Saturday, May 3, 2014

‪‎አምቦ‬- ትናንትና ዛሬ


ስለ አምቦ ስጠየቅ ብዙ ጊዜ የምመልሳት መልስ አለች። መልሴን ከእንግሊዞቹ አባባል ነው የወረስኳት። አዎ አምቦ ትንሽ ነች፤ ስሟ ግን ግዙፍ። እናም ብዙውን ጊዜ «ይህቺው ነች አምቦ?» የሚል ነው ጥያቄው። መልሴን ከመመለሴ በፊት ከተማዋን ለሁለት ከሚከፍላት ከሁሉቃ ወንዝ ድልድይ ወስዳቸዋለሁ። «ከዚህ ድልድይ ስር የሚፈሰው ይታያችኋል? አዎ በድልድዩ ስር የሚፈሰው ውሃ ሳይሆን የታሪክና የፍቅር ውሁድ ነው!!» እላቸዋለሁ።

ከ1992 ዓ/ም በኋላ አምቦን ያስተዋላት ሰው ይህቺን ከተማ ግልገሎቿን በጉልበተኛና ነጣቂ አዳኝ በየጊዜው ከምትነጠቅ ምስኪን እናት ጋር ሊያመሳስላት ይችላል። በ1992፣ 1994፣ 1996፣ እና በ1998 ዓ/ም በርካታ የአምቦ አጠቃላይ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪዎችን ሕይወት የቀጠፉ የተለያዩ የተቃውሞ ሰልፎች ተደርገዋል። በሀገራችን ካሉት አንጋፋ ከተሞች አንዷ ብትሆንም የእድሜዋን ያህል ግን አላደገችም። አምቦ ለምን የእድሜዋን ያህል አላደገችም የሚለውን ጥያቄ ብዙዎች ከድህረ ደርግ የፖለቲካ ምህዳር ጋር ያያይዙታል። የአምቦ ሕዝብ ሰው ወዳድ፣ እንግዳ ተቀባይ እና ተቻችሎ መኖርን የሚያውቅ ሕዝብ ነው። የዚያኑ ያህል ደግሞ እንደማንኛውም ሰው ሲረግጡትና ሲጫኑት የሚቀበል ሕዝብ አለመሆኑ በተለያዩ ጊዜያት ታይቷል። አምቦ የሚለው ስም ከጭካኔ ጋር የተያያዘ የሚመስላቸው ግለሰቦች ጥቂት አይደሉም። ብዙዎቻችን የአምቦ ልጆች ከአምቦ እንደመጣን ስንናገር በሰዉ ዘንድ መገረም ሲፈጠር ብዙ ጊዜ ታዝበናል። አምቦ የ«ሰው» ሀገር የማይመስላቸው ብዙዎች ናቸው። የዚህ ሁሉ ምንጩ የሀሰት ፕሮፓጋንዳ ነው። ኢህአዴግ በምዕራብ አዲስ አበባ በኩል ሲገባ አምቦ ላይ የገጠመው አልህ አስጨራሽ ጦርነት አምቦ ይህንን ስም እንድታገኝ እንዳደረገ ብዙዎች ያምናሉ። «በጥንቃቄ እና በማስተዋል ካልታዩ ሚዲያዎች ጨቋኙን ተጨቋኝ፣ ተጨቋኙን ደግሞ በዳይ አድርገው ያሳያሉ» ያለው ማልኮም ኤክስ ነው መሰለኝ።


