Wednesday, January 22, 2014

አንድነት ለጠ/ሚ/ሩና ለአማራ ክልል ፕሬዚዴንት የኢትዮ-ሱዳን ድንበር ጉዳይን አስመልክቶ የፃፈው የማብራሪያ ጥያቄ መልስ ባለማግኘቱ እነሆ ዛሬ ደግሞ ወደ ፓርላመው ዞሯል፡፡


አንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትሕ ፓርቲ (አንድነት)

UNITY FOR DEMOCRACY AND JUSTICE PARTY (UDJ)

ቁጥር አንድነት /811/2ዐዐ6
ቀን 11/ዐ5/2ዐዐ6 ዓም

ለተከበሩ አቶ አባዱላ ገመዳ
ለኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ
የሕዝብ ተወካዮች ም/ቤት አፈ-ጉባኤ
አዲስ አበባ

ጉዳዩ፡- በኢትዮጵያና ሱዳን ድንበር አካባቢ ያለውን የወሰን ጉዳይ ለሕዝብ ግልጽ ስለማድረግ

አንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትሕ ፓርቲ (አንድነት) በአገራችን ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት እንዲሰፍን በሠላማዊ መንገድ ከሚንቀሳቀሱ ፓርቲዎች አንዱ መሆኑ ይታወቃል፡፡ በዚሁ መሠረት በአገራችን የሚካሄዱ ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊና ፖለቲካዊ ጉዳዮችን በቅርብ ይከታተላል፡፡ በዚሁ ክትትል መሠረት በአሁኑ ወቅት ከተከሰቱ አብይ አገራዊ ጉዳዮች አንዱ የኢትዮጵያ ሱዳን ድምበር ይገኝበታል፡፡ ጉዳዩ ለሕዝቡ ግልጽ ያልሆነ አብይ የአገር ጉዳይ በመሆኑና ኃላፊነት ካለበት መንግሥት በማይጠበቅ መልኩ ሂደቱ ከሕዝብ ተሰውሮ በአገር ውስጥ ካለ የግልና የውጭ ሚዲያዎች እንድንሰማ ተገደናል፡፡


ስለሆነም

1. የወሰን ማካለል ጉዳይ በዋነኝነት ታሪካዊ፣ ሕጋዊና የመልካምድር አቀማመጥ ላይ ጥልቅ ጥናት ተደርጎ፤ ሠፊ ሕዝባዊ ውይይት ተካሂዶ የአካባቢውና የኢትዮጵያ ሕዝብ ሂደቱና ውጤቱን በግልጽ ማወቅ ይኖርበታል፡፡

2. ይህ ተግባር የግዛት ሉዓላዊነት ጉዳይ በመሆኑ ሕገ መንግሥታዊ መብትና ግዴታም ጭምር ስለሚሆን አሁን በተለያዩ የውጭ ሚዲያዎች ሱዳን ትሪቢዩንን ጨምሮ እንዲሁም ከአካባቢው ሕብረተሰብ በሚሰማው ሁኔታ መጓዙ አካባቢውን የግጭት ቀጠና ሊያደርገው ስለሚችል የጥንቃቄ ሂደት ያስፈልገዋል፡፡

3. ይህን እጅግና አብይ አገራዊ ጉዳይ ግልጽነት በጎደለው መልክ ምናልባትም ለጊዜያዊ የፖለቲካ ጥቅምም ከሆነ ወደፊት ሊያመጣ የሚችለውን ከባድ ችርግርና አካባቢያዊ ብሎም አገራዊ አለመረጋጋት ስለሚያመጣ ከወዲሁ አይነተኛ መፍትሔ ሊሰጠው እንደሚገባ ፓርቲያችን በጽኑ ያምናል፡፡

በመሆኑም የጉዳዩን አሳሳቢነት ለተከበሩ አቶ ኃይለማሪያም ደሳለኝ የኢፌድሪ ጠቅላይ ሚኒስትርና ለክልሉ ፕሬዚደንት ለተከበሩ አቶ ገዱ አንዳርጋቸው ጥር 7 ቀን 2ዐዐ6 ዓም ደብዳቤ የፃፍን ቢሆንም እነሆ እስከ አሁን ግልጽና ሕገ-መንግሥታዊ መልስ አልተሰጠውም፡፡ ፓርቲያችን አሁንም ቢሆን ድንበሩን በተመለከተ እያንዳንዱ ሂደትና ውሳኔ አብይና የሉዓላዊነት ጉዳይ በመሆኑ የተወካዮች ም/ቤት በጥልቀት ተወያይቶ ለሕዝብ ግልጽ ማድረግ ሕገ-መንግሥታዊ ግዴታው ነው እንላለን፡፡ ይህ ሳይሆን ቀርቶ ለሚፈጠረው ማንኛውም ዓይነት የድንበር ችግር የተወካዮች ም/ቤት ከሁሉም በላይ ከፍተኛ ኃላፊነት ያለበት መሆኑን እያስገነዘብን፣ አሁንም ቢሆን በዚህ አብይ አገራዊ ጉዳይ ላይ በም/ቤቱ አባላት ውይይት ተካሂዶበት ለሕዝብ ይበልጥ ግልጽ እንዲደረግና ሕገ-መንግሥታዊ መፍትሔ እንዲያገኝ በአክብሮት እንጠይቃለን፡፡

ከሠላምታ ጋር

ግዛቸው ሽፈራው (ኢ/ር)
የአንድነት ፓርቲ ፕሬዚደንት

እንዲታወቅ

- ለተከበሩ አቶ ካሣ ተ/ብርሃን የፌዴሬሽን ም/ቤት ፕሬዚደንት
- ለተከበሩ አቶ ኃይለማሪያም ደሳለኝ የኢፌዲሪ ጠቅላይ ሚኒስትር
- ለተከበሩ አቶ ገዱ አንዳርጋቸው የአማራ ክልል ፕሬዚደንት
- ለተከበሩ አቶ ግርማ ሠይፉ የተወካዮች ም/ቤት አባል
- ለመገናኛ ብዙሃን

የቢሮ ስልክ ዐ11 8 4ዐ ዐ8 11 ፖሣቁ 4222

ምንጭ፡ ፍኖተ ነፃነት

No comments:

Post a Comment