Saturday, July 6, 2013

በግብፅ ያየነው ህዝባዊ ትዕይንት በኢትዮጵያም እንደምናየው ጥርጥር የለንም!


ሰኔ 29 ቀን 2005 ዓ.ም

በአለማችን እጅግ አስከፊ አምባገነናዊ ስርዓቶች ታይተው አልፈዋል:: በቅርቡ ካየናቸው አምባገነኖች መካከል የግብፁ ሙባረክ፣ የቱኒዚያው ቤን አሊ፣ የሊቢያው ጋዳፊ፣ እንዲሁም የኛው መለስ ዜናዊ ይጠቀሳሉ። ለአምባገነናዊ ሥርዓት መፈጠር በዋናነት ከሚጠቀሱ ምክንያቶች አንዱ ከጥቂት ግለሰቦች ከልክ ያለፈ የበላይነትን የማፍቀር አስቀያሚ ባህሪ የመነጨ በመሆኑ፤ እንደነዚህ ያሉ ሰይጣን ግለሰቦች አሁንም ድረስ በሰው ልጅ መሃል መብቀላቸው አይቀሬ ነው። በተለይ በአፍሪካ የሚገኙ እንደ ኢትዮጵያ ያሉ ሃገራት ውስጥ አምባገነን ሲገረሰስ ሌላ አምባገነን ሊወጣ እንደሚችል አስቀድሞ ሊታሰብበት የሚገባ ጉዳይ ነው።

አምባገነኖች የግለኝነት ባህሪያቸውን በሚገርም መልኩ መቆጣጠር ባለመቻላቸው ምክንያት በሚችሉት አቅምና በሚያገኙት ቀዳዳ ሁሉ የግል ፍላጎታቸውን እውን ለማድረግ መሞከራቸው አይቀሬ ነው። ለዚህም በቅርቡ በግብፅ አምባገነኑ ሙባረክን ለማስወገድ በአንድነት የወጣው ህዝብ የእግር ኮቴ ሳይደርቅ ዳግም አምባገነን ለመሆን ሲሞክሩ የተወገዱት ፕሬዚዳንት ሙርሲን እንደ አብነት ማስታወሱ በቂ ይመስለናል:: የኚህ ሰው ታሪክ በራሱ አምባገነንን ለመጣል በሚደረግ ትግል ውስጥ ሌላ አምባገነናዊ ሥርዓት ዳግም እንዳይመጣ ለማረጋረጥ ሊወሰዱ የሚገቡ ወሳኝ ጥንቃቄዎች ስለመኖራቸው ጠቋሚ ነው። በዚህ ዙሪያም በቅርቡ ሃሳባችንን በስፋት ለማካፈልና ለመወያየት እንሞክራለን።

የሁሉም አምባገነናዊ ሥርዓቶችና በጭቆናቸው ቀንበር ስር ወድቀው የሚሰቃዩ ህዝቦች ብሶቶች ተመሳሳይነት በፅሁፋችን ርዕስ ባነሳነው ሃሳብ ዙሪያ መወያየቱ አስፈላጊ እንደሆነ ይናገራሉ። በተጨማሪም አበው “ነገር በምሳሌ …” እንዳሉት፤ በቅርቡ “የአረብ ስፕሪንግ” ተብሎ የሚጠራው በመካከለኛው ምስራቅና በሰሜን አፍሪካ የተካሄደውን የህዝብ አመፅ እንደ አብነት ማንሳቱ ጠቃሚ ይመስለናል::