አምቦና የተቃውሞ መዲናነቷ

የአምቦ የተቃውሞ መዲናነት በንጉሱ ጊዜ እንደጀመረ መናገር ይቻላል። በ1950ዎቹ መባቻ የተመሰረተውና በዘመናዊው የኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ የመብት ጥያቄን በተደራጀ መልኩ በመጀመር ፋና ወጊ የሆነው የሜጫና ቱለማ መረዳጃ ማህበር የተመሰረተው በአምቦ ነበር። ይህ ማህበር ለሕዝቡ ያበረከታቸው መልካም ነገሮችና ያደረጋቸው የተለያዩ ትግሎች እና ተጋድሎዎች በተለያዩ የታሪክ ድርሳናት ተጽፈው ይገኛሉ። የማህበሩ አባላትም ገሚሱ በሕይወት ይገኛሉ። የቀድሞው የሀገራችን ፕሬዝዳንት መቶ አለቃ ግርማ ወ/ጊዮርጊስ ከማህበሩ መስራች አባላት አንዱ ነበሩ።

በ1983 ዓ/ም የኢህአዴግ ጦር በምዕራብ በኩል ወደ አዲስ አበባ ሲገሰግስ አምቦ ላይ ነበር ያልታሰበ እክል የገጠመውና ብዙ ተጋደልቲዎችን የሰዋው። አምቦ ጥብቅ በር በመሆን አላስገባ ብላ የጥቂት ታጋዮችን ህልም አጨናግፋ ነበር። ከዚህ በተጨማሪም በቀድሞው የሃገሪቱ መሪ ኮ/ል መንግስቱ ኃ/ማርያም አፍ አምቦ በጀግንነት መወደሷ ተደማምሮ አምቦን ደመ መራራ አድርጓታል። ለዘመናት ሳታድግ ቆርቁዛ የቀረችውም በዚያ በቀል ነው ብሎ የከተማው ሕዝብ ያምናል። በሃገራችን ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ እና ከሐረማያ ዩኒቨርሲቲ በመቀጠል ሶስተኛው የከፍተኛ ትምህርት ማዕከል የነበረው የያኔው «አምቦ እርሻ ኮሌጅ» ወይም የአሁኑ አምቦ ዩኒቨርሲቲ ነበር። ይህ እርሻ ኮሌጅ እንኳ ወደ ዩኒቨርሲቲነት ያደገው ትናንትና እንደሆነ አብዛኞቻችን እናውቃለን። ኢህአዴግ አምቦን ከመቆጣጠሩ ጋር ተያይዞ አንድ የሚነገር ቀልድ አለ። ወታደሩ አንዱን የከተማውን ነዋሪ «አታ ለዚህ ኮተማ ሽሙ ማነው?» ሲል ይጠይቀዋል። በወታደሩ የተናደደውም የአምቦ ነዋሪ «አኒ ሂንቤኩ» ሲል ይመልሳል። ወታደሩም ሬዲዮውን ከፍቶ «ጆግናው የኢህአዴግ ሠራዊት የአኒሂንቤኩን ከተማ በቁጥጥር ስር አውሏል!!» ሲል አስተላለፈ። ( «አኒ ሂንቤኩ» በአፋን ኦሮሞ እኔ አላውቅም ማለት ነው።)

