(በላይ ማናዬ)
በአምስት ወራት ብቻ 16 ጋዜጠኞች ኢትዮጵያ ሀገራቸውን ለቅቀው፣ ከስርዓቱ ሸሽተው ወደ ውጭ ሀገር ተሰድደዋል፡፡ አንዳንዶቹ በእውነትም በሀገራቸው ለመስራት ባለመቻላቸውና በመንግስት ክስ የበረገጉ ሲሆኑ ሌሎቹ ደግሞ ሙያቸውን እንደ ሽፋን ተጠቅመው ከሀገር ለመውጣት ያላቸውን ምኞት ያሳኩ ናቸው ማለት እችላለሁ፡፡ (ድፍረት ሳይሆን በትክክል በማውቀው ጉዳይ ላይ ተመስርቼ ነው ይህን የምለው፡፡ ከተሰደዱት ውስጥ በግል የማውቃቸው ስለሚበዙ አቋማቸውን መታዘብ ችዬ ስለነበር የስደታቸው ምክንያት ሊያሳምነኝ ስለማይችል!)
በግሌ ስደትን እንደ መፍትሄ አልቆጥረውም፤ በስደትም ከጋዜጠኝነት መሸሸት የሚቻል አይሆንም፡፡ ጋዜጠኝነት ውስጥ (በተለይ በአምባገነን ስርዓት) የትኛውም አይነት ፈተና አለ፡፡ እስከሞት ድረስ የሚዘልቅ ፈተና፡፡ እስራት፣ ዛቻ፣ ድብደባ፣ ስድብ… ቀላሎቹ ፈተናዎች ናቸው፡፡ ደግሞስ ከማን ነው የሚሸሸው? ከስርዓቱ ወይስ ከራስ እውነት? ከራስ ሸሽቶማ ወዴት ይኬዳል?
ለማነኛውም እስኪ እስክንድር ነጋን ተመልከቱ!
ከሰባት ጊዜ በላይ በመለስ ዜናዊ የአምባገነን መንግስት ታስሯል፡፡ ሀገር ክህደት ከእነሱ ብሶ በሀገር ክህደት ወንጅለው እስር ቤት ልከውታል፡፡ ሲፈታ ሲታሰር፣ ‹ከእንግዲህስ አንተን ማሰር ሰለቸን› ብለውታል፡፡ ግን አልሰለቹም…‹‹አሸባሪ›› ብለው ለ18 ዓመታት ማጎሪያ ቤት እንዲቆይ ፈርደውበታል፡፡ እስክንድር ግን ይህን ሁሉ መከራ ለእውነቱ ሲል፣ ለጋዜጠኝነት ስብዕናው ሲል፣ ለሀገሩና ለወገኑ ሲል…ሁሉንም ነገር ተቀብሎ በጽናት አስተናግዶታል፤ እያስተናገደውም ይገኛል፡፡ ሂዱና ቃሊቱ እስር ቤት ውስጥ እስክንድርን ጠይቁት፡፡ ገና ወደእናንተ ሲመጣ ምትሃታዊ ፈገግታውን ይመግባችኋል፡፡ ደግሞ ውስጡ ሰላም እንደሚሰማው አግኝታችሁ ስታናግሩት ትረዱታላችሁ!
አዎ፣ እስክንድርን ተመልከቱ! ልጁ በእስር ቤት ተወልዷል፡፡ አሁን ከልጁ ናፍቆት ጋር በሰላም መኖርን ጠልቶ አይደለም በእስር የሚማቅቀው፡፡ ስለእውነት፣ ስለሀገር፣ ስለወገን ሲል ነው፡፡ እስክንድር አሁን የተፈረደበትን የ18 አመታት እስር ቆይታ መጨረስ ግድ ከሆነበት ከእስር ሲወጣ ልጁ ናፍቆት 25 ዓመት ይሞላዋል፡፡ ተመልከቱ! እስክንድር ከልጁ ናፍቆት ጋር ከእስር ቤት ውጭ የሚገናኘው ናፍቆት 25 ዓመት ሲሆነው ነው ማለት ነው፡፡
እስክንድር ግን ይህን ሁሉ እያወቀ ላመነበት ነገር መስዋዕትነት እየከፈለ ነው፡፡ እስክንድር ስደትን ቢመርጥ ለእሱ ቀላል ነበር፤ ከእነጭራሹ ወደ ኢትዮጵያ ሳይገባ በሀገረ አሜሪካ በድሎት መኖርም ይችል ነበር፡፡ ይህ ለእስክንድር የሚዋጥለት አልሆነም፡፡ ሀገሩ ኢትዮጵያ የእሱን አስተዋጽኦ ትፈልግ ነበር፤ እናም ለሀገሩ ማድረግ የሚችለውን ለማድረግ አላቅማማም!
ከአቅም በላይ በሆነ ምክንያት ሀገር ጥለው የተሰደዱት ወቀሳ አይሰነዘርባቸው ይሆናል፡፡ ግን ግን የእስክንድርን ጫማ መጫማት ስለምን አቃተን ብለው ራሳቸውን መጠየቅ የሚገባቸው ይመስለኛል፡፡ ርዕዮት ዓለሙ (እመቤቲቱ)፣ ውብሸት ታዬ፣ የሱፍ ጌታቸው፣…የሚከፍሉትን መስዋዕትነት እኛ ለመክፈል ስለምን ይከብደናል ብለው ራሳቸውን መጠየቅ ተገቢ ነው ብዬ አምናለሁ፡፡
እስክንድር የፅናት ምልክት! አሁን ላይ በጋዜጠኝነት ሙያ ኢትዮጵያ ውስጥ ላለን ሰዎች እስክንድር የሙያችን የተግባር መምህር መሆኑን እገነዘባለሁ፡፡ ለዚህም እስክንድርን እንመልከት! ጽናቱን እንጋራ፡፡ እነ ኔልሰን ማንዴላም ትናንት ‹‹አሸባሪዎች›› ነበሩ፡፡ እስክንድር ዛሬ በእነሱ እይታ ‹‹አሸባሪ›› ነው፡፡ እኔ ደግሞ የጽናት ምልክት፣ ላመነበት ሟች መሆኑን አይቻለሁ፡፡ (‹‹አሸባሪ››ን ማድነቅ አሸባሪነት ነው ለካ¡ ቢሆንም ራሴን ሴንሰር አላደርግም፡፡ ያመኑበትን በነጻነት መጻፍ ተምሬያለሁ፤ የምጽፈውን፣ የምናገረውን እኔ እንጂ ሌላ ሰው አይመርጥልኝም!)
አዎ፣ እስክንድር ነጋን ተመልከቱ!
No comments:
Post a Comment