ኢህአዴግ ያነበረውን ቋንቋንና ዘውግን መሰረት ያደረገ ፌዴራሊዝም አደገኛነት በተመለከተ በርካታ ምሁራን፣ ፖለቲከኞች፣ ጋዜጠኞች… ሳያሰልሱ ለመምከርና ለማስጠንቅቅ መዋተታቸውን አልዘነጋሁም፡፡ እኔም ከ“ፍትህ” ጋዜጣ እስከ “ፋክት” መጽሔት ድረስ ችክ ያልኩበትም ሆነ ዛሬ በዚህ ተጠየቅ የተመለስኩበት ምክንያት ችግሩ እያደር እየተባባሰ በመምጣቱና ከምንጊዜውም በላይ አዘናግቶ ወደተፈራው የእርስ በእርስ እልቂት ሊዘፍቀን እየተንደረደረ በመሆኑ፣ ቅድሚያ ሰጥተን በሕብረ-ድምፅ ‘የሀገር ያለህ!’ ብለን መጮህ እንዳለብን ስለማምን ነው፡፡
አርባ አራት ዓመት ወደኋላ…
በኢትዮጵያ የዘውግ ጥያቄ ለአደባባይ የበቃው በ60ዎቹ መጀመሪያ እንደነበረ ይታወሳል፡፡ ከዘመነኞቹ የተማሪ እንቅስቃሴ መሪዎች ይህንን ጥያቄ አለቅጥ ለጥጦና አጋንኖ በማቅረብ ግንባር ቀደሙ ዋለልኝ መኮንን ነው፡፡ በ1962 ዓ.ም በአራት ገፅ ቀንብቦ ባዘጋጀው ታሪካዊ ጽሑፉ አማካኝነት “የብሔሮች ጥያቄ” ይፋ ሆኖ ለውይይት ከመቅረቡ በፊት፣ የተማሪው ዋነኛ የመታገያ አጀንዳ የመሬት ጉዳይ እንደነበር የታሪክ ድርሳናት ያወሳሉ (በደብዛዛውም ቢሆን ይንፀባረቅ የነበረውን መደብ ተኮር መንፈስ ሳንረሳ)፡፡ ዋለልኝ የሀገሪቱን መንግስታዊ አወቃቀርም ሆነ ባሕልን በአማራና በትግሬ ተፅእኖ ስር ስለመውደቁ በተቸበት በዚያ “ዝነኛ” ጽሑፉ ላይ እንዲህ ይላል፡-
“…ማንንም ሰው የኢትዮጵያውያን ቋንቋ ምንድን ነው ብላችሁ ጠይቁ፤ የኢትዮጵያውያን ሙዚቃ የቱ ነው ብላችሁ ጠይቁ፤ የኢትዮጵያውያን ባሕል የቱ ነው ብላችሁ ጠይቁ፤ ብሔራዊ ልብሳችሁ የቱ ነው ብላችሁ ጠይቁ፤ የአማራ ወይም የትግሬ ይላችኋል፡፡”
ይህ ሀቲት በወቅቱ በአብዛኛው ተማሪ ዘንድ ቁጣ ከመቀስቀሱም በላይ ዋለልኝን በ‹ፀረ-አማራና ትግሬነት› አስፈርጆ ለውግዘት ዳርጎት ነበር፡፡ እራሱም ቢሆን በአንድ የዩንቨርስቲው መድረክ ላይ የተሰነዘረበት ከባድ ተቃውሞ በፈጠረበት ብስጭት ‹‹እኔም አማራ ነኝ፤ ያውም ከአማራ ሳይንት-ቦረና›› ማለቱ ይታወሳል (ቦረና በተለምዶ አማራ መጥቶበታል የሚባለው አካባቢ መሆኑን