Friday, January 31, 2014

የኢትዮጵያ መንግስት የግንቦት7 መሪዎችን ኮምፒዩተሮች በዘመናዊ የስለላ መሳሪያዎች ሲሰልል እንደተደረሰበት አንድ አለማቀፍ ተቋም አጋለጠ

ኢሳት ዜና :-የህዝቦችን ደህንነት ከመንግስታት ጥቃት ለመከላከል የተቋቋመው ፕራይቬሲ ኢንተርናሽናል የተባለው  ተቋም ለእንግሊዝ መንግስት የገቢዎቸና ጉምሩክ መስሪያ ቤት በጻፈው ደብዳቤ “ጋማ ኢንተርናሽናል የተባለው የእንግሊዝ ኩባንያ በአለም ላይ የሰብአዊ መብቶችን በመጣስ ለሚታወቁ አገሮች ኮምፒይተሮችን፣ የሞባይልና የስካይፕ የስልክ ግንኙነቶችን እንዲሁም የኢሜል ልውውጦችን በርቀት ሆኖ ለመከታተል የሚያስችለውን ፊን ፊሸር ወይም ፊን ስፓይ በሚል ስም የሚጠራውን የመሰለያ መሳሪያ ከአውሮፓ ህብረት ውጭ ላሉ አገሮች በመሸጥ ዜጎች እንዲሰለሉና ደህንነታቸው አደጋ ላይ እንዲወድቅ በማድረጉ  ምርመራ እንዲጀመር” ሲል ጠይቋል።

የግንቦት7 ከፍተኛ አመራር በሆኑት በ ዶ/ር ታደሰ ብሩ የግል ኮምፒዩተር ላይ የመሰለያ ቫይረሱ መገኘቱን በቶሮንቶ ዩኒቨርስቲ የሙንክ ስኩል ግሎባል አፌርስ የምርምር ተቋም የሆነው ሲትዝን ላብ ማረጋገጡን ፕራይቬሲ ኢንተርናሽናል በደብዳቤው ገልጿል።

የመሰለያ መሳሪያው የሰብአዊ መብቶችን በሚጥሱ 36 አገራት ላይ መሸጡን የገለጸው ፕራይቬሲ ኢንተርናሽናል፣ በተለይም በቬትናም፣ ማሌዚያና ኢትዮጵያ የፖለቲካ ተቀናቃኞችን ለመሰለያነት እየዋለ ነው ብሎአል።

በኢትዮጵያ የግንቦት7 ከፍተኛ አመራር የሆኑት ዶ/ር ታደሰ ብሩ ኮምፒተራቸው ሲሰለል መቆየቱን የገለጸው ፕራይቬሲ ኢንተርናሽናል፣ በአንድ የብሃሬን የሰብአዊ መብት ተማጓች ኮምፒዩተር ላይም ተመሳሳይ የስለላ ሶፍት ዌር መገኘቱን ገልጿል።
ዶ/ር ታደሰ ብሩ ለፕራይቪሴ ኢንተርናሽናል ጠበቃ የምስክርነት ቃላቸውን መስጠታቸውን ተናግረዋል። ፕራይቪሲ ኢንተርናሽናል የስለላ ቫይረሱን የሸጠውን ጋማ ኢንተርናሽናልን የተባለውን ድርጅት ወደ ፍርድ ቤት ለመውሰድ ማቀዱን ዶ/ር ታደሰ ገልጸዋል፡



ልፋ ያለው በሕልሙ ዳውላ ይሸከማል! ጠርናፊና ተጠርናፊ

በፕሮፍ. መስፍን ወልደ ማርያም

ጥር 2006

ሰሞኑን እንደአዲስ ሆኖ የሚወራው ስለጥርነፋ ነው፤ ጥርነፋ ከዲያብሎስ ፋብሪካ የወጣ የክፋትና የጭቆና መሣሪያ ነው፤ ሰዎችን በመጨቆንና በማሰቃየት፣ ምቾትና እንቅልፍ በማሳጣት፣ ፍርሃትንና ስጋትን በማሰራጨት ሕዝብን ለጥ-ጸጥ አድርጎ ለመግዛት የሚፈልጉ ጠርናፊዎች፣ አምባ-ገነኖች፣ ጨቋኞች፣ አፋኞች፣ ዘራፊዎች፣ ወሮበሎች፣ ምድራዊም ሆነ ሰማያዊ ሕግ የማይገዛቸው፣ አምላካቸው አድርገው የሚያገለግሏቸው ሎሌዎችን በሆዳቸው ገዝተው የሚያሰልፉ ናቸው፤  እንኳን የገጠር ልጆችና አኛም የአዲስ አበባዎቹ መሰንከል ምን እንደሆነ እናውቃለን፤ እንስሳትን (በቅሎዎችንና አህዮችን፣ አንዳንዴ በገግና ፍየልም) የፊት እግር ከኋላ እግር ጋር በአጭር ገመድ እያሰሩ እንደልባቸው እንዳይንቀሳቀሱ ማድረግ ነው፤ ሀብት በመሆናቸው ቢጠፉ ባለቤቶቹ ይጎዳሉ፤ ስለዚህ በየአካባቢያቸው ያለውን እየጋጡ ችለው እንዲኖሩ ለማድረግ ቀላሉ ዘዴ መሰንከል ነው፡፡

ለሰውም ቢሆን ዓላማውም ዘዴውም አንድ ነው፤ ልዩነቱ የሰው ልጅ እንቅስቃሴው አካላዊ ብቻ ሳይሆን አእምሮም መንፈስም ስላለው መሰንከሉ አካላዊ ብቻ አይሆንም፤ እንዳያስብ አእምሮውን ማፈን ግዴታ ይሆናል፤ ለአምባ ገነኖች ችግር የሚመጣው የሰዎች አእምሮ ሲያስብ ነው፤ ያሰበውንም መናገርና መጻፍ ሲጀምር ነው፤ ‹‹መጥፎ ሀሰብ››፣ ማለትም ለጨቋኞቹ የማይበጅ ጥሩ ሀሳብ በንግግር፣ በጽሑፍ፣ በራድዮና በቴሌቪዥን ቢተላላፍና ብዙ ሰዎች ቢሰሙት አገር ይረበሻል፤ ሰው ሁሉ ሽብርተኛ ይሆናል፤ አገዛዙ ሕዝቡን ለመሰንከል ብዙ ዘዴዎች አሉት፤ በስም ማጥፋት እንዳልከሰስ ዘዴዎቹን አልናገርም፤ ነገር ግነ ክፉ እንቅልፍ ይዞት የሄደ ካልሆነ በቀር የማያውቃቸው የለም፤ የማያውቅ ካለ በየቤቱ እየመጡ ይተዋወቁታል፡፡

Thursday, January 30, 2014

ማንነት

በመስፍን ወልደ ማርያም

ኅዳር 21/2006

በ1996 ዓ.ም. የክህደት ቁልቁለት በሚል ጽሑፌ ውስጥ ‹‹ማንነት ምንድን ነው፤ በሚል ንዑስ ርእስ ስር ከገጽ 98 ጀምሮ በተቻለኝ መጠን አፍታትቻለሁ፤ የሪፖርተር ጋዜጠኛ ይህንን ለማንበብ ጊዜ አላገኘም፤ ወይም የተገለጠለት ዱሽ ቅንጫቢ በቅቶት ይሆናል፤ የምጠቅሰውም ለሱ ሳይሆን ለሌሎች ነው፡፡

በቅርቡ በፌስቡክ ላይ አንድ አውቀቱ ይሁን ጤንነቱ፣ ወይም ኪሱ የተቃወሰበት ሰው በትግርኛ ስለማንነት ጽፎ ነበር፤ ከዚህ በፊትም ጽፎ አስተሳሰቡ ሁሌም የተወላገደ በመሆኑ አልፌው ነበር፤ አሁን ደግሞ ሲጽፍና በአንዳንድ የሱ ቢጤዎች አበጀህ! አበጀህ! ሲባል ሳይ አደገኛነቱን ተገነዘብሁ፤ አንዱን ጎባጣ ሀሳብ ቶሎ ካላስተካከሉት ብዙ ጎባጦችን ያፈራል፤ የተጣራና ቀና የሆነ ሀሳብን ለመግለጽ በጣም ያስቸግራል፤ ማሰብ መጨነቅን፣ ማበጠርን፣ ማጣራትን ይጠይቃል፤ አፍ እንዳመጣ መልቀቅ ቀላል ነው፤ በተለይ የሚዳኝ ከሌለ!

በመጀመሪያ ሀሳብን ለመግለጽ የተመረጠው ቋንቋ ጠበብ ያለና የተፈለጉ አድናቂዎች ዘንድ ለመድረስ ብቻ ከተፈለገ ሀሳቡም እንደቋንቋው ለተወሰኑ ሰዎች የተመጠነ ይሆናል፤ በዚህ ዓይነት የቀረበው ቅንጣቢ ሀሳብ በሌላ ቋንቋ ሊተረጎም አይቻልም፤ ደንቆሮነትን ማጋለጥ ይሆናል፤ ለምሳሌ በትግርኛ ‹‹ኢትዮጵያዊ ዝበሃል መንነት የለን፤›› የሚለውን ‹‹ኢትዮጵያዊ የሚባል ማንነት የለም፤›› በማለት፣ በእንግሊዝኛ ደግሞ ‹‹There is no identity called Ethiopian.›› ተብሎ ሊተረጎም ነው፤ እንግዲህ ይህ አወቀች፤ አወቀች ሲሏት መጽሐፉን አጠበች እንደተባለችው ሴትዮ፣ ወይም ደግሞ አላዋቂ ሳሚ እንትን ይለቀልቃል! የሚባል ነው፤ ‹‹ኢትዮጵያዊ ዝበሃል መንነት የለን፤›› ብሎ በትግርኛ የጻፈው ሰው የአለማወቁ አዘቅት ዓለምን በሙሉ የሚያናጋ መሆኑን አልተገነዘበም፤ (አሜሪካን፣ እንግሊዝ፣ ፈረንሳይ፣ ኢጣልያን … የሚባል ማንነት የለም ሊለን ነው፤) የመንደር ማንነትን በሁለት እጆቹ ይዞ፣ አእምሮውን በመንደር ማንነት ጨቅጭቆ በየፓስፖርቱ ላይ የማንነት መግለጫ ተብሎ የተሰየመውንና በዓለም አቀፍ ደረጃ የታወቀውን ማንነት ካደው፡፡

ወያኔን ያሸበረው የግንቦት 7 መንገድ ምንድነው?

የትግራይን ሕዝብ ከብሄር ጭቆና ነጻ አወጣለሁ በሚል ጠባብ ዓላማ ተደራጅቶና ታጥቆ ለበትረ ሥልጣን የበቃው ህወሃት ወይም ሕዝባዊ ወያኔ ሃርነት ትግራይ ሥልጣን ከተቆጣጠረ 23 አመት ሊሞላው እነሆ ጥቂት ወራቶች ብቻ ቀርተውታል።

ለጋራ ቤታችን ለሆነቺው አገራችን ኢትዮጵያና በአስተዳደር በደል ለከፋ ድህነት ለተዳረገው መላው ሕዝቦቿ የሚሆን አንዳችም ራዕይ ሳይኖረው ለመንግሥትነት ሥልጣን የበቃው ይህ ቡድን ላለፉት 23 ዓመታት ከግል ኑሮአቸው አሻግረው የአገርንና የወገንን ጥቅም ማየት የማይችሉ ወይም የማይፈልጉትን በዙሪያው አሰባስቦ እያካሄደ ካለው ዘርፈ ብዙ የሃብት ምዝበራ ወንጀል በተጨማሪ እየፈጸመ ያለው የመብት ጥሰትና አፈና ተዘርዝሮ የሚያልቅ አይደለም።

ሰሞኑን እያፈተለኩ በመውጣት ላይ ከሚገኙ ምስጥራዊ የድምጽ መረጃዎች ለማረጋገጥ እንደተቻለው ደግሞ ለጥቂቶች የሃብትና የብልጽግና ምንጭ የሆነው ሥልጣን ከእጃቸው እንዳይወጣ በአንድ በኩል በምርጫ ስም እንዴት አድርገው ሕዝቡን ቀፍድደው የምርጫው ተሳታፊ ማድረግ እንደሚችሉ ሲዶልቱና በሌላ በኩል ደግሞ በቁጥጥራቸው ሥር የሌሉትንና ለሥልጣናቸው ያሰጉናል ያሉዋቸውን የደሃዉን ልጅ በማጋፈጥ እንዴት በጦርነት እንደሚጨፈልቁዋቸው ሲመክሩ ተሰምተዋል።

ከወያኔው ቁንጮ አንዱ የሆነው በረከት ስሞን በየደረጃው ላሉት የአገዛዙ ሹሞችና ካድሬዎች ባደረገው ገለፃ መሬትን የመንግሥት ባደረገው ኮሚኒስታዊ አዋጅ ምክንያት የመንግሥት ጭሰኛ ለመሆን የተፈረደበትን ሰፊውን አርሶ አደር “ተኛ ስንለው ይተኛል፤ ቁም ስንለው ይቆማል ፤ እንደፈለግን ብንበድለው እንኳ አያማርረንም ” እያለ ሲዘባበትበት ተደምጦአል ። በአንድ ለአምስት ኮሚንስታዊ አደረጃጀት ተጠርንፎ የወያኔ የንግድ ድርጅቶች ብቻ የሚያቀርቡትን ማዳበሪያና ምርጥ ዘር ያለውዴታው እንዲራገፍበትና ከአቅሙ በላይ ዕዳ እንዲቀፈቅፍ የተፈረደበት የኢትዮጵያ አርሶ አደር በዚህ አይነት ንቀት ደረጃ የሚዘባበትበትን መሪ ከወያኔው በረከት ስሞን በፊት ገጥሞት አያውቅም ። ለወደፊትም ሊያይ አይፈልግም ። ወያኔን ሥልጣን ላይ ለማምጣት የሰሜኑ ክፍለአገራችን አርሶ አደር የተጫወተው ሚና ተዘንግቶ በበረከት ስሞን እንዲህ መዋረዱ እጅግ ያሳዝናል። ለነገሩ ከፍተኛ የህይወት መስዋዕትነት ከፍሎ ለድል ያበቃው የትግራይ ሕዝብ ቁም ስቅሉን እያየ አይደል?

Tuesday, January 28, 2014

በረከት መርገምቱ

በቅዱስ ዩሃንስ

ሃገራችን ኢትዮጵያን ነገስታት መርተዋታል፤ ወታደራዊ አምባገነኖች ጨፍረዉባታል፤ ዛሬ ደግሞ ዘረኛ አምባገነኖች ቁም ስቅሏን እያሳዩዋት ነዉ። እቺን ለአስተዋይ መሪዎች ያልታደለች የአስተዋዮች አገር ዛሬ አለም የሚያዉቃት በድህነት፤ በረሀብና በስደት ነዉ። ድህነት፤ ረሀብና ኋላ ቀርነት ኢትዮጵያ ላይ የተደቀኑ ታላላቅ አደጋዎች ቢሆኑም ዛሬ አገራችን ኢትዮጵያን ከምንም ነገር በላይ የሚያስፈራት ድህነትና ረሀብ ሳይሆን በግድ የተጫነባት የጋንግሪኑ የወያኔ አገዛዝ ነዉ። ይህ የጥፋት ቡድን በወሮበላዎች የተመሰረተ፡ ሃገራችንን እያቆረቆዘ ያለ አገዛዝ መሆኑ በግልፅ በሃያ ሶስት አመት የስልጣን ጉዞው አስመስክሯል። ህወሃት ወያኔን ከመሰረቱ ወሮበላ የጥፋት አምባሳደሮች አንዱና ዋነኛው ደግሞ ቆሪጡ በረከት ስምኦን ነው።

በረከት ስምኦን የኢትዮጵያን ትልቅነት የሚያቀልሉና የኢትዮጵያን ህዝብ ማንነት የሚያሳንሱ አያሌ አጥንት የሚሰብሩ ንግግሮች ያደረገ እብሪተኛ ቱልቱላ ነዉ። በረከት እዉነትን ከዉሸት፤ ቁምነገርን ከቧልት አገርን ያክል ትልቅ ነገርና የቤቱን ጓዳ ለይቶ ማየት የማይችል እንኳን ለአገር ስልጣን ለዕቁብ ዳኝነትም የማይመኙት ከሃዲ መሆኑ ይታወቃል። ሆኖም እሱና የደደቢት ጓደኞቹ አዲስ አበባን ሲቆጣጠሩ የስልጣን መያዣ መለኪያዉ ብስለትና አስተዋይነት ሳይሆን ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያዊነትን መጥላትና ማጥላላት በመሆኑ በረከት ስምኦን ዛሬም ድረስ እንደጨበጠ የያዘዉን ስልጣን ለመያዝ ችሏል። ከሰሞኑ ስራ ፈቱ የዲያቢሎስ ቁራጭ በረከት ስምኦን ለአገዛዙን ወሮበላ ሚኒስትሮችና ከፍተኛ የወያኔ ቅጥረኛ አስፈፃሚዎች በተዘጋጀው የምርጫ ተብየ ውይይትና ግምገማ ላይ ባደረገዉ ንግግር የኢትዮጵያ አርሶ አደር እስካሁን በተደረገለት ስራ በሚገባ የረካ ስለሆነ ” መንግስት ሰላማዊ ሰልፍ ውጣ ቢለው ይወጣል፣ መንግስት ተኛ ቢለው ይተኛል፣ ግፍ ብንፈጽም አንኳን አርሶ አደሩ ይህንን መንግስት ይሸከመዋል እንጂ ምንም አይለውም፣ በማለት ሃያ አመት ሙሉ መሬቱን ተቀምቶ በተገፋዉ የኢትዮጵያ አርሶ አደር ላይ አላገጠ። ቃለመጠይቅ መስጠትና አለመስጠት የራሱ ጉዳይ ነዉ። ሆኖም ቃለመጠይቁ በከፍተኛ የችግር አረንቋ ተመትቶ እየማቀቀ የሚገኘውን የሃገሬን ገበሬ ወገኔ መወረፉ ህመም ስለሆነብኝ ማርከሻ ይሆነዋል በሚል የዚህን እብሪተኛ ሰዉ ቃለመጠይቅ በዚህ ጽሁፌ ለመዳሰስ እሞክራለሁ።  ለነገሩ ጉጅሌ ወያኔዎች ከአለቃቸው ከሟቹ ቱልቱላ መለስ ጀምሮ መላ  ግብርአበሮቻቸው ለአነጋገራቸው ደንታ የሌላቸው፤ የሚያስቡት እንደጤናማ ሰው በጭንቅላት ሣይሆን እንደ አውሬ በጡንቻ መሆኑን ነፃነትን ናፋቂው ድፍን የኢትዮጵያ ህዝብ ጠንቅቆ ያውቃል፡፡

ዛሬ በወሮበላው የወያኔ አገዛዝ ምክንያት የገበሬው ኑሮም መዝቀጡ እጅግ ያስለቅሳል፡፡ ገበሬው በቀን አንድ ጊዜም የሚቀምሰው በሌለበት ሁኔታ፣ ገበሬው ከገጠር እየፈለሰ ወደከተሞች በመግባት የጐዳና ተዳዳሪ እየሆነ ባለበት ሁኔታ፣ ገበሬው በማዳበሪያ ዕዳ የስንግ ተይዞ ኤሎሄ እያለ በሚገኝበት ሁኔታ፣ ገበሬው በአድሎኣዊ የመሬት ሥሪት ምክንያት መድሎ እየተሠራበት ማለፊያው የውሃ መሬት ለካድሬዎችና ለወያኔዎች እየተሰጠ ጭንጫውና መናኛው መሬት ግን ለድሃ ገበሬ እየተሸነሸነ ባለበት ሁኔታ፣ ገበሬው ከማሳውና ከመኖሪያው እየተፈናቀለ መሬቱ በልማት ስም ለወያኔ ከበርቴዎች እየተቃረጠ ባለበት ሁኔታ፣ ጨርቁ በላዩ ላይ አልቆ በባዶ እግሩ እየሄደ በእሾህና በእንቅፋት አሣሩን እንዲበላ ተፈርዶበት ባለበት ሁኔታ፣ … ይህ የሰው ነቀርሳ በረከት ተብየ የተናገረውን መስማት ከህመም በላይ ትልቅ ህመም ነው። ይህ የሰይጣን አምላኪ ወፍዘራሽ የመርገምት ልጅ በህዝብ መሳለቅና  ሃገርን ማውደም እንደሚያረካው በተደጋጋሚ አይተናል፡፡

Monday, January 27, 2014

መፍትሄው በአንድነት መነሳት ብቻ ነው!