የደደቢት የእግር ኳስ ቡድን በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ መሳተፍ በጀመረበት ዓመት ድንቅ የሆነ ብቃት አሳይቶ ያለመሸነፍ ሲገሰግስ እንደነበር ይታወሳል። ይህ የደደቢት ያለመሸነፍ ግስጋሴ የተገታው በጊዜው በአምቦ ስታዲየም ጨዋታዎቹን ያደርግ በነበረው የሙገር ሲሚንቶ እግር ኳስ ቡድን ነው። ሙገር ደደቢትን አሸነፈ። ከዚህ የጨዋታ ዓመት በኋላ ሙገር ሲሚንቶ በተለያዩ ሰበባ ሰበቦች ምክንያት ሰፊ የሕዝብ ድጋፍ ባለው በአምቦ ከተማ ላይ ሲጫወት አልታየም። የዓለምአቀፉ እግርኳስ ፌዴሬሽን ፊፋ «goal project» በሚል ፕሮግራም በሶስት የአፍሪካ ሃገራት ከሚያሰራቸው ዓለም ዓቀፍ ደረጃቸውን የጠበቁ የእግር ኳስ ማሰልጠኛ ማዕከላት ግንባታ ፕሮጀክቶች አንዱ አምቦ ላይ እንዲሰራ የተወሰነው ነበር። አንድ አስርት ዓመት ያለፈው ይህ ፕሮጀክት እስካሁን ድረስ ተጠናቆ ስራ ላይ አልዋለም። በመንግስት ከተማው ይቀየር የሚል ሀሳብ ቀርቦ በፊፋ ባለስልጣናት እምቢታ አምቦ ላይ እንዲሆን እንደተወሰነም በወቅቱ ተወርቶ ነበር። ይህና ሌሎች መሰል ምክንያቶች የከተማው እድገት አቀንጭራዎች እንደነበሩ በሰፊው ይወሳል። ሎሬት ጸጋዬ ገብረመድኅን «ምነው አምቦ?» በሚለው ግጥማቸው የትውልድ ከተማቸውን የሚሞግቱት በነቢይ አይን ይመስለኛል፤ ምክንያቱም ይህ ግጥም የተጻፈው በ1960 ዓ/ም ነው። የዚያኔ ደግሞ ከተሞቻችን ያን ያክል ያደጉበት ወይም ወደ ኋላ የቀሩበት ጊዜ አልነበረም። የዚያ ግጥም እውነታ ግን ዛሬ በገሃድ ግዘፍ ነስቶ ይታያል።

አምቦ እና የተቃውሞ መዲናነቷ ሲነሳ መቼም ሳይነሳ የማይታለፈው የተማሪዎች ንቅናቄ ነው። በቀዳማዊ ኃ/ሥላሴ ጊዜ «ማዕረገ ሕይወት ቀ/ኃ/ሥ ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤት» ሲባል የነበረውና በደርግ ጊዜ «መስከረም ሁለት ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤት» የሚል ስያሜ የነበረው የ«አምቦ አጠቃላይ ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤት» ጉልህ ሚና ተጫውቷል። ይህ ትምህርት ቤት ለአምቦ ከተማ እና ለመላው ኦሮሚያ የተማሪ ንቅናቄ እንደ መነሻ ደወል አገልግሏል። አምቦ የተነሳ እሳት እንደሰደድ ይዳረሳል። በከተማው ያሉ የመጀመሪያ ደረጃ ት/ቤቶችም የትልቁን ትምህርት ቤት ፈለግ ወዲያውኑ ተከትለው ነበር፤ ምንም እንኳን በዚያ እድሜ ያሉ ሕፃናት የሚቃወሙትን ነገር በርግጥ መረዳታቸው ጥያቄ የሚፈጥር ቢሆንም። በዚህ ትምህርት ቤት የተነሱና የንጹሃን ተማሪዎችን ሕይወት የቀጠፉትን ተቃውሞዎች በቅደም ተከተል እንመልከት።

1960ዎቹ- እኔ ያልተሳተፍኩበት ወይም ያልታዘብኩት የተቃውሞ ታሪክ ነው። ይህ ታሪክ በቅርቡ በወጣው የዶ/ር መረራ ጉዲና መጽሃፍ ላይ በጥሩ ሁኔታ ተገልጿል። አካባቢውን ሲያስተዳድሩ በነበሩት በራስ መስፍን ስለሺ የጭቆና አገዛዝና ሌሎች የስርዓቱ ችግሮች ላይ የተነሳ ተቃውሞ ነበር። የዶ/ሩን ባለ ረዥም ርዕስ መፅሃፍ ይመለከቷል (የኢትዮጵያ ፖለቲካ ምስቅልቅል ጉዞና የሕይወቴ ትዝታዎች፤ ከኢትዮጵያ ተማሪዎች ንቅናቄ እስከ ኢህአዴግ-2006)።

