
በወያኔ ዘመን ኢትዮጵያ ዉስጥ በክርስቲያን ተቋሞችና በክርስቲያኖች ላይ የሚደርሰዉ ግፍና መከራ እየጨመረ መምጣቱን አባቶቹ ተራ በተራ የተናገሩ ሲሆን ፓትሪያሪኩም አባቶች የተናገሩትን በመደገፍ እውነት ነው ይህ ሁሉ መከራና ጫና አለብን በማለት በሊቀ ጳጳሳቱ የተነገረውን ሀሳብ ደግፈዋል። ከመላው አለም የተሰባሰቡ በሺዎች የሚቆጠሩ የሀይማኖቱ መሪዎች በተገኙበት ስብሰባ ላይ የተገኙት የመንግስት ባለስልጣናት የኢትዮጵያን የሀይማኖት ታሪክ አሳንሰዉና አጣጥለዉ ሲያቅርቡ ያዳመጡት አባቶች በቁጣ በመነሳት ለወያኔ አገዛዝ ባለስልጣናት ተገቢዉን ምላሽ ሰጥተዋል።
የኢትዮጵያን ህዝብ መሬት ነጥቃችሁ፣ ህዝቡንም መሬቱንም የመንግስት ያደረጋችሁት እናንተ ናችሁ፣ ኢትዮጵያዊው ሀብትና ንብረት እንዳይኖረው ያደረጋችሁትም እናንተዉ ናችሁ። የኢትዮጵያን ህዝብ ከዚህ ቀደም የነበሩት መንግስታት ካደረሱበት የበለጠ መከራና ስቃይ ያየዉ በዚህ መንግስት ግዜ ነዉ በማለት አባቶቹ የወያኔን ባለስልጣናት ግራ በጋባና ባስደነገጠ መልኩ ትችትና ወቀሳ አቅርበዋል። ከስብሰባዉ ተካፋዮች አንዱ የሆኑት ብጹዕ አቡነ ቄርሎስ “በአጼዎቹ ዘመን አገራችን ታሪኳ የተከበረ ነበር፤ እናንተም ይህችን አገር ስትረከቡ እስከ ታሪኩዋ ነው . . . ታሪኩዋን አላጠፋችሁም ወይ?” ብለዉ ሲጠይቁ አዳራሹ ዉስጥ የነበረዉ ሰዉ ሁሉ አድናቆቱን በጭብጨባ ገልጾላቸዋል። በዕለቱ ስብሰባ ላይ የተሳተፉት አብዛኛዎቹ የሀይማኖት አባቶች የቤተክስርቲያኗን ታሪክ አዛብታችሁዋል፣ ቤተክርስቲያኑዋንም ታሪኩዋን አጥፍታችሁዋል በማለት ባለስልጣናቱን ወጥረው መያዛቸው ታውቋል። በስብሰባዉ ላይ የሰሜን ወሎ አገረ ስብከት ሊቀጳጳስ ብጹዕ አቡነ ቄርሊዮስ፣ የምእራብ ወለጋ አገረ ስብከት ሊቀጳጳስ ብጹዕ አቡነ ሄኖክ፣ የጋሞ ጎፋ አገረ ስብከት ሊቀጳጳስ ብጹዕ አቡነ ኤሊያስ፣ የምስራቅ ጎጃም ሊቀ ጳጳስ ብጹ አቡነ ማርቆስና የደቡብ ጎንደር ሊቀጳጳስ ብጹዕ አቡነ እንድሪያስ ተገኝተዋል።
No comments:
Post a Comment