Monday, January 27, 2014

መፍትሄው በአንድነት መነሳት ብቻ ነው!

ስለአገራችን ኢትዮጵያ ያልተዳፈ ያልተነገረ በህዝቦቹም ላይ ያልተፈጸመ በደልና ግፍ የለም እየተፈጸመም ነው፡፡ ወያኔዎች የኢትዩጵያን ህዝብ በአንድ ብረት /አጥር/ ውስጥ ተዘግቶበት እንደሚኖር አንበሳ አድርገውታል። ከነሱ ጩኸትና የውሸት ፕሮፓጋንዳ ሌላ እንዳይሰማና እንዳያይ አድርገው የውጭ ሚዲያዎችን ሁሉ በመዝጋት አደንቁረው ረግጠው እየገዙት ይገኛሉ፡፡  የእስከአሁኑም ግፍ ጭቆናና በደል አልበቃ ብሏቸው በነሱ አቀማመር ቀጣይዎቹንም አሰርት አመታት ከአንድ ብሄር በተውጣጣው በህውሃት ቅኝ ግዛት ስር የሚቆይበትን ሥልት እያመቻቹ ነው፡፡

እንደሚታወቀው ህወሃት/ኢሕአዴግ ግን የሚያስጨንቀውና የሚያራውጠው ወይም እንቅልፍ የሚነሳው የሃገርና የህዝብ ጉዳይ ሳይሆን የስልጣን ዘመኑን የሚያራዝምበትን ስትራቲጂዎችን መቀየስ በመሆኑ ለዚህም እኩይ አላማውን ለማሳካት ይረዳው ዘንድ በአሁኑ ወቅት የትኛውም የኢትዩጵያ ህዝብ ሳይወድ በግድ ህወሃት/ኢሕአዴግን እንዲደግፍና አባል ማድረግ እንደዋነኛ አማራጭ ወስዶ ህዝብን በመሰብሰብና በማስጨነቅ ላይ ይገኛል፡፡  በመሆኑም ካድሬዎቹን ከከተማ እስከ ገጠር መንደሮች በማሰማራት ህዝብን በሃይል በማስማፈራራትና በማሰር እንዲያውም በገንዘብ በማታለል በአባልነት እንዲፈርም እያደረገ ነው፡፡ አባል ያልሆነውን ሠራተኛውን ከሥራ በማባረር ገበሬውንም መሬቱን በመንጠቅ ህዝቡን ለረሃብና ለስደት እንዲጋለጥ አድርጐታል፡፡


የመንግስት ሰራተኛውም ሆነ ገበሬው በስብሰባ ተወጥሮ የሥራ ጊዜውን በከንቱ እያባከነ የነሱን ጩኸት እንዲያዳምጥና በነሱ ሰይጣናዊ መንፈስ እንዲጠመቅ ወያኔ ሃይል በመጠቀም ላይ ሲሆን የአገሪቱንም ኢኮኖሚ ለራሱ አላማ ማስፈጸሚያ እያዋለው ይገኛል፡፡

እንግዲህ ይህ ሁሉ ሽርጉድ ለአንድ አምባገነን ፓርቲ ህዝብን አፍኖ ለሚገዛ ለሚገድልና በሰው ደም ለሚቀልድ እድሜ ማራዘሚያ ተብሎ ለስብሰባ ወጪ ማድረግ አባል ለሆነ በሚል በብዙ ሚሊዩን ብር የሚቆጠር አበልና ትራንስፓርት በመከፋፈል የመንግስት ገንዘብ ማባከን ምን ያክል በሃገርና በህዝብ ላይ መቀለድ ነው፡፡ በአጠቃላይ በተደጋጋሚ እንደተገለጸው የሃገር ነጻነት ሊመጣ የሚችለው በአንድነት በመተባበር ሲሆን ለዚህም ሁሉም የተቃዋሚ ፓርቲዎች አንድ የሆነ ወያኔን የማስወገድ አላማና ለአንድ አገር ለአንድ ህዝብ ነጻነት የሚታገሉ መሆናቸውን አምነው ትግሉን ሲቀላቀሉ ብቻ ነው፡፡ ለዚህ ስኬት ተባብረን የምንነሳበት ጊዜ አሁን ነው። በአንድነት እንነሳ፤ አንድነት ሃይል ነው!

ድል ለጭቁኑ የኢትዮጵያ ህዝብ!

No comments:

Post a Comment