1992 - ይህ ዓ/ም የምስራቅ አፍሪካ የዝናብ ምንጭ ተብሎ የሚታወቀው የባሌ ደን በእሳት የወደመበት ጊዜ ነበር። በወቅቱ እሳቱን ያስነሳው መንግስት ነው የሚል እምነት በሰፊው በሰዉ ልብ ሰርጾ ነበር። ለዚህም ምክንያት የሚሆነው በባሌ ደኖች ውስጥ የኦነግ ሰፊ ጦር ይገኛል ተብሎ መታመኑ ነው። ኦነግን ለማጥፋት እሳቱን መንግስት ለኮሰ፣ አግባብ አይደለም ተባለ። እነዚህን ባለ ብዙ መቶ አመት ዕድሜ ዛፎች ከመጥፋት እናድን፤ እሳቱን እናጥፋ የሚል ጥያቄ ይዘው ተማሪዎቹ ሰላማዊ ሰልፍ ወጡ። በጥይትና በዱላ ተቀበሏቸው። ብዙዎች ተደበደቡ፤ ጥቂቶች ሞቱ። የሰላማዊ ሰልፉ መሪዎችና አስተባባሪዎች የነበሩት የትምህርት ቤቱ ምስጉን የደረጃ ተማሪዎች እነ ገላና ነዲ እና እነ ሚሊዮን ቤለማ እንዲሁም ብዙ ሌሎች ታሰሩ። በዚህ አላበቃም። በወቅቱ የትምህርት ቤቱ ርዕሰ መምህር አቶ ገብረሚካኤል አቦምሳ ይባል ነበረ። በትምህርት ቤቱ ያሉትን የኦነግ አባል የሆኑ መምህራን ስም ስጥ ተብሎ ሲጠየቅ የተወሰኑ ስሞችን ሰጠ። በስም ዝርዝሩ ውስጥ የነበሩት መምህራን ስምም አቶ ስንቅነህ ዱሬሳ፣ አቶ ቀኖ ወዬሳ፣ አቶ መረራ ፋና፣ አቶ መርጋ ለገሰ፣ አቶ ፉፋ እና አቶ ዱጋሳ ፊጤ የሚል ነበር። የነዚህን መምህራን መታሰር እና የደረሰባቸውን የሰብአዊ መብት ጥሰት አስመልክቶ ኢሰመጉ በየአመቱ በሚያወጣቸው ጥራዞች ውስጥ ተመልክቷል፤ የ1995 ዓ/ም እትሙን መመልከት ይቻላል። አስመልክቶየኦህዴድ አባል ወይም ደጋፊ ያልሆነ ሰው «ኦነግ» የሚል ታፔላ እንደሚለጠፍለት አስረጅ አያስፈልገውም። እነኚህን መምህራን አንድ የሚያደርጋቸው የኦህዴድ አባላት ያለመሆናቸው ነበር። እሳቱም ብዙ ጥንታዊ ሃገር በቀል ዛፎች ፈጅቶ ጠፋ። ከጥቂት መንገላታት እና እስር በኋላ ተፈቱና ኑሮ ቀጠለ።

