Saturday, May 31, 2014

መረሳትና መርሳት በሃገራችን!


መረሳትና መርሳት የኢትዮጵያ ዋና ባህላችን ይመስለኛል:: መርሳት ካለን ጽናት ውሱንነት ይመነጫል:: በጽኑና በአንክሮ የምንፍፈልገውን: የምንከታተለውንና የምናስበውን ነገር የመርሳት እድላችን ጥቂት ነው:: በመርሳት ባህላችን ውስጥ ብዙ ነገሮችንም እንረሳለን: ደስታን: መሪር ሃዘንን: ጀግናን: ጭቆናንና ጨቋኝን...ወዘተ... የማንረሳው ነገር የለም:: በደልና ግፍን መርሳት በግለሰብ ደረጃ ቂም በቀልነትን ሊቀንስ ቢችልም እንደህዝብ ከረሳን ግን በደልና ጭቆናን ሁሌም የማንሰለች "ሁሉን ተሸካሚ" ማህበረሰብ ሆነን እንድዘልቅ ያደርገናል:: በእርግጥ እኛ የምንረሳው ነገሩን ጭራሽ "ማስታወስ" ስለማንችል ሳይሆን: አስታውሰን የምንሰጠው ትኩረት አናሳ በመሆኑ ነው:: ይህም ከጽናት ጉድለት ወይም ተስፋ ቢስነት ይመነጫል::

ይህን ማህበረሰባዊ ተውሳክ በአግባቡ ተረድቶ እንደአኢህአዲግ የተጠቀመበት ያለ መንግስት የለም:: ምንም የሚያስከፋንን: የሚያንጨረጭረንን; የሚያበሳጨንንም ነገር ሲወስድ: ሁሌም በአንድ ነገር እርግጠኛ ሆኖ ይመስለኛል:: ያም ትንሽ ቆይተን እንደምንረሳለት! በዚህም ምክንያት እኛን ደስ የሚያሰኘንን ሳይሆን ሁሌም እርሱን ደስ የሚያሰኘውን ነገር በእኛ ላይ ሊኖረው የሚችለውን ማንኛውንም ስሜት ከግምት ሳያስገባ ይወስዳል:: ይህን ሲወስድ ዋስትናው መሳሪያ ነው ብሎ ስለሚያምን አይመስለኝም: ይልቁን ዋስትናው የእኛ መርሳት ነው::
እስኪ በእኛ ዘመን "የረሳናቸው" የሚከተሉትን ጥቂት የአንድ ወቅት ክስተቶች እንመልከት:

1ኛ: በ1993 ዓ.ም በአዲስ አበባ ዩንቨርስቲ 300 የሚሆኑ ተማሪዎች ተባረው ፍትህ ሳያገኙ መቅረት:

2ኛ: በ1997 ዓ.ም ከምርጫ ጋር ተያይዞ ከ194 በላይ ሰዎች ሞትና በቂ ምርመራ እንኳ ሳይደረግ በዚያው ደመ ከል ሆነው መቅረት

3ኛ: በጋምቤላ ክልል ተፈጸመ የተባለው "ጄኖሳይድ" እንዲሁ ሳይጣራ መቅረት

Friday, May 30, 2014

ሀገሬ ኢትዮጵያ ብሔሬም ኢትዮጵያዊ ነው!!!


በዘርና በነገድ በቋንቋና በሃይማኖት መከፋፈልን አጥብቄ እቃዎማለሁ። ብዙም አልጽፍም በአገሬ ጉዳይ ዙሪያ የተከሰቱ ሁኔታዎችን ማዳመጥና በቻልኩት መጠን መርዳትን እመርጥ ነበር፣ በሰሞኑ የሚሰማው ዜና ግን ዝም እሚያሰኝ ዓይደለም። ልቤ እጅጉን ተጎዳ፤ ሰው በአገሩ እንዴት በማለት የውስጥ ሀዘንም ተሰማኝ፦ ሰዎች ከቤታቸው ተፈናቅለው ለጅብ ተሰጡ፥ በዓማራው የጀመረው የጥፋት ዘመቻ ወደ ኦሮሞውም መጥቷል፥ ኢትዮጵያ በጭንቅ ላይ ትገኛለች፥ የዓንድነት ዓቀንቃኞችን እንዳልሰማችሁ በመሆን የአማራውን እልቂት ከመናገር ተቆጠባችሁ እንጂ የብሔር ፓለቲካ ዓድጎ ጥርስ ዓውጥቷል፣ ወገኖች እርስ በዕርስ የሚበላሉበት ሰዓት ላይ ናቸው እያሉ ተቆርቋሪ ነን የሚሉ ወገኖች ብዙ ይጎስሙናል፥ ለማጉረምረማቸው እውነታነት በወለጋና በሃራማያ ዩኒቨሪስቲ ምልክቶች ፍጥጥ ብለው መታየት ጀምረዋል።

ከደቡብ ጠርዝ እስከ ሰሜን ጫፍ ዋይታ በዛ፣ የሕጻናትና የዓረጋውያን ለቅሶ፤ የጎበዙ የሞት ጣርና የወይዛዝርቱ የልብ ስብራት፤ የናቶች ሐዘንና ትካዜ የአባቶች የድረሱልን ድምጽ ይሰማል። ከሐረር እስከ ወለጋ፤ ከጎንደር እስከ ወሎ፣ ከአፋር እስከ አርሲና ጋሞጎፋ፤ ከወልቃይት ጸገዴ እስከ ጉራፋርዳ፤ ከሰቲት ሁመራ እስከ በደኖ አርባጉጉ፤ ከአብደራፊ መተማና ስናር እስከ ሱዳን ድንበሮች፣ ከአርማጭሆ የዋልድባ ገዳም እስከ ትልቁ የዓንዋር መስጊድ መርካቶ በሐገረ ኢትዮጵያ ጩኸት በረከተ….. ፦ ያጠላው የሞት ድባብ አሁንም በጋምቤላ አድርጎ በጉሙዝ ቤኔሻንጉል የብሔረ አማራን ማጋየት ቀጥሏል፤ እንደ ዕነርሱ አባባል አማራ አፈርድሜ እየበላ ነው።

Thursday, May 29, 2014

ግንቦት 20- የመከራ የስደትና ዘረኝነት አዲስ ምዕራፍ መጀመሪያ

ወያኔ ለንግሥና የበቃበትን ግንቦት 20 ቀን 1983 ዓመተ ምህረት መታሰቢያ በአል ለ23ኛ ጊዜ ለማክበር ሰሞኑን ደፋ ቀና ሲል ሰንብቷል። በኢትዮጵያ ግብር ከፋይ ህዝብ የሚተዳደሩ መገናኛ ብዙሃንና በተለያዩ የውጪ አገራት የተመደቡ የወያኔ ቆንስላ ጽ/ቤቶች በዚሁ የግንቦት 20 በአል አከባበር ሥራ ተጠምደው ከርመዋል። ለኢትዮጵያ አገራችንንና ለህዝቦቿ ባርነትን ለህወሃትና ለግብረ አበሮቹ ደግሞ አልመውት የማያውቁትን ድሎትና ብልጽግናን ያጎናጸፈው ግንቦት 20 በየአመቱ ሲዘከር ልብ ልንላቸው ከሚገቡ በርካታ ትሩፋቶቹ ጥቂቶቹ ማስታወስ ይችላል፦


  1. ኢትዮጵያ አገራችን ለመጀመሪያ ጊዜ ከአብራኳ በተገኙ ከሃዲዎች መዳፍ ውስጥ ወድቃ ሉአላዊነቷና አንድነቷ የተናጋበት ሁኔታ መፈጠሩ፤
  2. በዘመናት ጥረት የተቋቋመው ህብረ ብሄር የአገር መከላኪያ ሠራዊታችን ፈርሶ በምትኩ ለጠባብ የዘውግ ጥቅም የተሰባብሰቡ መንደርተኞች ሙሉ በሙሉ የሚቆጣጠሩት ተቋም መመስረቱ፤
  3. በከፈሉት የህይወት መስዋዕትነት አገራችንን ከውጪ ጠላት ተከላክለው ነጻነት ያወረሱን ጀግኖች አባቶቻችን ታሪክ እየተብጠለጠለ በታሪካችን እንድናፍር መደረጉ፤
  4. ዜጎች በብሄር ማንነታቸው ከመንግሥት ሥራና የግል ይዞታ የሚፈናቀሉበት ዘመን መፈጠሩ፤
  5. የመንግሥትና የህዝብ ሃብት የነበሩ የንግድና የአገልግሎት መስጫ ተቋሞች በሙሉ ወደ ህወሃት የግል ይዞታነት መዛወራቸው፤
  6. የዘር የሃይማኖትና የቋንቋ ልዩነት መስፈርት የሆነበት ሥርዓት ተቋቁሞ ዜጎች እርስ በርስ የሚላተሙበት ፤ ለዘመናት በሰላም ከኖርበት ቀያቸው በነቂስ የሚፈናቀሉበት ሁኔታ ደጋግሞ መከሰቱ፤
  7. በልማትና እድገት ሥም ሰፋፊ የእርሻ መሬቶቻችን ለህንድ፤ ለቻይናና ለአረብ ከበርቴዎች በመቸብቸቡ የነገው ትውልድ የእጅ አዙር ቅኝ አገዛዝ ውስጥ እንዲወድቅ መንገዶች መመቻቸታቸው፤
  8. በሚሊዮን የሚጠጉ ለጋ ወጣቶች ተስፋቸው ተሟጦ ለአሽከርነትና ለግርድና ወደ አረብ አገር የሚፈልሱበት ችግር እየተባባሰ መምጣቱ፤
  9. በታሪካችን ታይቶ የማይታወቅ ስደትና እንግልት ሰለባ መሆናችን ወዘተ
  10. ሃሳብን በነጻነት የመግለጽና የመደራጀት መብት ተጥሶ በርካታ ኢትዮጵያውያን በአስተሳሰባቸውና በአመለካከታቸው በእስር ቤት እንዲማቅቁ፣ እንዲገደሉና እንዲሰደዱ ተደርገገዋል ።

የወያኔ ጥላቻ ፍሬ


ፕ/ር መስፍን ወ/ማርያም  

ወያኔ ለትግራይ ሕዝብ ሀብትንና ብልጽግናን አመጣ ብለው የሚያምኑ ሰዎች ብዙ ናቸው፤ ወያኔ የሥልጣን ወንበሩ ላይ በመውጣቱ ትግሬዎች ሁሉ አልፎላቸዋል ተብሎ ይታመናል፤ በተለይ በአውሮፓና በአሜሪካ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን በዚህ ላይ የጠነከረ እምነት አላቸው፤ በዚህ ጉዳይ ላይ ከኢትዮጵያ ውጭ ብዙ ውይይትም ይሁን ንትርክ ይደረጋል፤ በኢትዮጵያ ውስጥ ግን የተፈራ ርእስ ነው፤ ውስጥ- ውስጡን እንጂ አደባባይ አይወጣም፤ ይህንን ጉዳይ በኢትዮጵያ ውስጥ አደባባይ ለማውጣት ጊዜው የደረሰ ይመስለኛል፤ አረጋዊ በርሄ፣ ገብረ መድኅን አርአያ፣ አስገደ ገብረ ሥላሴ፣ አብርሃ ደስታ (አሥር ቢሞሉልኝ ደስ ይለኝ ነበር!) እየደጋገሙ ቢያነሡትም ሌሎች በቁም-ነገር የተቀበሉት አይመስልም፤ ሕዝቡ ግን በራሱ መንገድ እየተናገረና ምስክርነቱን እየሰጠ ነው፤ በመቀሌ የተሠራውን የመኳንንት መንደር ሕዝቡ አፓርቴይድ ብሎ ሲሰይመው፣ በአዲስ አበባ የተሠራውን መንደር መቀሌ ብሎ ሲሰይመው እየመሰከረ ነው፤‹‹የለሁበትም!›› እያለ ነው።  

የትግራይ ሕዝብ መደህየቱ አልበቃ ብሎት ሲለምንም እየተሳቀቀ ነው፤ የሚለምነው ትግሬ ለብዙ ሰዎች ትግሬና ወያኔ አንድ መስሎ እንደሚታየው ያውቃል፤ አብዛኛው ሰው በወያኔ ላይ ያለውን ስሜት ያውቃል፤ ስለዚህም ሲለምን ሰዎች በወያኔ ላይ ያላቸውን ስሜት ስለሚያራግፉበት እየተሸማቀቀ ነው፤ አንድ የትግራይ ቄስ ከአርሲ ነኝ አሉኝና ለምን እውነቱን አይናገሩም ስላቸው እውነቱን ስናገር የማገኘው ስድብ ብቻ ነው አሉኝ፤ እኒህ ሰው ምን በወጣቸው የወያኔን ኃጢአት ተሸካሚ ይሆናሉ፤ በሌላ በኩል ደግሞ በትግሬነቱ የተጠቀመ አለ፤ እኔ የማውቀው የደርግ ወታደር የነበረ ትግሬ ቆስሎ ከውትድርና ወጣና በአንድ የመንግሥት መሥሪያ ቤት የጥበቃ ሥራ ላይ ነበር፤ በጣም ይቸግረው ነበር፤ ሚስቱ ሕመምተኛ ነበረች፤ የቤት ኪራይ መክፈል ይቸገር ነበር፤ ዛሬ ግን የሚለብሰው ልብስ ሌላ ነው፤ ከኑሮውም ተርፎ ለሲጃራና ለጫት እያወጣ ነው፤ ወይም ሌሎች እያወጡለት ነው፤ ትግሬነታቸው ብቻ እንዲህ የደላቸው በጣም፣ በጣም ጥቂቶች ናቸው፤ ስለዚህም በወያኔ አገዛዝ ትግሬ ሁሉ ተጠቅሞአል ማለት ከጉልሁ እውነት ጋር የሚጋጭ ስሕተት ነው፤ አብርሃ ሰዎች ትግሬ ሁሉ ተጠቃሚ ሆኗል ሲሉ ‹‹ያመኛል›› ማለቱ ይገባኛል።

7 Reasons Not to Celebrate Ginbot 20


It has been a while since I quitted expressing my views on matters of public concern on Ethiopia through social media outlets for reasons I am not gonna let you know at this moment. Nonetheless, I cannot withstand the internal urge I felt in my heart to tell it loud to our unelected rulers why I will not celebrate Ginbot 20 with them at a time they are deafening us with their achievements. Here are my laundry lists of seven reasons:-

1. As a hopeful citizen of that unfortunate polity – Ethiopia – I truly believed on the first anniversary of Ginbot 20 that the ground is going to be laid for a new era of democratic order. By ‘democratic order’ I intend to convey no sophistication or sheer idealism: I mean a political order in which any citizen of Ethiopia could elect or run for any public office without being required to have hailed from a well-armed political group. After 23 anniversaries of Ginbot 20, I was proven wrong as strong personalities from the former rebels – TPLF – hold politico-economic power monopolistically. Hence the first reason Ginbot 20 doesn’t belong to me.

