Thursday, July 4, 2013

ዋልያዎቹ 11 ደረጃዎችን አሻሻሉ

በአለም አቀፉ የእግር ኳስ አስተዳዳሪ አካል (ፊፋ) ወርሃዊ የሃገራት የእግር ኳስ ደረጃ ኢትዮጵያ 11 ደረጃዎችን አሻሻለች። ኢትዮጵያ ባለፈው ወር ከነበረችበት 106ኛ ደረጃ በዚህ ወር 95ኛ ደረጃ ላይ መቀመጥ ችላለች። በዚህም ከፈረንጆቹ 2006 በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ የምርጥ 100 ደረጃዎች ውስጥ በ381 ነጥቦች መግባት ችላለች።


የሃገራቱን ደረጃ ስፔን በ1532 ነጥብ ስትመራ ፥ ጀርመን በ1273 ነጥብ ሁለተኛ እንዲሁም የላቲኗ ተወካይ ኮሎምቢያ 4 ደረጃዎችን በማሻሻል በ1206 ነጥቦች ሶስተኛ ደረጃን ይዘዋል።


ቡታን ፣ ሳን ማሪኖ እና የተርክስ እና ሳይኮስ ደሴቶች ደግሞ ያለምንም ነጥብ የደረጃውን ግርጌ ይዘው ይገኛሉ።


በዚህ ወር ይፋ በሆነው የሃገራት ደረጃ ፥ ቀጣዩን የአለም ዋንጫ የምታስተናግደው ብራዚል 13 ደረጃ አሻሽላ 9ኛ ደረጃን ስትይዝ ፤ ጣሊያን 2 ደረጃ አሻሽላ 6ኛ በአንጻሩ እንግሊዝ 6 ደረጃዎችን ወደታች ወርዳለች።


በወርሃዊው ደረጃ መሰረት ሴኔጋል ፣ ስኮትላንድ እና ጊኒ ደረጃቸው በከፍተኛ ሁኔታ ሲያሻሽሉ ፥ የዋልያዎቹ የጳጉሜ 3 ተፋላሚ መካከለኛው አፍሪካ ፣ ጃማይካ እና ታይላንድ እስከ 30 ደረጃዎችን ወደ ታች በመውረድ አስከፊ የደረጃ ሽግሽግ አድርገዋል።

ምንጭ፡ የፊፋ ድረ ገጽ

No comments:

Post a Comment