Sunday, November 9, 2014

የህወሃቱን ፖለቲካ የአዋጁን በጀሮ!

ህወሃት በተፈጥሮው የፖለቲካ ብዙህነት ወይም ብዝሃነትን ማቻቻል የሚባል ነገር አያውቅም። ሌላው ቀርቶ በራሱ በድርጅቱ ውስጥ የሚነሱ የተለዩ ሃሳቦችን ሁሉ እንደጠላት ሃሳብ ፈርጆ ሰዎችን ደብዛቸውን ማጥፋት የተለመደ የህወሃት አሰራር ነው። ይህን የህወሃት ባህርይ በቅጡ ለመረዳት በቅርቡ የቀድሞው የህወሃት አመራር አባል የነበረው አቶ ገብሩ አስራት የጻፈው መጽሃፍ ጥቂት ገጾች በማየት መረዳት ይቻላል። ተቃዋሚ ፓርቲ ሰላማዊም ሆነ አልሆነ በህወሃት እንደጠላት ነው የሚቆጠረው።

ሰሞኑን ከትግራይ የህዝብና የመንግስት ግንኙነት ቢሮ ከሚባለው መስሪያ ቤት በትግረኛ ተጽፎ ለአባለት በሚስጥር የተሰራጨ ደብዳቤ ማንኛውምንም ተቃዋሚና ከህወሃት ውጭ የሚያስብና ህወሃትን የማይከተል ሁሉ “ፀላኢቲ” ጠላቶች ሲል ይፈርጃል። በዚህ ባለ 5 ገጽ ደብዳቤ ውስጥ እነዚህን “ፀላኢቲ” እንዴት እንደሚያሳድዱ፣ እንዴት እንደሚያዋክቡና እንደሚያጠፉ የሚመክር መመሪያ የሚሰጡ ሃሳቦች ተቀምጠዋል። በደብዳቤው ላይ ከአናቱ ሆነው የሚያስተዳደሩትን ወገናቸውን እንኳን አይለይም። በአጭሩ እኛ እንዳንመርጥ የሚፈልግ፣ የሚቀናቀንና ሌሎች ሰላማዊ ፓርቲወችን የሚመራና የሚደግፍ ሁሉ ፀላኢቲ ነው።

ይህ ለ2007 ዓ.ም የክትትል ስራ የተመደበው የህወሃት ቡድን ስራውን የሚያከናውነው ከታክስ ከፋዩ በሚገኝ የመንግስት ገንዘብ መሆኑ ይታወቃል።

ዘንድሮ የምርጫ አመት መሆኑን ተከትሎ የፀላኢቲ ክትትልና አፈና ከአሁን ተጠናክሮ በመካሄድ ላይ መሆኑም እየታየ ነው። ጠንካራ የተቃዋሚ ፓርቲ መሪዎች፣ ጋዜጠኞች፣ በየክልሉ ያሉ የተቃዋሚ ፓርቲ መሪዎችን ሁሉ በመታፈንና ወህኒ በመውረድ ላይ ናቸው።
የህወሃት ኢህአዴግ መሪዎች በአለም ዙሪያ ነጻነቴን የሚል የህዝብ ድምጽ በሰሙ ቁጥር የሚሰማቸውን ድንጋጤ የሚቀንሱት ዜጎችን በማፈን፣ በመግደል፣ በማሰቃየትና በማሰር ብቻ ነው።

ለህወሃት ምርጫና መድብለ ፓርቲ መልክን አሳምሮ ተቀባይነት ወደ ምእራባውያን ለልመና ለመውጫ እምጅ ዴሞክራሲያዊ ምርጫና የህዝብ ልእልና የሚባል ነገር ባጠገባቸው እንዲያልፍ ስለሚፈልጉ የሚያደርጉት አለመሆኑን በብዙ መንገዶች አሳይተውናል። ከህወሃት ውጭ ያልህ የኢትዮጵያ ህዝብ ሆይ አንተ ለወያኔ/ህወሃት ፀላኢቲ ጠላት ነህ። ወገኖቼ ብለህ የምታስብ ሁሉ ይህን የሚስጥር ደብዳቤያቸውን በማየት ብቻ ሳይሆን በተግባር አይተሃልና።


ያለህ ምርጫ እንደአባቶችህ፡-

እልም እንጅ ውሃ አይላመጥም፣
ጠላት ወዳጅ ላይሆን አልለማመጥም።

ብለህ መነሳይ ይኖርብሃል።

ትእግስት፣ አስተዋይነትና የፍቅር መንገድ መመኘት ከህወሃት ፀላኢቲነት አያላቅቅም። ህወሃትን ማስወገድ በጠላትነት ፈርጆ ሊውጥህ የመጣ ጠላትን ማስወገድ ማለት ነው።

ግንቦት 7 የፍትህ፣ የነጻነትና የዴሞክራሲ ንቅናቄ ከዚህ በጠላትነት ከፈረጀህ የዘርፎ አደሮች ቡድን እንድትላቀቅ አቅሙን በመገንባት ለወሳኝ ፍልሚያ እተዘጋጀ ነው። መላው ወገናችን ወያኔ የፈጠረልህን የክፍፍልና የልዩነት አጥር እያፈራረስክ አንድነትን አጠንክር። በያለህበት ለነጻነትህ ተነሳ። ኑሮን ለማሸነፍም ሆነ መረጃ በማጣት በወያኔ ስር ተደራጅተህ በሎሌነት እንድታገለግል የተፈረደብህ ወገን ሁሉ ወያኔ ጠላት ብሎ እንደሚቆጥርህ አትዘንጋ። የነፃነታችን ቀን ቅርብ ነው።

ድል ለኢትዮጵያ ህዝብ!!!

No comments:

Post a Comment