2. Growing up in Ethiopia, where availing equal opportunity to every citizen, was not the rule of the game, I believed that the Ginbot 20 rebels, who took control of governmental power on this fateful day, would lay the foundation for the ‘great equal society’ where merit, not the ethnic community to which you belong, determines your likelihood for achievements in most fronts of life. To the chagrin of many members of hitherto marginalized communities, the Ginbot 20 rebels gave us a hollow vocabulary of convenience – ‘nations and nationalities’ – but not genuine institutionalization of diversity and its constitutional protection. Though the gains in terms of granting language rights are no less achievements, in today’s Ethiopia, your ethnic origin still determines whether you would be, or would not be, trusted for vital governmental positions in the public sector. Hence another cause for feeling unenthusiastic about Ginbot 20.

Tuesday, May 27, 2014

እንኳን አደረሳችሁ፤ ተስፋና ሕልም ያለ ሕግ ከሚያሰቀጡበት፣ “በሕግ” ወደሚያስወነጅሉበት አገዛዘ ተሸጋግረናል

በመስፍን ነጋሽ

አገርን በራስ የግልና የአካባቢ ተሞከሮ ብቻ ለመበየን መሞከር ውስንነቶች እንደሚኖሩበት አሳምሬ አውቃለሁ:: የዚያኑ ያህልም አገር ያለ ግለሰቦች ተሞክሮ ቁንጽል ተረት ከመሆን አይድንምና የግል ተሞክሮ ርካሽ ነገር እንደሆነ አንቆጥርም።

የዛሬ 23 ዓመት የት ነበርኩ? ዛሬ የት ነኝ የሚሉትን ሰፊ ጥያቄዎች ወደ መመለስ አልሄድም:: 23 ዓመት ለአገር አጭር ቀን ነው። በአገሩ ለሚኖሩ ሰዎች ግን ሙሉ ዕድሜያቸው ወይም እኩሌታው ሊሆን የሚችል ነው። ህወሓት ኢሕአዲግ የዛሬ 23 ዓመት አዲስ አበባ ሲገባ የእኔ ትውልድ የደርግን መሄድ በትልቅ ተስፋ ሲጠብቅ ነበር። ተስፋችን ግን የሚመጣውን በማወቅ ላይ የተመሠረተ አልነበረም፣ ያለውን በመጥላትና በመፍራት እንጂ። በወቅቱ ደርግ እና ሌሎቹም ስለ ህወሓት ኢሕአዲግ ሲሉ የከረሙት ብዙ ቢሆንም የሚባለውን ለመመርመርም ሆነ የመጣውን ለመጠየቅ የሚያበቃ ቅንጦት አልነበረንም። በጭቆና ውስጥ ያለ ህብረተሰብ የለውጥ አጋጣሚ ካገኘ “ይሄኛው ጨቋኝ ሲሔድ የሚተካው የባሰ ሊሆን ስለሚችል፣ ከለመድኩት ጋራ ልኑር” የሚል ቅንጦተኛ ሊሆን አይችልም። ጭቆና ማለት ዜጎች ያለውንም ሆነ የሚመጣውን ሕይወታቸውን ለመረዳትና ለማቀድ እንዲሁም ለመቆጣጠር የማይችሉበት ሥርዓት ነው። ስለዚህ ምርጫቸው ወደፊት እየሄዱ የሚመጣውን ማየት ብቻ ነው። የህብረተሰብ የዕድገት ታሪክም ይህን ያሳየናል።(ዛሬ ደርሶ “ግብጾች ሙባረክ ይሻላቸው ነበር” የሚሉን ቅንጡዎች፣ ህወሓት ከሔደ ሰማይ ይወድቃል የሚሉን ነብያት ችግር ሳይገባኝ ቀርቶ ግን አይደለም፣ አሁን ዩክሬንም ማጫፈሪያ ሆናለች መሰለኝ።)ለማንኛውም፣ እኛም ከታጠቀ ገዳይ

በኢትዮጵያ ዩኒቨርስቲ ተማሪዎች ላይ የሚፈፀመው ኢሰብአዊ ወንጀል!

ከፕሮፌሰር አለማየሁ ገብረማርያም

ትርጉም በነጻነት ለሀገሬ

እ.ኤ.አ ሜይ 2/2014 ቢቢሲ/BBC እንደዘገበው በኢትዮጵያ በስልጣን ላይ እንደመዥገር ተጣብቆ የሚገኘው ገዥ አካል የጸጥታ ኃይሎች ከመናገሻ ከተማዋ ከአዲስ አበባ በስተምዕራብ በኩል በ80 ማይሎች ርቀት ላይ በምትገኘው የአምቦ ከተማ ላይ ቢያንስ 47 የዩኒቨርስቲ እና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ተማሪዎችን በአሰቃቂ ሁኔታ በጥይት ኢሰብአዊ በሆነ መንገድ ረሽነዋል፡፡ ስብዕናው በውሸት እና በሀሰት ውንጀላ የበከተው ገዥ አካል ይህንን እልቂት እንደተለመደው ሽምጥጥ አድርጎ በመካድ “ጥቂት ጸረ ሰላም ኃይሎች በቆሰቆሱት እና በአስተባበሩት አመጽ“ ምክንያት የሚል የሀሰት ፍረጃ በመስጠት በግፍ የተገደሉትን ወገኖቻችንን ቁጥር ለማሳነስ ጥረት አድርጓል፡፡ ይህ በወጣት ተማሪዎች እና ህጻናት ላይ የተፈጸመው የማንአለብኝነት የእብደት አሰቃቂ እልቂት በዓለም አቀፍ የዜና አውታሮች ዘንድ ሰፊ ሽፋን አልተሰጠውም፡፡

ሂዩማን ራይትስ ዎች/HRW የተባለው ዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅት “በአምቦ፣ በነቀምት፣ በጅማ እና በሌሎች ከተሞች በሰላማዊ መንገድ ተቃውሟቸውን ባሰሙት ንጹሀን ዜጎች ላይ እየተፈጸመ ያለው ግድያ እና ድብደባ ይቁም“ የሚል መግለጫ በማውጣት እኩይ ድርጊቱን አውግዟል፡፡ እንደ ሂዩማን ራይትስ ዎች ዘገባ “በኦሮሚያ የሚገኙ ከ15 በላይ የሚሆኑ ህብረተሰብ አቀፍ ገጠራማ እና ከተማ ቀመስ አካባቢዎችን ወደ አዲስ አበባ ማዘጋጃ ቤት የወሰን ክልል የሚያካትተው እና የኦሮሞ አርሶ አደሮችን እንዲሁም ሌሎች ኗሪዎችን የሚያፈናቅለው የአዲስ አበባ የተቀናጀ መሪ የልማት ዕቅድ ሀሳብ ተዘጋጅቶ ይፋ መሆኑን ተከትሎ የተማሪዎች የተቃውሞ አመጽ ገነፈለ“ ብሏል፡፡ በማስከተልም ሂዩማን ራይትስ ዎች በሰላማዊ መንገድ ተቃውሟቸውን ባሰሙት ተማሪዎች ላይ የገዥው አካል የጸጥታ ኃይሎች እየወሰዱ ያሉትን የኃይል እርምጃ በአስቸኳይ እንዲያቆሙ ጠይቋል፡፡

በዚህ መረን በለቀቀ ዕኩይ ድርጊት የተሰማኝን ሀዘን በቃላት ለመግለጽ ተስኖኛል ምክንያቱም ልብን ሰብሮ የሚገባው ይህ የአሰቃቂ እልቂት ሀዘን ልሸከመው ከምችለው ከአቅሜ በላይ ሆኖብኛልና፡፡ የብሩህ አዕምሮ ባለቤት እና የነገይቱ ኢትዮጵያ ተረካቢ የሆኑት እምቦቀቅላ ተማሪዎች ገና በወጣትነት ለጋ እድሚያቸው ኃላፊነት በማይሰማው መንግስት ነኝ ባይ የወሮበላ ቡድን ስብስብ በጥይት ውርጅብኝ በመጨፍጨፋቸው ታላቅ ሀዘን ተሰምቶኛል፣ እንዲሁም ቀጣይነት ባለው መልኩ ስሜቴን እየቆጠቆጠኝ ይገኛል፡፡ ተማሪዎቹ የሚሰማቸውን ቅሬታ በሰላማዊ መንገድ ለማቅረብ ህገመንግስታዊ ያልተገደበ መብት ነበራቸው፡፡ ያንን መብት በመጠቀም በሰላማዊ መንገድ ወደ አደባባይ በመውጣት ተቃውሟቸውን በማሰማታቸው ምክንያት ብቻ የጥይት በረዶ ተርከፍክፎባቸዋል፡፡ እናም ሁላችንም ልናዝንላቸው ይገባል፡፡ ኃላፊነት በጎደለው ገዥ አካል በተፈጸመው እልቂት ምክንያት የምርጥ እና የባለብሩህ አእምሮ ባለቤት የነበሩትን ወጣቶች ኢትዮጵያ በማጣቷ አጅግ በጣም ለኢትዮጵያ አዝናለሁ፡፡ የእልቂቱ ሰለባ ለሆኑት ወጣቶች ወላጆች እና ጓደኞች የተሰማኝን ጥልቅ ሀዘን መግለጽ እፈልጋለሁ፡፡ መጽናናትን እንዲሰጣቸውም ለኃያሉ አምላክ ጸሎቴን አደርሳለሁ፡፡

Monday, May 26, 2014

የሕወሓት አደገኛ የዘረኝነት መርዝ እና የናዚ ፍልስፍና

በሚኒሊክ ሳልሳዊ

ከመጀመርያው ዓለም ጦርነት ማገባደጃ ቦኋላ በጀርመን ማደግ ጀምሮ የነበርው ´´የናሺናል ሶሻሊስት ፓርቲ´´ የናዚ የፖለቲካ ዘይቤን በማስፋፋት ፣ የፋሺስቶች የቀኝ ክንፍ እንቅስቃሴ በዛን ወቅት በዋናነት ይታገል ፣ ይዋጋ ነበረው አንዱ ኮሚኒስቶችን ነበር ፡፡ እነዚህን ክፍሎች ዒላማ ካደረገበት ምክንያት አንዱ ፣ በወቅቱ በዓለማችን ዙርያ እየተጠናከረ የነበረውን ፣ የኮሚኒስቶች እንቅስቃሴ ለመቋቋምና ፣ በስራቸው እየተደራጀ የነበረውን የሰራተኛውን ክፍል (working class ) ከኮሚኒስቶች ነጥሎ በናዚስቶች ስር ለማሰለፍና ነበር ፡፡

የናዚ ፍልስፍና መሰረት ፣ የ አርያን ታላቅ ዘር (Aryan master race ) ከሌሎች የሰው ፍጠረት ዘሮች ሁሉ የላቀና ፣ የተመረጠ ሕዝብ እንደሆነ ያምናሉ ፡፡ እነሱ የሚሰጡትን ገጸ-ባህሪያት የማያሟላ ፣ እንደ ሰው ካለመቁጠራችወም በላይ ``በስህተት ወይም ሳይፈለጉ ተፈጥረው ``የተገኙ ነገሮች ተደርገው ስለሚታዩ ፣ መደምሰስ ወይም መጥፋት አለባቸው ብለው ያምኑ ነበር ፡፡ በዚህም የተነሳ ታሪክ እንደመዘገበው ከነሱ ዝርያ ውጪ ናቸው ብለው ፣ በተለያየ ዘርፍ የመደብዋቸውን ፣ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሌሎች ዜጎችን በየማጎርያ ካንፑና (concentration camp)፣ በየእስር ቤቱ እየተሰበሰቡ በሚያሰቅቅ ሁኔታ በጋዝ ጢስ ፣ በጥይት እሩምታና በተለያየ መንገድ እንደጨረሱዋቸውና ፣ ከፊሎቹንም ፣ በጣም አሰቃቂና ፣ኢ-ሰባዊ በሆነ መንገድ ፣ ሰውነታቸውን ለህክምና ምርምር ይጠቀሙባቸው ነበር ፡፡ ከዚያም አልፈው ሄደው፣ የሰውን ልጅ ክቡር ፍጡር ከእንሳት በታች አድርገው በመቁጠር ፣ ቆዳቸውን ለማስታዎሻ (souvenir) ለመብራት አንፖል ማጌጫና ፣ ለቤት ማሳመርያ ቁሳቁስ ይጠቀምባቸው እንደነበር ፣ ዛሬ ከነማስረጃው በተለያዩ የማጎርያ ካንፕ ፣ ሙዝየም ውስጥ ተቀምጠው ማየት ይቻላል ፡፡

እነዚህ ከአርያን ዘር ውጪ ያሉትን ፣ መፈጠር አይገባቸውም ነበር ብለው የመደቧቸውን ፣ ይሁዲዎችን ፣ ጂብሲዎችን ፣ የአዕምሮ ህመምተኞችን ፣ አካለ ስንኩላንን፣ ጥቁሮችን ፣ ከነሱ ሃይማኖት ውጪ ያሉትን ፣ እንደ የጆሃቫ እምነት ተከታዮችን ፣ የፖለቲካ ተቀናቃኞቻቸውንና ፣ የተለየ ጾታዊ አቀራረብ እምነት የነበራቸውን ፣ ከሰባዊ ማንኛውም ፍጡር በታች አድርገው ከማየታቸውም በላይ እንደ የግል መገልገያ ቁሳቁስ አድርገው ፣ አዕምሮዋችን መገመት ከሚችለው በላይ ፣ ኢሰባዊ ድርጊት ይፈጽሙባቸው ነበር ፡፡ የፓርቲ መመሪያቸውም ከላይ የተዘረዘሩትን ከነሱ ውጭ የተፈጠሩትን ፣ የማጥፋት መብት እንዳላቸው ተደርጎ እንዲታመንበት ተቃኝቶ የተዘጋጀ ንድፈ -ሃሳብ ወይም የፖለቲካ ዘይቤ( ideology) ስለነበር ፣ አብዛኛው ሕዝባቸውን በዚህ ፍልስፍና አሳምነው ፣ አሳስተው ከጎናቸው ማሰለፍ ችለው ነበር ፡፡

