ከፕሮፌሰር አለማየሁ ገብረማርያም
ትርጉም በነጻነት ለሀገሬ
የዴሞክራሲን ስርዓት ወደ ጎን አሽቀንጥሮ በመጣል ወደ ዘራፊነት የአገዛዝ ስርዓት ሲሄድ ሊገኝ የሚችለው የስርዓት ዓይነት ምንድን ነው?
ሌላ ምንም ነገር ሳይሆን የወሮበላ ዘራፊነት የአገዛዝ ስርዓት ነው፡፡
ወሮበላ ዘራፊዎች በይስሙላው የቅርጫ ምርጫቸው አሸነፍን ብለው በማወጅ እንደገና በድጋሜ የፖለቲካ ስልጣኑን ሲጨብጡ የበለጠ ዘራፊዎች ይሆናሉ፡፡ ዘራፊዎች እንደገና ሲመረጡ ስልጣኑን በድጋሜ በመቆጣጠር የወሮበላ የዘራፊዎች የአገዛዝ ስርዓትን ያስፋፋሉ፡፡
ዴሞክራሲ .የህዝብ፣ በህዝብ ለህዝብ የተቋቋመ መንግስታዊ ስርዓት ከሆነ የወሮበላ የዘራፊነት መንግስታዊ አገዛዝ ደግሞ የዘራፊዎች፣ በዘራፊዎች ለዘራፊዎች የተቋቋመ መንግሰታዊ የወሮበላ የዘራፊዎች አገዛዝ ነው፡፡
የወሮበላ የዘራፊዎች መንግስታዊ የአገዛዝ ስርዓት ዓይነት ዋና መለያ ባህሪው ተመራጮች በይስሙላ የዴሞክራሲያዊ የምርጫ ሂደት እንደተመረጡ በማስመሰል ህዝብን በማደናገር ስልጣንን ከተቆጣጠሩ በኋላ የጫካ ወሮበላ ቡድኖች የመንግስትነት ስልጣንን በብቸኝነት በመያዝ ቢከተት ቢከተት የማይሞላውን ቀዳዳውን ኪሳቸውን እና የእነርሱ አጫፋሪዎች እና ሎሌዎች ኪስ ለመሙላት ሲባል ሌት ቀን የሚዘርፉበት የስርዓት ዓይነት ነው፡፡
እራሱን ህዝባዊ ወያኔ ሀርነት ትግራይ (ህወሀት) እያለ የሚጠራው ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ እ.ኤ.አ ግንቦት 24/2015 በአፍሪካ ደረጃ የመጀመሪያ የሆነውን የወሮበላ የዘራፊነት የአገዛዝ ስርዓት የፓርላማ የቅርጫ ምርጫን አካሂዷል፡፡
እ.ኤ.አ ግንቦት 27/2015 አሶሸትድ ፕሬስ የተባለው ዓለም አቀፍ የዜና ወኪል እንዲህ የሚል ዘገባ አስነብቧል፣ “ገና በመጀመሪያዎቹ የድምጽ ቆጠራ ውጤት ገዥው አምባገነን ፓርቲ ህዝባዊ ወያኔ ሀርነት ትግራይ (ህወሀት) ከ442 የፓርላማ መቀመጫዎች ውስጥ ሁሉንም በማሸነፍ መቶ በመቶ ውጤት አግኝቷል፡፡ በጠቅላላው ከተያዙት 547 የፓርላማ ወንበሮች ውስጥ እነዚህን ቀሪዎችን 105 የፓርላማ መቀመጫዎች በመቆጣጠር የወያኔ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ መቶ በመቶ አሸነፍኩ እንደሚል በምንም ዓይነት መልኩ ለማንም የሚያጠራጥር ጉዳይ አይደለም።
የወያኔ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ የዘራፊ ወሮበላ አገዛዝ እ.ኤ.አ በ2010 ተደርጎ በነበረው የይስሙላ ሀገር አቀፍ የቅርጫ ምርጫ መቶ በመቶ ለማሸነፍ ጥቂት ነበር የቀረው፡፡ እነዚህ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስቦች 99.6 በመቶ ድምጽ አገኘን በማለት መቶ ለመሙላት ቁርጥራጭ ቁጥሮች ብቻ ቀርተዋቸው ነበር፡፡
በዓለም ላይ ለመጨረሻ ጊዜ ምርጫን መቶ በመቶ ማሸነፍ የተቻለው እ.ኤ.አ በ2002 ነበር፡፡ አሁን በህይወት የሌለው አምባገነኑ ሳዳም ሁሴን የ11,445,638 መራጮችን ድምጽ አንድ በአንድ በማሸነፍ 99.9 በመቶ ሳይሆን መቶ በመቶ አሸነፍኩ ብሎ አምባገነናዊ ስርዓቱን አስቀጥሎ ነበር፡፡ ያው በነበር ቀረ እንጅ፡፡
የወያኔ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ አባላት አቦ የምስራች እንኳን ደስ አላችሁ፡፡ ለዓለም ህዝብ እንከን የሌለውን ታምራዊ የይስሙላ የቅርጫ ምርጫ አሳያችሁ፡፡ ጎሽ ጀግናው ወያኔ! ምንም ዓይነት ሀፍረት የማይሰማው ፈጣጣው ፍጡር! የሌባ አይነደርቅ መልሶ ልብ አድርቅ!
እውነት ለመናገር የወያኔ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ እንከን የለሽ የቅርጫ ምርጫ ቃልኪዳኑን በሚገባ ፈጸመ፡፡
እ.ኤ.አ የካቲት 2015 የወያኔ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ የይስሙላ አሻንጉሊቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ የእርሱ ፓርቲ ህጎችን በማውጣት በስራ ያዋለ ስለሆነ በቀጣይ እንከንየለሽ ምርጫ እናካሂዳለን ብሎ ነበር፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ በእውነቱ ቃሉን በተግባር ላይ የሚያውል የተግባር ሰው ነው፡፡ እ.ኤ.አ ግንቦት 24/2015 በተካሄደው ቅርጫ (ምርጫ አላልኩም) እንከን የለሽ ቅርጫ አካሂዷል፡፡
ዊንስተን ቸርቺል በአንድ ወቅት እንዲህ ብለው ነበር፣ “ከሌሎች ከሁሉም ስርዓቶች በስተቀር ዴሞክራሲ መጥፎው የመንግስት አወቃቀር ስርዓት ዓይነት ነው፡፡“
እኔ ከዚህ ጋር በፍጹም አልስማማም፡፡ የወሮበላ የዘራፊነት አገዛዝ መጥፎው ዓይነት የመንግስት አወቃቀር ስርዓት ነው፡፡ አራት ነጥብ!