ስለአገራችን ኢትዮጵያ ያልተዳፈ ያልተነገረ በህዝቦቹም ላይ ያልተፈጸመ በደልና ግፍ የለም እየተፈጸመም ነው፡፡ ወያኔዎች የኢትዩጵያን ህዝብ በአንድ ብረት /አጥር/ ውስጥ ተዘግቶበት እንደሚኖር አንበሳ አድርገውታል። ከነሱ ጩኸትና የውሸት ፕሮፓጋንዳ ሌላ እንዳይሰማና እንዳያይ አድርገው የውጭ ሚዲያዎችን ሁሉ በመዝጋት አደንቁረው ረግጠው እየገዙት ይገኛሉ፡፡  የእስከአሁኑም ግፍ ጭቆናና በደል አልበቃ ብሏቸው በነሱ አቀማመር ቀጣይዎቹንም አሰርት አመታት ከአንድ ብሄር በተውጣጣው በህውሃት ቅኝ ግዛት ስር የሚቆይበትን ሥልት እያመቻቹ ነው፡፡

እንደሚታወቀው ህወሃት/ኢሕአዴግ ግን የሚያስጨንቀውና የሚያራውጠው ወይም እንቅልፍ የሚነሳው የሃገርና የህዝብ ጉዳይ ሳይሆን የስልጣን ዘመኑን የሚያራዝምበትን ስትራቲጂዎችን መቀየስ በመሆኑ ለዚህም እኩይ አላማውን ለማሳካት ይረዳው ዘንድ በአሁኑ ወቅት የትኛውም የኢትዩጵያ ህዝብ ሳይወድ በግድ ህወሃት/ኢሕአዴግን እንዲደግፍና አባል ማድረግ እንደዋነኛ አማራጭ ወስዶ ህዝብን በመሰብሰብና በማስጨነቅ ላይ ይገኛል፡፡  በመሆኑም ካድሬዎቹን ከከተማ እስከ ገጠር መንደሮች በማሰማራት ህዝብን በሃይል በማስማፈራራትና በማሰር እንዲያውም በገንዘብ በማታለል በአባልነት እንዲፈርም እያደረገ ነው፡፡ አባል ያልሆነውን ሠራተኛውን ከሥራ በማባረር ገበሬውንም መሬቱን በመንጠቅ ህዝቡን ለረሃብና ለስደት እንዲጋለጥ አድርጐታል፡፡

23 ዓመት + አስደንጋጭ + አሳዛኝ = ወዴት እየሄድን ነው?

“የአዲስ አበባ ተማሪዎች ለከፍተኛ የስነ ምግባር ጉድለት ተጋልጠዋል”


  • ተማሪዎች ያለዕድሜያቸው ጫት፣ ሲጋራና ልቅ ወሲብ ይጀምራሉ
  • ሴት የቢሮ ሠራተኛ ሴቶች በወሲብ ንግድ ኑሮአቸውን ይደጉማሉ
  • ኢትዮጵያ ልጆችዋን እየከሰረች ነው
  • ትግራይ ጫት መቃም ክልክል ነው
  • “በስነምግባር የታነፁ ዜጐችን በማፍራት ረገድ አገሪቱ ፈታኝ ሁኔታ ላይ ናት”

በአዲስ አበባ ከአንደኛ ደረጃ እስከ ከፍተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የሚማሩ ተማሪዎች፤ ለከፍተኛ የስነ ምግባር ጉድለቶች እንደተጋለጡ ጥናቶች አመለከቱ፡፡ ሰሞኑን የአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ ከባለድርሻ አካላት ጋር “ስነምግባር ለእድገት ሁሉ መሠረት ነው” በሚል ርዕስ ባዘጋጀው የውይይት መድረክ ላይ በቀረቡት ጥናቶች በተለይ የሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎች፤ በየትምህርት ቤቶቹ አካባቢ ባሉ ህገወጥ የአልኮል፣ የአደንዛዥ እጽ መጠቀሚያ እና የወሲብ ፊልሞች ማሣያ ቤቶች መበራከት የተነሣ ለችግሩ ተጋላጭነታቸው በከፍተኛ ደረጃ መጨመሩ ተጠቁሟል፡፡ አብዛኞቹ ተማሪዎች ወሲብ መፈፀም የሚጀምሩት በዚሁ የትምህርት ደረጃ ላይ እያሉ ነው ተብሏል፡፡ ከጥናት አቅራቢዎቹ አንዷ የሆኑት ወ/ሮ ጽዮን አክሊሉ በጥናታቸው እንዳመለከቱት፤ ተማሪዎች ሲጋራ፣ የአልኮል መጠጥ፣ ጫት እና ልቅ ወሲብ የሚጀምሩት በአብዛኛው ሁለተኛ ደረጃ ከገቡ በኋላ ሲሆን 41.5 በመቶ የሚሆኑት የሁለተኛ ደረጃ ተማሪ እያሉ ሲጋራ ማጨስ እንደሚጀምሩ ጠቅሰው፤ 67.1 በመቶ ያህሉ ደግሞ በዚህ የትምህርት ደረጃ ወሲብ መፈፀም ይጀምራሉ ብለዋል፡፡

ህወሓት/ኢህአዴግ የትግራይ ህዝብ አማራጭ ሀሳብ እንዳያገኝ እያካሄደ ያለውን አፈና አጥብቀን እንቃወማለን!!!


ከአንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትሕ ፓርቲ (አንድነት) የተሰጠ መግለጫ

ፓርቲያችን አንድነት በአፅንኦት እንደሚያምነው የትግራይ ህዝብ እንደ ሌላው ኢትዮጵያዊ ሁሉ የዴሞክራሲ ዕጦት ሰለባ ነው፡፡ ስርዓቱ በየትኛውም የኢትዮጵያ ክልል እንደሚያደርገው በትግራይም ሰብዓዊ መብት ይረግጣል፣ ፍትህ ይደፈጥጣል፣ በካድሬዎች ይደበደባል፣ ይንገላታል፣ እንዲሰደድ ይደረጋል፡፡ ስርዓቱና በስርዓቱ ውስጥ የደላቸው ሹማምንት በስሙ ከመነገድ በዘለለ ዋጋ የተከፈለበትን ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ዘርግቶ ተጠቃሚ ማድረግ አልቻለም፡፡

ህወሓት/ኢህአደግ ክልሉን እንደዋና ካምፕ በማየት በአፈና ውስጥ እንዲኖር አድርጎታል፡፡ የትግራይ ህዝብ የነፃ ፕሬስ ውጤቶችን እንዳያገኝ፤ አማራጭ የፖለቲካ ፓርቲዎችን እንዳያዳምጥ የተፈረደበት ሕዝብ ነው ማለት ማጋነን አይደለም፡፡ ይሄ እውነትም ሕወሓት/ኢህአዴግ በተለያየ ጊዜ በህዝቡ ላይ በፈፀማቸው ኢ-ዴሞክራሲያዊና ኢ-ፍትሃዊ ድርጊቶች የታየ ነው፡፡

ለዚህ ማሳያ የሚሆነው አምባገነኑ ህወሓት/ኢህአዴግ አረና ባለፈው ሳምንት በትግራይ ክልል አዲግራት ከተማ ሊያደርግ የነበረው ሕዝባዊ ስብሰባ ልክ እንደ ከዚህ ቀደሙ ሁሉ ታፍኖበታል፣ አባላቱ ተደብድበዋል እንዲሁም ታስረዋል፡፡ ይሄ የሆነበት ምክንያት የትግራይ ህዝብ አማራጭ እንዳያገኝና በጉልበት የህወሓት አንጡራ ሀብት ብቻ ሁኖ እንዲያገለግል ከመፈለግ ነው፡፡ ከዚህ በፊትም ፓርቲያችን በመቀሌ ከተማ ሊያደርግ የነበረው የተቃውሞ ሰልፍ በከፍተኛ አፈናና እስር እንዲያስተጓጉል መደረጉ የቅርብ ግዜ ትዝታ ነው፡፡ አንድነት ፓርቲ የትግራይ ህዝብ አማራጭ ሓሳብ የማዳመጥ፣ የሚጠቅመውን የመምረጥና የመቃወም ሕገ-መንግስታዊ መብቱ የተጠበቀ መሆኑን በፅኑ ያምናል፡፡ ስለዚህ አማራጭ ሓሳብ በሚያቀርቡ ፓርቲዎች ላይ ህወሓት/ኢህአዴግ እየወሰደ ያለውን ኢ-ዴሞክራሲያዊ ርምጃና አፈና በጥብቅ እንቃወማለን፡፡

ሂውማን ራይትስ ዎች በኢትዮጵያ የፖለቲካ ምህዳሩ ይበልጥ ጠቧል አለ!

መንግስት፤ ተቋሙ የተቃዋሚዎች የፕሮፖጋንዳ ማስፈፀሚያ ነው

“በኢትዮጵያ የነፃ ሚዲያ ህልውና አደጋ ላይ ነው”
“በኤርትራ የመብት ጥያቄ ማንሳት ነውር ሆኗል” ብሏል

የኢትዮጵያ መንግስት የዜጐችን  ሰብአዊ መብት በስፋት ይጥሳል በማለት ተደጋጋሚ ወቀሳና ስሞታ የሚያቀርበው ሂውማን ራይትስ ዎች የተሰኘው አለማቀፍ የመብት ተቋም፤  ሰሞኑን ይፋ ባደረገው አመታዊ ሪፖርቱ፣ በኢትዮጵያ የፖለቲካ ነፃነት ይበልጥ መጥበቡንና የነጻ ሚዲያ ህልውና አደጋ ላይ መውደቁን ገለፀ፡፡

የኢትዮጵያ መንግስት በበኩሉ፤ የተቋሙን ሪፖርት ያጣጥላል፡፡ በአገሪቱ ውስጥ የፖለቲካ ነፃነትና የፖለቲካ እንቅስቃሴ የማካሄድ እድል (የፖለቲካ ምህዳር) እየጠበበ የመጣው ከምርጫ 97 በኋላ መሆኑን የገለፀው ሂውማን ራይትስ ዎች፤ ከዚያ ወዲህ በመንግስት የፀደቁትን የፀረ - ሽብር እና የበጐ አድራጐት ማህበራት አዋጆችን በምሳሌነት ጠቅሷል፡፡ በፀረ - ሽብር አዋጁ መነሻነት ፖለቲከኞችና ጋዜጠኞች ሽብርተኛ ተብለው እንደታሠሩና እንደተፈረደባቸው የተቋሙ ሪፖርት ጠቅሶ፣ በህጋዊና ሰላማዊ መንገድ የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች በፍርሃት እንዲሸበቡ ተደርገዋል ብሏል፡፡

ጋዜጠኞች የፀረ-ሽብር አዋጁን በመፍራት የሙያ ተግባራቸውን እንዳያከናውኑ መታፈናቸውን ሲገልጽም፤ የአዋጁ አንቀፅ እየተጠቀሰ እሥራት የተፈረደባቸው ጋዜጠኞች መኖራቸውንም አውስቷል፡፡

በኢትዮጵያ ጐልተው የሚታዩት የሰብአዊ መብት ጥሰቶች የፖለቲካ ምህዳር መጥበብና የኘሬሶች አፈና ቢሆኑም፤ ሌሎች የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችም መሻሻል አላሣዩም ብሏል ሪፖርቱ፡፡

Sunday, January 26, 2014

የወያኔ የውሸት ዘገባዎች ሲጋለጡ

“ኦክስፋም” በመልካም ሥራቸው ከታወቁ ትላልቅ ዓለም ዓቀፍ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች አንዱ ነው። በቅርቡ አንድ መቶ ሀያ አምስት አገሮችን ያካተተ ከምግብ አቅርቦትና አጠቃቀም ጋር የተያያዘ ጥናት ውጤት ይፋ አድርጓል። ጥናቱ አራት ዝርዝርና አንድ አጠቃላይ አመላካቾች አሉት።

1. አመላካች አንድ: የምግብ እጥረት

ይህ አመላካች “በየአገሮቹ ምን ያህል ለበላተኛው የሚበቃ ምግብ አለ?” የሚለውን ይለካል። በጥናቱ ውጤት መሠረት በምግብ እጥረት እጅግ የተጎዱ የመጨረሻዎቹ አስር አገሮች የሚከተሉት ናቸው: – ቡሩንዲ፣ የመን፣ ቻድ፣ ኢትዮጵያ፣ ማዳጋስካር፣ ናይጄሪያ፣ ላኦስ፣ ባንግላዴሽ፣ መካከለኛዉ አፍሪካ ሪፑብሊክ እና ህንድ። ኢትዮጵያ አገራችን ከመጨረሻ አራተኛ ናት።

2. አመላካች ሁለት: ለምግብ የመክፈል አቅም (Affordability)

ይህ አመላካች “የአገሩ ሕዝብ በአገሩ ዋጋ ምግብ ገዝቶ ለመብላት ምን ያህል አቅሙ ይፈቅድለታል?” የሚለውን የሚመልስ ነው። አሁንም ከመጨረሻ እንጀምር። አንጎላ፣ ዚምባቡዌ፣ ቻድ፣ ጉያና፣ ኢትዮጵያ፣ ናይጄሪያ፣ ኮንጎ፣ ኬንያ፣ ጋምቢያ እና ኢራን የየአገሩ ሕዝብ ምግብ መሸመት የሚቸገሩባቸው አገሮች ናቸው። አገራችን ኢትዮጵያ ከመጨረሻ አምስተኛ ናት።

3. አመላካች ሶስት: የምግብ ጥራት

ይህ የምግብ ይዘትንና የአያያዝ ንጽህናን የሚመለከት ሲሆን ኢትዮጵያ፣ ማዳጋስካር፣ሞዛምቢክ፣ ቻድ፣ ቶጎ፣ ዛምቢያ፣ ማሊ፣ ናይጄሪያ፣ ባንግላዴሽ፣ ሌሶቶ ከመጨረሻው እስከ አስረኛ ደረጃ ይዘዋል። ኢትዮጵያ በምግብ ጥራት የመጨረሻዋ አገር ናት።

Saturday, January 25, 2014

የሃይምኖት ቀበኛው ወያኔን በጋራ እንታገል!

በቅዱስ ዮሃንስ 

ወያኔ ሥልጣን ላይ ከወጣበት ጊዜ ጀምሮ በአሰቦት ገዳም መነኮሳትና በአካባቢው ሕዝበ ክርስቲያን ላይ የደረሰው አሰቃቂ ጭፍጨፋና እንዲሁም በአርባምንጭ ከተማ የኦርቶዶክስና የፕሮቴስታንት አማኞችን በማጋጨት የፈሰሰው ደም ፣ በጂማና በኢሊባቦር በስልጤና በጋሙጎፋ ክርስቲያኖችና አብያተክርስቲያናት ላይ የደረሰው ዘግናኝ ጭፍጨፋ በዓይን ላየው ሁሉ መፈጠሩን የሚጠላበት ክስተት ነው::

በዚሁ በጅማ ባለፈው ዓምት አካባቢ ከ40 በላይ የፕሮተስታንት ቤተክርስቲያኖች እና ንብረቶች ወድመዋል:: በአጠቃላይ ይህ መንግሥት ሙስሊሙ ከኦርቶዶክሱ ኦርቶዶክሱ ከፕሮቴስታንቱ ተፋቅሮና ተቻችሎ እንዳይኖር አንዱን በአንዱን ላይ እያነሳሳ የሃይማኖት አቋማት ሲቃጠሉ ዳር ቆሞ እሳት መሞቅ የሚፈልግ መንግሥት ነው::

የሃይማኖት ተቋማት አልጋጭ ሲሉትም እርስ በእርሳቸው ማለትም ኦርቶዶክሱን ከኦርቶዶክስ ፣ ፕሮቴስታንቱን ከፕሮቴስታንቱ ፣ ሙስሊሙን ከሙስሊሙ እያተራመሰ የሃይማኖት ተቋማት ሰላም እንዳያገኙ እያደረገ ይገኛል:: ከዚህም አልፎ ተርፎ ከ1500 ዘመን በላይ ተከብሮ የቆየውን የዋልድባን ገዳም እያፈረሰ በውስጡ የሚኖሩ መነኮሳትንም እያሳደደ ይገኛል:: በዚህ ገዳም ብዙ አባቶች ከዓለማዊ ፍላጎትና ከእህል ተቆጥበው ቅጠላቅጠልና ፍራፍሬ ብቻ እየተመገቡ ቤት ሳይኖራቸው በዋሻና በዛፍ ሥር ተጠልለው ሰለ አገር ብቻ ሳይሆን ስለ መላው ዓለም የሚጸልዩ አባቶች ያሉበት ገዳም ነው:: በከተማ የደሀ ጎጆ እያፈረሰ በገዳም የአባቶችን ዋሻ እያረሰ መነኮሳቱን እያሳደደ በእጁ የገቡትን አስሮ እያሰቃየና እየገደለ ይገኛል:: ገዳማትንም ያለ ቅርስ ትውልዱን ያለውርስ እያስቀረ ነው::

ሰማያዊ ፓርቲ በኢትዮ-ሱዳን ድንበር ላይ በጎንደር ሰላማዊ ሰልፍ ሊያደርግ ነው


በመስከረም አያሌው

ሰማያዊ ፓርቲ መንግስት በኢትዮ-ሱዳን ድንበር ላይ ለህዝቡ ግልፅ የሆነ መረጃ እንዲሰጥ ግፊት ለማድረግ በጎንደር ከተማ ሰላማዊ ሰልፍ ለማካሄድ የማሳወቂያ ደብዳቤ ለጎንደር ከተማ ማዘጋጃ ቤት ማስገባቱን ገለፀ።

የፓርቲው የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ብርሃኑ ተ/ያሬድ ትላንት ለሰንደቅ ጋዜጣ እንደገለፁት ሰላማዊ ሰልፉ የሚደረገው ሱዳን ትሪቡዩንን ጨምሮ የተለያዩ የመገናኛ ብዙሃን የኢትዮጵያ መንግስት ለህዝቡ ግልፅ ባልሆነ፣ በታሪክም ሆነ በባህል ከህዝቡ ጋር ባልተገናኛ መልኩ ታሪካዊ የሆኑ ቦታዎችን ጭምር ለሱዳን አሳልፎ ለመስጠት መስማማቱን እየዘገቡ በመሆኑ መንግስት ግልጽ የሆነ መረጃ እንዲሰጥ ግፊት ለማድረግ ነው።

“እነሱ የሚሉት መልሶ መከለል (Re demarcation) ነው። እኛ ደግሞ ከዚህ በፊት የተከለለ ነገር የለም። አሁን ሲከለል 40 ኪ.ሜ ወደ ውስጥ የኢትዮጵያ ግዛት ይነካል። ግዛቱን መንካት ብቻም ሳይሆን፣ የኢትዮጵያን ታሪካዊ እና ከህዝቡ ጋር የተቆራኙ ቋራን የመሳሰሉ ግዛቶችን ወደ ሱዳን እንደሚከለሉ የኛ መረጃ ያመለክታል እያልን ነው” ያሉት አቶ ብርሃኑ፣ ይህን ጉዳይ መንግስት ግልጽ እንዲያደርግ በማሰብ በተለያዩ ክልሎች ሰላማዊ ሰልፍ ለማድረግ ማሰባቸውን ገልጸዋል።

