Friday, May 23, 2014

ይድረስ ለኢትዮጵያ ሰራዊት......!

በቅዱስ ዮሃንስ

በአሁኑ ጊዜ የአገራችን አንድነትና ሉአላዊነት ላይ የተደቀነው ፈተና እስካሁን ከተለመደው በአይነትም፡ በይዘትም፡ በአፈፃፀምም አንድ ቢመስልም በጣም ልዩ አስገራሚና የበለጠ አሳዛኝ የሚያደርገው ግን ይህ በአገር አንድነትና ሉአላዊነት ላይ የሚደረግ መሰርያዊ ዘመቻ ተፈፃሚ እየሆነ ያለው ኢትዮጵያዊ ነን በማለት በኢትዮጵያ ስም በሚነግዱ ባንዳ አገር ሻጮች ማለትም በሕወሓት ወያኔ ቡችሎች መሆኑ ነው። አዎን ይህ ክስተት ገፅታውን ካሳየን ውሎ አድሯል። የፋሽስቱ ህወሓት ቡድን የፖለቲካ ቅኝቱ የኢትዮጵያን አገራዊ አንድነት፡ ሉአላዊነትና ብሄራዊ ክብር በዋናነት መፃረር፡ ታሪኳን ማንቋሸሽና ህዝቧን መናቅ አብይ ተግባሩ እንደሆነ በተደጋጋሚ በተግባር አረጋግጦልናል። ማነኛውም በገዥ አካልነት የተሰየመ ክፍል ዋነኛ ተቀዳሚ ተግባሩ የአገርን አንድነትና ሉአላዊነት በቀናኢነት ማስከበር፡ የህዝቡን ደህንነት ማስጠበቅ ነው። ነገር ግን አለመታደል ሆኖ ዛሬ አገራችንን ሰቅዞ የያዛት መቅሰፍቱ የጉጅሌው ወያኔ ይህንን ሃላፊነት መወጣት አለመቻል ብቻ ሳይሆን ተፃርሮ የቆመ መሆኑን የኢትዮጵያ ህዝብ በቁጭትና በሃዘኔታ የተገነዘበው ጉዳይ ነው። ይህ ከሆነ ታዲያ እንዴትና በምን ምክንያት ይሆን እንደዚህ አይነት አገር የማጥፋት ሴራ ያሸረበ የፋሽስት ቡድን ለ 23 አመታት በስልጣን መቀጠል የቻለው? ይህንን መሰረታዊ ጥያቄ ድፍን የኢትዮጵያ ህዝብ ራሱን ይጠይቅበት ዘንድ በመተው ዛሬ ላካፍላችሁ ወደወደድኩት አብይ ጉዳይ ልለፍ።

ታሪክ እንደሚዘክረው በሁሉም ዘርፎች የተሰለፈው የኢትዮጵያ ሰራዊት የእናት አገርን ዳር ድንበር ከማስጠበቅ አልፎ ከአገሩ ውጭ ባደረጋቸው ተጋድሎዎችን በከፈላቸው ክቡር መስዋዕትነቶች ባስመዘገባቸው ስመ ጥርና  አኩሪ ተግባራት፡ አገሩንና ህዝቡን ያኮራና በመልካም ስም ያስጠራ ነው። የኢትዮጵያ ህዝብም በገዢዎቹ ለሚቀርብ አገራዊ ጥሪ ጨርቄን ማቄን ሳይልና ሳያመነታ አወንታዊ ምላሽ  በመስጠትና ሳይከፋፈል አንድ ላይ በመቆም በትዕቢት ተሞልተውና በትዕቢት ተወጥረው በየጊዜየው የአገራችንን አንድነትና ህልውና ለመፈታተን ድንበር ገፍተውና ባህር ተሻግረው የመጡ እብሪተኞች ድባቅ እየመታ ነው አገራችንን ጠብቆ ያቆየን። ታዲያ ዛሬስ ታሪክ ጀግንነቱን የዘመረለት ሰራዊትም ሆነ የአገራችን ህዝብ በአገር ሻጮቹ የወያኔ ቁንጮዎች ችሮታ የአገር ዳር ድንበት ተቆርሶ ለባዕድ ሲሰጥ ዝምታን ስለምን መረጠ? ይህ ስለ እውነት አግራሞትን የሚጭር ዝምታ ስለመሆኑ ምንም ማስተባበያ አያስፈልገውም።