ዴሞክራሲ እንደ አንድ መንግስታዊ ስርዓት የተጣረሰ ታሪክ አለው፡፡
ጥንታዊዎቹ የአቴንስ የከተማ መንግስት ዜጎች ዴሞክራሲ የሚለውን ቃል ከክርስቶስ ልደት በፊት በ5ኛው ክፍለ ዘመን ላይ ለዓለም ህዝብ አስተዋወቁ፡፡ ዓላማው ህዝባዊ አገዛዝ ለማስፈን ታስቦ ነበር፡፡ ተራው ህዝብ እራሱን በእራሱ የማስተዳደር ስርዓትን ይለማመዳል፡፡
አገዛዙ ህዝቡን በህዝብ መሰብሰቢያ አደባባዮች ላይ በመሰብሰብ በአቴናውያን ነጻ ወንዶች ውይይት እና ውሳኔዎችን የማሳለፍ ስራዎች ይሰሩ ነበር፡፡ እያንዳንዱ ዜጋ የፖለቲካ ውሳኔ ከማስተላለፍ ጋር በተያያዘ መልኩ መሳተፍ የሚያስችል ግላዊ ቀጥተኛ ዴሞክራሲያዊ መብት ነበረው፡፡
የአቴናውያን ዴሞክራሲ ከአምስት ኗሪዎች ለአንዱ ብቻ አገልግሎት የሚሰጥ ነበር፡፡ ሴቶች፣ ባሮች እና የውጭ ዜጊች የዜግነት መብት አልነበራቸውም፡፡ እነዚህ የህብረተሰብ ክፍሎች ከዴሞክራሲያዊ ስርዓቱ ሂደት የተገለሉ ነበሩ፡፡
ከአቴናውያን የዴሞክራሲ ስርዓት ጋር ጎን ለጎን ታዋቂ የሆነ የመንግስት አወቃቀር ዓይነት በሮም የከተማ መንግስት ተግባራዊ ሆኖ ነበር፡፡ ሮማውያን ያንን ዓይነት የመንግስት አወቃቀራቸውን የህዝብ ጉዳይ በማለት ይጠሩት ነበር፡፡
የሮማውያን የህዝብ ጉዳይ በህዝብ አደባባዮች ላይ ተግባራዊ ይደረግ ነበር፡፡ በዚያ የከተማ መንግስት አማካይነት መድረክ ተሰጥቶት ተግራዊ ይደረግ ነበር፡፡
እንደ አቴናውያን ሁሉ ሮማውያንም የዜጎችን ተሳትፎ መገደብ ጀመሩ፡፡
አቴናውያን ከሚያደርጉት በሚጻረር መልኩ የሮማውያን ዜግነት በተፈጥሮ እና በባሮች ጌቶች አማካይነት ለባሮች ነጻነት በመስጠት በትውልድ ይረጋገጥ ነበር፡፡
ሮማውያን ወካይ ወይም ደግሞ ቀጥተኛ ያልሆነ ዴሞክራሲ እንዲተገበር ጥረት ያደርጉ ነበር፡፡ ዜጎች በቀጥታ በመንግስታዊ የአስተዳደር መዋቅሩ ውስጥ ከመሳተፍ ይልቅ ለእነርሱ ውሳኔዎችን እንዲያሳልፉላቸው ተወካዮችን ይመርጡ ነበር፡፡ የመጨረሻው የፖለቲካ ስልጣን ከህዝቡ ላይ እንዲቀር ይደረግ ነበር፡፡ ሆኖም ግን ህዝቡ ተወካዮቹን ለተወሰነ ጊዜ እንዲያገለግሉት በመምረጥ ውክልና ይሰጣቸው ነበር፡፡
አብዛኞቹ የሮማውያን ዜጎች እንደ አቴናውያን ሁሉ በህዝብ ጉዳይ ላይ በቀጥታ አይሳተፉም ምክንያቱም ከመድረኮቹ አቅራቢያ አይኖሩም ነበርና ነው፡፡ ሙሉ በሙሉ ይገለሉ ነበር፡፡
የሮማውያን ዓይነት የዴሞክራሲ ውክልና የምዕራቡን ዓለም ተወካዮች ለዘመናት ስቦ ቆይቷል፡፡
በ17ኛው እና በ18ኛው ክፍለ ዘመኖች የሬፐብሊካን መንግስትነት ዓይነት አወቃቀር ቀጥተኛ ያልሆነን ዴሞክራሲ መሰረት በማድረግ በአሜሪካ፣ በእንግሊዝ እና በሌላው የዓለም ክፍል መስፋፋት ጀመረ፡፡
እ.ኤ.አ በ1176 የተካሄደውን የአሜሪካንን አብዮት ተከትሎ የግለሰብ ነጻነቶችን፣ የንብረት የባለቤትነት መብት እና የህግ የበላይነት እንዲከበር የሚሉትን በስፋት ባካተተ መልኩ አሜሪካኖች ሊበራል ዴሞክራሲን መሰረቱ፡፡
እንግሊዞች እ.ኤ.አ በ1668 ከተካሄደው ታዋቂው አብዮት በኋላ ፓርላሜንታዊ ዓይነት የውክልና ዴሞክራሲን ህጋዊ አደረጉ፡፡ የእነርሱ የውክልና ዴሞክራሲ ችግኝ በአንቀጽ 61 በማግና ካርታ እ.ኤ.አ በ1215 ተተከለ፡፡
የዓለም የመጀመሪያ የሆነው ወሮበላ የዘራፊ አገዛዝ ስርዓት መመሰረት፣
በስልጣኔ በኖሩ መንግስታት ታሪክ እስከ አሁን ድረስ ምንም ዓይነት ወሮበላ የዘራፊ አገዛዝ ስርዓት በፍጹም የለም፡፡
የወያኔ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ በዓለም የመጀመሪያ የሆነውን የወሮበላ የዘራፊ አገዛዝ ስርዓት የመሰረተ መሆኑን መሞገት እፈልጋለሁ፡፡
የወያኔ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ የምርጫ ዴሞክራሲን እንደመሳሪያ በመጠቀም እና አታላይነትን በተላበሰ መልኩ መርሆዎችን እና ተሞክሮዎችን በማዛባት የወሮበላ የዘራፊ አገዛዝ ስርዓት በመመስረት እነዚህ የተደራጁ ወሮበላ ዘራፊዎች የፖለቲካ መሳሪያ በማድረግ ብቸኛው ዓላማቸው የመንግስት ስልጣንን በመጠቀም የብሄራዊ ግምጃ ቤቱን ገንዘብ እየዘረፉ ወደ ውጭ ሀገር ለማስወጣት፣ የሀገሪቱን ሀብት ለመዝረፍ እና እጅግ ግዙፍ የሆነውን የሀገሪቱን ሀብት በመዝረፍ የእራሳቸውን እና የሎሌዎቻቸውን ጥቅም እና ስልጣን ለማጠናከር አበርትቶ እየሰራ ነው፡፡
በምዕራቡ ዓለም የገንዘብ እርዳታ እና ሙሉ ድጋፍ ባለፈው ሩብ ክፍለ ዘመን ከ10 ቢሊዮን ዶላር በላይ በመመደብ የወያኔ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ አገዛዝን በማጠናከር ወያኔው የወሮበላ ዘራፊነት አገዛዝ ስርዓትን ለመመስረት ችሏል፡፡