1994- በወቅቱ የተቃውሞው ምክንያት የነበረው የማዳበሪያ ዋጋ መናርና የእህል ዋጋ መርከስ ነው። መንግስት ለምግብ ዋስትና የሰበሰበውን እህል ወደ ገበያ በመልቀቁ ምክንያት ነው የእህል መርከስ ደረሰ ተብሎ የተነገረው። ተማሪ እዚህ ውስጥ ምን አገባው የሚል ሊኖር ይችላል። አምቦ አጠቃላይ ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤት የሚማሩት የአምቦ ከተማ ተወላጆች ብቻ ሳይሆኑ በዙሪያው ካሉ ወረዳዎች ገጠር እና ከተሞች የሚመጡ የገበሬ ልጆችም ጭምር ናቸው። ለምሳሌ በሃገራችን የከፍተኛ ትምህርት ተቋም መግቢያ ፈተና ታሪክ ከፍተኛውን ውጤት ያመጣው ልጅ ከዚሁ ትምህርት ቤት የወጣ ነው፤ ነገር ግን የአምቦ ከተማ ልጅ አይደለም። የማዳበሪያ እዳ የተቆለለባቸው የገበሬ ልጆች በከተማ ያለው ኑሮአችን ከበደብን እንዴት እንማር ሲሉ ጥያቄያቸውን አቀረቡ። ቤተሰቦቻችን ተራቡ ሲሉ ኡኡታቸውን አሰሙ። የከተማው ተማሪ የናንተ ችግር ነው በማለት አላለፈውም። ችግራችሁ የኛም ነው በማለት አብሮ ተቃውሞውን አሰማ እንጂ። ፈጥኖ ደራሽ ፖሊስ መጥቶ ጊቢ ውስጥ ገብቼ ተማሪ ልደብድብ በማለት ሲጠይቅ በሬሳዬ ላይ ተራምዳችሁ ብቻ ት/ቤቱ ጊቢ ትገባላችሁ በማለት ከልክሎ በሚወረወረው የድንጋይ ዝናብ መሃል ሆኖ «እባካችሁ ልጆቼ ተዉ» ሲል የሚማጸን አንድ ድንቅ ሰው ነበር። በወቅቱ የትምህርት ቤቱ ርዕሰ መምህር የነበረው አቶ ታዬ ዋጋሪ!! ለብዙዎች ምሳሌ ሊሆን የሚችል ድንቅ ሰው!! ተቃውሞው አብቅቶ ከተማው እንደተረጋጋ ወዲያው ከቦታው አነሱት። የደግ ሰዎች እጣ ፈንታ!! ከትምህርት ቤቱ ቅጥር ጊቢ ውጪ ግን ብዙዎች ተደበደቡ፤ ቁጥሩ በውል ያልተረጋገጠ ሞትም ተከሰተ።
1995- በአምቦ ከተማ የሚገኙ ሁሉም ትምህርት ቤቶች በነሱ ያልተፃፈ መፈክር እና መልዕክት ይዘው የሚወጡበት አንድ በየአመቱ የሚመጣ ክብረ-በዓል ነበር። የኦህዴድ የምስረታ በዓል። ተማሪው በግድ ውጡ ልንባል አይገባም። አንወጣም አለ። ጥቂት ረብሻ ተፈጠረ። ከዚያ በኋላ እኔ እስከማስታውሰው የኦህዴድን ምስረታ ለማክበር ተማሪዎች በሰልፍ መውጣታቸው ቀረ። የፈረደባቸው የመንግስት ሰራተኞች ብቻ መሰለፍ ጀመሩ።

1996- በተሳሳተ መረጃ ምክንያት የተነሳ ተቃውሞ ነበር። ተወዳጁ የአፋን ኦሮሞው ድምፃዊ ሂርጳ ጋንፉሬ ተገደለ በሚል መረጃ ምክንያት የተነሳ ተቃውሞ ተነስቶ ነበር። ሂርጳ ጋንፉሬ የፖለቲካ መልዕክት ያላቸው ዘፈኖቹ በኦሮሞ ሕዝብ ልብ ውስጥ የቀሩለት ዘፋኝ ነበር። ሂርጳ ጋንፉሬ አልሞተም። የተማሪ ስሜታዊነትና የተቃውሞውን ሌጋሲ የማስቀጠል ፍላጎት የፈጠሩት ተቃውሞ እንበለው? በዚህ ጊዜም ባልተረጋገጠ ወሬ በተነሳ አሳዘኝ ተቃውሞ ብዙዎች ተጎድተዋል።