ቱኒዚያ የአረብ ስፕሪንግ ጀማሪዋ ሃገር መሆኗ ይታወቃል:: የህዝብ አመፁ በቱኒዚያ በተሳካ ሁኔታ ከተጠናቀቀና ቤንአሊም ከተባረረ በኋላ ይህ የህዝብ አመፅ ወደ ግብፅ ሊሄድ ይችል ይሆን? በሚለው ጥያቄአዊ ሃሳብ ላይ የፖለቲካ ጠበብቶች ብዙ ብለው ነበር:: በተለይ ቱኒዚያ ግብፅ አይደለችም ስለዚህ የህዝብ አመፁ እንደ ቱኒዚያ ሁሉ በግብፅ ሊከሰት አይችልም የሚለውን አስተሳሰብ ደግፈው ምክንያታቸውን ሲደረድሩ የነበሩ ብዙ ናቸው::
ይህንን ቱኒዚያ ግብፅ አይደለችም የሚል ሃሳባቸውን ለማስረዳት ሲጠቅሷቸው ከነበሩት ምክንያቶች መካከል በቱኒዚያ ህዝብ መካከል ያለው የሙስሊሙና የክርስትናው ሃይማኖቶች ውጥረት ግብፅ ካለው እጅግ በጣም ያነሰ ስለሆነ በግብፅ ህዝብ አንድ ሆኖ ሊታገል አይችልም፣ ቤንአሊ እንደ ሙባራክ ጨካኝ አይደለም፣ ሙባራክ ጠንካራ የጦር ሰራዊት አለው ስለዚህ በቀላሉ ከህዝብ መካከል ጥቂቶችን ገድሎ ሊቀጨው ይችላል፣ ቱኒዚያዎች ከግብፆች የበለጠ የተማሩ ናቸው፣ የፌስቡክና ሌሎች የማህበራዊ ሚዲያዎችንም ቱኒዚያዎች በስፋት ተጠቃሚዎች ስለሆኑ ግብፅ ውስጥ እንደ ቱኒዚያ ያለ አመፅ ሊከሰት አይችልም፣ ሌላም ሌላም… እያሉ ትንታኔዎችን ሲያቀርቡ እንደነበር ይታወቃል:: ይታዩአቸው የነበሩት ምክንያቶች ግብፆች በሙባረክ አምባገነናዊ አገዛዝ ለአመታት ብዙ ተረግጠዋል፣ ተጎድተዋል፣ ተበዝብዘዋል፣ እነርሱ በድህነት እየማቅቁ ሳሉ ጥቂት ግለሰቦች በሃብት ሲትረፈረፉ ምንም አላደረጉም የሚሉት ብቻ ነበሩ:: ነገር ግን ፍፃሜው ላይ የታየው እውነታ፤ ግብፆች እጅግ ማራኪ የሆነ የህዝብ ትብብርና ሰላማዊ ተጋድሎን በአደባባይ ለአለም ህዝብ በሚገባ ማሳየታቸውና፤ አስፈሪና ጨካኝ እየተባለ ሲነገርለት የነበረውን የሙባረክ ስርዓት ከትከሻቸው ላይ አሽቀንጥረው መጣል መቻላቸው ነው:: በዚህ ዙሪያ ምሁሮቹና ፖለቲከኞቹ ያለማስተዋል ችላ ብለውት የነበረው ዋናው ቁምነገር የህዝብ እምቅ ሃይል በአምባገነኖች አስፈሪነት ሊሟሽሽ ፈፅሞ እንደማይችል ነበር::

የወያኔ/ኢህአዴግ ቡድን ስልጣን ከተቆናጠጠበት ሰአት ጀምሮ በኢትዮጵያ ህዝብ ላይ እጅግ ስር የሰደዱ ችግሮችንና በደሎችን ሲፈፅም ኖሯል:: የኢትዮጵያ ህዝብ የተጫነበት ህመም ከግብፅና ከቱኒዚያ እጅግ የከፋ ነው:: በአሁኑ ወቅት የኢትዮጵያ ህዝብ 11ኛው ሰአት ላይ እንደሚገኝ ለሁላችንም ግልፅ ነው:: ስለሆነም የኢትዮጵያ ህዝብ ልክ እንደ ግብፆቹ ሁሉ፤ የወያኔ/ኢህአዴግ ጦር ሰራዊት መብዛት፣ ፍቅር እያለው በዘር በሃይማኖት ሳይወድ መከፋፈሉ፣ ጥቂቶች ሲበለፅጉ እርሱ ግን በድህነት መማቀቁ፣ በተቃውሞ ሰልፍ ብሶቱን ለማሰማት በወጣ ቁጥር በአጋዚው የወያኔ ሃይል በተደጋጋሚ በግፍ መጨፍጨፉ፣ መታሰሩና፣ ስቃይን መቀበሉ የህዝብን እምቅ ሃይል በበለጠ ያጎለብትለት እንጂ ሊያዳክመው ፈፅሞ አይቻለውም::

ነገር ግን በግብፅ የተደረገው የተሳካ አመፅ ዝም ብሎ በመላ የመጣ አይደለም:: የአመፁ አስተባባሪዎችና አንቀሳቃሾች እጅግ በጣም በሳል ስራዎችን ስለሰሩ፣ የህዝብን የልብ ትርታ እጅግ አድርገው በመረዳታቸው፣ ቁስሉ ስለተሰማቸው፣ የሙባረክ ስርዓት ሃገርንና ህዝብን እንደሚያጠፋ በመረዳት እውነታውን ለህዝብ ስላመላከቱት፣ ብሎም ህዝብ ወዶና በቃኝ ብሎ ትግሉን እንዲቀላቀል ስላስቻሉት ነው:: የኛም ፖለቲከኞችና የድርጅት መሪዎች ፍፁም የሆነ የአመለካከትና የአካሄድ መሰረታዊ ለውጥ በማድረግ፤ የህዝብ ቁስል ሊያማቸው፣ እውነታውንም ሊነግሩትና፣ ወደ ህዝብ ገብተው ከዚህ ስቃይና መከራ ሊታደጉት ይገባል:: ስለሆነም እጅግ ብዙ ስራዎች እንደሚጠብቃቸው መረዳት ያለባቸው ይመስለናል:: ከግብፆቹ ተምረው እራሳቸውን ካስተካከሉ የምንመኛትን፣ ለሁሉም እኩል የሆነችና፣ የህዝብ የበላይነት የተረጋገጠባት ኢትዮጵያን በቅርቡ እንደምናያት ጥርጥር የለንም::

ድል ለኢትዮጵያ ህዝብ!!!

ስምንቶቹ

No comments:

Post a Comment