Thursday, May 1, 2014

“ዘረኝነት ትልቅ በሽታ ነው!”


በአስራት አብርሃም

ዘረኝነት ትልቅ በሽታ ነው። በዘረኝነት የታወረ ሰው ስለእውነት፣ ስለአብሮ መኖር አይጨነቅም፤ ምክንያቱም ብሩህ የሆነ መጪ ጊዜ አይታየውም፤ የለውምም። ለሁሉም ነገር መፍትሄውን ሳይሆን ጨለማውን ነው የሚታየው። ጠቡ ከህዝብ ጋር ነውና ለበሽታው በቀላሉ መፍትሄ የሚገኝለት አይደለም። እውቀት፣ ሚዛናዊነት እና ሰብኣዊነት በእርሱ ህሊና ላይ ወንበር አይኖራቸውም። ሰውን ያህል ክቡር ፍጡር በጅምላ ይፈርጃል፤ በጅምላ ያወግዛል፤ በጅምላ ይመርቃል፤ በጅምላ ይረግማል። ከዚያ በኋላ በመጨረሻ መፍትሄ ሆኖ ወደ አንጎሉ ሊመጣለት የሚችለው ነገር ሜንጫ ወይም ገጀራ ነው የሚሆነው። በዚያ ገጀራ ደግሞ አንገት ለመቅላት ወደ አደባባይ ይወጣል፤ ሄዶ ሄዶም ይሄ የጥላቻ አዝመራ ፍሬ ማፍራቱ አይቀርምና እልቂት፣ በዘር ተለያይቶ መጨፋጨፍ ይሆናል ውጤቱ።

እንደዚህ ዓይነቱን በሽታ ወደ ሌሎች እንዳይጋባ ማድረግ የሚቻለው አንድም በተቻለ መጠን የመረጃ ክፍተቱን በመሙላት፣ እውነት የሆነውንና እውነት ያልሆነውን በበቂ እውነት አስደግፎ ለይቶ በማሳየት ነው። አንድም ደግሞ እንደዚህ ያለውን አስተሳሰብ የበላይነት አግኝቶ የትውልድ እልቂት ከማድረሱ በፊት በሀሳብ፣ በፖለቲካና በማነኛውም አውድ መታገልና ማጋለጥ ሲቻል መሆኑ ልብ ሊባል ይገባል። ምክንያቱም ከህዝብ እና ከሀገር የሚበልጥ ነገር ስለሌለ! እንዲሁም ለእውነት መቆም በሚያስፈልግ ስዓት ዋጋ የሚያስከፍል ቢሆን እንኳ ለእውነት መቆም የህሊና ጥያቄ ስለሚሆን ነው። በመሰረቱ አንድን ህዝብ ለይቶ በጅምላ የሚጠላ እና የሚያወግዝ የማንም ወዳጅ ሊሆን አይችልም። እስካሁን ከዓለም ታሪክ እንደምንማረው ስለፍትህ፣ ስለእኩልነትና አብሮ በሰላም ስለመኖር የታገሉት እንጂ በዘረኝነት መንገድ ቁልቁለት የተጓዙ ሲያሸንፉም ሆነ ክብር ሲያገኙ አላየንም። በዓለም ላይ ሁሉ ሰብአዊነት እና የሰውን ክቡርነት እየገነነ በሚሄድበት ጊዜ አንዳንዱ ደግሞ በባለፈው ዘመኑ ተኝቶ ይኖራል፤ ያ ዘመኑ ‘ሃንጎበር’ ሆኖ ስለሚጫጫነው ቶሎ መንቃት ይከብደዋል፤ ስለዚህ ገፋ ቢል ያቃዠው እንደሆነ እንጂ እውነተኛ ትንሳኤ አይኖረውም።


የዛሬው ፅሁፌ መነሻ ባለፈው ሳምንት የእንቁ መፅሔት እትም ላይ አምሳሉ ገ/ኪዳን አረጋው የተባለ ሰው “ወያኔ የትግራይን ሕዝብ ፈጠረ ወይስ የትግራይ ሕዝብ ወያኔን?” በሚል ርዕስ በቅጥፈት ያላልኩትን እንዳልኩ አስመስሎ ጥላሸት ቢቀባኝ ግርምት ቢፈጥርብኝ ነው። ‘ሰዓሊ’ መሆኑ ለዚህ ሳያግዘው አልቀረም። ስለእኔ ሲናገር እንዲህ ነው ያለው፤
“ለምሳሌ በአንድ ወቅት አቶ አስራት አብርሃ ከኢሳት ሬድዮና ቴሌብዥን ጋር ባደረጉት ቃለ መጠይቅ፣ አቶ ገብሩም እንደዚህ ለቮኦኤ በሰጡት ቃለ መጠይቅ ሌሎችም እንደዚሁ በተለያዩ አጋጣሚዎች ሲያነሱት እንደሰማነው የትግራይ ህዝብ በወያኔ እንደተከዳ ይናገራሉ። አቶ አስራት ካሉት ብጠቅስ ‘የትግራይ ሕዝብ ወያኔ ከገባልን ቃል አልፈፀመልንም ከሚለው አንዱ በወሎ በኩል የትግራይ ድንበር አለ ውኋ ምላሽ ነው ብሎ ህዝቡ ያምናል’ ይሉና ወያኔ ግን እስከዛሬ ድረስ ይሄንን ድንበር አላስመለሰም በማለት በቁጭትና በብስጭት ያነሳሉ።”