በአሁኑ ጊዜ በፀረ- ኢትዮጵያዎቹ የወያኔ ቁንጮዎች ችሮታ ንፁሃን ዜጎቻችን አንድም ጊዜ ከኢትዮጵያ ሙሉ ባለቤትና ቁጥጥር ስር ወጥቶ ከማያውቀውና ከትውልድ ትውልድ ከተላለፈላቸው አንጡራ መሬታቸው፡ በሱዳን የባዕድ ጦር ታፍነው፡ በባዕድ አገር በእስር እንዲገላቱ፡ ሃብታቸውን ንብረታቸው በነዚሁ ባዕዳን እንዲቃጠልና እንዲወረስ፡ መሬታቸውም ወደ ባዕድ እንዲከለልና እንዲሰጥ መደረጉ ይታወቃል። ታዲያ ለአገሩና ለወገኑ ያለውን የላቀ ፍቅር ያስመሰከረ ሰራዊት የነበራት አገራችን ኢትዮጵያ፡ ዛሬስ ይህ ሁሉ በደል በአገራችንና በወገኖቻችን ላይ ሲፈፀም የሰራዊቱ ዝምታ ለምን ይሆን ብለን እንድንጠይቅ እንገደዳለን? እውነት ግን ስለምን ይህ ሁሉ ውርደት በአገርና በወገን ሲፈፅም ሰራዊቱ የአገሩን ዳር ድንበር ማስከበር ብሎም አገር ሻጭ ለሆነው ወሮበላ የፋሽስት አገዛዝ እምቢኝ አሻፈረኝ አልታዘዝም ብሎ በህዝብ ጎራ በመሰለፍ አገዛዙን መፋለም ተሳነው? እዚህ ላይ መታወቅ ያለበት ጉዳይ የአገራችንን ዳር ድንበር ፋሽስቶቹ ወያኔዎች እንዳሻቸው እየቆረሱ ለባዕዳን ሲሰጡ ዝም ብለን መመልከታችን ከታሪክ ተጠያቂነታችን እንደማያድነን ነው።

ቀደምት አገዛዞች ለአገራቸው አንድነትና ለወገናቸው ክብር ቅድሚያ በመስጠት ራሳቸውን መስዋዕት ያደረጉላት፡ እልፍ አእላፍ ዜጎች አጥንታቸውን ከስክሰው ደማቸውን አፍስሰውና ምትክ የሌለው ህይወታቸውን ገብረው በከበረ መስዋዕትነት ታፍሮና ተጠብቆ የቆየውን ከሱዳን ጋር የሚዋሰነው የአገራችን ድንበር በባንዳዎቹ የህወሓት ቱባ ቁንጮዎች መሰሪ እቅድ ሆን ተብሎ በገፀ በረከትነት ለሱዳን ተላልፎ ተሰጥቷል። የፋሽስቱ ወያኔ አገዛዝ ታሪክን፡ ባህልንና ህግን በተላለፈ መልኩና ከህዝብ ጀርባ በተለመደው መሰርያዊው የእብሪት ባህሪው ከሁመራ እስከ ጋምቤላ ከ1600 ኪ. ሜ ርዝማኔና እስከ 60 ኪ. ሜ ጠልቆ የሚገባ የኢትዮጵያን አንጡራ ለም መሬት ለሱዳን አሳልፎ በመስጠት፡ ህዝብን ለማደናገርና ለማጭበርበር ይረዳው ዘንድ በማስረጃነት ለማቅረብ የሚሞክረው ደግሞ የጎረቤት አገር የሆነችው ሱዳንን በቀኝ ገዥነት ይገዛ የነበረው የአገረ እንግሊዝ አንድ ሻለቃ ግዌን የሚባል ግለሰብ በኢትዮጵያ በኩል ማንም ተወካይ ሳይነኖር ብቻውን እንደፈለገው በወረቀት ላይ ያሰፈረውንና ከአፄ ሚኒሊክ እስከ ደርግ እንደ ህጋዊ ውልነት ያልተቀበሉትና እውቅና ፈፅሞ ያልሰጡትን ጉዳይ ከተቀበረበት ቆፍሮ  በማውጣት ነው።

