
የአልሽባብ ሽብርተኞች እንደሆኑ የሚነገረዉ ሁለቱ የሶማሌ ዜጎች እጃቸዉ ላይ ከፈነዳዉ ቦምብ በተጨማሪ መጠናቸው ያልተገለጸ ቦምቦችና አንድ ሽጉጥ ከሁለት ካርታ ጥይት ጋር ፣ የፈንጂ ማቆጣጠያና የአደጋ መከላከያ ጃኬቶች፣ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ማሊያና ቀበቶዎች መገኘታቸውም ተገልጿል፡፡ የአንድ ግለሰብ ሰርቪስ ቤት ተከራይተው ከነበሩት ሁለቱ የሶማሌ ዜጎች ዉስጥ አንደኛው ከ20 ቀናት በላይ የቆየ ሲሆን፣ ሌላኛው ፍንዳታው ከመድረሱ ከሁለት ሰዓታት በፊት የደረሰ መሆኑን ግብረ ኃይሉ ማረጋገጡን አስረድቷል፡፡ ከሶማሊያውያኑ ጋር ቀጥታ ግንኙነት አላቸው የተባሉ ሦስት ተጠርጣሪዎችና የቤቱ አከራይ በቁጥጥር ሥር ውለው ምርመራ እየተካሄባቸው መሆኑንም ግብረ ኃይሉ አክሎ ገልጿል፡፡
የወያኔ አገዛዝ የሶማሊያን ግዛትዘልቆ አየገባ በሚፈጽመዉ ጥቃት የተነሳ ኢትዮጵያ ለአመታት ለአልሽባብና ሌሎችም አክራሪ ኃይልች የሽብር ጥቃት የተጋለጠች መሆኗ የሚታወቅ ሲሆን በላፈዉ ወር ኬንያ ናይሮቢ ዉስጥ ለደረሰዉ የሽብር ጥቃት አልሽባብ ሀለፊነት ከወሰደ በኋላ ግን ኢትዮጵያ የሚቀጥለዉ የአልሽባብ ጥቃት ሰለባ ትሆናለች የሚል ከፍጠኛ ፍራቻ አንዳለ ብዙዎች ተናግረዋል። ይህ በእንዲህ እንዳለ ቦሌ ዉስጥ እንደዚያ አይነት ከፍተኛ የቦምብ ፍንዳታ ደርሶ ፖሊስ አደጋዉ ወደ ደረሰበት ቦታ የመጣዉ ከ30 ደቂቃ ቆይታ በኋላ መሆኑን የገለጹት የአካባበዉ ነዋሪዎች ስጋታቸዉን ገልጸዋል። እንደ ነዋሪዎቹ አባባል አደጋዉ ደረሰዉ በተወሰነ ቦታ መሆኑና ተጠርጣሪዎቹም ወዲያዉ ስለሞቱ ነዉ አንጂ እንደ ኬንያው ዌስትጌት ጥቃት ቢሆን ኖሮ ፖሊስ የሚደርሰዉ ብዙ ሊተርፍ የሚችል ሰዉ ከሞተ በኋላ ነበር በማለት ብዙ የአካባቢዉ ነዋሪዎች በፖሊስ ላይ ያላቸዉን ስጋት ገልጸዋል።
No comments:
Post a Comment