Tuesday, May 27, 2014

እንኳን አደረሳችሁ፤ ተስፋና ሕልም ያለ ሕግ ከሚያሰቀጡበት፣ “በሕግ” ወደሚያስወነጅሉበት አገዛዘ ተሸጋግረናል

በመስፍን ነጋሽ

አገርን በራስ የግልና የአካባቢ ተሞከሮ ብቻ ለመበየን መሞከር ውስንነቶች እንደሚኖሩበት አሳምሬ አውቃለሁ:: የዚያኑ ያህልም አገር ያለ ግለሰቦች ተሞክሮ ቁንጽል ተረት ከመሆን አይድንምና የግል ተሞክሮ ርካሽ ነገር እንደሆነ አንቆጥርም።

የዛሬ 23 ዓመት የት ነበርኩ? ዛሬ የት ነኝ የሚሉትን ሰፊ ጥያቄዎች ወደ መመለስ አልሄድም:: 23 ዓመት ለአገር አጭር ቀን ነው። በአገሩ ለሚኖሩ ሰዎች ግን ሙሉ ዕድሜያቸው ወይም እኩሌታው ሊሆን የሚችል ነው። ህወሓት ኢሕአዲግ የዛሬ 23 ዓመት አዲስ አበባ ሲገባ የእኔ ትውልድ የደርግን መሄድ በትልቅ ተስፋ ሲጠብቅ ነበር። ተስፋችን ግን የሚመጣውን በማወቅ ላይ የተመሠረተ አልነበረም፣ ያለውን በመጥላትና በመፍራት እንጂ። በወቅቱ ደርግ እና ሌሎቹም ስለ ህወሓት ኢሕአዲግ ሲሉ የከረሙት ብዙ ቢሆንም የሚባለውን ለመመርመርም ሆነ የመጣውን ለመጠየቅ የሚያበቃ ቅንጦት አልነበረንም። በጭቆና ውስጥ ያለ ህብረተሰብ የለውጥ አጋጣሚ ካገኘ “ይሄኛው ጨቋኝ ሲሔድ የሚተካው የባሰ ሊሆን ስለሚችል፣ ከለመድኩት ጋራ ልኑር” የሚል ቅንጦተኛ ሊሆን አይችልም። ጭቆና ማለት ዜጎች ያለውንም ሆነ የሚመጣውን ሕይወታቸውን ለመረዳትና ለማቀድ እንዲሁም ለመቆጣጠር የማይችሉበት ሥርዓት ነው። ስለዚህ ምርጫቸው ወደፊት እየሄዱ የሚመጣውን ማየት ብቻ ነው። የህብረተሰብ የዕድገት ታሪክም ይህን ያሳየናል።(ዛሬ ደርሶ “ግብጾች ሙባረክ ይሻላቸው ነበር” የሚሉን ቅንጡዎች፣ ህወሓት ከሔደ ሰማይ ይወድቃል የሚሉን ነብያት ችግር ሳይገባኝ ቀርቶ ግን አይደለም፣ አሁን ዩክሬንም ማጫፈሪያ ሆናለች መሰለኝ።)ለማንኛውም፣ እኛም ከታጠቀ ገዳይ
ወደ ታጠቀ ዘራፊና ገዳይ አስተዳደር የተሸጋገርነው በዚሁ ምርጫ አልባ የአገዛዝ ሥርዓቶች የሽግግር ሕግ ነበር። ሆኖም ተስፋ አደረግን። ተስፋ ማድረግ ወደሚቻለበት ዘመን የተሸጋገርን መሰለን። ለራስም ሆነ ለአገር የተለየ ሕልም ማለም፣ ባያሸልም እንኳን የሚያሰቀጣ መሆኑ የቀረ መሰለን። “ቀርቷል አሉን”፣ አመንናቸው። ልብ ብሎ ላየው፣ በዘመነ ደርግ ያ ሁሉ ወጣት የረገፈው ወይም ትውልዱ እርስ በርሱ የተጫረሰው “ከእኛ የተለየ ተሰፋ ለምን ኖረህ? እኛ ካለምነው የተለየ ሕልም ከየት አመጣሽ?” እየተባለ ነበር። ተስፋና ሕልም ወንጀል ተደረጉ። ሰውን በተስፋው፣ በሕልሙ፣ በሐሳቡ የተነሣ እንደ ወንጀለኛ መቁጠር ተራ ነገር ሆነ፣ ይህም ሳይበቃ ወንጀሉ በሕግ እንኳን ሳይተረጎም የተሰፋ ወንጀለኞች ያለርሕራሄ ተገደሉ፣ ታሰሩ፣ ተሰቃዩ፣ ተሰደዱ። የአገራቸውን ሕልም በተለየ መንገድ ለመተርጎም የሞከሩ እንደ አውሬ ታደኑ፣ እድለኞች ታሰሩ ወይም ተሰደዱ፣ ሌሎቹ በግፍ ተገደሉ። የደርግ ሥርዓት ማለት በአንድ መልኩ ይህ ነበር። ይህ ስርአት ሲሄድ ከተስፋ ሌላ ምን ይታያል?