ለዓለም የመጀመሪያ የሆነውን የወሮበላ የዘራፊነት አገዛዝ ስርዓት በመመስረቱ ረገድ የወያኔ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ የውክልና ዴሞክራሲን በማዋረድ፣ ወደኋላ እንዲንሸራተት በማድረግ የፖለቲካ ስልጣንን ክህዝብ ስልታዊ በሆነ መልኩ በመቀማት በጣም ጥቂት ለሆኑ ሆኖም ግን በጥብቅ በተደራጁ የጫካ ሽፍቶች ታሪካዊ የሆነ ጉልህ ድርሻን አበርከተዋል፡፡
በርካታዎቹ አንባቢዎቼ የአፍሪካ ወሮበላ የዘራፊነት አገዛዝ ለሚለው ህልዮቴ እንግዳ አይደሉም፡፡ ከዚህ አንጻር የአፍሪካ አምባገነኖች ዝግመታዊ ከፍተኛ ደረጃው ወሮበላ የዘራፊነት አገዛዝ እንደሆነ የክርክር ጭብጤን አቅርቤ ነበር፡፡
ይህንን ድርጊት መሰረት በማድረግ የወያኔ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ የወሮበላ ዘራፊነት አገዛዝን ከፍ ወዳለ እና የዘራፊነት አገዛዝ ወደሚለው አዲስ ምዕራፍ ያሻገረው በመሆኑ ጉዳይ ላይ የክርክር ጭብጤን ላቀርብ እችላለሁ፡፡
የወያኔ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎችን ለማዳከም፣ አገዛዙን ህጋዊ ለማድረግ እና የፖለቲካ መሳሪያውን በመጠቀም፣ ሸፍጥ በመስራት እና የፖለቲካ ጨዋታ በመጫወት ወያኔው እንዴት አድርጎ ውስብስብ እና ከባድ የሆነ የምርጫ ሂደትን እንደሚያዛባ ግልጽ ነው፡፡ የወያኔ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ አባላት በእድሜ ከመግፋታቸው አንጻር እና በተግባር ምንም ዓይነት ትምህርት የሌላቸው የደናቁርት ስብስብ ቢሆኑም በፖለቲካው መሰላል ላይ የመውጣታቸው እና ስኬታማ የመሆናቸው ጉዳይ የሚያስደንቅ ሁኔታ ነው፡፡
በኢትዮጵያ የወሮበላ ዘራፊነት አገዛዝ ስርዓት መነሳሳት ልዩ ጥናት፣
የቀድሞው የኢህአዴግ/ህወሀት ፕሬዚዳንት የዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ ማስረጃ፣
እ.ኤ.አ በ2009 ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ በኢትዮጵያ ህዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኢህአዴግ) አገዛዝ የቀድሞው የኢትዮጵያ ፕሬዚዳንት የነበሩት የወያኔ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ ወሮበላ ዘራፊነት አደረጃጀት እና ተግባሩን በማስረጃነት ያቀርባሉ፡፡ (የወያኔ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ እራሱን ኢህአዴግ ብሎ በመጥራት ማንነቱን ለመደበቅ ጥረት አድርጓል፡፡ በትክክል ኢህአዴግ ግንባር ነው፣ ሆኖም ግን ግንባርነቱ ለኢትዮጵያ ህዝቦች ሳይሆን ለወያኔ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ አባላት ብቻ ነው፡፡)
ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ በምዕራብ ኢትዮጵያ በኦሮሚያ በቀለም ወለጋ ዞን በደምቢዶሎ እ.ኤ.አ በ2009 በግል የተወካዮች ምክር ቤት መቀመጫ በመያዝ በድርጅቱ ውስጥ ያለውን ሁኔታ በተግባር አስመስክረዋል፡፡
በዚያን ወቅት ዶ/ር ነጋሶ በደምቢዶሎ የምርጫ ቅስቀሳ ሲያደርጉ በነበረበት ጊዜ የወያኔ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ ምርጫን የወሮበላ ዘራፊነት መሳሪያ አድርጎ በመጠቀም በስልጣን ላይ እንደ መዥገር ተጣብቆ ለመኖር የሚያደርገውን ጥረት በጨረፍታ አመላክቷል፡፡
በዚያን ጊዜ ዶ/ር ነጋሶ በደምቢዶሎ የምርጫ ቅስቀሳ በማድረግ ላይ ነበሩ፡፡ ወዲያውኑም በአካባቢው የሚገኙት የድርጀቱ ታዛዥ ሎሌዎች አማካይነት እንዳይቀሰቅሱ እና እንዲባረሩ ነው የተደረገው፡፡
የአካባቢው የወያኔ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ ተወካዮች ክሀዝብ ጋር ምንም ዓይነት ስብሰባ ማድረግ እንደማይችሉ ወይም ደግሞ ምንም ዓይነት ውይይት ላይ መሳተፍ እንደማይችሉ ነበር የተነገራቸው፡፡
ዶ/ር ነጋሶ በዚህ ድርጊት ላይ እምነት በማጣት እና በሀሳባቸው በመጽናት የአካባቢውን የንግዱን ማህበረሰብ አባላት፣ የአካባቢውን የማህበረሰብ መሪዎች፣ መምህራንን፣ የጤና ባለሙያዎችን፣ የኃይማኖት መሪዎችን፣ የቀበሌ አመራሮችን፣ የግል ምሁራንን፣ የዩኒቨርስቲ ተማሪዎችን፣ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ሰራተኞችን እና የኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግረስ አባላት እና ደጋፊዎችን በመሰብሰብ የግል ውይይት ለማድረግ ጥረት አድርገው ነበር፡፡
ሆኖም ግን ማንኛውም ግለሰብም ይሁን ቡድን ከዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ ጋር በመሰብሰብ ውይይት ወይም ደግሞ ንግግር የሚያደርግ ከሆነ የወሮበላው ገዥ አካል የጸጥታ ኃይል ዒላማ እንደሚሆን ተከታታይነት ያለው ማስፈራሪያ ሲደረግ ነበር፡፡
