Thursday, December 19, 2013

የፍርሃት ባህልን (culture of fear) እያነገሰ ያለው የኢትዮጵያ ፖለቲካ፤ አንድ እርምጃ ወደፊት ሁለት ወደ ኋላ

(ክፍል አንድ)

ያሬድ ኃይለማርያም

ከቤልጅየም፤ ብራስልስ  

ኅዳር 27/2006 ዓ.ም.

ፍርሃት የግለሰቦች ባህሪ መገለጫ ስለሆነ በማኅበረሰብ ደረጃ የሚኖረውን ገጽታ እና ትርጓሜ ማስቀመጥ ያስቸግራል። አንዱ ሰው የሚፈራውን ነገር ሌላው ላይፈራው ስለሚችል ፍርሃት እንደ የግለሰቡ ባህሪ እና ጥንካሬ ወይም ስነ-ልቦናዊ ሁኔታ የተለያየ መልክ ይኖረዋል። ይሁንና በአንድ ማኅበረሰብ ውስጥ የሚገኙ ሰዎች የሚጋሩት ባህልና ስነ-ልቦናዊ ሁኔታ እንደመኖሩ ሁሉ የሚጋሩትም ፍርሃት ወይም ደስታ ወይም ሃዘን ወይም ድፍረት ወይም ሌሎች ባህሪያት ይኖራል። በዚህም ምክንያት አንዳንድ ሰዋዊ ባህሪያት ለአንድ ማህበረሰብ ወይም ለበርካታ ሰዎች የወል መገለጫ ተደርጎ ሲገለጽ ይስተዋላል። ‘የዚህ አካባቢ ሰዎች ጀግኖች ወይም ጸብ ፈሪዎች ወይም እሩህ ሩህዎች ወይም ጨካኞች ወይም ቂመኞች ወይም ገራገሮች ወይም ተንኮለኖች ወይም ጎጠኞች ወይም ሌላ ባህሪ ያላቸው ናቸው’ የሚል አገላለጽ የተለመደ ነው። ይህ አይነቱ አነጋገር ሳይንሳዊ መሰረት ያለው ባይሆንም በአካባቢው ላይ ጎላ ብለው በሚታዩ ሰዎች ላይ ተደጋግሞና ተዘውትረው የሚታዩ ተመሳሳይ ባህሪያት የአካባቢው ሰው ሁሉ መገለጫ ተደርገው ስለሚወሰዱ ድምዳሜው ለስህተት የተጋለጠ ሊሆን እንደሚችል ከወዲሁ ለመግለጽ እወዳለሁ። ከዚህ መንደርደሪያ በመነሳት በዚህ ጥልቅ ጥናት ባላካሄድኩበት ነገር ግን ደጋግሜ ሳብሰለስለው በቆየሁት የፍርሃት ባህል እና በኢትዮጵያ የፖለቲካ ድባብ ዙሪያ ያለኝን ምልከታ ለአንባቢያን ለማካፈልና በጉዳዩም ላይ ለመወያየት ወሰንኩ።