ለመሆኑ የጉጅሌው ወያኔ አገዛዝ እነኝህን የመሳሰሉ የአገርንና የህዝብን ጥቅም በቀጥታ የሚፃረሩ አሳፋሪና አዋራጅ፡ ቀደም ሲል በነበሩ አገዛዞች ህጋዊነት ስለሌላቸው በቀጥታ ወድቅ የተደረጉና ተቀባይነት ፈጽሞ ያልነበራቸውን፡ በታሪክም ተቀባይነት የማይኖራቸውን ማስረጃ ተብየዎች በተደጋጋሚ ሲያቀርብ በተመሳሳይ ሁኔታ ኢትዮጵያን አንድነቷ እንዳይሸረሸር ምን አደረግ? ለመሆኑስ በኢትዮጵያና በኢትዮጵያዊነት፡ በአንድነቷና በሉአላዊነቷ ላይ አምርሮ መዝመቱስ ለምንድን ነው? ብለን መጠየቅ ያስፈልጋል። በርግጥ ከአገር ሻጭና ከሃዲ የህወሓት ጭፍሮች ምንም ቀና መልስ አይጠበቅም። ስለዚህ በተለይ የአገር መከታና የህዝብ ጠባቂ የሆነ ማነኛውም የሰራዊት አባል ሁሉ ከአሁኑ ሰአትና ደቂቃ ጀምሮ፡ ማንን እያገለገለ እንዳለ፡ ታማኝነቱም ሆነ ተጠሪነቱ ለማን እንደሆነ- ለአገርና ለህዝብ ወይንስ ለአገር ሻጭ፡ የአገር አንድነትና የህዝብን ክብር እያዋረደ ላለ የባንዳው የፋሽስቱ ህወሓት ቡድን? ይህንን የወቅቱ አንገብጋቢ ጥያቄ መልስ መስጠትና በተጠንቀቅ መቆም እንዳለበት ማሳሰብ እወዳለሁ።

የተከበርከው የሰራዊት አባል ሆይ

በአገራችን የመከላከያ ሃይል ውስጥ ከተራ ወታደር እስከ ከፍተኛ የአዛዥነት ደረጃ የሚገኝ የሰራዊት አባል ሁሉ ምንጊዜም ሊረሳ የማይገባው፡ ሰራዊቱ የተቋቋመውና የሚተዳደረው ጎስቋላው አርሷ አደር ገበሬ፡ ሰራተኛው ሌላውም የህብረተሰብ ክፍል በድሃ ጎኑ ከአፉ ነጥቆ በሚከፈለው ግብር እንደሆነና አላማውና ተልዕኮውም የአገሩን ዳር ድንበር ለማስከበርና ለወገኑ አለኝታ መከታ እንዲሆን እንጂ፡ አገሩን አሳልፎ  ለመስጠት ወይንም አገሩን አሳልፈው ከሚሰጡ አገር ሻጭ የወሮበላ ቡድን ጎን እንዲሰለፍና ወገኑ እንዲወጋ አይደለም። የኢትዮጵያን አገራዊ አንድነትና ሉአላዊነት ለማስከበርና ለመጠበቅ ‘’ከራስ በፊት ለአገር’’ ብሎ ቃለ ማሃላ የፈፀመ የማነኛውም የአገር መከላከያ ሰራዊት አባል፡ አገር አንድነትና የሉአላዊነት አደጋ ከየትኛውም አቅጣጫ ይምጣ ከየት፡ አደጋውን የመመከትና ሴራውን የማክሸፍ ታሪካዊ፡ ህጋዊና ሙያዊ ግዴታ አለበት።

ባለፉት የህወሓት 23 የሰቆቃ አመታት የአገራችን አንድነት ተናግቶ፡ ከራስህ ጥቅም በላይ በቅንነትና በቆራጥነት ለማገልገል ቃለ መሃላ ሰጥተህ የተሰለፍክላት አገርህ ከአንድ የውጥረት ሁኔታ ወደ ሌላ የባሰ የውጥረት ሁኔታ እየተሸጋገረች፡ አንድነቷንና ሉአላዊነቷን በሚፈታተን የባንዳ አገዛዝ እየሾረች፡ የኢትዮጵያ ህዝብ መብቱ ታፍኖ፡ ጥቂቶቹ የአገዛዙ ቡችሎች በድሎት የሚንደላቀቁባት፡ ሰፊው ህዝብ ታይቶ ተሰምቶ ለማያውቅ መረን የለቀቀ ችግር ተዳርጎ የጉስቅልና ኑሮ በሚገፋበት፡ ዜጎች ከሚወዷት አገራቸው በገፍ የሚሰደዱባት፡ ብዙዎች መዳረሻቸው ሳይታወቅ በርካቶች ለአሰቃቂ ሞት እየተዳረጉ ወዘተ.... ያለበት ጊዜ እንደሆነን ለአንተ ለመናገር መድፈር ለቀባሪ ማርዳት እንዳይሆን እሰጋለሁ። ታዲያ ይህ ሁሉ በአገርህና በወገንህ ሲፈፀም ዝምታው ለምን ይሆን? አገልግሎትህስ ለህዝብ (የህዝብን መብት ለማስከበር) እና የአገርን አንድንትና ሉአላዊነት ለማስጠበቅ አይደለምን?