ልብ ይሏል)፡፡ ግና፣ ዋናው ጥያቄ የእርሱ አማራ መሆን ያለመሆን አይደለም፤ እዚህ ድምዳሜ ላይ የደረሰበት ምክንያት ከተጨባጩ እውነታ ጋ ምን ያህል ይዛመዳል? የሚል ነው፡፡ ሌላው ነገር ደግሞ ከዚህ ጽሑፍ በፊት ብሔር ተኮር ጎዳዮችን አንስቶ ካለማወቁም በዘለለ፣ ሌሎች ሲያነሱ ፅንፈኛ ተቃዋሚ ስለነበረ ነው፡፡ ለምሳሌ ተማሪ ኢብሳ ጉተማ (ኋላ ላይ የኦነግ መስራችና አመራር የሆነው) ‹‹ኢትዮጵያዊ ማነው?›› በሚል ርዕስ ባቀረበው ግጥም እጅግ ተናድዶ ‹‹እንዴት እንዲህ አይነት ግጥም ታቀርባለህ? ዘረኛ ነህ፤ ኢትዮጵያውያንን የመከፋፍል ዓላማ ነው ያለህ?›› በማለት እስከመቃወም መድረሱ የክርክሩ አንዱ ጭብጥ ነው፡፡
ታዲያ ዋለልኝ መኮንን ድንገት እዚህ ድምዳሜ ላይ የደረሰው ከምን የተነሳ ይሆን? በርግጥ ለዚህ ድንገቴ የአቋም ለውጥ ሶስት መላ-ምቶች ሲነገሩ ቆይተዋል፡፡ የመጀመሪያው ‹በአፄው ሥርዓት ላይ አሴረዋል› ተብለው ከተከሰሱትና ‹ኦሮሞ እየተጨቆነ ነው› የሚል እምነት ከነበራቸው ጄነራል ታደሰ ብሩ ጋር በታሰረበት ወቅት፣ በጄነራሉ ስብከት አመለካከቱ ተቀይሮ ሊሆን ይችላል የሚለው ሲሆን፤ ሁለተኛው ደግሞ ‹‹መገንጠልን መደገፍ በመጨረሻ የማትገነጠል ሀገር እንድትኖር ያደርጋል›› በማለት ከተከራከረበት ከራሱ አቋም ጋር የሚያያዝ ነው፤ ሶስተኛው ‹የሻዕቢያ (ኤርትራውያን ተማሪዎች) አሊያም የአሜሪካኑ የስለላ ተቋም (ሲ.አይ.ኤ) መጠቀሚያ ሆኖ ነው› የሚሉት ዋነኞቹ ናቸው፡፡ ይሁንና ከዋለልኝ ጀርባ ‹ስውር እጅ›ን ለመፈለግ ያስገደደው በጊዜው ብዙሁ ተማሪ ለሀገሪቱ ዘርፈ-ብዙ ችግሮች ‹የንጉሣዊው አስተዳደር ኋላቀርነት እና ስግብግበነት ነው› ብሎ ከማመኑም ባለፈ፣ ከፌዴራላዊ ይልቅ የቻይና ኮሙኒስታዊ ሥርዓት አድናቂ የመሆኑ ጉዳይ ነው፡፡ ሌላው ቀርቶ የተማሪውን እንቅስቃሴ በመምራት በዘመኑ ከዋለልኝ የላቀ ተሰሚነት የነበረው ጥላሁን ግዛው ‹‹ጎሰኝነትን›› በአደባባይ አጥብቆ ይቃወም እንደነበረ፣ በ1968 እ.ኤ.አ የታተመው ‹‹Struggle›› ቅፅ 3፣ ቁጥር 1 መጽሔት ጋር ያደረገውን ቃለ-መጠይቅ መጥቀስ ይቻላል፡-