በአንድ ማኅበረሰብ ውስጥ የፍርሃት ድባብ እንዲሰፍን እና ከዚያም አልፎ ባህል እንዲሆን ምክንያት ከሆኑት በርካታ ነገሮች መካከል የተወሰኑትን ልጥቀስና በእኛ ማኅበረሰብ ውስጥ ያላቸውን ገጽታ በመጠኑ ለመዳሰስ እሞክራለሁ። በስነ-ልቦና ጠበብቶች ከሚጠቀሱት ዋና ዋና የፍርሃት ምንጮች መካከል፤ ነፃነትን ማጣት፣ ነገ የሚሆነውን ማወቅ አለመቻል፣ የህሊና እና የአካል ቁስልን ባስከተሉ ትላንቶች ውስጥ ማለፍ፣ የማያቋርጥ ብስጭት ወይም ንዴት፣ ድህነት በሚያስከትለው ስቃይ ውስጥ መማቀቅ፣ አጋር እና አለኝታ ማጣት፣ በሌሎች ክፉኛ መነቀፍ፣ መንጓጠጥ፣ መጠላት እና መገለል፣ በሚኖሩበት ማኅበረሰብ ዘንድ ተቀባይነትን ማጣት፣ የሞት አደጋን ማሰብ፣ ሽንፈት ወይም ስኬት አልባ ሆኖ መቆየት፣ እና ሌሎችም ይገኙበታል። ከእነኝህ መክንያቶች ውስጥ የአንዱ መከሰት አንድን ሰው ወደ ፍርሃት ውስጥ ሊከት እንደሚችል ጥናቶች ይጠቁማሉ። እነኝህ ምክንያቶች ተደራርበውና በአንድ ጊዜ በአንድ ሰው ወይም በአንድ ማኅበረሰብ አባላት ላይ ሲከሰቱና ዕልባት ሳያገኙ እረዘም ላለ ጊዜ ሲቆዩ ደግሞ አደጋቸው የከፋ ነው የሚሆነው። ከዚህም በመነሳት ወደ እኛ ማህበረሰ ስንመለስ በግላችንም ሆነ በጋራ ህይወታችን ከላይ ከተጠቀሱት የፍርሃት መንሰዔዎች መካከል ስንቶቹ በህይወታችን ውስጥ ተከስተዋል፣ ስንቶቹን በአሸናፊነት አለፍናቸዋል፣ ስንቶቹስ ዛሬም ድረስ አብረውን ይኖራሉ፤ የሚሊቱን ጥያቄዎች እያንዳንዱ ሰው እራሱን እንዲጠይቅ እየተውኩ በወል በምንጋራቸው ጥቂት የፍርሃት መንሰዔዎች ላይ ላተኩር።


የነፃነት ማጣት

ሰብአዊ መብቶች በገፍ በሚጣሱበት እና ዜጎች የሰውነት ክብራቸው ተገፎ፣ ተዋርደውና ነፃነታቸውን ተነጥቀው በሚኖሩበት አገር ሁሉ ፍርሃት ትልቁ ገዢ ኃይል ነው። በእንዲህ ያለው ማህበረሰብ ውስጥ የፍርሃት ሰለባ የሆኑት እና ነፃነት አልባ ሕይወትን የሚገፉት ተጨቋኞቹ ብቻ ሳይሆኑ ጨቋኞቹም ጭምር ናቸው። ተጨቋኖቹ በግፍ ልንገደል፣ ልንታሰር፣ የስቃይ ሰለባ ልንሆን፣ ታፍነን ልንሰወር፣ ከሃገር ልንሰደድ፣ ከሥራ ልንባረር፣ ንብረታችን ሊወረስ፣ በግዞት ከቦታ ቦታ ልንዛወር፣ ከቅያችን ልንፈናቀል፣ በሃሰት ክስ ልንወነጀል፣ ደሞዛችንን ልንነጠቅ፣ ከሥራ ደረጃችን ልንቀነስ፣ ወዘት … እያሉ አደጋዎችን እያሰቡ በሽብርና በፍርሃት ቆፈን ተይዘው ‘ጎመን በጤና’ በሚል የማፈግፈጊያ ስልት መብቶቻቸውን አሳልፈው በመስጠት የግፍ እንቆቋቸውን እየተጎነጩ መራራ ሕይወታቸውን ይመራሉ። ጨቋኞቹም ይህን በነፍጥ እና በሕግ አንበርክከው ነፃነቱን የነጠቁትና ለስቃይ የዳረጉት ሕዝብ በአንድ አይነት ተአምር በቁጣ ገንፍሎ ከተነሳ አንድም ቀን እንደማያሳድራቸው ጠንቅቀው ስለሚያውቁ እያንዳንዱን ደቂቃና ሰዓታት ልክ እንደ ተጨቋኙ በፍርሃት እና በሽብር ነው የሚያሳልፉት። ከቦታ ቦታ ሲንቀሳቀሱም፣ የእለት ሥራቸውንም ሲያከናውኑ፣ ሲተኙም ሆነ ሲዝናኑ በሠራዊትና በመሣሪያዎች ጋጋታ ታጅበው ነው። ምናልባትም ከተጨቋኞቹም በባሰ ፍርሃት ውስጥ ነው የሚኖሩት።

