Monday, July 29, 2013

ኢትዮጵያዊው ዳያስፖራ

በታዬ ዘሐዋሳ

ከዞን ዘጠኝ ጦማር የተወሰደ

በሃገራችን በነበረው ፖለቲካዊ ቀውስ ወይም አመለካከት የተነሳበርካታ ኢትዮጵያውያን በስደት እንደሚኖሩ ይታወቃል:: የሚኖሩበትም ሃገር ብዛትና ስብጥር በራሱ ከሌሎች ሃገራት ዜጎች የተለየን ያደርገናል ብዬአስባለሁ:: እንደ ሃገራቱ ስብጥር እና ብዛት ሁሉ የሃበሻ አመለካከትም እጅግብዙ ነው:: ይህ ብዛት ያለው ስብጥር ደግሞ ወጥ የሆነ አመለካከት እንዳይኖረን አድርጓል::ክፍፍላችንም እንደዚያውብዙ ነው:: ፍረጃችንም ጭምር::የዛኑ ያክልም ኢትዮጵያዊ ዳያስፖራለመፈራረጅ ወይምለመሞጋገስ ከንፋስየፈጠነ ነው:: ፍረጃው ከተለያዩ አካላት ይጀመር እንጂ አብዛኛዎቹን ፍረጃዎች በማዳነቅና በማሟሟቅ ረገድ የሁሉም ድርሻ አለበት:: አንዲት የፌስቡክ ወዳጅ ስለፍረጃዎች ብዛትእና ጥልቀት ትዝብቷን አካፍላን ነበር:: ከነዚህ የርስ በርስ ፍረጃዎች ውስጥ የሚከተሉት በስፋትየምናስተውላቸው ናቸው:-

 .ኢቲቪ ወይም ኢሳት
 .ኢህአዴግ ወይም ተቃዋሚ
. አይጋፎረም ወይም ኢትዮጲያን ሪቪው
. አዲስዘመን ወይም ፍትህ
. ኢትዮጲያወይም ሞት ወይም ገንጣይ ተገንጣይ
. እምየሚኒሊክ ወይም አፄ ዮሃንስ
. ኢትዮጲያፈርስት ወይም ኦሮሞ ፈርስት
. ልማትወይም ሰብአዊ መብት
. ንኡስከበርቴ ወይም ደሃ
. ኪራይሰብሳቢ ወይም ልማታዊ
. ሰለፊስትወይም አህባሽ
. የውጪሲኖዶስ ወይም የሃገር ውስጥ ሲኖዶስ
. የምርጫትግል ወይም የትጥቅ ትግል
. ጠባብወይም አገር ወዳድ
. ባንዳወይም ጀግና
. የባንዳልጅ ወይም የጀግና ልጅ
. X ወይምY እያለ ይቀጥላል::