ከላይ ያለው አባባል አርቲስት ጌትነት እንየው በግጥሙ፤

‘ የማይቻል አንድ ነገር…
እውነት- ቤት ስትሰራ:-
ውሸት- ላግዝ ካለች
ጭቃ ካራገጠች
ምስማር ካቀበለች
ቤቱም አልተሰራ
እውነትም አልኖረች።”

እንዳለው ዓይነት ነው። እንደዚህ ዓይነቱ አገላለፅ የእውነትና የውሸት ዲያሌክቲካል ተጣምሮ ያለው ነው። በመሰረቱ ከኢሳት ጋር ያደረኩት ቃለ መጠይቅ ከአረና ከለቀቅኩ በኋላ የተደረገ ስለነበር በአረና አመራርነቴ የሰጠሁት አልነበረም። የቃለ መጠይቁ ምክንያት “የውህደቱ ቁማርተኞች” የሚል ፅሁፍ በመፃፌ ነበር። ቃለ መጠይቁን የተከታተሉ ሰዎች መገንዘብ እንደሚችሉት እጅግ በጣም ፈታኝ የሚባል ዓይነት አጠያየቅ የተከተለ ነበር። እንደዚህ የሆነበት ምክንያት በዚያ ጽሁፍ ላይ በኢትዮጵያ ስላለው የፖለቲካ ኃይሎች አስላለፍ መሰረታዊ የሆነ ነገር በማንሳቴ ነው። ይሄም ቢሆን ግን አዲስ አልነበረም በ“ፍኖተ ቃኤል” መፅሀፌ ላይም በስፋት የዳሰስኩት ጉዳይ ነበር። የሆነ ሆኖ ቃለ መጠይቁ ምንም ሳይቀናነስና ሳይቆራረጥ በመተላለፉ በጣም ደስ ብሎኛል። ይሄ በእንቁ ላይ ተወለጋግዶና ሌላ መልክ ይዞ እንዲወጣ ስለሆነው ርዕሰ ጉዳይ ግን የተወሰነ ብል ደስ ይለኛል፤ በዚህ አጋጣሚም ‘google’ ላይ “with special guest Asrat Abraham” በሚል ‘search’ በማድረግ ሙሉውን ቃለመጠይቅ ማዳመጥ እንደሚቻል ለመግለፅ እፈልጋለሁ።

በቃለ መጠይቁ መሀል ከወሎ እና ከጎንደር ወደ ትግራይ ሄዷል ስለሚባለው መሬት ጥያቄ አነሳልኝ፤ እኔ ደግሞ በመርህ ላይ የተመሰረተ መልስ ለመስጠት ጥረት አደረኩ። እኔ ባለኝ እውቀት ወደ ትግራይ የመጣ መሬት ብቻ አይደለም ያለው፤ ከትግራይም መሬት ሄደዋል ለምሳሌ ወደ አፋር ምድር የተጠቃለለ መሬት አለ፣ በአገው በኩል ወደ አማራ ክልል የተከለለ መሬት አለ። እንደዚሁም ከጎጃም ወደ ኦሮሚያ እና ወደ ቤንሻንጉል የተከለለ መሬት አለ፤ ከዚህ ሁሉ ይሄ ወደ ትግራይ መጣ ስለሚባለው መሬት ብቻ ጮህ ተብሎ የሚነገርበት ምክንያት ለምን ይመስለሃል? ብዬ ነው ራሱ ጋዜጠኛውን መልሼ የጠየኩት። ከሁሉም በላይ ደግሞ ያለባሀር የቀረንበት ጉዳይ እያለ፤ የአሰብ ጉዳይ እያለ፤ ሌሎች ያለአግባብ ለኤርትራ የተሰጡት መሬቶች እያሉ ይሄ በራሳችን ሉዐላዊነት ውስጥ ያለመሬት ጎልቶ የፖለቲካ አጀንዳ እንዲሆን ሲደረግ ጤናማ ነገር አይደለም።

