የፓርተው የአምስት አመት ዕቅድና የስትራቴጂ መፅሀፍ የምከተለውን ይላል፡-
----------------------
በብሄርተኝነት ዙርያ ያለ የተሳሳተ ግንዛቤና እንደምታዎቹ
ኢትዮጵያ የብዙ ብሔር ብሔረሰቦች አገር እንደመሆንዋ የብሔር ብሔረሰቦች መብት መከበር በአገራችን ፖለቲካ ትልቅ ስፍራ እንደያዘ የሚኖር ጉዳይ ነው፡፡ የብሄር ብሄረ ሰብ መብት መከበር በቋንቋ የመናገር መብት ብቻ አይደለም' በፖለቲካ የመወከልና የመደመጥ፤ በኢኮኖሚና በማሕበራዊ ዘርፍ አድልዎን የማጥፋትና ፍትሕንና እኩልነትን የማንገስ ጉዳይ ነው፡፡ በመሆኑም ይህ ስስ ጉዳይ በሚገባ ሊያዝ ይገባዋል፡፡
የብሄር ጉዳይ አያያዝን በሚመለከት በአገራችን ሁለት ጫፍ የረገጡ አዝማምያዎች ይታያሉ፡፡ አንዱ ጫፍ ለኢትዮጵያ አንድነት እንጨነቃለን ከሚሉ ግን የብሔር መብትን ለመቀበል ከሚቸገሩ ወገኖች የሚመጣ ሆኖ ጉዳዩን የማሳነስና የማጣጣል ብሎም የብሔር መብት ጥያቄ የሕዝብ መብት ጥያቄ መሆኑን የመካድ ዝንባሌን የሚያጠቃልል ነው፡፡ አንዳንድ ወገኖች የሕዝብና የአገራችን አንኳር ጉዳይ መሆኑን በመቀበል ፈንታ የየብሄሩ ልሂቃን የስልጣን ጥማቸውን ለማርካት ብለው የፈጠሩት ችግር አድርገው ያነብቡታል፡፡ ልሂቃኑ አይለጥጡትም ማለት አይቻልም፡፡ ሆኖም ግን የጉዳዩን ክብደትና በአገራችን ፖለቲካ ውስጥ ያለውን ስፍራ ለማሳነስ ምክንያት ሊሆን አይገባም፡፡
ሁለተኛው ጽንፍ የረገጠው አመለካከት የብሔር ብሔረ ሰብ መብትን ለማስጠበቅ እንታገላለን ከሚሉ ወገኖች የሚመጣና የብሄር መብት መከበርን ከአገር አንድነትና አብሮነት ነጥሎ የሚመለከት ዝንባሌ ነው፡፡ ከእነዚህ ወገኖች ውስጥ ጉዳዩን በማክረር ውጤቱ መገንጠል እንዲሆን የሚፈልጉ አሉ፤ በግልጽ መገንጠልን እንደ ዓላማ ያነገቡም አሉ፡፡ እነዚህ ወገኖች እኛ ያልነው ካልሆነ በማለት አንድነትን በመያዣነት ያግቱታል (ሆስቴጅ ያደርጉታል)፡፡ ሁሉም የየራሱን መብት እያጠበቀና እያከረረ ከሄደ እያንዳንዱ ብሄረሰብ ከአጠገቡ ካለው ሌላ ብሄረሰብ እየተናከሰ እንደሚኖርና ከአንድነቱ መፍረስ ጋራ ሰላምም እንደሚደፈርስ ያለመገንዘብ ችግር አለባቸው፡፡
ሁለቱም አመለካከቶች በሃሳብ ብቻ ሳይሆን ልዩነታቸው በአደረጃጀትም መልክ ይታያል፡፡ የመጀመርያው ሕብረ ብሄራዊ አደረጃጀት የያዘ ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ ብሄራዊ ወይም ክልላዊ የአደረጃጀት መልክ ያያዘ ሆኖ አንዱ ከሌላው ጋር አብሮ መስራትና መኖርን የማይቀበሉ ናቸው፡፡
በአገራችን ፖለቲካ ውስጥ በብሄር/ብሔረሰብ መብት ማስከበር ዙርያ ያለውን ልዩነት ማጥፋት አይቻል ይሆናል፡፡ ጫፍ ከረገጡት ሁለቱ አመለካከቶች ወጣ ያለና የአገር አንድነትን እና የብሔርብሄረሰቦች እኩልነትን የሚያረጋግጥ አማካይ መስተጋብር መቅረጽና አብዛኛው ሕዝብ ወደዚህ አስተሳሰብ እንዲመጣ መስራት ያስፈልጋል፡፡ በአደረጃጀትም እንደዚሁ ሕብረ ብሄራዊውና ክልላዊ አደረጃጀቶችን (ያቀናጀ) ያስተሳሰረ አንድ አገር አቀፍ መዋቅር ለመፍጠር መስራት ይገባል፡፡ አሁን ያለው ሁኔታ የኢትዮጵያ ሕዝብ ተባብሮ በአንድ ድምጽ የኢህአዴግን አገዛዝ እንዳያስወግድ እንቅፋት እየሆነና ለቀጣይነቱ ምቹ ሁኔታ እየፈጠረ ነው።
ክልላዊና አካባብያዊውን ገጽታ እንዲሁም አገራዊ ገጽታዎችን ያጣመረ አንድ አገራዊ ስብስብ ወይም ፓርቲ እንዴት ይፈጠራል? ይህንን የሚያንጸባርቅ አደረጃጀትስ ምን መልክ ይኖረዋል? የሚሉትን ጥቄዎች መመለስ አንድነት ፓርቲ እንደ አንድ ትልቅ ፖለቲካዊ ተግዳሮት ይመለከተዋል፡፡
ከላይ የተዳሰሱት ሃሳቦች የያንዳንዱን የማህበረሰብ ክፍል የልብ ትርታ የማዳመጥን አስፈላጊነት አጉልተው ያሳያሉ፡፡ እንደዚሁም በተለያዩ የኢትዮጵያ ብሄርብሄርሰቦች የአስተሳሰብ አስኳል ጋር ተቀናጅቶ እንዲሄድ የሚያደርግ ስትራቴጂ የመቀየስ አስፈላጊነትን ያሳያሉ፡፡ ስትራቴጂው የእያንዳንዱን ብሄረሰብ ልዩ ሁኔታ/ስፍራ/ችግር መሰረት ያደረገ ይዘት እንዲኖረው የተቻለውን ሁሉ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡
No comments:
Post a Comment