ይህን የፍረጃ ብዛት እና አይነት ለግዜው በዚህ እናብቃው:: የፅሁፌ መነሻ ርዕሥ በርካታ ሃሳቦችን ማስነሳት እንዲሁም ኢትዮጵያዊ ዳያስፖራንበተመለከተ የተለያዩሃሳቦችን ማንሳትና ማወያየት እንደሚችል ግልፅ ነው:: አነሰም በዛም እነዚህን ሃሳቦች እያነሱ መወያየትም ሆነ መተራረም ስለ ድክመታችን አውቀን የማስተካከያ እርምጃ እንድንወስድ ይረዳናል:: ድክመቱን በገደምዳሜ እያየንየምናልፈው ከሆነግን ለሃገራችንም ሆነ ለህዝባችን ፋይዳ አናመጣም:: መፅሃፉ እንዳለውም አስቀድሞ በአይናችን ያለውን ምሰሶ ማውጣት ስንችል ነው የጓደኛችንን ጉድፍ ማየት የምንችለው:: ነገርግን የኛ ዳያስፖራ እሱ ያለው እንጂ ሌላው የሚለው ትክክል አይደለም ብሎ የማሰብ አዝማሚያያሳያል::እናም ምናልባት የኔ ሃሳቦች ከተወደደው ዳያስፖራሃሳብ ጋር ካልተስማሙ የማይስማሙበትን ሁኔታ ለመስማት ዝግጁ መሆኔን አስቀድሜ ልግለፅ:: የባህርያችንን ጥልቀት ለማሳየትም ይመስላል "ኢትዮጵያየገባ አንድ ፀሃፊ በማግስቱ ስለ ኢትዮጵያውያን ከአንድ በላይ መፅሃፍ ሊፅፍ ይችላል:: በሁለተኛው ቀን ምናልባት ከተሳካለት ለጋዜጣየሚሆን መጣጥፍ ሊፅፍ ይችላል:: ሳምንት ሲቆይ ግን ያ ሰው ስለ ኢትዮጵያውያን አንድአረፍተ ነገር እንኳ መፃፍ አይችልም" አለየሚባለው:: ለማንኛውም ለዛሬ የሚከተሉትን "እዛም እዛም የረገጡ" ሃሳቦችንላንሳ:: ነገር ግን የማነሳቸው ሃሳቦች ከጥቂት ኢትዮጵያውያን ዳያስፖራዎችጋር ግንኙነት የሌላቸው እና እንደማይመለከታቸውም ባውቅም ብዙሃኑን ይወክል ዘንድ እነዚያን ጥቂቶችም የፅሁፌ አካል አድርጌያቸዋለሁ:: ለዚህአስቀድሜ ይቅርታ እጠይቃለሁ::

1)  የእርስ በእርስ ፍረጃ መፍትሄ ይሆነናል?

ፍረጃ በማንኛውም ልኬትቢለካ ወደምንፈልገው የልማት ግብ ሊያደርሰን አይችልም::ክፍፍሎችንና ፍረጃዎችንእየተከተልን ስንጨቃጨቅእና ስንፈራረጅ ዓለም ጥሎን መሄዱ አይቀርም::  የፍረጃችንን ጥልቀትየሚያሳይ አንድ ትዝብት ላንሳ:: አንዱ የውጭ ሃገር ዜጋ ስለኛ ክፍፍል እና ፍረጃ ከሃበሻ ጋር ሲወያይ "እናንተኢትዮጵያውያን በእስካሁኑሂደት በብሄር፤ በጎሳ፤ በቋንቋ፤ በሀይማኖት እናበመሳሰሉት ተከፋፍላችኋል:: አሁን የቀራችሁ ነገር ቢኖር በስማችሁ ፊደል ቅደም ተከተል መከፋፈል ነው፡፡" አለየሚባል መራራ የቀልድ እውነታ አለ:: በብዛት እንደምንታዘበውም አብዛኛውስለወቅታዊው ፖለቲካየሚያወራልን ኢትዮጵያዊሁሉ አንድነትን ወይም ህብረትን የሚሰብክልን የራሱብሄር ከፍታ ቦታ ላይ ሊሆን እንደሚችል ካሰበ ብቻ ነው:: የርሱን ብሔር የተመለከተ ሌላ ታሪክ ወይም ድርጊት ከተነገረ ከርሱ በላይ የዘር ፖለቲካን አራማጅ የለም:: ፍረጃውም በአይነት በአይነት ተደርድሮ ይቀርባል:: ይህንን አይነት አካሄድን የሚያሳየን ደግሞ በተለያዩ ግዜያት ጣል በሚደረጉ አመለካከቶች ስር የሚሰጡ አስተያየቶችን መመልከትስንችል ነው:: እንደዚህ አይነት አመለካከትና አካሄድምናልባት የምንፈራውን ከማፋጠን ያለፈ ፋይዳ የለውም:: ስለ አንድነት ሲሰብክ የነበረ ኦሮሞ ስለ ኦሮሞ እርሱ የማያምንበት ተፅፎሲያነብ ለዛ ፅሁፍ መልስ ወይም ማስተካከያ እና መከራከሪያ ሃሳብ ከማቅረብ ይልቅ የፀሃፊውን ዘር እያነሱ ጥንብ እርኩሱን በማውጣት ፍረጃ የሚያወጣለት ከሆነምኑን ስለ አንድነት ሰበከው? ስለዘር ፓለቲካ ጎጂነት አሳምሮ አቀነባብሮ የሚሰብከንሰው ስለትግሬ መጥፎነት በማውራት እና በመፈረጅ ካጠናቀቀው የቱላይ ነው አንድነትን የሚያሳየው?አንድነት ሃይል ነው እያለ የሚያስተምር ሰውስለ አማራ ጨቋኝነት እያነሳ እና አማራውን እየፈረጀ ሌላው ብሄር አማራን እንዲጠላ ከሰበከ የቱ ላይ ነው አንድነቱ ያለው? አንድ ነን እያለ ትግሬን አትመኑ ካለን፣ አንድ ነን እያለ አማራ በድሎናል በማለት ያለፈ ታሪክ ካወራ፣ አንድ ነን እያለ ኦሮሞ የመጣው ከዚያ ነው ካለ የቱ ጋር አንድነቱ ያለው? የሚወራው አንድነትስ የማን ነው? አንድነቱ ከግለሰቦች ካልጀመረ እንዴትስ አንድነት ይሆናል? ይህን ትዝብት ለግዜው እዚህ ልግታዉና ወደ ቀጣይ ሃሳብ ላምራ::


