ኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች በሃይማኖት ነፃነትና መብታችን ላይ የተፈፀሙ ጥሰቶች እና ተያያዥ በደሎችን በመቃወም በመስጂዶች ስናካሂድ የቆየነውን የተቃውሞ ትዕይንት፣ “ጥያቄዎቻችንን በሰከነ አዕምሮ ለማጤን ይችል ዘንድ ለመንግሥት ፋታ እንስጠው” በሚል ከአሚራችን ድምፃችን ይሰማ በተላለፈው ትዕዛዝ መሠረት ጋብ ማድረጋችን ይታወቃል፡፡ ይህ የአሚራችን ትዕዛዝ የተላለፈው በዒድ አል ፊጥር ዋዜማ ነበር፡፡ ትዕዛዙ ከተላለፈበት ጊዜ አንስቶ ህዝበ ሙስሊሙ በየትኛውም የአገሪቱ ክፍል አንድም መስጂዶችን ማዕከል ያደረገ የተቃውሞ ትዕይንት አላካሄደም፡፡ በዚህም፣ በየትኛውም የአገሪቱ ጫፍ ያለው ሙስሊም ማኅበረሰብ ምን ያህል ለአሚሩ ትዕዛዝ ታዛዥ እንደሆነና፣ ባነሳቸው ጥያቄዎችና በሰላማዊ ትግሉ ዙርያ ምን ያህል በጠንካራ የአንድነት ገመድ እንደተሳሰረ በገሃድ አሳይቷል፡፡ መንግሥት ቢገባው፣ ይህ በራሱ ትልቅ መልዕክት ነበር፡፡
በአንጻሩ መንግሥት በዒድ አል ፊጥር ዋዜማ ድምፃችን ይሰማ በይፋ የእፎይታ ጊዜ ማወጁን እያወቀ፣ በዕለተ ዒድ በተለይ በአዲስ አበባ እንኳንስ አገር የሚያሥተዳድር መንግሥት ይቅርና ተራ የጫካ ሽፍታ የማይፈጽመውን አስነዋሪ ድርጊት ፈፀመ፡፡ የዒድ ሰላቱን አጠናቆ የሚመለሰውን ሰላማዊ ህዝብ በተለያዩ አቅጣጫዎች በተሰማሩና በየቅያሱ አድፍጠው፣ እንዲሁም በመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ቅጥረ ግቢ መሽገው በሚጠባበቁ የፌደራልና ‹የአዲስ አበባ› ፖሊሶች ከፊትና ከኋላ እያስቆረጠ ህፃን፣ አዋቂ፣ አዛውንት፣ ወንድ፣ ሴት ሳይል በጅምላ በፖሊስ ቆመጥና በዱላ አስቀጠቀጠ፡፡ ሐሙስ ነሐሤ 2 ቀን 2005 በዕለተ ዒድ በአዲስ አበባ ነዋሪ ሙስሊሞች ላይ የተፈፀመው ጅምላ ቅጥቀጣ፣ ከጥቃት መፈፀሚያ መሣሪያው አኳያ ካልሆነ በስተቀር፣ በባህሪው የካቲት 12 ቀን 1929 የፋሺስት ኢጣሊያ ወታደሮች በአዲስ አበባ ከተማ ህዝብ ላይ፣ እንዲሁም ደርግ በሐውዜን እና በመርሳ ነዋሪዎች ላይ ከፈፀመው ጅምላ ጥቃት የተለየ አልነበረም፡፡ …
ኢሕአዴግ መራሹ መንግሥት በአዲስ አበባ ሙስሊሞች ላይ እንዲፈፀም ያደረገው ይህ አስነዋሪ የጅምላ ቅጥቀጣ በተጎጂዎችና በቤተሰቦቻቸው፣ በቤተ ዘመዶቻቸውና የተጎጂዎችን ጉዳት ዓይተው በመሰከሩ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ዘንድ መቼም የሚረሳ አይደለም፡፡ … መንግሥት በህዝብ ላይ ጅምላ ቅጥቀጣ ማካሄድ በምንም መለኪያ ተቀባይነት ሊያገኝ የማይችል እጅግ አስነዋሪ ድርጊት መሆኑን ቢያውቅም፣ ድርጊቱን ለማስተባበልም ሆነ የጅምላ ጥቃቱ ተጎጂ የሆነውን ህዝበ ሙስሊም ይቅርታ ለመጠየቅ አልደፈረም፡፡ ኢህአዴግ ይህ መንግሥታዊ ውንብድና በአንድ ወይም በሌላ መልኩ ዋጋ አያስከፍልም ብሎ የሚያስብ ከሆነ፣ እጅግ በጣም ተሳስቷል፡፡
