Friday, May 9, 2014
"ኪላርክን እንዳይዘምር ሊያዘው የሚችል እኮ እሱ ማን ነው?"
አምባገነንን መዋጋት ቀላል አይደለም፣ ክፍያው ብዙ ነው፡፡ ይህንን እያወቁ ትግሉ ላይ ለሚሳተፉት ሰዎች አድናቆቴ ከፍ ያለ ነው፡፡ አምባገነን ኃይል ተፋላሚውን ማንበርከክ ብሎም ማጥፋት ያስችለኛል በማለት የጦር ኃይል፣ ለሆዳቸው ያደሩ ሰዎችን ከተራው ሰው ጀምሮ እስከ ለሰማይና ለምድር የከበዱ ሙህራንንና የሀይማኖት አባቶችን ይጠቀማል፡፡ ያስራል፣ ያፍናል፣ ከቤትና ከቀየ ያፈናቅላል ይገላል፡፡ ሕሊናውን የሸጠ ቅልብ ጨካኝ ሰራዊት አሰማርቶ እያስፈራራና እየገደለ የሰው ልጅ በኑሮው፣ በስራው፣ በማህበራዊ ህይወቱ፣ በሁሉም የህይወት ገጽታው በሃይል እየገዛው ለመኖር ሰርክ ይጥራል፣ ይወጣል ይወርዳል፡፡ ይህንን ለማድረግ የተለያዩ ‹‹የፍትህ›› አካላትና የሚዲያ ተቋማት ጭራቸውን እየቆሉ ከስር ከስሩ ይከተሉታል፡፡ ትልቁና በታላቅ የሞራል ከፍታ ላይ ያለው ኃይል ደግሞ በብዕሩ የሰው ልጆችን ነጻነት የገፈፉ አማባገነኖችንና ጨቋኞችን ይታገላል፣ በትግሉ ላይም ይሞታል፣ ይሰደዳል፣ ይታሰራል፡፡ ደጋፊዎቹንም ያለምንም ጫናና ተጽዕኖ በነጠረ የአስተሳሰብ አንድነት አስተባብሮ ከጎኑ ያሰልፋል፣ ሰላም ለእናነንተ ይሁን! አሜን!!
ይህንን የሚያስብለኝ ነገር ምን እደሆነ መቼም ይጠፋችኋል ብየ አላሰብም፡፡ ፌስ ቡክ ከሚሉት ጉድ ርቄ ነበር፤ ይህ የማህበረሰብ ድህር ገጽ ከአመት በፊት በብዙ ባለተሰጥኦ እና ድንቅ አሳቢ ሰዎች የተሞላ ስለነበር ከኮምፒውተሬ ፊት ለፊት ቁጭ ብየ እነሱ የሚጽፉትን ነገር ማንበብ ከስራየ በላይ ዋናው እለታዊ ጉዳየ ነበር፣ ነገር ግን እነኛ ሁሌም ሳነባቸው ነፍሴን የሚሞሏት ልጆች ቀን ሲሄድ ቀን ሲመጣ ቀስ በቀስ ከዚህ ትስስር እየራቁ ሲመጡና በአንጻሩም ጭንጋፎች ብቻ እየሞሉት ሲመጡ ይታወቀኝ ጀመር፤ ሆኖም ግን አልፎ አልፎም ቢሆን መጎብኘቴ አልቀረም፡፡ አሁንም ከወር በላይ ርቄው ወደነበርኩት ፌስ ቡክ የመለሰኝ ዞን 9 የተባሉት የጦማርያ ቡድን ታሰሩ የሚል ወሬ ሰምቼ ነው፣ አልደነገጥኩም፤ ምክንያቱም መታሰር ብርቅ አይደለም፤ ምክንያቱም በእኛ ሀገር ከጻፍክ ሰውም ካነበበህ በቃ ትታሰራለህ፤ ይህንን ከአሁን በፊት አይተናል፣ ሰምተናል፤ …. ስለዚህም ብርቅ አይደለም፡፡
ግና እዚህ ገጽ ላይ ስለነሱ ሀሳቤን ልገልጽ ፈልጌ፣ ሀሳብ ከየት ይምጣ?፣ እስኪ አሁን ስለ ዘላለም መታሰር ምን ብየ ልጽፍ እችላለሁ፣ ስለበፍቃዱ ስለአቤላ እስር ቤት መታጎርስ ምን አይነት አረፍተ ነገር ልመሰርት እችላለሁ? ማህሌት(ማሂፋንቲሽ) የተባለች ነፍስ እስር አይገባትም ብየ ብጽፍ እናንተስ ብትሆኑ አትታዘቡኝም? ናትናኤል እና አጥናፍ፣…….. አልቻልኩም ፣ ግና ከአሁን በፊት እዚሁ ገጽ ላይ የለጠፍኩትን አገኘሁና እሱን ለጥፌ መገላገል ፈለኩኝ ሰተቶው “መንግስቴ” ህጎችን ማውጣት ይችልበታል፣ ስለውበታቸውም አብዝቶ ይጨነቃል፡፡ አሁን አሁን እየተበላሸ ቢመጣም ህጎችን ሲያወጣ ከአማልክት ጋር ተማክሮ የሚያወጣ ይመስል ነበር፡፡ ለዚህም ህገ መንግስታችንን መመልከት ይበቃል፤ እንደ አንቀጽ 39 አይነቶችን አንድ ሁለት ሶስት ያህል አንቀጾችን ትተን ብናስተውለው ድንቅ የሚባል “ህገመንግስት” አለን፡፡ ነገር ግን እሱ ያወጣቸውን ህጎች በመጣስ ህጎችን ለማስከበር ካለው ፍጥነት በጣም ይልቃል፣ ይልኙታ የሚባል ነገር ከነጭራሹ አልፈጠረበትም፡፡
1. ማንኛውምሰው ያለ ማንም ጣልቃ ገበነት የመሰለውን አመለካከት መያዝ ይችላል፡፡
2. ማንኛውምሰው ያለ ማንም ጣልቃ ገበነት ሀሳቡን የመግለጽ ነጻነት አለው፡፡ …………..
