Wednesday, July 3, 2013

በትግራይ ክልል አስተዳዳሪዎች ከህዝብ ጋር እየተጋጩ ነው

አንድ፥ አፅቢ

በአፅቢ በወረዳ አስተዳዳሪዎችና ህዝብ መካከል አለመግባባት ተፈጥሮ ብዙ ዜጎች ለእስር ተዳርገዋል። ችግሩ የተፈጠረው በግጦሽ መሬት ሲሆን የወረዳው አስተዳዳሪዎች ህዝቡ የራሱን ሳር እንዳይጠቀም (ግጦሹ እንዲከበር) ትእዛዝ ያስተላለፉ ሲሆን የወረዳው ህዝብ ግን የራሱን ሳር መጠቀም ይፈልጋል።

አስተዳዳሪዎቹ ብዙ ፖሊሶችና ምልሻዎች ሰለማዊ ህዝቡ እንዲደበድቡ አዘው ብዙ ችግር ካደረሱ በኋላ 'አስተባባሪዎች' ተብለው የተፈረጁ አርሶ አደሮች በፖሊስ በሃይል እንዲታሰሩ ስለተደረገ ወደ 1500 የሚደርስ ህዝብ ተሰብስቦ አመፅ ማስነሳቱ ታውቃል። ፖሊሶች አስተባባሪዎቹን ለማሰር በሚሞክሩበት ግዜ ህዝቡ ድንጋይ እየወረወረና እየጮኸ ተቃውሞውን አሰማ። ፖሊሶች ህዝቡን በዱላ በመደብደብ ለመበተን ሞክረው ስላልተሳካላቸው ብዙ እንደተኮሱና ' የዓመፁ አስተባባሪዎች' ተብለው ከተፈረጁ አርሶ አደሮች መካከል ህድሮም ሃይለስላሴ የተባለ ተሳታፊ ሦስት ግዜ ተተኩሶበት አንድ ግዜ ልብሱ ተመቶ ሁለቴ እንደሳቱት መረጃ ደርሶኛል። (ህድሮም የታጋይ ልጅ ሲሆን አባቱ በትግሉ ወቅት ተሰውቷል።) ወልደገብርኤል ሃይሉ የተባለ ሌላ አርሶ አደር ደግሞ በፖሊሶች አስከፊ ድብደባ ደርሶት ወደ ሆስፒታል መወሰዱና ከዛም መታሰሩ ተነግሯል።

የህዝቡን ተቃውሞ ለማክሸፍ የተሞከረው ጠንከር ያለ አስተያየት ይሰጡ የነበሩ አርሶ አደሮችን ከነከብታቸው በማሰር ነበር። በዚህ መሰረት 41 አርሶ አደሮችና 60 ከብቶች ታስረው ነበር። ታስረው በዋስ ከተለቀቁ መካከል ሻለቃ አታክልቲ ገብረኪሮስ፣ ታጋይ ክንፈ ገብረህይወት፣ ወ/ሮ ፃድቃን ገ/ሄር፣ ወ/ሮ አከዛ በርሀ፣ ንጉሰ ነጋሽ፣ ወልደገብር ኤል ሃይሉ፣ ህድሮም ሃይለስላሴ .... ይገኙባቸዋል። ጠፍተዋል ተብለው በፖሊስ እየተፈለጉ ያሉ ደግሞ ካሕሳይ ፅሑፍ፣ ወ/ሮ አለማት ብርሃንና ደስታ ብርሃን ናቸው።