ፓርቲው የመጀመሪያውን ሰላማዊ ሰልፍ የፊታችን ጥር 15 ቀን 2006 ዓ.ም በጎንደር መስቀል አደባባይ ለማድረግ ያቀደ ሲሆን፣ በሰልፉ ላይም የተለያዩ ጥያቄዎች ይነሳሉ። የመጀመሪያውም መንግስት ጉዳዩን ለህዝብ ግልፅ አድርጎ ከህዝቡ ጋር ውይይት እንዲያደርግ ሲሆን፣ ሁለተኛው ደግሞ የኢትዮጵያ ታሪካዊ ግዛቶች ከጫካ ውል ተነስቶ ያለምንም ታሪካዊ መሰረት ለሌላ ሀገር መስጠቱን ፓርቲው እንደሚቃወመው መግለፅ መሆኑን አቶ ብርሃኑ ገልፀዋል።

ለስርኣቱ ቅርበት አላቸው ያሉ ምንጮች ወያኔ ወገቡ እንደተሰበረ እየተናገሩ ነው::

በምንሊክ ሳልሳዊ

ወያኔ እየመራው የሚገኘው ኢኮኖሚ ተሽመድምዶ ሃገርን ረመጥ ላይ እየከተታት ሲሆን የወያኔ ሳቦታጅ ጥቂት ሰዎች በሃገር ሀብት በህዝብ ላይ እንዲፈነጩ አድርጓቸዋል::በሃገሪቱ ማንኛውም አይነት የኢኮኖሚ እንቅስቃሴዎች ከበፊቱ በተለየ እና በባሰ ሁኔታ ተንኮታኩተው አፈር መልበሳቸው በይፋ ታውቋል::ለስርኣቱ ቅርበት አላቸው ያሉ ምንጮች ወያኔ ወገቡ እንደተሰበረ እየተናገሩ ነው::በፖለቲካው ረገድ የስርኣቱ ገዢ ፓርቲዎች እርስ በርስ አለመተማመን ደረጃ ላይ ከመድረሳቸውም በላይ አመራሮቹ አድፍጠው አንዱን አንዱን እየጠበቀ በፍራቻ አለም ውስጥ እየዋተቱ ይገኛሉ::አቤት የሚባልበት እየጠፋ ነው፡፡ የውሳኔ ሰጪ ያለህ ቢባል መልስ አይገኝም፡፡ ፋይሎች የሚያያቸውና የሚያነባቸው አጥተዋል፡፡ መልካም አስተዳደር ገደል ገብቷል::በአላማ ሳይሆን በጊዜያዊ የመኖር ሂደት ላይ የተመሰረተው የካድሬዎቹ ሩጫ ድካምን በመፍጠሩ ሁሉም በያለበት ቆም ብሎ እያሰበ ሲሆን አሳቡም የገፈፍኩትን ገፍፌ ሃገርን ድባቅ መትቼ ልሽሽ ሆኗል::

ገበናን ገበና ይገፈዋል እንደሚባለው የወያኔ ጁንታ በተጭበረበረ ፖለቲካ ላይ የገነባው ኢኮኖሚያዊ ገበና በገበና ተጋልጧል:: የማይሰማ ነገር የለም እና እኛም ሰማን አነበብን አየንም እነሆ ታዝበን ዝም አላልንም ገበናዎቹ ገበናውን ሲገልቡት አብረን አልሳቅንም ሀገር ነውና ገበናዎቹን ተመርኩዘን የምንለውን ልንል ይኸው ተከሰትን::

Wednesday, January 22, 2014

አንድነት ለጠ/ሚ/ሩና ለአማራ ክልል ፕሬዚዴንት የኢትዮ-ሱዳን ድንበር ጉዳይን አስመልክቶ የፃፈው የማብራሪያ ጥያቄ መልስ ባለማግኘቱ እነሆ ዛሬ ደግሞ ወደ ፓርላመው ዞሯል፡፡


አንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትሕ ፓርቲ (አንድነት)

UNITY FOR DEMOCRACY AND JUSTICE PARTY (UDJ)

ቁጥር አንድነት /811/2ዐዐ6
ቀን 11/ዐ5/2ዐዐ6 ዓም

ለተከበሩ አቶ አባዱላ ገመዳ
ለኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ
የሕዝብ ተወካዮች ም/ቤት አፈ-ጉባኤ
አዲስ አበባ

ጉዳዩ፡- በኢትዮጵያና ሱዳን ድንበር አካባቢ ያለውን የወሰን ጉዳይ ለሕዝብ ግልጽ ስለማድረግ

አንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትሕ ፓርቲ (አንድነት) በአገራችን ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት እንዲሰፍን በሠላማዊ መንገድ ከሚንቀሳቀሱ ፓርቲዎች አንዱ መሆኑ ይታወቃል፡፡ በዚሁ መሠረት በአገራችን የሚካሄዱ ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊና ፖለቲካዊ ጉዳዮችን በቅርብ ይከታተላል፡፡ በዚሁ ክትትል መሠረት በአሁኑ ወቅት ከተከሰቱ አብይ አገራዊ ጉዳዮች አንዱ የኢትዮጵያ ሱዳን ድምበር ይገኝበታል፡፡ ጉዳዩ ለሕዝቡ ግልጽ ያልሆነ አብይ የአገር ጉዳይ በመሆኑና ኃላፊነት ካለበት መንግሥት በማይጠበቅ መልኩ ሂደቱ ከሕዝብ ተሰውሮ በአገር ውስጥ ካለ የግልና የውጭ ሚዲያዎች እንድንሰማ ተገደናል፡፡

የወያኔ ነፍስ በበረከት ስምዖን በኩል ስትቃዥ

ነፃነት ዘለቀ (አዲስ አበባ)

አንደኛው መስከረም ጠብቶ ሌላኛው መስከረም እስኪጠባ ድረስ ባሉት የ365.25 ቀናት ውስጥ ስንት ጉድ መስማት እንዳለብን የሚጠቁም አሃዛዊ መረጃ ሊኖር እንደማይችል መቼም ግልጥ ነው፤ ነገር ግን የዘመናችን ኢትዮጵያ የታሪክ ጎርፍ ያመጣብን ከወያኔና መሰሎቹ በስተቀር ሌሎቻችን ያልጠበቅነው ዱብዕዳ ክስተት ምሥጋና ይንሳውና በዬቀኑ የማንሰማውና የማናየው ዕንቆቅልሽ እንዳይኖረን ሆነናል፡፡ በዚህ መልክ በተለይ ባለፉት 22.8 ዓመታት ውስጥ የታዘብነው የታሪክ ምፀትና ወኔያዊ የውሸት ስንክሳር በረጂሙ ታሪካችን ታይቶም ሆነ ተሰምቶ እንደማያውቅ ማንም ጤናማ ኅሊና ያለው ዜጋ የሚመሰክረው ይመስለኛል፡፡ ለዛሬ አንዱን የወያኔ ነጭ ውሸት እንመለከታለን፡፡

በነገራችን ላይ ወያኔና እውነት ዐይንና ናጫ መሆናቸውን የማይረዳ ወገን እንደማይኖር እገምታለሁ፡፡ የወያኔን ተፈጥሮ ወያኔ ራሱን ጨምሮ ሁሉም ያውቃል፤ የወያኔ እውነት፣ የእውነት ግልባጭ የሆነችው ሀሰት ናት፡፡ ለወያኔ ውሸት ማለት እውነት ናት፡፡ ለወያኔ እንደእውነት የሚመርና የሚያቅር ነገር የለም፡፡ በተቃራኒው ደግሞ ለወያኔ እንደሀሰት የሚጣፍጥ ምንም ነገር የለም፡፡ ወያኔና እውነት በሂሳባዊ አገላለጽ ‘asymptote’ ናቸው – መቼም ሊገናኙ የማይችሉ ተጻራሪ ኑባሬያት በመሆናቸው፡፡ ወያኔ የሀሰት የህግ ባል ነው፤ የሚለያዩት ወይም የሚፋቱት ከሁለት አንድኛቸው ወይም ሁለቱም ሲሞቱ ብቻ ነው፡፡ ሀሰት ግን እስከዓለም ፍጻሜ ስለምትኖር ወያኔ ካልጠፋ ከውሸታምነቱና ከሀገር አጥፊነቱ ተፈጥሯዊ ባሕርይው ሊፋታ አይቻለውም፡፡ ታሪክ ግን ሥራውን የማይረሣ ቆፍጣና ገበሬ በመሆኑ ጊዜውን ጠብቆ እነዚህን ጉግማንጉጎች ወደማይቀረው መቃብራቸው እንደሚሰዳቸው የታመነ ነውና መፍረስ የጀመረው የበሰበሰ ሥርዓታቸው ከነሰንኮፉ ተገርስሶ ሀገራችን በቅርቡ ነጻ እንደምትወጣ በሙሉ ልብ አምናለሁ፡፡ በዚህች መንደርደሪያ ወደሰሞነኛው የበረከት ስምዖን ውሽከታ እንለፍ፡፡

“የኢትዮጵያ አርሶ አደር እስካሁን በተደረገለት ሥራ በሚገባ የረካ ስለሆነ ‹መንግሥት ሰልፍ ውጣ ቢለው ይወጣል፤ መንግሥት ተኛ ቢለው ይተኛል፤ ግፍ ብንፈጽም እንኳን አርሶ አደሩ ይህንን መንግሥት ይሸከመዋል እንጂ ምንም አይለውም፡፡”

Tuesday, January 21, 2014

ለአፅቢ-ወንበርታ የህዝብ ዓመፅ ተጠያቂ ህወሓት ነው!

በኣብርሃ ደስታ

በአፅቢ ወንበርታ ወረዳ የህዝብ ዓመፅ መቀስቀሱ ይታወቃል። ለዓመፁ መቀስቀስ ተጠያቂው ህወሓት ነው። ምክንያቱም ህዝባዊ ዓመፁ የተቀሰቀሰው ገዢውን ፓርቲ ህወሓት መንግስታዊ ሐላፊነቱ ስላልተወጣ ነው። ምክንያቱም የአፅቢ ወንበርታ ወረዳ አርሶአደሮች ያመፁበት ምክንያት በመንግስት ለተወሰደባቸው መሬት መንግስት ተገቢውን ካሣ መክፈል ባለመቻሉ ነው። መንግስት ተገቢውን ካሣ አለመክፈሉ የመንግስት ችግር ነው። ስለዚህ ዓመፁ የተቀሰቀሰው በመንግስት ጉድለት እስከሆነ ድረስ ለዓመፁ ተጠያቂ በህወሓት/ኢህአዴግ የሚመራው መንግስት ነው።

ዜጎች አስፈላጊውን ካሳ ሳይከፈላቸው ከቀያቸው ማፈናቀል ሕገ ወጥ ነው። መንግስት ለሁለት ዓስርት ዓመታት ለአርሶአደሮች ካሳ ሳይከፍል መቆየቱ ለህዝቡ ያለው ንቀት የሚያሳይ ነው። ህዝብ ለተወሰደበት መሬት ይሁን ሌላ ንብረት ካሳ የመጠየቅ ሙሉ መብት አለው። የአፅቢ ወንበርታ ህዝብም ለተወሰደበት መሬት ካሳ የመጠየቅ ሕገመንግስታዊ መብት አለው። ህዝቡ ካሳ ጠየቀ፤ መብቱ ጠየቀ። ስለዚህ የአፅቢ ወንበርታ ህዝብ ዓመፅ የመብት ጥያቄ ነው።

መንግስት ለቀረበለት የህዝብ ጥያቄ ተገቢውን መልስ ከመስጠት ይልቅ የሃይል እርምጃ ወሰደ። መንግስት ሐላፊነቱን ባለመወጣቱ ምክንያት የመብት ጥያቄው ወደ ዓመፅ ተሸጋገረ። መንግስት በአግባቡ ካሳ የመክፈል ግዴታው፣ ፍትሕ የማስፈን ሐላፊነቱ፣ ህዝቦችን በእኩልነት የማገልገል ተልእኮው ቢወጣ ኑሮ ዓመፁ አይቀሰቀስም ነበር። ስለዚህ ለዓመፁ መቀስቀስ ገዢው ፓርቲ ህወሓት ሐላፊነት ወስዶ ህዝቡን ይቅርታ መጠየቅ አለበት።

የ 2014 የዓለም የሰብአዊ መብቶች ሁኔታ ሪፖርት፡- ኢትዮጵያ

ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ እ.ኤ.አ በነሀሴ ወር 2012 ዓ.ም. መሞታቸውን ተከትሎ በኢትዮጵያ የተተካው አዲሱ አመራር ሰብዓዊ መብቶችን የሚመለከቱ ማሻሻያዎች እንደሚያደርግ ተጥሎ የነበረው ተስፋ ተዳፍኗል፤ በ2013 ዓ.ም ተጨባጭ የሆነ የፖሊሲ ለውጥ አልታየም፡፡ ይልቁንም የኢትዮጵያ ባለስልጣናት ሃሳብን የመግለጽ፣ የመደራጀት እና በሰላም የመሰብሰብ ነጻነት ላይ የጣሉትን ጥብቅ ገደብ ማስፈጸማቸውን የቀጠሉበት ሲሆን የሲቪል ማህበራትን እና ነጻ መገናኛ ብዙሃንን እንቅስቃሴ ለማዳከም አፋኝ ሕጎችን ይጠቀማሉ፤ግለሰቦችንም ፖለቲካዊ መነሾ ያላቸውን ክሶች በመመስረት የጥቃት ዒላማ ያደርጋሉ።

መንግስት በሃይማኖታዊ ጉዳዮቻቸው ላይ ጣልቃ መግባቱን የተቃወሙ ሙስሊሞች ዓመቱን ሙሉ በጸጥታ ሃይሎች የዘፈቀደ እስር፣ እገታ፣ ድብደባ እና ሌሎች ተገቢ ያልሆኑ አያያዞች ተፈፅሞባቸዋል፡፡ በሐምሌ ወር 2012 ዓ.ም. የታሰሩት 29ኙ የተቃውሞው መሪዎች የፍርድ ሂደት ከጥር ወር 2013 ጀምሮ ለህዝብ፣ ለመገናኛ ብዙሃን፣ እና ለቤተሰብ አባላት ዝግ ተደርጓል፡፡ እጅግ አወዛጋቢና መሠረታዊ ግድፈት ያለባቸውን ድንጋጌዎች በያዘው  የሃገሪቱ የጸረ ሽብርተኝነት ህግ መሰረት ጥፋተኛ የተባሉ የተቃዋሚ መሪዎች እንዲሁም አራት ጋዜጠኞች አሁንም በእስር ላይ ይገኛሉ፡፡

ከሃገር ውስጥ በሚገኝ ገቢ እና ከውጭ በሚመጣ እርዳታ በሚደገፉ ስፋት ያላቸው የልማት ፕሮግራሞች አፈጻጸም ምክንያት  የአንዳንድ ማህበረሰብ ተወላጅ ነዋሪዎች ያለበቂ ምክክር ወይም ምንም አይነት ካሳ ሳይከፈላቸው ከመኖርያቸው እንዲፈናቀሉ ይደረጋል፡፡ የጸጥታ ሃይሎች ነዋሪዎችን ከመኖሪያ ቀያቸው አንስተው ወደ ሌላ ቦታ ለማስፈር ሃይል፣ ማስፈራሪያ እና ዛቻ ይፈጸማሉ፤ ለምሳሌ በታችኛው የኦሞ ሸለቆ የሚገኙ ተወላጅ ነዋሪዎች ለዘመናት የኖሩበት መሬት መንግስት ለሚያካሂደው የስኳር መስኖ ልማት ይፈለጋል በሚል መፈናቀላቸው እንደቀጠለ ነው።

በሰላም የመሰብሰብ ነጻነት
ከ2012 ዓ.ም. ጀምሮ ከሀገሪቱ አጠቃላይ ህዝብ ቢያንስ 30 በመቶ የሚሆነውን ቁጥር የሚይዙት የኢትዮጵያ ሙስሊም ማህበረሰብ አባላት ተከታታይ ህዝባዊ ተቃውሞ አድርገዋል፡፡ የተቃውሞው መነሻ ምክንያት መንግስት በእስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት ውስጥ እና በአዲስ አበባ በሚገኘው የአወሊያ መስጊድ ላይ ይፈጽማል የተባለውን ጣልቃ ገብነት በመቃወም ነው፡፡

Sunday, January 19, 2014

ከመንግስትና ከህግ የበላይ ማነው?

ይህ ትዝብት እንጂ ጥያቄ አይደለም!

በዶ/ር በድሉ ዋቅጅራ

አንዳንድ አንባቢ የመጣጥፌን ርእስ ሲመለከት ጥያቄ ሊመስለው ይችላል፡፡ እኔ ግን አልጠየቅኩም፡፡ መላሽ በሌለበት ለራስ የቀረበ ጥያቄ ትዝብት እንጂ ጥያቄ አይደለም፡፡ የሰለቸው ጠያቂ ታዛቢ ይሆናል ብዬ ታዛቢ ሆኛለሁ፡፡ የትዝብት ዋናው ጥቅም መልስ አለማስናፈቁ ነው፡፡ ከዚህ ዋና ጥቅም የበለጠው ሌላው ዋናው ጥቅም ደግሞ ለህሊና ቁንጥጫ እንጂ ለታጣቂ እርግጫ አሳልፎ አለመስጠቱ ነው፡፡… እና እታዘባለሁ፤ መታዘብ ደልቶኛል፡፡

በጥንቃቄ ነው የምታዘበው፡፡ ከስሜታዊነት የራቀ ትዝብት ቆሽት አያሳርርምና ትዝብቴ ከስሜቴ እንዳይቀየጥ አብዝቼ እጥራለሁ፡፡ እናም መንግስታችንን ባቆመው ሳይሆን በጣሰው ህግ ታዘብኩት፡፡ እውነቴን ነው! መንግስት ህገ-መንግስት አርቅቆና በህዝብ አጸድቆ ሀገር ያስተዳድራል፡፡ በአብዛኛው ግን ህግ የሚጥሰው መንግስት ሆኖ በታየኝ ጊዜ ታዘብኩት፡፡ እዚህ ላይ መንግስት ማለት በየደረጃው የሾማችው ሙያተኞችና ባለስልጣናት ናቸው፡፡ ደግሞ ህግ ቆሞላቸዋል፤ እንዲጠብቁትና እንዲመሩበት፡፡ ብዙዎቹ ግን እኛ መንጋዎቹ የምናከብረውን ህግ፣ ከመጤፍ አይቆጥሩትም፡፡

መገናኛ ላይ አንድ ትራፊክ ፖሊስ ቀኑን ሙሉ ወደ ሲኤምሲ የሚሄድ ሚኒባስ ታክሲ እያስቆመ (አሳቻ ቦታ ተደብቆ) ትርፍ የጫኑትን በወረቀትና በጉቦ ሲቀጣ ውሎ፣ ማታ እራሱ በሞላ ታክሲ ላይ በትርፍነት ተሳፍሮ (ያውም በነፃ) ወደ ቤቱ ይሄዳል፡፡… ትራፊክ በሀሰት ቢከስና ቢያስቀጣ ምስክር አይጠየቅም፡፡ እንግዲህ መንግስትን እንደሰው ብናየው … ትራፊኩ የጣት ያህል ነው፡፡ ግን ቢሆንም ጣትነቱ ህግን የመሻር ‹መብት› ከመጎናፀፍ አላገደውም፡፡ … አንድ ትራፊክ ከፈለገ የተጨናነቀ የመሰለውን መንገድ ዘግቶ፣ ቤታችን መግቢያ ሊያሳጣን፣ ዙሪያ ገባ ሲያሽከረክረን ሊውል ይችላል፡፡ ስድብና ማመናጨቁንማ እዚያው ስልጠናው ላይ የሚማሩት ይመስለኛል፡፡ ህግ ያስከብረው ዘንድ ትራፊክን መንገድ ላይ አቆመ፡፡ መከበርን ያገኘው ግን ህጉ ሳይሆን ትራፊኩ ነው፡፡ አብዛኞቹ ህግ አስከባሪዎቻችን በህግ መከበርን አግኝተው ይኖራሉ፡፡ ግን ይህን በአንድ ሹመኛ ግለሰብ/ህግ አስከባሪ ላይ የሚታይ ከህግ ወጥቶ ህግን መብለጥ ኢህአዴግ አያውቅም? እርግጠኛ ነኝ ያውቃል! ታዲያ ስለምን ሉጋም አያበጁለትም? ብዬ ልጠይቅ አስብና ትውት አድርጌ፣ ‹‹አሁን ይሄ ህዝብ ገና ደጁ ላይ በትራፊክና በህግ አስከባሪ የጀመረው የህግ ጥሰት፣ ቀኑን ሙሉ በየመስሪያቤቱ ባለስልጣን ሲከመርበት አንጎሉ እየዞረ፣ በየመንገዱ ዳር በተዘጋጀለት ጉድጓድ እየተደነጎረ ጎረምሳው/ኮረዳይቱ ቢሰበሩ፣ ሽማግሌው/አሮጊቱ ቢሞቱ፣ ወይም ደግሞ፣ የመንዳት ፈቃድ እንጂ ችሎታ በሌለው ሰው በሚነዳ መኪና ቢዳጥ አያሳዝንም! በማለት ሀሳቤን የነፍስ ሙግት፣ ትዝብት አደርገዋለሁ፡፡ ለምን ቢሉ መልስ ያጣ ጠያቂ ታዛቢ ይሆናል፡፡

በሃይማኖት ጭቆና ስም የሚረጩ አደገኛ መርዞች!