አሚራችን ድምፃችን ይሰማ የመንግሥት ኃይሎች በዕለተ ዒድ በሰላማዊው የአዲስ አበባ ነዋሪ ሙስሊም ላይ በፈፀሙት አስነዋሪና አሳዛኝ ጅምላ የኃይል ጥቃት እርምጃ ተገፋፍቶ በዒዱ ዋዜማ ይፋ ያደረገውን የእፎይታ ጊዜ ውሳኔ አላጠፈም፡፡ ኢሕአዴግ ይህንን የድምፃችን ይሰማ በውሳኔ የመጽናት እርምጃ በምን መልኩ እንደተረዳው በእርግጠኝነት ማወቅ አይቻልም፡፡ ቀደም ሲል እንደተጠቀሰው ግን በመላ አገሪቱ ያለው ሙስሊም ማኅበረሰብ የአሚሩን ትዕዛዝ በማክበር ላለፉት ሁለት ወራት በመስጂዶች አንዳችም የተቃውሞ ድምጽ አላሰማም፡፡ ነገር ግን፣ በመላው አገሪቱ የሚገኘው ህዝበ ሙስሊም ተቃውሞውን ጋብ ከማድረጉ ጋር፣ ይህ የእፎይታ ጊዜ ‹‹ጥያቄያችንን በጥሞና ያጤነው ዘንድ ለመንግሥት የተሰጠ ፋታ ነው›› የሚለውን ሐሳብ በዕዝነ ልቡናው ቋጥሮ የመንግሥትን አዎንታዊ እርምጃዎች በትዕግሥት እየጠበቀ መሆኑ ፈጽሞ መዘንጋት የለበትም፡፡ ስለዚህም፣ የኢሕአዴግ መንግሥት የህዝበ ሙስሊሙን ከተቃውሞ የመታቀብ እርምጃ በተሳሳተ መንገድ ገምግሞ በተሳሳተ የጥፋት አቅጣጫ መጓዝን ከመቀጠል፣ በጠንካራ መሠረት ላይ ለተገነባውና ከሃይማኖታዊ እምነት ለመነጩት የህዝበ ሙስሊሙ ጥያቄዎች አዎንታዊ ምላሽ ቢሰጥ መልካም ነው፡፡
የመንግሥት በ“ምን ታመጣላችሁ” ዕብሪት መታበይ፣ በተለያዩ የመንግሥት መዋቅሮችና ተቋማት ላሉ “አስፈፃሚ” እና “ኃላፊ” ተብዬዎች የልብ ልብ እየሰጠ በሙስሊም ኢትዮጵያውያን ላይ የሚፈፀሙ የመብት ረገጣዎች ዕለት በዕለት በዓይነትና በመልክ እየበረከቱ ነው፡፡ እነዚህ መረን እየለቀቁ ያሉ ሁኔታዎች የህዝበ ሙስሊሙን ለዜግነት መብቱና ለሃይማኖት ነፃነቱ የመታገል መንፈስ ይበልጥ ያደነድኑታል እንጂ ፈጽሞ አያዳክሙትም፡፡ ይህ ሁኔታ በዚሁ ከቀጠለ በሃይማኖት ነፃነትና መብቶቹ ላይ ተደራራቢ ጥሰቶች እየተፈፀሙበት ያለው ህዝበ ሙስሊም በእምነቱ ምክንያት የሚፈፀሙበትን ገደብ ያጡ ጥሰቶችና ኢ ፍትኅዊ እርምጃዎች ለማስቆም ሰላማዊ ትግሉን ይበልጥ አጠናክሮ ከመቀጠል ውጪ አማራጭ እንደማይኖረው ሊታወቅ ይገባል፡፡ በአሚራችን ድምፃችን ይሰማ ተደጋግሞ እንደተገለፀው፣ መንግሥት ህዝበ ሙስሊሙ የሰጠውን የእፎይታ ጊዜ ከፍርኃት (ድብደባን፣ እሥርን አልያም ሞትን ከመፍራት) የመነጨ አድርጎ ከወሰደው በጣም ትልቅ ስህተት ነው የሚሆነው፡፡