ዛሬ ኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን ሁኔታ በቅጡ ያጤንን እንደሆነ ገዢና ተገዢ እርስ በእርስ የሚፈራሩበት፤ መንግሥት ተቃዋሚ ፓርቲዎችን፣ ተቃዋሚዎች መንግሥትን የሚፈሩበትና አንዱ ሌላውን የማያምንበት ሁኔታ ነው የተፈጠረው። የመንግሥት ፍርሃት ከተቀናቃኝ የፖለቲካ ኃይሎች አልፎ የሲቪክ ማኅበረሰቡን፣ የሙያ ማኅበራትን፣ ነጋዴውን፣ ምሁራኑን፣ ገበሬውን፣ ወጣቱን እና ሌላውንም የኅብረተሰብ ክፍል ክፉኛ የሚፈራበትና በቁራኛ የሚከታተልበት፤ እነሱም መንግስትን እንደ ተናካሽ አውሬ የሚፈሩበት ሁኔታ ተፈጥሯል። በመንግሥትና በሕዝቡ፣ በተቃዋሚ ፓርቲዎችና በመንግሥት፣ በሕዝቡና በተቃዋሚ ፓርቲዎች መካከል ካለመተማመን የመነጨው ይህ ጥልቅ ፍርሃት በአገሪቱ የኢኮኖሚ፣ የፖለቲካ እና ማኅበራዊ እንቅስቃሴዎች ላይ ጥቁር ደመናን ጋርዷል። በገዢው ኃይል በኩል ያለውን የፍርሃት ድባብ ለመመልከት በየጊዜው መንግሥት የሚወስዳቸውን የኃይል እርምጃዎች፣ የሚያወጣቸውን የማፈኛ ሕጎች፣ እያጠናከረ የሄደውን የሥለላና የአፈና መዋቅር፣ በመገናኛ ብዙሃን የሚያሰራጫቸውን ሕግን ያልተከተሉ እና በሽብር መንፈስ የተዋጡ መግለጫና ዘገባዎችን መመልከት በቂ ነው። በተለይም የ1997ቱን ምርጫ ተከትሎ የተቀሰቀሰው የሕዝብ ቁጣ ያስደነበረው የወያኔ መንግሥት ከላይ የጠቀስኳቸውን እና አጥብቆ የሚፈራቸውን የኅብረተሰብ ክፍሎች ቀፍድዶ ለመያዝና እንቅስቃሴዎቻቸውን ለመገደብ ባወጣቸው የጸረ-ሽብር፣ የሲቪክ እና የበጎ አድራጎት ድርጅቶች መተዳደሪያ፣ የፕሬስ እና የፖለቲካ ፓርቲዎችን ምዝገባ፣ የፀረ-ሙስና እና ሌሎች አዋጆች ሥርዓቱ የአፈና  እና የመብት እረገጣ ተግባሩን ሕጋዊ ወደማድረግ ሂደት የተሸጋገረ መሆኑን ያሳያሉ። ፍጹም ሰላማዊ እና ሕጋዊ በሆነ መልኩ የመብት ጥያቄዎችን ባነሱ ዜጎች ላይ፤ አቅመ ደካሞችን እንኳን ሳይለይ ‘የፈሪ በትሩን’ ሲያሳርፍ በተደጋጋሚ ተስተውሏል።