በፋሲል የኔያለም

( የግል አስተያየት)

አራተኛውን የኢቲቪ “ጥናታዊ ፊልም” አየሁት፤ ዝቅ ሲል ለምርጫ ቅስቀሳ፣ ከፍ ሲል ደግሞ ከፋፍሎ ለመግዛት ተብሎ የተዘጋጀ ይመስለኛል። ፊልሙ ኢህአዴግንና የቀድሞ ስርዓቶችን ያነጻጽራል፤ ማንም ነፍስ ያለው ሰው ኢትዮጵያ ውስጥ የሃይማኖት ጭቆና አልነበረም ብሎ አይክድም፤ ልዩነቱ የሚጀመረው “ጨቋኙ ማን ነው? ተጨቋኙስ?” የሚለውን ለመመለስ ሲሞከር ነው። በእኔ እይታ ጨቋኞቹ የኦርቶዶክስ እና የኦርቶዶክስ እምነት ተከታይ መንግስታት ብቻ እንደነበሩ ተደርጎ የሚቀርበው አስተያየት ስህተት ነው፣ ተጨቋኞቹ ከኦርቶዶክስ ውጭ ያሉ ሃይማኖቶች ብቻ እንደነበሩ ተደርጎ የሚቀርበውም አስተያየት በታሪክ ያልተደገፈ፣ የስህተት ትምህርት ነው ። ታሪካችን እንደሚነግረን ከ66ቱ አብዮት በፊት፣ ሁሉም ስልጣን የያዙ ሃይሎች ስልጣናቸውን ለማቆየት ወይም ግዛታቸውን ለማደራጀት እነሱ የሚደግፉትን ሃይማኖት በሌላው ላይ ለመጫን ሙከራ አድርገዋል። የአጼ ሃይለስላሴ መንግስት የመጀመሪያውን የጽሁፍ ህገመንግስት ስላረቀቀና በህገመንግስቱ ላይ “ ኦርቶዶክስ ሃይማኖት” የመንግስት ሃይማኖት መሆኑን በይፋ ስላወጀ ዛሬ እንደ ትልቅ ግኝት ተጋኖ ይቀርባል እንጅ፣ ከዚያ በፊት የነበሩት ገዢዎች ኦርቶዶክስን ብቻ ሳይሆን፣ካቶሊክንና እስልምናን የመንግስት ሃይማኖት ለማድረግ ሞክረዋል። ክርስትናን በይፋ ከተቀበለው ከመጀመሪያው ንጉስ ኢዛና ጀምሮ እስከ አክሱም ስርወ-መንግስት ውድቀት ድረስ ኦሮቶዶክስ ሃይማኖት የመንግስት ድጋፍ ነበራት፤ ዮዲት መጣችና ስርዓቱን ለማፍረስ ሞከረች። ቀደም ብሎ ክርስትናን የማያውቁት አገዎች፣ ክርስትናን ከአክሱሞች ስለተቀበሉ፣ ኦርቶዶክስ ሃይማኖት ያለምንም ችግር የመንግስት ሃይማኖት ሆኖ ቀጠለ። ይኩኖ አምላክ ከዛግዌዎች ስልጣኑን ከቀማበት እስከ ግራኝ አህመድ ዘመቻ ድረስ ኦሮቶዶክስ አሁንም የመንግስት ሃይማኖት ሆና ቆይታለች። ይሁን እንጅ ኦርቶዶክሳዊ የሆኑት ነገስታት ከኦሮቶዶክስ ውጭ ያሉ ሃይማኖቶችን ብቻ ሳይሆን የኦርቶዶክስ ሃይማኖት ተከታዮች ሆነው፣ የአስተምህሮ ልዩነት የነበራቸውን ሳይቀር፣ ሃይማኖታቸውን በነጻነት እንዳያስፋፉ ያግዱ ነበር። የደቂቀ እስጢፋኖሳውያን ታሪክ ለዚህ ጥሩ ምሳሌ ነው። ደቂቀ እስጢፋኖሳውያን እስከመጨረሻው ኦርቶዶክሶች ነበሩ፣ከሙስሊሙ ወይም ከቤተ-እስራኤላውያን ባላነሰ መልኩ ወከባ ደርሶባቸዋል።

Saturday, January 18, 2014

ዛሬ የሚያስፈሯሯችሁን እስከ ዘላለሙ የማትሰሙበት ግዜ ይመጣልና አትፍሩ!

ህወሃት የሚያራምደው የዘረኝነት ፖለቲካና፤ የተዘፈቀበት የሙስና አዘቀት ሊወጣ ከማይችልበት አዙሪት ውስት ከተውታል።ከእንግዲህ ወዲህ ለህወሃቶች የቀራቸው አንድ አማራጭ ብቻ ነው። ሁሉንም ዜጎች በዘረኝነት ሰንሰለት አስሮ ቀጥቅጦ እና አፍኖ መግዛት ቀጣዩ ቅዥታቸው ነው።

የዚህ አፍኖ የመግዛት ቅዥታቸው መገለጫም ዜጎች ህወሃት ስለሚፈፅመው ወንጀል ምንም ዓይነት መረጃ እንዳያገኙ ማድረግ አንዱ ነው።ህወሃት የሚፈፅመው ወንጀል ከህዝብ ዓይንና ጆሮ ተሠውሮ እንዲረሳ ይመኛል። ይሄን ምኞቱን እውን ለማድረግም ሌሎች ነፃ ሚዲያዎችን አሸባሪ ማለት ወይም ደግሞ ሌላ የተሰወረ አጀንዳ ያላቸው እያለ ማላዘንን ሥራየ ብሎ ተያይዘውታል። ከሰሞኑ አዲስ አበባ ውስጥ የሚታተሙ ስምንት የግል ህትመቶችን አሸባሪዎች በማለት ክስ መስርተዋል። አስቀድመው ፈርደው ከጨረሱ በኋላ ክስ መመሥረት የህወሃቶች የተለመደ የፍትህ ሥርዓት ነው። በአገሪቷ ታሪክ ውስጥ ለመጀመሪያ ግዜ ከመንግስት ቁጥጥር ውጪ ሁኖ የተቋቋመውን ኢሳትንም አሸባሪ እያሉ ሰሚ አልባ ጩኸት እየጮኹ ነው። የኢሳት ቴሌቭዥንና ሬዲዮንን የሚሰማም በአሸባሪነት ይከሰሳል እያሉ በየዜጎች ደጅ እየተንከላወሱ ለማስፈራራት እየሞከሩ ነው።

እኛ ግን እንዲህ እንላለን !!! አትፍሩ ! አትፍሩ ! አትፍሩ ! ኢሳትን ሰምታችኋል ብሎ የሚያስፈራሯችሁን ለዘላለሙ የማትሰሟቸው ግዜ እየመጣ ነው። የነፃነት ጎህ ቀዶ ሁላችን የፈለግነውን ሰምተን፤ ያልፈለግነውንም የምንተውበት ዘመን እሩቅ አይደለም። ግንቦት ሰባት የፍትህ የነፃነት እና የእኩልነት ንቅናቄም የተቋቋመው ዜጎች ያለማንም ጣልቃ ገብነት የወደዱትን ወስደው፤ የጠሉትን መተው የሚችሉበትን መንገድ ለማመቻቸት ነው። ዘረኞቹ በደምና አጥንት ታውረው ጭካኔን ከጀግንነት ቀላቅለው እኛ ብቻ ወንድ ባሉበት መንደር ሌላ ጀግና ኢትዮጵያዊ ወንድ ገስግሶ የሚመጣበት ዕለት እየደረሰ ነውና እንዳትፈሩ እንመክራችኋለን። ህወሃቶች ዜጎችን ከሰው በታች አድርገው ለመግዛት እንዲመኙ ያደረጋቸው እብሪት የሚተነፍስበት ዘመን እሩቅ አይሆንምና አሁንም አትፍሩ።

ህወሃቶች ከእነርሱ ቁጥጥር ውጪ ያሉ ነፃ ሚዲያዎችን እንደማይታገሱ የታወቀ ነው። ለምን ቢሉ የወንጀላቸው ብዛት፤ የክፋታቸው ጥልቀት ሳይነገር ተሠውሮ እንዲቀር ስለሚመኙ ነው። ይህን ምኞታቸውን እውን ለማድረግም ራሳቸው የሠረቱን ህግ ውልቅልቁን አውጥተው ያፈራርሱታል። ዜጎች መረጃ የማግኘት መብት አላቸው ተብሎ እነርሱ “ህገ-መንግስታችን” እያሉ በሚጠሩት ላይ በማያሻማ ሁኔታ የተቀመጠ ቢሆንም እነርሱ ግን ለራሳቸው ህግ መታመንን አልመረጡም። እንዲያውም እነርሱ ሞተንለታል የሚሉትን ህግ አፈር አስገብተው ራሳቸው ህግ ሆነው ተፈጥረዋል። እነርሱ ህግ ሁነው በመፈጠራቸውም በየዜጎች ደጅ እየተንከላወሱ ኢሳትን ብትሰሙ ወዮላችሁ እያሉ ያስፈራራሉ። ዜጎች ግን የሞኝ ዘፈናቸውን መልሰው መልሰው ለሚያላዝኑ ኢሕአዴጋዊያን ዛቻ የሚንበረከኩ አይሆኑም። አገራቸውን በተመለከተ ማንኛውንም መረጃ ለመስማት ያላቸውን ነፃነትም ለምናምንቴዎች አሳልፈው የሚሰጡ አይሆኑም።

“የግንቦት 20 ፍሬን የምንለካው ኢህአዴግ በሰላማዊ መንገድ ከሥልጣን ሲወርድ ነው”


ጭቆና ትግልን ያጠነክራል እንጂ አይገድልም...
ኢህአዴግን በምርጫ ለማሸነፍ የአንድ ወር ሥራ በቂ ነው….
ኢህአዴግ ሁልጊዜ የትግራይ ህዝብ በስጋት እንዲኖር ነው የሚፈልገው

 በቅርቡ ለፓርቲዎች የውህደት ጥያቄ አቅርባችኋል፡፡ ለየትኞቹ ፓርቲዎች ነው ጥያቄውን ያቀረባችሁት? መስፈርታችሁስ ምን ነበር? እኛ እንግዲህ ያሰብነው በመድረክ ውስጥ ካሉት ፓርቲዎች ጋር ውህደት ለመፈፀም ነው፡፡ ግን ከመድረክ ውጪም ቢመጣ ችግር የለብንም፡፡ እንግዲህ በጠየቅናቸው ፓርቲዎች ሙሉ ፈቃደኝነት በቅርቡ ከግንባር ወደ ውህደት እንሄዳለን የሚል እምነት ነው ያለኝ። ጥያቄውን ለኦፌኮ፣ ለአንድነት እና ለደቡብ ህብረቶች አቅርበናል፡፡ እነሱም በጐ ምላሽ እየሰጡን ነው፡፡ ውህደት የተጠየቁት ፓርቲዎች የመድረክ አባል ከሆኑ ለምን ራሱን መድረክን አልጠየቃችሁም? ፓርቲዎቹን በተናጠል መጠየቅ ለምን አስፈለገ? ሁለት አቅጣጫ ነው ያለው፡፡ እንዳልከው በቀጥታ መድረክንም መጠየቅ ይቻል ነበር፤ ግን በተናጠል የመጠየቁን መንገድ ነው የመረጥነው፡፡ ይሄን ጥያቄ ያነሳሁት “አረና በመድረክ ላይ እምነት የለውም” የሚሉ አስተያየቶች ስለሚሰነዘሩ ነው… በተናጠል መጠየቁን በመድረክ ህልውና ካለማመን የመጣ ነው የሚሉ ወገኖችም አሉ… እኛ እኮ ሁሉንም ነው የጠየቅነው፡፡ ነጥለን የተውነው ፓርቲ ቢኖር ሊያስብል ይችላል፡፡ ግን የጠየቅናቸው በአጠቃላይ በመድረክ ውስጥ ያሉትን ነው:- አረና፣ ኦፌኮ፣ አንድነት እና የደቡብ ህብረት፡፡ አረና ተነሳሽነቱን ወስዶ ነው የእንዋሃድ ጥያቄውን ያቀረበው፡፡

ስለዚህ መድረኩን አይፈልጉትም የሚያስብል ሁኔታ አይፈጥርም፡፡ ይሄኛውን መንገድ መምረጣችን ብዙም ችግር አለው ብዬ አላስብም፡፡ ለውህደቱ ጥያቄ መነሻችሁ ምንድን ነው? እንዴትስ ይሄኛውን ጊዜ መረጣችሁ? ምናልባት ምርጫውን አስባችሁ ይሆን? እኛ የተቋቋምነው በክልላዊ ፓርቲነት ነበር፡፡ ህወኃት ቅድሚያ ለትግሬነት ስለሚሰጥ ነው እኛም በክልላዊ ፓርቲነት የተቋቋምነው፡፡ በቀላሉ ተቀባይነትን ለማግኘት በመሻት ነው እንጂ የአረና የመጀመሪያ አላማው ሀገራዊ እሳቤን ያዘለ ነው፡፡ ክልላዊነታችን የአጀማመር ጉዳይ ነው እንጂ ለዘለቄታው ያነገብነው አላማ ሀገራዊነትን ነው፡፡ ከሌሎች ፓርቲዎች ጋር ውህደት መፍጠራችንም ሀገራዊ አላማ አንግበው የሚታገሉ ፓርቲዎች፣ በትግራይ ህዝብ በቀላሉ ተሰሚነት እንዲያገኙም አጋዥ ይሆናል የሚል እምነት አለኝ፡፡ ለዚህች ሀገር ሁነኛ መፍትሄ የሚሆነው ትግራይ ለብቻው፣ ኦሮሞው ለብቻው፣ አማራው ለብቻው፣ ሌላውም ለብቻው ሊታገል ሳይሆን ሁሉም በአንድነት ተዋህዶ ተስማምቶ ሲታገል ነው፡፡

ፓትርያርኩ: የቤተ ክርስቲያኒቷ የመዋቅር ለውጥ ሕግ ረቂቅ ‹‹የእኔ ጩኸት ነው›› አሉ

  • አደረጃጀትና አሠራር ለውጥ የሚሰማው የካህናቱና ምእመናኑ ጩኸት በርክቷል
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በአስተዳደራዊ መዋቅሯ ትክክለኛውን መሥመር ይዛ ወደ ቀደመ የቅድስናና ንጽሕና ክብሯ እንድትመለስ በአደረጃጀትዋና አሠራሯ ላይ እየተካሔደ የሚገኘው የተቋማዊ ለውጥ ጥናት፣ ‹‹ከጅምሩም የእኔ ጩኸት ነው፤ የእኔ አጀንዳ ነው፤ ዛሬ ከደረሰበትም ወደ ኋላ አይመለስም፤›› ሲሉ ፓትርያርክ አቡነ ማትያስ ቃል ገቡ፡፡

ፓትርያርኩ ይህን የተናገሩት፣ የአዲስ አበባ ሀ/ስብከት የአደረጃጀትና አሠራር ለውጥ ጥናት ሳይዘገይ ተግባራዊ እንዲኾን ጥያቄ ያቀረቡ የገዳማትና አድባራት አስተዳዳሪዎችን፣ የጽ/ቤት ሠራተኞችን፣ ካህናትን፣ መምህራንና ምእመናንን ጥር 2ና 5 ቀን 2006 ዓ.ም. በጽ/ቤታቸውና በመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት አዳራሽ ተቀብለው ባነጋገሩበት ወቅት ነው፡፡

ከሌሎች አህጉረ ስብከት በተለየ ኹኔታ የበርካታ ገዳማትና አድባራት፣ የብዙ ንዋያተ ቅድሳትና ቅርሶች፣ የሰው ኃይልና ፋይናንስ ሀብቶች የሚገኝበት የዐዲስ አበባ ሀ/ስብከት÷ በአስተዳደር መዋቅሩ፣ በሒሳብ አሠራርና ቁጥጥሩ መሠረታዊውን ክህነታዊና የስብከተ ወንጌል ተልእኮ በሚደግፍ አኳኋን ሥር ነቀል ለውጥ እንዲካሔድበት በባለሞያዎች የቀረበውና በተለያዩ ዙሮች የተወያዩበት የአደረጃጀትና አሠራር ለውጥ ጥናት የቤተ ክርስቲያኒቱን ብሩህ የልማትና የመልካም አስተዳደር ትንሣኤ ያሳያቸው መኾኑን ካህናቱና ምእመናኑ በከፍተኛ ስሜት ገልጸዋል፡፡

ካህናቱና ምእመናኑ፣ የአደረጃጀትና አሠራር ለውጥ ጥናቱ የቅ/ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ በሰጠው የአፈጻጸም አቅጣጫ መሠረት በውይይቱ በተሰበሰቡት አስተያየቶችና ትችቶች ታርሞና ተስተካክሎ በቋሚ ሲኖዶሱ በአስቸኳይ እንዲጸድቅ፣ በተሳካና በተሟላ መንገድ ተግባራዊ ለማድረግና ዘለቄታዊነቱም ለማረጋገጥ ይቻል ዘንድም ከአስተዳደር ሠራተኞች፣ ከካህናት፣ ከሰንበት ት/ቤቶችና ከምእመናን የተውጣጣ የተቋማዊ ለውጥ አስፈጻሚ አካል እንዲቋቋም ጠይቀዋል፡፡

Friday, January 17, 2014

የወያኔን የሚዲያ አፈና ማመከን የጊዜው አጣዳፊ ተግባር ነው

ዘረኛዉ የወያኔ አገዛዝ የአገራችንን በትረ ሥልጣን ከተቆጣጠረበት ጊዜ ጀምሮ ህዝባችን ስለራሱና ሰለአገሩ ምንም አይነት መረጃ ከአማራጭ የመገናኛ ብዙሃን ምንጮች እንዳያገኝ ያሉትን ዕድሎች በሙሉ ድርግም አድርጎ ዘግቶ ኖሮአል።

የወያኔ መሪዎችና ተሿሚዎች በየግላቸው ምንም ቁብ በማይሰጡትና ተቃዋሚዎች እንዲያከብሩት ነጋ ጠባ በሚወተውቱት የአገሪቱ ህገመንግሥት አንቀጽ 29 ዕውቅና ካገኙ የዜግች መብቶች አንዱ ሃሳብን በነጻነት የመግለጽ ተፈጥሮአዊ መብት ሆኖ ሳለ እየተካሄደ ያለውን የሥልጣን ብልግናና አገሪቱን እያራቆተ ያለውን ዘረፋ በመተቸታቸው ብቻ በአንድ ወቅት እንደ አሸን ፈልተው የነበሩ የነጻ ጋዜጣ አዘጋጆችና አሳታሚዎች በሽብርተኝነት ተወንጅለው ከፊሉ ከአገር እንዲሸሽ ሌላው አፉን ዘግቶ እንዲቀመጥ አለያም የፈጠራ ክስ እየተመሰረተባቸው እስር ቤት እንዲማቅቁ ተደርገዋል። አሁንም በመደረግ ላይ ናቸው። በወያኔ ሃሳብን በነጻነት የመግለጽና የዜጎች መረጃ የማግኘት መብት አፈና የአሜሪካና የጀርመን መንግሥታት በየግላቸው የሚያስተዳድሩዋቸው የአሜሪካና የጀርመን ድምጽ ሬዲዮኖች እንኳ ከጥቃቱ ማምለጥ ስላልቻሉ እነሆ እስከዛሬ ያልተቋረጠ የማጥላላት ዘመቻ ይካሄድባቸዋል።

ዜጎች ሃሳባቸውን በነጻነት መግለጽ ከቻሉና ከየትኛውም መዲያ መረጃ የማግኘት መብታቸው ከተረጋገጠ ሥልጣን ላይ ውሎ እንደማያድር ጠንቅቆ የተረዳው የወያኔ አገዛዝ በዚህ የሚዲያ አፈና ተግባሩ በመቀጠል ከሰሞኑ የኢትዮጵያ ሳታላይት ቴለቪዥንና ሬዲዮን እንዲሁም ህዝብ አልፎ አልፎ ሃሳቡን ለመግለጽ በሚገለገልባቸው ጥቂት የአገር ውስጥ ህትመቶች ላይ የተለመደውን የጥቃት ጅራፉን ለማሳረፍ ታጥቆ ተነስቶአል። ባለፈው ሳምንት መጨረሻ ላይ በመረጃና ደህንነት መሥሪያ ቤቱ ተዘጋጅቶ የህወሃት ቀድሞ ታጋዳላዮች በሚቆጣጠሩትና እንደግል ንብረታቸው በሚፈነጩባቸው የኢትዮጵያ ቴሌቪዥንና ሬዲዮ የተሰራጨው ዘገባ እንደሚያመለክተው ከአሁን ቦኋላ ማንኛዉም የመንግስት ባለስልጣን፤ የገዢዉ ፓርቲ አባላትና የተቃዋሚ ፓርቲ መሪዎች ምንም አይነት ቃለመጠይቅ ለኢትዮጵያ ሳተላይት ቴለቪዥንና ሬዲዮ እንዳይሰጡ ማስጠንቀቂያ ተሰጥቶአል። ማስጠንቀቂያውን ተላልፎ በተገኘ ማንም ሰው ወይም ድርጅት ላይ የአሸባሪነት ወንጀል ክስ እንደሚመሰረትበትም ዛቻና ማስፈራሪያ በተለመደው የቃላት ጋጋታ ተገልጾአል።

ግራና ቀኝ ጠፋን!