Sunday, May 25, 2014

የመጨረሻዉ ካርድ

አገራችን ኢትዮጵያ ባለፉት ሃያ ሦስት አመታት ያለፈችበትን የግፍና የመከራ ዉጣ ዉረድ ወደ ኋላ መለስ ብሎ መመለክት መፈጠርን የሚያስጠላና ልብን የሚያደርቅ እራሱን የቻለ ሌላ በጭንቅና በመከራ የተሞላ ዉጣ ዉረድ ነዉና አለመሞከሩ ይመረጣል። ሆኖም አገራችንን ከዚህ ሳትወድ በግድ እጇን ታስራ ከገባችበት የጥፋት ቁልቁለትና የመከራ አዘቅት ዉስጥ ላንዴና ለመጨረሻ ግዜ ጎትቶ ለማዉጣት የግድ እዘህ ድቅድቅ ጨለማ ዉስጥ እንዴት ገባች ብሎ እራስን መጠየቅ ያስፈልጋልና ወደድንም ጠላን የሃያ ሦስቱን አመት ጉዟችንን ወደ ኋላ ዞር ብለን በጥሞና ማጤኑ አማራጭ የሌለዉ መንገድ ነዉ። የወያኔ ዘረኞች ፋሺስቱን ደርግ ጣልን ይበሉ፤ በ99.6 በመቶ ድምጽ ተመርጥን ይበሉ ወይም እድገት አመጣን ይበሉ የእነሱ ፍላጎት ምን ግዜም ቢሆን የኢትዮጵያን ህዝብ ረግጦ መግዛት ነዉ እንጂ ህዝብን በጨዋነት ማስተዳደር አይደለም። አንድን ህዝብ ረግጦ ለመግዛት የሚያስፈልገዉ ደግሞ ጠመንጃና ባዶ ጭንቅላት ብቻ ነዉ፤ ጠመንጃና ባዶ ጭንቅላት በገፍ የሚገኝበት ድርጅት ነዉና ወያኔ ደግሞ በዚህ በፍጹም አይታማም። የወያኔ ዘረኞች ፍላጎት የኢትዮጵያን ህዝብ ከጣሊያን ፋሺስቶች ባልተለየ መንገድ እየረገጡ መግዛት ቢሆንም አንድን ህዝብ ዝንተ አለም ረግጦ መግዛት አንደማይቻል በሚገባ ያዉቃሉ፤ ለዚህ ነዉ የኢትዮጵያ ህዝብ ሙሉ ኃይሉን እነሱ ላይ ለማሳረፍ በቆረጠ ቁጥር ህዝብን ከህዝብ የሚለያይና የሚያራርቅ ካርዳቸዉን እየመዘዙ ጸረ ህዝብና ጸረ አገር ጨዋታቸዉን የሚጫወቱት። በእርግጥም ወያኔዎች በስልጣን በቆዩባቸዉ ባለፉት ሃያ ሦስት አመታት የተለያዪ ካርዶችን መዝዘዋል – ፌዴራሊዝም እያሉ በፌዝራሊዝም ቀልደዉብናል፤ እድገትና ልማት እያሉ ጠብ ያለዉን ሁሉ እነሱ እራሳቸዉ እየዋጡ ሌሎቻችንን የበይ ተመልካቾች አድርገዉናል፤ በጎሳ ከፋፍለዉናል፤ በዘር አጥር አጥረዉናል። ዛሬ ደግሞ ለእነዚህ ተራ በተራ ለመዘዟቸዉ የክፋት ካርዶች አልታለልም ያለዉን የኢትዮጵያ ህዝብ ካዝናቸዉ ዉስጥ የቀረችዉን የመጨረሻ ካርድ መዝዘዉ በጎሳና በዘር ከመለያየት አልፈዉ በዘር ለማጋጨትና ደም ለማፋሰስ ጉድ ጉድ እያሉ ነዉ።

ኢትዮጵያ ዉስጥ ማንም ኃይል በምርጫ ሥልጣን ያዝኩ ብሎ አፉን ሞልቶ ለመናገር ኦሮሚያና አማራ ክልል ዉስጥ ምርጫዉን ጉልህ በሆነ ብልጫ ማሸነፍ አለበት፤ ወይም አማራና ኦሮሚያ ዉስጥ ተሸንፎ ፓርላማ ዉስጥ አብዛኛዉን ወንበር ተቆጣጥሮ መንግስት መመስረት አይቻልም። ወያኔ ዛሬ ያንን የእንቅልፋሞች ፓርላማዉ ተቆጣጥሮ መንግስት ነኝ ብሎ የሚፏልለዉ ሁለቱን የአገራችንን ግዙፍ ብሄረሰቦች ለያይቶና አንዱ ሌላዉን በጥርጣሬ አይን እንዲመለከት አድርጎ ነዉ እንጂ ወያኔ በየቀኑ የሚያስራቸዉ፤ የሚደበድባቸዉ፤የሚያሳድዳቸዉና የሚገድላቸዉ የአማራና የኦሮሞ ህዝቦች በፍላጎታቸዉ መርጠዉታማ አይደለም። ወያኔ ዛሬ ከሚታይበት የፖለቲካ ኪሳራና ህዝባዊ መተፋት አንጻር እንደቀድሞዉ ኦሮሞንና አማራን በመከፋፈልና በመለያየት ብቻ ስልጣን ላይ መቆየት እንደማይችል ስለተረዳ እነዚህ ሁለት የአገራችን ግዙፍ ብሄረሰቦች እርስ በርሳቸዉ ተጋጭተዉ እንዲተላለቁ የሚቻለዉን ሁሉ እያደረገ ነዉ። ወይም ቀለል ባለ አማርኛ ወያኔ ከጫካ ይዞት የመጣዉን የመጨረሻ ካርድ መዝዞ አገራችንን በቀላሉ ወደ ማትወጣዉ የዘርና የጎሳ ግጭት ዉስጥ ለመክተት ቁጭ ብድግ እያለ ነዉ።

Saturday, May 24, 2014

በራችንን ከፍተን የወያኔን ሌብነት ማቆም አንችልም!

የወያኔ ጉጅሌና ሎሌዎቹ ስልጣናቸውን በህዝብ ፈቃድ ላይ እንዳልቆመ አሳምረው ያውቃሉ። ነጻ የህዝብ ምርጫ ቢኖር ምን እንደሚሆኑ የዛሬ ዘጠኝ አመት በአይናቸው አይተዋል፣ በጀሮቸው ሰምተዋል። ከዚያ ተመክሮ ተነስተው ዳግም የህዝብ ፈቃድ ላለመጠየቅ ምለዋል። ቅዱሱን የዴሞክራሲና የፍቅር መንገድ ሳይሆን ሳይጣናዊውን የከፋፍሎና አናክሶ የመግዛትን መንገድ ዋና ምርጫቸው አደርገው ከወሰዱ ሰንብተዋል። የፍትህና የዴሞክራሲ ሂደት በኢትዮጵያ እነሱ እስካሉ ድረስ እንዳይነሳ አድረገው ቀብረውታል። በራሳቸውና ጥቅማቸው ላይ ኮሽታ በመጣባቸው ቁጥር ችግሩ በምስኪኑና የነሱ ሰለባ በሆነው ህዝብ ውስጥ መካከል እንደተፈጠረ ግጭት ለማስመሰል እና ለማድረግ የማያደርጉት ነገር የለም።

ወያኔ ሰሞኑን በመላው የኦሮሞ ተወላጆች የመጣበትን ተቃውሞ የአማራና የኦሮሞ ህዝቦች ጠብ ለማድረግ ያላደረገው ነገር የለም። መሰረታዊ የሆነውን የኦሮሞ ተማሪዎች ጥያቄ የባህርዳር እና በሌሎች የሀገሪቱ የሚገኙ ተማሪዎች ደግፈው ሂወታቸውን ያጡለትን የጋራ የወገንን ጥያቄ ለመቀልበስና፣ የኦሮሞና የአማራ ህዝብ ጠብ ለማድረግ ያላደረገው ጥረት የለም።

መሰረታዊ የሆነውን የኦሮሞ ተማሪዎች ጥያቄ በጥይት ብቻ ሊመልሰው እንደማይችል የተረዳው ወያኔ፤ በግርግሩ ውስጥ አማሮችና ኦሮሞዎች ደም እንዲቃቡና እንዲጋጩ አድርጎ ገላጋይ ለመምሰል የሚያደርገው ሙከራ ባይሳካለትም ይህን ተንኮል በህዝቡ ውስጥ የመትከል አባዜ ስራውን በስፋት ተያይዞታል። ሰሞኑን በመላው ኦሮምያ ካድሬ በማሰማራትና ገላጋይ በመምሰል ዋናውን የወያኔ መሬት ዝርፊያ ይቁም የሚለውን ጥያቄ በማለባበስና በማፈን ዘዴ ላይ ይገኛል።

ወያኔ ይህን ስልት የመረጠው ወያኔን የምንቃወም የነጻነትና የዴሞክራሲ አንድነት ሃይሎች የትብብር ደረጃ ያለበትን ሁኔታ ከግንዛቤ በማስገባት ነው። በርግጥ ይህን ሳይጣናዊ በር የከፈትንለት እኛው የነፃነትና የዴሞክራሲ ሃይሎች ነን። በመካከላችን የተቀናጀና የተባበረ እንቅስቃሴ ማድረግ አለመቻላችን በብዙ መልኩም ህዝባችን የሚያስተባብር የጋራ አመራር በመጥፋቱ ነው።

Friday, May 23, 2014

ይድረስ ለኢትዮጵያ ሰራዊት......!

በቅዱስ ዮሃንስ

በአሁኑ ጊዜ የአገራችን አንድነትና ሉአላዊነት ላይ የተደቀነው ፈተና እስካሁን ከተለመደው በአይነትም፡ በይዘትም፡ በአፈፃፀምም አንድ ቢመስልም በጣም ልዩ አስገራሚና የበለጠ አሳዛኝ የሚያደርገው ግን ይህ በአገር አንድነትና ሉአላዊነት ላይ የሚደረግ መሰርያዊ ዘመቻ ተፈፃሚ እየሆነ ያለው ኢትዮጵያዊ ነን በማለት በኢትዮጵያ ስም በሚነግዱ ባንዳ አገር ሻጮች ማለትም በሕወሓት ወያኔ ቡችሎች መሆኑ ነው። አዎን ይህ ክስተት ገፅታውን ካሳየን ውሎ አድሯል። የፋሽስቱ ህወሓት ቡድን የፖለቲካ ቅኝቱ የኢትዮጵያን አገራዊ አንድነት፡ ሉአላዊነትና ብሄራዊ ክብር በዋናነት መፃረር፡ ታሪኳን ማንቋሸሽና ህዝቧን መናቅ አብይ ተግባሩ እንደሆነ በተደጋጋሚ በተግባር አረጋግጦልናል። ማነኛውም በገዥ አካልነት የተሰየመ ክፍል ዋነኛ ተቀዳሚ ተግባሩ የአገርን አንድነትና ሉአላዊነት በቀናኢነት ማስከበር፡ የህዝቡን ደህንነት ማስጠበቅ ነው። ነገር ግን አለመታደል ሆኖ ዛሬ አገራችንን ሰቅዞ የያዛት መቅሰፍቱ የጉጅሌው ወያኔ ይህንን ሃላፊነት መወጣት አለመቻል ብቻ ሳይሆን ተፃርሮ የቆመ መሆኑን የኢትዮጵያ ህዝብ በቁጭትና በሃዘኔታ የተገነዘበው ጉዳይ ነው። ይህ ከሆነ ታዲያ እንዴትና በምን ምክንያት ይሆን እንደዚህ አይነት አገር የማጥፋት ሴራ ያሸረበ የፋሽስት ቡድን ለ 23 አመታት በስልጣን መቀጠል የቻለው? ይህንን መሰረታዊ ጥያቄ ድፍን የኢትዮጵያ ህዝብ ራሱን ይጠይቅበት ዘንድ በመተው ዛሬ ላካፍላችሁ ወደወደድኩት አብይ ጉዳይ ልለፍ።

ታሪክ እንደሚዘክረው በሁሉም ዘርፎች የተሰለፈው የኢትዮጵያ ሰራዊት የእናት አገርን ዳር ድንበር ከማስጠበቅ አልፎ ከአገሩ ውጭ ባደረጋቸው ተጋድሎዎችን በከፈላቸው ክቡር መስዋዕትነቶች ባስመዘገባቸው ስመ ጥርና  አኩሪ ተግባራት፡ አገሩንና ህዝቡን ያኮራና በመልካም ስም ያስጠራ ነው። የኢትዮጵያ ህዝብም በገዢዎቹ ለሚቀርብ አገራዊ ጥሪ ጨርቄን ማቄን ሳይልና ሳያመነታ አወንታዊ ምላሽ  በመስጠትና ሳይከፋፈል አንድ ላይ በመቆም በትዕቢት ተሞልተውና በትዕቢት ተወጥረው በየጊዜየው የአገራችንን አንድነትና ህልውና ለመፈታተን ድንበር ገፍተውና ባህር ተሻግረው የመጡ እብሪተኞች ድባቅ እየመታ ነው አገራችንን ጠብቆ ያቆየን። ታዲያ ዛሬስ ታሪክ ጀግንነቱን የዘመረለት ሰራዊትም ሆነ የአገራችን ህዝብ በአገር ሻጮቹ የወያኔ ቁንጮዎች ችሮታ የአገር ዳር ድንበት ተቆርሶ ለባዕድ ሲሰጥ ዝምታን ስለምን መረጠ? ይህ ስለ እውነት አግራሞትን የሚጭር ዝምታ ስለመሆኑ ምንም ማስተባበያ አያስፈልገውም።

Thursday, May 22, 2014

ፍትህ! ፍትህ! ፍትህ!

ሰዓቱ 10ጉዳይ … ለአስር ነው፡- ህብረት ግዜዋ ነች!!!