'ሰሚ የለ፣ ፍትሕ የለ' እያሉ ያማርራሉ።

ሁለት፥ ሓውዜን

በሓውዜን አደገኛ ውጥረት ነግሷል። የወረዳው አስተዳዳሪዎች (ና ሌሎች የህወሓት ከፍተኛ መሪዎች) 'ሓውዜን የከተማነት ደረጃ አይገባትም' ብለው ይከራከራሉ፤ ማዘጋጃቤት እንዳይኖራት ለማድረግ። የሓውዜን ህዝብ ይህንን ተግባራቸው ተቃውሟል። ህዝቡ 'የሓውዜን ከተማ በማዘጋጃቤት የማትተዳደርበት ምክንያት ምንድነው?' ብሎ ይጠይቃል።። አስተዳዳሪዎቹም 'ሓውዜን መዘጋጃቤት የማይገባት አስፋልት መንገድ ስለሌላት ነው' ይላሉ። ህዝቡ አስፋልት መንገድ የሌላቸው ሌሎች ከተሞች በማዘጋጃቤት እንደሚተዳደሩና አስፋልት እንደመስፈርት ሊወሰድ እንደማይችል በማስረጃ ሲያረጋግጥ ባለስልጣናቱ ደግሞ የከተማው ነዋሪ ህዝብ ቁጥር በግማሽ በመቀነስ የሓውዜን ህዝብ ቁጥር ለከተማነት እንደማያበቃ አስረግጠዋል።

ግን የህዝብ ብዛት ቁጥር መቀነስ ለምን አስፈለገ? አስፋልት መንገድ እንደመስፈርት የሚወሰድ ለሓውዜን ከተማ ብቻ ነው እንዴ? ደግሞ'ኮ አስፋልት መገንባት የአስተዳዳሪዎቹ ስራ እንጂ የህዝቡ አይደለም። ሓውዜን እስካሁን አስፋልት መንገድ ከሌላት ተጠያቂ ከህወሓት ውጭ ማን ሊሆን ነው? ራሳቸው በፈጠሩት ችግር ህዝብ ተጠያቂ ማድረግ እስከመቼ? ደግሞ ሓውዜን ማዘጋጃቤት እንዳይኖራት መከራከር ለምን አስፈለገ? የከተማው አስተዳዳሪዎች ለከተማው ዕድገት ካልሰሩ ዓላማቸው ምንድነው?

የሓውዜን ህዝብ በአስተዳዳሪዎቹ ተግባር በጣም አዝነዋል። ብዙ ሰው 'አስተዳዳሪዎቹ ሓውዜን መጋጃቤት እንዳይኖራት የሚታገሉ የአከባቢው ተወላጆች ስላልሆኑ ነው' የሚል ግምት አላቸው (ከድሮ ጀምሮ የሓውዜን አስተዳዳሪዎች ከሌላ አከባቢ የመጡ ሰላዮች ናቸው፤ እነሱ የሓውዜን ህዝብ አያምኑም፣ ህዝቡም አያምናቸውም)። 'ወረዳ ሊያስተዳድር የሓውዜን ተወላጅ የለም ማለት ነው?' ብለው ይጠይቃሉ።

ለማንኛውም ዉጥረቱ አይሏል። ህዝቡ በተለያየ መንገድ ተቃውሞውን እያሰማ ነው። የ'ሰኔ 15 የሰማእታት መታሰቢያ በዓል' በተቃውሞው ምክንያት ተሰናክሏል። የሓውዜን ህዝብ የጉዳዩ ተወካዮች መቀለ ድረስ መተው አቤቱታቸውን ለክልል መንግስት ለማቅረብ እየተዘጋጁ ናቸው።

የሓውዜን የድሮ ታጋይ ነዋሪዎች አሕፈሮም የተባለ የወረዳው አስተዳዳሪ ማስፈራራታቸውና አሁን በከተማው በነፃነት እንደማይንቀሳቀስ ታውቋል። አንድ የወረዳው ሰራተኛ ደግሞ 'ተቃውሞ የለም፣ የሚረብሹ አንዳንድ ዱርየዎች ናቸው' ብሎ ለድምፂ ወያነ ሬድዮ አስተያየት በመስጠቱ በከተማው ቁጣ መቀስቀሱ ተሰምቷል።

