Monday, August 18, 2014

_______ ለአገረ-ኢትዮዽያ _______


በድቅድቅ ጽልመት ውስጥ..
እንደክዋክብቱ..የሚያንፀባርቁ
በሃይለ-ብርሐናቸው..
ገዝፈው የሚታዩ..ጐልተው የደመቁ
በፍርሐት በረሐ..
እንደምንጭ የነጡ..ጠርተው የፈለቁ
በዕውቀት የዘለቁ..
ከድንቁርና ጋር..ቀድመው የተራራቁ
የማይታረቁ..
ከአመጽ..ከብጥብጥ..
ከሁከት..ከነውጥ..
ከሽብር መንፈስም..የማይተዋወቁ
እነሐሳበ-ስንቁ..እነብዕር ትጥቁ
ተቃራኒ ሃይላትን..
በእኩይ ተግባራቸው..ክፉኛ ያስጨነቁ
በማይታሰረው..
በማይበገረው..
ሠርክ በሚኖረው..
ጽኑ መንፈሳቸው..የነጻ አዕምሯቸው
በብርቱ ኃይላቸው..በብሩህ ተስፋቸው

ለገዛ ሕሊናቸው..በመገዛታቸው
ስለሰበ-ልዕልና..
ስለፍትሕ..ርትዕ..በመሟገታቸው
ከሐቅ ጋር ወግነው..በሐቅ መቆማቸው
እስር ቤት የተጣሉ..
በጽልመት ውስጥ ያሉ..ብርሐናት ናቸው::
እስር ያልገታቸው..
ከሐሳበ-አቁዋማቸው..ፈቅ ያላረጋቸው
የእኩያውያን ሴራ..
ተንኮልና ደባ..ያልነቀነቃቸው
ሰላምን ዘማሪ..ሰላማውያን ናቸው::
ምንም እንኩዋ ዛሬ...
ያለተፈጥሯቸው..
ያለምግባራቸው..
ለበጎ ሥራቸው..
የማይገባቸው..
የማይመጥናቸው..
ስምም ቢሰጣቸው..ከግል ጥቅማቸው
ከሆዳቸው ይልቅ..
ለክብረ-ሕሊናቸው..ቅድሚያ የመስጠታቸው
ነገረ-ምሥጢሩ...
ለአገር..ለወገን..አርቀው የሚያስቡ
በሰላም የመነኑ..በሰላም የቆረቡ
ነፍጥ ያላነገቡ..
ፀረ-ጠመንጃዎች..በሃይል የማይመኩ
ሰባኪያን ናቸው..ፍቅርን የሚሰብኩ::
ለትውልድ አርአያ..በበጎ የሚወሱ
በቁም ነገራቸው..ሠርክ የሚጠቀሱ
ለመብት ተሟጋቾች..በስም የሚነሱ
የሰላም..የፍቅር..ሕያው ታጋያውያን
ተምሳሌቶች ናቸው..
ለአገረኢትዮዽያ..ለመላው ኢትዮዽያውያን::
እነኚህ መናኒያን!..
እነኚህ ሰባኪያን!..እነኚህ ቆራቢያን!..
የታሠሩበቱን..የእጅ ሠንሰለቱን
እንደክር በጣጥሰው..የማረሚያ ቤቱን
ፍርግርግ ብረቱን..ቅጥሩን አፈራርሰው
ዛሬም ሳይታክቱ..
ሥርዓተ-እስር ቤቱን..ሕገ-ደንቡን ጥሰው
ስለፍቅር ያወጋሉ..
ስለሰላም ይሰብካሉ..መልሰው..መላልሰው::
* * *

No comments:

Post a Comment