የኢትዮጵያ ህዝብ በፋሽስቱ የወያኔ አገዛዝ በጦር መሳሪያ ተረግጦ በድህነት አዘቅት መኖሩ እሙን ነው፡፡ የመሳሪያን ጉልበት ያላንበረከከ ህዝብ መቼም ቢሆን ኑሮው ለቅሶ ነው፡፡ የእኛ ህዝብም ኑሮ አረረ መረረ ከማለት ያለፈ ሆኖ የማያውቀው የዚህ የጦር መሳሪያ ተሸካሚዎች ቀንብር ውጤት ነው፡፡ ፋሽስቱ ወያኔ 23 ዓመት የመረጠው መንገድ ቢኖር ወጣቶቻችንን ማሰር፤ መንገደል፤ ማሰቃየትን ነው፡፡በዚህ አይነት ሁኔታ የሚቀጥልበት መንገድ ግን ፈጽሞ መኖር የለበትም፡፡ ፍርሀት በውስጡ ተስፋ ላለው ነገር እንጂ ነገ ደረሶ ያጠፋኛል እያሉ ሊሆን ፈጽሞ አይገባም፡፡

ወያኔ በደህንነት እና በወታደር ጉልበት ሲያስለቅሰን ሊኖር አይችልም፡፡ ከሰሞኑ የኦሮሞ ህዝብ ሁሉ አቀፍ ትግል፤ የነጻነት ትግሉ መሀል እንደተሻገረ የሚያሳይ ነው፡፡ ሁሉም በየፊናው የሚያደርገው ትግል ደግሞ ከዚህ ጋር ሲዳመር፤ ሰዓቱ አስር ጉዳይ ለአስር መሆኑ የሚያሳይ ነው፡፡የትግራይ የወጣቶቹ እና የዓረና ፓረቲ ትግል፤ በአዲስ አበባ የአንድነት እና የሰማያዊ ፓሪቲ ህዝባዊ ተቃውሞዎች፤ አሁን የኦሮሞ ህዝብ ትግል መጥቀስ ያለውን ሁኔታ ያስረዳናል፡፡ ከመቼው ግዜ በላይ የዲሞክራሲ ጥያቄ በትውልድ አዲስ ራእይ ላይ ተከንካበሎ የጋራ ትብብር እና ህብረት የሚፈልግበት ደረጃ መድረሱን የሚያለክት ነው፡፡

ለዚህ ደግሞ በወያኔ ላለፉት ለ23 የመከራ ዓመታት ሲነሰነስ የኖረውን ያለመተማመን ደባን ገሸሽ አድርጎ የመተባበሪያ መንገዶችን መፈለግ ወሳኝ ያደርገዋል፡፡ የሰው ልጅ ሁላ በየትኛውም ግዜ፤ እና ቦታ ፍትህን ይፈልጋል፡፡ ፍትህ ማለት ደግሞ ከኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት እስከ አካለዊ ህልውና ማለት ነው፡፡ ሀገራችን በዚህ ረገድ የታደለች አይደለችም፡፡ ስለዚህም የትኛውንም ብሄር የምትወክል ብትሆን ከዚህ የፍትህ ጥያቄ ውጪ ልትሆን አትችልም፡፡ በነገህ እጣ ላይ መሳሪያ የያዘ ተቀምጦ፤ አጠገብህ ያለው መሳሪያ ያልያዘው ጠላትህ ሊሆን አይችልም፡፡ የኢትዮጵያ የፖለቲካ ሃይሎች ሁላ ማወቅ ያለባቸው ነገር ቢኖር ህዝቡ የሚፈልገውን መወሰን የማችልበት ሁኔታ ላይ ተቀምጦ፤ ጎን ለጎን እርስ በእርስ ቢፋጩ ህዝቡን እየጎዱ እንደሆነ ነው፡፡ስለዚህ መሳሪያ ለያዘው ኃይል (ወያኔ) የማይመች የትግል ስልት መከተል የግድ ይላል፡፡ ለዚህ ደግሞ ራሱን ፍትህን የመታገያ መንገድ ማድረግ ተገቢ ነው፡፡

Tuesday, May 20, 2014

የኢህአዴግ ብሔርተኝነትና የተቀናጀ ማሰተር ፕላን…?


በግርማ ሠይፉ ማሩ

የጣና ሀይቅ የጎንደር ነው ወይስ የጎጃም? የሚል የይገባኛል ጥያቄ እንዳለ ያወቅሁት በደርግ የመጨረሻ ዘመን ምስራቅ ጎጃም እና ምዕራብ ጉጃም የሚል የአሰተዳደር አካባቢ የተመሰረተ ሰሞን ነው፡፡ በዚያን ጊዜ ጢስ አባይ ፏፏቴን ለማየት እየሄድን እያለ አብሮን ያለው ጎንደሬ ጓደኛችን አካባቢው የጎንደር መሆኑን ለማረጋገጥ ማየት ያለብን እረኛውን መሆኑን ነገረን፡፡ እረኛን አይቶ መሬቱን የጎንደር ወይስ የጎጃም ተብሎ እንዴት ይለያል ብለን በአግራሞት ተመለከትነው፡፡ እረኛው የሚጠብቃቸው በጎቹ እረኛቸውን ተከትለው የሚሄዱ ከሆነ ጎንደሬዎች ናቸው አለን፡፡ እንዳለንም በጎቹ እረኛውን ተከትለው ሲሄዱ ተመልክተን፡፡ ፈጠን ብዬ ሄጄ እረኛውን ጎንደሬ ነህ ወይስ ጎጃሜ? ስለው ጎንደሬ ነኝ አለኝ፡፡ ታዲያ አሁን ይህ አካባቢ ጣናን ጨምሮ ምዕራብ ጎጃም ተባለ ምን ይሰማችኋል? ብዬ ጥያቄ አሰከተልኩበት፡፡ እረኛው ለዕድሜ ልኬ የሚሆን ትምህርት ሰጠኝ፡፡ “ዋ! ውሃም መሬቱም እዚሁ ድሮ ያለበት አይደለ?” አለኝ በሚያስደንቅ ፍጥነት፡፡

የተማረው ጓደኛዬ የጎንደር መሬትና ውሃ ለጎጃም ተሰጠ ብሎ ሲብሰለሰል እረኛው ችግር የለም የት ይሄዳል ብሎ ከተማረው ጓደኛዬ የተሻለ መልስ ሰጠኝ፡፡ የጎንደር መሬት ለትግራይ ተሰጠ የሚለውን የክልል ድንበር ችግር ብዙም ሰሜት የማይሰጠኝ የትም ቢሆን መሬቱ በኢትዮጵያ ግዛት ክልል በመሆኑ ይመስለኛል፡፡ ይህ የጎንደር እረኛ ያስተማረኝ ሊሆን ይችላል፡፡ ከእረኛ ለመማር ዝግጁ ከሆነን ማለቴ ነው፡፡ በተጨማሪም በኢትዮጵያዊነቴ እንጂ በዘር ተቆጥሮ የሚሰጠኝ መሬት ስለማልፈልግ ነው፡፡ ወደዚህ ትዝታ የመረኛ በቅርቡ በአዲስ አበባ እና ፊንፊኔ ዙሪያ የሚገኙ የኦሮሚያ ከተሞች የተቀናጀ ማስተር ፕላን አስመልክቶ ደም አፋሳሽ ድጋፍና ታቃውሞ መነሳቱ ነው፡፡

የከተማ ኮንስትራክሽን እና ቤቶች ሚንሰትር አቶ መኩሪያ ኃይሌ ለምክር ቤት ቀርበው ሪፖርት ሲያቀርቡ ይህን ጉዳይ በሚመለከት “የአዲስ አበባና ፊንፊና ዙሪያ ከተሞች የተዘጋጀው የተቀኛጀ ፕላን ዝግጅት ይህን ያህል ጫጫታ የፈጠረው የኢህአዴግ ፖሊሲ ውጤት ነው ብለው ያምናሉ? መቼም ይህን ጉዳይ በተቃዋሚዎች አያሳብቡም” የሚል አሰተያየት አዘል ጥያቄ አቅርቤ ነበር፡፡ ሚኒሰትሩ መልስ ሲሰጡ ለልማት በጋራ መቆም እንዳለብን ገልፀው በአሁኑ ጊዜ እገሌ ነው ጥፋተኛ ማለት ተገቢ እንዳልሆነ ነገር ግን የኢትዮጵያ ህዝብ ብቻ ሳይሆን በዓለም ዕይታ መነፅር ውስጥ መሆናችንን በመጥቀስ በተፈጠረው ሁኔታ ደሰተኛ እንዳልሆኑ የሚገልፅ ሰሜታቸውን መደበቅ ተሰኖዋቸው ነበር፡፡ እንዲህም ሆኖ ግን ከቅላፂያቸው ተቃዋሚን ለመከሰስ ፍላጎታቸውን መረዳት አያሰቸግርም ነበር፡፡ በእኔ እምነት ለዚህ ለተነሳው ተቃውሞ መንስዔዎች የኢህአዴግ የተሳሳቱ ፖሊሲዎች ናቸው ብዬ አምናለሁ፡፡

ትኩረት በህወሓት፣ ኦህዴድ፣ ብአዴንና ደህዴድ ላይ ይሁን!!!

ዛሬ አገራችን ኢትዮጵያ መንታ መንገድ ላይ ትገኛለች። በአንድ በኩል ህወሓት እና  አገልጋይ ድርጅቶቹ በተለይም ኦህዴድ፣ ብአዴንና ደህዴድ የተነሳባቸው ሕዝባዊ  ተቃዉሞ ለመሸፈን የሕዝብ ለሕዝብ ጠብ ለመጫር የተቻላቸውን ሁሉ እያደረጉ  ነው።  በየተገኘው  አጋጣሚ  ሁሉ  ዘርን  መሠረት  ያደረጉ  ስድቦች፣  ዘለፋዎችና  ጥቃቶች እንዲኖሩ በካድሬዎቻቸውና በቅጥረኞች አማካይነት እየጣሩ ነው። በዚህ  እኩይ  ተግባር  ውስጥ  ባለማወቅ  በስሜት  ብቻ  የሚነዱ  የወያኔ  ደጋፊ  ያልሆኑ  ወገኖችም እየተሳተፉበት ነው። በሌላ በኩል ደግሞ በዘውግም ይሁን በአገር ደረጃ  የተደራጁ የፓለቲካ ድርጅቶች መሪዎች የጋራ ጠላቶቻችን ወያኔና ግብረአበሮቹ  ስለመሆናቸው  የጠራ  አቋም  እየያዙ  ነው።  ወያኔና  ግብረአበሮቹን    ለማስወገድ  በጋራ  መታገል  የሚያስፈልግ  መሆኑ  እና  ከወያኔ  አገዛዝ  በኋላ  በእኩልነት  ላይ  የተመሠረተ አገር የመገንባት የጋራ ኃላፊነት ያለብን መሆኑ ሰፊ ግንዛቤ እያገኘ  መጥቷል።     

ይህ  መንታ  መንገድ  በሁሉም  ቦታ  በባሰ  ኦሮሚያ  ውስጥ  ጎልቶ  እየታየ  ነው።  በኦሮሚያ  አካባቢዎች  የሚደርሰው  ጥቃትና  መፈናቀል  ያስቆጫቸው  ወጣቶች  የሚያደርጉት ፍትሃዊ ተቃውሞ ቀጥሏል። በአምቦ፣ በነቀምት፣ በጊምቢ፣ በሀረር፣  እና  ሌሎችም  አካባቢዎች  በተለይም  የዩኒቨርስቲ  ተማሪዎች  ሥርዓቱን  በመቃወማቸው  ከፍተኛ  ጥቃት  እየደረሰባቸው  ነው።  በመቶዎች  የሚቆጠሩ  ሕይወታቸውን አጥተዋል፤ በሺዎች የሚቆጠሩ ታስረዋል። በእነዚህ ቦታዎች ሁሉ  የእንተባበር ጥሪዎች ጎልተው እየተሰሙ ነው። በኦሮሚያ በሚገኙ ዩኒቨርስቲዎች  የሌሎች አካባቢዎች ተማሪዎች ከጎናቸው እንዲቆሙ የኦሮሞ ተማሪዎች ተደጋጋሚ  ጥሪዎችን አቅርበዋል። የሌሎች አካባቢዎች ተማሪዎችም ከኦሮሞ ወንድሞቻቸውና  እህቶቻቸው  ጎን  ቆመዋል።  ይህ  ተስፋ  የሚሰጥ  እና  መበረታታት  ያለበት  ነገር  ነው።  ሆኖም ግን ከዚሁ ጎን ለጎን ህወሓትና ኦህዴድ የሕዝቡን ጥያቄ ወደ ዘር  ግጭት  ለማዞር  እየሠሩ  ነው።  በተማሪዎች  መፈክሮች  ውስጥ  ዘርን  ለይተው  የሚያንቋንሽሹ  መልዕክቶች  ሰርገው  እንዲገቡ  እየተደረገ  ነው።  ኦሮሞ  ባልሆኑ  በተለይም በአማራ ተወላጆች ላይ ጥቃት እየደረሰ ነው። የወያኔ ጆሮ ጠቢዎችና  ካድሬዎች በስሜት የተገፋፉ ወጣቶችን ወደ ዘር ግጭት እየመሯቸው ነው። ይህ  እጅግ አሳሳቢና በአስቸኳይ መቆም የሚኖርበት ነገር ነው።  

ዘር ማጥራት ወይስ ኢህአዴግን ማፍረስ ? (ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ )

ኢህአዴግ ያነበረውን ቋንቋንና ዘውግን መሰረት ያደረገ ፌዴራሊዝም አደገኛነት በተመለከተ በርካታ ምሁራን፣ ፖለቲከኞች፣ ጋዜጠኞች… ሳያሰልሱ ለመምከርና ለማስጠንቅቅ መዋተታቸውን አልዘነጋሁም፡፡ እኔም ከ“ፍትህ” ጋዜጣ እስከ “ፋክት” መጽሔት ድረስ ችክ ያልኩበትም ሆነ ዛሬ በዚህ ተጠየቅ የተመለስኩበት ምክንያት ችግሩ እያደር እየተባባሰ በመምጣቱና ከምንጊዜውም በላይ አዘናግቶ ወደተፈራው የእርስ በእርስ እልቂት ሊዘፍቀን እየተንደረደረ በመሆኑ፣ ቅድሚያ ሰጥተን በሕብረ-ድምፅ ‘የሀገር ያለህ!’ ብለን መጮህ እንዳለብን ስለማምን ነው፡፡

አርባ አራት ዓመት ወደኋላ…

በኢትዮጵያ የዘውግ ጥያቄ ለአደባባይ የበቃው በ60ዎቹ መጀመሪያ እንደነበረ ይታወሳል፡፡ ከዘመነኞቹ የተማሪ እንቅስቃሴ መሪዎች ይህንን ጥያቄ አለቅጥ ለጥጦና አጋንኖ በማቅረብ ግንባር ቀደሙ ዋለልኝ መኮንን ነው፡፡ በ1962 ዓ.ም በአራት ገፅ ቀንብቦ ባዘጋጀው ታሪካዊ ጽሑፉ አማካኝነት “የብሔሮች ጥያቄ” ይፋ ሆኖ ለውይይት ከመቅረቡ በፊት፣ የተማሪው ዋነኛ የመታገያ አጀንዳ የመሬት ጉዳይ እንደነበር የታሪክ ድርሳናት ያወሳሉ (በደብዛዛውም ቢሆን ይንፀባረቅ የነበረውን መደብ ተኮር መንፈስ ሳንረሳ)፡፡ ዋለልኝ የሀገሪቱን መንግስታዊ አወቃቀርም ሆነ ባሕልን በአማራና በትግሬ ተፅእኖ ስር ስለመውደቁ በተቸበት በዚያ “ዝነኛ” ጽሑፉ ላይ እንዲህ ይላል፡-

“…ማንንም ሰው የኢትዮጵያውያን ቋንቋ ምንድን ነው ብላችሁ ጠይቁ፤ የኢትዮጵያውያን ሙዚቃ የቱ ነው ብላችሁ ጠይቁ፤ የኢትዮጵያውያን ባሕል የቱ ነው ብላችሁ ጠይቁ፤ ብሔራዊ ልብሳችሁ የቱ ነው ብላችሁ ጠይቁ፤ የአማራ ወይም የትግሬ ይላችኋል፡፡”