የገዥው አካል የደህንነት መሳሪያ አሻንጉሊቶች በእያንዳንዱ አባወራ ቤት ገብተው ህዝቡን መውጫ ቀዳዳ በማሳጣት እያተራመሱ እንዳሉ በውል የተገነዘቡበት ወቅት ነበር፡፡
ዶ/ር ነጋሶ በዚያን ወቅት በደምቢዶሎ በመገኘት ባስተዋሉት እና በደረሰባቸው ድርጊት አጅግ በጣም አዝነው እና ተክዘው ሁኔታውን ለህዝብ ግልጽ አድርገው ነበር፡፡
በአካባቢው ያለው የወያኔ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ ፓርቲ የደህንነት መዋቅር ከጨቋኙ የደህንነት መሳሪያ ጋር በማበር ያንን የመሰለ ኢዴሞክራሲያዊ የሆነ ድርጊት ሲፈጽሙ እንደነበር በወቅቱ ለህዝብ ይፋ አድርገው ነበር፡፡
አባወራዎች፣ ጎጦች፣ መንደሮች፣ ወረዳዎች፣ ከተሞች እና ዞኖች ሁሉ በአንድነት ለአንድ ዓላማ ለትዕዛዝ እና ለቁጥጥር በሚያመች መልኩ በኮሚሳሪያት ቁጥጥር ስር ተጠርንፈው የህዝብ ጠላት ናቸው ብለው የሚያስቧቸውን ኃይሎች ከጨዋታ ውጭ በማድረግ ምርጫው እንዲካሄድ በማድረግ እንከን የለሽ የቅርጫ ምርጫ ውጤቶችን አግኝተው ነበር፡፡
ለማስፈራራት፣ ለማሸማቀቅ፣ የስለላ መረጃዎችን ለመሰብሰብ እና የተቃዋሚ ፓርቲዎችን እንቅስቃሴ ከጥቅም ውጭ ለማድረግ ሲባል ረዥም እጆች ያሏቸው እና ፍተኛ የሆነ የመረጃ እና ሚስጥር አቀባይ ፖሊስ መሳይ ጆሮ ጠቢዎች እንደነበሯቸው ግልጽ አድርገዋል፡፡
የአካባቢው የደህንነት መዋቅር ከኦህዴድ/ኢህአዴግ ፓርቲ ጋር እጅ እና ጓንት በመሆን በደንቢዶሎ ሲሸርቡት የነበረው ደባ ፍጹም መረኑን የለቀቀ የአምባገነኖች ስራ እንደነበር የተስተዋለበት ሁኔታ ነበር፡፡ እንደ ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ ገለጻ ከሆነ በደምቢዶሎ በፖለቲካ እና በደህንነት መዋቅሩ መካከል ምንም ዓይነት የስራ ክፍፍል አልነበረም፡፡ ሁለቱም ተዳብለው እንደ አንድ የፖለቲካ ፓርቲ በመስራት በአጠቃላይ ህዝቡን ብቻ ሳይሆን አካባቢውን ሁሉ በመቆጣጠር እና በአካባቢው የፖለቲካ እና ሌሎች ጉዳዮችም ላይ የበላይነታቸውን ያሳዩበት ሁኔታ ተፈጥሮ እንደነበር በግልጽ ተስተውሏል፡፡
የወያኔ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ ውስብስብ የምርጫ ሂደት በዶ/ር ነጋሶ እይታ እና ምስክርነት እንዲህ የሚል አስደንጋጭ ሁኔታን ፈጥሮ አልፏል፡ የኦህዴድ/ኢህአዴግ የእራሱ እና የወረዳ አስተዳደሩ እንዴት እንደተዋቀሩ ማወቁ በጣም ጠቃሚ ነገር ነው፡፡ በደምቢዶሎ የቀለም ወለጋ ዞን የኦህዴድ/ኢህአዴግ ጽ/ቤት አለ፡፡ ይህ ጽ/ቤት መረጃዎችን ትዕዛዞችን አዲስ አበባ ከሚገኘው የክልሉ ቢሮ ይቀበላል፡፡ መልዕክቶችን ወደ ዝቅተኛው መዋቅር በማስተላለፍ የፓርቲውን የፕሮፓጋንዳ እና የድርጅታዊ ስራዎችን ይሰራል፡፡ ይህ ጽ/ቤት በእያንዳንዱ መንደር፣ ትምህርት ቤት እና የጤና ተቋማት ቅርንጫፎች አሉት፡፡ እነዚህ ቅርንጫፎች እንደገና መሰረታዊ ወደሆኑ ህዋሶች የከፋፈላሉ፡፡ የእነዚህ ህዋሶች ቅርንጫፎች በደጋፊ ቡድኖች፣ በእጩ ቡድኖች እና በሙሉ አባላት ቡድኖች ይታገዛሉ፡፡
ከዚህም በተጨማሪ ፓርቲው ህዝቡን በወጣቶች፣ በሴቶች እና በአነስተኛ ብደር እና ቁጠባ ተቋማት ማህበራት በመጠቀም ከፍተኛ የሆነ ጥብቅ ቁጥጥር እና በቀላሉ የፓርቲውን የፕሮፓጋንዳ ስራዎችን ለማስተላለፍ ይጠቀምበታል፡፡ የደምቢዶሎ ከተማ በልዩ የወረዳ ከተማ አስተዳደር ስር የተዋቀረች ከተማ ናት፡፡ የከተማው አስተዳደር በአራት ትናንሽ ከተሞች የተከፈለ ነው፡፡ እ.ኤ.አ በ2008 ምርጫ ከመካሄዱ በፊት ከተማው በሰባት ቀበሌዎች ተዋቅሮ ነበር፡፡ እያንዳንዱ ቀበሌ ተጠሪነቱ ለወረዳ ካውንስል የሆነ 15 የካቢኔ አባላትን አካትቶ ይይዛል፡፡ ኦህዴድ/ኢህአዴግ የቅድመ ካውንስል ተመራጭ እጩዎችን ስም ዝርዝር ለቀበሌ ካውንስል አቅርቦ እንዲጸድቅ ያስደርጋል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ 24 ቀበሌዎችን ያካተተ ሳዮ የገጠር ወረዳ አለ፡፡ የሳዮ ወረዳ አስተዳደር በደምቢዶሎ ከተማ የመቀመጫ ወንበር አለው፡፡ እነዚህ ሁሉም የፓርቲው ተጠቋሚዎች ናቸው፣ እናም ለፓርቲው ዓላማ ግብ መምታት ያለ የሌለ ኃይላቸውን ሁሉ በመጠቀም ጥረት ያደርጋሉ፡፡ አራቱ መንደሮች አንዳንድ ጊዜም ክፍለ ከተማ እየተባሉ የሚጠሩት እያንዳንዳቸው የየራሳቸው ካውንስል አላቸው፡፡ አንድ ካውንስል 300 አባላትን አካትቶ የያዘ ነው፡፡ አባላቱ እ.ኤ.አ በ2008 የተመረጡ ናቸው፡፡ ከሰዎች ጠይቄ እንዳገኘሁት መረጃ ከሆነ ሁሉም እነዚህን እጩዎች ፓርቲው አስቀድሞ የጠቆማቸው እንደሆኑ ግንዛቤ ወስጃለሁ፡፡ ቀበሌው በእራሱ የእራሱ ካቢኔ አለው፣ እንደዚሁም እነዚህ የካቢኔ አባላት የፓርቲው አባላትም ናቸው፡፡ ቀበሌዎች እንደገና ወደ ትናንሽ የዞን ክፍፍሎች ይከፋፈላሉ፡፡ እነዚህ ትናንሽ የዞን ክፍፍሎች ጋሬ ወደሚባሉ አነስተኛ ክፍፍሎች ይከፋፈላሉ፡፡ በእያንዳንዱ ዞን 17 ጋሬዎች አሉ፡፡