መስፍን ወልደ ማርያም

ታኅሣሥ 2006

በአለፉት ሃያ ዓመታት ውስጥ ወያኔ-ኢሕአዴግ የሚወቀስበት ሥራ በጣም ቢያመዝንም የሚመሰገንበት ሥራ የጽሑፍ ቁጥጥርን ማስቀረቱ ብቻ ነው፤ ሁልጊዜም አንድ ጥሩ ነገር የሚያስከትለው አብዛኛውን ጊዜ የማይጠበቅ ነገር ሊኖር ይችላል፤ ለምሳሌ አጠቃላይ ነጻነት ሲመጣ ወንጀለኛነት ይጨምራል፤ እንዲሁም የጽሑፍ ቁጥጥር ሲነሣ ጸሐፊዎች ይበዛሉ፤ ትምህርት በተስፋፈበትና ማንም እንደፈለገ ለመጻፍና ለማሳተም ችሎታውም ዕድሉም በማይገኝበት፣ ሳያበጥርና ሳይሰልቅ አሰር-ገሰሩን ጽፎ በአደባባይ የሚወጣውን ጥምብ-እርኩሱን አውጥተው ሁለተኛ እንዳይለምደው የሚያደርጉ የታወቁና የሰላ አእምሮና ብዕር ያላቸው አርታእያንና ሐያስያን (ገምጋሚዎች) ባሉበት ብዕሩን የሚያባልግ ጸሐፊ አይወጣም፤ ይህ ሁሉ ባልተሟላበት እንደኛ ባለ አገር ውስጥ ብዕርን ማባለግ እንደመብት ወይም እንደነጻነት እየታየ ነው፡፡

በአደባባይ የሚጽፉ ሰዎች ሁለት ነገሮችን ለይተው መገንዘብና ለሌሎችም ሲየያስተላልፉ ለይተው ማስተላለፍ አለባቸው፤ አንዱ የሆነና የተረጋገጠ ሁነት ነው፤ይህንን ሳይበርዙና ሳይከልሱ እንዳለና እንደተገኘ ማስተላለፍ ግዴታ ነው፤ ሁለተኛው የራስ አስተያየት ነው፤ የጠራውንና የነጣውን አውነት ከጎደፈ የግል አስተያየት ጋር አጋብቶ ማቅረብ ወይ አለማወቅ ነው፤ አውቀው ከሆነም ለማታለል ከመሞከር የሚቆጠር ነው፤ በአለንበት ዘመን አብዛኛውን ጊዜ የምናየው ፊደሎቹን ማወቅ እንደሙሉ እውቀት ይቆጠራል፤ ወይም በሌላ አነጋገር ፊደልን ማወቅ የመጻፍ ችሎታን ይሆናል፤ ይህ ትልቅ ስሕተት ነው፤ ፊደሎችን ማወቅ ትልቅና መሠረታዊ የእውቀት ጎዳና ላይ መግባት ነው፤ ጎዳናው ግን በጣም ረጅም ነው፤ በእውቀት ጎዳና ላይ መግባት የእውቀት ባለቤት ከመሆን ጋር እንዳይደባለቅ በጣም መጠንቀቅ ያስፈልጋል፤ በአገራችን ፊደልን ማወቅ ሌላም አደጋ አለው፤ ፊደልን ማወቅ ከሥልጣን ጋር ሲጋባ የሚያስከትለውን ውድቀት ከአንዴም ሁለቴ አይተናል፤ እያየንም ነው፤ ስለዚህም ፊደል ኃላፊነትን ያመጣል፤ አለዚያ በአለፉት ሠላሳ ዓመታት ያየነው ውድቀት እየተከበረ ይቀጥላል፡፡

Thursday, January 16, 2014

አንድነት በኢትዮ-ሱዳን ድንበር ማካለል ዙሪያ ሕዝባዊ ውይይት ሊያደርግ ነው

ከያሬድ አማረ/ ፍኖተ ነፃነት ጋዜጣ

አንድነት ፓርቲ ጥር 18/2006ዓ.ም በኢትዮ ሱዳን ድንበር ማካለል ዙሪያ ከህዝብ ጋር ውይይት እንደሚያካሂድ አስታወቀ።

አንድነት ለዲሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ በኢትዮ ሱዳን የድንበር ማካለል በሚል በሁለቱ መንግስታት ብቻ በሚስጥር በተያዘው መርሀ ግብር ዙሪያ ከህዝብ ጋር ውይይት እንደሚያደርግ ተገልጧል፡፡

ፓርቲው በመጪው ጥር 18ቀን 2006ዓ.ም የሚያካሂደው ህዝባዊ ውይይት በኢትዮጵያ በመንግስትና በሱዳን መንግስት መካከል ይፋ ባልሆነው የድንበር ማካለሉ ሂደት ግልፅነት የጎደለው የድንበር ማካለል በሚል ሽፋን ሊደረግ የታሰበና በአካቢው የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ዜጎችን ለሰቀቀን የዳረገ ከመሆኑም ባሻገር በጉዳዩ አሳሳቢነት ዙሪያ መወያየት አስፈላጊ በመሆኑ ፓርቲው ከህዝብ ጋር ተወያይቶ ግልፅ አቋሙን የሚያሰቀምጥበት በመሆኑ የኢትዮጵያ ጉዳይ ያገባኛል የሚል ሁሉ በውይይቱ ላይ በመገኘት ሃሳቡን እንዲገልፅ አንድነት ጥሪውን አቅርቧል፡፡

በሌላ ዜና አንድነት ፓርቲ ለአማራ ክልል እና ለጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ የኢትዮ ሱዳን ድንበር ማካለል ጉዳይ በአጭር ግዜ ውስጥ ለህዝብ ግልፅ እንዲሆን በደብዳቤ አሳሰበ።

አንድነት ለአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳደርና ለጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ በኢትዮ ሱዳን የድንበር ማካለል ዙሪያ ግልፅ የሆነ ማብራሪያ በአጭር ግዜ ውስጥ ለህዝብ እንዲሰጥ በደብዳቤ ጠይቋል።

የአንድነት ህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ሀብታሙ አያሌው ለፍኖተ ነፃነት እንደገለፁት ኢህአዴግ በሉአላዊ ግዛት ማስከበር ጉዳይ የግዴለሽ አመለካከት ያለው በመሆኑ ብሔራዊ ጥቅማችንን ሊጎዳ የሚችል እርምጃ ሲወስድ በመቆየቱና የተለማመድው በመሆኑ አሁንም በተለመደው ግብሩ ለህዝብ ግልፅ ባልሆነ ሁኔታ ሊካሄድ የታቀደው የድንበር ማካለል የኢትዮጵያን ጥቅም ባላስጠበቀ መንገድ ሊፈፀም እንደሚችል ፓርቲው ከፍተኛ ስጋት ስላደረበት ጉዳዩን በቅርበት እየተከታተለና በሚስጥር የያዘው የአማራ ክልል ርእሰ መስተዳደርም ሆነ ጠቅላይ ሚንስትሩ ስለ ድንበር ማካለሉ አጠቃላይ ዝርዝር ሁኔታ ለህዝቡ በአጭር ግዜ ውስጥ ግልፅ የሆነ ማብራሪያ እንዲሰጥ በደብዳቤ መጠየቃቸውን ገልፀዋል፡፡

Tuesday, January 14, 2014

በጅምላ ገድሎ በጅምላ መቅበር ወያኔ ተወልዶ ያደገበት ሙያዉ ነዉ!

በወያኔ ዘርኝነት፤ ጎጠኝነትና ወደር የለሽ ጭቆና ከሁለት አስርተ አመታት በላይ ጀርባዉ የጎበጠዉ የኢትዮጵያ ህዝብ ባለፉት ሁለት ወራት ዉስጥ በሁለት እጅግ አስቀያሚና ዘግናኝ በሆኑ የታሪክ ምዕራፎች ዉስጥ አልፏል። ለወትሮዉ በወርሃ ህዳርና ታህሳስ፤ ህዳር ሚካኤልንና የገና በዐልን እያከበረ አጆቹን ወደ ፈጣሪዉ የሚዘረጋዉ የኢትዮጵያ ህዝብ፤ ዘንድሮ ከእነዚህ ሁለት የቆዩ ባህሎቹና ወጎቹ ፈቀቅ ብሎ በሁለት ክብሩን ባዋረዱና ማንነቱን ጥያቄ ዉስጥ በከተቱ ከስተቶች ልቡ ቆስሎ ከራሱ ጋር ሲነታረክ ሰንብቷል። የፈጠረዉን አምላክ መለምን እንጂ በፈጣሪዉ አማርሮ የማያዉቀዉ የኢትዮጵያ ህዝብ . . . የሚያስብልኝ መንግስት እንደለሌለኝ አዉቃለሁ፤ አምላኬ ግን በፍጹም አይረሳኝም። ምነዉ ቅዱስ ሚካኤል አንተና ሰይፍህ እያላችሁ እንዴት እንዲህ ይደረጋል አንዴ . . . እያለ በምድራዊዉም በሰማያዊዉም መንግስታት ላይ የመረረ ጩኸቱን አሰምቷል።

በህዳር 2006 ዓም የኢትዮጵያ ህዝብ አገራቸዉ ዉስጥ የስራ ዕድል ተነፍገዉ ስራ ፍለጋ ወደ ሳዑዲ የተሰደዱ ወገኖቹ በሳዑዲ ፖሊስና ህዝብ ከፍተኛ በደል ሲፈጸምባቸዉ ተመልክቶ በኃዘንና በቁጭት ልቡ በግኗል። በተለይ ወንዶች ልጆቹ ፈለጊ እንደሌለዉ እንስሳ በየአደባባዩ ሲረገጡና ሲደበደቡ፤ ሴቶች ልጆቹ ደግሞ በየማጀቱ ሲደፈሩ ተመልክቶ ለህዝብና ለአገር ለሚያስቡ አስተዋይና ጨዋ መሪዎች ባለመታደሉ በባዕድ አገር ዉስጥ በደረሰበት ዉርደትና መከራ በአለም አቀፍ ደረጃ ጩኸቱን አሰምቷል።በዚሁ በ2006 ዓም በታህሳሰ ወር አጋማሽ ላይ ደግሞ የኢትዮጵያ ህዝብ በተለይ ብርድ ልብስ ተጠቅልሎ የተጣለ የሰዉ ልጅ አጽም ቀርቶ በስመአብ ተብሎ የታረደ በሬ ስጋም ማየት በማይፈልግበት በገና ፆም ወቅት የገዛ ወገኖቹ አጽም በመንገድ ቆፋሪዎች ከመሬት ዉስጥ እየተጎተተ ሲወጣ አይቶ በቆሰለ ልብና በነደደ አንደበት “እባክህ ፈጠሪ ወይ ዉረድ ወይ ፍረድ” እያለ ከወያኔ ጋር ከመኖር የፈጣሪን ፍርዱን አለዚያም ዳግም ምጽአቱን ተመኝቷል።

ባለፉት ሁለት ወራት ሳዑዲ አረቢያ ዉስጥ በሚገኙ ኢትዮጵያዉያን ወገኖቻችን ላይ የደረሰዉ ግፍና መከራ ድፍን ህዳርንና ታህሳስን በአለም ዙሪያ በአራቱም ማዕዘን የሚኖሩ ኢትዮጵያዉያንን ያሰባሰበ፤ ያነጋገረ፤ ያበሳጨ፤ ያስቆጨና አንጀት ያሳረረ ጉዳይ ነበር። አዎ የ2006 ህዳርና ታህሳስ አገር ዉስጥም ካገር ዉጭም ለምን መጡ የሚያሰኙ የቀን ጎደሎዎች ነበሩ። የወገኖቹ በባዕድ አገር አላግባብ መታሰር፤መደብደብና መገደል ያበሳጨዉ የኢትዮጵያ ህዝብ ከዚህ ሀዘኑና ብስጭቱ ሳይላቀቅ ነበር ባለፈዉ ታህሳስ 18ትና 19 ቀን ሌላ አሳዛኝና አስደንጋጭ ዜና የጭንቅና የመከራ ጓዳ የሆነችዉን መዲናችን ከአዲስ አበባን አንደ ሐምሌ ጨለማ የከበባት። ደርግን አሸንፈዉ ስልጣን ሲይዙ ደርግ ገድሎ የቀበረዉን አስከሬን መቃብር እየቆፈሩ ያወጡት የወያኔ መሪዎች እነሱም በተራቸዉ በጅምላ ገድለዉ በብርድ ልብስ እየጠቀለሉ የቀበሯቸዉን ኢትዮጵያዉያን አስከሬን ዬት እንደቀበሩት እንኳን ሰለማያዉቁ እነሱ እራሳቸዉ እየቆፈሩ አዉጥተዉ ወንድሞቹና እህቶቹ እንደወጡ የቀሩበትን የኢትዮጵያን ህዝብ አንጀት እንደገና አቁስለዋል።

Monday, January 13, 2014

የህወሓት መፈክር፡ ‘የአማራ የበላይነት ይውደም!’

በአብርሃ ደስታ

ግርማይ ገብሩ የቀድሞ የህወሓት ታጋይና የአሁን የቪኦኤ (VOA) ዘጋቢና ደራሲ ነው። ዓላማዬ ስለ ግርማይ ገብሩ ለመፃፍ አይደለም፤ ግርማይ በፌስቡክ ገፁ ስላሰፈረው መረጃ ለመዋስ እንጂ። መረጃው ከዚህ በፊትም አውቀው ነበር። ግን ለማስረጃ ያህል ግርማይን ልጥቀስ: ምክንያቱም ግርማይ የህወሓት ታጋይ ነበርና።

ግርማይ በ1969 ዓም የህወሓት (ተሓህት) ሦስቱ መፈክሮች ሲጠቅስ የመጀመርያውና ዋነኛው አድርጎ የፃፈው “አፄነት፣ መስፍንነትና የአማራ የበላይነት ይወድማሉ” ይላል።
በትግርኛ “ካብ ጭርሖታት ህወሓት 1969 ዓም: ሃፀይነት፣ መስፍንነትን ናይ አምሓራ ዕብለላን ዓነውቲ እዮም!” ይላል። ግርማይ ገብሩ አልተሳሳተም። ከህወሓቶች ጋር የማልስማማበት ግን ነጥብ አለኝ።

እርግጥ ነው። እኔም አፄነትና መስፍንነትን እንደ ስርዓት አልቀበልም። ምክንያቱም አፄነትና መስፍንነት (እንደ ስርዓት) ላሁኗ ኢትዮጵያ አይመጥኑም። የአፄነትና መስፍንነት ስርዓት በኢትዮጵያ ታሪክ እዚ ግባ የሚባል ለውጥ አላመጣም። ስለዚህ እኛ የሚያስፈልገን ዘመናዊ (ከዘመኑ ንቃተ ህሊናችን ጋር አብሮ የሚሄድ) የህዝብ አስተዳደር (ዴሞክራሲ) እንጂ ንጉስነት (የሰው ገዢነት) አይደለም። የምንፈልገው የሕግ የበላይነት እንጂ የንጉስ የበላይነት አይደለም።

ግን አፄነትና መስፍንነት እንደ ስርዓት ባልቀበለውም የንጉሳውያን ቤተሰቦችና መሳፍንቶች መጥፋት አለባቸው ብዬ ግን አላምንም። እኔ ብሆን እነኚህ የንጉስ ቤተሰቦችና መሳፍንት ቁልፍ የመንግስት ስልጣን አልሰጣቸውም ነበር። በሀገራቸው በሰላም እንዲኖሩ ግን እፈቅድላቸው ነበር። ምክንያቱም እንደማንኛውም ሰው ዜጎች ናቸው፤ ለሀገራቸው በተቻላቸው መጠን አስትዋፅዖ አድርገዋል። ስለዚህ ንጉሳዊ ቤተሰብና መሳፍንት ስለሆኑ ብቻ መጥፋት አለባቸው ብዬ አልፈርድም። እንደ ጠላትም አላያቸውም፣ እንደ ዜጎች እንጂ።

ህወሓት ግን በመፈክር ደረጃ በጠላትነት ፈረጃቸው። በተግባርም አጠፋቸው፣ ገደላቸው። በንጉሳዊ ቤተሰብና መስፍንነት ዝንባሌዎች ሰበብ ብዙ የተምቤን፣ ዓጋመ፣ እንደርታ፣ ዓድዋ፣ ሽረ፣ አክሱም ወዘተ መሳፍንቶች እንዲጠፉ ተደረገ። ‘ትግራይ ከመሳፍንቶች ነፃ ወጣች’ ተባለ። እውነታው ግን ‘ትግራይ ተገደለች’ መባል ነበረበት። መሳፍንቶች ከስልጣን ማውረድ እየተቻለ መግደል ምን አመጣው (ህወሓቶች ከስልጣን ማውረድ እየተቻለ መግደል ለምን ያስፈልጋል)?

Sunday, January 12, 2014

ሚኒስትር ሲያረጅ አምባሳደር ይሆናል

በበድሉ ዋቅጅራ

ይህ ትዝብት እንጂ ጥያቄ አይደለም!