ምክንያቱም ጎንደርም ትግራይም በአንድ ሀገር ውስጥ ነው ያለው፤ መሬቱ የትም አልሄደም፤ ለአስተዳደር ያልተመቼ፣ ለኗሪውም ህዝብ ያስቸገረ ነገር ካለ ደግሞ መፍትሄ የሚሆነው የስርዓት ለውጥ አድርጎ ዴሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ በዚያ የሚኖረው ህዝብ ወዴት ነው መከለለ የምትፈልገው ተብሎ በሪፈረንደም ይጠየቅና አብዛኛው ወደመረጠው ይከለላል። ከዚህ ውጪ ግን ይሄ የትግራይ ነው፣ ይሄ የወሎ ነው የሚባል ቋሚ የሆነ ድንበር በሌለበት ሁኔታ፣ አከላለሉም አንዴ ሲሰፋ አንዴ ሲጠብ ለዘመናት በኖረ ምድር ላይ ስለተወራ ብቻ እውነትም መፍትሄም ሊሆን እንደማይችል ነው ያስቀመጥኩት። በኃይል የሚደረግ ነገር ደግሞ ሌላ ብጥብጥ፣ ሌላ ጦርነት ያስከትል እንደሆነ እንጂ ዘላቂ ነገር እንደማያመጣ ነው፤ በዚህ ላይ ደግሞ ለዴሞክራሲ የሚደረገውን ትግል ሊያጓትት የሚችል፤ በስልጣን ላይ ያለውን ኃይል ዕድሜ የሚያስቀጥል ነው የሚሆነው የሚል ነበር የእኔ ሀሳብ። ለምሳሌ የትግራይ ህዝብ ድንበራችን “አለ ውኋ” ምላሽ ነው የሚል እምነት እንዳለው ገልጫለሁ። አያቴ ወደ አዲስ አበባ ስንመጣ ወንዙን በመስኮት በማሳየት የትግራይ ድንበር እዚህ ድረስ ነው ብሎውኛል። በሌላ በኩል ደግሞ አንድ የኦነግ አመራር የኦሮሞ መሬት ከኬኒያ እስከ መቀሌ ነው ማለታቸውን አውቃለሁ። ስለዚህ ሰዉ እንደመሰለው ብዙ ሊያወራ እንደሚችል ከመግለፅ ውጪ ህወሀት ድንበሩን አላስመለሰም ብዬ አልተናገርኩም፤ አልወቀስኩምም። የትግራይ ህዝብ ዓረና እሚደግፍበት ምክንያትም የዴሞክራሲ፣ የልማት፣ የፍትህ፣ በነፃነት የመናገርና የመደራጀት መብት አልተከበረልኝም ብሎ ነው እንጂ ፀሀፊው እንዳለው ህውሀት ዘርፎ ስላላመጣት አይደለም።

እንዲህ ዝም ብሎ እኮ ያለ ምንም ማስረጃ በጥንቆላ አይወራም። በመጀመርያ ሀገሩን ዞሮ ማየትና ማወቅ ይገባዋል። የትግራይ ገበሬ ከጎጃሙ ገበሬ በምን እንደሚሻል፤ መቀሌ ከባህረዳር ወይም ከአዳማ ወይም ከአዋሳ በምን እንደሚበልጥ ማሳየት ይኖርበታል። የትግራይ ህዝብ ማለት የህወሀት ባለስልጣናት ማለት ካለሆነ በስተቀር አሁን ካለው ስርዓት ሰባራ ሳንቲም አይግኝቶ እንደማያውቅ መመስከር እችላለሁ። አርስቶትል ከእውነት በላይ ማንም አይበልጥብኝም እንዳለው እኔም ከእውነት በላይ ላስቀድመው የምችለው ነገር የለም። በመሰረቱ ህወሀትን እያዳኑ፣ ዓረና እና ህዝቡን መስደብ የማን አጀንዳ ሊሆን እንደሚችል ሳስበው የሚፈጥርብኝ ግርምት መግለፅ ከምችለው በላይ ነው።

ሌላው የገረመኝ ነገር ደግሞ ፀሀፊው “ወያኔ የትግራይ ሕዝብ ለደርግ ጥላቻ እንዲኖረውና ከጎኑ እንዲሰለፍ ለማድረግ ደርግ በሕዝቡ ላይ የፈፀመው አስመስሎ የፈፀማቸው የግፍ ሴራዎች ስለሰመሩለት” ማለቱ ነው። ደርግ ግፍ አልፈፀምም ለማለት ተፈልጎ ነው! ይሄ ነገር ፍቅረ ስላሴ ወግደረስ ወይም ለገሰ አስፋው ቢሆን ያለው ብዙም ላይገርመኝ ይችል ነበር። ለምሳሌ ፍቅረ ስላሴ ወግደረስ “መንግስቱ ኃይለማርያምን የምወቅስበት የሞራል ልዕልና የለኝም” ብለዋል፤ ቢወቅስ ነበር የሚገርመው፤ አብሮ የሰውን አንገት ሲቀነጥስ የነበረ ሰው ነውና።

ፀሐፊው ማንን ወክሎ እንደሚናገር ግልፅ ባይሆንም “ስለዚህ የኢትዮጵያ ሕዝብና የፖለቲካ ፓርቲዎች ከወያኔ ጋር ስላለብን ችግሮች መደራደር ካለብን ከትግራይ ሕዝብ ጋራ ነው ማለት ነዋ? ወያኔ የፈጠረብን ችግሮች ሁሉ በወያኔ መወገድ አብረው የሚወገዱና የሚፈቱ አይደሉም ማለት ነዋ?” ይለናል። እና ህዝቡን እንዳለ ማስወገድ ፈልገ እንዴ! ለዚህ ሰው ኢትዮጵያዊ ማለት ወይም ኢትዮጵያዊነት ምን ማለት ይሆን!

No comments:

Post a Comment