የፓርቲው የፕሮፓጋንዳ እና ድርጅታዊ ኮሚቴ በዞን፣ በወረዳ እና በቀበሌ አስተዳደራዊ ህንጻ ውስጥ ይገኛል፡፡ ፓርቲው ለሚጠቀምባቸው የቢሮ ክፍሎች ኪራይ አይከፍልም፡፡ የኮሚቴው አባላት የፓርቲ ካድሬዎች ናቸው፣ ሆኖም ግን ወርሀዊ ደመወዛቸው እና አበል የሚከፈላቸው ከህዝብ ገንዘብ በአስተዳደሩ በኩል ነው፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ሁሉም የመንግስት ሰራተኞች የፓርቲው አባላት ናቸው፡፡ አባላት በየወሩ የሚያዋጡት የፓርቲው መዋጮ የሚሰበሰበው በወረዳው የገንዘብ እና ኢኮኖሚ ልማት ጽ/ቤት ሲሆን ክፍያውም ሰራተኛው በወሩ መጨረሻ ደመወዙን ሲቀበል የሚቆረጥ ነው፡፡ የፓርቲው ባለስልጣኖች የመንግስት ማቴሪያሎችን፣ አላቂ ዕቃዎችን እና የስራ መሳሪያዎችን እንዲሁም የባለስልጣን ተሸከርካሪዎችንም ጭምር ይጠቀማሉ፡፡ ፓርቲው የከተማ እና የቀበሌ የመሰብሰቢያ አዳራሾችን ያለምንም የኪራይ ክፍያ በነጻ ይጠቀማል፡፡ በጤና እና በትምህርት ቤት ተቋማት የሚገኙትን የመሰብሰቢያ አዳራሾች እና ክፍሎች ያለምንም ክፍያ በፈቃደኝነት ለፓርቲው አገልግሎት እንዲውሉ ይደረጋል፡፡ ይኸ ተሞክሮ ከዞን ጀምሮ እስከ ጋሬ ድረስ ባሉት ደረጃዎች ላይ ተግባራዊ ይደረጋል፡፡ ሆኖም ግን የኦህዴድ/ኢህአዴግ ተቃዋሚ የሆኑት የፖለቲካ ፓርቲዎች እነዚህን አዳራሾች እና ለቢሮ የሚያገለግሉ ክፍሎች ከግለሰቦች ወይም ደግሞ የህዝብ አዳራሾችን ያለ ኪራይ በነጻ ብቻ ሳይሆን ክፍያ ከፍለውም ቢሆን ለመከራየት ፍጹም አይፈቀድላቸውም፡፡ ለትምህርት ቤቶች እና ለወረዳ ግንኙነት የሚያገለግሉ ቴሌቪዥኖችን ከተቋቋሙበት ዓላማ በተጻረረ መልኩ ለፓርቲው ፕሮፓጋንዳ አገልግሎት እንዲውል ይደረጋል፡፡
ዶ/ር ነጋሶ ከዚህም በተጨማሪ ጨቋኙን የደህንነት ከባቢ አየር በሚያስፈራ የቋንቋ አጠቃቀም መሰረት እንዲህ ይገልጹታል፡
ኦህዴድ/ኢህአዴግ ከእርሱ ጋር ሊወዳደር የሚችል ሌላ የፖለቲካ ፓርቲ በአካባቢው እንዲንቀሳቀስ እንደማይፈቀድ የወሰነ ይመስላል…ይህ አይነት አካሄድ ማንም ለጉብኝት ወደ አካባቢው የሚመጣ ጸጉረ ልውጥ ሰውን ይጨምራል፡፡ ለእንግድነት የሚመጡ ሰዎች በድብቅ እና በስውር ክትትል ይደረግባቸዋል፣ ከየት እንደመጡ፣ ለምን እንደመጡ፣ ማንን ለመጎብኘት እንደመጡ እና ምን እንደተናገሩ ሳይቀር ምርመራ ይደረግባቸዋል… በአካባቢው የሚኖሩ ሰዎች እና ከእነዚህ ጎብኝ እንግዶች ጋር ግንኙነት አላቸው ተብለው የሚጠረጠሩ ሰዎች በደህንነቶች ተጠርተው ይጠየቃሉ፡፡ ከእኔ ሁኔታ አንጻር ከእህቴ ባለቤት ጋር የቆየሁ ሲሆን ከደምቢዶሎ እና ከነቀምት የደህንነት ኃይሎች የስልክ ጥሪዎችን ተቀብሏል፡፡ እኔ ደምቢዶሎ ለምን እንደመጣሁ፣ በቀጣዩ ምርጫ ዝግጅት ወይስ ለሌላ ጉዳይ እንደመጣሁ ተጠይቋል፡፡
የዩኤስ ኤይድ/USAID ጎብኝ ቡድንም እንደዚሁ ተመሳሳይ መስተንግዶን እንዲያስተናግድ ተደርጓል፡፡ ቡድኑ ከተመለሰ በኋላ በርካታ የደህንነት ሰዎች የደንቢዶሎን ቤቴል መካነ እየሱስ ቤተክርስቲያን ኃላፊ የሆኑትን ጥያቄ አቅርበውላቸዋል…ከቤተክርስቲያን መሪዎች አንዱ በዞኑ አሰተዳደር ጽ/ቤት ተጠርተው ከአዲስ አበባ ስለመጡት ጎብኝዎች ዝርዝር ጥያቄዎች ቀርበውላቸዋል፡፡
የኦሮሞ ፌዴራሊስት ዴሞክራቲክ ንቅናቄ/OFDM እና የተወካዮች ምክር ቤት አባል የሆኑትን ዶ/ር በላይነሽን ለመጠየቅ የመጡ ሰዎች በቁጥጥር ስር እንዲውሉ ተደርገው በርካታ ጥያቄዎች ሲቀርቡላቸው ከቆዩ በኋላ ይህም አልበቃ ብሎ ከ24 እስከ 48 ሰዓታት ለዘለቀ ጊዜ ወደ እስር ቤት ተወርውረው ታስረዋል፡፡ ሌሎችም የምክር ቤቱ አባላት የሆኑ ሰዎች እየተፈለጉ እና እየታደኑ ነበር፡፡
የቀድሞው የኢህአዴግ/ህወሀት የመከላከያ ሚኒስትር የነበሩት የአቶ ስዬ አብርሀ አስረጅነት፣
እ.ኤ.አ በ2010 የተካሄደውን ሀገር አቀፍ የቅርጫ ምርጫ ትንተና በሚመለከት የቀድሞው የኢህአዴግ/ህወሀት የመከላከያ ሚኒስትር የነበሩት አቶ ስዬ አብርሀ የወያኔ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ 99.6 በመቶ ድምጽ በማግኘት ምርጫውን እንዴት ማሸነፍ እንደቻለ በጣም ልዩ የሆነ ምልከታ አድርገው ነበር፡፡ (የ2010ን ምርጫ፡ ወደኋላ መለስ ብሎ መመልከት፡ ዓለም አቀፍ የኢትዮጵያ ጥናት መጽሄት/see Election 2010: A Retrospective, International Journal of Ethiopian Studies, vol. 5. No. 2 (Fall/Winter 2010 – 2011) pp. 53 – 78)
ስዬ እንዲህ የሚል የክርክር ጭብጥ አቅርበው ነበር፡
