Friday, May 30, 2014

ሀገሬ ኢትዮጵያ ብሔሬም ኢትዮጵያዊ ነው!!!


በዘርና በነገድ በቋንቋና በሃይማኖት መከፋፈልን አጥብቄ እቃዎማለሁ። ብዙም አልጽፍም በአገሬ ጉዳይ ዙሪያ የተከሰቱ ሁኔታዎችን ማዳመጥና በቻልኩት መጠን መርዳትን እመርጥ ነበር፣ በሰሞኑ የሚሰማው ዜና ግን ዝም እሚያሰኝ ዓይደለም። ልቤ እጅጉን ተጎዳ፤ ሰው በአገሩ እንዴት በማለት የውስጥ ሀዘንም ተሰማኝ፦ ሰዎች ከቤታቸው ተፈናቅለው ለጅብ ተሰጡ፥ በዓማራው የጀመረው የጥፋት ዘመቻ ወደ ኦሮሞውም መጥቷል፥ ኢትዮጵያ በጭንቅ ላይ ትገኛለች፥ የዓንድነት ዓቀንቃኞችን እንዳልሰማችሁ በመሆን የአማራውን እልቂት ከመናገር ተቆጠባችሁ እንጂ የብሔር ፓለቲካ ዓድጎ ጥርስ ዓውጥቷል፣ ወገኖች እርስ በዕርስ የሚበላሉበት ሰዓት ላይ ናቸው እያሉ ተቆርቋሪ ነን የሚሉ ወገኖች ብዙ ይጎስሙናል፥ ለማጉረምረማቸው እውነታነት በወለጋና በሃራማያ ዩኒቨሪስቲ ምልክቶች ፍጥጥ ብለው መታየት ጀምረዋል።

ከደቡብ ጠርዝ እስከ ሰሜን ጫፍ ዋይታ በዛ፣ የሕጻናትና የዓረጋውያን ለቅሶ፤ የጎበዙ የሞት ጣርና የወይዛዝርቱ የልብ ስብራት፤ የናቶች ሐዘንና ትካዜ የአባቶች የድረሱልን ድምጽ ይሰማል። ከሐረር እስከ ወለጋ፤ ከጎንደር እስከ ወሎ፣ ከአፋር እስከ አርሲና ጋሞጎፋ፤ ከወልቃይት ጸገዴ እስከ ጉራፋርዳ፤ ከሰቲት ሁመራ እስከ በደኖ አርባጉጉ፤ ከአብደራፊ መተማና ስናር እስከ ሱዳን ድንበሮች፣ ከአርማጭሆ የዋልድባ ገዳም እስከ ትልቁ የዓንዋር መስጊድ መርካቶ በሐገረ ኢትዮጵያ ጩኸት በረከተ….. ፦ ያጠላው የሞት ድባብ አሁንም በጋምቤላ አድርጎ በጉሙዝ ቤኔሻንጉል የብሔረ አማራን ማጋየት ቀጥሏል፤ እንደ ዕነርሱ አባባል አማራ አፈርድሜ እየበላ ነው።


ሜሬቱ ተቆርሶ፣ ለሱዳን መሞዳሞጃ፥ በልማት ስም ለም ዕርስቱ ለባለጊዜ ቱጃሮች በርካሽ ይቸበቸባል፥ እምቢ ዓሻፈረኝ ያሉ ወንድሞቻችን በመርዝና በጥይት ይግደላሉ፥ እህቶቻችንን በመመረዝ የዘር ቅንሳ ዘዴ ሰለባ እንደሆኑ መረጃዎች በግልጽ እየወጡ ነው፥ የዜጎቻችን በግፍ መጨፍጨፍ በዛ፦ ሃዘኑና መገፋት የበዛባቸው ሽማግሌዎች ለሞት ወጣቶች ለስደት እየተዳረጉ ነው፥
አገር ፈረሰ፤ ድንበር ተቆረሰ፤ ሐይማኖት ተጣሰ፦የአማራ ሕዝብ መከራና ስቃይ ከልኩ አለፈ…እኖር ማለት፣ ሰላም ፈላጊ መሆንና ትግስት ማድረግ እንደ ፍርሃት ተቆጠረ፦ ይህ የወያኔ የጥፋት ዘመቻ ጥፋት በቅደም ተከተል መሆኑ ነው እንጂ በዕያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ላይ በተራ እንደሚደርስ፥ እየታየ ነው።