2)  ምን ያህል ዳያስፖራዎች ናቸው ሃገራቸውን የሚወዱት?

የግሌ መልስ "ምናልባት20% የሚሆኑት ይወዱ ይሆናል" ባይነኝ:: ሃገርን የመውደድ ልኬቱ በኔና በነሱ ሊለያይ ይችላል:: ለኔ ሃገርን መውደድ ማለት የግል ፍላጎትን እና ምቾትን ለሃገር አሳልፎ መስጠት ነው:: ሃገርን መውደድ ማለት እራስን አሳልፎ እስከመስጠት ማለት ነው:: ሃገርን መውደድ ማለት መከራን እና ችግርን መሸሽ አይደለም:: አንድ ሰው ፖለቲከኛ ሲሆን ለግል ጥቅሙ ሳይሆን ለህዝብና ለሃገር ሊሰራ ቆርጦ ተነሳ ማለት ነው:: ሆኖም ግን አንድ ችግር ሲያጋጥመው የሚኮበልልከሆነ ቀድሞውኑ የተነሳው ለራሱ ግላዊ ጥቅም እንጂ ለሃገርና ለህዝብ አልነበረም ማለት ነው:: ከዚህ የፖለቲከኞች ቁማር ጋር በተያያዘ የበርካቶችን ታሪክ ማንሳት ይቻላል:: ነገር ግን ከዚህ በፊትም ብዙ ስለተባለ ልለፈው:: በኔ አመለካከት ፖለቲከኛ ለያዘው አላማ ሞትን የሚጋፈጥ እንጂ የሚሞዳሞድ ወይምወደ ባእድ ሃገር የሚፈረጥጥ አይደለም::