እ.ኤ.አ በ2010 ተካሂዶ ስለነበረው ሀገር አቀፍ ምርጫ ሊታመን የማይችል እውነታ እራሱን የኢትዮጵያ ህዝቦች አብዮታዊ ግንባር (Ethiopian People’s Revolutionary Democratic (EPRDF) የሚጠራው ገዥ ፓርቲ ማሸነፉ አልነበረም፡፡ ያ አዲስ ነገር ሳይሆን ሲጠበቅ የነበረ ጉዳይ ነው፡፡ ይልቁንም በጣም የሚያስደንቀው ወያኔው በ99.6 በመቶ የማሸነፉ ጉዳይ ነው፡፡ እንደዚህ ያለ ድል በአመክንዮ ላይ ተመስርቶ ፍርድ ለሚሰጥ አዕምሮ ሊታሰብ የማይችል እና ማብራሪያም ሊሰጥበት የማይችል ነገር ነው፡፡ ሌላው ቀርቶ እራሳቸው የኢህአዴግ አባላት እንኳ የምርጫው ውጤት በድል አድራጊነት መጠናቀቁ ከተገለጸ በኋላ ሊያሳፍር በሚችል መልኩ እራሳቸውን ዝቅ አድርገው ሲሸማቀቁ ተስተውለዋል፡፡ ሊታመን የማይችለው የድል ህዳግ በአጋጣሚ የተገኘ አልነበረም፡፡ ያ ውጤት የተገኘው እንዲሁ በዘፈቀደ ሳይሆን መሪ ዕቅድ ተዘጋጅቶለት ስንት ደባ እንዲሰራ ተደርጎ ነው፡፡ ያልታሰበ የዘመቻ እና የምርጫ ስልት በመያዝ ህጋዊውን መንገድ ህገወጥ ከሆነው ነገር ጋር በማጣረስ ስነምግባር ከኢስነምግባር ጋር በማቀላቀል የተሰራ ሸፍጥ ነበር፡፡
እ.ኤ.አ በ2010 ስዬ የወያኔ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ ብቸኛ ምሽገ ነው በሚለው በሰሜን ኢትዮጵያ በትግራይ ክልል የምርጫ ቅስቀሳ ዘመቻ አካሂደው ነበር፡፡
ስዬ የወያኔ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ ዋና የምርጫ ዕቅድን በማስመልከት እንዲህ የሚል የመከራከሪያ ጭብጥ አቅርበው ነበር፣ “እ.ኤ.አ በ2008 የህወሀት ዋናው ስልት የድርጅቱን መዋቅራዊ አደረጃጀት ማጠናከር እና የገጠሩን አካባቢ ከፍተኛ የሆነ የደህንነት መረብ እና የፖለቲካ መዋቅር በመዘርጋት ከፍተኛ ቁጥጥር ማድረግ ነበር፡፡ በዩናይድ ስቴትስ በጥቂት አካባቢዎች ታሪካዊ በሆነ መልኩ ሲተገበር እንደነበረው በስልጣን ላይ ላለው ፓርቲ በርካታ የምርጫ ድምጽ መስጠት ነው፡፡“
ስዬ እንዲህ የሚል ገለጻ አድርገው ነበር፣
ለህወሀት የፖለቲካ ፓርቲ እና የመንግስት ስራ ምንም ዓይነት ልዩነት የላቸውም፡፡ የፓርቲ ስራዎች በመንግስት ጽ/ቤት ፋሲሊቲዎች፣ ትራንስፖርት፣ አበል፣ ወዘተ አማካይነት ከመንግስት ስራ ጋር አብሮ ጎን ለጎን እየተሰራ ይገኛል፡፡ ህወሀት ለፖለቲካ ስራ ስብሰባ ሲጠራ የመንግስት ስራ ነው የሚል የውሸት ሽፋን ይሰጣል፡፡ በዚህም መሰረት ለዚህ ስብሰባ የሚወጣው ወጭ በዋናነት ከሴፍቲ ኔት/safety net እና ከመሰረታዊ የማህበራዊ አገልግሎቶች ጥበቃ/protection of basic services ፕሮግራሞች ከተመደበው በጀት በመውሰድ ከታሰበለት ዓላማ ውጭ ለፓርቲ ፖለቲካ ክፍያ ይፈጸማል፡፡“ በስብሰባዎች ላይ እንዲሳተፉ የሚጋበዙ የቀበሌ እና የመንደር ባለስልጣኖች ከዚሁ ገንዘብ የውሎ አበል እንዲከፈላቸው ይደረጋል፡፡ የቀበሌው ሊቀመንበር የተወሰነ ደመወዝ ተከፋይ ባይሆንም እንኳ ከፍተኛ የሆነ የውሎ አበል ግን ያገኛል፡፡ ይህ ሰው በስብሰባዎች፣ ወርከሾፖች፣ ሴሚናሮች እና በመሳሰሉት የሚሳተፍ ከሆነ ቢያንስ በወር ለ15 ቀናት ያህል በውሎ አበል የሚቆይ ይሆናል፡፡ በዚህም መሰረት ለእንደዚህ ዓይነት ስብሰባ መጋበዝ ጠንካራ የሆነ ውድድር እና አድሏዊነት እንዲፈጸም ያደርጋል፡፡ በእንደዚህ ያሉ ስብሰባዎች ላይ ለመሳተፍ የሚመጡ ሰዎችን ለመምረጥ የቀበሌው ሊቀመንበር ትልቅ ሚና አለው፡፡ በዚህም መሰረት ሊቀመንበሩ ከተመረጡት ሰዎች ከእያንዳንዳቸው ላይ ኮሚሽን ይቀበላል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ የቀበሌው ሊቀመንበር ማን የህዝብ እርዳታ እና ጥቅማጥቅም ማግኘት እንዳለበት የመወሰን ስልጣን አለው፡፡ በነጻ ጉልበት ስም ተጠቃሚ በመምረጥ ገንዘብ ይቀበላል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ የቀበሌ አስተዳዳሪ ህገ ወጥ በሆነ መልኩ መሬት ከአንድ አርሶ አደር በመውሰድ ለሌላ በመስጠት እንደዚሁም ለደን ጥበቃ ተብሎ የተከለለን መሬት ለቀበሌው አስተዳዳሪ እገዛ ለሚያደርጉ ሰዎች እንዲሰጥ ይደረጋል፡፡ በእነዚህ እና በሌሎች መንገዶች ደመወዝ የማይከፈለው የቀበሌው አስተዳዳሪ ደመወዝ ከሚከፈለው የቀበሌው ስራ አስኪያጅ/ manager ሁለት እጅ የበለጠ ያገኛል፡፡ በወያኔ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ ውሰጥ እያንዳንዱ ሰው በተነገረው መሰረት የሚሰራ ከሆነ እንደዚህ ያሉት የሙስና ድርጊቶች በትዕግስት ይታለፋሉ፡፡ በዚህም መሰረት የአካባቢ ባለስልጣኖች ስልጣኖቻቸውን ያለአግባብ ከህግ አግባብ ውጭ መጠቀም ይጀምራሉ፣ እናም በገበሬው ኪሳራ እነርሱ እራሳቸውን ያበለጽጋሉ፡፡
