በአብርሃ ደስታ
ዓረና ትግራይ ፓርቲ ህዝባዊ ስብሰባ ጠራ
ፓርቲው ለእሁድ ሓምሌ 14, 2005 ዓም በመቐለ ማዘጋጃቤት አዳራሽ ህዝባዊ ስብሰባ መጥራቱ ተሰምቷል። ፓርቲው ‘አሉ’ በሚላቸው የህዝብ ችግሮች (ኑሮ ውድነት፣ የወጣቶች ስደት፣ የግብር አከፋፈል ችግሮችና የሙስና ሁኔታ፣ የመልካም አስተዳደር እጦትና የመሳሰሉት የህዝብ ችግሮችና በዓረና ትግራይ የሚቀርቡ አማራጭ መፍትሔ ሓሳቦች ከመቐለና አከባቢው ህዝብ ነዋሪዎች መወያየት እንደሚፈልግ አስታውቋል። ሁላችን ተጋብዘናል፤ እንሳተፋለን።
ስንሳተፍ ግን ምን እንጠብቃለን? ዓረናዎች የህዝብ ችግሮችና የመፍትሔ አማራጫቸውን ሲነግሩን የህወሓት ደጋፊዎች (መሳተፋቸው አይቀርም ከሚል ነው) ደግሞ ‘ እናንተ ዓረናዎች እኮ ያው ናችሁ። ህወሓት ነበራቹ። ያኔ ለውጥ አላመጣችሁም።’ የሚል የተለመደ የፕሮፓጋንዳ ስትራተጂ መጠቀማቸው አይቀርም።
እኔም እላቸዋለሁ፡ አዎ! አብዛኛው የትግራይ ህዝብ የህወሓት ታጋይ ነበር፤ የህወሓት ፓርቲ አመራር አባል ግን አልነበረም። እነኚህ የዓረና አባላትም የትግራይ ህዝብ አባላት እስከሆኑ ድረስ የህወሓት ታጋዮች ነበሩ። የህወሓት ታጋይ መሆን በራሱ ስሕተት አይደለም። ህወሓት እንደ ትግልና እንደ ገዢ መደብ የተለያዩ ናቸው።
ግን ደግሞ የህወሓት ደጋፊዎች (አብዛኞቹ የህወሓት አባላት) ዓረናዎችና ህወሓቶች ‘ያው አንድ’ መሆናቸው የሚያምኑ ከሆነ ለህወሓት የሚሰጡትን ድጋፍ ለዓረናም መስጠት አለባቸው ማለት ነው፤ ምክንያቱም ‘ያው አንድ’ አይደሉም እንዴ? በአንድ በኩል ‘ዓረናና ህወሓት ያው ናቸው፤ አብረው ነበሩ። ስለዚህ ዓረና ፓርቲ ከህወሓት የተለየ ለውጥ ሊያመጣ አይችልም’ ብለው ይከራከራሉ። በሌላ በኩል ደግሞ ዓረና ትግራይ ፓርቲን በጠላትነት በመፈረጅ ህወሓትን የሚቃወም ሰው ፀረ የትግራይ ህዝብ ትግል አስመስለው ያቀርባሉ።
አዎ! እነኚህ ዓረናዎች የህወሓት ታጋዮች ነበሩ። የህወሓት የአመራር አባላት የነበሩ የዓረና ትግራይ አባላት ግን በቁጥር ሦስት ብቻ ናቸው። አንደኛ እነዚህ ሦስት ሰዎች ከህወሓት አመራርነት ወደ ዓረና አመራርነት ስለተቀየሩ ዓረናና ህወሓት ‘ያው አንድ’ ናቸው ሊያስብል አይችልም፤ ምክንያቱም የዓረና አባላት ሦስት ብቻ አይደሉም።
ሁለተኛ እነኚህ ሦስት ሰዎች (ወይም ማንኛውም ሰው) ህወሓት ወይ ዓረና ወይ ሌላ የሚያደርጋቸው የፖለቲካ አስተሳሰባቸው (አመለካከታቸው) ነው። ሦስቱ የአመራር አባላት ከህወሓቶች ‘ያው አንድ’ ቢሆኑ ኑሮ ለምን ህወሓትን ለቀው ወጡ? ከፍተኛ ባለስልጣናት አልነበሩምን? ለምን ስልጣናቸውን ጠብቀው ‘ተከብረው’ አልኖሩም? ከህወሓቶች ያው ቢሆኑ ኑሮ ለምን በህወሓት መሪዎች ይሰደባሉ? ይዋረዳሉ? ይታሰራሉ?