ሌላው በዚህ ርዕስ ስር የማነሳው ሃሳብ ሰልፍን ይመለከታል:: በተለያዩሃገሮች ላይ ሃበሾች ሰልፍ ሲወጡ ይታያሉ:: ለምንድን ነው ሰልፍ የሚወጡት? ሀገራቸውን ስለሚወዱወይስ በሌላ ምክንያት? ከላይ እንዳልኩት 80%ቱምክንያታቸው ሌላነው:: ሃገሩንና ህዝቡን የሚወድ ሰው በሩቁ ሆኖ "ሊመታችሁነው ተጠንቀቁ""ሊገላችሁ ነው ሽሹ" ወይም"ገደላቸው ገረፋቸው" እያሉ በባዶ ሜዳ መፈክር ማሰማት አይደለም:: ሃገሩን የሚወድ ሞትንም ቢሆን ተጋፍጦ ለሃገሩ ለውጥ ያመጣል እንጅ በተንደላቀቀ ኑሮ ላይ ሆኖ እንዲህ እኔ እንደምጽፈው መፈክር እያዘጋጁ መሰለፍ አይደለም:: ከተሰላፊዎቹ መካከልበርካታ የሃገሪቱ አንጡራ ሃብት ፈሶባቸው በከፍተኛ ደረጃ የተማሩ ነገር ግን ብር ስላነሳቸው ብቻ ወይም የተንደላቀቀ ኑሮስላማራቸው ብቻበባእድ ሃገር ከሙያቸው ጋር ፍጹም ግንኙነት የሌለው ስራ እየሰሩ የሚኖሩ ነገር ግን ለሃገር ተቆርቋሪ የሚመስሉ አሉ:: በበርካታ ሺህ የሚቆጠሩ የህክምና ባለሞያዎች ሃገርቤት ያለ ወገናቸው በበሽታ እያለቀ እነርሱ ግን ብር ፍለጋ ብቻ አሜሪካ ወይም አውሮፓ ገብተው የሾፒንግ ካሸር ወይም የጽዳት ሰራተኛ ሆነው የሚሰሩ አሉ:: እውን እነዚህ ሰዎች ሃገራቸውንና ህዝባቸውን ይወዳሉ?በምርምር ስራቸውና የማስተማር ስራቸውአንቱ ተብለው ሲኖሩ የነበሩ ምሁራን ወደ ፈረንጅ ሃገር መጥተው ከሙያቸው ጋር የማይገናኝ ስራ እየሰሩ ነገር ግን ሰልፍ የሚወጡ እውን ሃገራቸውን ወደው ነው? ሃገርን መውደድ ማለት የደሃ ገንዘቧን አውጥታ ያስተማረችኝን ሃገርቢያንስ በሙያዬ ሳገለግላት እንጅሰባራ ሳንቲም ባላወጣብኝ ሃገርላይ ሳገለግል አይደለም:: ሃገርን መውደድ ማለት ወገንን ከድንቁርናና ከበሽታ መታደግ ማለት ነው:: ሃገርን መውደድ ማለት ወገንን እና ሃገርን ከጥፋት መታደግ እንጂ መታሰርን ወይም መሞትን መሸሽ አይደለም:: የዛሬ የኛ በገንዘብ ተቸግሮ ሃገሪራችንን ማገልገልማለት የነገውን ትውልድ እንዳይቸገር ማድረግ ነው:: የአንድ ሰው መታሰር ወይም መሞት ሚሊዮኖችን መተካት እንጂ መሞት አይደለም:: ይህንን የሰልፍ ጉዳይ በተመለከተ በእርግጠኝነት መናገርየምንችልባቸው በርካታሰዎችን ማንሳትና መነጋገር እንችላለን:: እነዚህ ሰዎች ባሉበት ሃገር የፖለቲካ ጥገኝነት ጠይቀው ውሳኔ እስኪተላለፍላቸው ድረስሰልፍ ያስተባብራሉ:: ሰልፍ ይወጣሉ:: ነገር ግን የነዚህን ሰዎች መቃወም ሳይሆን መፈጠራቸውን እንኳየኢትዮጵያ መንግስትእንደማያውቀው እራሳቸውምይረዱታል:: የግል ጥቅማቸውን ለማሳካትሲሉ ብቻ ሰልፈኞች ናቸው:: አንድ ከፌስቡክ ጓደኞቼ መሃል ታሪኳን የማውቀው እህትን ጉዳይ ላንሳ:: ይህች እህት በ2010 ኢትዮጵያ እያለች የተሳካላት አስጎብኚነበረች:: ሃገር ቤት እያለች የመንግስት ደጋፊምነበረች:: ነገር ግን በአንድ ወቅት ከጎብኚዎች ጋር ተመሳጥራ ተሰደደች:: ሆኖም በተሰደደችበት ሃገርላይ በቶሎ ፈቃድ ማግኘት ስላልቻለች ያላትአማራጭ ከተቃዋሚዎች ጋር አብሮ መስራት እንዲሁም መስራቷን ለማሳየት የተለያዩ ፎቶዎችን መነሳት፣ ሰልፎችን ማስተባበር ነበረባት::አደረገችው:: እንዲህአይነት በርካታ ሰዎችን ማንሳት እንችላለን:: ነገርግን መራራ ሃቅ ስለሆነ የሚጋፈጠው የለም::ሲነካም የሚያጉረመርመው ብዙ ስለሆነ ለውይይት ሲቀርብ አይስተዋልም::

