Saturday, October 12, 2013

ዘረኛዉ የወያኔ አገዛዝ የዩኒቨርስቲ ተማሪዎች አክራሪነትና ሽብረተኝነት ላይ ስልጠና እንዲወስዱ እያስገደደ ነዉ


እሱ እራሱ ሽብርተኛ የሆነዉ የወያኔ አገዛዝ ከአንደኛ ደረጃ ጀምሮ ባሉ የትምህርት ተቋማት ስለ አክራሪነት፤ ሽብርተኝነትና ጸረ ሰላም እያለ ስለሚጠራቸዉ ኃይሎች መስጠት የጀመረዉን ስልጠና ለዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችም ለመስጠት ማቀዱ ተሰማ። የኢትዮጵያ ትልቁ ችግር ዘረኝነት፤ ሙሰኝነትና የሰብዓዊ መብቶች መደፍጠጥ መሆኑን በዉል ለሚረዳና የእነዚህ ሁሉ ችግሮች ምንጭ ደግሞ ወያኔ መሆኑን ለተገነዘበ ህዝብ ወያኔ አክራሪነትና ሽብርተኝነት በሚል ስልጠና መስጠት መጀመሩ ህዝቡ ልቡ እንዲሸፍት ከማድረግ ዉጭ ምንም ዉጤት የማይኖረዉ ከንቱ ድካም መሆኑን አንዳንድ የወያኔ አባላትን ጨምሮ ብዙዎች ይስማሙበታል። በተለይ እንዲህ አይነት ስልጠና ለህጻናት ጭምር መሰጠቱ ብዙዎችን አስቆጥቷል። ለምሳሌ ከሁለት ሳምንት በፊት በክልል ለሚገኙ የሲቪል ሰርቪስ ሰራተኞችና መምህራን ስልጠናው በተሰጠበት ወቅት፣ በርካታ ተሳታፊዎች እድሜያቸው ከ15 አመታት በታች የሆኑ ተማሪዎች ስልጠናውን እንዳይወስዱ ጠይቀው ነበር።


የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የቴክኖሎጂ ፋኩልቲ ተማሪዎች ባለፈው አርብ እና ቅዳሜ ለአዲሱ የትምህርት ዘመን ለመመዝገብ ወደ ግቢ በገቡበት ሰአት፣ ምዝገባ ቆሞ ተማሪዎች ስድስት ኪሎ ወደሚገኘው የስብሰባ ማእከል እንዲያቀኑ ከታዘዙ በኋላ በአዉቶቡሶች እየተጫኑ ወደ ስልጠና ቦታ ተወስደዉ ያለፍላጎታቸዉ ቀኑን ሙሉ ስልጠናዉን ሲከታተሉ ዉለዋል። በስልጠናዉ ወቅት የወያኔ ካድሬዎች ለአገዛዙ አደጋ ይፈጥራሉ ብለዉ ያመኑባቸዉን እንደ ግንቦት7፣ ኦነግና ኦብነግ የመሳሰሉትን ድርጅቶች በጸረ ሰላምነትና በአሸባሪነት እንደምሳሌ ተጠቅመዉባቸዋል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ በኦሮሚያ ክልል ከአክራሪነት ጋር በተያያዘ ለሚሰጠው ስልጠና የተለያዩ መስሪያ ቤቶች ለ10 ቀናት ተዘግተዋል። በከፍተኛ የአመራር ደረጃ የሚገኙ የኦህዴድ ባለስልጣናት ለ10 ቀናት በአዳማ ከተማ በአክራሪነት እና ሽብርተኝነት ዙሪያ ስልጠና ሲሰጣቸው ከቆየ በሁዋላ፣ አሁን ደግሞ ስልጠናው ወደ ታች አመራር አባላት በመውረዱ በተለያዩ መስሪያ ቤቶች የሚገኙ ሰራተኞች ለ10 ቀናት ያክል ጽህፈት ቤቶቻቸውን ዘግተው ስልጠናውን እየወሰዱ ነው።

አገልግሎት ፈላጊዉ ህዝብ ጉዳዩን ለማስፈጽም ወደ ተለያዩ መስሪያ ቤቶች ሲሄድ ባለስልጣናቱ ስልጠና ላይ ናቸው የሚል መልስ እየተሰጠ ነው። መንግስት በዚህ ስልጠና ምን ለማግኘት እንዳሰበ በግልጽ ባይታወቀም ስልጠናው ወደ ወረዳዎች ሁሉ ይዘልቃል ተብሎአል። እስካሁን ድረስ በስብብሰባው ላይ የሚቀርቡት አስተያየቶች እንደሚያመለክቱት አብዛኛው ተሰብሳቢ በኢትዮጵያ ውስጥ አክራሪነት አለ ብሎ አያስብም። ይህ ደግሞ ወያኔን ክፉኛ እንዳስደነገጠዉ ለማወቅ ተችላል።

No comments:

Post a Comment