Thursday, May 15, 2014

ኢህአዴግ ፍፃሜው መቼ ነው?

ይህን ጥያቄ ሲሰሙ የሚከፉ ጥቂት የስርዓቱ ተጠቃሚ ሰወች ቢኖሩም አብዛኛው ኢትዮጵያዊ ግን የሚናፍቀው ቀን ነው:: ብዙ ሰው ቀኑን ከመናፈቁ የተነሳ የነዚህስ ዕድሜያቸው ረዘመ ምን አለ ፈጣሪ ቢገላግለን ሲል ይሰማል:: እኔ ግን እላለሁ ህወሓት/ ኢህአዴግ ን እኛ ራሳችን በተለይም አዲሱ ትዉልድ እስካልደገፈው ድረስ ከዚህ በኋላ ዕድሜው አጭር ነው:: ለምን?

የመጀመሪያዉ ምክንያት ተፈጥሯዊ ነው:: ላለፉት 23 ዓመታት ሀገሪቱን ሲመሩ የነበሩት ሰወች አሁን እርጅና እየተጫናቸው ሲሆን በመጭወቹ ዓመታት አብዛኞቹ በእርጅና ምክንያት መስራት የማይችሉበት ደረጃ ይደርሳሉ ወይም እንደመለስ ይሞታሉ:: ይሄ ነገር ስርዓቱ ላይ የሚፈጥረው ችግር ቀላል አይሆንም:: በተለይም ድርጅቱ የይስሙላ መተካካት ሲያካሂድ የቆየ መሆኑ ችግሩን የከፋ በማድረግ ዉድቀቱን ያፋጥነዋል::

ሁለተኛዉ ምክንያት ድርጅቱ የሰበሰባቸው አባላት ጥራት ጉዳይ ነው:: ባለፉት 10 ዓመታት ኢትዮጵያ ዉስጥ በመንግስት ሥራ ለመቀጠር ፣ ለመነገድ ፣ በግብርና ሥራ ለመተዳደር ወይም በሌላ ሥራ ለመሰማራት የድርጅቱ አባል መሆን ግዴታ ነበር አሁንም ነው :: በአሁኑ ወቅት ያለው አብዛኛዉ የድርጅቱ አባል ባብዛኛዉ ወዶ ሳይሆን ተገዶ የገባ ነው :: እንደዚህ አይነቱ አባል ድርጅቱን ለማፍረስ አድፍጦ የሚጠብቅ ኃይል ከመሆኑም በላይ ድርጅቱን በሙስና እንዲጨማለቅ አድርጎታል:: አምነዉበት የገቡት አባላትም ቢሆን በድርጅቱ መሰረታዊ ባህሪ የተነሳ መጠየቅ እና የራስን ነፃ ሃሳብ ማራመድ በድርጅቱ እንደነዉር ስለሚቆጠር ፈሪ እና ተከታይ እንጅ ሃሳብ አመንጭ አይደሉም ፤ እንደነዚህ አይነቶቹ ሰወች ያለመሪ ድርጅቱን ማዳን የሚችሉ አይደሉም::


ሶስተኛዉ ምክንያት የህዝብ ብሶት ነው:: ድርጅቱ ለሕዝብ አበርክቸዋለሁ የሚለው እና ሕዝብ ስለድርጅቱ የሚያስበው ነገር ተቃራኒ ናቸው:: ድርጅቱ ሀገሪቱን ቀይሮ ሕዝቡን የተሻለ ኑሮ እንዲኖር እንዳስቻለ አፉን ሞልቶ ሲከራከር ሕዝብ ደግሞ የኑሮ ዉድነት አማሮት ከዕለት ወደ ዕለት ኑሮዉ እየቆረቆዘ ነው:: ድርጅቱ ደርግ የተባለን ስርዓት ገርስሶ ፍትህ እና እኩልነትን እንዳሰፈነ በኩራት ሲናገር ሕዝብ ደግሞ እለት ተዕለት የሚያየው ግድያ ፣ እስር እና የፍትህ እጦት የሚሰማዉን ነገር ፌዝ አስመስሎበታል:: በተጨማሪም የመረጃ አቅርቦት መስፋፋት የመንግስትን ዉሸት እና የይስሙላ ምርጫወች ህዝብን ማታለያነታቸው ጊዜ ያለፈበት የሞኝ ጨዋታ አድርጎታል:: ከሁሉም በላይ ግን አሁን ስልጣን ላይ ያሉት ሰወች ትልቁንም ትንሹንም ችግር ከእስር እና ግድያ ዉጭ የሚፈታዉ ሌላ አማራጭ እንዳለ የሚያውቁ አይመስሉም፤ ይሄ በምርጫ 97 መለስ ያስተማራቸው ነገር ነው፣ ነገር ግን መለስ በወቅቱ ከእሥር እና ግድያ ጎን ለጎን ሕዝቡን በውይይት ሃሳቡን እንዲገልፅ እያደረገ ጉዳዩን ለማብረድ የወሰዳቸውን ሌሎች እርምጃወችን እረስተዋቸዋል::