ይህ ሀቲት በወቅቱ በአብዛኛው ተማሪ ዘንድ ቁጣ ከመቀስቀሱም በላይ ዋለልኝን በ‹ፀረ-አማራና ትግሬነት› አስፈርጆ ለውግዘት ዳርጎት ነበር፡፡ እራሱም ቢሆን በአንድ የዩንቨርስቲው መድረክ ላይ የተሰነዘረበት ከባድ ተቃውሞ በፈጠረበት ብስጭት ‹‹እኔም አማራ ነኝ፤ ያውም ከአማራ ሳይንት-ቦረና›› ማለቱ ይታወሳል (ቦረና በተለምዶ አማራ መጥቶበታል የሚባለው አካባቢ መሆኑን ልብ ይሏል)፡፡ ግና፣ ዋናው ጥያቄ የእርሱ አማራ መሆን ያለመሆን አይደለም፤ እዚህ ድምዳሜ ላይ የደረሰበት ምክንያት ከተጨባጩ እውነታ ጋ ምን ያህል ይዛመዳል? የሚል ነው፡፡ ሌላው ነገር ደግሞ ከዚህ ጽሑፍ በፊት ብሔር ተኮር ጎዳዮችን አንስቶ ካለማወቁም በዘለለ፣ ሌሎች ሲያነሱ ፅንፈኛ ተቃዋሚ ስለነበረ ነው፡፡ ለምሳሌ ተማሪ ኢብሳ ጉተማ (ኋላ ላይ የኦነግ መስራችና አመራር የሆነው) ‹‹ኢትዮጵያዊ ማነው?›› በሚል ርዕስ ባቀረበው ግጥም እጅግ ተናድዶ ‹‹እንዴት እንዲህ አይነት ግጥም ታቀርባለህ? ዘረኛ ነህ፤ ኢትዮጵያውያንን የመከፋፍል ዓላማ ነው ያለህ?›› በማለት እስከመቃወም መድረሱ የክርክሩ አንዱ ጭብጥ ነው፡፡

Sunday, May 18, 2014

አኖሌ…..የባህር ዳር ነውር….አምቦ እና ግምቢ

ኢትዮጵያችን አደጋ ላይ ነች። የአደጋዋ ምንጭ ህወሃት እና ህወሃት ነው። ህወሃቶች በአገራችን ላይ የመዘዙት የበቀል ሰይፍ ወደ ሰገባው የሚመለስ አልሆነም። ከበቀል ስሜታቸው ጋር መቶ ዓመት የመንገስ ምኞት አላቸው። ምኞታቸውንም እውን ለማድረግ የንፁሃን ደም ለህወሃቶች መስዋዕት ሆኖ መቅረብ ይኖርበታል። እስከ ዛሬ ብዙ ኦሮሞዎችና አማሮች መሥዋዕት ሁነዋል። የመስዋዕቱ ምንጭ እንዳይደርቅ አሩሲ ላይ አኖሌ ቁሟል።እርሱን ተከትሎ ባህር ዳር “አማራና ኦሮሞ” ኳስ እንዲጫወቱ ሁኖ ነውር የሆኑ ስድቦች እየተነቀሱ ወጥተው በኢቲቭ እንዲተላለፍ ተደረገ። ይሄን ተከትሎ የመሬት ቅርምቱ ተከሰተ። አምቦና ግምቢ ላይ በህወሃት-ኦህዴድ ፊታውራሪነት የንፁሃን ደም በከንቱ ፈሰሶ ህወሃት የለመደውን ምሱን አገኘ።

ህወሃት የአኖሌ ሃውልት እንዲሰራ ሲፈቅድ የሚታየው በዚህ ሃውልት ምክንያት አብረው የኖሩ ህዝቦች ደም ተቃብተው በጠላትነት ሲቆሙ ነው።የአኖሌ ሃውልት በህወሃት-ኦህዴድ እጅ ሁኖ የሚሰብከው አብሮነትን ሳይሆን ልዩነትን ነው። ፍቅርን ሳይሆን ጥላቻን ነው። የአኖሌን ሃውልት የሚመስል ሌላ ሰማይ ጠቀስ ኃውልት በመቀሌ ከተማ ለትውልድ የሚተላለፍ ቂምን እየሰበከ ቁሟል። ስሙንም “የሰማዕታት” ሃውልት ብለው ይጠሩታል። ከአሩሲው አኖሌም ሆነ ከመቀሌው ሠማዕታት ሃውልት ትውልዱ የሚያተርፈው ቂም እና በቀል ነው። እነዚህ ሁለት ኃውልቶች ሠላምን አይሰብኩም፤ አብሮ መኖርን አያስተምሩም። ሃውሎቶቹን ያየ ግማሹ ቂም ይቋጥራል፤ ገሚሱ ይገረማል፤ ሌላውም የአገሪቱን መፃኢ ሁኔታ እያሰበ ይተክዛል። ህወሃቶች እጅግ ብዙ አሰቃቂ፤ አስገራሚ እና አሳዛኝ ነውሮችን በዚያች አገር ላይ መፈፀማቸው የታወቀ ነው።

የአኖሌ ኃውልት ተሠርቶ ከተመረቀ በኋላ በባህር ዳር ከተማ አማራና ኦሮሞ ኳስ እንዲጫወቱ ተደረገ። በዚያ ስቴዲየም ህወሃት-ብአዴን ያሰለጠኗቸው ምናምንቴ ካድሬዎች በኦሮሞዎቹ ላይ የስድብ ናዳ አወረዱ። ስድቡም በቀጥታ በቴሌቭዥን ለህዝቡ እንዲደርስ ሆነ። ይሄን ተመልክተው የሚቆጡ ሌሎች ምናምንቴዎች በህወሃት-ኦህዴዶች ተዘጋጅተው ወደ ህዝቡ መካከል ዘው ብለው ገቡ። የሚያቆማቸውም የመንግስት አካል አልተገኘም።

ግንቦት 7 ሕዝባዊ ሃይል ላለፉት ሶስት ወራት ያሰለጠናቸውን የአራተኛ ዙር ታጋዮችን አስመረቀ

የኢትዮጵያዊያንን ስቃይና መከራ ሊያቅብና እንባቸውን ሊየብስ፤ ሀገራችን ኢትዮጵያ በጎጠኛው ሕወሃት የደረሰባትንና እየደረሰባት ያለውን ውርደት ወደ ክብር ለመለወጥና የናቋትና ያዋረዷት በፍትህ ሚዛን ላይ እንዲቀመጡና ፍርዳቸውን እንዲያገኙ ለማድረግ ዓላማየ ብሎ ምሎ ዱሩ ቤቴ ካለ ገና ሁለት ዓመት እንኳ ያልሞላው ግንቦት 7 ሕዝባዊ ሃይል በቃሉ መሰረት አራተኛውን ዙር የታጋዮች የምረቃ በአል ሚያዚያ 26 2006 ዓ/ም ጥሪ የተደረገላቸው የክብር እንግዶች በተገኙበት ማክበሩን አስታወቀ። ይህ የአራተኛው ዙር ስልጠና በሰልጣኞች ቁጥርም ሆነ በስልጠናው ጥንካሬ ካለፉት ሶስት ዙሮች በእጅጉ የተለየ እንደነበር የተገለጸ ሲሆን በአሁኑ ሰአት ያለውን የሀገሪቱን ነባራዊ ሁኔታ ያገናዘበና ወቅቱ የሚፈልገውን ቴክኖሎጅ በመጠቀም መረጃን መቀበልና ማስተላለፍን የጨመረም እንደነበር ተያይዞ ተጠቅሷል።

በሀገር ውስጥ ፋሽስት ወያኔ እያደረሰው ባለው መረን የወጣ ግፍ የተበሳጩና ሁሉም ልክ እንዳለው ለማሳየት ቆርጠው የተሰለፉት እነዚህ ምሩቅ ታጋዮች ከወታደራዊው ስልጠና በተጨማሪ የፖለቲካ፣ መረጃና ደህንነት እንዲሁም ሌሎችንም ተያያዥ ክህሎቶችን በበቂ ሁኔታ እንደቀሰሙም ተጠቁሟል። ስልጠናው ታጋዮቹ ወደፊት ከሚያጋጥማቸው ጠንካራ ፈተናና ከሚሰለፉበት ጥብቅ ግዳጅ አንጻር በቀላሉ ተስፋ እንዳይቆርጡ ለማድረግ በአካልም ሆነ በመንፈስ ዝግጁ እንደሚያደርጋቸው የተገለጸ ሲሆን የተጀመረው ሕዝባዊ ትግል በግለሰብ ደረጃ ሳይሆን በጋራና በተቀነባበረ ሃይል ለድል እንደሚበቃና ይህን የጋራ ሃይል በጠነካራ እጆች ላይ ላመስቀመጥም የተሰጠው ስልጠና ከበቂ በላይ ነበር ተብሏል።

Thursday, May 15, 2014

የሞት ጣር ድምፅ በግምቢ ወለጋ ተሰማ!

በቅዱስ ዮሃንስ

ወያኔ የቀበረው የዘር መርዝ በቅሎና አድጎ አፈራለት ማለት ነው? እኛም እንደ ሩዋንዳ ልንሆን ነው? አረ እግዚኦ በል ወገን፣ እኔ የምሰማውን ላምን አልቻልኩም፥ እንባየንም ማስቆም ቸገረኝ ፤ ከመቼውም በላይ ልቤ አዘነ፣ ቅስሜ ተሰበረ ፣ ወገኖች በሳኡዲ ሲታረዱ አለቀስኩ ፣ ተሰለፍኩ ፣ ድምጼን ከፍ አድርጌ ከወገኔ ጋር በእልህ ጮህኩ፦ አሁንስ ለማን እንጩህ ፣ ዕባካችሁ ምከሩ ጎበዝ፦ በአገራችን ኢትዮጵያ ክፉ ቀን እያንዣበበ ነው፦ ወንድሙ ወንድሙን እንደ ኣውሬ አሳዶ ሊበላው ነው፤ የጨለማ ሰዓት መጣ በአገራችን ፤ በወገን ላይ ስጋትና ሺብር እጅግ ነገሡ ፦ ኢትዮጵያዊው አባት ድረሱልኝ ይላል ፥ እናት ነብሴ ተጨነቀች ሞትና እኛ ፊት ለፊት ተፋጠናል ፥ ማድረግ የሚቻል ነገር ካለ በፍጥነት ድረሱልን ይላሉ።

ሰላም ወዳድ የኦሮሞ እና የአማራ ሕዝብ ሆይ አድምጠኝ ፣ አንድነታችን በእሳት እየተፈተነ ነው፤ የስንት ታላላቅ አገር ኢትዮጵያ በእኛ ዘመን እንደዚህ አትሆንም እምቢ ለዘረኝነት እንበል ። የጎጠኝነት በሽታ ሕዝባችንን ሲያሸብር እያየን በምንም መልኩ አንታገሰው ፣ እነማን እንደሚያቀነባብሩት እናውቃለን ፣ የጋራ ጠላታችን ወያኔ ነው።

ዝክር ለግንቦት 7 1997 እና ለግንቦት 7 ቀን 2000 ዓ.ም.

ዘንድሮ፣ የታሪካዊው ግንቦት 7 ቀን 1997 አገር ዓቀፍ ምርጫ ዘጠነኛ ዓመት እና ንቅናቄዓችን የተመሠረተበት ስድስተኛ ዓመት የምንዘክረው ከመችውም በላይ አገራችን አሳሳቢ ሁኔታ ላይ ሁና ነው። ወያኔ የማይገዛትን አገር እንዳትኖር ለማድረግ እማትወጣው አረንቋ ውስጥ ከመክተት የማይመለስ ኃይል መሆኑን ዛሬ በአምቦ፣ በጉደር፣ በጊምቢ እና መሰል ቦታዎች በተግባር እያስመሰከረ ነው።

የኢትዮጵያ ሕዝብ በታሪኩ ለመጀመሪያ ጊዜ እውነተኛ ፍላጎቱን የመግለጽ አንፃራዊ ነፃነት አግኝቶ የነበረበት የግንቦት 7 ቀን 1997 ዓ.ም. ምርጫን ስናስብ ዛሬ ያለንበት ሁኔታ መመዘናችን አይቀርም። ያኔ ለአብዛኛው የኢትዮጵያ ሕዝብ እንደ እጁ መዳፍ ቀርባ ትታየው የነበረችው ድል እስከዛሬ አልጨበጣትም። ትግሉ ግን ቀጥሏል። የዛሬው ትግላችን የኢትዮጵያ ሕዝብ ከያኔው በበለጠ ከታሪክና ከራስዋ ጋር የታረቀች አገር የመመሥረትን ርዕይ አስፈላጊነት ላይ ትኩረት መስጠትን የሚጠይቅ ሆኗል።

ወያኔ ከተፈጠረበት ጊዜ ጀምሮ ለአለፉት አርባ ዓመታት ሲያብላላው የቆየው፤ በመንግሥት ሥልጣን በቆየባቸው ሃያ ሶስት ዓመታት ውስጥ ደግሞ በፓሊሲ ደረጃ ሲያስፈጽመው የቆየውን የዘር ፓለቲካ አስከፊ ውጤት አሁን እየታየ ነው። ይህ የዘር ፓለቲካ ራሱ ወያኔን ያጠፋዋል። ችግሩ ግን የዘር ፓለቲካ ወያኔን ነጥሎ አያጠፋም፤ ከወያኔ ጋር አገራችንንም ሊያጠፋ ይችላል። ከሁሉም በላይ አሳሳቢው ጉዳይ ደግሞ የዘር ፓለቲካ የበርካታ ኢትዮጵያዊያንን ሕይወት አደጋ ላይ ሊጥል ይችላል። በጎረቤት አገራት ውስጥ ያየነውን ዓይነት የእርስ በርስ እልቂት ወደ አገራችን ለማምጣት ህወሓትና ኦህዴድ ተግተው እየሠሩ ነው። ሌሎች የወያኔ ተቀጥላ ድርጅቶችም የዚህ ትልቅ የጥፋት ፕሮጀክት አካል ናቸው።

የግንቦት 7 1997ቱ ብሩህ ተስፋ በፋሺስቱ ወያኔ የግፍ አፈና ሲጨልም፤ ያ ተስፋ እንዲያንሠራራ በግንቦት 7 2000 ዓ.ም. የተቋቋመው ግንቦት 7: የፍትህ፣ የነፃነትና የዲሞክራሲ ንቅናቄ ዛሬ የኢትዮጵያን ተስፋ ለማጨለም ከተነሱ ኃይሎች በተፃራሪ በመቆም የሕዝብና የአገር አለኝታነቱ ማረጋገጥ ይኖርበታል።