1998 - የጥቅምት ወር መገባደጃ የመጨረሻ ቀናት። አቶ አለማየሁ ኡመታ የትምህርት ቤቱ ርዕሰ መምህር ነበር። 10ኛ ክፍል ተማሪዎች ከሚማሩበት አንዱ ክፍል ገብቶ አንድ ተማሪ ደብተሩን ይዞ እንዲወጣ ነገረው። ይህ ሞት የተፈረደበት ተማሪ ጃገማ በዳኔ ይባላል። ከዚህ በፊት በነበረው ተቃውሞ ታስሮ ከትምህርቱ ተስተጓጉሎ ስለነበር አንገቱን ደፍቶ መማር የጀመረ ልጅ ነበር። ጃገማ አሁንም የተማሪ ተቃውሞ ልትመራ ትችላለህ ስለዚህ ወደ ቤትህ ሂድ ተብሎ እንደተጠራ ይነገራል። ከትምህርት ቤቱ ግቢ መውጫ በር ሲደርስ ግን ጥይት ነበር የጠበቀው። ጃገማ ደሙ ፈሶ የሞተው ትምህርት ቤቱ በር ላይ ነበር። ያ በር ላይ ደሙ እየፈሰሰ የሞተ ወጣት ምስል የኔን ጨምሮ ከብዙዎች ሕሊና እስከዛሬ አልጠፋም። እርሱ ለዘልዓለም ያሸለበበት የትምህርት ቤቱ በርም አስከዛሬ ተዘግቶ ይገኛል። የሚያሳዝነው ነገር ጃገማ በጥይት ሲመታ ያየና ወደርሱ የሮጠው ሌላ ልጅም አዚያው መገደሉ ነበር። ጥቁር ቀን። የጃገማን እነ የሁለተኛውን ልጅ ሞት ተከትሎ በቀብራቸው ዕለት አምቦ ውስጥ ታይቶ የማያውቅ ሰላማዊ ሰልፍ ተደረገ። ከአንድ ወር ላለፈ ጊዜም ትምህርት ቤቱ ተዘግቶ ሰነበተ። ሰላማዊ ሰልፉ ከከተማው ጫፍ እስከ ጫፍ የተደረገ ነበር። አቶ አለማየሁ ኡመታም ስራውን ስለሚያውቅ ተሰወረ።

2006- የዚህን ተቃውሞ መነሻ መግለጽ አስፈላጊ አይደለም። አምቦን ጨምሮ በተለያዩ ቦታዎች የንፁሃን ደም ፈሰሰ። አምቦ ላይ ግን እንደተለመደው የሕፃናት ደም ተገበረ። እንደተለመደው ለድንጋይ ውርወራ መልሱ ጥይት ሆነ። ሕፃናቱ ይህንን አስልተው ይደርሱበታል ብሎ ማንም አያምንም። ሕፃናት ናቸውና ጥበቃ ያስፈልጋቸው ነበር። እንዲጠብቃቸው የተጠራው አጥፊያቸው ሆነ። የልጆቹ ደም ሳይደርቅና የታጠቁ ወታደሮች በከተማው ውስጥ እያሉ ከቀጣዩ ሰኞ ጀምሮ ወላጆች ልጆቻቸውን ወደ ትምህርት ቤት እንዲልኩ ታዘዙ። እሳቱን ማጥፋት/ማስወገድ ትተው ልጆቻችሁን ወደ እሳቱ አስገቧቸው ተባሉ። እነኚህ ሕፃናት አሁንም ሕፃናት ናቸውና ምንም ነገር ሊያደርጉ ይችላሉ። የሞቱት ጓደኞቻቸው ደም ስሜታዊ ሊያደርጋቸው ይችላል። የዚህ ጊዜ የእነሱንም ደም ደመ ከልብ የሚያደርጉት ፖሊሶች ባሉበት ሁኔታ ወደ ትምህርት ይግቡ ተብሎ ተወስኗል።
ነገሩ አልተፈጸመምና እግዚአብሄር ይጠብቃቸው። እግዚአብሄር ይጠብቀን።. . . . .ሌላ ምን ይባላል?

No comments:

Post a Comment