‹‹በመጀመሪያ ደረጃ በጎሰኝነትና በሶሻሊዝም መካከል ያለውን ልዩነት ማሳየት እፈልጋለሁ፡፡ ጎሠኝነት በተወሰነ አካባቢ ብቻ የሚቀርና አካባቢ ቀመስ ነው፡፡ ሶሻሊዝም ግን ዓለም ዓቀፋዊ ነው፡፡ …እንደ ዩንቨርስቲ ተማሪነታችንና እንደ እጩ ምሁርነታችን የሕብረተሰባችንን አቋም ከመደብ አንፃር መተንተን እንጂ በጎሣ መከፋፈል አይገባም›› ማለቱ ይታወሳልና፡፡
የህወሓት-ውልደት
ዋለልኝ መኮንንን ‹‹የብሔር ጭቆና›› ትንተናን መሰረት ያደረጉ ጥቂት የማይባሉ የፋኖ ድርጅቶች መመስረታቸው አይካድም፡፡ ከእነዚህም መንግስታዊውን ሥልጣን ለመጨበጥ የበቃው ህወሓት አንዱ ነው፡፡ የአማራና ትግሬ ጨቋኝነትን የሚያውጀው ጽሑፍ በተሰራጨ በአምስተኛው ዓመት የትግርኛ ተናጋሪውን ብሔራዊ ጭቆና ለማስረገጥ ጽሑፉን እንደ ሰነድ ማስረጃ ቆጥረው ‹‹ትግራይን ነፃ እናወጣለን!›› ያሉ ፋኖዎች ነፍጥ አንግበው በረሃ ቢወርዱም፣ በመጀመሪያዎቹ ጥቂት ዓመታት አካባቢ ‹‹እንታገልለታለን›› በሚሉት ዘውግ ተወላጆች ሳይቀር መናፍቅ ተደርገው መወገዛቸው ይታወሳል፡፡ ደራሲና ገጣሚ አስማማው ኃይሉም ‹‹ኢህአሠ›› በተባለው መጽሐፉ እንዲህ ይለናል፡-
‹‹በ1969 ዓ.ም አጋማሽ አካባቢ በእምባ ሰገንይቲ ወረዳ ነበለት አካባቢ ሽምዕጭ ተብሎ በሚጠራው መንደር የህወሓትና የኢሕአሠ አባላት ሕዝብን ለመቀስቀስ ተገኝተው ነበር፡፡ ሁለቱም ቡድኖች የድርጅታቸውን ዓላማ ካስረዱ በኋላ ያካባቢው አዛውንት ማሳረጊያውን ንግግር አደረጉ፡፡ አዛውንቱ መሔድ የሚሳናቸው ስለነበሩ ሰዎች ደግፈው ወደ በቅሏቸው እንዲያወጧቸው ከጠየቁ በኋላ የሚከተለውን ንግግር አደረጉ፡፡ ወደ ህወሓት አባላት እጃቸውን ዘርግተው ‹እናንተ ከሆዳችን የወጣችሁ ልጆቻችን ናችሁ›፤ ወደ ኢሕአሠ አባላትም ፊታቸውን አዙረው ‹እናንተ ደግሞ ከሁሉም የኢትዮጵያ ግዛት መጥታችሁ ለእኛ ስትሉ ነው የምትታገሉት፡፡ የሆነው ሆኖ እኛ የትግራይ ሰዎች ሆነን ስንቀር ኢትዮጵያ ከማን ጋር ልትቀር ነው? ስለሆነም እኛ ኢትዮጵያዊ ከሚል ጋር ነው የምንወግነው› ሲሉ ሃሳባቸውን ሰነዘሩ፡፡›› (ገፅ 235)