ሀሳብ ቁፋሮ ነው፤ በ‹ለምን› ዶማ ዙሪያ ገባን በተጠየቅ መቆፈር ነው ሀሳብ! ምን፣ እንዴት፣ ለምን፣ በማን … እያልን የእራሳችንን፣ የቤተሰባችንን፣ የማህበረሰባችንን፣ የሀገራችንን ውሎና አዳር ስንጠይቅ አሰብን ማለት ነው፡፡ እንደ ዶማችን ጥንካሬ የቁፋሯችን ስፋት ይለያያል፡፡ አንዳንዶቻችን የለምን ዶማችን ዶልዱሞ የራሳችንን ማሳ እንኳ በወጉ አንቆፍርም፤ የአንዳንዶቻችን የለምን ዶማ ደግሞ የሾለ ነው፤ ከራስ ጠለል፣ ከቤተሰብና ከሸንጎ ተሻግሮ፣ የዜጎችን ማሳ፣ የሀገርን ርስት በተጠየቅ ይቆፍራል፡፡ ከፋም ለማ፣ ጠበበም ሰፋ ሰው በህይወት ካለ ያስባል፡፡

እኔም ሰው ነኝ፣ በህይወትም አለሁ፤ እና አስባለሁ፡፡ አንዳንድ ሀሳቦች አሉኝ፤ ሳልወድ የማስባቸው፡፡ በለምን ዶማዬ ብቆፍር ብቆፍር ተጠየቃዊ ሰበብ የማላገኝላቸው፡፡ ተጠየቃዊ ሰበበ-መንስኤ አላገኘሁላቸውምና ሁልጊዜ ለቁፋሮ የለምን ዶማዬ ፊት ይጋረጣሉ፡፡ ደጋግሜ ብቆፍራቸውም ጠብ የሚል ተጠየቃዊ ነጥብ አላገኝላቸውም፡፡ ዘወትር በለምን ዶማዬ ቆፍሬ፣ ልብ የሚያርስ እንኳን ባይሆን ከልብ የሚደርስ ተጠየቃዊ መልስ ካላገኘሁላቸው ነጥቦች አንዱ የኢህአዴግ ሹም - ሽር ነው፡፡

ሁልጊዜ (ላለፉት ሃያ ምናምን አመታት) ሳስበው የኢህአዴግ ሹም-ሽር ይገርመኛል፡፡ ግን ቆይ በኢህአዴግ ዘመን የተደረገ ሹም-ሽር አለ? በጭራሽ! የለም! ኢህአዴግ ሾሞ አይሽርም፡፡ በኢህአዴግ ሹም-ሽር የለም፡፡ በኢህአዴግ አንድም ሹም-እስር፣ አንድም ሹም-ሹም ነው ያለው፡፡ ሹም-እስር ማለት ከሹመት ወደ እስር ቤት የሚደረግ ሽግግር ነው፡፡ በዚህ ስር አቶ ታምራት ላይኔ፣ አቶ ስዬ አብርሃ፣… ሌሎችም ይመደባሉ፡፡ ሁለተኛው መደብ ደግሞ ሹም-ሹም ነው፡፡ በዚህ ስር ከግማሽ በላይ የሚሆኑትን የሀገሬን ከፍተኛ ባለስልጣናት መኮልኮል አይገድም፡፡ ለአብነት ግን ወ/ሮ ገነት ዘውዴ፣ አቶ አያሌው ጎበዜ፣ አቶ ሽፈራው ሽጉጤ፣ … የአሁኑን ፕሬዚዳንት ዶ/ር ሙላቱን ጭምር መጥቀስ ይቻላል፡፡

Saturday, January 11, 2014

ሻምበል ጉታ ዲንቃ፤ ጊዜውን ጠብቆ ይነጋል – ከፕ/ር መስፍን ወ/ማርያም

በአሁኑ ጊዜ ወያኔ ሰውን እያፈረሰ፣ ማህበረሰብን እያፈረሰ ሰማይ-ጠቀስ ሕንጻዎችን በሚሠራበት ጊዜ፣ ከትናንት ወዲያ የሰዎችን ቤቶች አፍርሶ ትናንት የመኪና መንገድ ከሠራ በኋላ ዛሬ መንገዱን አፍርሶ የባቡር መንገድ እየተሠራ አዲስ አበባ በትራፊክ መጨናነቅ መኪና መንዳት አደገኛ በሆነበት ጊዜ፣ ዛሬ ባለሥልጣኖች የሚሠሩት ጠፍቶአቸው የጠቅላይ ሚኒስቴር ቢሮ የሚባለውን በአማካሪዎች ከሞሉት በኋላ ለሚኒስትሮችም አማካሪ መሾም በተጀመረበት ጊዜ፣ ዛሬ በሳኡዲ አረብያ ኢትዮጵያውያን እንደአደገኛ አውሬ እየታደኑ በሚደበደቡበት፣ በሚታሰሩበት፣ በሚደፈሩበትና በሚገደሉበት ጊዜ፣ ዛሬ በኬንያና በዩጋንዳ እንዲሁም በእሥራኤል ኢትዮጵያውያንን የማንገላታት ዝንባሌዎች በሚታዩበት ጊዜ፣ ዛሬ ኢትዮጵያውያን ከስዊድን እስከአውስትራልያ እየተሰበሰቡ በመጮህ ለማይሰሟቸው ሁሉ አቤቱታቸውን በሚያቀርቡበት ጊዜ፣ ዛሬ በተለያዩ አገሮች በኢትዮጵያውያን ላይ በሚፈጸመው ጥቃትና በደል፣ አለሁላችሁ የሚል መንግሥት በሌለበት ጊዜ —- ዛሬ ታሪካዊትዋ ኢትዮጵያ፣ ራሳቸውን የሚያከብሩና ኩራት ራታችን የሚሉት ኢትዮጵያውያን አልቀው ለሆድ በየሰው አገር መሰደድ ባህል በሆነበት ጊዜ፣ ዛሬ ዶር. በድሉ ዋቅጅራ ስለኢትዮጵያና ስለኢትዮጵያውያን ውርደት ደጋግሞ የነፍሱን ኡኡታ ባሰማበት ጊዜ በድንገት አንገታችንን ቀና አድርጎ ኩራታችንን ሊያስጎነጨን የሞከረ ሰው ተገኘ! ኢትዮጵያ ሁሌም የተአምር አገር ነች።

በታላቁ ሰው በኔልሰን ማንዴላ እረፍት ምክንያት አንድ ተደብቆ የኖረ ክቡር ኢትዮጵያዊ ብቅ አለ፤ ማንዴላ ለሥልጠና በኢትዮጵያ በነበረበት ጊዜ ምናልባትም እንግሊዞች ማንዴላን ሊያስገድሉ ከጠባቂዎቹ አንዱ የነበረውን ወታደር በገንዘብ ገዝተው ዓላማቸውን ለመፈጸም አቅደው ነበር፤ ወታደሩ ገንዘቡን ከተቀበለ በኋላ ሀሳቡን ለውጦ ገንዘቡን ለአለቃው ሰጠ፤ ማንዴላ ከሞት ተረፈ፤ አንድ ተራ ኢትዮጵያዊ ራሱንና አገሩን የሚያስከብር ሥራ ሲሠራ የሚኮሰኩሳቸው ባለሥልጣኖች ለእነሱ የማይተላለፍ ክብር በመሆኑ ተዳፍኖ እንዲኖር አደረጉት፤ እነሱ ሞተው ወይም ተሰድደው ሲያልቁ የተዳፈነው ምሥጢር ብቅ አለ፤ ባለሥልጣኖቹ ሸልመውት ይሆናል፤ ግን አላከበሩትም፤ ሻምበል ጉታን ያከበረው የማንዴላ ሞት ነው፤ የሚያሳዝነው ማንዴላ ይህንን የሱን ሕይወት ለማትረፍ ሁለት ሺህ ፓውንድ ያጣውን ኢትዮጵያዊ ወታደር ሳያውቀው መሞቱ ነው።

Thursday, January 9, 2014

የኢትዮጵያ ትምህርት አደረጃጀት ለዉድቀት ወይስ ለጥራት?

ትምህርት ሚኒስተር በ1ኛና በ2ኛ ደረጃ ት/ቤቶች ላይ የመማር ማስተማሩን ሂደት በጥራት ለማከናወን ይረዳል በሚል ስበብ በየግዜዉ የሚፈበረኩ የአደረጃጀት ኩልኩሌ /ጋጋታ/ በማምጣት መምህራንን፤ተማሪንና ወላጅን ከማስጨነቅ አልፎ የትምህርቱን ጥራት ከመቸዉም በላይ እየዘቀጠ እንዲሄድ አድርጓል። ለዚህ መረጃ ይሆን ዘንድ ዓለም ባንክ በዲሴበር 7/2012 በ221 ገጽ በዘጠኝ ምዕራፍ በሰጡት መግለጫ አንኳር ነገሮችን አንስተዋል። እነዚህም አንኳር ጉዳዮችን በሰፊዉ በማተት የችግሩን አሳሳቢነት በማጉላት መንግስት በአስቸኳይ ርምት መዉሰድ እንዳለበት በአንክሮ ያስጠነቀቀ ሲሆን ችግሩንም በአፈጣኝ መግታት ካልተቻለ በአገርና በህዝብ ላይ ለያመጣ የሚችለዉን ችግር በግምገማዉ አስቀምጧል።

ኢህአደግ በየግዜዉ አዳዲስ የአደረጃጀት ጋጋታ በማምጣት ከመምህራንና ከተማሪዎች ጋር ግብግብ ሲፈጥር ይታያል እነዚህም አዳዲስ የትምህርት አደረጃጀቶች፡-የትምህርት ጥራትፓኬጅ፤ ኮማንድ ፖስት፤አንድ ለአምስት፤ BPR/መሰረታዊ የስራ ሂደት፤የመምህራን ዉጤት ተኮር፤የልማት ሰራዊት፤ታህድሶ ፤የለዉጥ ሰራዊት፤ተማሪን ያማከለ የማስተማር ሂደት፤ሪፎርሜሽን/Reformation/…,የመሳሰሉትን የአደረጃጀት ኩልኩሌ/ጋጋታ/በማምጣት በትምህርቱ፤ በመምህራንና በተማሪዎች ዘንድ መቀቃርን በመፍጠር በትምህርት ዘርፉ ላይ ግዙፍ የጥራት ኪሳራ አሳይታል።እኔም ከዚህ በላይ የጠቀስኋቸዉን/የተጠቀሱትን የአደረጃጀት ጋጋታዎች በመዳሰስ አዎንታዉና አሉታዊ አካሄዳቸዎን ለማስቀመጥ እሞክራለሁ።

የቀደምቶቹን ወንጀል ለማጋለጥ መቃብር ሲምስ የኖረው ወያኔ በራሱ ጦር ካምፕ ውስጥ የተገኘውን አስከሬን መደበቅ ለምን አሰፈለገው?

አዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ፈረንሳይ ለጋሲዮን በሚገኘው የክብርዘበኛ ጦር ካምፕ ውስጥ ማንነታቸው ያልታወቁ የ6 ዜጎች አስከሬን ለመንገድ ሥራ በተሠማሩ ቆፋሪዎች አማካኝነት መገኘቱ የሰሞኑ አሳዛኝ ዜና ነው።

አንድ አይነት ቀለም ባላቸው ብርድ ልብሶች ተጠቅልለው ከተገኙ 6 አስከሬኖች የመጀመሪያዎቹ ሁለት ሰለባዎች ታስረውበት የነበረው የእጅ ሰንሰለታቸው እንኳ እንዳልወለቀና ከተቀሩት የአንዱ እጆች ደግሞ የፍጥኝ ወደ ኋላ እንደታሰሩ መገኘታችው ግድያው በቅርብ እንደተፈፀም አንዱ አስረጂ ነው።

በእንዲህ አይነት ጭካኔ የተገደሉ ዜጎች አስከሬን መገኘት በመንግሥት ተብየው አካል ካለመገለጹም በላይ ግቢውን በማስተዳደር ላይ የሚገኘው 3ኛ ክፈለ ጦርም ሆነ በግብር ከፋይ ገንዘብ የሚተዳደሩ መገናኛ ብዙሃን እስከዛሬ አንድም ቃል መተንፈስ አለመፈለጋቸው ጉዳዩን እጅግ የሚያሳዝን ብቻ ሳይሆን የሚያስገርምም አድርጎታል። ይባስ ተብሎም በመንገድ ሥራ ቁፋሮው የበለጠ አስከሬን ሊወጣ ይችላል በሚል ስጋት አካባቢው በፖሊስ እንዲታጠር ከተደረገ በኋላ ሥራውም እንዲቋረጥ ተደርጓል።

በፓለቲካ መስመር ልዩነት ምክንያት ደርግ ያለ ርህራሄ የጨፈጨፋቸውን ከመቃብር እያወጣ ዘመድ አዝማድ በማላቀስ የፖለቲካ ትርፍ ለማግኘት ሲዳክር የኖረ አገዛዝ በእንዲህ አይነት አሳዛኝ ሁኔታና አጋጣሚ የተገኘውን የጅምላ አስከሬን አይቶ አንዳላየ ለማለፍ መሞከሩ ለምን ይሆን?

አብዛኛው የአዲስ አበባ ነዋሪ እንደሚያስታውሰው የክብር ዘበኛ ጦር ካምፕ በመባል የሚታወቀው የጃን ሜዳ 3ኛ ክፍለ ጦር ግቢ ድህረ ምርጫ 97 ወያኔ ለጅምላ እስር ቤትነት ከተጠቀመባቸው የማጎሪያ ቦታዎች አንዱ ነበር። ከዚያን ጊዜ በፊትና በኋላም ቢሆን ካምፑ በወያኔ ጠላትነት ተፈረጀ በጸጥታ ሠራተኞች ከታገቱ በኋላ አድራሻቸው እስከዛሬ ተሰውሮ ላሉ በርካቶች በምስጢር እስርቤትነት በማገልገል ላይ ከሚገኙ ወታደራዊ ካምፖች አንዱ እንደሆ ይታወቃል።

በኢትዮጵያ ሬዲዮና ቴሌ,ቭዥን ድርጅት የተላለፈ ዘገባን ይመለከታል! (ከአንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትሕ ፓርቲ)

አንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትሕ ፓርቲ (አንድነት)

UNITY FOR DEMOCRACY AND JUSTICE PARTY (UDJ)
-------------------------------------------------------

ቁጥር አንድነት /801/2ዐዐ6
ቀን 01/ዐ5/2ዐዐ6 ዓም

-------------------------------------------

ለኢትዮጵያ ሬዲዮና ቴሌዥዥን ድርጅት
አዲስ አበባ
-------------------------------------------

ጉዳዩ፡- በኢትዮጵያ ሬዲዮና ቴሌ,ቭዥን ድርጅት የተላለፈ ዘገባን ይመለከታል
-------------------------------------------

የኢትዮጵያ ሬድዮና ቴሌቭዥን ድርጅት በአዋጅ የተቋቋመና ለሁሉም ኢትዮጵያውያን የጋራ አገልግሎት እንዲሰጥ ኃላፊነት ያለበት የመገናኛ ብዙሃን መሆኑ ይታወቃል፡፡

ይሁን እንጂ ድርጅታችሁ ከብሔራዊ መረጃና ደህንነት ጋር በመተባበር ‹‹ሽብርተኝነት በኢትዮጵያ የአሸባሪ ድርጅቶች አሰያየምና ማንነት›› በሚል ርዕስ ታህሣሥ 15፣18ና 25 ቀን 2ዐዐ6 ዓ.ም በተላለፈው ዘገባ ላይ፡-

1. ፓርቲያችን አንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትሕ ፓርቲ (አንድነት) ከሽብርተኛ ቡድኖች ጋር የሚሰራ ፓርቲ እንደሆነ የሚያስመስል ዘገባ መተላለፉ፡፡
2. በሕግ አውጭው አካል ባልተፈረጀ ወይም በሕግ ተጠያቂ ያልሆነን ተቀማጭነቱን በውጭ ያደረገውን የኢትዮጵያ ሳተላይት ቴሌቭዥን ጣቢያን እያጣቀሱና የፓርቲያችን አመራሮች የሰጧቸውን መግለጫዎችና ቃለ-ምልልሶችን ጭምር በመጠቀም እንዲሁም ምስሎቻቸውን እያቀረቡ የተሳሳተ መረጃ ለሕብረተሰቡ ተሰራጭቷል፡፡

የምንናገርበትን የመገናኛ ብዙሃን ማንም እንዲመርጥልን ወይም እንዲወስንልን አንፈቅድም!!!!


ከሰማያዊ ፓርቲ የተሰጠ መግለጫ

የብሔራዊ ደህንነት መረጃ እና የፀረ ሽብር ግብረ ኃይል የጋራ ኃይል አድርጎ ራሱን የሚጠራ አካል የዜጎችንና የተቋማትን ሕገ-መንግስታዊና ዲሞክራሲያዊ መብት በመጣስ ጥፋተኝነታቸው በፍርድ ቤት ሳይወሰን ወንጀለኛ ሲያደርጋቸውና ስማቸውን ሲያጎድፍ ማየት እየተለመደ የመጣ ተደጋጋሚ ጉዳይ ሆኗል፡፡ ይህ ከላይ ከተጠቀሱት ሁለት ተቋማት ተውጣጥቶም ይሁን ተቀናጅቶ የሚሰራ አካል በተደጋጋሚ ጊዜ በሽብር ወንጀል ጠርጥሬአቸዋለሁ የሚላቸውን ሁሉ በመክሰስ ወደ እስር ቤት እንዲወርዱ እያደረገ ጉዳያቸው የፍርድ ቤት ውሳኔ ሳያገኝ እንደፈለገ በሚቆጣጠረው ወይም በሚያዘው የኢትዮጵያ ቴሌቪዥንና ሬዲዮ ድርጅት አማካኝነት የፈለገውን ዓይነት ፍረጃና ሥም ማጥፋት ሲያካሒድባቸው ቆይቷል፡፡

ይህ ራሱን ከሕግ በላይ የሰቀለ አካል ያለምንም ገደብ ከሚሰራቸው ተግባራት እንዲታቀብ በሕግ የሚያስቆመው በመጥፋቱ እስካሁን የፈፀማቸውን የማንአለብኝነት ተግባራት እንደጥፋት ሳይሆን እንደ መልካም ሥራ ቆጥሯቸው በተመሳሳይ የሥም ማጥፋትና የፍረጃ ተግባሩ እንዲገፋበት አድርጎታል፡፡ በዚሁም መሰረት ታህሳስ 25 ቀን 2006 ዓ.ም ምሽት በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ባስተላለፈው የዘጋቢ ፊልም ፕሮፓጋንዳ አሸባሪ ያላቸውን ድርጅቶችና ግለሰቦች አድርሰውታል ያለውን ጥፋት በዝርዝር አቅርቧል፡፡ ፓርቲያችንን በዚሁ ዘገባ ከተጠቀሱት “አሸባሪ” ድርጅቶች ጋር በማገናኘት ስም ለማጉደፍና ለማስፈራራት የተደረገውን መፍጨርጨር አይተናል፣ ሰምተናል፣ ተገርመናል በመጨረሻም አዝነናል፡፡

በዘጋቢ ፊልሙ የቀረቡ ፓርቲያችንን የማይመለከቱ ጉዳዮችን ትተን ከፓርቲያችን ጋር በማገናኘት የተጠቀሰው “ኢሳት” የተባለ የመገናኛ ብዙሃን በኢትዮጵያ መንግስት በሽብርተኝነት ከተፈረጀ ድርጅት የገንዘብ ድጋፍ እንደተደረገለትና በሰላማዊ መንገድ የሚንቀሳቀሱ ድርጅቶች በተለይም ሰማያዊ ፓርቲ በዚህ የመገናኛ ብዙሃን እንዳንጠቀም የማስጠንቀቂያ ዛቻ ተላልፎልናል፡፡ ይህ አስፈራሪ አካል ራሱን ሕግ አውጭና ሕግ ተርጓሚ በማድረግ የፈለገውን አካል ለመፈረጅ፣ ለመክሰስና ለመፍረድ ሥልጣኑን ከየት እንዳገኘ የማይታወቅ ሲሆን የዚህች ሐገር ዜጎችም ሃሳባችንን የምንገልፅበትንና የማንገልፅበትን የመገናኛ ብዙሃን እየመረጠልንና እየወሰነልን ይገኛል፡፡ ሰማያዊ ፓርቲ እንዲህ ዓይነቱን የእብሪት መልዕክት ከተራ ርካሽ ፕሮፓጋንዳነት የማያልፍ የሕግና የዲሞክራሲያዊ መብት ገደብን ካለማወቅ የሚመነጭ አስተሳሰብ ነው ብሎ ያምናል፡፡

