አዲስ አበባ ዉስጥ ከመገናኛ ወደ ቦሌ በሚወስደው ቀለበት መንገድ አካባቢ የአክሰስ ሪል ስቴት አክሲዮን ማኅበር አፓርትመንቶችን የገነባው ጋቢ ኢንቨስትመንት በመባል የሚታወቀዉ ኩባንያ የአፓርትመንቶቹ አሠሪ የሆነውን አክሰስ ሪል ስቴት ኩባንያን በ72.8 ሚሊዮን ብር ያልተከፈለ ዕዳ እንደከሰሰዉ ከአዲስ አበባ የደረስን ዜና አስረዳ::ጋቢ ኢንቨስትመንት አክሰስ ሪል ስቴት አክሲዮን ማኅበር ላይ የመሰረተዉን ክስ ያቀረበዉ ለፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ሲሆን የፌዴራሉ ፍርድ ቤቱ መዝገብ ቤት ክሱን ተቀብሎ ለስድስተኛ ፍትሐ ብሔር ምድብ ችሎት የመራዉ መሆኑን ለማወቅ ተችሏል::
ጋቢ ኢንቨስትመንት ያቀረበው ክስ እንደሚያመለክተው፣ አክሰስ ሪል ስቴት የካቲት 15 ቀን 2002 ዓ.ም. በቦሌ ክፍለ ከተማ ዉስጥ ለአፓርትመንት አገልግሎቶች የሚውሉ አምስት ብሎኮችን በ174.7 ሚሊዮን ብር ለመገንባት ሥራውን እንደተረከበ የሚታወቅ ሲሆን ይህ ዉል በተግባር ላይ እንዳለ በሚያዚያ ወር 2003 ዓ.ም የግንባታ ዋጋ ማሻሻያ ክለሳ ስምምነት በማድረጋቸው የግንባታ ዋጋው ወደ 224.13 ሚሊዮን ብር ከፍ ብሏል:: ከዚህ በተጨማሪ አክሰስ ሪል ስቴት ሌሎች ሦስት ብሎኮችን ገንብቶ እንዲያስረክበው ግንቦት 4 ቀን 2002 ዓ.ም. የ108.3 ሚሊዮን ብር ውል ከጋቢ ኢንቨስትመንት ጋር ተፈራርሟል:: ጋቢ ኢንቨስትመንትና አክሰስ ሪል ስቴት ይህንንም ስምምነት በሚያዚያ 2003 ዓ.ም. በድጋሚ የማጠናቀቂያ ዋጋ ሳይጨምር የዋጋ ክለሳ ስምምነት አድርገው፣ የግንባታ ዋጋው ወደ 136.11 ሚሊዮን ብር ከፍ እንዲል ማድረጋቸው በክሱ ላይ ተገልጿል::
በጥቅሉ ጋቢ ኢንቨስትመንት ጠቅላላ ሥራውን ለማከናወን፣ አክሰስ ሪል ስቴት ደግሞ 360.24 ሚሊዮን ብር ለመክፈል መስማማቱንና አከፋፈሉም በየወሩ 20 ሚሊዮን ብር እንዲሆን ሁለቱ ኩባንያዎች ውል መግባታቸውን የቀረበው ክስ ያስረዳል:: የጋቢ ኢንቨስትመንት ክስ እንደሚያስረዳው፣ ግንባታውን ለማካሄድ የሚያስፈልጉትን የተለያዩ ዓይነት ግብዓቶች፣ ከባድና ቀላል ማሽነሪዎች፣ እንዲሁም አስፈላጊውን የሰው ኃይል አሰማርቶ ከተከፈለው በላይ ግንባታ ቢያከናውንም፣ አክሰስ ሪል ስቴት አልፎ አልፎ የተወሰነ ክፍያ ከመክፈል ውጭ በስምምነቱ መሠረትና በክፍያ ሠርተፊኬቱ ላይ በተገለጸው መጠን አለመከፈሉን ያስረዳል::
ጋቢ ኢንቨስትመንት በአምስት የመክፈያ ሠርተፊኬቶች ከተረጋገጠው 214.8 ሚሊዮን ብር ውስጥ አክሰስ ሪል ስቴት 25.8 ሚሊዮን ብር ካልከፈለ ውሉን እንደሚያቋርጥ ማስጠንቀቂያ መስጠቱን ክሱ ያስረዳል:: በማስጠንቀቂያው መሠረት አክሰስ ሪል ስቴት በአምስቱም የክፍያ ሠርተፊኬቶች የቀረበው የክፍያ ጥያቄ ሕጋዊና ትክክለኛ መሆኑን፣ ገንዘቡ በቀሪ ዕዳነት የሚፈለግበት መሆኑን በማመን፣ ገንዘቡን ከ10.5 በመቶ ወለድ ጋር በተቻለ ፍጥነት እንደሚከፍል ቃል በመግባት ግንባታው እንዲቀጥል በመማፀን እንደጠየቀ የጋቢ ክስ ያስረዳል:: ጋቢ ኢንቨስትመንት ይህን የአክሰስ ሪል ስቴት ቃል በማመን አምስት ሚሊዮን ብር የሚያወጣ ሥራ በሁለት ተጨማሪ የክፍያ ሠርተፊኬቶች መሥራቱንና በአጠቃላይ የተሠራው የግንባታ ሥራ 220.02 ሚሊዮን ብር እንደደረሰ በክሉ ላይ አትቷል:: አክሰስ ሪል ስቴት ለጋቢ ኢንቨስትመንት በአጭር ጊዜ እከፍላለሁ ያለውን 25.8 ሚሊዮን ብር፣ እንዲሁም በሁለት የክፍያ ሠርተፊኬቶች የተጠየቀውን ገንዘብ እንዳልከፈለ የጋቢ ክስ ያስረዳል::
No comments:
Post a Comment