ስለዚህ,,,,,

ወገኔ የኢትዮጵያ ሕዝብ ሆይ ሀሳብህን አስማማና በአንድ ድምጽ በያለህበት ተናገር፤ ዓንዱ ሲጎዳ በቸልተኝነት ዝም ዓትበል፥ ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያዊነትን ድንገት እያጣን ነው ወገኔ፥ የማንነታችን አሻራ የጥቁር ዘር ኩራት የሆነችውን ኢትዮጵያችንን ለማጥፋት ጨክኖ ከተነሳ ሀገር በቀል ጠላት ለመታደግ ሰዓቱ አሁን ነው፤ የወያኔን መሰሪ ደባ ለማስቆም ሳይመሽ እንሰባሰብና እንምከር።

የወያኔ ዋናው ዓላማ ታላቋን ኢትዮጵያን አጥፍቶ ድንክየ አገሮች ለመፍጠር እንደሆነ በውስጥ አዋቂዎች በዐጽንኦት ይነገራል።
የማጥፋት ዘመቻው ያነጻጸረውም፦ የጋራ መግባቢያ በሆነው በአማርኛ ቋንቋችንና የአንድነታችን መሰረት በሆኑት በሐይማኖታችን ላይ ጀምሮ፥ ለኢትዮጵያ አንድነት ምሶሶ በሆነው ብሔረ አማራ እና በታላቁ የኦሮሞ ሕዝብ ላይ ነው።

የሁለቱን ታላላቅ እምነት ተከታዮች እስላምና ክርስቲያኑን፤ እንዲሁም የአገሪቱ አምድ የሆኑትን ብሔረ አማራንና ብሔረ ኦሮሞን ለማጣላት የተሞከረው አልተሳካላቸውም ግን ወያኔዎች ዓሁንም ዓጥብቀው እየሞከሩ ነው፤ እነሱ እንደሚጠሯቸው በአናሳ ጎሳዎች ታላቁን የአማራ ሕዝብ ለማስመታት የተጀመረው ድፍረት በፍጥነት ካልቆመ፥ ሰው በዓገሩ በሰራው ቤትና በኖረበት ቀየው ዓርጅቶ በወግ እንዳይቀበር የተያዘው የማፈናቀልና ከስር የመንቀል ዘመቻ ካልቆመ እንዲህ ተዳፍኖ ተዳፍኖ የሚነሳውን እሳት ማብረድ እጅግ ይቸግራል፣ ለፓለቲካ ፍጆታ ሲባል ስም ከመጥራት ልቆጠብ ቢዳዳኝም አስተዋይ የሆኑ የትግራይ ተወላጆችና በጎሰኝነት ልክፍት የተለከፉ ሆዳም የወያኔ መናጆዎች በጥብቅ ሊያስቡበት ይገባል።

አገርና ሕዝቡን ወዳጅ፣ ልበ ሰፊና መንፈሰ ጽኑ የሆነውን የአማራ ነገድ ቅስሙን ለመስበርና ዘሩንም ለማጥፋት የሚደረገውን ሩጫ በአንድነት እንቃዎምና እናስቁም፣ ላማንኛችንም አይጥቅምምና ዘረኝነትን በየጎጣችን እንዋጋ፣ ሁላችን በመከባበር በጋራ የምንኖርባት ዲሞክራሲያዊት ኢትዮጵያን ለመገንባት በአንድነት ድምጻችንን እናሰማ፣ በምንችለው ሁሉ እንታገል!!!

ድል ለኢትዮጵያ ህዝብ!!

No comments:

Post a Comment