Tuesday, April 14, 2015
በአሉቧልታ ማሳ ላይ ቅጥፈት ዘርቶ እያዘመረ ጫን ጫን ውሸት የሚያመርተው መንግስት
በኢትዮጵያችን የመንግስታት ታሪክ ውስጥ በቅጥፈት የወያኔን አገዛዝ ከቶም የሚስተካከለው አይገኝም፡፡ ሲጀመር የስርዓቱ ህዋስ ህወሓት ልክ እንደ አሜባ በሀሰት እግሮቹ እየተራመደ ከደደቢት ወደ ምኒልክ ቤተ መንግስት የመጣ ነው፡፡ ለድፍን 24 ዓመታት ሲጓዝ በባጀባቸው የቅዠት ዓለም ጎዳናዎችና የመንደር ውስጥ መንገዶች ላይም በራሱ እግሮች ሲጓዝ መቸም ቢሆን የተከሰተበት ጊዜ ፈጽሞ የለም፡፡ ብአዴን፣ ኦህዴድና ደህዴን የሚሰኙ የብሄር ድርጅት ስሞች አሉ፡፡ ነገር ግን በፖለቲካ ስጋና ደም ርዕዮተ ዓለም ጥምረት ቆመው ነብስ የዘሩ አካላት ሳይሆኑ ግዑዛን ናቸው፡፡ ስለዚህ ኢህአዴግ የሚሉት የፖለቲካ ድርጅት የተንዘረፈፈ የሀሰት ሙዝ ዛፍ ነው፡፡ ከላይ የሚታዩት ሰዎችም ቢሆን በገሀዱ አለም ፈልገን ልናገኛቸው የማንችል ቀይ መፅሐፍ ተንተርሰው በማሸለብ ለዘላለሙ አንቀላፍተው በረሀ ላይ የቀሩ ናቸው፡፡ የተዳበለ ስብዕና ባለቤቶች ስለሆኑ እለት ከዕለት የሚፈጽሙትን ስህተት በውል አይረዱትም፡፡
ወያኔ እንደ አንድ የአገር መንግስት ሰይሆን ከአንድ ግለሰብ ያነሰ ተክለ ቁመና ባለቤት ነው፡፡ ወያኔ ራሱን ይዋሻ፤ አባላትና ደጋፊዎቹን ይዋሻል፤ የኢትዮጵያን ህዝብ ይዋሻል፤ ዓለምን በጠቅላላ ይዋሻል፤ ሌሎች ተቀብለው እንዲዋሹለትም ያገሪቱን አንጡራ ሀብት ይከሰክሳል፡፡ ስሙን ቀይሮ አብዮታዊ ዴሞክራሲ ይበለው እንጂ የሚከተለው ርዕዮተ ዓለም ውሸት ነው፡፡
ቅጥፈት ከወያኔ ብልሹ ባህሪያት ውስጥ አንዱና ዋነኛው ነው፡፡ ወያኔ ልዩ ልዩ ፋብሪካዎችን በማቋቋም ፋንታ ራሱ የውሸት ማምረቻ ፋብሪካ ሆኗል፤ ወያኔ ውሃ በቧንቧ በማሰራጨት ፋንታ በአየር ሞገድ አማካኝነት ያለማቋረጥ ውሸት ያሰራጫል፡፡
ወያኔ ቁጥር ስፍር የሌላቸው ብሄራዊና ዓለማቀፋዊ ውሸቶችን ሲዋሽ ኖሯል፡፡ ረሃብ፣ ጥማትና እርዛት በአንድ እየዶሎቱ በችጋር ዱላ ለዘመናት ከደበደቡት የኢትዮጵያ ህዝብ ገላ ላይ ታትሞ በጉልህ የሚታየው የድህነት ጠባሳ ዋና አስረጅነቱ እንዳለ ሆኖ ኦክስፎርድ ዩኒቨርሲቲና የተባበሩት መንግስታት የልማት ፕሮግራም ሪፖርት የዘመነ ወያኔ ኢትዮጵያን ከአስሩ መናጢ ድሃ አገሮች ተርታ አሰልፎ ከኒጀር ቀጥሎ በዓለም በድህነቷ ሁለተኛ ደረጃ ላይ እንደምትገኝ በጥናቱ እያረጋገጠ ወያኔ በጎን ይዋሻል ያስዋሻል፡፡