የወያኔ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ ምርጫን ለመቆጣጠር እና የድምጽ ውጤትን ለማሳወቅ የወረዳውን አስተዳደራዊ መዋቅር ይጠቀማል፡፡ እንደ ስዬ አባባል ከሆነ፡
በወረዳ ደረጃ ያለው የመንግስት መዋቅር የወረዳ ምክር ቤቶችን እና የወረዳ ካቢኔዎችን ያካትታል፡፡ የወረዳ ምክር ቤት የአባላት መጠን በመጠን ከቦታ ቦታ የሚለያይ ቢሆንም በአጠቃላይ መልኩ ሲታይ ከ150 እስከ 200 ይይዛል፡፡ በቆላ ተምቤን ወረዳ ስለአካባቢው ጉዳይ ህግ ማውጣት ስራቸው ያደረጉ 159 የወረዳ ምክር ቤት አባላት ነበሩ፣ ሆኖም ግን በተግባር ሲታይ ምክር ቤቱ ለመንግስት ፖሊሲዎች ተግባራዊነት በመቆም ያስፈጽማል፡፡
ሁሉም የምክር ቤቱ አባላት የህወሀት/ኢህአዴግን ካርድ የያዙ ናቸው፡፡ የወረዳ ካቢኔ ከ15 እስከ 17 አባላት ያሉት ሲሆን የሚመራውም በወረዳ አስተዳዳሪው ነው፡፡ ይህ የወረዳ አስተዳዳሪ በዝቅተኛው የመንግስት መዋቅር ከፍተኛው ባለስልጣን ሲሆን የእርሱ ስራ ልክ እንደ ጠቅላይ ሚኒስትሩ እና እንደ ክልል ፕሬዚዳንቶች ነው፡፡ ምክትል አስተዳዳሪው ለገዥው ፓርቲ እና ለመንግስት የፕሮፓጋንዳ ኃላፊ ነው፡፡ በወረዳ የአደረጃጀት መዋቅር መሰረት 3ኛ እና 4ኛ ዋነኛ ሚና ተጫዋቾች የአካባቢውን ፖሊስ እና ሚሊሻ እንዲሁም የግብርና ኃላፊውን የሚቆጣጠር እና ለአስቸኳይ ጊዜ እርዳታ፣ ለስርጭት እና በሴፍቲ ኔት ፕሮግራም በዩኤን ወኪሎች፣ በዩኤስ ኤአይዲ፣ በዓለም ባንክ፣ በአውሮፓ ህብረት፣ ወዘተ…የሚሰጡትን እርዳታዎች የሚያዝዙበት ይሆናል፡፡
ስዬ ከዚህም በተጨማሪ እጅግ በጣም ብዙ የሆነ ገንዘብ ወደ ወረዳ ባለስልጣኖች እንዲፈስ እየተደረገ እነዚህ ሰዎች የፓርቲ አባላትን፣ የደህንነት እና የፖለቲካ አመራሩን ስራዎች እንዲያስተባብሩ ይደረጋል፡፡
እንደ ስዬ ገለፃ ከሆነ ምንም ቢሆን የወያኔ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብን ከማገልገል መታቀብ የለበትም፡፡ እንዲያውም ምሁራንም እንኳ ሳይቀሩ የወያኔ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብን እንዲያገለግሉ ይገደዳሉ፡፡
በገጠሩ አካባቢ የትምህርት ቤት ርዕሰ መምህሩ በአካባቢው በጣም የተማረ ሰው ተደርጎ ስለሚቆጠር ለወያኔ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብም የአገልጋይነት ዒላማ ነው፡፡ አብዛኛውን ጊዜ በርካታ ሚናዎችን ይጫወታል፡፡ የትምህርት ጉዳዮች ኃላፊ በመሆን በካቢኔው ውስጥ ቦታውን ይዞ ይቀመጣል፡፡ በትምህርት ቤቱ የፓርቲው ድርጅት ዋና ኃላፊ ነው፡፡ እንደዚሁም ደግሞ የቀበሌው መራጭ ኮሚቴ ኃላፊ ነው፡፡ ለምሳሌ እኔ ድምጽ በሰጠሁበት ቀበሌ ተሻገር ሀጎስ የተባለው ርዕሰ መምህር በእንደዚህ ያሉት ዘርፈ ብዙ የኃላፊነት ቦታዎች ላይ አገልግሏል፡፡
የወያኔ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ መቶ በመቶ የምርጫ ድል አድራጊነት ሚስጥር፣
የወያኔ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ አጠቃላይ የቅርጫ ምርጫ ድል አድራጊነት ማስረጃ አስገዳጅ እና አሳማኝ ነው፡፡ የወያኔ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ ወሮበላ የዘራፊ አገዛዝ ድምጽ ለመግዛት እና በድምጽ ላይ ደባ ለመስራት በጣም የተወሳሰበ የአሰራር ሂደትን ይከተላል፡፡ መቶ በመቶ የሆነ የምርጫ ድምጽ አሸናፊነትን ለመቀዳጀት ወያኔው በርካታ መንገዶችን ይጠቀማል፡፡ ከእነዚህም ውሰጥ፡
የህዝብን ሀብት፣ የመገልገያ መሳሪያዎች፣ ማሽነሪዎችን ወይም ደግሞ ግላዊ ለሆነ ትክክል ላልሆነ የምርጫ ስራ አለአግባብ በስራ ላይ ማዋል፣
የህዝብ መሰብሰቢያ አዳራሾችን እና ቦታዎችን ለግል የፖለቲካ ፓርቲ መሰብሰቢያ እና ከህግ አግባብ ውጭ ለምርጫ ውድድር ማድረግ እና ስልጣንን ከህግ አግባብ ውጭ መጠቀም እና ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች ግን እንደዚህ ያለውን ጥቅም ማግኘት እንዳይችሉ መከልከል፣
የህትመት እና የኤሌክትሮኒክ ሜዲያዎችን ከህግ አግባብ ውጭ በመጠቀም ነጻውን ፕሬስ እና ሀያሲ ጋዜጠኞችን መጨቆን፣
የተጭበረበረ ድምጽ ለማግኘት ሲባል ገንዘብ መክፈል፣ እርዳታን፣ ማዳበሪያን፣ መንገዶችን፣ ፕሮጀክቶችን፣ ወዘተ ከህግ አግባብ ውጭ ለደጋፊዎቻቸው መስጠት እና ይቃወሙናል ብለው የሚጠረጥሯቸውን መከልከል፣
የተቃዋሚ ፓርቲ መሪዎችን፣ ደጋፊዎችን እና የነጻውን ፕሬስ አባላት ማሸማቀቅ፣ ማስፈራራት፣ ማሰር እና ማሰቃዬት፣
እ.ኤ.አ ግንቦት 2015 የወያኔ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ የቅርጫ ምርጫ ነበረው፡፡ ይህንንም ቅርጫ መቶ በመቶ በማሸነፍ ድልን ተቀዳጅቷል!