Wednesday, January 8, 2014

ዛሬ የታተመውን ሰንደቅ ጋዜጣ ሙሉ እትም እነሆ

ሰንደቅ ጋዜጣ በዛሬው እትም …


  • ቴዲ አፍሮ ሰጥቶታል በተባለው ቃለመጠይቅ ውዝግብ 10 ሚሊዮን ብር አጣ
  • የዶ/ር ነጋሶ ስንብት፣ የአንድነት ብሔራዊ ምክር ቤት ግምገማ፤ የኢንጅነር ግዛቸው አዲስ የቀያጭነት ጥሪ እና የመድረክ አንደምታዎች
  • የፌዴሬሽን ምክርቤትን የከፈለው የአቶ መላኩ ፈንታ ጥያቄ
  • ሰራተኛውና መንግስት የተፋጠጡበት መድረክ
  • የአርቲስት ታደለ ሮባ “ምስጋና” እና አንዳንድ ነገሮች


የሚሉ እና ሌሎች ወቅታዊ ጉዳዮችን ይዞልን ቀርቧል።

 ሙሉውን ጋዜጣ በpdf ለማንበብ እዚህ ላይ ይጫኑ።

2014፡ የኢትዮጵያ የአቦ-ጉማሬው ትውልድ ዓመት

ከፕሮፌሰር አለማየሁ ገብረማርያም

ትርጉም በነጻነት ለሀገሬ

(ክፍል አንድ) 2014 የኢትዮጵያ የአቦ -ጉማሬው ትውልድ የሚነሳሳበት ዓመት፣

እ.ኤ.አ በ2013 በመጀመሪያው ሳምንት ባቀረብኩት ሳምንታዊው ትችቴ ዓመቱ “የኢትዮጵያ የአቦሸማኔው (የወጣቱ ትውልድ) ዓመት ይሆናል “የሚል ትንበያ ሰጥቼ ነበር፡፡ እንደትንበያውም ዓመቱ የኢትዮጵያ የአቦሸማኔው (ወጣቱ) ትውልድ ታላቅ የስኬት ዓመት ሆኖ ተጠናቅቋል፡፡

2014 ደግሞ “የኢትዮጵያ የአቦ-ጉማሬው ትውልድ ዓመት ይሆናል” የሚል ትንበያ እሰጣለሁ፡፡ የአቦ-ጉማሬው ትውልድ በአፈጣጠሩ የጉማሬው (የቀድሞው ትውልድ) አባል ሲሆን በተግባራዊ እንቅስቃሴው ግን እንደ አቦሸማኔው (ወጣቱ ትውልድ) የሚያስብ፣ አቦሸማኔውን የሚመስል እና እንደ አቦሸማኔው ሁሉ የክንውን ድርጊቶችን የሚፈጽም የማህበረሰብ ክፍል ነው፡፡ ከዚህም በተጨማሪ የአቦ-ጉማሬው ትውልድ ለፍትህ እና ለነጻነት በሚደረገው የትግል ሂደት ላይ የጉማሬው (የቀድሞው ትውልድ) የሚያንጸባርቃቸውን ድክመቶች በሚገባ የተገነዘበ እና እነዚህን ግድፈቶች በማስወገድ የወጣቱን የትግል መንፈስ እና ወኔ ወደ ላቀ የእድገት ምዕራፍ ለማሸጋገር በአንድ ዓላማ ለአንድ ዓላማ ከአቦሸማኔው (የወጣቱ) ትውልድ ጎን በመሰለፍ የሚሰራ የህብረተሰብ ክፍል ነው፡፡

የኢትዮጵያ የአቦ-ጉማሬው ትውልድ በአፈጣጠሩ ልዩ የሆነ የትውልድ ዝርያ ነው፡፡ ይህ ትውልድ በተፈጥሮው ድልድይ ቀያሽ እና በኃይል አሰላለፍ ላይ ያለውን ወቅታዊ እና ነባራዊ ሁኔታ በተገቢው መንገድ እያጠና ወጣቱን ትውልድ ለድል የሚያበቁ የኃይል ምንጮችን ቀጣይነት ባለው መልክ የሚፈበርክ የህብረተሰብ አካል ነው፡፡ የአቦ-ጉማሬው ትውልድ ወጣቱን ከቀዳሚው ትውልድ የሚያገናኙ ጠንካራ ትውልድ አገናኝ የትውልድ ድልድዮችን የሚገነቡ ናቸው፡፡ ደኃውን ከሀብታም የሚያገናኙ ድልድዮችን የሚገነቡ ናቸው፡፡ ህዝቦችን ከአምባገነናዊ ስርዓት ወደ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት የሚያሸጋግሩ ድልድዮችን የሚገነቡ ናቸው፡፡ በጎሳ የተለያዩ ህዝቦችን የሚያገናኙ ድልድዮችን የሚገነቡ ናቸው፡፡ “ክልላዊ ደሴቶች (የጎሳ መንደሮች ወይም ባንቱስታንስ)” ተብለው ተነጣጥለው የሚኖሩ ህዝቦችን የሚያገናኙ ድልድዮችን የሚገነቡ ናቸው፡፡ በቋንቋ፣ በኃይማኖት እና በክልል ተነጣጥለው የተቀመጡ ህዝቦችን የሚያገናኙ ድልድዮችን የሚገነቡ ናቸው:: ባለመተማመን ሸለቆዎች፣ በእምነት ማጣት ጥልቅ ገደሎችና እና በጥርጣሬ ጎርፍ ወንዞች ላይ ድልድዮችን የሚገነቡ ናቸው፡፡ ብሄራዊ ዕርቅ ለማውረድ እና የብሄራዊ አንድነትን ለማምጣት ህዝቦችን የሚያገናኙ ድልድዮችን የሚነገነቡ ናቸው፡፡ በአገር ቤት ውስጥ ያሉትን ወጣቶች በውጭ አገር ከሚኖሩት የዲያስፖራ ወጣቶች ጋር የሚያገናኙ ድልድዮችን የሚገነቡ ናቸው፡፡ የአቦ-ጉማሬው ትውልድ ለመሻገር አስቸጋሪ በሆኑ የውኃ አካላት ላይ ድልድዮችን የሚገነቡ ናቸው፡፡

Saturday, January 4, 2014

አይ ስብሐት ነጋ!


በመስፍን ወልደ ማርያም

ታኅሣሥ 2006

በኢትዮጵያ ውስጥ ሥልጣን ሳይኖረው ባለሙሉ ሥልጣን፣ እውቀት ሳይኖረው ባለሙሉ እውቀት የሆነ ሰው ስብሐት ነጋ ብቻ ነው፤ እንዲያውም ከዚያም አልፎ ራሱን የቻለ ሉዓላዊ ነጻነት ያለው ግለሰብ ነው ለማለት የሚቻል ይመስለኛል፤ በዚህ ግለሰብ ላይ የማደንቃቸው ሁለት ነገሮች ናቸው፤ በሉዓላዊነቱ የተጎናጸፈውን ሥልጣን ሙሉ በሙሉ ይጠቀምበታል፤ ይቆጣኛል ወይም ይቀጣኛል ብሎ የሚፈራው የለም፤ ስብሐት ነጋ የሚፈራው ምንም ነገር የለም፤ ሁለተኛ በሉዓላዊነቱ ያለውን ሙሉ ነጻነት በሙሉ ልብ ይጠቀምበታል፤ ናስ በላይ ከበደ እንዳለው ‹‹የቅብጠት መዘላበድ›› ሊሆን ይችላል፤ ስብሐት ነጋ የተናገረው ነገር ትክክል ይሁን አይሁን ጉዳዩ አይደለም፤ ዋናው ነገር መናገሩ ነው።

በቅርቡ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ከጋዜጠኛነት ተማሪዎች ጋር ባደረገው ውይይት ላይ ሁለት ሰዎች ጽፈው አይቻለሁ፤ ዶር. በድሉ ዋቅጅራ በፋክት ላይ፣ ናስ በላይ አበበ በኢትዮ-ምኅዳር ላይ፤ ሁለቱም ሰዎች አልወደዱለትም ማለት ያንሳል፤ የሚወዱለትና የሚያጨበጭቡለት መኖራቸውም ሳይታለም የተፈታ ነው፤ ነገር ግን ስብሐት ነጋም ሆነ ደጋፊዎቹ አደባባይ ወጥተው ለመከራከር አይችሉም፤ ናስ በላይ አበበ እንደሚነግረን ‹‹አቶ ስብሐት ነጋ የውጭ ሰው እንዳይገባ ከተማሪዎቹ ጋር ተደራድረው ነበር የመጡት፤ ስለሆነም ነበር ከፍተኛ ጥበቃ አልፈን የገባነው፤›› ብቻውን ተናግሮ በጭብጨባ የሚሸኝበት መድረክ በመፈለጉ በከባድ ጥያቄም ቢሆን የሚያጣድፉት ሰዎች እንዳይኖሩ ማረጋገጡ በተማሪዎቹም ቢሆን ውሎ አድሮ ትዝብት ላይ ይጥለዋል።

ዶር. በድሉ ዋቅጂራ ስለስብሐት ነጋ ከኢትዮጵያዊነት መውደቅ በሚል በጻፈው ላይ ዶር. ዳኛቸውን እንደሚከተለው ይጠቅሳል፤ ‹‹ከኢትዮጵያዊነት መውደቅ ማለት፤ በቃ በአጭሩ (ኢትዮጵያዊ ሆኖ) ኢትዮጵያዊ አለመሆን ነው፤›› በቅንፍ ውስጥ ያለው የኔ ነው፤ ልክ ነው፤ አንድ ግለሰብ በማናቸውም ምክንያት ከኢትዮጵያዊነት ቢወድቅ ኢትዮጵያዊነቱ የከሸፈ ነው ለማለት ይቻላል፤ ነገር ግን ከኢትዮጵያዊነት መውደቅንና ኢትዮጵያዊነትን መጣልን ለይተን ማየት ያስፈልጋል፤ አንድ ሰው በማናቸውም ምክንያት ከፍተኛውን የኢትዮጰያዊነት ባሕርይና ግዴታ መሸከም አቅቶት ቢወድቅ ለዚያ ሰው ኢትዮጵያዊነቱ ከሸፈ፤ ለስብሐት ነጋና ለጓደኞቹ ከከሸፈባቸው የቆየ ይመስለኛል፤ ከራሱ አልፎ የሌሎችን ኢትዮጵያዊነት ለማክሸፍ የሚሞክር ደሞ ከመክሸፍ አልፎአል፤ ከኢትዮጵያዊነት መውደቅ ማለት የከሸፈ ኢትዮጵያዊነት ነው ማለት ነው።

Friday, January 3, 2014

አንድ ለአምስት – ከቃሊቲ ዉጭ ሌላ ቃሊቲ

ወያኔ የጫካ ዉስጥ ኑሮ በቃኝ ብሎ አዲስ አበባን ከረገጠ በኋላ ኢትዮጵያ ዉስጥ ብዙ አዳዲስ ቃላት ተፈጥረዋል፤ አንዳንድ አብረናቸዉ ያደግናቸዉ ቃላትና የቦታ ስሞች ደግሞ እየፋፉ መጥተዉ የሌሎች ሰፋ ያሉ ሀሳቦች መግለጫ ሆነዋል። ለምሳሌ የዛሬ ሃያ አምስት አመት ኮሌጅ የጨረሰ ልጅ አባቱን ቃሊቲ መግባቴ ነዉ ብሎ ቢነግረዉ አባቱ . . . . ምንዉ ስራ አገኘህ እንዴ ብሎ ከመጠየቅ ዉጭ በልጁ አባባል በፍጹም አይደነግጥም። ዛሬ ግን “ዕድሜ ለወያኔ” ቃሊቲ ሲባል የማይደነግጥ ኢትዮጵያዊ የለም። በፋብሪካ ማዕከልነቷ ትታወቅ የነበረችዉ ቃሊቲ ዛሬ አጥሩ ዉስጥ ወያኔ አፍኖ የከተታቸዉ ሰላማዊ ዜጎች ከአጥሩ ዉጭ ደግሞ የእነዚሁ ሰላማዊ ዜጎች ቤተሰቦች የሚተራመሱበት የጭንቅና የመከራ አምባ ሆናለች። አዎ ቃሊቲ እንደ አልባኒያዋ ቡሪልና እንደ ሩሲያዋ ሳይቤሪያ ዜጎችን ለማፈንና በዜጎች ላይ ሰቆቃ ለመፈጸም ሆን ተብላ እንደገና የተፈጠረችና አለፍላጎቷ አስቀያሚ ገጽታ የተከናነበች ከተማ ሆናለች። ቃሊቲ ታሪክ ከክፋታቸዉና ከጭካኔያቸዉ ዉጭ በፍጹም የማያስታዉሳቸዉን የሩሲያዉን ጆሴፍ ስታሊንና የአልባኒያዉን ኤንቨር ሆዣን እኛ ኢትዮጵያዉያን አለዝምድናችን በግድ እንድናስታዉሳቸዉ የተገደድንባት የአምባገነንነት ተምሳሌት ናት። የሚገረመዉ ቃሊቲ ወያኔ ተሸክሞ ካመጠልን የጆሴፍ ስታሊንና ኢንቨር ሆዣ መንታ ትዝታዎች አንዷ ናት። ጆሴፍ ስታሊንና ኢንቨር ሆዣ የሩሲያንና የአልባኒያን ህዝብ እስር ቤት ዉስጥ ብቻ አልነበረም ያሰሩት፤ አንድ ለአምስት በሚሉት ማለቂያ በሌለዉ ሰንሰለታቸዉ በመኖሪያ ቤቱ ዉስጥ፤ በሚሰራበት ፋብሪካ ዉስጥ፤ በሚማርበት ት/ቤቶች ዉስጥና በተደራጀበት ገበሬ ማህበር ዉስጥ ጭምር ጭምድድ አድርገዉ አስረዉታል።

የኢትዮጵያን ህዝብ የሚረገጡትንና እንደ እንስሳ እየታሰሩ የሚገረፉበትን መንገድ ለማወቅና ልምድ ለመቅሰም አልባኒያ ድረስ የሄዱት ዘረኞቹ የወያኔ መሪዎች ከአልባኒያ ይዘዉብን የመጡት ቃሊቲን ብቻ አይደለም፤ ከቃሊቲ ዉጭ ህዝብን በሰንሰለት ማስር የሚያስችላቸዉን “አንድ ለአምስት” አደረጃትም ይዘዉ መጥተዉ ኢትዮጵያ ዉስጥ ተግባራዊ አድርገዋል። አንድ ለአምስት ወያኔ ምንም ይበለዉ ምን በግንብና በሽቦ አጥር ያልታጠረ ሰፊ እስር ቤት ነዉ፤ ወይም አንድ ለአምስት – ከቃሊቲ ዉጭ የሚገኝ ሌላ ቃሊቲ ነዉ። ወያኔ የኢትዮጵያን ህዝብ በአንድ ለአምስት ሰንሰለት ማሰር ከጀመረ ቆይቷል። ዛሬ ወያኔ ይህንን የእነ ስታሊንን የመከራ ማራዘሚያ ገመድ ከገመደብን ከአመታት በኋላ “እንድ ለአምስትን” እንደገና ማንሳት የፈለግነዉ ጉዳዩ አዲስ ሆኖብን ሳይሆን ሁለት ነገሮች አሳስበዉን ነዉ፤ አንደኛዉ ወያኔ የ“እንድ ለአምስት” አደረጃጀትን የህብረተሰባችን መሰረት ወደ ሆነዉ ወደ ቤተሰብ ደራጃ ሲያወርደዉ በማየታችን ሲሆን፤ ሁለተኛዉ ደግሞ “እሾክን በእሾክ” እንዲሉ የኢትዮጵያ ህዝብ ከወያኔ ዘርኝነት፤ሰቆቃና ጭቆና ለመላቀቅ ወያኔ የፈጠረዉን አንድ ለአምስት አደረጃት በመሰላልነት ተጠቅሞ እራሱን እንዲያደራጅና ለወሳኙ ፍልሚያ እራሱን እንዲያዘጋጅ ለማሳሰብ ነዉ።

ወያኔ ነገረ ስራዉ ሁሉ ከጉልበትና ከሀይል ጋር የተያያዘ ነዉ፤ ስልጣን የያዘዉ በጠመንጃ ሀይል ነዉ፤ ስልጣን ላይ የቆየዉ በጠመንጃ ሀይል ነዉ። የኢትዮጵያን ህዝብ አንድ ለአምስት እያለ የሚያደራጀዉም በሀይል እያስገደደ ነዉ እንጂ የኢትዮጵያ ህዝብማ በወያኔ ስር መደራጀት ቀርቶ ወያኔ ድርጅቱ ብቻ ሳይሆን ወያኔ የሚባል ቃሉ እራሱ ከምድረ ኢትዮጵያ ቢጠፋ ደስታዉን አይችለዉም። የሚገርመዉ ወያኔ በዚያ ጠመንጃ በጨበጠበት እጁ የጻፈዉ ህገ መንግስት አንቀጽ 31 ማንኛዉም ሰዉ ለማንኛዉም አላማ በማህበር የመደራጀት መብት አለዉ ይላል፤ ሆኖም ይህ ህገመንግስታዊ መብት ለይስሙላ የተቀመጠ የባዶ ቃላት ክምር ነዉ እንጂ ኢትዮጵያ ዉስጥ ህዝብ በራሱ ፈቃድ መደራጀትም አለመደራጀትም አይችልም። ለመሆኑ ወያኔ በፍጹም በማይመለከተዉ በቤተሰብ ጉዳይ ጣልቃ የሚገባዉ ለምንድነዉ? እኛስ ኢትዮጵያዉያን ይህንን የወያኔ ጣልቃ ገብነት እንዴት አድርገን ነዉ እራሳችንን ነጻ ለማዉጣት የምንጠቀምበት?

