Thursday, May 15, 2014

ዝክር ለግንቦት 7 1997 እና ለግንቦት 7 ቀን 2000 ዓ.ም.

ዘንድሮ፣ የታሪካዊው ግንቦት 7 ቀን 1997 አገር ዓቀፍ ምርጫ ዘጠነኛ ዓመት እና ንቅናቄዓችን የተመሠረተበት ስድስተኛ ዓመት የምንዘክረው ከመችውም በላይ አገራችን አሳሳቢ ሁኔታ ላይ ሁና ነው። ወያኔ የማይገዛትን አገር እንዳትኖር ለማድረግ እማትወጣው አረንቋ ውስጥ ከመክተት የማይመለስ ኃይል መሆኑን ዛሬ በአምቦ፣ በጉደር፣ በጊምቢ እና መሰል ቦታዎች በተግባር እያስመሰከረ ነው።

የኢትዮጵያ ሕዝብ በታሪኩ ለመጀመሪያ ጊዜ እውነተኛ ፍላጎቱን የመግለጽ አንፃራዊ ነፃነት አግኝቶ የነበረበት የግንቦት 7 ቀን 1997 ዓ.ም. ምርጫን ስናስብ ዛሬ ያለንበት ሁኔታ መመዘናችን አይቀርም። ያኔ ለአብዛኛው የኢትዮጵያ ሕዝብ እንደ እጁ መዳፍ ቀርባ ትታየው የነበረችው ድል እስከዛሬ አልጨበጣትም። ትግሉ ግን ቀጥሏል። የዛሬው ትግላችን የኢትዮጵያ ሕዝብ ከያኔው በበለጠ ከታሪክና ከራስዋ ጋር የታረቀች አገር የመመሥረትን ርዕይ አስፈላጊነት ላይ ትኩረት መስጠትን የሚጠይቅ ሆኗል።

ወያኔ ከተፈጠረበት ጊዜ ጀምሮ ለአለፉት አርባ ዓመታት ሲያብላላው የቆየው፤ በመንግሥት ሥልጣን በቆየባቸው ሃያ ሶስት ዓመታት ውስጥ ደግሞ በፓሊሲ ደረጃ ሲያስፈጽመው የቆየውን የዘር ፓለቲካ አስከፊ ውጤት አሁን እየታየ ነው። ይህ የዘር ፓለቲካ ራሱ ወያኔን ያጠፋዋል። ችግሩ ግን የዘር ፓለቲካ ወያኔን ነጥሎ አያጠፋም፤ ከወያኔ ጋር አገራችንንም ሊያጠፋ ይችላል። ከሁሉም በላይ አሳሳቢው ጉዳይ ደግሞ የዘር ፓለቲካ የበርካታ ኢትዮጵያዊያንን ሕይወት አደጋ ላይ ሊጥል ይችላል። በጎረቤት አገራት ውስጥ ያየነውን ዓይነት የእርስ በርስ እልቂት ወደ አገራችን ለማምጣት ህወሓትና ኦህዴድ ተግተው እየሠሩ ነው። ሌሎች የወያኔ ተቀጥላ ድርጅቶችም የዚህ ትልቅ የጥፋት ፕሮጀክት አካል ናቸው።

የግንቦት 7 1997ቱ ብሩህ ተስፋ በፋሺስቱ ወያኔ የግፍ አፈና ሲጨልም፤ ያ ተስፋ እንዲያንሠራራ በግንቦት 7 2000 ዓ.ም. የተቋቋመው ግንቦት 7: የፍትህ፣ የነፃነትና የዲሞክራሲ ንቅናቄ ዛሬ የኢትዮጵያን ተስፋ ለማጨለም ከተነሱ ኃይሎች በተፃራሪ በመቆም የሕዝብና የአገር አለኝታነቱ ማረጋገጥ ይኖርበታል።


በዚህም ምክንያት፣ በዚህ ወሳኝ ወቅት የግንቦት 7 አባላትና ደጋፊዎች የሆንን ሁሉ በከፍተኛ የኃላፊነት ስሜት መንቀሳቀስ ይኖርብናል። በግራም ይሁን በቀኝ ያለ ጽንፈኝነት አገራችን አይጠቅምም፤ የምንመኛትን ኢትዮጵያ አያመጣልንም። ሕዝባችንና አገራችንን ከዚህ አረንቋ ማውጣት የሚቻለው የአንድነትና የእኩልነት ፓለቲካን አሸናፊ ማድረግ ስንችል ነው።

