተው የተከሰተውን ችግር ከቤት ገዢዎቹና ከአዲሱ ቦርድ ጋር በመሆን መፍትሔ ማፈላለግ አለባቸው፡፡ አድራሻቸው ስለሚታወቅ መንግሥት ከቦርዱና ከቤት ገዢዎቹ ጋር ሆኖ ወደ አገር ቤት የሚመለሱበትንና የመፍትሔ አካል የሚሆኑበትን መንገድ ሊፈጥር ይገባል ብለዋል፡፡ ይኼ የማይሆን ከሆነ በኢንተርፖል አማካይነት መንግሥት እንዲያስመጣላቸው፣ የመፍትሔው አካል ሆነው የሚሠሩበትን ሁኔታ እንዲያመቻች መጠየቃቸውንና በድጋሚም እየጠየቁ መሆኑን አብራርተዋል፡፡ 

ጉዳዩ የግለሰቦች ውል ከመሆን አልፎ አገራዊ ጉዳይ መሆኑን መንግሥት መገንዘቡን፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም በቅርቡ ሪል ስቴቶችን አስመልክቶ ከጋዜጠኞች ለተነሱላቸው ጥያቄዎች ከሰጡት ምላሽ መገንዘባቸውን ያስታወሱት የቦርዱና የቤት ገዢዎቹ ተወካዮች፣ ሰሞኑን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ተደውሎ እንደተነገራቸው ከሆነ የሚያነጋግራቸው አንድ ቡድን መቋቋሙን ለማወቅ ችለዋል፡፡ 

መንግሥት በጉዳዩ ጣልቃ ገብቶ አክሰስ ሪል ስቴት ያለበትን ዕዳና ያለውን ሀብት በገለልተኛ የሒሳብ ባለሙያ እንዲሠራ ካላደረገላቸው፣ አቶ ኤርሚያስ ሪል ስቴቱን አወሳስበውና እንዳይፈታ አድርገውት ስለሄዱ፣ ለብቻ መፍትሔ ፍለጋ መሄድ አዋጭ አለመሆኑን ገልጸዋል፡፡ መንግሥት ከረዳቸው ችግሩ በቀላሉ ሊፈታ እንደሚችልም አክለዋል፡፡ 

አክሰስ ሪል ስቴት በመፈራረስ ላይ መሆኑን በመመልከት አስቸኳይ ጠቅላላ ጉባዔ በማድረግ ችግሩን ለመለየት መቻሉን የገለጹት ተወካዮቹ፣ ድርጅቱ ገንዘብ ከመቀበልና ከተወሰኑት በስተቀር አንድም ቤት ሠርቶ አለማስረከቡን ጨምሮ ከ23 በላይ የሚሆኑ በቀጣይ ሊሠሩ የሚችሉ ሥራዎች እንዳሉ መለየታቸውን ገልጸዋል፡፡ 

በአክሰስ ሪል ስቴት ላይ ቀጥታ ክስ ለመመሥረት እንደማይቻል የገለጹት ተወካዮቹ፣ ምክንያት ያሉትም አቶ ኤርሚያስ ትልልቅ ንብረቶችንና ቦታዎችን የገዙት በቤት ገዥዎች ስምና በሌሎች ሪል ስቴቶች መሆኑን ነው፡፡ ቤት ገዢዎችን ማስገደድ ስለማይቻል ምንም ማድረግ አለመቻሉን አክለዋል፡፡  

በነባሩ ቦርድ ውስጥ ያሉና ጥሩ አመለካከት ያላቸውን ግለሰቦች እንዲሁም ባለአክሲዮኖችን ጨምሮ አዲስ የተሰየመው ቦርድ፣ ሙሉ መረጃ ከተቋሙ ሊያገኝ በመቻሉ፣ የቤት ገዥዎችን ጠቅላላ ዝርዝር፣ 41 የተገዙ ሳይቶችን (19 ግንባታ ተጀምሮባቸዋል)፣ አራጣ በሚመስል ሁኔታ ለቢሮ ሠራተኞች በረጅም ጊዜ ክፍያ በሚሊዮን የሚቆጠር ብድር፣ ከ200 ሚሊዮን በላይ ለኮንትራክተሮች የተከፈለ ገንዘብና ሌሎችንም መረጃዎች ሊሰበስቡ መቻላቸውን አስረድተዋል፡፡ የተሰበሰቡት ማስረጃዎች እውነት ናቸው ብሎ ለማረጋገጥ በቅድሚያ በገለልተኛና በታዋቂ የሒሳብ ባለሙያዎች መመርመር እንዳለበት ቦርዱም ሆነ የቤት ገዢዎቹ ስምምነት ላይ መድረሳቸውን የገለጹት ተወካዮቹ፣ ይህን ለማድረግ ግን የመንግሥት ጣልቃ ገብነት ወሳኝ መሆኑን ደጋግመው አስረድተዋል፡፡ 