ያለፉት ስህተቶች ትምህርት እንጂ ማነቆ አይሁኑ - ግርማ ካሳ

እንደ ፈረንጆች አቆጣጠር፣ ኖቬምበር 17 ቀን 1996 ነበር። በሰርቢያ (የቀድሞ ዩጎስላቪያ) ፣ የክልል ምርጫ ይደረጋል። በቩክ ድራስኮቪች የሚመራዉ SPO ፣ በቬስና ፔሲች የሚመራዉ GSS እና ሌሎች ድርጅቶች በአንድ ላይ ሆነው አብላጫ ድምጽ ያገኛሉ። ነገር ግን በወቅቱ የነበሩ አምባገነን ባለስልጣናት፣ እነ ስሎቦዳን ሚሎሶቪች አጭበረበሩ። ከኖቬምበር 17 1996 እስከ ፌቡሩያሪ 11 1997 ድረስ፣ «ያጄድኖ» የሚል፣ ሕዝባዊ ተቃዉሞዎች በስፋት ተደረጉ። ባለስልጣናቱ፣ የሕዝቡ ሰላማዊ ተቃዉሞ አይሎ መምጣቱን ሲያዩ አፈገፈጉ። የተቃዋሚዎች ስብስብ በክልል ምርጫዉ ያገኙትን ምርጫ፣ ተቀበሉ። ሊበራል ዴሞክራቱ ዞራን ጂንጂች የአገሪቷ መዲና የቤል ግሬድ ከንቲባ ሆኑ።

ብዙም አልቆየም፣ በተቃዋሚዎች መካከል ችግር መታየት ጀመረ። በቩክ ድራስኮቪች የሚመራዉ ፓርቲና በዞራን ጂንጂች በሚመራዉ ፓርቲ መካከል ልዩነቶች ተፈጠሩ። መካረር መጣ። የሕዝብን ጥያቄ አንግቦ በጋራ መቆም ተሳናቸው። በአደባባይ መወጋገዝ ጀመሩ። በአመቱ አገራዊ የፕሬዘዳንት ምርጫ ሲደረግ የሚሎሶቪች የሶሻሊስት ፓርቲ በቀላሉ ስልጣኑን ጨበጠ። የተለፋበት፣ የተደከመበት ሕዝባዊ እንቅስቃሴ ከሸፈ። አምባገነኖች አሸነፉ። በሕዝብ ትግል የተገኙ ዉጤት እንደገና ተቀለበሱ። ዞራን ጂንጂችም ከናካቴዉ ከተመረጡበት የቤልግሬድ ከንቲባነት ተነሱ።

በ1998 በየክልሉ ተማሪዎች «ኦትፖር» ( በሰርቢያን ቋንቋ እምቢተኝነት) በሚል ስም ከታች ወደ ላይ የሆነ እንቅስቃሴ ጀመሩ። የተከፋፈሉ የፖለቲካ ደርጅቶች በአንድ ላይ እንደገና ተሰባሰቡ። ካለፉት ስህተቶች በመማር፣ ፍጹም ሰላማዊና ሕጋዊ በሆነ መንገድ ለሚቀጥለው ምርጫ መዘጋጀት ጀመሩ። ከፍተኛ ጫና እየተደረገም ዝግጅቱ ተጧጧፈ። የገዥዉ ፓርቲ ደጋፊዎችን የመሳብ ሥራ በስፋት ተሰራ። በዚህም ምክንያት በርካታ የገዢዉ ፓርቲ አባላትና ደጋፊዎች ተቃዋሚዎችን መቀላቀል ጀመሩ። ኢቫን ስታምቦሊች ፣ የሚሎሶቪች አጋር የነበሩ ፖለቲከኛ ፣ ተቃዋሚዎች በመቀላቀላቸውም በሚሎሶቪሽ የደህንነት ሰራተኞች ታፍነው ተገደሉ።

ሴፕቴምበር 2000 ዓ.ም ምርጫ ተደረገ። የሚሎሶቪች ምርጫ ቦርድ፣ አሁንም የተጭበረበረ የምርጫ ዉጤት ይፋ አደረገ። ያንን አስከትሎ ኦክቶቦር 2000 ዓ.ም ፣ ትልቅ ተቃውሞ ሰልፍ ተደረገ። ምርጫ ቦርድ የምርጫዉን ዉጤት ወደ ነበረበት እንዲመልስ ተገደደ። የተቃዋሚዎች እጩ የሆኑት ኮስቶኒሳ እንዳሸነፉ ተገለጸ። የሚሎሶቪች ስልጣን ፍጻሜ ሆነ። የሰርቢያ ሕዝብ የማይቀለበስ ድል ተቀዳጀ።

የአንድነት ለዲሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ ልዩ ጉባኤው የአቋም መግለጫ!

ዛሬ በደረስንበት 21ኛው ክፍለዘመን በአለማችን የሚገኘው ሕዝብ ሰብአዊና ዲሞክራሲያዊ መብቶቹ በተከበሩበት ሁኔታ መመራት ይሻል፡፡ በዚህ ዘመን አምባገነን መሪዎችና መንግስታት በየትኛውም መስፈርት ስልጣን ላይ የመቆየት እድል የላቸውም፡፡ በዚህ ረገድ በቅርብ አመታት ውስጥ የማይደፈሩና እንደ ፈርኦን ይመለኩ የነበሩ አምባገነን መንግስታት በህዝባዊ ማዕበል ተጥለቅልቀውና ተንጠው መቀመቅ ሲወርዱ የአለም ህዝብ ሁሉ አስተውሏል፡፡ በአሁኑ ወቅት የዲሞክራሲና የነፃነት ጥየቄ ከዳቦ ጥያቄ ይበልጥ አንገብጋቢ እየሆነ መጥቷል፡፡

የአለማችን አንድ አካል የሆነችው አገራችን ኢትዮጵያ የዘመናት የስልጣኔ ጉዞዋ የምድራችን ቁንጮ የታሪክ ባለቤት ያደርጋታል፡፡ በየዘመናቱ የተነሱ ገዢዎቻችን ሲጭኑብን የቆዩት የአገዛዝ ቀንበር ወገባችንን ቢያጎብጠውም የኢትዮጵያ አንድነትና ሉኣላዊነት ፍፁም ሳይሸራረፍ ተጠብቆ ዘመን እንዲሻገርና ለትውልድ እንዲተላለፍ የማይሻ ኢትዮጵያዊ የለም፡፡

ወታደራዊው ደርግ ከሥልጣን በተወገደ ማግስት ዲሞክራሲና ነፃነት የሰፈነበት የዜጎች ሰብአዊና ዲሞክራሲያዊ መብቶች የሚከበሩባትን ኢትዮጵያ ለማየት ያልጓጓ ኢትዮጵያዊ አልነበረም፡፡ ህልማችን በእውነት ሳይፈታ ቀረ፣ ተስፋ ያደረግነው ነገር ከዓመት ዓመት እየጨለመ መጣ፡፡ ኢህአዴግ ባለፉት 23 ዓመታት የምኒሊክን ቤተመንግስት ቢቆጣጠርም የአገርን ህልውና ከመጠበቅና የህዝብ እንባን ከማበስ ይልቅ ዜጎችን መውጪያ መግቢያእያሳጣና የመከራን ገፈት እያስጨለጠ ጉዞውን ቀጥሏል፡፡ ስደቱ፣ እንግልቱ፣ ግርፋቱ፣ እስራቱ፣ ግድያው፣ አፈናው፣ ስቃዩ ከመቀነስ ይልቅ በየጊዜው እየከፋ ይገኛል፡፡ አንድነት ለዲሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ ይህን ቀንበር ለመስበር እንደ መርፌ ቀዳዳ በጠበበው የፖለቲካ ምህዳር ውስጥ እየተንቀሳቀሰ በመላው አገሪቱ ህዝብን ለትግል እያሰለፈ ይገኛል፡፡

Thursday, January 2, 2014

የወያኔን “አንድ ለአምስቶች” ወያኔን ለማዳከም እንጠቀምባቸው

ወያኔ የኢትዮጵያን ሕዝብ ለመቆጣጠር እንዲያመቸው በ“አንድ ለአምስት” አደረጃጀት እያደራጀው ነው።  ይህ አደረጃጀት  ስታሊን ለሠላሳ ዓመታት ሶቭየት ኅብረትን፤ ኤንቨር ሆዣ ደግሞ ለአርባ ዓመታት አልባኒያን ጠፍረው የገዙበት ስልት ነው። በዚህ የአገዛዝ ስልት መሠረት እያንዳንዱ ሰው በመዋቅር ተይዞ አራቱ ለአንዱ መረጃ የሚያቀብሉበት ሥርዓት ይዘረጋል።  

ሕዝብን በድርጅት አባልነት ስም በመዋቅር ማስገባት ለአንባገነኖች የሚሰጠው ዋነኛ ጥቅም የማኅበረሰብን ስነልቦና መስበሩ ነው። ይህ አወቃቀር ዜጎች የአምባገነኑን መንግሥት ኃይል ከመጠን በላይ አግዝፈው፤ እራሳቸውን ደግሞ አንኳሰው እንዲመለከቱ ያደርጋቸዋል። ዜጎች፣ “መንግሥት እያንዳንዱን ነገር አብጠርጥሮ ያውቃል” በሚል የፍራቻ ቆፈን እንዲያዙ ያደርጋቸዋል። እያንዳንዱ ሰው ጓደኛውን እንዲጠረጥር በማድረግ አምባገነኖች የስለላ ተቋማቸዉ ጠንካራና ሁሉን-አዋቂ እንዲመስል ያደርጉታል።

ይሁን እንጂ የማኅበረሰብ ስነልቦና ካልተሰበረ፤ በፍራቻ ፋንታ በራስ መተማመን ከዳበረ ማንም ያደራጀው ማን ነፃ ህሊና ያላቸው አባላት ድርጅቱን ራሳቸውን ነፃ ለማውጣት ይጠቀሙበታል። አሁን በደረስንበት ሁኔታ ይህንን በአገራችን ተግባራዊ የማድረግ ሰፊ እድል አለን።  የኢትዮጵያ ሕዝብ ከወያኔ ፍራቻ እራሱን ነፃ እያወጣ ነው። ወያኔ ከስታሊንም ሆነ ከኤንቨር ሆዣ በተለየ መንገድየአመለካከትና የርዕዮተዓለም ጉዳይ የሚያሳስበዉ ሀይል አይደለም።ቢያሳስበውም የሕዝብን ቀልብ የሚይይዝበት ምንም ነገር የለውም። ይህ ባህሪይዉ ነዉ ነው ወያኔ በእጅጉ የተጠላ ኃይል እንዲሆን ያደረገው።

እንዲህ በግዴታ እንጂ በእምነት ያልተሰባሰቡ ሰዎች ባሉበት ሁኔታ ተመሳሳይ ፀረ-ወያኔ አቋም ያላቸው ሰዎች በአንድ “አንድ ለአምስት” ሕዋስ ውስጥ የመገኘታቸው አጋጣሚ የጎላ ነው።  እነዚህ አባላት በግልጽ ከተነጋገሩበት ሕዋሱን ለፀረ-ወያኔ ትግል ሊጠቀሙበት ይችላሉ።  በመሆኑም ወያኔን ለመጨቆኛ መሣሪያነት ያዋቀረውን “አንድ ለአምስት” ራሱ ወያኔን መታገያ ብሎም ማዳከሚያ መሣሪያ ማድረግ ይቻላል። “አንድ ለአምስትን” በሽፋንነት በመጠቀም ውስጥ ውስጡን መጀራጀት በስፋት  ልንይዘዉና ልንሰራበት የሚገባ ስትራቴጄ ነው።

የወያኔ “አንድ ለአምስት” የኑሯችን አካል እየሆነ መጥቷል። በአንዳንድ ቦታዎች አለመደራጀት ሥራ የሚያሳጣ እየሆነ ነው።  በማናቸውም ምክንያት ራሳቸውን ወያኔ ጉያ ውስጥ ያገኙ የሕዝብ ወገኖች ካሁን በኋላ
መሥራት ያለባቸው ወያኔን ከውስጥ ሆኖ የማዳከምን ሥራ ማፋጠን ነው። ለዚህ ደግሞ እንደ “አንድ ለአምስት” አመቺ የሆነ መዋቅር አይገኝም።

በአሁኑ ሰዓት ግንቦት 7 ሕዋሳቶቹን በሁሉም ቦታ ለማዋቀር ከፍተኛ ጥረት እያደረገ ይገኛል፤በዚህም መሠረት  የግንቦት 7 ሕዋሶች በሁሉም የአገሪቱ አካባቢ ባልተማከለ መልኩ በብዛት እየተመሠረቱ ነው። ከዚህ ህዋሳቶችን ከመዘርጋት ሥራ ጎን ለጎን ህዝቡ በያለበት የወያኔንየራሱንመዋቅር በመጠቀም ወያኔንና ስርዐቱን መገዝገዝ አለበት።

ይህንን ለማድረግ የግንቦት 7ን መመሪያ መጠበቅ አያስፈልግም። እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ በራሱ መንገድ ተግባራዊ ሊያደርገው የ የሚችለዉ ነገር ነው።

በመሆኑም ግንቦት 7፡ የፍትህ፣ የነፃነትና የዲሞክራሲ ንቅናቄ የወያኔ “አንድ ለአምስቶችን” ወያኔን ለማዳከም እንጠቀምባቸው የሚል ጥሪ ያቀርባል።

ድል ለኢትዮጵያ ሕዝብ!!!

Wednesday, January 1, 2014

እ.ኤ.አ የ2013 ዓመት የኢትዮጵያ የአቦሸማኔው (ወጣቱ ትውልድ) መነሳሳት ሲገመገም፣

ከፕሮፌሰር አለማየሁ ገብረማርያም

ትርጉም በነጻነት ለሀገሬ

እ.ኤ.አ በጃንዋሪ 2013 “እ.ኤ.አ 2013 የኢትዮጵያ የአቦሸማኔው ትውልድ ዓመት ይሆናል“ በማለት ትንበያ ሰጥቸ ነበር፡፡ እንዲህ ስልም ቃል ገብቸ ነበር፣ “የኢትዮጵያ ወጣቶች ለፍትህና ለዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ የሚያደርጉትን ትግል ለመደገፍ እና ወደ ላቀ ደረጃ ከፍ እንዲል የእራሴን ሙሉ አስተዋጽኦ እንደማደርግ እንዲሁም ትግሉ ወደ አዲስ ምዕራፍ እንዲሸጋገር ወጣቱ ትውልድ እንዲነሳሳ ሳደፋፍር ነበር፡፡” በዚህም መሰረት ጀግኖቹ ወጣቶች ትግላቸውን ቀጥለው ከፍ ወዳለ ደረጃ ላይ አድርሰውታል፡፡ ለወጣቶቹ እንዲህ በማለትም ተማጽኘ ነበር፣ “ብዙዎቹን ወጣቶች፣ ለመድረስ፣ ለማስተማር እና የበለጠ ግንዛቤ እንዲያገኙ ጥረት አድርጉ፡፡” ከዚህ አንጻር ቃሌን ሙሉ በሙሉ በማክበር ስኬታማ ስራ በመሰራቱ የተሰማኝን ኩራት ለመግለጽ እወዳለሁ፡፡

እ.ኤ.አ ዴሴምበር 2013 በአሜሪካ በአርሊንግተን ከተማ ከሰማያዊ ፓርቲ ሊቀመንበር ከይልቃል ጌትነት ጋር በመገናኘቴ ታላቅ ደስታ እና ክብር የተሰማኝ ሲሆን ለወደፊትም ከኢትዮጵያ የአቦሸማኔው (ወጣቱ ትውልድ) ጋር ያለኝን የትግል አጋርነት በጽናት እንደምቀጥል ቃል ገብቻለሁ፡፡

እ.ኤ.አ በዴሴምበር 2013 የአቦ-ጉማሬው (የወጣቱ እና የቀድሞው ትውልድ) ትውልድ በሰላማዊ ትግሉ ሂደት በንቃት ከሚሳተፈው ከኢትዮጵያ አቦሸማኔ ትውልድ ጋር ያለውን የትግል አጋርነት ይፋ አድርጓል፡፡ እንዲህ ብዬ ተናግሬም ነበር፣ “የአቦ-ጉማሬው ትውልድ አባል መሆኔ በኩራት እንድሞላ አድርጎኛል፡፡” በአሁኑ ጊዜ በኢትዮጵያ የአቦ-ጉማሬ ትውልድን “የመፍጠር” አስፈላጊነት ከምንም በላይ ተቀዳሚ ተግባር ሆኖ ተገኝቷል፡፡ የአቦ-ጉማሬው ትውልድ በአፈጣጠሩ የጉማሬው (የቀድሞው ትውልድ) አባል ሲሆን በተግባራዊ ድርጊቱ ግን እንደ አቦሸማኔው (ወጣቱ ትውልድ) የሚያስብ፣ አቦሸማኔውን የሚመስል እና እንደ አቦሸማኔው ሁሉ የክንውን ድርጊቶችን የሚፈጽም የማህበረሰብ ክፍል ነው፡፡ ከዚህም በተጨማሪ የአቦ-ጉማሬው ትውልድ የጉማሬውን (የቀድሞውን ትውልድ) ድክመቶች በሚገባ የተረዳ እና እነዚህን ግድፈቶች በማስወገድ የወጣቱን ትግል ወደ ላቀ የእድገት ምዕራፍ ለማሸጋገር በአንድ ዓላማ ለአንድ ዓላማ የሚሰራ የህብረተሰብ አካል ነው፡፡

የአቦ-ጉማሬው ትውልዶች ድልድይ ገንቢዎች ናቸው፡፡ ወጣቱን ከቀዳሚው ትውልድ የሚያገናኙ ጠንካራ የትውልድ ድልድዮችን የሚገነቡ ናቸውና፡፡ ህዝቦችን በዴሞክራሲ፣ በነጻነት እና በሰብአዊ መብት ጥበቃ የሚያስተሳስሩ ድልድዮችን ይገነባሉና፡፡ በትውልድ ቦታቸው እና አካባቢያቸው ተጠርንፈው የተያዙ ህዝቦችን የሚያገናኙ እና ጥልቅ የጎሳ ሸለቆዎችን ሰንጥቀው የሚያቋርጡ ድልድዮችን  የሚገነቡ ናቸውና፡፡ በቋንቋ፣ በኃይማኖት እና በክልል ተነጣጥለው የተቀመጡ ህዝቦችን የሚያገናኙ ድልድዮችን ይገነባሉና፡፡ ደኃውን ከሀብታም የሚያገናኙ ድልድዮችን የሚገነቡ ናቸውና፡፡ ብሄራዊ ዕርቅ ለማውረድ እና የብሄራዊ አንድነትን ለማምጣት ህዝቦችን የሚያገናኙ ድልድዮችን የሚገነቡ ናቸውና፡፡ በአገር ቤት ውስጥ ያሉትን ወጣቶች በውጭ አገር ከሚኖሩት የዲያስፖራ ወጣቶች ጋር የሚያገናኙ ድልድዮችን ይገነባሉና፡፡

በእ.ኤ.አ 2013፣ የኢትዮጵያ ወጣቶች የእራሳቸውን የኃይማኖት ጉዳይ እራሳቸው በሚፈልጉበት መልክ ማስተዳደር እንዲችሉ እና በእምነታቸው ላይ የሚካሄደውን የመንግስት ጣልቃገብነት በመቃወም በሰላማዊ ሰልፍ ብሶታቸውን በመግለጻቸው ብቻ በገዥው አካል ብዙሀን መገናኛ ዘዴዎች ረበየለሽ እና ግዙፍ የፕሮፓጋንዳ ዘመቻ ተካሂዶባቸዋል፣ በታጠቁ ኃይሎች በዘፈቀደ ከህግ አግባብ ውጭ በቁጥጥር ስር እንዲውሉ ተደርገዋል፣ በየማጎሪያ እስር ቤቶችም እንዲጋዙ ተደርገዋል፡፡ ሀገር በቀል የእስልምና አክራሪዎች እና አሸባሪዎች “የኃይማኖት ጦርነት” በማወጅ በኢትዮጵያ ውስጥ የእስላም መንግስት ማቋቋም ይፈልጋሉ በሚል ሰበብ በህዝብ ዘንድ ለማጋለጥ በማሰብ ገዥው አካል “ጅሃዳዊ ሃራካት” (“የኃይማኖት ጦርነት እንቅስቃሴ“ የሚል ርዕስ በመስጠት ለአንድ ሰዓት የዘለቀ “ዘገባዊ ፊልም” አዘጋጅቶ በአየር ላይ አውሏል፡፡ ያ የሞራል ዝቅጠት የተንጸባረቀበት፣ ሆን ተብሎ ዜጎችን ለማጥቃት በማለም እና ለምንም የማይጠቅም እርባናየለሽ ዘገባዊ ፊልም ለህዝብ በማሳየት የኢትዮጵያ ሙስሊም ወጣቶች በናይጀሪያ በመንቀሳቀስ በህዝብ ላይ ጅምላ ፍጅት በማድረስ ላይ የሚገኘው ቦኮ ሃራም የተባለው ጽንፈኛ እስላማዊ አክራሪ ድርጅት ተከታዮች እና የአልቃይዳ ታዛዦች እና አሸባሪዎች ናቸው በማለት ወጣቶቹን ከህዝብ ነጥሎ ለማሳየት የታለመ ነበር፡፡ ያንን አስቀያሚ እና መቅንየለሽ ዘገባዊ ፊልም በጣም አድርጌ እኮንነዋለሁ፡፡ ምክንያቱም “ውሸቶች ታጭቀውበታል፣ ዓይን ያወጡ ደረቅ ውሸቶች፣ የተወገዙ ውሸቶች እና ሞራለቢስ ቅጥፈቶች፡፡ ‘ጅሃዳዊ ሃራካት’ የእነዚህ የአራት ቀጥፈቶች ጥቅል አንድ መጠሪያ ስም ነው::”