አቤ ሊንኮልን በእርግጠኝነት የሚከተለውን ምልከታ አድርገው ነበር፣ “ሁሉንም ሰዎች ለጥቂት ጊዜ ልታታልል ትችላለህ፣ ጥቂት ሰዎችን ደግሞ ሁልጊዜ ልታታልል ትችላለህ፡፡ ሆኖም ግን ሁሉንም ሰዎች ሁልጊዜ ስታታልል ልትኖር ከቶውንም አትችልም፡፡“
አቤ ይህንን መጨመር ነበረባቸው፣ “ሆኖም ግን እራስህን ሁልጊዜ እና ሁልጊዜ ልታታልል ትችላለህ፡፡“
የወያኔ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ 99.6 በመቶ እንዲሁም 100 በመቶ አሸነፍን እያሉ እራሳቸውን ያታልላሉ (የሞቱትን ድምጽ ሰጭዎች በማካተት)፡፡
እ.ኤ.አ በ2010 ተካሄደ የተባለውን የይስሙላ ምርጫ ስልት እንዳለ ወስዶ በመድገም የወያኔ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ እ.ኤ.አ በ2015 አሁን ባሳለፍነው ግንቦት ወር አጠቃላይ ድል አድራጊነቱን አውጇል፡፡ በእርግጠኝነት በ2010 ተካሄደ የተባለው የቅርጫ ምርጫ ውጤት መቶ በመቶ ለመሆን የቀረችው ህዳግ የአንድ ፐርሰንት አራት አስረኛ የሆነች ቁርጥራጭ ቁጥር ነበረች፡፡ 99.6 በመቶ ውጤት መቶ በመቶ ከሚለው ብዙም ልዩነት የለውም፡፡
እ.ኤ.አ በ2015 የወያኔ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ የቅርጫ ምርጫውን የእራሱ አድርጓል፣ ፐውዞታል እናም ለእርሱ በሚሆን መልኩ አመሳስሎታል፡፡
እ.ኤ.አ በ2015 የወያኔ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ የቅርጫ ምርጫውን የእራሱ አድርጓል፣ ፐውዞታል እናም ለእርሱ በሚሆን መልኩ አመሳስሎታል፣ የቅርጫ ቦርዱን እና የመራጮች መመዝገቢያ ስርዓቱን የግል መጠቀሚያ ዕቃ አድርጎታል፡፡
እ.ኤ.አ በ2015 የወያኔ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ የእራሱ የግሉ የሆነ የቅርጫ ምርጫ ስነ ምግባር ኮድ አዘጋጅቶ ተግባራዊ አድርጓል፡፡
እ.ኤ.አ በ2015 የወያኔ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ የእራሱን የቅርጫ ምርጫ ታዛቢዎች አዘጋጅቶ አሰማርቷል፡፡
እ.ኤ.አ በ2015 የወያኔ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ ከእራሱ ጋር እንዲወዳደሩ የተለጣፊ የተቃዋሚ ፓርቲዎችን እራሱ መርጦ፣ እራሱ አጽድቆ፣ እራሱ አሰልጥኖ እና እራሱ የዳረጎት እርጥባን ሰጥቶ ኑ ተወዳደሩኝ ብሎ አሰማርቷቸዋል፡፡
እ.ኤ.አ በ2015 የወያኔ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ የቅርጫ ምርጫው ነጻ፣ ዴሞክራሲያዊ፣ ፍትሀዊ እና በህዝብ ዘንድ ታማዕኒነት ያለው ነው ብሎ እራሱ አውጇል፡፡
እ.ኤ.አ በ2015 የወያኔ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ የቅርጫ ምርጫውን የድምጽ ውጤት ያለምንም ሀፍረት እራሱ ቆጥሮታል፡፡
እ.ኤ.አ በ2015 የወያኔ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ የቅርጫ ምርጫውን ማን እንዳሸነፈ ወስኗል፡፡
እ.ኤ.አ በ2015 የወያኔ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ እንከን የለሽ የቅርጫ ምርጫ አካሂዷል፡፡
እ.ኤ.አ በ2015 የወያኔ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ የእራሱ የግሉ የሆነ ዴሞክራሲ ፈጥሯል፡፡
እ.ኤ.አ በ2015 የወያኔ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ መቶ በመቶ የቅርጫ ምርጫ ድል ተቀዳጅቷል፡፡ በዚህም መሰረት የእራሱ የሆነ ልዩ ዴሞክራሲ/ብራንድ መስርቷል፡፡ (በዴሞክራሲ ላይ መቀለድ ይሏል ይህ ነው፡፡)
እ.ኤ.አ በ2015 የወያኔ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ እራሱን የዓለም የመጀመሪያው የወሮበላ የዘረፋ አገዛዝ እውቅናን በማግኘት ታዋቂነትን ተቀዳጅቷል!
ኢትዮጵያ በክብር ለዘላለም ትኑር!
ሰኔ 3 ቀን 2007 ዓ.ም
No comments:
Post a Comment