ይበል ኢንዱስትሪያል ኢንደጂነሪንግ 114.1 ሚሊዮን ብር፣ ሊቪንግ ስቲል ኮንስትራክሽን ከ117 ሚሊዮን ብር በላይ፣ በድምሩ ሁለቱም ተቋራጮች ከ200 ሚሊዮን ብር በላይ ግንባታ ለማካሄድ የተፈራረሙበት ሰነድ መገኘቱን የገለጹት ተወካዮቹ፣ ኮንትራክተሮቹ በወሰዱት ገንዘብ ሥራውን እንዲቀጥሉ ወይም እንዲመልሱ ሲጠየቁ፣ ከግማሽ በላይ የሚሆነውን ገንዘብ ሥራውን የሠሩበት መሆኑን በማንሳት እየተከራከሩ እንደሚገኙ አስታውቀዋል፡፡ በዚህም ላይ የመንግሥት ሚና ከፍተኛ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡ 

አቶ ኤርሚያስ መገናኛ አካባቢና ሰንራይዝ ሳይት የሚባሉትን ጨምሮ በ19 ሳይቶች ግንባታ ያከናወኑ ሲሆን፣ ግምታቸው ከ200 ሚሊዮን ብር እንደማያንስ፣ ከሪል ስቴቶች ማለትም ምቾት ሪል ስቴት፣ ፓስፊክ፣ መሪ ዲፕሎማት፣ ደግነት፣ አደይ አበባ ከሚባሉ ሪል ስቴቶችና ከሌሎችም ግለሰቦች ጋር አብሮ ለማልማት በሚል መሬት በገንዘብ መግዛታቸውን፣ ለዚህም 948 ሚሊዮን ብር ወጥቷል ማለታቸውን በሰነድ ላይ ሰፍሮ ማግኘታቸውን አውስተዋል፡፡ 

አቶ ኤርሚያስ ያወጡት የ2,034 ኢትዮጵያውያን ገንዘብ አግባብነትን በሚመለከት አስተማማኝ ጭብጥ ላይ ለመድረስ፣ የመንግሥት ጣልቃ ገብነት ወሳኝ መሆኑን ተወካዮቹ ደጋግመው ተናግረዋል፡፡ ቦርዱና ቤት ገዢዎች ባደረጉት ስምምነት የፋይናንስ፣ የመሬት፣ የውልና የኦዲት ሰነዶችን ለመመርመር፣ በአካል በሌሉ ቦታዎች ላይ ቤት እንደሚሠራላቸው በመግለጽ በደል የተፈጸመባቸውን ቤት ገዢዎች ጉዳይ ማጣራትና በክፍት ቦታዎች ላይ መደልደል፣ ፈቃደኛ ላልሆኑ ገንዘባቸው የሚመለስበትን ሁኔታ ማመቻቸት፣ ሁኔታው ተስፋ አስቆርጧቸው ክስ የመሠረቱ ቤት ገዢዎች ክሳቸውን አቁመው ኮሚቴውን እንዲቀላቀሉ ብርቱ ጥረት ማድረግንና ሌሎችንም ወደ 23 የሚደርሱ ተግባራትን ለመፈጸም መስማማታቸውን ገልጸዋል፡፡ 

በውጭ አገርና በአገር ውስጥ ያሉ ዜጎች ሙሉ፣ ግማሽና ሲሶ ለቤት ግዥ ክፍያ የፈጸሙት መንግሥትና ሕግ ባለበት አገር፣ በሕዝብ እጅ አላግባብ የተከማቸን ገንዘብ በአንድ ወይም በሌላ ዘዴ በልማት ላይ እያዋለ ያለ ልማታዊ መንግሥት ባለበት አገር፣ ከ2,000 በላይ የሆኑ ዜጎች ላይ በሪል ስቴት ስም የተፈጸመው ጉዳት ብቻ ሳይሆን በመንግሥት ፖሊሲ ላይ ጭምር የተቃጣ አፍራሽ ተልዕኮ መሆኑን መንግሥት ሊገነዘብላቸው እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡ ድርጊቱ በአገር ውስጥ ያሉ ኢትዮጵያውያን በቁጠባና በኢንቨስትመንት እንዳያምኑ ለማሸማቀቅ፣ የሚያደርግና በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንም ዝርፊያ የሚካሄድበት አገር ነው በማለት እንዲሸሹ በአክሲዮን ለመሥራት የሚመጡ የውጭ ኢንቨስተሮችንም የሚያሸሽ ተግባር በመሆኑ፣ መንግሥት ሳይውል ሳያድር ጣልቃ በመግባት የተጎጂዎችን እንባ ሊያብስ እንደሚገባ ተወካዮቹ አቤቱታ አቅርበዋል፡፡    

ምንጭ፡ ሪፓርተር ጋዜጣ

No comments:

Post a Comment