የፋሽስቱ ወያኔ አገዛዝ የህዝብን መብት ለማፈንም ይሁን፡ የአገዛዝ ዕድሜውን ለማርዘም በሚያደርጋቸው የውክልና ጦርነቶች፡ የራሱን ወገን ከቤቱና ከቀየው ለማፈናቀል ይሁን፡ የአገርን መሬት እንዳሻው ቆርሶ ለባዕድ ለመስጠት ወዘተ..... በመሳሪያነት የሚጠቀመው የአገርህን አንድነትና የወገንህን ክብር ለማስጠበቅ ቃለ መሃላ የፈጸምከውን አንተኑ መሆኑ ነው። ይህ ደግሞ ክስተቶችን እጅግ አሳዛኝ ያደርጋቸዋል። ይህ በባንዳዎች የተዋቀረ የጉጅሌው ወያኔ ቡድን በማናለብኝና በትዕቢት ተወጥሮ በሱዳን አዋሳኝ የፈጸመው የአገራችንን ድንበርን ቆርሶ ለባዕድ የመስጠት ሴራ የአገር ክህደት ለመሆኑ ምንም ጥርጥር የለውም። በወታደራዊ ህግ እንደሚታወቀው ማንም ከጠላት የተባበረና ተግባሩ በመረጃ የተረጋገጠበት ሁሉ አድራጎቱ አገር ክህደት ስለሆነ ቅጣቱ የማያወላዳና ግልጽ ነው። ፋሽስቱ ወያኔ ደግሞ የአገርና የህዝብ ጠላት መሆኑን ለማስረገጥ ማስረጃ ካስፈለገ ሩቅ ሳናማትር ድንበር ቆረሶ ለባዕድ ሱዳን መስጠቱን መመልከት ብቻ በቂ ነው። ስለዚህ ከአገር ሻጩ የጉጅሌው ወያኔ ጎን መቆም በአገር ክህደት ያስጠይቃልና ቆም ብለህ ዳግም ልታጤነው ይገባል ስል ወገናዊ ምክሬን ዳግም እለግስሃለው። በርግጥ ነገ እንደ ጤዛ የሚረግፍና እንደ ጉም የሚተን ጊዜያዊ ጥቅምን በማስቀደም የአገዛዙ ተቀጣሪና አገልጋይ በመሆን የአገዛዙ ጭቆና መሳሪያ መሆንና በአገር በህዝብ ላይ ግፍና በደል እንዲደርስ በማስቻል በታሪክና በህግ ፊት በግልም ሆነ በወል ተጠያቂ መሆን ምርጫው የእያንዳንዱ መለዮ ለባሽ ሰራዊት አባል ነው።

ስለዚህ የተከበራችሁ የሰራዊቱ አባላት የሆናችሁ ሁሉ ዘረኞቹ ወያኔዎች በሚያደርጉት በዚህ እጅግ አሳፋሪ የአገር ክህደት ተግባር ተባባሪ ላለመሆን መጠንቀቅና መወሰን  “እምቢ!” ማለት ያሻል። ይህን ስታደርግ በህግና በታሪክ ፊት ተጠያቂ ከመሆን አንተን ብቻ ሳይሆን የልጅ ልጆችህን ከዝንታለም ሃፍረት ፀፀት ታድናለህ። በመጨረሻም ከዚህ በኋላ የአገራችንን ዳር ድንበር እየሸነሸነ ለባዕድ የሚሰጠውን፡ የአገራችንን አንድነትና ሉአላዊነት እንዲሁም ህዝቧን እያዋረደ የሚገኘውን ፀረ- ኢትዮጵያዊ ህወሓት የተባለ የወሮበላ ቡድን ለመቅበር አገር ወዳዱ የኢትዮጵያ ህዝብ አቅም በፈቀደለት መንገድና በልዮ ልዮ መልክ እያደረገ ያለውን የሞት የሽረት ትግል በመቀላቀል የዜግነት ግዴታችሁን ትወጡና አገራችሁን ነፃ ታወጡ ዘንድ ወገናዊ ጥሪያችንን በአፅንኦት እናቀርባለን።

ድል ለኢትዮጵያ ህዝብ!

No comments:

Post a Comment