በአንድ በኩል ‘ህወሓት የነበሩ ናቸው፣ በስልጣን በነበሩበት ግዜ ለውጥ አላመጡም’ ይባላል። በሌላ በኩል ደግሞ ‘ሰዎቹ ዓረና የሚል የተቃዋሚ ፓርቲ የመሰረቱት ስልጣን ፈልገው ነው’ የሚል የመከራከርያ ነጥብ አለ። ሁለቱም ነጥቦች እርስበርሳቸው ይጣረሳሉ። የህወሓት አመራር አባላት በነበሩበት ግዜ ከፍተኛ ባለስልጣናት ከነበሩ እንዴት ስልጣን ፈልገው ከህወሓት ወተው ሌላ ፓርቲ መሰረቱ ሊባል ይችላል? የስልጣን ጥማት ቢኖራቸው ኑሮ እንደ አንዳንዶቹ ‘ይቅርታ’ ጠይቀው ወደ ፓርቲው ተመልሰው ገብተው ስልጣን አይዙም ነበር?
‘ከህወሓት ጋር አብረው በሰሩበት ግዜ ለውጥ አላመጡም’ በሚል ሓሳብ ግን እስማማለሁ። አዎ! ተገቢውን ለውጥ አላመጡም። ነገር ግን በህወሓት የፖለቲካ ስትራተጂ መሰረት ለውጥ ወይ ውድቀት የሚያመጣው ግለሰብ ሳይሆን ድርጅቱ እንደስርዓት ነው። የህወሓት የፖለቲካ አሰራር ‘ዴሞክራቲክ ሴንትራሊዝም’ ነው። በ‘የተማእከለ ዴሞክራሲ’ (Democratic Centralism) እሳቤ መሰረት ማንኛውም የፓርቲው አባል (ወይ አባላት) ድርጅቱን የሚቃወም ሓሳብ ማራመድ አይችልም። የፓርቲው አሰራር መተቸት የሚቻለው በድርጅቱ ውስጣዊ ግምገማ ብቻ ነው። ተቃውሞውን ለህዝብ ይፋ ከሆነ የተቃወመውን ሰው ከድርጅቱ ይባረራል።
እነኚህ ከህወሓት የለቀቁ የአመራር አባላት ተቃውሟቸውን ሲገልፁ ቆይተዋል። ግን ለህዝብ ይፋ አልሆነም ነበር። በመጨረሻ ግን ከዓቅም በላይ ተወጥሮ ፈነዳ። መቃወማቸው ታወቀ። እንደዉጤቱም ፓርቲው ለቀው ወጡ። በዴሞክራቲክ ሴንትራሊዝም አመራር አባላት የማይደግፉትን አሰራር ጭምር እንዲተገብሩ ይገደዳሉ። የማያምኑበትን አሰራር ለመተግበር ሲገደዱ በስራቸው ዉጤታማ ላይሆኑ ይችላሉ። በህወሓት የፖለቲካ አሰራር መሰረት ለውጥ የሚያመጡ ወይ የማያመጡ ግለሰቦች ሳይሆኑ ድርጅታዊ ስርዓቱ ነው (የግለሰቦች ሚና የማይናቅ ቢሆንም)። እናም ህወሓትን የምንቃወመው ስርዓቱን እንጂ ግለሰቦችን አይደለም።
ስለዚህ የዓረና አመራሮች በህወሓት እያሉ ተገቢውን ለውጥ ስላላመጡ አሁንም (በዓረና ፓርቲ) ለውጥ ሊያመጡ አይችሉም የሚል ድምዳሜ ትክክል አይመስለኝም። ምክንያቱም ሰዎቹ ‘ያው’ ቢሆኑ እንኳን የስርዓቱ አሰራር የተለያየ ነው (ወይም ተቀይሯል)። የህወሓትና የዓረና የፖለቲካ አሰራር የተለያየ ነው፣ በዓረና ፓርቲ ዴሞክራቲክ ሴንትራሊዝም አይሰራም። ዓረና ለውጥ ሊያመጣ ይችላል።
ህወሓት እየተከተለው ያለው የፖለቲካ ፍክክር ስትራተጂ ጤናማ አይደለም። የዓረና አመራሮች ያው ህወሓት የነበሩ ናቸው ካልን የህወሓት አባል የነበረ ሁሉ ከሌላ ፓርቲ ጋር መቀላቀል አይችልም ማለት ነው? (ይህን አቅጣጫ የራሳቸው የህወሓት አባላትን ፖለቲካ መብት የሚጋፋ ነው።) የህወሓት አባል የሆነ (ወይ የነበረ) ሰው የፈለገውን የፖለቲካ አመለካከት የመያዝ መብት የለውም ማለት ነው? የትግራይ ህዝብ ትግል ለነፃነት ካልሆነ ለሞት ነበር ማለት ነው? የህወሓት ታጋዮች የፈለጉትን ፓርቲ እንዲመሰርቱና እንዲደራጁ ካልተፈቀደላቸው የትግላቸው ውጤት ታድያ ምንድነው? ሌላ ዓፈና? በትግሉ የተሳተፉ ሰዎች እንዲህ መብታቸው ከተነፈጉ በትግሉ ያልተሳተፈ (በግዜ ምክንያት) አዲሱ ትውልድ የመደራጀት መብቱ እንደሚጠበቅለት በምን እርግጠኞች መሆን እንችላለን? ህወሓት ለነ ገብሩ አስራት ያልበጀች ለኔ ትጠቅማለች ብዬ እንዴት ልመን?
