Tuesday, May 13, 2014

አየሽ ሀገር ሲያረጅ

በአገኘው አሰግድ

ዕድሜ ወጣትነት በሆነበት ዓለም
ከአንዲት ሀገር ማርጀት በላጭ ሀዘን የለም
ይሁልሽ እናቴ;
ሺ ዓመታት ዘለቅሽ
ልምድ ዕውቀት አዳበርሽ
ብሎ መደሰትን የቃጣን ቢሆንም
በዕድሜሽ ማርጀት እንጂ መላቅ አላየንም

አየሽ ሀገር ሲያረጅ:
ሥልጣኔ መሀል ሁዋላ ቀርነትን ሸልሞ ይሾማል
ክቡር ሰውን በልቶ በኩራት ይቆማል

አየሽ ሀገር ሲያረጅ
ዜናችን ቢነበብ
ግዋዳችን ቢዘገብ
ታጎሩ: ታሰሩ: ዱላ አረፈባቸው
ከሚለው አይዘልም;
ሰው ልሁን ያለን ሰው "ሰዎችሽ" አይምሩም!


መንገድ ዘግተሽብን መንገድ ሰራሁ ብለሽ ታወሪያለሽ አሉ
ይህንን የሰሙ በቀልድሽ ንቅሳት ጥርሳቸውን ክዋሉ
እመንገድሽ መሀል: መንገድ አልባው እኔ
መንገድ ያልሽው ጠፍቶኝ ይሄው መባከኔ

መሀል ከተማ ላይ ጅቦች ይጮሀሉ
እንዲህ የሚያጯጩህ ምን አግኝተው በሉ?
ከተሜ ጅቦችሽ
እንዲህ የሚያውካኩ-
እንዲህ የሚያስካኩ
አቁስለው አድምተው ሺ ቦታ በልተው
ስለጠገቡ ነው ነፃነትን በልተው

አየሽ ሀገር ሲያረጅ
የነፃነት ቀብር
አደባባይ እንጂ ሌላ ቦታ አይመርጥም
ሰው የመሆን ክብር ቦታውን አይረግጥም!
አየሽ ሀገር ሲያረጅ
በቁመቱ ሲጃጅ
ደንባራውን መሪ ከፊት ቅደም ይላል
ልበ-ብሩሁን ሰው ከሁዋላ ያስከትላል
አድጌያለሁ ብሎ ተናግሮ ሳይጨርስ ባፍጢሙ ይደፋል
አገር ሲያረጅ እንዲህ ቁጭ አንቺን ይመስላል!

No comments:

Post a Comment