ህወሓት በትግራይም ሆነ በተቀረው የሀገሪቱ ክፍል የነበረውን አገዛዛዊ ጭቆና፣ የብሔር አስመስሎ እስከ መገንጠል ቢንደረደርም፣ የገጠመው ተቃውሞ ፕሮግራሙን ለመከለስ አስገድዶታል፡፡ ዘግይቶ ላገኘው ድጋፍም ቢሆን ከዘውግ ተኮሩ ተረት-ተረት ይልቅ አምባ-ገነናዊው የደርግ አስተዳደር የወለደው ሽብርና ጭፍጨፋ የተሻለ ጠቅሞታል፡፡ ለዚህም በዛሬይቷ ትግራይ ከሶስት ያላነሱ ፀረ-ህወሓት ድርጅቶች መኖራቸው ማሳያ ይሆናል ብዬ አስባለሁ፡፡
በሌላ በኩል ከህወሓት ምስረታ አንድና ሁለት ዓመት አስቀድሞ ወደ አደባባይ የመጡት ኢህአፓና መኢሶን የትግል አጀንዳቸው የመደብ ቅራኔ ላይ የተመሰረተ ነበር፡፡ ይህ ግን በወቅቱ ከህወሓትም በከረረ መልኩ ‹‹የብሔር ጥያቄ በመገንጠል ብቻ ነው የሚፈታው›› የሚል እምነት ተከታዩ ኦነግን ህልውና አያስክድም፡፡ እዚህ ጋ የምንመለከተው ሌላኛው ግራ አጋቢ ጉዳይ የመጀመሪያው የቀዳማዊ ኃ/ስላሴ ዩንቨርስቲ ተማሪዎችን የ‹‹መሬት ላራሹ››ን ሠልፍ (በ1957 ዓ.ም) አስተባብሮ የሕግ-መወሰኛው ምክር ቤት ድረስ የመራው ባሮ ቱምሳም (በአብዮቱ ሰሞን የኢጭአት የአመራር አባል ነበር) ሆነ፤ የመኢሶኑ ቁልፍ ሰው እንደሆነ የሚነገርለት ኃይሌ ፊዳን የመሳሰሉ የኦሮምኛ ቋንቋ ተናጋሪ ልሂቆች፣ ከኦነግ በተቃራኒው ከብሔር ይልቅ የመደብ ጥያቄ አቀንቃኝ የነበሩ መሆኑን ነው፡፡ በነገራችን ላይ በግሌ ዛሬም ቢሆን ኢትዮጵያዊ ብያኔ እነዋለልኝ የለጠጡትንና ያጎኑትን ያህል እንኳ ባይሆንም እንደገና መከለስ እንደሚያስፈልገው አምናለሁ፡፡
የሆነው ሆኖ ህወሓት መንግስታዊውን ሥልጣን በጨበጠ ማግስት ‹የሰነበተውን የብሔር ቅራኔ በማያዳግም ሁኔታ የሚፈታ› ሲል ያንቆለጳጰሰውን ቋንቋ ተኮር ፌዴራሊዝም ቢተገብርም፤ ከዚሁ ጋር ተያይዘው የሚነሱ ችግሮችን የመግታት አቅም እንደሌለው ለማረጋገጥ የአንድ እጅ ጣቶች ያህል ዓመታት እንኳን አልፈጀም፡፡ በደቡብ በጉጂ እና ጌዲዮ፣ በጉጂ እና ቡርጂ፤ በጋምቤላ በአኝዋክ እና ኑዌር፤ በቤንሻንጉል በጉምዝ እና በርታ መካከል የተከሰቱት የይገባኛል ግጭቶች በማሳያነት ይጠቀሳል፡፡