የህወሓት መሪዎች ለህዝብ እንደሚሰሩ ይነግሩናል። በተግባር ግን ህዝብ አማራጭ የፖለቲካ ድርጅት እንዳይኖረው ይጥራሉ። በግብፅ የምናየው የፖለቲካ ቀውስ የሙባረክ መንግስት ያጠፋው ጥፋት ውጤት ነው። የሙባረክ መንግስት የተደራጁ የፖለቲካ ፓርቲዎች እንዳይኖሩ ያደርግ ነበር። አሁን ችግሩን መፍታት የሚችል የተደራጀ ሃይል ጠፋ። ህዝቡ ቀውስ ውስጥ ገባ። ህወሓትም በተመሳሳይ መንገድ እየተራመደ ነው። ህዝብ አማራጭ ፓርቲ እንዳይኖረው የተለያዩ ተፅዕኖዎች እየፈጠረ ‘ከኔ በኋላ ሰርዶ አይብቀል’ እያለን ነው።
ህወሓት ለህዝብ ከቆመ ለምን ህዝቡ እንዲደራጅ አይፈቅድለትም? መደራጀትኮ ሓይል ይፈጥራል (‘ዉዳበ ሓይሊ እዩ!’ እንዶ ይብሉና አይነበሩን ግዲ!)። ህዝብ አማራጭ ፖለቲካዊ ድርጅት ሊኖረው ይገባል።
ዓረና ፓርቲን ስንገመግም ‘አመራር አባላቱ እነማን ነበሩ?’ በሚል መሆን የለበትም። የትናንት አስተሳሰባቸው ስሕተት መሆኑ ተረድተው ሌላ የተሻለ ፖለቲካዊ አመለካከትና አሰራር ይዘው መጥተው ሊሆኑ ይችላሉ (ወይ ላይሆኑ ይችላሉ)። ‘ሌላ የተሻለ አሰራር አላቸው ወይስ የላቸውም ?’ የሚል ጥያቄ ለመመለስ የፖለቲካ ፕሮግራማቸውና ፖሊሲዎቻቸው መመርመር ያስፈልገናል። ለመመርመር ደግሞ ያቀረቡትን አማራጭ ማወቅ ያስፈልገናል። ለማወቅ ደግሞ የፓርቲው ሰዎች ከኛ (ከህዝብ) ጋር የሚገናኙበት መንገድ ሊመቻችላቸው ይገባል። ስለዚህ ህዝባዊ ስብሰባዎች መፈቀዳቸው ጥሩ ነው። አሁን የሚፈለገው የኛ ተሳትፎ ነው። በዚህ መንገድ ዓረና ፓርቲ ጥሩ አማራጭ መሆኑ ወይ አለመሆኑ ህዝቡ ይወስናል።
እስቲ በአደራሹ ተገኝተን የዓረና ትግራይ ፓርቲ አማራጭ ሓሳቦች ምን እንደሆኑ ሰምተን እንገምግም። በዚህ ጉዳይ ከህዝባዊ ስብሰባው በኋላ አስተያየት እሰጥበታለሁ።
የዓረና አማራጭ ሓሳብ ምንም (ጥሩ ወይ መጥፎ) ሊሆን ይችላል። ያም ሁኖ ግን ዓረና ፓርቲ አማራጭነቱ እንደተጠበቀ ነው። የአማራጭ መጥፎ ደግሞ የለም።
ለራሳቸው (ለህወሓቶች)ም ነፃ ልናወጣቸው ይገባል።
It is so!!!