ባለፉት ሃያ አመታት የአገዛዝ ሥርዓቱ የፈሪ በትሩን በተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ላይ አሳርፏል። ብዕርና ወረቀት በያዙ ከከፍተኛ ደረጃ ተማሪዎች እስከ አንደኛ ደረጃ ትመህርት ቤት ሕፃናት ጋር ሳይቀር በተደጋጋሚ ጊዜያት ተላትሟል። በርካቶችን ገድሏል፣ አስሮ አሰቃይቷል፣ ደብድቧል፣ ከትምህርት ገበታቸው ላይ አፈናቅሏል፣ ከአገር አሰድዷል፣ በሃሰት ወንጅሎ አስፈርዷል። በእምነት ቤቶች ውስጥ ገብቶ ከአማኞች፣ ከመንፈሳዊ አባቶች እና ይህን አለም ሸሽተው በገዳም ከከተሙ መነኮሳት ጋር ሳይቀር ተላትሟል። የኃይማኖት ተቋማት እንዲከፋፈሉና በገዢው ፓርቲ የፖለቲካ ተሿሚዎች ቁጥጥር ስር እንዲወድቁ ተደርገዋል። ምእመናን በመስጊዶችና በቤተክርስቲያን ውስጥ እያሉ በታጠቁ ኃይሎች ተገድለዋል፣ ተደብድበዋል፣ ተዋርደዋል። ቀሳውስት ጥምጥማቸውን እንዲያወልቁ እና መስቀላቸውን እንዲጥሉ ተደርጎ በማጎሪያ ካምፖች ውስጥ የማሰቃየት ተግባር ተፈጽሞቻቸውል። ኢማሞች ጺማቸው እየተጎተተ ተወስደው ተደብድበዋል፣ ታስረዋል። ይህ ሕዝብን የማዋረድ እና የማሸበር ተግባር የመነጨው እንደ እኔ እምነት የገዢው ኃይል እየተባባሰበት ከመጣው የፍርሃት እና የመሸበር ስሜት የተነሳ በራስ የመተማመን ስሜቱ እየተቦረቦረ በመሄዱ ነው። ዛሬ ሥርዓቱ የገዛ ጥላውንም የሚፈራበት፣ አባላቱ ላይ እንኳን እምነት ያጣበት ደረጃ ላይ ደርሷል። ለእዚህም አንዱ ማሳያው በነጋ በጠባ ቁጥር ማቆሚያ በሌለው የግምገማ ስብሰባ አባላቱን ሲያስጨንቅ መታየቱ እና ለዚሁ የሚያባክነው ጌዜ እና የሕዝብ ገንዘብ፣ የባለሥልጣናት ተደጋጋሚ  ሹም ሽር እና ከአገር ከድተው የሚወጡ ባለሥልጣናት እና የወያኔ አባላት ቁጥር መጨመሩ ነው።

ይህ የገዢው ኃይል የሕግን ልጓም በመበጣጠስ የፈረጠመ ክንዱን ይቀናቀኑኛል ባላቸው ግለሰቦች፣ ጋዜጠኞች፣ የፖለቲካ ኃይሎችና የሙያ ማኅበራትና አባላቶቻቸው ላይ ሁሉ ማሳረፉ ቀሪውን የኅብረተሰብ ክፍል ክፉኛ እንዲደነብርና በፍርሃት ቆፈን እንዲሸማቀቅ አድርጎታል። ዛሬ ኢትዮጵያ ውስጥ የሰብአዊ መብቶች መከበር፣ የዴሞክራሲ ጥያቄዎች እና የሕግ የበላይነት መረጋገጥ የሁሉንም የኅብረተሰብ ክፍል የዕለት ተዕለት ሕይወት የሚነካ ቢሆንም የጥቂቶች ጉዳይ ተደርጎ ተወስዷል። በእነዚህ ጉዳዮች ላይ ጥቂት የሲቪክ ማኅበራት፣ ጥቂት ጋዜጠኞች፣ የተቃዋሚ ፓርቲዎች እና በጠአት የሚቆጠሩ ግለሰቦ ብቻ ናቸው ባላቸው ውሱን ጉልበት እና አቅም ሲወያዩ፣ የምንግሥትን መጥፎ ተግባራት ሲቃወሙ፣ ለዜጎች መብት ሲሟገቱ እና ባደባባይ ሲጮሁ የሚስተዋለው።    



