Saturday, May 31, 2014
መረሳትና መርሳት በሃገራችን!
መረሳትና መርሳት የኢትዮጵያ ዋና ባህላችን ይመስለኛል:: መርሳት ካለን ጽናት ውሱንነት ይመነጫል:: በጽኑና በአንክሮ የምንፍፈልገውን: የምንከታተለውንና የምናስበውን ነገር የመርሳት እድላችን ጥቂት ነው:: በመርሳት ባህላችን ውስጥ ብዙ ነገሮችንም እንረሳለን: ደስታን: መሪር ሃዘንን: ጀግናን: ጭቆናንና ጨቋኝን...ወዘተ... የማንረሳው ነገር የለም:: በደልና ግፍን መርሳት በግለሰብ ደረጃ ቂም በቀልነትን ሊቀንስ ቢችልም እንደህዝብ ከረሳን ግን በደልና ጭቆናን ሁሌም የማንሰለች "ሁሉን ተሸካሚ" ማህበረሰብ ሆነን እንድዘልቅ ያደርገናል:: በእርግጥ እኛ የምንረሳው ነገሩን ጭራሽ "ማስታወስ" ስለማንችል ሳይሆን: አስታውሰን የምንሰጠው ትኩረት አናሳ በመሆኑ ነው:: ይህም ከጽናት ጉድለት ወይም ተስፋ ቢስነት ይመነጫል::
ይህን ማህበረሰባዊ ተውሳክ በአግባቡ ተረድቶ እንደአኢህአዲግ የተጠቀመበት ያለ መንግስት የለም:: ምንም የሚያስከፋንን: የሚያንጨረጭረንን; የሚያበሳጨንንም ነገር ሲወስድ: ሁሌም በአንድ ነገር እርግጠኛ ሆኖ ይመስለኛል:: ያም ትንሽ ቆይተን እንደምንረሳለት! በዚህም ምክንያት እኛን ደስ የሚያሰኘንን ሳይሆን ሁሌም እርሱን ደስ የሚያሰኘውን ነገር በእኛ ላይ ሊኖረው የሚችለውን ማንኛውንም ስሜት ከግምት ሳያስገባ ይወስዳል:: ይህን ሲወስድ ዋስትናው መሳሪያ ነው ብሎ ስለሚያምን አይመስለኝም: ይልቁን ዋስትናው የእኛ መርሳት ነው::
እስኪ በእኛ ዘመን "የረሳናቸው" የሚከተሉትን ጥቂት የአንድ ወቅት ክስተቶች እንመልከት:
1ኛ: በ1993 ዓ.ም በአዲስ አበባ ዩንቨርስቲ 300 የሚሆኑ ተማሪዎች ተባረው ፍትህ ሳያገኙ መቅረት:
2ኛ: በ1997 ዓ.ም ከምርጫ ጋር ተያይዞ ከ194 በላይ ሰዎች ሞትና በቂ ምርመራ እንኳ ሳይደረግ በዚያው ደመ ከል ሆነው መቅረት
3ኛ: በጋምቤላ ክልል ተፈጸመ የተባለው "ጄኖሳይድ" እንዲሁ ሳይጣራ መቅረት
4ኛ: በባለፉት ሁለትና ሶስት ዓመታት በተለያዩ የሃገሪቱ ክፍሎች የሚኖሩ የአማራ ብሄር አላቸው የተባሉ ዜጎችን በሃይል አፈናቅለው ካለፍትህና ካሳ እንዳሰናበቷቸው መቅረት
5ኛ: በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስትያን ውስጥ ከፓትሪያርክ ሹመት ጋር በተያያዘ ከ1980ዎቹ ጀምሮ መንግስት የወሰዳቸው እርምጃዎች (የተከፋፈለች ቤተ ክርስትያን እንድትመሰረት)
5ኛ: በአወሊያ ት/ቤትና የእስልምና ካውንስል አስተዳደር ላይ ከ1990ዎቹ መጀመሪያ ጀምሮ እስካሁን ድረስ የወሰዳቸው እርምጃዎች: በነገራችን ላይ የታሰሩት መፍትሄ አፈላላጊ የኮሚቴ አባላትም እስከ ትላንት ድረስ ከትኩረታችን ርቀው እንደከረሙ ልብ ይሏል:: ከዚህ ጋር ተያይዞ አርሲ ውስጥ የተገደሉ ሰዎች ደመ ከልብ ሆኖ መቅረት
6ኛ: የቴዴ አፍሮ በእስሩ ዘመን አንድ ወቅት መረሳት ("ጉድ ያረጘኝ አይኔ" ነው የሚለው ዘፈኑ ባይለቀቅ ኖሮማ ጭራሹኑም ትዝ ሳይለን ከርሞ ሊለቀቅ ነበር)
7ኛ: በእስር ቤት የሚገኙ እነእስክንድር ነጋ: ርዮት ዓለሙ: በቀለ ገርባ: አንዷለም አራጌና ሌሎች ጋዜጠኞችና ፖለቲከኞች:: እንዲሁ አንዳንዴ የውጭ ሚዲያ ሲያነሳቸው ካልሆነ ብዙ ጊዜ አብዛኞቻችን አናስታውሳቸውም:: በነገራችን ላይ ከ1997 ምርጫ በኋላ የታሰሩት የቅንጅት አመራሮች የሆነ ወቅት በእስር ቤት እያሉ ከህዝብ ትኩረት ተነፍገው እንደነበር ትዝ ይለኛል::
8ኛ: አሁን ከጥቂት ሳምንታት በፊት በአምቦና በጎንደር ከተማ የተገደሉት ሰዎች እንዲሁ እንደቀልድ ከሃሳብ መዝገባችን እየደበዘዙ መሄድ
9ኛ....ቀጣዮች የመርሳት ባህላችን ተረኞች የዞን ዘጠኝ አባላት...ይሆናሉ ብዬ አምናለሁ::
ከላይ የጠቀስኳቸው እጅግ ውስን ናቸው:: እንግዲህ ከእነዚህ ውስጥ አንዱ እንኳ የመረሳት እጣ ፈንታ ባያጋጥመው...በሃገራችን ውስጥ ትልቅ መሰረታዊ ለውጥ ለማምጣት እንደምክንያት ሊሆን ይችል ነበር:: ግን እንደህዝብ እንረሳለን...ስለዚህ እንዲህ አይነት ነገሮች ደጋግመው ቢመጡም ሁሌ እንግዳ ናቸው: የማንለምዳቸው: ሁሌ የሚያስደነግጡን እንግዳዎች!
Subscribe to:
Post Comments (Atom)
No comments:
Post a Comment