Wednesday, November 6, 2013

የመከላከያ የሒሳብ ሰነዶች በዋናው ኦዲተር እንዳይታዩ የሚያደርግ አዋጅ ተረቀቀ


 በ2004 በጀት ዓመት ባልተሟላ ሰነድ ከ3 ነጥብ 2 ቢሊየን ብር ባላይ ወጪ በማድረጉ በፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት ጠንካራ ትችት የቀረበበት የመከላከያ ሚኒስቴር የሒሳብ መዛግብቱን ዋናው ኦዲተርን ጨምሮ ለማንኛውም አካል ሚስጢር ማድረግ የሚያስችለውን ረቂቅ አዋጅ አዘጋጀ።

በሚኒስትሮች ም/ቤት ፀድቆ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሰሞኑን የቀረበው የኢፌዲሪ መከላከያ ሠራዊት ረቂቅ አዋጅ ሰነድ በአንቀጽ 72 ንዑስ አንቀጽ 3 መሰረት አገራዊ ጥቅምንና ደህንነትን ለመከላከል ሲባል እጅግ ጥብቅ ሚስጢር ብሎ የሰየማቸውን የሰው ኃይል ፕሮፋይል፣ የሒሳብ መዝገቦችና ሰነዶች እና የክፍያ ማስረጃዎች ለማንም አካል እንዳይገለጹ ሊያደርግ ይችላል ሲል ደንግጓል።

በአንቀጽ 71 ንዑስ አንቀጽ 2 መሰረት ሚኒስቴሩ ከውጭ አገር ወደ አገር ውስጥ የሚያስገባቸው ለአገር መከላከል ዓላማ የሚውሉ ዕቃዎችና መሳሪያዎች ከጉምሩክ ቀረጥና ታክስ በነጻ እንደሚያስገባ የደነገገ ሲሆን፤ ዕቃዎቹን እንዲያስፈትሽ ወይም ሰነዶቹን እንዲያስመረምር እንደማይገደድ አስቀምጧል።

ሆኖም አንቀጽ 70 ንዑስ አንቀጽ 2 ከላይ ሚኒስቴሩ ከሚከተሉት ምንጮች የሚያገኘውን ገቢ የሚኒስትሮች ምክር ቤትን እያስፈቀደ ለመከላከያ አቅም ግንባታ እንዲውል ያደርጋል። በዚህ መሰረት የመከላከያ ተቋማት በሠላም ጊዜ የሚኖራቸውን የማምረትና አገልግሎት የመስጠት አቅም ለገቢ ማስገኛ ተግባር እንዲውል በማድረግ የሚገኘውን ገቢ፣ ለመከላከያ ጠቀሜታ የማያስፈልጉ ንብረቶችን በማስወገድ የሚገኘው ገቢ፣ በተቆጣጣሪ ባለስልጣንነት ከሚመራቸው ድርጅቶች የሚገኘውን የትርፍ ድርሻ እና ከሠላም ማስከበር ስምሪቶች የሚገኘው ገቢ በዋናው ኦዲተር ወይም እርሱ በሚሰይማቸው ኦዲተሮች በየዓመቱ እንዲመረመር እንደሚያደርግ በረቂቅ አዋጁ ተደንግጓል።

የፌዴራል ዋናው ኦዲተር ባለፈው ዓመት ሚያዚያ ወር ማጠናቀቂያ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባቀረበው የ2004 ዓ.ም የኦዲት ሪፖርት መሰረት የመከላከያ ሚኒስቴር ባልተሟላ ሰነድ 3 ነጥብ 5 ቢሊየን ብር ወጪ ካደረጉ ዘጠኝ ያህል የመንግስት ተቋማት መካከል 3 ነጥብ 2 ቢሊየን ብር በማስመዝገብ የላቀ ድርሻ መያዙ ይፋ ከተደረገ በኋላ የመከላከያ ሚኒስትሩን አቶ ሲራጅ ፈጌሳ ጨምሮ ሌሎች የመከላከያ ሹማምንት ሪፖርቱን ሳይቀበሉት ቀርተዋል። ጠ/ሚኒስትር ኃ/ማርያም ደሳለኝም በዚያው ወቅት በፓርላማ መድረክ ተገኝተው ባደረጉት ንግግር በየትኛውም አገር የመከላከያ ሚስጢር የተጠበቀ መሆኑን በመጥቀስ በቀጣይ የመከላከያን ሚስጢሮች በጠበቀ መልኩ ኦዲት ለማካሄድ የሚያስችል ሕግ እንደሚወጣ ቃል መግባታቸው ይታወሳል።

ምንጭ፡ ሪፖርተር ጋዜጣው 

No comments:

Post a Comment