የፌዴራሊዝሙ ቀዳዳዎች
ዘውግ ተኮር ፌዴራሊዝሙ፣ ገና ከጠዋቱ ለከፋ ዕልቂት ሊዳርግ እንደሚችል በማስታወስ ይሰሙ የነበሩ የተራዘሙ ጩኸቶችን ችላ ብሎ ዛሬ ላይ ቢደርስም፤ ለፕሮፓጋንዳ በሸነቆራቸው ቀዳዳዎች እየገባ ያለው ከባድ ንፋስ ከራሱ አልፎ ሀገሪቷንም ከበታኝ አደጋ ፊት አቁሟታል፡፡ ለዚህም አገዛዙ የፈጠራ ትርክቱን ለማስረፅ የሄደበት የኑፋቄ መንገድ የአንበሳውን ድርሻ ይወስዳል፡፡ በፓርቲው ካድሬዎች በኩል በየዕለቱ የሚዘራው የጥላቻ ፖለቲካ፣ ሐውልት ማነፅ፣ ከፋፍሎ ማቆም እና መሰል ስልቱ በተጨማሪ ሜጋ በሚያሳትማቸው መጻሕፍት እልቂት ጠሪ ዘውግ ተኮር ቅስቀሳዎችን እስከማሰራጨት መድረሱን ተመልክተናል፡፡ ለአብነትም የሚከተለውን ግጥም ልጥቀስ፡-
“ነፍጠኞች እቤታቸው በክብር ይጎለታሉ፣
እኛን በኃይል አስገድደው ያሰራሉ፣
ቁጥቋጦ እንደምትመነጥረው መንጥራቸው
ወደመጡበት ወደ ሸዋ አባራቸው፡፡” (“ተራሮችን ያንቀጠቀጠ ትውልድ” ቅፅ 3፤ ገፅ 145)
ግና ‹‹ሸዋ›› ሱዳን ወይም ግብፅ አይደለምና ዛሬ ከጉራፈርዳ እስከ ደንቢዶሎና ጊምቢ ለተተገበረው የማባረር ዘመቻ ዋነኛው ተጠያቂ የሥርዓቱ ኤጲስ ቆጶሳት መሆናቸውን ግጥሙ ያስረግጣል፡፡ በግልባጩ እነዚህ ሰዎች በ97ቱ ምርጫ ዋዜማ፣ ሚያዚያ 30 ቀን መስቀል አደባባይ ቅንጅት በጠራው ሕዝባዊ ስብሰባ ላይ፣ አቶ በድሩ አደም ‹‹ወደመጡበት እንመልሳቸዋለን›› ማለታቸውን፣ ወደ ዘውግ ጥላቻ ከመቀየራቸውም በላይ፣ የቅንጅቱን አመራሮች ለቅመው ካሰሩ በኋላ የሰውየውን ንግግር ‹‹የዘር ማጥፋት ሙከራ!›› ሲሉ ለመሰረቱባቸው ክስ በማስረጃነት ማቅረባቸውን አስታውሳለሁ፡፡ በዚያው ሰሞን አቦይ ስብሃት ነጋም የብአዴን ጓዶቻቸውን ‹‹እኛ ወደመቀሌ ስንባረር፤ እናንተን መንዝ ላይ አራግፈን ነው የምንሄደው!!