በአሁኑ የኢትዮጵያ ፓለቲካ ለሀገራችን የሚጠቅማትና ትክክለኛ ነው ብለን የምናምነው ለኢትዮጵያ ሉዓላዊነት የሚታገል፤ የተለያዩ የኅብረሰተሰብ ክፍሎች በመሰላቸው መንገድ ለመደራጀት መብታቸው እውቅና የሚሰጥ፤ በኢትዮጵያ የሚገኙ ማኅበረሰቦች በሙሉ በእኩልነት የሚስተናገዱበት ሥርዓትን የሚያልም፤ መሰማማት፣ መቻቻል እና ከዚያም አልፎ መተጋገዝ ያለበት የኢኮኖሚና የፓለቲካ ሥርዓት እንዲኖር የሚታገል፤ የእምነቶች እኩልነትን የሚያከብር፤ በታሪክ ውስጥ የተፈፀሙ በደሎችን መርምሮ ማኅበራዊ እርቅ ለመፍጠር ፍላጎት ያለው ፓለቲካ ነው።

ይህ ዓይነቱ የአንድነትና የእኩልነት ፓለቲካ በአሸናፊነት እንዲወጣ ማድረግ ይቻላል ብሎ ግንቦት 7: የፍትህ፣ የነፃነትና የዲሞክራሲ ንቅናቄ ያምናል። ይህ ለሁላችንም የሚበጀው ፓለቲካ አሸናፊ ለማድረግ የሚከተሉትን መፈፀም ይጠበቅብናል።


  1. በማንኛውም የኢትዮጵያ ክፍል ውስጥ የሚደርስ የሰብዓዊ መብት ጥሰት በፍጹም የማንታገስ መሆኑን ማመንና በተግባሮቻችንም ይህንኑ መግለጽ፤
  2. ኢትዮጵያ ከገባችበት ችግር መውጫው መንገድ ወያኔን ማስወገድና በምትኩ የዜጎችን እኩልነት የሚያረጋግጥ፣ ሕዝብን ከሕዝብ የሚያስታርቅና የሚያስተሳስር መንግሥት መመሥረት መሆኑን ማመንና በተግባሮቻችን ማሳየት፤
  3. የኢትዮጵያ ዋነኛ ጠላቶች ወያኔ እና ተቀጥላዎቹ፣ በተለይም ህወሓት፣ ኦህዴድ፣ ብአዴን እና ደህዴድ መሆናቸውን በማመን ትኩረታችንን ነቀሎ ወደሌላ ከሚወስዱ አስተሳሰቦችና ድርጊቶች መቆጠብ፤
  4. በብሔር ከተደራጁ ኃይሎች ጋር በሚለያዩን ነገሮች ላይ ሳይሆን በሚያስተባብሩን ጉዳዮች ላይ በማተኮር የወያኔን የከፋፍለህ ግዛ አጀንዳ ማክሸፍ፤
  5. በስሜትከተሞሉ የአጭር ጊዜ እይታዎች ለእርስ በርስ ግጭቶች ከሚዳርጉ አስተሳሰቦችና ተግባራት መቆጠብ፤ እና
  6. አርቆ አስተዋይነትና ታጋሽነት በተላበሰ መንገድ ለኢትዮጵያ ሕዝብና ለኢትዮጵያ ደህንነት፣ለፍትህና ለነፃነት በግንባር ቀደምትነት መቆም፤

የግንቦት 7 ንቅናቄ አባላትና ደጋፊዎች ከላይ የተዘረዘሩትን ለመፈጸም የሚቻለንን ሁሉ ለማድረግ ያለንን ዝግጁነት እየገለጽን፣ መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ወያኔና ግብር አበሮቹ ከፊቱ የደቀኑበትን ከፍተኛ አደጋ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ተባብሮ እንዲያስወግድ ግንቦት 7: የፍትህ፣ የነፃነትና የዲሞክራሲ ንቅናቄ ጥሪውን ያቀርባል።

አስቸጋሪ ወቅት ላይ የምንገኝ ቢሆንም እንኳን በርትተን ከታገልን የተረጋጋች፣ ዲሞክራሲያዊ ሉዓላዊ አገር – ኢትዮጵያ – ይኖረናል። ለዚህ ውጤት በርትተን እንታገል።

ክብር የግንቦት 7 1997 ሀገራዊ ተስፋን እውን ለማድረግ ለወደቁ ሰማዕታት!

ድል ለኢትዮጵያ ሕዝብ !!!

No comments:

Post a Comment