ጉዳዩ እየከረረ ሲሄድ አስተዳዳሪዎቹ 'ሓውዜን በማዘጋጃቤት የምትተዳደር ከሆነ የሴፍቲኔት እርዳታ አይሰጣችሁም' የሚል ቀሺም ማስፈራርያ ተጠቅመው ህዝቡ ተቃውሞውን እንዲያቆም ጥረት እያደረጉ ናቸው።

ሦስት፥ ኢሮብ

የኢሮብ ወረዳ ነዋሪዎች (በኢትዮ ኤርትራ ድንበር የሚገኙ ናቸው) በተደጋጋሚ በሻቢያ ጥቃት ሲደርስባቸው የህወሓት መንግስት ዝምታን ይመርጣል። እስካሁን በመንግስት እንደተገለሉ ናቸው። ምክንያቱ ምን ይሆን? ምናልባት ባድመ (በአልጀርሱ ስምምነት መሰረት) ለኤርትራ ስትሰጥ ከፍተኛ ተቃውሞ አንስተው ስለነበር ይሆን? በወቅቱ የኢትዮዽያ መንግስት ባድመ በውሳኔው መሰረት ለኤርትራ መሰጠት እንዳለበት ከወሰነ በኋላ የትግራይ ህዝብ ተቃውሞ ነበር። በተለይ የኢሮብ ህዝብ ጉዳዩ ለማብራራትና (ባድመ ለኤርትራ መሰጠት እንዳለበት) ለማሳመን ወደ ወረዳው የተላኩ የህወሓት ባለስልጣናት ሰድቦና አዋርዶ ስለመለሳቸው አሁን እየተበቀሉት ይሆን? በዛን ግዜ ተወስደው እስካሁን ደብዛቸው የጠፋ አንድ መቶ (100) የሚሆኑ የኢሮብ ተወላጆች ጉዳይ በመንግስት ደህንነታቸው አይጠበቅም ማለት ነው? እነኚህ የሚደርሱ የኢሮብ ተወላጆች የት አሉ? ይሄን ጉዳይ መንግስት የሚመለከት አይደለምን??? የኢሮብ ተወላጆች እስካሁን ድረስ እየታፈኑ ወደ ኤርትራ ይወሰዳሉ። የወረዳው አስተዳዳሪዎች ግን ምንም እርምጃ ወስደው አያውቁም።

አራት፥ እንደርታ

በእንደርታ ወረዳ ደርግዓጀን ተብሎ በሚታወቅ አከባቢ የሚኖሩ ህዝቦች በሁለት ተከፍለው እርስበርሳቸው እንዲፋጁ እየተደረገ ነው። አንዱን ቡድን በአከባቢው አስተዳዳሪዎች የሚደገፍ ሲሆን በሌላኛቸው ቡድን ብዙ (ሞትን ጨምሮ) ኪሳራ በማድረሱ የሌላኛው ቡድን ወጣቶች ተሰብስበው ወደ ዓፋር መግባታቸው ተሰምቷል። የወረዳው አስተዳዳሪዎችም የወጣቶቹ ስም ዝርዝር ይዘው ወደ አለቆቻቸው በመቅረብ 'ወጣቶቹ ጠግበው ሽፍትነት መምረጣቸው' አስረድተዋል።

ወይ ግርም! 'ኪድንያ አይትበሎ፣ ከም ዝኸድንከ ግበሮ' ዶ በሉታ።

አስተዳዳሪዎች ግን የህዝብ ክብር አያውቁም እንዴ? ወይስ ራሳቸው ተስፋ ስለቆረጡ ነው?

ለማንኛውም ህዝብ በማገልገል እንጂ በማስፈራራት ማስተዳደር እንደማይቻል ከደርግ ስርዓት ትምህርት መውሰድ ያለብን ይመስለኛል።

It is so!!!

ምንጭ፡ አብርሃ ደስታ

No comments:

Post a Comment