በድህነት አረንቋ ውስጥ ተዘፍቆ መቆየት

ሌላው እና ትልቁ የፍርሃት ምንጭ በከፋ ድህነት ውስጥ ለረዥም ጊዜ እየማቀቁ መቆየት እና ድህነቱ ባስከተለው የስቃይ ህይወት አካላዊና መንፈሳው አቅም ተሸርሽሮ ክፉኛ መጎዳት እና መዳከም ነው። ሕዝብን በድህነት ውስጥ አምቆ በማቆየት ለሰው ልጅ ከሚገባው ክብር ወርዶና ከእንስሳ ያልተሻለ ሕይወት እንዲኖር በማድረግ ቅስሙን መስበር የአምባገነኖች አንዱ የሥልጣን እድሜአቸውን ማራዘሚያ ሥልት ነው። የድህነት ክፋቱ ኪስን ብቻ ሳይሆን የሚያራቁተው ክብርንም ጭምር ነው። አንድ ሰው በመንገድ ላይ ቆሞና እራሱን ከመጽዋቾቹ ሥር ዝቅ አድርጎ ቁራሽ ምግብ ወይም ቤሳ ሲለምንና ሲማጸን በኩራትና በደስታ ስሜት ውስጥ ሆኖ አይደለም። እያፈረ እና እየተሸማቀቀ በተሸናፊነትና በዝቅተኝነት ስሜት ውስጥ ሆኖ ነው። ይህ ክስተት በሙሉ ጤንነት እና በወጣትነት ወይም በጉልምስና እድሜ ላይ ባሉ ሰዎች ውስጥ ሲሆን ደግሞ ያለው የውስጥ ሕመም እና የሕሊና ቁስል እጅግ የከፋ ነው። የድህነት ክፋቱ ያፈሩትን ቅሪት ብቻ ሳይሆን የሚያሳጣው ወይም ኑሮን ለማሸነፍ የሚያስችል አቅምን ብቻ ሳይሆን የሚሸረሽረው መንፋሳዊ ወኔንም ጭምር ነው ከላያችን ገፎ የሚወስደው። ከሰውነት ደረጃ ላይ የሚያቆመንን መንፈሳዊ ልዕልና ካጣን በኋላ ቁሳዊ ድህነቱን ብናሸንፈው እንኳን መንፈሳዊ ድህነቱ ይከተለናል። እዚህ ላይ ለማሳሰብ የምወደው ነገር ድሃ ሁሉ ፈሪ ነው ወይም በፍርሃት ቆፈን የተተበተበ ነው የሚል የተሳሳተ ግንዛቤ እንዳይወሰድ ነው። በከፋ የኢኮኖሚ ድህነት ውስጥ እየኖሩ ክብራቸውን አስጠብቀውና እና በላቀ የመንፈሳዊ ወኔያቸው እራሳቸውንና አገራቸውን አስከብረው ያለፉ ድሃ አያት ቅድመ አያቶቻችንን ማሰብ የግድ ይላል። ዛሬም የገንዘብ እጦትና ድህነት ያላላሸዋቸውና መንፈሳዊ ልዕልናቸውን አስጠብቀው በክብር የሚሞቱ ወገኖች አሉን፤ ትቂቶች ቢሆኑም።    

የዚህ ጽሁፍ ትኩረት ግን በቁሳዊውም ሆነ በመንፈሳዊ  ማንነታቸው ውስጥ ድህነትና ፍርሃት ተረባርበው ወይም ከሁለቱ በአንዱ ተጠልፈው ስብእናቸው ፈተና ውስጥ የወደቀባቸውን ሰዎች የሚመለከት ነው። በተለይም በዚህ ግለኝነት በነገሠበት እና ገንዘብ በሚመለክበት የአለም ወቅታዊ  ሁኔታ ውስጥ መናጢ ድሃ ሆኖ ለዘመናት መቆየት መዘዙ ብዙ ነው። ብዙዎች ከዚህ መቋጫው ከጠፋው የድህነት አረንቋ ለማምለጥ ስደትን አማራጭ አድርገው በተለያዩ አቅጣጫዎች አገሪቷን ለቀው ለአረብ አገራት ባርነት ተሰደዋል። ቀሪዎች ደግሞ የአገዛዝ ሥርዓቱ ሎሌ በመሆን ነፃነታቸው በቤሳ መሸቀጥን ቀጥለዋል። ለሁለቱም እድሉን ያጡ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ድሆች ደግሞ በየጎዳናው ላይ ተበትነው ዝናብ፣ ውርጭና ፀሃይ እየተፈራረቁባቸው የመጽዋቾቻቸው ደጅ ጠኞች ሆነዋል።