{{{… ከዚህ ቀጥዬ አነጋገሬን የወል ከማድረግ በመቆጠብ የግል አቋሜን እናገራለሁ፡፡ አቋሜን የምትጋሩ ወንድምና እህቶች ይህን ጽሑፍ Like በማድረግ አልያም በሰሌዳችሁ ላይ Share በማድረግ የጋራ ጥያቄዎቻችን ከፖለቲካዊ ሸፍጥ የፀዳ ተገቢ ምላሽ ያገኙ ዘንድ እስከመጨረሻው በጽናት ለመታገል ያላችሁን ቁርጠኝነት እንድትገልፁ ለጋራ ሃይማኖታዊ ነፃነትና መብታችን መከበር ድምፃችንን እና ድምፃቸውን በማሰማታቸው ለህልፈት፣ ለእሥር፣ ለድብደባ እና ለአካላዊ ጉዳት በተዳረጉ ሙስሊም ወንድሞቻችን እና እህቶቻችን ስም እጠይቃችኋለሁ፡፡…}}}
ላነሳኋቸው ከሃይማኖታዊ እምነቴ የመነጩ ጥያቄዎችና በአጠቃላይም ለዜግነት መብቶቼ መከበር ከሙስሊም ወገኖቼ ጋር በጋራ በማደርገው ትግል ሂደት በማንኛውም ጊዜ በፖሊስ ቆመጥ ልደበደብ፣ ለእሥር አልያም ለሞት ልዳረግ እንደምችል አውቀዋለሁ፡፡ ይህ ባለፉት ሁለት ዓመታት አያሌ ወንድሞቼ እና እህቶቼ ያለፉበት መንገድ ነው፡፡ በአሳሳ፣ በገርባና በኮፈሌ በርካታ ወንድሞቼ ይህንን ጥያቄ በማስተጋባታቸው ሳቢያ በግፈኞች እጅ ተገድለው ሰማዕታት ሁነዋል፡፡ በዚህች ቅፅበት በብዙ መቶዎች የሚቆጠሩ ወንድሞቼ ስለመብቴና ስለመብታቸው መከበር ድምፃቸውን በማሰማታቸው ብቻ ወህኒ ተዘግቶባቸው የጥቅምት ብርድ እንደሚፈደፍዳቸው አውቃለሁ፡፡ የአጋጣሚ ጉዳይ ሁኖ እንጂ እኔ ከእነርሱ የተለየሁ ሙስሊም አይደለሁም፡፡ እነርሱ የጮሁትን ጩኸት እኔም ጮኼዋለሁ፡፡ ጩኸቴ ሰሚ እስኪያገኝ ድረስም ገና እጮኻለሁ! … ሞት፣ እሥርና ድብደባን ፈርቼ ከቶ እንደምን ነው ወንድሞቼ ከተሰዉለት፣ ከታሠሩለት እና ከተደበደቡለት ዓላማ የምሸሸው?! … መንግሥት ሙስሊሙ ማኅበረሰብ ፈርቶ የተቃውሞ እንቅስቃሴውን ያቆማል ብሎ ከማሰብ ይልቅ፣ በዚህ የእፎይታ ጊዜ እኔን ጨምሮ መላው ህዝበ ሙስሊም በጋራ ላነሳናቸው ከእምነታችን የመነጩ የሃይማኖት ነፃነትና የመብት ጥያቄዎች ተገቢና ፍትኃዊ ምላሽ ቢሰጥ ይበጀዋል፡፡ … ኢትዮጵያዊ ነኝ፡፡ ኢትዮጵያዊ ሙስሊም! በሃይማኖታዊ እምነቴ ምክንያት እንደ ሁለተኛ ዜጋ መታየትን አሜን ብዬ ለመቀበል በፍፁም አ-ል-ፈ-ቅ-ድ-ም!!!
ለሙስሊም ሰማዕታት ወንድሞቼ አላህ ጀነትን ይመንዳቸው፡፡ በእሥር ላይ ለሚገኙ ወንድሞችና እህቶቼ ፈረጃውን ያቅርብላቸው፤ በግፈኞች በትር ለተደበደቡ ወንድምና እህቶቼ ደግሞ የላቀ ብርታትና ፅናትን ይስጣቸው፡፡ ኢና ሊላሂ ወኢና ኢለይሂ ራጂዑን፡፡ [እኛ የአላህ ነን፤ እኛም ወደ እርሱ ተመላሾች ነን፡፡]
ድልም ከአላህ እንጂ ከሌላ አይደለም፡፡ አላሁ አክበር!!!
No comments:
Post a Comment