Thursday, July 11, 2013

ሰበር ዜና ከደሴ – ኢትዮጵያ ትጣራለች እያሉን ነዉ አንድነቶች

አንድነት ፓርቲ በጠራው ሰላማዊ ሰልፍ የከተማው መስተዳደሮችና የፀጥታ ኃይሎች ፓርቲው ህጋዊ የማሳወቅ ስራውን መስራቱን ገልፀው ሰልፉን መከልከል እንደማይችሉ ካረጋገጡ በኋላ፣ በከተማው ያሉ የቀበሌ ሰራተኞች መደበኛ ስራቸውን ጥለው በሰላማዊ ሰልፉ ዙሪያ በየቤቱ እየዞሩ ማስፈራራትና ሰላማዊ ሰልፉ ላይ ማንም እንዳይገኝ፣ ሰልፉ ህገወጥ ነው በሚል ቅስቀሳ እየሰሩ መሆናቸውን ከስፍራዉ የደረሱ ዜገባዎች ይጠቁማሉ።፡

«ነዋሪው በበኩሉ የፓርቲው ጥያቄ የእኛም ጥያቄ ስለሆነ በሰልፉ ላይ እንገኛለን፣ ፓርቲው የሚያካሂደው ሰላማዊ ሰልፍ ህገወጥ ከሆነ እነሱን (ፓርቲውንና ቅስቀሳ የሚሰሩትን ) ለምን አታግዷቸውም» የሚል ጥያቄ ሲያነሱባቸው፤ ለቅስቀሳው የተሰማሩት የቀበሌ ሰራተኞች «እምቢ ብለው የሚወጡ ካሉ እስራት ይጠብቃቸዋል፤ በሚደርስባቸው ችግር ኃላፊነቱን አንወስድም» ሲሉ ማስፈራሪያና ዛቻ እያቀረቡ ይገኛሉ።

የደቡብ ወሎ ዞን የአንድነት ፓርቲ ሰብሳቢ አቶ ብስራት አቢ፣ ቅስቀሳ በማድረግና በራሪ ወረቀት ሲበትኑ መጀመሪያ የደሴ ከተማ 4ኛ ፖሊስ ጣቢያ ያለምንም ምክንያት አስሯቸው የጣቢያው አዘዦች ከሰዓታት በኋላ ሲለቋቸው፣ 2ኛ ፖሊስ ጣቢያ በድጋሚ ምክንያቱን ሳይገልፅላቸው ለአንድ ሰዓት አስሮ እንደለቀቃቸው ተናግረዋል፡፡ አቶ ብስራት «አሁንም ድረስ መስተዳደሩ ከፈቀደ በኋላ በጎን ህገወጥ ስራ መስራቱ እንዳሳዘናቸውና ሰላማዊ ሰልፉ ህገወጥ ነው ካለም፣ ደብዳቤ መፃፍና እንዲቀር ማድረግ ሲችሉ፣ ከላይ ፈቅደው እታች ላሉት መመሪያ አላስተላለፉም፤ ይሁን እንጂ ሰላማዊ ሰልፉ ህጋዊና ሰላማዊ ስለሆነ እንቀጥልበታለን፣ ህገወጥ ናችሁ የሚል አካል ካለ ሰልፉን ለማድረግ የሚያስችል ህጋዊ ሰነድ ይዘናል። ያንን እናሳያቸዋለን» በማለት አሁንም ቅስቀሳ ላይ እንደሆኑ ማረጋገጥ ተችሏል፡፡


የከተማው ፅጥታ ዘርፍ ኃላፊ አቶ ሙሉጌታ በላይ በበኩላቸው «እኛ ሰልፉን ለማደናቀፍ ያሰርነው የለም፣ እኔ አሁን ከከተማ ውጭ ስለሆንኩ አረጋግጬ እነግርሃለው፤ የእውነት የታሰረ ካለም አረጋግጡና ንገሩን» ብለዉ ዳግም ሲደወልላቸው ሊገኙ እንዳልቻሉም የደረሰን ዘገባ ይጠቁማል።

የከተማው ከንቲባ አቶ አለባቸው የሱፍን በጉዳዩ ዙሪያ ትናንት ሐምሌ 3 ቀን 2005 ዓ.ም ተጠይቀዉ «ምንም የሚፈጠር ችግር እንደሌለና ከፓርቲው አመራሮች ጋርም ለመመካከርና ለመወያየት ቀጠሮ ይዘናል፣ ፓርቲው ህጋዊ በሆነ መንገድ አሳውቆናል፣ መከልከልም ሆነ ማገድ አንችልም፤ ነገር ግን በፀጥታው ጉዳይ ለመነጋገር ነው ያሰብነው» የሚል አስተያየት ሰጥተዉ ነበር።

«ዛሬ በቀበሌ ሰራተኞችና በየቀጠናው ባሉ ፖሊሶች እየተደረገ ስላለው ምላሽ እንዲሰጡ ወደ ቢሯቸው ቢኬድም «ከቢሮ ውጭ ስብሰባ ላይ ናቸው» የሚል ምላሽ ተሰቷል። ከሰዓት በኋላ በተንቀሳቃሽ ስልካቸው ሲደወል ምላሽ ባለመስተጣቸው ምላሻቸውን በዚህ ዘገባ ማካተት አልተቻለም።

ይህ በእንዲህ እንዳለ የአንድነት ፓርቲ ከፍተኛ አመራሮች መካከል የመጨረሻው ዙር ከአዲስ አበባ አቶ ግርማ ሰይፉ(ብቸኛው የተፎከካሪ ፓርቲ የፓርላማ አባል)፣ አቶ ዳንኤል ተፈራ የፓርትዊ የሕዝብ ግንኙነት ክፍል ሃላፊ፣ አቶ በላይ ፈቃዱን ጨምሮ ሌሎች አመራሮች ለእሁዱ ሐምሌ 7 ቀን 2005ዓ.ም. ሰላማዊ ሰልፉ ዛሬ ደሴ ከተማ ገብተዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ከሼህ ኑሩ ይማም መገደል ጋር በተያያዘ በርካት ወጣቶች አሁንም እየታሰሩ መሆኑን 4ኛ ፖሊስ ጣቢያ የተመለከትኩ ሲሆን ይህ በሌሎችም ጣቢያዎች እየተከናወነ መሆኑም የከተማው ነዋሪዎች ይናገራሉ።

የአንድነት ፓርቲ አባላትን ደጋፊዎች ምንም እንኳን ጫናዉና እንግልቱ ቢቢረታም ጉልበታቸው እንዳልዛለ፣ ድምጻቸውን ከፍ በማድረግ፣ «ኢትዮጵያ ትጣራለች!» እያሉ ሕዝቡን መቀስቀሳቸውን እንዳላቆሙ የደረሰን መረጃ ያስረዳል።

የአንድነት ብሄራዊ ምክር ቤት ሰብሳቢ አቶ ዘካሩያስ የማነአብ ወደ ጎንደር ከማምራታቸው በፊት በደሴ የሰጡትን ቃለ መጠይቅ ከዚህ በታች ማዳመጥ ይችላሉ።

Source: abugidainfo.com

No comments:

Post a Comment