ከተወሰኑ አሥርት አመታት በፊት አንድ ሰው በድህነቱ ምክንያት እራሱንና ልጆቹ የትምህርት፣ የጤና አገልግሎት፣ መሰረታዊ የሆን አልባሳትና መጠለያ ጎጆ ባለቤት ለማድረግ የሚገጥመው ፈተና ቢኖርም ይህን ያህል የመረረ አልነበረም። ዜጎች በወር ከሁለት ብር አንስቶ እንደ የአቅማቸው የቀበሌ እና የኪራይ ቤቶችን ቤቶች ተከራይተው የመጠለያ ችግራቸውን ይቀርፉ ነበር። በአገሪቷ ውስጥ የነበሩ በርካታ የሕዝብ ትምህርት ቤቶች ከመመዝገቢያ ያልዘለለ አነስተኛ ገንዘብ እየተቀበሉ ተማሪዎችን በነጻ ያስተናግዱ ነበር። ብዙ ምሁራንንም አፍርተዋል። በየቀበሌው ከተደራጁ ጤና ጣቢያዎች አንስቶ በተለያዩ የመንግሥት ሆስፒታሎች ዜጎች በነፃና እጅግ ተመጣታኝ በሆነ ክፍያ ጥሩ ሕክምና የማግኘት እድል ነበራቸው። በአንድ ብር በሚገዛው አስር ትንንሽ ዳቦ ወላጆች ልጆቻቸውን አብልተው ያሳድሩ ነበር። ዛሬ አገሪቱ በልማት እየገስገሰች እንደሆነ በሚነገርበት በዚህ ወቅት ዜጎች በኑሮ ውድነትና ዋስትና ማጣት በጨለማ  ህይወት ውስጥ እየተደናበሩ ይገኛሉ።