እናም በፈረንጅ ሃገር የምንኖር ሃበሾች በእውነቱ እራሳችንን ወይም አጋሮቻችንን መመርመር አለብን:: አንድ ሰው የመኖሪያ ፈቃድ ለማግኘት አስቦ ሰልፍ ሲጠራን ተግበስብሰን መሄድንማቆም አለብን:: እውነተኛ የሀገር እና የህዝብ ፍቅር ካለን ግን አካሄዳችንን ማስተካከል አለብን::እውን ሃገሬን እወዳለሁ? ማለት አለብን:: ለምንድን ነው ሃገሬን የምወደው ብለን ራሳችንን መጠየቅ አለብን:: የተማርነው ደግሞ ሃገራችንን ከወደድን ገንዘብን እና ምቾትን ትተን ወደ ሃገራችን ተመልሰን ሃገራችንን ማገልገልአለብን:: "አሳሪወይም ገዳይ አለ" ብለንከፈራን ግን ሃገራችንን ሳይሆንእራሳችንን ነውናየምንወደው ዝምእንበል:: ፓለቲካው ላይ ያሉትን ሰዎች ስናይ የተማረ ባለስልጣን በስንት መከራ ነው የምናገኘው:: ለምን ሲባል ደግሞ የተማረው ሆዳም እና ምቾት ፈላጊ ስለሆነ ነው:: እውን ሃገራችንን የምንወድ ከሆነ የራሳችንን አካሄድማሰብ አለብን:: ለራሳችን የግል ምቾት ተቆርቋሪ ሆነን ሳለ ለሃገር አሳቢ መስለን እኛ የማንደፍረውን ወይምየሸሸነውን ነገርሌላው እንዲያደርገው መምከርና የሃገሪቱን የወደፊት እጣ ፈንታ ባለህበት እርገጥ እንዲል ማድረግ የለብንም:: ሃገሩን የሚወድ የራሱን ምቾት ወዲያ ጥሎ በፈለገው አካሄድ ለአላማው መቆም አለበት:: መሸሽ ወይም በውጭ ሆኖ ሰልፍ መውጣት ሃገርን መውደድ አይደለም:: ሃገራችን የተማሩ ልጆቿን ጣልቃ ገብነት ትፈልጋለች:: ያልተማሩ እና ለሆዳቸው ያደሩ እየመሯት ታድጋለች ማለት የህልም እንጀራ ነው:: ቢሆንማ ኖሮ ባለፉት 40 አመታትብቻ የብልጽግና ማማ ላይ በወጣን ነበር:: መስሪያ ቤቶቻችን በተማሩ ሰዎች መሞላት አለባቸው:: ይህንን ማድረግ የሚቻለው ደግሞ የተማረው የሰው ሃይል አላማ ሲኖረውና በሆድ ማሰብን ትቶ በጭንቅላቱ ማሰብሲጀምር ነው:: "ምንም ብጎሳቆል የተሻለች ነገን በሀገሬ ላይ ለማየት በሙያዬ ልሰራ ይገባኛል" ማለት ስንችል ነው:: መሸሽ ወይም ሃገር ጥሎ መኮብለል መፍትሄ አያመጣም::

3) ማነው ሙሰኛው?