ኢትዮጵያ በመከላከያ ተቋሟ ከምድራችን ከሚገኙ አገሮች ጋር ተወዳድራ በሰው ኃይልና በመሳሪያ ብዛትና ጥራት ከአፍሪካ አራተኛ ከዓለም ደግሞ 46ኛ ደረጃ ላይ ተቀመጠች ተብሎ በራሱ በወያኔ እንድ የማህበራዊ ድረ ገፅ የወጣው የሰሞኑ ወሬ ደግሞ ሌላኛው ዓለም አቀፋዊና ከ2007 ዓ.ም ታላላቅ ውሸቶች አንደኛው ነው፡፡
ግሎባል ፋየር ፓወር ተቋም በ2015 ዓ.ም የ106 አገሮችን ወታደራዊ አቅም በደረጃ አስቀመጠና ኢትዮጵያ 340 ሚሊዮን ዶላር ወታደራዊ በጀት፣ 2300 ታንክ፣ 81 የጦር አውሮፕላንና 182 ሺህ ሠራዊት አላት ተብሎ በወያኔ ማህበራዊ ድረ ገፆች የተለቀቀው ይህ ወሬ ነጭ ውሸት መሆኑን ይናገራል የቀድሞው የአየር ኃይል የተዋጊ ሄሊኮፕተር ስኳድሮን አዛዥና የበረራ አስተማሪ የነበረው ሻለቃ አክሊሉ መዘነ ፡፡
ወያኔ ለጊዜያዊ ስልጣንና ንዋይ ጥሙ መቁረጫ የሚሆኑ የግፍ መፍለቂያ ጥልቅ፣ ጥልቅ ጉድጓዶችን ይቆፍራል እንጂ የኢትዮጵያና ህዝቧ ዘላቂ ጥቅም እንኴን በውኑ በህልሙም አቃዥቶት አያውቅም፡፡ በመሆኑም ለሩብ ምዕተ ዓመታት በስልጣን ላይ ሲቆይ ህዝቡን በጉልበት ረግጦ የሚገዛበትን ክንዱን ሲያፈረጥም እንጂ የአገሪቱን ሉኣላዊነት በመጠበቅ ለዘመናት ሳይደፈር የኖረውን ዳር ድንበሯን ሊያስከብር የሚችል በሰው ኃይልም ሆነ በጦር መሳሪያ ብዛትና ጥራት የተደራጀ ለአንዲት ኢትዮጵያ በእንድነት የመቆም ስነ-ልቦና ያለው የሀገር መከላከያ ሰራዊት አልገነባም፡፡
ከዚህ ይልቅ በማይድን አፍቅሮተ ስልጣን ደዌ የተለከፈው ወያኔ በጎሳ ቤተ ሙከራ ውስጥ ቀምሞ ለስልጣን እድሜ ማራዘሚያ ክኒንነት በባንዳነት ፋብሪካ ውስጥ ያመረተውን ሰራዊት ከጓድ መሪ እስከ ላይ እስከ ኤታማጆር ሹሙ ድረስ የሞያ ብቃትን ከግምት ውስጥ ባላስገባ መልኩ በቋንቋና የበከተ ፖለቲካ ወንፊት በተጣሩ የተዳበለ ስብዕና ባላቸው በአንድ በታኝ በሆነ የብሄር ፖለቲካ አራማጅ ድርጅት አባላት ብቻ በማዋቀርና እንደ ፌሮ በጠነከረ እዝና ቁጥጥር ሰቅዞ ይዞ መተንፈሻ በማሳጣት ጎራ ለይቶ እርስ በርሱ አንዲሰላለፍና በተስፋ መቁረጥ ረግረግ ውስጥ ቆሞ እስካንገቱ ድረስ እንዲጠልም ብሎም የማንነቱን ኢትዮጵያዊ ስነ-ልቦና ጭምር እንዲሰለብ አድርጎታል፡፡ በመሆኑም ራሱን ነፃ ለማድረግ በአሁኑ ጊዜ ባገኘው ቀዳዳና አጋጣሚ ሁሉ በመሹለክ ወደ በረሃ በመኮብለል የነፃነት ትግሉን በመቀላቀል ላይ ይገኛል፡፡