መንግሥት በኢኮኖሚውም፣ በፖለቲካውም ሆነ በሌሎች ኃይማኖታዊና ማኅበራዊ ጉዳዮች ያሻውን ቢያደርግ  በሕዝብ በኩል መላሹ ዝምታ ሆኗል። አብዛኛው ሕዝብ ከተዘፈቀበት የድህነት አረንቋ ሳይወጣ በርካታ ነገሮች ተቀይረዋል። በመቶና በሁለት መቶ ይገዛ የነበር ጤፍ በሺዎች ሲያወጣ ምላሹ ዝምታ ሆኗል። ቲማቲም እንኳን ባቅሟ በኪሎ ከሁለት ብር ወደ ሃያ ብር ስትጠጋ አንዳንዴም ስትዘል ዝምታ፣ የቤት ኪራይ ከመቶዎች ወደ ሺዎች ሲንር ዝምታ፣ የነዳጅ ዋጋ በየጊዜው ሲያሻቅብ ዝምታ፣ የመብራት፣ የውሃ፣ የስልክ እና የኢንተርኔት አገልግሎቶች በሰአታት፣ ከዚያም ለቀናት አንዳንዴም በተወሰኑ ቦታዎች ለሳምንታት ሲጠፉ ዝምታ፣ መነኮሳት እና አድባራት ሲዘረፉና ሲዋረዱ ዝምታ፣ መስጊዶች እና ኢማሞች ሲዋክቡና ሲታሰሩ ዝምታ፣ የአገር ሽማግሌዎች፣ ፖለቲከኞች፣ ጋዜጠኞች እና የሰብአዊ መብት ተሟጋቾች ሲደበደቡ፣ ሲታሰሩና ሲሳደዱ ዝምታ፣ የንግዱ ማኅበረሰቡ ሲዋክብና ሲጉላላ ዝምታ፣ ገበሬዎች በማዳበሪያ እዳ ንብረታቸውን ሲነጠቁና ከዛም አልፎ ከትውልድ ትውልድ ያቆዩትን ይዞታቸውን እየተነጠቀ ለውጪ ቱጃሮች ሲቸበቸብ ዝምታ፣ ወንዶች ሚስቶቻቸውና ሴት ልጆቻቸው እፊታቸው ሲደፈሩና ሲጠቁ እያዩ ዝምታ፣ እናቶች ልጆቻቸውና ባሎቻቸው በየወጡበት ሲቀሩ እያዩ ዝምታ፣ በየከተማው የሚገኙ ነዋሪዎች ቤታቸ በላያቸው ላይ እንዲፈርስ እየተደረገ ከነልጆቻቸ በየሜዳው ተበትነው ይዞታቸው ለስግብግብ ባለሃብቶች ሲሰጥ ዝምታ፣ የሙያ ማኅበራት ሲጠቁ ዝምታ፣ መምህራኖች ሲዋከቡ ዝምታ፣ በብዙ ሺዎች የሚቆጠሩ ሠራተኞች ከሥራ ገበታቸው ‘በድህነት ቅነሳ እስትራቴጂ’ ስም ሲፈናቀሉና ለርሃብ ሲዳረጉ ዝምታ፣ ባለሥልጣናት የከፋ ሙስና ውስጥ ተዘፍቀው ሲንቦጫረቁ ዝምታ፣ ሕፃናት ሳይቀሩ በየአደባባዩ ግንባራቸው በጥይት እየተቦደሰ ሲረሸኑ ዝምታ፣ የአገሪቷ የትምህርት ሥርዓት ክፉኛ አቆልቁሎ ትውልድን ወደማክሰም ደረጃ ላይ ሲደርስ እየተመለከትን ዝምታ፣ መንግሥት ድህነትን ሸሽተው ከሃገር የሚሰደዱ ወጣቶችን መንገዱን ጨርቅ ያድርግላችው እያለና ገንዘብ እየቃረመ ለዘመናዊው ባርነት እያዘጋጀ ፓስፖርት ሰጥቶ ሲያሰድድ ዝምታ፣ በየጎዳናው የወደቁ  ሕፃናቶችን በጉዲፈቻ ስም መንግስት ለውጪ ዜጎች በብዙ ሺ ዶላር ሲቸበችብ እያየን ዝም፣ መንግስት የራሱን ሕገ-መንግስት እየናደ የፈቀደውን ሁሉ በዜጎች ላይ ሲፈጽም የህዝብ ምላሽ ዝምታ፣ ዝምታ፣ ዝምታ…..። ስንቱ ተጠቅሶ ይቻላል?

አንድ ሕዝብ ይህ ሁሉ ውርጅብኝ ያለፋታ ሲዥጎደጎድበት እና መገለጫ የሌልውን ግፍ እና ጭቆና በጫንቃው ላይ ሲጫንበት ውስጥ ውስጡን እያጉረመረመ፣ እያለቀሰና ልቡ እየደማ እንዴት ነህ ሲሉት ደህንነቱን ለመግለጽ ‘እግዚያብሄር/ አላህ ይመስገን’ እያለ የውሸት ሳቅ እየሳቀ እንዲኖር ያስገደደው ምንድን ነው? መንፈሱና አካሉ በቁሙ ተሸርሽረው እያለቁ ባልሞትኩም ባይነት የአያቶቹን ገድል በህሊናው እያመነዥከ በዘመኑ ለተጋረጡበት ፈተናዎች፤ በተለይም ድህነት፣ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ጭቆዎችና በገዛ አገሩ ተዋርዶ መኖርን ለመሸሽ ስደትን ወይም ልመናን ወይም ሕሊናን ቀብሮ ለሥርዓቱ አገልጋይ መሆንን ከማን ተማረ? ይህ ጥልቅ የሆነው ዝምታችን የፍርሃት? ወይስ የትእግስት? ወይስ በፍርሃትና በትእግስተኛነት መካከል ሌላ ደሴት ወይም መንጠልጠያ ስፍራ አለ? እራሳችንን እንጠይቅ!



በቀጣዩ ክፍል እስከምንገናኝ በቸር እንሰንብት!

No comments:

Post a Comment