ሌላው ርዕሴ ሙስና ነው:: ሙስና ሲባል አብዛኛውን ግዜ የሚመጣብን የመንግስት ባለስልጣናትን ሙስና ብቻ ነው:: ከሰሞኑ ትውስታ ብናይ እንኳ ከአንድ ባለስልጣን ቤት ብቻ በርካታ ገንዘብ እንደተገኘ ሰምተናል::ይህንን ድርጊት መንግስት አጥብቆ እንዲገፋበት በተቻለንአቅም ሁሉ አስተያየት በመስጠትስናበረታታ ነበርን::ጠቅላይ ሚኒስትራችንም በተለያዩ ግዜያት በፀረ-ሙስና ትግሉ ላይ ያላቸውን ቁርጠኝነት አስረግጠው ቃልገብተውልናል:: እርሳቸውበቃላቸው የሚፀኑ ከሆነ መላው ህዝብ እንደሚተባበራቸውና የፀረ-ሙስና ትግሉ ተፋፍሞ እንደሚቀጥል የታወቀነው:: ይህ እንዳለ ሆኖ ግን "እውንየመንግስት ባለስልጣናትብቻ ናቸው ሙሰኞች?" በማለትመጠየቅ እወዳለሁ:: የመንግስት ባለስልጣናትን በሙስና ስንከስ ህብረተሰቡንም አብረን መክሰስ አለብን:: ሙስና በተፈጥሮው የሰጪናየተቀባይ ሂደት እንጂ የተቀባይ ብቻ አይደለም:: ዋነኛው ጥፋተኛ ሰጭው አካል ነው:: ካለው ስግብግብነት የተነሳበገንዘቡ መደራደርን የመረጠ የህብረተሰብ ክፍል ሰጪ ባይሆን ተቀባይም አይኖርም:: በማንኛውም ልኬት ቢታይ ሙሰኞች የሚቀበሉት ከሰጪ ላይ በሰጪ ፍላጎት እንጂ አስገድደው አይደለም:: ላስገድድ የሚሉትማ በወቅቱ በህግ ቁጥጥር ስል ይውላሉ:: በባህሪያቸው ሙስናንየሚጠየፉና የተመሰገኑሰዎችን በስልጣን ላይ ስላስቀመጥንም ሙስናን መከላከል አይቻልም፡፡ የሰጪዎችአመለካከት እስካልተቀየረ ድረስ ተቀባይ ሁሌም ይኖራል::

በሌላ አቅጣጫ ደግሞ የተማረውን ስደተኛእንይ:: አንድን የህክምና ባለሙያ ለማስመረቅ ቢያንስበድሮው ካሪኩለም ሰባት አመት፣ በአሁኑ ስድስት አመት ያስፈልጋል:: በነዚህ አመታት የህክምና ትምህርቱን ለማሳካት የሚያስፈልገውን አጠቃላይ ወጪ ብናሰላው በትንሹ ከ1 ሚሊየን እስከ 1.5 ሚሊየንብር ድረስ ይወጣበታል:: ነገርግን ስንቶች ናቸው ይህ ሁሉ ገንዘብ ከወጣባቸውና ከተማሩበኋላ ሀገራቸውን ጥለው የወጡት? ይህ ሙስና አይደለምን? ይህበሌሎች የሙያ ዘርፎችም ተመሳሳይ ነው:: ሃገሪቱ በከፍተኛ ክፍያ አስተምራቸው የሃገራቸውመንገድ በቻይና ባለሙያ ሲሰራ እነርሱ ግን የአውሮፓን መንገድየሚቀይሱት ሙሰኞችአይደሉምን? የሃገሪቱዩኒቨርሲቲዎች መሪእያጡ ወይም ብቁ አስተማሪ እያጡ እነርሱ ግን አውሮፓና አሜሪካ ተሰደው የሚያስተምሩት ሙሰኞችአይደሉምን? ለትምህርትጥራቱ ማሽቆልቆል የየራሳችን አስተዋፅኦሊኖረን የቻለውም በዚህ የተደበቀ ሙስና አይደለምን? የሙስና ትግል ስናነሳ ትግሉ ከሁላችንም ቤትሊጀምር ይገባዋል:: ሙስናን ሁላችንም ልንጠየፈው ይገባናል::መንግስት ወይም የፓርቲ አባላት ብቻ ሙስናን እንዲፀየፉ አንጠብቅወይም አንስበክ:: እኛስ? ስንቶቻችን ነን ለሃገራችን ያልከፈልነው ገንዘብእንዳለብን የምናውቀው?ሃገራችን እኛን ለማስተማር ያፈሰሰችውንገንዘብ ይዘን እንደጠፋን ስንቶቻችንእናውቅ ይሆን? ሀገራችን እኛን ለማስተማር ያወጣችውንገንዘብ ዘርፈን ለባእድ ሀገር በነፃ ያስረከብንስ ሙሰኞች አይደለንምን?

