Monday, July 22, 2013

ወያኔ የቀረበውን የሚያደማ እሾህ ነው! ሼህ ይማም ኑሩን ማን ገደላቸው?

በምርጫ 97 ማግሥት “ድምፃችን ይከበር” በማለታቸው ከሁለት መቶ በላይ ንፁሀን ዜጎች በግፍ መጨፍጨፋቸው በተነሳ ቁጥር የወያኔ ሹማምንት ከሰልፈኞቹ መሀል መሣሪያ የታጠቁ እንደነበሩና ሦስት ፓሊሶችም መገደላቸውን ይናገራሉ። የእነዚያ ፓሊሶች ሞት አሳዛኝ አውነት ሲሆን አሟሟታቸው ግን ጉዳዩን እንዲያጣራ ለተቋቋመው አጣሪ ኮሚሽን እንኳን ምስጢር ነው። ለጊዜው እውነት ተዳፍናለች፤ ፍትህ ተረግጣለች። ጊዜው ሲደርስ ግን የፓሊሶቹ አውነተኛ ገዳይ መውጣቱ አይቀርም። ይኽ ዛሬ ምስጢር የሚመስለን የሦስቱ ፓሊሶች አሟሟት “ንፁሀን ዜጎችን ለመፍጀት ሰበብ ለማግኘት ሲባል በሥራ ገበታቸው ላይ በነበሩ የፓሊስ አባላት የተፈፀመ አጅግ መሠሪና አስነዋሪ ወንጀል” ተብሎ የሚጠቀስበት ወቅት ይመጣል። ይህ የወያኔ ድርጊት ይበልጥ አሳሳቢ የሚያደርገው የአንድ ወቅት የተናጠል ክስተት አለመሆኑ ነው።

ከአሜሪካ ኤምባሲዎች ሾልከው የወጡ በርካታ ሰነዶች የተዘረገፉበት ዊኪሊክሰ በተሰኘው ድረገፅ የተገኙ መረጃዎች እንደሚያረጋግጡት ወያኔ ሰዎችን ገደሎ በተቃዋሚዎች እንደሚያላክክ አሜሪካ ታውቃለች። ከእነዚህ ሰነዶች አንዱ – ለምሳሌ – ወያኔዎች ሚኒባስ ታክሲ ውስጥ ቦንብ አፈንድተው በተቃዋሚዎች ማሳበባቸው ተብራርቷል።


ከምርጫ 97ም ሆነ ከዊኪሊክስ በፊትም ሆን በኋላ ወያኔ በእንዲህ ዓይነት አኩይ ተግባራት መካኑ ተከታዮቹና ደጋፊዎቹ የነበሩ ሰዎች የሚመሰክሩት ሀቅ ነው። የሀውዜን ሕዝብ አንዲጨፈጨፍ የተደረገው የትግራይ ሕዝብ በደርግ ላይ እንዲያመር በወያኔ በተረቀቀ ስልት መሆኑ ጉዳዩን በቅርበት የሚያውቁ የቀደሞ አባላቱ ደጋግመው የሰጡት ቃል ያረጋግጣል። በኦሮሞ ማኅበረስብ ተሰሚነት የነበራቸው አቶ ደራራ ከፈኔን በኮሜቴ ውሳኔ አስገድለው በኦነግ ማላከካቸው በወቅቱ ውስጥ አዋቂ የነበረ ጋዜጠኛ በፃፈው መጽሐፍ አሳውቆናል። የወያኔ መሠሪነት ልክም ድንበርም የለውም።

ከላይ የተዘረዘረው መረጃ ያለው ሰው ሼህ ይማም ኑሩን ማን አንደገደላቸው መገመት አይቸግረውም። ግምቱም ተራ ግምት ነው የሚባል አይደለም። ዋነኛው ተጠርጣሪ መርማሪ በሆነበት ሥርዓት ውስጥ ከዚህ የተሻለ ማስረጃ ማግኘት ይከብዳል። ዋነኛው ተጠርጣሪ መርማሪም ዳኛም በሆነበት ሥርዓት የሼህ ይማም ኑሩ እውነተኛው ገዳይ ለፍርድ እንደማይቀርብ እርግጠኛ መሆን ይቻላል።

ከዚህ አሳዛኝ የግድያ ድራማ የምንቀስመው ትምህርት ምንድነው?

ዜጎች ከዚህ የሚከተሉትን ነጥቦች በአንክሮ እንዲያጤኑ ግንቦት 7: የፍትህ፣ የነፃነትና የዲሞክራሲ ንቅናቄ ይመክራል።

1. ወያኔን መጠጋት ከህሊና ጋር ቢያጣላም እንኳን ጥቅም የሚያስገኝ “ቢዝነሰ” አድርጋችሁ ለምታዩ ሁሉ እውነታው የምታስቡትን ተቃራኒ ሊሆን የሚችል መሆኑን እወቁ። ወያኔ ጥቅም የሚያስገኝ መሰሎ ከታየው የራሱንም ሰዎች ለእርድ ያቀርባል። ወያኔ ከራሱ በስተቀር ወዳጅ የለውም። ወያኔ የቀረበውን የሚያቆስል የአጋም እሾህ ነው። ጥቅም የሚያስገኘለት ከሆነ ወያኔ የሚላላኩለትንም የሚበላ አኩይ ኃይል መሆኑን ከሸህ ይማም ኑሩ እጣ ፈንታ እንማር።

2. ለጊዝያዊ ጥቅም ወያኔን መጠጋት በክፉ ቀን ከጎን የሚቆም አጋርን ማጣት እና የግል ታሪክን ማቆሸሽ መሆኑን እንገንዘብ። በታሪክ ውስጥ ሼህ ይማም የሚታወሱት በእምነት ወንድሞቻቸውና እህቶቻቸው እንደተነሱ ሰው መሆኑ የማይቀር ነው።

3. ከፋሺስቱ ወያኔ ጋር በመሆን ፍትህ እንዲጓደል፤ ሰቆቃ እንዲበዛ አስተዋጽዖ እያደረጋችሁ ያላችሁ ዳኞች፣ ፓሊሶች፣ የመንግሥትም ሆነ መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማት ሠራተኞች ከዚህ ተግባራችሁ ተቆጠቡ። ወያኔ ለእናንተም አ
ይበጅም።

ይህንን ምክር አልሰማ ብላችሁ ከወያኔ ጋር በማበር ሕዝብን ለሞት፣ ለእስራት፣ ለሰቆቃ፣ለመፈናቀል፣ ለስደት እና ለእንግልት የምትዳርጉ አድርባዮች ከህሊና ወቀሳ ብቻ ሳይሆን ከቅጣት የማታመልጡ መሆኑን ግንቦት 7: የፍትህ፣ የነፃነትና የዲሞክራሲ ንቅናቄ በጥብቅ ያስታውቃል።

ድል ለኢተዮጵያ ሕዝብ!

No comments:

Post a Comment