በሰለጠነ ክፍለዘመን የብሔር ፖለቲካ አሳፋሪ ነው፡፡

 ‪
አንድነታችንን ሊያጠናክሩ የሚችሉ ጉዳዮች ላይ ብናተኩር ሁላችንንም ይጠቅመናል፡፡

ኢትዮጵያ የአማራ ብቻ አይደለችም፤ ኢትዮጵያ የኦሮሞ ብቻም አይደለችም፤ ኢትዮጵያ የደቡብ ብቻም አይደለችም፤ ኢትዮጵያ የትግራይ ብቻም አይደለችም፤ ኢትዮጵያ የሁሉም ናት፡፡ ስለዚህ አንዱ ብሔር ከአንዱ ብሔር አይበልጥም፡፡ አንዱ ብሔር ከአንዱ ብሔርም አያንስም፡፡ ሁሉም እኩል ነው፡፡ አንዱ ከአንዱ ይሻላል በሚል ጽንፈኛ የብሔር ፖለቲካ አንድነታችንን ማፍረስ አይገባንም፡፡ የሁሉም ብሔሮች መገኛ የሆነችውን ኢትዮጵያን መመልከት ይገባል፡፡ በዚህም ረገድ ራሳችንን መሳል ተገቢ ነው፡፡ ያለበለዚያ ግን በየጊዜው እየዶለዶምን ሄደን አንድነታችንን ልናጣው እንችላለን፡፡

ኢትዮጵያ ምሳሌ ልትሆንበት የምትችልበት ነገር ሃይማኖት ብቻ አይደለም፡፡ ኢትዮጵያ ከሰማንያ በላይ ብሔር ብሔረሰቦችን በውስጧ አቅፋ የያዘች አገር ናት፡፡ አይደለም ሰማንያ ቀርቶ ሁለት ብሔረሰቦች ያሉባቸው አገሮች ግጭት ውስጥ ሲገቡ እናያለን፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ጥቃቅን ግጭቶች የሉም ማለት ባንችልም፣ በአጠቃላይ ግን ለመኖር የሚያዳግት ግጭት ግን አስተናግዳ አታውቅም፡፡ ይህ ታሪካችን የሚያኮራን ቢሆንም፣ አሁን አሁን ግን የሚስተዋሉት ነገሮች ሃይ ሊባሉ የሚገባቸው ናቸው፡፡ስለአብሮ መኖር ታሪካችን የማንጠነቀቅለት ከሆነ ይህ አኩሪ ታሪክ ሊበላሽና ሊጠፋ ይችላል፡፡ በተለያዩ ወቅቶች በአገሪቱ ውስጥ በሚገኙ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ውስጥ የሚነሱ የብሔር ግጭቶች የጉዳዩን አሳሳቢነት ሊያሳዩን ይችላሉ፡፡ በተለይም አገሪቱ ተስፋ የምታደርግባቸው እነዚህ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ጠባብ በሆነ የብሔር ፖለቲካ ውስጥ ገብተው ሲጋጩና ሲበጣበጡ ማየት አሳፋሪ ነው፡፡

ኢህአዴግ ፍፃሜው መቼ ነው?

ይህን ጥያቄ ሲሰሙ የሚከፉ ጥቂት የስርዓቱ ተጠቃሚ ሰወች ቢኖሩም አብዛኛው ኢትዮጵያዊ ግን የሚናፍቀው ቀን ነው:: ብዙ ሰው ቀኑን ከመናፈቁ የተነሳ የነዚህስ ዕድሜያቸው ረዘመ ምን አለ ፈጣሪ ቢገላግለን ሲል ይሰማል:: እኔ ግን እላለሁ ህወሓት/ ኢህአዴግ ን እኛ ራሳችን በተለይም አዲሱ ትዉልድ እስካልደገፈው ድረስ ከዚህ በኋላ ዕድሜው አጭር ነው:: ለምን?

የመጀመሪያዉ ምክንያት ተፈጥሯዊ ነው:: ላለፉት 23 ዓመታት ሀገሪቱን ሲመሩ የነበሩት ሰወች አሁን እርጅና እየተጫናቸው ሲሆን በመጭወቹ ዓመታት አብዛኞቹ በእርጅና ምክንያት መስራት የማይችሉበት ደረጃ ይደርሳሉ ወይም እንደመለስ ይሞታሉ:: ይሄ ነገር ስርዓቱ ላይ የሚፈጥረው ችግር ቀላል አይሆንም:: በተለይም ድርጅቱ የይስሙላ መተካካት ሲያካሂድ የቆየ መሆኑ ችግሩን የከፋ በማድረግ ዉድቀቱን ያፋጥነዋል::

ሁለተኛዉ ምክንያት ድርጅቱ የሰበሰባቸው አባላት ጥራት ጉዳይ ነው:: ባለፉት 10 ዓመታት ኢትዮጵያ ዉስጥ በመንግስት ሥራ ለመቀጠር ፣ ለመነገድ ፣ በግብርና ሥራ ለመተዳደር ወይም በሌላ ሥራ ለመሰማራት የድርጅቱ አባል መሆን ግዴታ ነበር አሁንም ነው :: በአሁኑ ወቅት ያለው አብዛኛዉ የድርጅቱ አባል ባብዛኛዉ ወዶ ሳይሆን ተገዶ የገባ ነው :: እንደዚህ አይነቱ አባል ድርጅቱን ለማፍረስ አድፍጦ የሚጠብቅ ኃይል ከመሆኑም በላይ ድርጅቱን በሙስና እንዲጨማለቅ አድርጎታል:: አምነዉበት የገቡት አባላትም ቢሆን በድርጅቱ መሰረታዊ ባህሪ የተነሳ መጠየቅ እና የራስን ነፃ ሃሳብ ማራመድ በድርጅቱ እንደነዉር ስለሚቆጠር ፈሪ እና ተከታይ እንጅ ሃሳብ አመንጭ አይደሉም ፤ እንደነዚህ አይነቶቹ ሰወች ያለመሪ ድርጅቱን ማዳን የሚችሉ አይደሉም::

Tuesday, May 13, 2014

አየሽ ሀገር ሲያረጅ

በአገኘው አሰግድ

ዕድሜ ወጣትነት በሆነበት ዓለም
ከአንዲት ሀገር ማርጀት በላጭ ሀዘን የለም
ይሁልሽ እናቴ;
ሺ ዓመታት ዘለቅሽ
ልምድ ዕውቀት አዳበርሽ
ብሎ መደሰትን የቃጣን ቢሆንም
በዕድሜሽ ማርጀት እንጂ መላቅ አላየንም

አየሽ ሀገር ሲያረጅ:
ሥልጣኔ መሀል ሁዋላ ቀርነትን ሸልሞ ይሾማል
ክቡር ሰውን በልቶ በኩራት ይቆማል

አየሽ ሀገር ሲያረጅ
ዜናችን ቢነበብ
ግዋዳችን ቢዘገብ
ታጎሩ: ታሰሩ: ዱላ አረፈባቸው
ከሚለው አይዘልም;
ሰው ልሁን ያለን ሰው "ሰዎችሽ" አይምሩም!

ለመላው የኢትዮጵያ ህዝብና በተለይ ለሀገር ተረካቢ ወጣትና ምሁራን ብሎም በውጪ ለሚገኙ ዜጎች!!


ከባለራዕይ ወጣቶች ማህበር የተሰጠ መግለጫ

ስፊው የኢትዮጵያ ሕዝብ በሀገራቸው ሉአላዊነት እና በህዝቦች መፈቃቀድ መፈቃቀርና መኖር ዙሪያ ማንም ሰንካላ ምክንያት በማቅረብ እንዲበታትነው መፍቀድ የለበትም በተለይ ይመራናል ያስተዳድረናል በምንለው መንግስት ከህዝቦች ፍቃድና እውቅና ውጪ በማስተዳደርና በመግዛት ዙሪያ ያለው የተራራቀ ልዩነትና የመንግስታችን አተያየም የመግዛት በመሆኑ የግዛት ጊዜውን በማራዘም የጭቆና ቀንበሩን ለማፅናት ሲል ለ3 ሺ ዘመናት የነበራትን ታሪክ በማበላሸትና በዚያ አኩሪ ታሪኳም ለዜጎች ብቻ ሳይሆን ለአፍሪካ የነፃነት ተምሳሌትና ኩራት የሆነች ባላት ታሪክና ትሩፋት በተለይ በህዝቧ ያኗኗር ዘይቤ በኢትዮጵያ እድገት ውስጥ ያበበና ጎልቶ የወጣ ልዕልናዋም ከአጉረ አፍሪካ ተሻግሮ ለአለም መደነቂያ የሆነች ሀገራችን ላይ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ አጥልቶ ያለው የተቃርኖ እዳ የእርስ በርስ ግጭት እንዲፈጠር እየተጠነሰሰ ያለና በተግባራዊነቱም ጎልቶ የታየበት ጊዜ አይታወስንም በመሆኑም ዜጎች በመንግስት ትንኮሳና ሸር እየተፈፀሙ ያሉት ዜጎችን ከቦታቸው የማፈናቀል ለጠየቁት ጥያቄ አወንታዊ እርምጃ መውሰድ በጋዜጠኞችና በጦማሪያን ላይ የእስር እንዲሁም በቶፎካካሪ ፓርቲ አባላትና መሪዎች ላይ የሚደርሰው እንግልትና ወከባ የዚህች ሀገር ጎዞ ወዴት እያመራ ነው የሚለው እጅግ አሳሳቢ ነው ከዚህም በተረፈ በሚፈጠረው ግርግር ሰፊው የሀገራችን ህዝብ ተጎጂ የሚሆን በመሆኑና በተለይም በግንባር ቀደምነት የሀገራችን አምራችና አንቀሳቃሽ ብሎም ሀገር ተረካቢና አንቀሳቃሽ በምንለው ወጣት እጅጉን እየከፋ በመሄዱና ለጥቃትም ተጋላጭ በመሆኑ ይህን መግለጫ ለማውጣት ተገደናል፡፡

1. የሀገራችንን ህዝቦች ለመከፋፈልና ወደ ማያቋርጥ እልቂት ለመምራት በፈጠራ ታሪክ ላይ ተመስርቶ እየተሰራበት ያለው ሴራ ባስቸኳይ እንዲቆም እና የእልቂት መነሻ የሚሆን በተለይም አኖሌ የተገነባው ሀውልት ባስቸኳይ እንዲፈርስ በምትኩም ህዝቦች በጋራ ተቻችለው የሚኖሩበትና የጋራ አሴት ሊፈጥር የሚችል የመደጋገፍና የመረዳዳት ህልውናውን የሚያጠናክር መዘከር እንዲሰራ እንጠይቃለን፡፡

Sunday, May 11, 2014

የወያኔ ጥላቻ ፍሬ


ፕሮፍ. መስፍን ወልደ ማርያም

ወያኔ ለትግራይ ሕዝብ ሀብትንና ብልጽግናን አመጣ ብለው የሚያምኑ ሰዎች ብዙ ናቸው፤ ወያኔ የሥልጣን ወንበሩ ላይ በመውጣቱ ትግሬዎች ሁሉ አልፎላቸዋል ተብሎ ይታመናል፤ በተለይ በአውሮፓና በአሜሪካ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን በዚህ ላይ የጠነከረ እምነት አላቸው፤ በዚህ ጉዳይ ላይ ከኢትዮጵያ ውጭ ብዙ ውይይትም ይሁን ንትርክ ይደረጋል፤ በኢትዮጵያ ውስጥ ግን የተፈራ ርእስ ነው፤ ውስጥ-ውስጡን እንጂ አደባባይ አይወጣም፤ ይህንን ጉዳይ በኢትዮጵያ ውስጥ አደባባይ ለማውጣት ጊዜው የደረሰ ይመስለኛል፤ አረጋዊ በርሄ፣ ገብረ መድኅን አርአያ፣ አስገደ ገብረ ሥላሴ፣ አብርሃ ደስታ (አሥር ቢሞሉልኝ ደስ ይለኝ ነበር!) እየደጋገሙ ቢያነሡትም ሌሎች በቁም-ነገር የተቀበሉት አይመስልም፤ ሕዝቡ ግን በራሱ መንገድ እየተናገረና ምስክርነቱን እየሰጠ ነው፤ በመቀሌ የተሠራውን የመኳንንት መንደር ሕዝቡአፓርቴይድ ብሎ ሲሰይመው፣ በአዲስ አበባ የተሠራውን መንደር መቀሌብሎ ሲሰይመው እየመሰከረ ነው፤ ‹‹የለሁበትም!›› እያለ ነው።

የትግራይ ሕዝብ መደህየቱ አልበቃ ብሎት ሲለምንም እየተሳቀቀ ነው፤ የሚለምነው ትግሬ ለብዙ ሰዎች ትግሬና ወያኔ አንድ መስሎ እንደሚታየው ያውቃል፤ አብዛኛው ሰው በወያኔ ላይ ያለውን ስሜት ያውቃል፤ ስለዚህም ሲለምን ሰዎች በወያኔ ላይ ያላቸውን ስሜት ስለሚያራግፉበት እየተሸማቀቀ ነው፤ አንድ የትግራይ ቄስ ከአርሲ ነኝ አሉኝና ለምን እውነቱን አይናገሩም ስላቸው እውነቱን ስናገር የማገኘው ስድብ ብቻ ነው አሉኝ፤ እኒህ ሰው ምን በወጣቸው የወያኔን ኃጢአት ተሸካሚ ይሆናሉ፤ በሌላ በኩል ደግሞ በትግሬነቱ የተጠቀመ አለ፤ እኔ የማውቀው የደርግ ወታደር የነበረ ትግሬ ቆስሎ ከውትድርና ወጣና በአንድ የመንግሥት መሥሪያ ቤት የጥበቃ ሥራ ላይ ነበር፤ በጣም ይቸግረው ነበር፤ ሚስቱ ሕመምተኛ ነበረች፤ የቤት ኪራይ መክፈል ይቸገር ነበር፤ ዛሬ ግን የሚለብሰው ልብስ ሌላ ነው፤ ከኑሮውም ተርፎ ለሲጃራና ለጫት እያወጣ ነው፤ ወይም ሌሎች እያወጡለት ነው፤ ትግሬነታቸው ብቻ እንዲህ የደላቸው በጣም፣ በጣም ጥቂቶች ናቸው፤ ስለዚህም በወያኔ አገዛዝ ትግሬ ሁሉ ተጠቅሞአል ማለት ከጉልሁ እውነት ጋር የሚጋጭ ስሕተት ነው፤ አብርሃ ሰዎች ትግሬ ሁሉ ተጠቃሚ ሆኗል ሲሉ ‹‹ያመኛል›› ማለቱ ይገባኛል።

Friday, May 9, 2014

"ኪላርክን እንዳይዘምር ሊያዘው የሚችል እኮ እሱ ማን ነው?"