4)  የዳያስፖራ አንድነትና ትዕግስት

በመጨረሻም አንድነትንና ትዕግስትንበተመለከተ ትንሽልበል:: በበርካታ ግዜያት እንደምናየው ዳያስፖራዎች ስለአንድነት እንዲሁም ብንከፋፈል ስለሚደርስብን ጉዳት ይተነትኑልናል:: ነገርግን ማነው አንድነትን ያጣው?ከላይ ያነሳኋቸው የፍረጃ አይነቶች የሚመነጩት ወይምተጧጡፈው የሚገኑት በዳያስፖራው እንጂሃገር ቤት ባለው አይደለም:: አንዳንዴ ሲታይ ዳይስፖራዎች የሚያነሷትኢትዮጵያ እንደ ኢቲቪዋ የተለያየች እንደሆነች ሊሰማንሁሉ ይችላል:: "ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር" የሚልመፈክር እያሰማ ሌላውን ብሄር ሙልጭ አድርጎ የሚሰድብ እና የሚያንኳስስ ሰውያለው ዳያስፖራ ውስጥ ነው:: ኢትዮጵያ ለዘላለም ልትኖር የምትችለው ብሄር ብሄረሰቦቿ ተስማምተውና ተከባብረውሲኖሩ እንጂ ተሰዳድበው አይመስለኝም::ዳያስፖራው ወቅታዊውንንፋስ እየተከተለ የሚነፍስ ፖለቲከኛ ብቻ ነው:: አፉ የጣፈጠ ቀጣፊ ሲያወራለት ተከትሎ የሚጓዝ ነገር ግን የተወሰነ ርቀት ላይ ሲደርስ እርሱ የሚያስበውን ካልተናገረለት ያንንሰው አፈር ካላስገባሁ ለማለትየሚፈጥን ፖለቲከኛ ያለው ዳያስፖራ ውስጥ ነው:: መዋደድን፣ መከባበርን፣በሃሳብ ተለያይቶ በሰለጠነ መልኩ መነጋገርን ዳያስፖራውሊማር ይገባዋል:: ለፍቅርም፣ ለጥላቻምመፍጠን ሃገርን ይጎዳል እንጂ የትም ሊያደርስ አይችልም:: መንግስትን በፍረጃው እየከሰሱ ከመንግስት እጅግበላቀ መልኩ ፈራጅ ሆኖ መገኘት ምን የሚሉት ስልጣኔስ ነው? ዳያስፖራው ተፈረጅኩ ብሎ ሰልፍ እንደሚወጣው ሁሉ እርሱ እንዲፈርጅ የሚያፈቀድለት ምክንያት አይታየኝም:: ተስማምቶ፣ተግባብቶ ለመነጋገር ዳያስፖራችን ገናእንጭጭ እድሜ ላይ እንዳለ ለመረዳት አንዱን የፌስቡክ አክቲቪስት ጓደኛ አድርጎ አስተያየት ሰጭዎችንመታዘብ ብቻ በቂ ነው:: ከተቻለም ፓልቶክ ላይ ገባ ብሎ ለ10 ደቂቃ የሚባለውን መስማት በቂ ነው:: ስብሰባ ጠርቶ ማስጨብጨብ ወይም ከስብሰባው በኋላ "የርሱብሄር እንዲህ ነው" "የርሷብሄር እንዲህ ነው" እያሉእርስ በእርስ መንኳሰስ አንድነትን አያሳይም:: ሃገር ቤት ያለው ኢትዮጵያዊ በምንምመልኩ ይህንን አይነት ድርጊት አያደርግም:: እናምዳያስፖራ ሆይ አንድነት አለኝ ትለን ይሆን? ትዕግስትስ አለኝትለን ይሆን? መከባበርስ አለኝትለን ይሆን? በሰለጠነ መልኩ ልዩነትን አክብሮ መወያየትስ እችላለሁትለን ይሆን? እራስህን መርምር::