›› አሉ መባሉም ጉዳዩ በራስ ላይ ሲደርስ ምን ያህል አሳማሚ እና ለበቀል እንደሚያነሳሳ ሁነኛ ጥቁምታ ቢሰጥም፣ ገዥዎቻችን ትምህርት ሊወስዱበት አለመቻላቸው ያስቆጫል፡፡ እንዲያውም ከምርጫ 97 በኋላ በዩንቨርስቲዎች ግቢ የሚነሱ ተቃውሞዎች ዘውግ-ተኮር ወደመሆን ነበር የተሸጋገሩት፡፡ ኢህአዴግም ቢሆን በዩንቨርስቲዎች በተናጠል (በህወሓት፣ ብአዴን፣ ኦህዴድ እና ደኢህዴን) ስር ማደራጀት የጀመረው ከዚሁ ምርጫ በኋላ እንደነበረ አይዘነጋም፤ ለእንዲህ አይነቱ የፓርቲው ተልዕኮ ደግሞ እንደ ዶ/ር አድማሱ ፀጋዬ አይነት የገዥው-ፓርቲ መንፈስ የሰረፀበት ‹‹ምሁር›› ጠቀሜታን ለመረዳት አሁን አዲስ አበባ ዩንቨርስቲ ያለበትን ሁኔታ መቃኘቱ ብቻ በቂ ነው፡፡ በርግጥ ባለፉት ሁለት አስርታት የህወሓት አባልና ደጋፊ ተማሪዎች የግቢውን መንፈስ አይመረምሩም (አይሰልሉም) ነበር እያልኩ አይደለም፤ በግላጭ የጓደኞቻቸውን እንቅስቃሴ እየተከታተሉ ሪፖርት ያደርጉ ነበርና፡፡ በአናቱም የዘውግ ተኮር ፖለቲካው መተግበር በጀመረበት ወቅት ወደ ትምህርት ቤት የተላኩ ልጆች፣ ዛሬ ለዩንቨርስቲ መብቃታቸው፣ አጀንዳው በቅፅበት ሊፈፀም የመቻሉን እውነታ በኦሮሚያ ሰሞኑን የተመለከትነው ቀውስ በቂ ማሳያ ይሆናል፡፡
የተጭበረበረው አጀንዳ
‹የብሔር ጥያቄ ዋነኛው የቅራኔ ቅርፅ ነው› የሚለው ህወሓት ይህን ጥያቄ መፍታት ሥርዓታዊ ግብ እንደሆነ እስኪሰለቸን ቢደሰኩርም፤ አጀንዳውን ከማጭበርበሪያነት የዘለለ ዋጋ አልሰጠውም፡፡ እናም ታሪክ ቢያንስ በዚህ በኩል በበጎ እንደማያስታውሰው ለመናገርም ብዙ ማስረገጫዎችን መጥቀስ አይገድም፡፡ አሁንም ኢትዮጵያን እየናጣት ያለው፤ ጥያቄያችን አልተመለሰም› የሚሉ ብሔርተኛ ቡድኖች መበርከት መሆኑ ይታወቃል፡፡ በስያሜ ደረጃ እንኳን (መሬት ላይ ያላቸውን ጉልበት ትተን) ከአስራ አንድ የማያንሱ ተገንጣይ ንቅናቄዎች መኖራቸው እውነት ነው፡፡ የእነዚህን ከኦጋዴን እስከ ጋምቤላ፤ ከቤንሻንጉል እስከ አፋር ድረስ ያሉ አማፅያን እንቅስቃሴን የጥቂት ልሂቃን ቅብጠት አድርጎ መውሰድ ርትዕ አይሆንም (ስለምን ቢሉ ደርግም ህወሓትን የሚያስበው እንዲያ ነበርና)፡፡ እናም ከትልቁ ኦሮሞ ጥያቄ መጠለፍ ጀምሮ፤ እነዚህ ጉዳዮች አስቀድሞ ግንባሩ የብሔር ጥያቄን ለሥልጣን መወጣጫ ብቻ ለመጠቀም ማስላቱን ይጠቁሙናል፡፡