አምባገነንን መዋጋት ቀላል አይደለም፣ ክፍያው ብዙ ነው፡፡ ይህንን እያወቁ ትግሉ ላይ ለሚሳተፉት ሰዎች አድናቆቴ ከፍ ያለ ነው፡፡ አምባገነን ኃይል ተፋላሚውን ማንበርከክ ብሎም ማጥፋት ያስችለኛል በማለት የጦር ኃይል፣ ለሆዳቸው ያደሩ ሰዎችን ከተራው ሰው ጀምሮ እስከ ለሰማይና ለምድር የከበዱ ሙህራንንና የሀይማኖት አባቶችን ይጠቀማል፡፡ ያስራል፣ ያፍናል፣ ከቤትና ከቀየ ያፈናቅላል ይገላል፡፡ ሕሊናውን የሸጠ ቅልብ ጨካኝ ሰራዊት አሰማርቶ እያስፈራራና እየገደለ የሰው ልጅ በኑሮው፣ በስራው፣ በማህበራዊ ህይወቱ፣ በሁሉም የህይወት ገጽታው በሃይል እየገዛው ለመኖር ሰርክ ይጥራል፣ ይወጣል ይወርዳል፡፡ ይህንን ለማድረግ የተለያዩ ‹‹የፍትህ›› አካላትና የሚዲያ ተቋማት ጭራቸውን እየቆሉ ከስር ከስሩ ይከተሉታል፡፡ ትልቁና በታላቅ የሞራል ከፍታ ላይ ያለው ኃይል ደግሞ በብዕሩ የሰው ልጆችን ነጻነት የገፈፉ አማባገነኖችንና ጨቋኞችን ይታገላል፣ በትግሉ ላይም ይሞታል፣ ይሰደዳል፣ ይታሰራል፡፡ ደጋፊዎቹንም ያለምንም ጫናና ተጽዕኖ በነጠረ የአስተሳሰብ አንድነት አስተባብሮ ከጎኑ ያሰልፋል፣ ሰላም ለእናነንተ ይሁን! አሜን!!

ይህንን የሚያስብለኝ ነገር ምን እደሆነ መቼም ይጠፋችኋል ብየ አላሰብም፡፡ ፌስ ቡክ ከሚሉት ጉድ ርቄ ነበር፤ ይህ የማህበረሰብ ድህር ገጽ ከአመት በፊት በብዙ ባለተሰጥኦ እና ድንቅ አሳቢ ሰዎች የተሞላ ስለነበር ከኮምፒውተሬ ፊት ለፊት ቁጭ ብየ እነሱ የሚጽፉትን ነገር ማንበብ ከስራየ በላይ ዋናው እለታዊ ጉዳየ ነበር፣ ነገር ግን እነኛ ሁሌም ሳነባቸው ነፍሴን የሚሞሏት ልጆች ቀን ሲሄድ ቀን ሲመጣ ቀስ በቀስ ከዚህ ትስስር እየራቁ ሲመጡና በአንጻሩም ጭንጋፎች ብቻ እየሞሉት ሲመጡ ይታወቀኝ ጀመር፤ ሆኖም ግን አልፎ አልፎም ቢሆን መጎብኘቴ አልቀረም፡፡ አሁንም ከወር በላይ ርቄው ወደነበርኩት ፌስ ቡክ የመለሰኝ ዞን 9 የተባሉት የጦማርያ ቡድን ታሰሩ የሚል ወሬ ሰምቼ ነው፣ አልደነገጥኩም፤ ምክንያቱም መታሰር ብርቅ አይደለም፤ ምክንያቱም በእኛ ሀገር ከጻፍክ ሰውም ካነበበህ በቃ ትታሰራለህ፤ ይህንን ከአሁን በፊት አይተናል፣ ሰምተናል፤ …. ስለዚህም ብርቅ አይደለም፡፡

Thursday, May 8, 2014

Ethiopia: Brutal Crackdown on Protests – Human Rights Watch report

Security Forces Fire On, Beat Students Protesting Plan to Expand Capital Boundaries


(Nairobi) – Ethiopian security forces should cease using excessive force against students peacefully protesting plans to extend the boundaries of the capital, Addis Ababa. The authorities should immediately release students and others arbitrarily arrested during the protests and investigate and hold accountable security officials who are responsible for abuses.

On May 6, 2014, the government will appear before the United Nations Human Rights Council in Geneva for the country’s Universal Periodic Review of its human rights record.

“Students have concerns about the fate of farmers and others on land the government wants to move inside Addis Ababa,” said Leslie Lefkow, deputy Africa director. “Rather than having its security forces attack peaceful protesters, the government should sit down and discuss the students’ grievances.”

Since April 25, students have demonstrated throughout Oromia Regional State to protest the government’s plan to substantially expand the municipal boundaries of Addis Ababa, which the students feel would threaten communities currently under regional jurisdiction. Security forces have responded by shooting at and beating peaceful protesters in Ambo, Nekemte, Jimma, and other towns with unconfirmed reports from witnesses of dozens of casualties.

የወያኔን ውድቀትና የኢትዮጵያን ትንሣኤ ለማፋጠን ኅብረታችን ይጠንክር!!!

ግንቦት 7፡ የፍትህ፣ የነፃነትና ዲሞክራሲ ንቅናቄ፣ በግፍ ሕይወታቸው ባጡ ዜጎች መርዶ የተሰማውን ጥልቅ ሀዘን እና ቁጭት ይገልፃል፤ ለቤተሰቦቻቸውም መጽናናትን ይመኛል። ህወሓት እና አጋፋሪው ኦህዴድ በነዙት ሽብር ሳቢያ የአካል ጉዳት የደረሰባችሁ፣ የተደበደባችሁ እና ለእስር የተዳረጋችሁ ወገኖቻችንም ህመማችሁም እስራችሁም የሁላችንም ነው። መላው ኢትዮጵያዊ ወገናችሁ ከእናንተ ጋር ተገድሏል፣ ቆስሏል፣ ተደብድቧል፣ ተግዟል፣ ታስሯል። ህወሓት፣ ኦህዴድ እና በዚህ ጭፍጨፋ እጃቸው ያለበት ሁሉ ከተጠያቂነት የማያመልጡ መሆኑን ግንቦት 7 ደጋግሞ ያስገነዝባል።

በህወሓት ዘረኛና ፋሽስታዊ አገዛዝ ያልተበደለ የኢትዮጵያ ክፍል የለም። የወያኔ አጋፋሪ የሆነው አህዴድ የኦሮሞ ወጣቶችን፣ ሕፃናትንና አዛውንትን ሲጨፈጭፍና ሲያስጨፈጭፍ፣ ሌላው አጋፋሪ ብአዴን ደግሞ በጎንደርና አካባቢው ተመሳሳይ ጭፍጨፋዎችን አካሂዷል። ወያኔ ከፋሺስት ኢጣልያ ወርሶ ለሃያ ዓመታት በትጋት ያራመደው “የከፋፍለህ ግዛ” ፓሊሲ ምርት እነሆ ዛሬ በዓይኖቻችን እያየን ነው። ፋሽስት ጣልያን ጀምሮት የነበረውን ኢትዮጵያን የማጥፋት ስትራቴጄ ለማጠናቀቅ ህወሓት በጥድፊያ ላይ ነው። ይህን እኩይ ዓላማ ማስቆም የሁላችን ኃላፊነት ነው።

የመከላከያ ሠራዊት እና የፊደራል ፓሊስና አባላት ሆይ፣ ለዘረኛው ወያኔ መሣሪያ ሆናችሁ ወገናችሁን አትፍጁ! እናንተ የምታገለግሉት ሥርዓት፣ ከእናንተ መካከል ኦሮሞ ያልሆኑት እየመረጠ ኦሮሞዎች ወገኖቻችንን እንዲገሉ፣ አማራ ያልሆኑት ተመርጠው አማሮችን እንዲገሉ የሚልክ መሠሪ መሆኑን የምታውቁት ነው። ወኔን አንዳችንን በሌላችችን ላይ እያዘመተ እርስ በርስ ሊያፋጀን ቆርጦ መነሳቱን አስተውሉ። ይህን እኩይ ዓላማ የማክሸፍ ሥራ የናንተም ኃላፊነት እንደሆነ ግንቦት 7 ያስገነዝባል።

Saturday, May 3, 2014

ኢትዮጵያ በህግ አምላክ የሚባልባት ሀገር መሆኗ ቀርቷል

ግፈኛውና ዘራፊው የወያኔ መንግስት በኢትዮጵያ መሬት ከሚሰራቸው ትልልቅ ወንጀሎች አንዱና ምናልባትም ዋነኛው በህግና ሕገ-መንግስት ላይ የሚያካሄደው ቀልድና ጭዋታ ነው። ሕገ-መንግስት ህዝብን ከእብሪተኛ መንግስት መጠበቂያ መሳሪያ መሆኑ ቀርቷል። ህግና ሕገ-መንግስት ለወያኔ ሲፋጅ በማንኪያ ሲበርድ በጣት የሚበላ ነገር ነው። ወያኔና አፋኝ ስርአቱ ህግ የሚጠቅሱት ለራሳቸው ይጠቅመናል ባሉበት ሰዓት ነው። ህግ ለነሱ ካልተመቻቸው ተቀዶ የሚጣል ቆሻሻ ወረቀት ነው።

በኢትዮጵያ ምድር ዋናው ሕገወጥ ተቋም ራሱ ላወጣው ሕግ የማይገዛው ወያኔ/ህወሃት ነው። ለዚህ ነው “ለሚመለከተው አካል ከማሳወቅ ውጪ ሰላማዊ ሰልፍ ለማካሄድ ፈቃድ አይጠየቅም” የሚለውን ራሱ ያወጣውን ህግ ጥሶ ሰሞኑን ተቃዋሚዎችን ቁም ስቅላቸውን የሚያሳያቸው። ለዚህም ነው ሃሳብን በጽሁፍና በቃል ለመግለጽ ቅድመ ምርመራ እና እገዳ አይኖርም ብሎ ጽፎ፣ አለም አቀፍ የሰበአዊ መብት ድንጋጌዎች እንዳሉ ተቀብያለሁ ብሎ የተናገሩና የጻፉ ሰዎችን የሚያሳድደውና በሽብርተኝነት የሚከሰው።

ኢትዮጵያ “በሕግ አምላክ” የሚባልባት ሀገር መሆኗ ቀርቷል። ወያኔ ይህን ለህግ ትልቅ ክብር ያለውን የህዝባችንን የዘመናት እምነት ድራሹን በማጥፋት ላይ ይገኛል። ፍትህ በወያኔ አፋኞች መዳፍ እጅ ወድቃለች።

በዚያ አስከፊ የደርግ መንግስት ስርአት እንኳን ዳኞችን “እንዲህ ብላችሁ ፍረዱ” የሚል ትእዛዝ አልነበረም።

‪‎አምቦ‬- ትናንትና ዛሬ


ስለ አምቦ ስጠየቅ ብዙ ጊዜ የምመልሳት መልስ አለች። መልሴን ከእንግሊዞቹ አባባል ነው የወረስኳት። አዎ አምቦ ትንሽ ነች፤ ስሟ ግን ግዙፍ። እናም ብዙውን ጊዜ «ይህቺው ነች አምቦ?» የሚል ነው ጥያቄው። መልሴን ከመመለሴ በፊት ከተማዋን ለሁለት ከሚከፍላት ከሁሉቃ ወንዝ ድልድይ ወስዳቸዋለሁ። «ከዚህ ድልድይ ስር የሚፈሰው ይታያችኋል? አዎ በድልድዩ ስር የሚፈሰው ውሃ ሳይሆን የታሪክና የፍቅር ውሁድ ነው!!» እላቸዋለሁ።

ከ1992 ዓ/ም በኋላ አምቦን ያስተዋላት ሰው ይህቺን ከተማ ግልገሎቿን በጉልበተኛና ነጣቂ አዳኝ በየጊዜው ከምትነጠቅ ምስኪን እናት ጋር ሊያመሳስላት ይችላል። በ1992፣ 1994፣ 1996፣ እና በ1998 ዓ/ም በርካታ የአምቦ አጠቃላይ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪዎችን ሕይወት የቀጠፉ የተለያዩ የተቃውሞ ሰልፎች ተደርገዋል። በሀገራችን ካሉት አንጋፋ ከተሞች አንዷ ብትሆንም የእድሜዋን ያህል ግን አላደገችም። አምቦ ለምን የእድሜዋን ያህል አላደገችም የሚለውን ጥያቄ ብዙዎች ከድህረ ደርግ የፖለቲካ ምህዳር ጋር ያያይዙታል። የአምቦ ሕዝብ ሰው ወዳድ፣ እንግዳ ተቀባይ እና ተቻችሎ መኖርን የሚያውቅ ሕዝብ ነው። የዚያኑ ያህል ደግሞ እንደማንኛውም ሰው ሲረግጡትና ሲጫኑት የሚቀበል ሕዝብ አለመሆኑ በተለያዩ ጊዜያት ታይቷል። አምቦ የሚለው ስም ከጭካኔ ጋር የተያያዘ የሚመስላቸው ግለሰቦች ጥቂት አይደሉም። ብዙዎቻችን የአምቦ ልጆች ከአምቦ እንደመጣን ስንናገር በሰዉ ዘንድ መገረም ሲፈጠር ብዙ ጊዜ ታዝበናል። አምቦ የ«ሰው» ሀገር የማይመስላቸው ብዙዎች ናቸው። የዚህ ሁሉ ምንጩ የሀሰት ፕሮፓጋንዳ ነው። ኢህአዴግ በምዕራብ አዲስ አበባ በኩል ሲገባ አምቦ ላይ የገጠመው አልህ አስጨራሽ ጦርነት አምቦ ይህንን ስም እንድታገኝ እንዳደረገ ብዙዎች ያምናሉ። «በጥንቃቄ እና በማስተዋል ካልታዩ ሚዲያዎች ጨቋኙን ተጨቋኝ፣ ተጨቋኙን ደግሞ በዳይ አድርገው ያሳያሉ» ያለው ማልኮም ኤክስ ነው መሰለኝ።

የትግራይ ህዝብ ጠላትች የህወሓት-ኢህኣደግ መሪዎች ናቸው!!!!


ምክንያቱም:

የህወሓት-ኢህኣደግ መሪዎች እጃቸው በንጹሐን ደም የጨቀየ፣ አንደበታቸው በውሸት የረከሰ፣ ኪሳቸው በሙስና ገንዘብ የተሞላ፣ ጭንቅላታቸው ከሥልጣቸው ውጪ አርቆ ማሰብ የማይችል የደርግ ፎቶ ኮፒዎች።
እንዴት???