ሳጠቃልል:- ሁላችንም ባለንበት ወይም በተሰማራንበት ሙያላይ ሆነን የምንፈልገውን ለውጥማምጣት እንችላለን:: ጋዜጠኛ "ዋሽ"ሲባል "አልዋሽም"ብሎ መተባበር እንጂ መሸሽ ውሸቱን አያቆመውም:: ፖሊስም "ግደል"ሲባል "ወንጀለኛንለህግ አቀርባለሁ እንጂ አልገድልም" ብሎ መተባበር እንጅ ስልጣንን ማስረከብ መፍትሄ መንደማይሆን ዳያስፓራውሊያስተምር ይገባል::ባለስልጣንም "ዋሽ"ወይም "አስገድል"ወይም "ሃገርሽጥ" ሲባልመሸሽ ወይም "ስልጣናችሁን አልፈልግም"ማለት መፍትሄ አይሆንም:: ተቃዋሚዎችም "የውሽት ምርጫ ነው" እያሉማማረር ሳይሆን "አስተካክሉት" ማለትአለባቸው:: ተቃዋሚ ለመሆን ብቻ መስራትንም ማቆምአለባቸው:: በስልጣን ላይ ያለው መንግስት አነሰም በዛም ባለው ፖሊሲ መሰረት እንደሚሰራ እናውቃለን::በስመ ተቃዋሚነት የተሰሩ ስራዎችን ጭፍልቅ አርጎ እንዳልተሰራ መስበክመቆም አለበት:: የተሰራውን ጠቅሶያልተሰራውን እንዲሰራመጠየቅ መፍትሄ ይሆነናል:: የዳያስፖራ ሰልፍም የሚያጠነጥነው ሁሌም በተቃውሞ እንጂ አማራጭን ታሳቢ ያደረገ አይደለም:: አማራጭ ማሳየት ሳይቻል ዝም ብሎ መቃወም በራሱ መፍትሄ አይሆንም:: ተቃዋሚዎቹ ለመቃወምብቻ ሳይሆን አማራጭ ፓርቲ ሆኖ ለመቅረብ መስራት አለባቸው:: ገዥው ፓርቲም "የተለመደ ውንጀላ ነው" እያለገንቢ አስተያየቶችን ከመግፋት ይልቅ አስተያየቶቹን ገምግሞገንቢ የሆኑትን ወስዶ ሌላውን መተው መልመድ አለበት:: "አንተከዚያ ነህ አንተም ከነዚያ ነህ" እያለመፈረጁን ማቆም አለበት:: እየተፈራረጅን የትም መንቀሳቀስ አንችልም:: አንድ ሰው ተቃወመም፣ ደገፈም በሙያው ግን ሀገራዊ ግዴታውን መወጣት አለበት:: ተመሪም ሆነ መሪ ፍረጃን አቁሞ ለሃገር ለመስራት መፎካከር አለበት:: የተማርነውም እስኪከትንሿ ሃላፊነታችን እንጀምር:: የሙያ ሃላፊነታችንን ምንያህል እንደተወጣን እንፈትሸው:: እስኪወደፊት ትምህርቴን ስጨርስ ምን ማድረግ ነው ያሰብኩት እንበል:: ከዛም የፍተሻውን ውጤት ከሃገርና ከህዝብ ፍቅር አንጻር እንመዝነው:: የራሳችንን ምቾትለማሳካትና ለባዕድሃገር ለመስራት እየተሯሯጥን በይስሙላብቻ ሀገርን መቃወም ፍይዳ ያለው አይመስለኝምና ራሳችንን እንመርምር:: ዳያስፖራ የሚልከው ገንዘብ እጅግ ብዙ ነው እያልንም ራሳችንን አንሸውድ:: ሃገርን ከፓርቲ እንለይ:: በመጨረሻም ዳያስፖራሆይ እራስህን መርምር:: የቆምክ መስሎህ ከሆነ ተዘናግተሃል:: አበቃሁ::

ጸሐፊውን ለማግኘት jhnb4775@gmail.com ይጠቀሙ::
---
የዚህጽሑፍ ዋና ቅጂ በኢትዮጵያ እንዳይነበብ በታገደው በዞን ዘጠኝ ጦማር ላይ ይገኛል፡፡

No comments:

Post a Comment