ከላይየተገለጹት ሁለት ነጠቦች በኢፌዴሪ ህገመንግስት አንቀጽ 29 ላይ በወርቅ ቀለም ተጽፈው የሚገኙ ናቸው፡፡ ይህንን አንቀጽ ያነበበ ሰው የሚሰማው ነገር ልክ በአሸዋ ሳጥን (Sandbox) ውስጥ እንደተቀመጠ ያህል ነው፡፡ አስተማማኝ በሆነ የህግ ከለላ ያለው ይመስለዋል፡፡ ትላንትና ስለ እስክንድር ነጋና አንዱአለም አራጌ የሰማነው ጉዳይ እደከዚህ ቀደሙ ሁላችንን በጥልቅ መከፋት ውስጥ ጥሎናል፡፡ የእስክንድር ነጋ፣ የአንዱአለም አራጌ ፣የርዮት አለሙ፣ የበቀለ ገርባ፣ የአበበ ቀስቶ፣…… ጥፋታቸው ሀገራቸውን መውደዳቸውና አንቀጽ 29 የምር መውሰዳቸው ብቻ ነው፡፡ ይህንን ህገ መንግስት ተማምነው የመረጡትን አመለካከት ያዙ፣ የያዙትን አመለካከት ደግሞ በነጻነት ገለጹ፣ አራመዱ፡፡ ነገር ግን ይህ ህገ መንግሰት ወፍን ለማጥመድ ከተዘጋጀው አሽክላ ውስጥ እደተበተነው ጥራጥሬ ነው፡፡
ገዢዎቻችን ያሳዝኑኛል፣ የምር ይከረፉኛል!! ለእነሱ ህግ ጭዋታ ነው፤ ህግ ለነሱ ጠረፔዛ ላይ እንደሚቀመጥ አበባ፣ ሁሉም ሰው ሲያየው ደስ እንደሚሰኝበት፣ ሁሉንም ሰው በመዓዛው እንደሚያውድ ሳይሆን፤ ሙዳይ ውስጥ ታሽጎ እንደሚቀመጥ፣ በፈለጉ ጊዜ ብቻ አውጥተው እንደምያጌጡበት ጨሌ ነው፡፡ እሱ ሲፈልግ ህገመንግስቱን በተለያዩ ደንቦች ደፍጥጦ እንደ ጭራቅ እያሽካካ ያለርህራሄ ዜጎቹን እስርቤት ያጉራል፤ ሲፈልግ ደግሞ ህገመንግስቱን ሳጥን ውስጥ ያስቀምጥና ያለከልካይ ሜዳውን ሁሉ ብቻውን ሽምጥ ሲጋልብበት ይውላል፡፡
ታላቁባለቅኔ ካህሊል ጅብራን በኦርፋሌስ ከተማ ላሉት ወዳጆቹ ስለ ህጎች ሲያስተምራቸው እንዲህ አላቸው ፡
“ህጎችን ስታወጡ አብዝታችሁ ደስ ትሰኛላችሁ ይበልጡን ግን ደስ የምትሰኙት ህጎችን በመጣስ ነው፡፡
በውቅያኖስ ዳርቻ እየቦረቁ በቀናነት የአሽዋ ታወሮችን እንደሚገነቡ እና በኋላ እየቦረቁ እንደሚያፈርሷቸው ብላቴኖች ናችሁ፡፡ ……………
…….. የኦርፋሌስ ህዝቦች ሆይ ከበሯችሁን ልታፍኑት፣ የበገናችሁን ክሮች ልታላሏቸው ትችላላችሁ፡፡ ነገር ግን የሰማዩን ዘማሪ ወፍ(ኪላርክ) እንዳይዘምር ሊያዘው የሚችል እኮ እሱ ማን ነው? ”
“There may be times when we arepowerless to prevent injustice, but there must never be a time when we fail toprotest.” .Elie Wiesel
“A kingdom founded on injusticenever lasts.” Lucius Annaeus Seneca
ሁላችንም ዞን9 ነን!
#FreeZone9bloggers #Ethiopia
Subscribe to:
Post Comments (Atom)
No comments:
Post a Comment