በተለይም ደግሞ 81 የጦር አውሮፕላን ታጠቀ የተባለው አየር ኃይል አባላት ተዋጊ ሄሊኮፕተርና ጀት ድረስ ይዘው ከአየር ምድቦቻቸው ሰማይ ድንገት እየተሰወሩ በመጥፋት ላይ መሆናቸውን ሁሉም ሰው የሚያውቀው ሃቅ ነው፡፡
የጎሳና ፖለቲካ እግረ ሙቅ ያጠለቀው አየር ኃይል የሰላም ማስከበር ግዳጁን በብቃት ሳይወጣ በመቅረቱ አገሪቱ በዓለም አቀፉ ወታደራዊ መድረክ ላይ የውርደት ሸማ እንድትከናነብ ሆኗል፡፡
በኃይል ስር ሰድዶ የተንሰራፋ የአመራር ንቅዘት፣ የአስተዳደራዊ ማነቆ፣ ጎዘኝነት፣ የሞያ ብቃቱ የተረጋገጠ የሰው ኃይል አለመኖር፣ የጥገና መለዋወጫ መሳሪያና አጠቃላይ የሆነ የሎጅስቲክ እጥረት ቢሾፍቱ የመሸገውን አየር ኃይል ባቦጋያ ሃይቅ ውስጥ በአናቱ በመትከል እየደፈቁ ሩሁን እያሳቱት የሚገኙ ዋና ዋና እና መቼም ቢሆን ሊፈቱ የማይችሉ ችግሮች ናቸው፡፡ ታድያ ለጥቂት ጊዜም ቢሆን በጣዕረ ሞት ላይ ለመቆየት የውጭ አገር ዜግነት ያላቸው አብራሪዎችን ከአገሪቱ አቅም በላይ በሆነ ከፍተኛ ክፍያ እስከመቅጠር ደርሷል፡፡
የምድር ኃይሉም ቢሆን በአብዛኛው ማለት በሚቻል ሁኔታ ከዚህ ቀደም ምንም አይነት የውጊያ ልምድ የሌላቸው ገና አፍላ ወጣት የድሃ ልጆች ተጠቅጥቀው የሚገኙበትና ከአንደኛው የዓለም ጦርነት የውጊያ አገልግሎት ጥቅም ላይ የዋሉ እጅግ በጣም ኋላ ቀር የነብስ ወከፍና የቡድን ጦር መሳሪያዎች የታጠቀና በአስተዳደራዊ በደልና ጎሰኝነት ምሬት ውስጥ የሚገኝ ነው፡፡
ወያኔ ዋሽቶ የሚያስዋሸው የሰሞኑ ወሬ እውነት እንኳን ቢሆን አንድ አምባገነን ምንግስት ምንም ያክል ጦርና የጦር መሳሪያ ቢኖረው የጊዜ ጉዳይ ይሆናል እንጂ የመጨረሻው አሸናፊና የድል ባለቤት ህዝብ መሆኑ የማይታበል ሀቅ ብቻ ሳይሆን የተፈጥሮ ህግ ነው፡፡ ደግሞም አንዲት ፍሬ ክብሪት የምታክል እውነት የራስ ዳሽንን ተራራ የሚስተካከል የጭድ ክምርን ውሸት አንድዳ ወደ አመድነት ትቀይራለች፡፡
Subscribe to:
Post Comments (Atom)
No comments:
Post a Comment