የእለቱን ስብሰባ የመሩት የንቅናቁዉ የህዝብ ግኑኝነት ዘርፍ ሃለፊ አቶ ኤፍሬም ማዴቦ ስብሰባዉን በንግግር ሲከፍቱ ባሰሙት ንግግር ግንቦት 7 ብዙ ግዜ ከተገንጣዮች ጋር ይደራደራል ተብሎ በተደጋጋሚ የሚነሳዉን ክስ አስመልክተዉ ሲናገሩ ከተገንጣይ ኃይሎች ጋር እንመክራለን እንደራደራለን፤ ለምን ቢባል እነሱም እንደማናችንም ኢትዮጵያዉያን ናቸዉ ብለን እናምናለን፤ ደግሞም ትናንት በጡንቻችን ተማምነን በኤርትራ ጉዳይ ላይ የሰራነዉን ስህተት መድገም አንፈልግም። የምናወራዉ ስለ አንድነታችን ከሆነ፤ የምናዉራዉ ስለሁሉን አቀፍ ዲሞክራሲያዊት ኢትዮጵያ ከሆነ፤ የምናወራዉ ስለዘላቂ የአገራችን ሰላም ከሆነ መደራደርና መወያየት ያለብን ከወዳጆቻችን ጋር ሳይሆን የአገራችንን አንድነትና ሰላም አደጋ ላይ ጥለዋል ከሚባሉ ኃይሎች ጋር ነዉ እንጂ ከወዳጅ ጋርማ አብሮ መምከርና መስራት ነዉ እንጂ ድርድር አያስፈልግም ብለዋል።
በዕለቱ ስብሰባ ላይ ሰፋ ያለ መረጃ ለስብሰባዉ ተካፋዮች ያቀረቡት አቶ አንዳርጋቸዉ ጽጌ ሲሆኑ እሳቸዉም በበኩላቸዉ ወያኔን ለማስወገድ የሚደረገዉ ትግል በአሁኑ የአገራችንና የአካባቢያችን ተጨባጭ ሁኔታ መሰረት የግድ ከኤርትራ መንግስት ጋር አብሮ መስራትንና ትብብር መፍጠርን የሚጠይቅ ጉዳይ ነዉ ብለዋል። ግንቦት ሰባትና ኤርትራ ዉስጥ የሚገኙ የተለያዩ ለኢትዮጵያ ህዝብ ነጻነት የሚታገሉ ኃይሎች መስክ ላይ የሚያደርጉትን የትግል ትብብር በምስል አስደግፈዉ የተናገሩት አቶ አንዳርጋቸዉ ጽጌ መለስ ዜናዊ ትግራይ ዉስጥ አጥፍቼዋለሁ ብሎ ይፎክር የነበረዉ የኢትዮጵያዊነት መንፈስ አለመጥፋቱንና ጭራሽ እያበበ መሆኑን ተናግረዋል። ኤርትራ ዉስጥ ካሉ ህዝባዊ ኃይሎች ጋር በተለይ ከትግራይ ህዝብ ዲሞክራሲያዊ ንቅናቄ ጋር እየተደረገ ያለዉ የመስክ ላይ ትብብር በቅርብ ግዜ ዉስጥ ከወያኔ ጋር የሚደረገዉን ትንንቅ ወደ ሌላ ምዕራፍ ይወስዳዋል ብለዉ እንደሚያምኑ ተናግረዋል። ወያኔ አሁን ድረስ ተዝናንቶ የሚገዛን በራሱ ጥንካሬ ሳይሆን በኛ በራሳችን ድክመት ነዉ ያሉት አቶ አንዳርጋቸዉ ጽጌ አዉሮፓና አሜሪካ ዉስጥ የሚገኘዉ ኢትዮጵያዊ እርስ በርስ መናቆሩን ትቶ መሳሪያ ካነሳዉ ኃይል ትምህርት በመቅሰም ህብረት ፈጥሮ የወያኔን እድሜ እንዲያሳጥር ጠይቀዋል።
ለስብሰባዉ ተካፋዮች የግንቦት ሰባትን አንኳር አላማና ግብ ባጭሩ ያሰቀመጡት ዶ/ር ብርሀኑ ነጋ የግንቦት ሰባት ብቸኛ አላማ ወያኔን ማስወገድና አገሪቱ ወደ ትክክለኛ ዲሞክራሲያዊ ስርዐት ሽግግር እንድታደርግ መርዳት ነዉ ካሉ በኋላ ንቅናቁዉ ይህንን አላማዉን ከግብ ለማድረስ የሚረዳ ድፕሎማሲያዊ ጥረቶችን ያደርጋል እንጂ በፕሮግራም ደረጃ የሚያራምደዉ የዉጭ ግኑኝነት ፖሊሲ የለዉም ብለዋል። ከዚህ በተጨማሪ ዶ/ር ብርሀኑ ግንቦት 7 ከዚህ ቀደምም፤ አሁንም ሆነ ወደፊት በኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅሞች ላይ በምንም መልኩ አይደራደርም ለመደራደርም ሙከራ አያደርግም ብለዋል። የአሰብን ወደብ ለመመለስ ትታገላላችሁ ወይ ተብሎ ለተጠየቁት ጥያቄ ዶ/ር ብርሀኑ ሲመልሱ ግንቦት ሰባት የተቋቋመበት ዋና አላማ ኢትዮጵያ ዉስጥ ወያኔ ተደምስሶ የፍትህና የዲሞክራሲ ስርዐት እንዲመሰረት ማድረግ ነዉና ይህንን አላማችንን ተግባራዊ ለማድረግ የማንፈነቅለዉ ድንጋይ አይኖርም ካሉ በኋላ ይንን የተነሳንለትን አላማ የሚያለሰልሱና ክንዳችንን ወደ ተለያዩ አቅጣጫዎች እንድንሰነዝር የሚያደርጉንን ሌላ የጎን ስራዎች አቅሙ ስለሌለንና ትኩረታችንንም ስለሚያላሉት አንሰራምም አንሞክርምም ብለዋል።
በመጨረሻም አዳራራሹ ዉስጥ የተገኘዉ ህዝብ እንዴት እንርዳችሁ ብሎ የጠየቀዉን ጥያቄ ሲመልሱ ግንቦት ሰባትንና ህዝባዊ ኃይሉን መርዳት የሚፈልግ ማንኛዉም ኢትዮጵያዊ የሁለቱን ድርጅቶች ድረገጽ በመጎብኘት መረጃ ማግኘት ይችላል ካሉ በኋላ ግንቦት ሰባት የተቋቋመበትን ዋነኛ አላማ ማለትም ወያኔን የማስወገዱን ተግባራዊ እንቅስቃሴ ሲጀምር ያኔ ከህዝብ ጋር እንደሚመክርና እርዳታም እንደሚጠይቅ ተናግረዋል።
No comments:
Post a Comment