ተስፋችን እውነት የመሰለበት ጊዜም ነበር። ከነብዙ ጉድለቱ ሥርአቱ ተስፋችንን እያዳበርን የምንጓዝበትም ነበር፤ ወይም መስሎን ነበር። በእርግጥም ኢሕአዲግ ከደርግ የሚሻልባቸው ነገሮች ነበሩት። የግፉ መጠን የቀነሰ ስለመሰለን በሒደት ፍትሕ የሚሰፍን መሰለን። ተሳስተን ነበር። ወደ ስልጣን የመጣው ቡድን የዴሞክራሲም ሆነ የአዎንታዊ ማህበረሰባዊ ሽግግር ግብ እንደሌለው ለመረዳት ጊዜ ወሰደብን፣ ካላየን አናምንም እንዳልነው እነሆ እያየን እያመንን መጣን።

በመጨረሻም የዛሬ 23 ዓመት የተደረገው ሽግግር ምን አይነት እንደሆነ በገሃድ እያየን ነው። ደርግ ተስፋንና ሐሳብን ወንጀል አድርጎ “ወንጀለኞቹን” ለመቀጣት የቃል ትእዛዘ ይበቃው ነበር። ደርግ የተለየ ሕልም አይተዋል ወይም ተርጉመዋል የሚላቸውን ለማጥፋት ቀላጤ በቂው ነበር። በድካሙ ለማደግ፣ አገሩን በቻለው መንገድ ለመጥቀም ተስፋ የሚያደረግ ሰው ዛሬም ወንጀለኛ ሊባል ይችላል። በደምና በጥቅም ሰንሰለት ለተያያዘው ቡድን የማይጥም ሕልም ማለም ለቶርቸርና ለረጅም ዘመን እስራት ሊዳርግ ይችላል። ለውጡ አሁን ቅጣቱ የሚወሰነው የወሮበላ መፈንጫ በሆኑ “የፍትሕ” “ተቋማት” መሆኑ ብቻ ነው። ሌላው ለውጥ ኢሕአዲግ የተደራጀ አፋኝ ብቻ ሳይሆን የተደራጀ ዘራፊ መሆኑም ነው። ደርግን ለጣሉልን ወገኖቻችን አክብሮታችንን እንቸራቸዋለን። ነገር ግን መስዋእትነታቸው በቁማርተኞች መታገቱን ቢያውቁ ምንኛ ባዘኑ።

የበቀለ ገርባ ወንጀል የበጎ ተሰፋና የቀና ሕልም ባለቤት መሆኑ ነው። ይህን የሚጠራጠር ቢኖር በድፍረት ደርሶብህ እየው እላለሁ። የርእዮት ዓለሙ ወንጀል የተለየ ሐሳብ ባለቤት መሆኗ ነው። ይህን የሚጠራጠር ቢኖር በድፍረት ደርሶብህ እየው እላለሁ። የአቡበከር አህመድ ወንጀል እምነታችሁን አከብራለሁ፣ እምነቴን ተዉልኝ ማለቱ ነው። ይህን የሚጠራጠር ቢኖር በድፍረት ደርሶብህ እየው እላለሁ። የዞን 9 ልጆች ወንጀል የበጎ ተሰፋና የቀና ሕልም ባለቤት መሆናቸው ነው። ይህን የሚጠራጠር ቢኖር በድፍረት ደርሶብህ እየው እላለሁ። በተመሳሳይ ብዙ ስሞች መዘርዘር ይቻላል፣ በደርግም ጊዜ ይቻል ነበርና። እነዚህ ሰዎች በተከሰሱበት ድርጊት ያልተሳተፉ፣ ንጹሓን ናቸው። አንዳንድ ጊዜ እነዚህ ሰዎች “ወንጀላቸው ምንድን ነው?” እያልኩ ራሴን እጠይቃለሁ። ተስፋ ከማደረጋቸውና ለጋራ አገራችን ይበጃል ያሉትን ከማሰብና ከመመኘት የተለየ “ወንጀል” ፈለጌ አላገኘሁም። ምናልባትም በዘመነ ደርግም በተመሳሳይ ተስፋና ሕልም የተነሣ የግፉ ሰለባ ሊሆኑ ይችሉ እንደነበር ይሰማኛል። ታዲያ እንዴት አድርጌ ደርግ ሄዷል ልበል?

No comments:

Post a Comment