ሌላኛው ጭብጥ አሁንም ድረስ ማንነት ተኮር ጥያቄዎች አለመቆማቸው ነው፡፡ ከቅማንት እስከ ወለኔ እና ቁጫ ድረስ ያሉት ‹‹ማንነታችን ታውቆ ዞን ይሰጠን›› ጩኸቶች ማቆሚያቸው የቱ ጋ እንደሆነ ራሱ ኢህአዴግም የሚያውቅ አይመስለኝም፡፡ በግልባጩ ለእነዚህ ሶስት የማህበረሰብ ክፍሎች ጥያቄ በቅርቡ የሠጠው ምላሽ ጭፍለቃ መሆኑን ስናስተውል፤ ‹ተነሳሁለት› ከሚለው የብሔር ጭቆናን ማጥፋት አኳያ የሚነግረን ሀቅ ሥርዓቱ የሄደበትን ቁልቁለት ብቻ ነው፡፡
በሶስተኛነት ከዚሁ ጋር አያይዘን ልናነሳው የምንችለው ርዕሰ ጉዳይ የመገንጠል መብት ነው፡፡ ከዋለልኝ እስከ ጥላሁን ታከለ እና ቱሞቱ ሌንጮ (ፕ/ር እንድሪያስ እሸቴ) ድረስ የነበሩ የዘመኑ ትውልድ መንፈስ ተርጓሚዎች መገንጠልን ሕብረ-ሱታፌ (ሶሻሊስታዊ) ሥርዓት ለመገንባት መዳረሻ መንገድ አድርገው ቢያቀርቡትም፤ ጥራዝ ነጠቆቹ ህወሓቶች ሕገ-መንግስቱ ውስጥ ቀርቅረውታል፡፡ ለዚህም እንደምክንያት ‹‹መገንጠልን ለመከላከል ነው›› ቢሉም፤ ከፌደራሊዝሙ አወቃቀር አኳያ ‹የማይተገበር መብት› ስለመሆኑ ብዙ ተብሏል፡፡ ይህንን ለማስረገጥ በዋናነት ሁለት ነጥቦች ይነሳሉ፤ ‹እንደ ስታሊኒስቷ ሩሲያ ሁሉ መብቱ በሕገ-መንግስቱ ውስጥ ቢካተትም፣ የማዕከላዊ መንግስቱ ሥልጣን ፍፁማዊ መሆን እንዳይተገበር ያደርገዋል› የሚለው የመጀመሪያው ነጥብ ነው፡፡ ሁለተኛው የመብት አፈፃፀሙ ራሱ በተለያዩ አስገዳጅ ተዋረዳዊ ትግበራዎች መጠላለፉ ነው፡፡ በተለይም ሁለትና ከዚያ በላይ ዘውጎችን ያቀፉ ክልሎች የመገንጠል ጥያቄ ቢያነሱ ተፈፃሚነት እንደማይኖረው ለመረዳት የክልሎቹን አወቃቀር መመልከቱ ብቻ በቂ ይመስለኛል፡፡ ከእነዚህ ሁለት ነጥቦች ስንነሳ የመገንጠል ግብ ያላቸው እንቅስቃሴዎች በትጥቅ ትግል አገዛዙን ካላስወገዱት በቀር በሕገ-መንግስቱ መሰረት በሰላማዊ መንገድ ሊተገበሩ አለመቻላቸውን እንገነዘባለን፡፡ ይህ ሁነትም ሥርዓቱ ቋንቋን መሰረት ያደረገ ፌዴራሊዝም ያነበረው ከፋፍሎ ለመግዛት እንጂ፤ እስክንደነቁር በጩኸት ስለሚነግረን ‹‹ጭቁን ብሔር ብሔረሰቦች›› መብት ደንታ ኖሮት እንዳልሆነ ያስረግጥልናል ብዬ አስባለሁ፡፡
ግን እስከመቼ?
