Sunday, October 6, 2013

በምስራቅ ጎጃም ስለተቃጠሉ ስምንት አብያተ ክርስቲያናት መንግስት ባስቸኳይ ማብራሪያ እንዲሠጥ እንጠይቃለን!!!

ከሰማያዊ ፓርቲ የተሰጠ መግለጫ

መንግስት በሚያስተዳድረው ሐገር ውስጥ የሚኖሩ ዜጎችን፣ ተቋማትን፣ የሀገር ሉዓላዊነትን፣ ታሪክን፣ ባህልን፣ የእምነት ነፃነትንና ደህንነትን ማስጠበቅ ተቀዳሚ ተግባሩ ነው፡፡ ይሁን እንጂ ምክንያቱ ባልታወቀ ሁኔታ በምስራቅ ጎጃም በአዋበልና አነደድ ወረዳ የሚገኙ ስምንት አብያተ ክርስትያናት ከሚያዚያ እስከ ነሐሴ 2005 ዓ.ም ድረስ ባለው ጊዜ ብቻ በእሳት ተቃጥለው በቤተክርስቲያናቱ ውስጥ የሚገኙ ነዋየ ቅድሳት፣ ልዩ ልዩ አልባሳት፣ ብዙ መጽሐፍትና ንብረት ወድሟል፡፡
እጅግ የሚያሣዝነው የአካባቢው ነዋሪዎች በመንግስት በኩል ምክንያቱ ታውቆ አስፈላጊው እርምጃ እንዲወሠድ በተደጋጋሚ ቢጠይቁም ሰሚ ጆሮ አላገኙም፡፡ ጉዳዩንም የኢትዮጵያ ሕዝብ እንዲያውቀው በክልሉ ቴሌቪዥን በዜና መልክ እንዲገለፅ ያደረጉት ጥረት አልተሳካም፡፡ በአንድ አካባቢ በተለያየ ጊዜ በተደጋጋሚ በቤተክርስትያን ላይ የማውደም ተግባር ስምንት ጊዜ ሲፈፀም በሀገር ውስጥ መገናኛ ብዙሀን አንድም ቀን አለመገለፁና በመንግስት በኩል መፍትሔ አለመስጠቱ ፓርቲያችንን ከልብ አሳስቦታል፡፡ በመሆኑም እነዚህ ከታች የተዘረዘሩት አብያተ ክርስቲያናት፡-

1. አንጋጫ ኪ/ምህረት 2. ዳገት ሚካኤል 3. የደርበን ሚካኤል
4. ዋሻ መድሀኒዓለም 5. መንክር ማሪያም 6. ቀዝቀዝ ገብርኤል
7. ደማም እየሱስ 8. ምስለ ዋሻ ጊዮርጊስ

አንዳንዶቹ ሙሉ በሙሉ በቃጠሎ የወደሙ ሲሆን የተወሰኑት በአካባቢው ሕብረተሰብ ጥረት በከፊል ተቃጥለው የተወሰነ ንብረት ሊተርፍ ችሏል፡፡ ፓርቲያችን በህግ ተመዝግቦ ህጋዊ እንቅስቃሴ ሲያደርግ ተወዳደሮ የመንግስት
ሥልጣን ከመያዝ በተጨማሪ በተለያየ ጊዜ በሐገርና በህዝብ ላይ የሚደርሱ ችግሮችን መከታተልና በሚመለከተው አካል መፍትሄ እንዲያገኙ ጥረት ማደረግ ስለሆነ በመንግስት በኩል ጉዳዩ ትኩረት ተሰጥቶት የቃጠሎው ምክንያት ተጣርቶ ድርጊቱን የፈፀመው አካል በህግ ተጠያቂ እንዲሆንና ይህም ለኢትዮጵያ ህዝብ እንዲገለፅ እያሳሰብን እንዲህ ዓይነቱ በሕዝብ አመኔታ የሚጣልባቸው ተቋማትን የማውደም ተግባር ወደፊትም እንዳይደገም በመንግስት በኩል አስፈላጊው ጥበቃ እንዲደረግ በአፅንኦት እንጠይቃለን፡፡

መስከረም 26 ቀን 2006 ዓ.ም
አዲስ አበባ



No comments:

Post a Comment