ከላይ የተገለፁት ምክንያቶች እና ሌሎች ነገሮች ተዳምረው በመጭወቹ ዓመታት ከሶስት አቅጣጫወች ድርጅቱን የሚንዱ ፈተናወች ይገጥሙታል:: የመጀመሪያዉ አደጋ ምንጭ ዉጫዊ ነው:: ከግብፅ ጋር በአባይ ጉዳይ የተፈጠረው ዉዝግብ ፣ የደቡብ ሱዳን እና የሶማሊያ ችግር እንዲሁም ያልተፈታዉ የኤርትራ ጉዳይ ነገሮች ገፍተው ከመጡ ይሄ ከህዝብ ተነጥሎ የቆመ መንግስት ሊቋቋማቸው የሚችሉ አይደሉም:: በተለይም ግብፅ ገፍታ ብትመጣ ሀገር ዉስጥ ለመንግስት ያለው ከፍተኛ ጥላቻ እና የብሔር ፖለቲካዉ የፈጠረው ሁኔታ የድርጅቱን ብቻ ሳይሆን የሀገሪቱን ሕልዉናም ሊንድ የሚችል ይሆናል::

ሁለተኛዉ እና መሰርታዊው ፈተና የሚመጣዉ ከራሱ ከህዝብ ነው:: በአሁኑ ወቅት ሕዝብ በድርጅቱ ላይ ተስፋ ቆርጧል:: ይባስ ብሎም ድርጅቱ ቀንበሩ እና ግፉን ከዕለት ወደእለት እያከበደው መጥቷል፤ ይህም ሕዝባዊ ተቃዉሞወች እና ትግሎች እየጠነከሩ እንዲሄዱ ማድረጉ የማይቀር ነው::

ሶስተኛው አደጋ የሚፈጠረው በድርጅቱ በራሱ ዉስጥ ይሆናል:: የመለስን መሞት ተከትሎ ድርጅቱን እና አባላቱን በአንድ አሰባስቦ በግድም በዉድም የሚመራ ሰው እስካሁን አልተገኘም ድርጅቱ ዉስጥ ያለም አይመስልም ፤ ይህም በዋናነት መለስ በዘመኑ ተቀናቃኞቹን አንድ በአንድ ስላጠፋቸው እና ተከታይ እንጅ መሪ ስላላፈራ ነው:: በዚህ ላይ አሁን ያሉት ነባር አመራሮች በእርጅና እና በሞት ድርጅቱን መምራት የሚያቆሙበት ደረጃ ላይ እየተቃረቡ ስለመጣ ድርጅቱ ዉስጥ የዉስጥ ትግል መፈጠሩ አይቀርም:: ይህን ችግር የከፋ የሚያደርገው ድርጅቱ ባለፉት 23 ዓመታት የተከተላቸው ብሄርን መሰረት ያደረገ ፖለቲካ እና ድርጅቱን የመሰረቱት 4ቱ አባል ድርጅቶች የብሔር ድርጅቶች መሆናቸው ነው:: ይህም በተለይ ህወሓት አሁን ያለዉን የወታደር እና የድህንነት የበላይነት ካጣ በድርጅቶቹ መካከል መከባበር እና አብሮ መስራት ፈታኝ ብቻ ሳይሆን እርስ በእርስ መናከሳቸው አይቀርም ፤ በዛ ላይ ባይናገሩትም ኦህዴድ ፣ ብአዴን እና ደኢህዴን ባለፉት 23 ዓመታት የህወሓት ተላላኪ ሁነው መቆየታቸው ያፈኑትን ቁጭት እንዲያወጡ ያደርጋል ::

በአጭሩ አለማቀፋዊ ለዉጦች እንዳሉ ሁነው መጭዉን ዘመን አሁን ካሉት ሽማግሌ ባለስልጣናት ይልቅ በአዲሱ ትውልድ እጅ ነው:: ትዉልዱም ኃላፊነት በተሞላበት መንገድ ተከባብሮ እና በሰለጠነ መንገድ የሀገሪቱን ዕጣ ፈንታ መወሰን ከቻለ የምንወዳት ሀገራችን እንድትሆን እንደምንፈልጋት ትሆናለች ካለበለዚያ ግን ቀጣዩ አምባገነን ምን አልባትም አንድ ክፍል ዉስጥ አብሮህ ቁጭ ብሎ የተማረ ጓደኛህ ወይም እዚህ ፌስቡክ ላይ ስትቀላለደው ወይም ስትሰዳደበው የምትዉለው ጓደኛህ ሊሆን ይችላል:: ማን ያውቃል ?

No comments:

Post a Comment