በዘመናዊቷ ኢትዮጵያ ታሪክ ከአፄ ኃይለስላሴ ቀጥሎ ረዘም ላለ ዓመታት ሀገሪቱን የመምራት ዕድል ያገኘው ኢህአዴግ የተሻለች ሀገር የመገንባት በርካታ ዕድሎችን አምክኗል፡፡ ወደሥልጣን በመጣ ማግስት ዘውገኝነትን የመንግስታዊ መዋቅሩ ብቸኛ ገፅ ሲያደርገው፣ ከብዙ ጫፎች ከተነሳበት ከባባድ ተቃውሞዎች መሀል፡- ቋንቋ ተኮር ፌዴራሊዝሙ ማሕበረ-ባሕላዊ መሰረቱ በጣም የተሳሳተ መሆኑን እና የዘውግ ማንነትን ብቸኛው የክልሎች ድንበር አሰማመር መነሻ ማድረግ ለእርስ በእርስ የዜጎች ትንቅንቅ ያጋልጣል የሚሉት ዋነኞቹ ነበሩ፡፡ ሥርዓቱ ይህን ጆሮ ሰጥቶ ከማዳመጥ ይልቅ ቢያፈገፍግም፣ ያሳለፍናቸው ሃያ ሶስት ዓመታት በሞቶችና በመከራዎች የተፃፉ ኩነቶችን አሳይተውናል፡፡ ‹‹ባለሥልጣን›› እና ‹‹ሥልጣን የለሽ›› (ባለቤትና መጤ) በሚል ጨዋታ፣ በየክልሎቹ የሚገኙ የሌላ ቋንቋ ተናጋሪዎች ከክልሉ የሥራ ቋንቋ ውጪ በመናገራቸው ብቻ፣ አንዳችም ተቋማዊ ውክልና እንዳያገኙ ማድረጉ፣ ከየአካባቢዎቹ በግፍ ለተፈናቀሉት የማሕበረሰብ ክፍሎች ዋነኛው መነሻ ሆኗል፡፡ አዲሱን የአዲስ አበባ የማስፋፊያ ዕቅድ ተከትሎ የተነሳው የኦሮሞ ተማሪዎች ተቃውሞም ሌላ ቅርፅ ወደመያዝ መሻገሩ አንዱ ሰሞነኛ ማሳያ ነው፡፡ በምዕራብ ወለጋ ለረዥም ጊዜ ኑሯቸውን መስርተው የነበሩት የአማርኛ ቋንቋ ተናጋሪዎች አካባቢውን ለቀው እንዲወጡ መገደዳቸው የሚቀጥል ከሆነ ደግሞ፣ የአማራ ክልልን ጨምሮ የየክልሎቹ ዘውጎች ‹‹መጤ›› ያሏቸውን ማባረር ላለመጀመራቸው እርግጠኛ መሆን የምንችልበት ምንም አይነት ዋስትና የለንም፡፡ እናሳ! ይህ አይነቱ ክልልን ከ‹‹መጤ›› ዘውግ የማንፃት ሂደት ማቆሚያው የቱ ጋ እንደሆነ ማን ሊገምት ይቻለዋል? ዘግናኝ ደም መፋሰስስ ሳያስከትል ይህንን ክፉ ድርጊት መሻገር የምንችለው እንዴት ነው?
እንግዲህ ይህ ሁሉ የፍርሰት መርዶ እየተሰማ ያለው፣ የሥርዓቱ ሰዎችና የጥቅም ተጋሪዎቻቸው ለዚህ ከፍታ የበቁበትን ሃያ ሶስተኛ የድል ዓመት በፌሽታ ለማክበር ደፋ ቀና በሚሉበት ዋዜማ ላይ ቆመን ቢሆንም ‹‹ጊዜው ከቶም ቢዘገይ አልረፈደም›› እንዲሉ፤ ተገፍቶ ገደል ጠርዝ የተንጠለጠለውን የኢትዮጵያን ህልውና በደለደለ መሰረት አፅንተን ለቀጣዩ ትውልድ ለማሻገር አንዳች እርምጃ መውሰዱ ብቸኛ አማራጭ ነው ብዬ አምናለሁ፡፡ ለዚህ ዘመን ለጣለው ትውልዳዊ የማንነት ዕዳ ክንውን ቀዳሚው ተግባር ኢህአዴግን ‹‹በቃህ!›› ብሎ ማስቆም እንደሆነም መቀበል የሚያስቸግር አይመስለኝም፡፡ ግና፣ ይህ ሳይሆን በወታደራዊ ጡንቻ ካሳለፍናቸው ዓመታት ጥቂቱን እንኳ እንዲሰነብት ከፈቀድንለት፣ የደም ባሕር ሲያጥለቀልቀን ቆመን ለመመልከት ተስማምተናል ማለት ነው፡፡
Source Ethiomedia
No comments:
Post a Comment