መጀመርያ "የህወሓት-ኢህአዴግ መሪዎች እጃቸው በንጹሐን ደም የጨቀየ" የሚለው በተለያየ መንገድ እስኪ እንየው። ኣንደኛው እነኚ መሪዎች በሽዎች የሚቆጠሩ ንፁሃን ገበሬዎች በነ ግርማይ መጎስና ብስራት ኣማረ ኣስፈፃሚነት ሂወታቸው እንዲጠፋ ያደረጉ ናቸውና እጃቸው በንጹሐን ደም የጨቀየ ቢባሉ ኣይበዛባቸውም። በሌላ እይታ ስንመጣ ደግሞ እላይ የተጠቀሱት ገበሬዎችም ሆኑ ከስልሳ ሽ በላይ ታጋዮች በመራራው ትግል ሂወታቸው የተከፈለው ጨቋኝ ስርኣት ተወግዶ ህዝቦች በእኩልነት ፍትህ፤ እድገትና ሰላም የሚያገኙበት ስርኣት ለመፍጠር ነበር። ይሁንን ያንን ኣላማ ረስቶ የህወሓት-ኢህአዴግ መሪዎች የድሆችን ቤት ህጋዊ ኣይደለም እያሉ እያፈረሱ ለራሳቸው ግን ህጋዊ ባልሆነ የተከለለ ደን ውስጥ ገብቶ ፎቆች ሲሰሩ፤ ህዝቡን በስራ እጦና የሚታረስ መሬት በማነሱ ኣገር ትቶ በሚሰደድበት ትራክተር ገዝቶ ኣደራጅቶ ከመስጠት ይልቅ ራሳቸው ከውጭ ኩባንያዎች ተደራጅቶ መዝረፋቸው፤ ብትግራይ ህዝብ ስም እየነገዱ የትእምት ሃብት ለራሳቸውና ቤተሰቦቻቸው መጠቀምያ ማድረጋቸው ሁሉ የንፁሃኑ የተሰውት ደም ከንቱ የሚያስቀር በመሆኑ የህወሓት፡ኢህአዴግ መሪዎች በደም የጨቀዩ መባላቸው ኣያንስባቸውም ባይ ነኝ።

"አንደበታቸው በውሸት የረከሰ፣ ኪሳቸው በሙስና ገንዘብ የተሞላ" የሚሉት ኣጠቃልለን ስናያቸው ደግሞ ህዝቡ በሳምንት ኣንድ ግዜ ውሃ በሚያገኝበት ግዜ የውሃ ሽፋን 80%- 90% ደረሰ እያሉ የሚዎርጩ የውሸት ዶክትሬት ያላቸው እንደሆኑ ላንተም መገመት ኣያቅትህም። ኪሳቸው በሙስና የተሞላ የሚለው እንኳን መንግስት ራሱም የሚያውቀው ስለሆነ ኣያከራክረንም። ነገር ግን በጣም የሚያሳዝነኝ የቅዱሳን ነጋና ባለቤትዋ በተሰብ የሆኑት ዶክተር ጌታቸውና ኣቶ ኣማኑኤል የመቐሌ ከተማ የውሃ ሽግር ለመፍታት የተመደበ 100 ሚልዮን ብር በልቶ ቻይናና ጃፓን ተደብቆ እየኖሩ ነው። የመቐሌ ህዝብም የውሃ ችግሩ ሚፈታለት ኣጥቶ እየተሰቃየ ነው። እነዛ በሙስና የጨቀዩ ባለስልጣናትም በኢንተርፖል ኣድርጎ ሰዎቹ ባያስሩዋቸውም ብሩን እንዲመለስ ኣድርጎ የህዝቡን ችግር መፍታት እየቻሉ ቤተሰቦቻቻው ለለመጉዳት ዝምታን መረጡ። ታድያ የህወሓት፡ኢህአዴግ መሪዎች ኪሳቸው በሙስና ገንዘብ የተሞላ መባላቸው የቱ ላይ ነው ጥፋቱ?

“አውሬነት” – ለማንም አይበጅምና ጠንቀቅ!!


(የጎልጉል ርዕሰ አንቀጽ)

አሁን ከኢህአዴግ ጋር ገድለሃል አልገደልክም የሚል ክርክር የለም። ራሱ ባንደበቱ “ገድያለሁ” ብሏል። ነፍስ ማጥፋቱን አውጇል። ያልገለጸው በጸጥታና በስም እንጂ አንጋቾቹ ህይወት መቅጠፋቸውን አረጋግጧል። ግድያው በዚህ ስለማብቃቱ ማረጋገጫ አልተሰጠም። ተቃውሞውም እየቀጠለ ነው። ከዚያስ? በደም እየታጠቡ፣ ወንጀልን እያባዙና የደም ጎርፍ እየጎረፈ “ህግ” ማስከበር እስከመቼ ያስኬዳል። ያዋጣልስ? የህዝብ እንባስ እንዲሁ ከንቱ ይቀራል?

በርግጥ ህግ ማፍረስ አይደገፍም። ህግ መከበር አለበት። ከሁሉም በላይ ደግሞ ህገመንግስት ክቡር የመተዳደሪያ ዋስትና በመሆኑ ሊናድ አይገባውም። ህግን የማክበርና የማስከበር ጥያቄ አይለያዩም። ኢህአዴግ እንዳሻው የሚምልበትን ህገ መንግሥት እየጨፈላለቀና እየጎራረደ ሌሎች ህግ እንዲያከብሩ መጠየቅ ለምዶበታል። ሰዎች መብታቸውን እንዲለማመዱ አይወድም። ይህ ችግሩ በደም የታጠበ፣ የደም እዳ ያለበት፣ ታሪኩ ሁሉ ከደም ጋር የተሳሰረ እንዲሆን አድርጎታል። እስኪ ወደ ዛሬው ጉዳይ እናምራ!

አልታደልንም

ህዝብን የሚያከብር፣ ለህዝብ ቅድሚያ የሚሰጥ፣ በህዝብ የሚምል፣ ህዝብ ውስጥ የሚኖር፣ ህዝብ እውቅና የሰጠው፣ ህዝብ የሚያምነው፣ ሲፈልግ የሚቀጣው፣ ሲፈልግ የሚያሞግሰው አስተዳደር አጋጥሞን አያውቅም። የቀደመውን ኮንኖ የሚመጣው ከቀደመው የማይሻል፣ ደም የጠማው፣ ጠመንጃ አምላኩ የሆነ አገዛዝ ነው። አገሪቱም፣ ትውልዱም፣ የወደፊቱ እንግዳ ዘርም ሁሉም በስህተት ቅብብል በርግማን ይኖራሉ። ነፍጠኛ፣ ትምክተኛ፣ ጎጠኛ፣ ጠባብ፣ ኪራይ ሰብሳቢ፣ አንጃ … ቃላት እንደ ፋብሪካ ምርት እየተፈበረኩልን ስንሰዳደብ እንኖራለን። የሁሉም አስተሳሰብ አንድ ብቻ ነው – የራሱን ህልውና ለማስፈን የሚቃወሙትን ሁሉ መደምሰስ! “በጠላቶቻችን መቃብር ላይ …” የሚለው መፈክር ደርግ ቢለውም የራሱ በማድረግ አንግቦ የሚዞረው ግን እጅግ በርካታ ነው፡፡

Thursday, May 1, 2014

“ዘረኝነት ትልቅ በሽታ ነው!”


በአስራት አብርሃም

ዘረኝነት ትልቅ በሽታ ነው። በዘረኝነት የታወረ ሰው ስለእውነት፣ ስለአብሮ መኖር አይጨነቅም፤ ምክንያቱም ብሩህ የሆነ መጪ ጊዜ አይታየውም፤ የለውምም። ለሁሉም ነገር መፍትሄውን ሳይሆን ጨለማውን ነው የሚታየው። ጠቡ ከህዝብ ጋር ነውና ለበሽታው በቀላሉ መፍትሄ የሚገኝለት አይደለም። እውቀት፣ ሚዛናዊነት እና ሰብኣዊነት በእርሱ ህሊና ላይ ወንበር አይኖራቸውም። ሰውን ያህል ክቡር ፍጡር በጅምላ ይፈርጃል፤ በጅምላ ያወግዛል፤ በጅምላ ይመርቃል፤ በጅምላ ይረግማል። ከዚያ በኋላ በመጨረሻ መፍትሄ ሆኖ ወደ አንጎሉ ሊመጣለት የሚችለው ነገር ሜንጫ ወይም ገጀራ ነው የሚሆነው። በዚያ ገጀራ ደግሞ አንገት ለመቅላት ወደ አደባባይ ይወጣል፤ ሄዶ ሄዶም ይሄ የጥላቻ አዝመራ ፍሬ ማፍራቱ አይቀርምና እልቂት፣ በዘር ተለያይቶ መጨፋጨፍ ይሆናል ውጤቱ።

እንደዚህ ዓይነቱን በሽታ ወደ ሌሎች እንዳይጋባ ማድረግ የሚቻለው አንድም በተቻለ መጠን የመረጃ ክፍተቱን በመሙላት፣ እውነት የሆነውንና እውነት ያልሆነውን በበቂ እውነት አስደግፎ ለይቶ በማሳየት ነው። አንድም ደግሞ እንደዚህ ያለውን አስተሳሰብ የበላይነት አግኝቶ የትውልድ እልቂት ከማድረሱ በፊት በሀሳብ፣ በፖለቲካና በማነኛውም አውድ መታገልና ማጋለጥ ሲቻል መሆኑ ልብ ሊባል ይገባል። ምክንያቱም ከህዝብ እና ከሀገር የሚበልጥ ነገር ስለሌለ! እንዲሁም ለእውነት መቆም በሚያስፈልግ ስዓት ዋጋ የሚያስከፍል ቢሆን እንኳ ለእውነት መቆም የህሊና ጥያቄ ስለሚሆን ነው። በመሰረቱ አንድን ህዝብ ለይቶ በጅምላ የሚጠላ እና የሚያወግዝ የማንም ወዳጅ ሊሆን አይችልም። እስካሁን ከዓለም ታሪክ እንደምንማረው ስለፍትህ፣ ስለእኩልነትና አብሮ በሰላም ስለመኖር የታገሉት እንጂ በዘረኝነት መንገድ ቁልቁለት የተጓዙ ሲያሸንፉም ሆነ ክብር ሲያገኙ አላየንም። በዓለም ላይ ሁሉ ሰብአዊነት እና የሰውን ክቡርነት እየገነነ በሚሄድበት ጊዜ አንዳንዱ ደግሞ በባለፈው ዘመኑ ተኝቶ ይኖራል፤ ያ ዘመኑ ‘ሃንጎበር’ ሆኖ ስለሚጫጫነው ቶሎ መንቃት ይከብደዋል፤ ስለዚህ ገፋ ቢል ያቃዠው እንደሆነ እንጂ እውነተኛ ትንሳኤ አይኖረውም።

ጭፍጨፋውና አፈናው ይቁም፤ ወያኔ ይወገድ !!!

ግንቦት 7: የፍትህ፣ የነፃነትና የዲሞክራሲንቅናቄ፣ ዘረኛው ወያኔ በኦሮሚያ ሕዝብና ወጣቶች ላይ እያካሄደው ያለውን አረመኔያዊ ጭፍጨፋ፣ እስርና አፈናን በጥብቅ ይቃወማል። ህወሓት፣ ኦህዴድ እና በዚህ ጭፍጨፋ እጃቸው ያለበት ሁሉ ከተጠያቂነት የማያመልጡ መሆኑን ያስገነዝባል።

የአሮሚያ ወጣቶች በአዲስ አበባ ማስተር ፕላን ስም የድሀ ገበሬዎች መፈናቀልን መቃወማቸው ፍትሀዊ ነው። የወያኔ “ማስተር ፕላኖች” የወያኔ የዘረፋ እቅዶች መሆናቸው በተደጋጋሚ የታየ ጉዳይ ነው። ነዋሪዎቹን ያላማከረ፣ ግንባር ቀደም ባለጉዳዮችን ባለቤት ያላደረገ፣ የሕዝብ ይሁንታ ያላገኘ ማስተር ፕላን ተፈፃሚ ማድረግ አይቻልም።

ወያኔ ኦሮሚያን ብቻ ሳይሆን መላዋን ኢትዮጵያ በምስለኔዎቹ አማካይነት እየገዛ የኢትዮጵያን ውድ ልጆች በራሳቸው ጉዳይ ባይተዋር አድርጓቸዋል። ኦህዴድ በወያኔ ቅጥረኛነት የኦሮሚያ ወጣቶችን በማስጨፍጨፍ ላይ ያለ እኩይ የአድርባዮች ስብስብ ነው።  ወጣቶች የተቃወሙት ይህንን ነው።እነዚህ ወጣቶች በአካባቢያቸው ጉዳይ ብቻ ሳይሆን በመላው ኢትዮጵያ ጉዳይ ያገባቸዋል። ድምፃቸው ሊሰማ ይገባል። የሌላው አካባቢም ወጣት የኦሮሚያ ገበሬ መፈናቀል ያገባዋል። ኢትዮጵያዊያን በኢትዮጵያ ውስጥ በሚደረግ ጉዳይ ሁሉ ያገባናል። በየትኛውም የኢትዮጵያ ክልል ውስጥ ወያኔ የራሱን እቅድ እንዲጭንብን አንፈልግም።

Addis Ababa’s brutal regime on a killing spree again

The brutal TPLF minority regime has been arresting, torturing and mercilessly killing Ethiopians for the past 23 years. As recently as last week, the regime in Ethiopia made a house to house search and arrested Blue Party leaders and members who were in the process of staging a peaceful demonstration. This week the regime’s security forces arrested three journalists, social media activists and six pro-democracy bloggers (founders of a group known as Zone Nine). Yesterday, Addis Ababa’s killing machine that has zero tolerance for dissent struck again, killing Oromo students and innocent civilians who protested Addis Ababa’s new Master Plan that enlarges the area of the city by evicting poor Oromo peasants from their ancestral land and annexing surrounding towns against the will of the Oromo people.

On April 30, 2014 armed security forces opened fire on Oromo students who were waging a peaceful protest in the town of Ambo, Western Oromia. According to CNN iReport and eye witness testimonies, the TPLF security forces shot and killed more than 30 people including 8 students, and wounded unspecified amount of protesters.

Ginbot 7, Movement for Justice, Freedom and Democracy condemns the killing of peaceful demonstrators in its strongest terms and holds the Ethiopian regime fully accountable for its indiscriminate killing of innocent civilians, and for all political and social unrests that unfold with the killing. Ginbot 7 strongly believes that regardless of their ethnic and religious background, all citizens of Ethiopia have the right to freely express their ideas and wage peaceful demonstrations. Ginbot 7 urges the TPLF regime to immediately and unconditionally alienate itself from the “Gun solves everything” attitude and understand or comprehend that it’s about time to be civil.