Monday, December 16, 2013

የወያኔ 40 በ 60 እና 10 በ 90 የቤት ስራ ዕቅድ ገንዝብ መዝረፊያ መንገድ መሆኑ ተረጋገጠ

የወያኔ አገዛዝ 40 በ 60 እና 10 በ 90 ብሎ የጀመረዉ የቤት ልማት ዕቅዱ በድምሩ ከአንድ ሚሊዮን በላይ አገር ዉስጥና ዉጭ አገር የሚኖሩ ኢትዮጵያዉያንን መዝግቦ ገንዘበቸዉን ከተቀበለ በኋላ ቃል የገባዉን ልማት ለማካሄድ አለመቻሉን ከአገር ቤት የሚደርሱን ዜናዎች ጠቆሙ። በውጭ አገር ለሚገኙ ኢትዮጵያውያንና የገንዘብ አቅሙ ላላቸው የአገር ዉስጥ ዜጎች የ40 በ60 አዲስ አበባ በአነስተኛ ገቢ ለሚተዳደሩ ዜጎች ደግሞ የ10 በዘጠናና የ20 በ80 የቤት ስራ ጅምሮችን ያቀፈዉ የወያኔ የቤት ልማት ዕቅድ በችግር ላይ ችግር እያጋጠመዉ ምንም ያክል ወደ ፊት መራመድ አለመቻሉ በስፋት እየተነገረ ነዉ። በዚህ የቤት ልማት ዕቅድ አገር ዉስጥ በ10/90 850 ሺ በ 20/80 ደግሞ 350 ሺ የአዲስ አበባ ነዋሪ ተመዝግቦ እድሉን በመጠባበቅ ላይ ሲሆን ከ12 ሺ በላይ በውጭ አገር የሚኖሩ ኢትዮጵያውያም በ40 በ60 በሚባለው ውስጥ ታቅፈዉ እድላቸዉን እየተጠባበቁ ቢሆንም በመርሀግብሩ ዝግጅት የተሳተፉ የውስጥ ምንጮች እንደገለጹት የወያኔ አገዛዝ ይህን እቅድ ለማሳካት ከፍተኛ የሆነ ፈተና ገጥሞታል ።

በባዶ ሜዳ ላይ ዕቅድ ማዉጣት የለመደዉ የወያኔ አገዛዝ የቤት ልማት እቅዱን ተግባራዊ ለማድረግ ወደ 2 ሚሊዮን የሚደርሱ ቤቶች መገንባት የሚኖርበት ሲሆን ይህን ያክል ብዛት ያለዉ ቤት ለመገንባት ደግሞ ቢያንስ 30 ሺ ሄክታር ስፋት ያለው ቦታ ያስፈልጋል። ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸዉ ወገኖች አስረግጠዉ እንደሚናገሩት ደግሞ አዲስ አበባ ዉስጥ ይህንን ያክል ሰፊ መሬት ማግኘት በፍጹም አይቻልም። የማዕከላዊዉ መንግስት ለአዲስ አበባ ከተማ ሰፋ ያለ የማስተር ፕላን በማዘጋጀት በማስተር ፕላኑ ውስጥ የኦሮሚያ ልዩ ዞኖች የሚባሉትን ሱሉልታን፣ ሰንዳፋንና ገላንን በማካተት በቂ የቤት መስሪያ ቦታዎችን ለማፈላለግ እቅድ ነድፎ እየተንቀሳሰ ቢሆንም ፣ የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ግን ” ከእንግዲህ መሬት ለአዲስ አበባ መስተዳድር መሬት የምንሰጠው በመቃብራችን ላይ ነው” የሚል አቋም ወስዶ በአቋሙ እንደጸና ነዉ።

በኦሮሚያ ክልል አቋም አጣብቂኝ ውስጥ የገባው የፌደራሉ መንግስት ከተለያዩ መስሪያ ቤቶች የተውጣጡ ባለስልጣናትን በመሰብሰብ እና አንድ ኮሚቴ በማዋቀር ወደ ክልሎች ልኳቸዋል። እነዚህ ባለስልጣኖች ወደ ተለያዩ ክልሎች በመሄድ አዲስ አበባ ዉስጥ ቤት እንዲሰራላቸዉ ገንዝብ ለከፈሉ የዲያስፖራ ኢትዮጵያውያን በየክልሉ የቤት መስሪያ ቦታ እያፈላለጉ ነዉ። ክልሎች ቦታ ለመስጠት ፈቃደኛ ከሆኑ ደግሞ የወያኔ ሁለተኛዉ ስራ እንደለመደዉ ወደ ዳያስፖራ በመምጣት ቤት ለማሰራት ገንዘባቸዉን የሰጡትን የዲያስፖራዉን አባላት ከአዲስ አበባ ወጣ ብለው በክልሎች ግንባታ እንዲያካሂዱ ማግባባት ሊሆን እንደሚችል ዉስጥ አዋቂ ምንጮች በእርግጠኝነት በመናገር ላይ ናቸዉ።

መንግስትን የገጠመው ሌላው ፈተና የገንዘብ እጥረት ነው። ንግድ ባንክ ለቤቶች ግንባታ የሚሆን 12 ቢሊዮን ብር ብድር መስጠት የሚኖርበት ሲሆን፣ በቅርቡ የንግድ ባንኩ ፕሬዚዳንት ከጠ/ሚኒስትር ሀይለማርያም ደሳለኝ ጋር በተገናኙበት ወቅት ባንካቸው ማበደር የሚችለው 6 ቢሊዮን ብር ብቻ መሆኑን ገልጸውላቸዋል። አቶ ሀይለማርያምም ባንኩ ቢያንስ 10 ቢሊዮን ብር ማበደር እንዳለበት ትእዛዝ ሰጥተዋል። ባንኩም ለታዋቂዎቹ የመጠጥ አምራች ድርጅቶች ማለትም ለሀይነከንና ዲያጎ የቢራ አምራች ፋብሪካዎች ፈቅዶት የነበረውን የ3 ቢሊዮን ብር የብድር ውል በመሰረዝ፣ ድርጅቶቹ 560 ሚሊዮን ብር ብቻ እንዲበደሩ በማድረግ ቀሪውን ገንዘብ ለዚሁ ፕሮጀክት ለማዋል ተስማምቷል። ባንኩ እስካሁን 8 ቢሊዮን ብር ለማሰባሰብ የቻለ ሲሆን፣ የመንግስትን ጥያቄ ለማሙዋላት ተጨማሪ 2 ቢሊዮን ብር ከየት እንደሚያመጣ ግልጽ አልሆነም።

በሌላ በኩል ደግሞ የቤቶች መስሪያ ዋጋ መጀመሪያ ከታቀደበት መጠን እንዲከለስ ተደርጓል። በመጀመሪያ ለ3 መኝታ ቤት መስሪያ የተመደበው ገንዘብ 385 ሺ የነበረ ሲሆን በተከለሰው አዲስ ዋጋ ግን ይህ ዋጋ በእጥፍ አድጎ 779 ሺ ብር እንዲሆን ተደርጓል። ይህ ዋጋ በቅርቡ እየታየ ያለውን የዋጋ ንረት ግምት ውስጥ በማስገባት ወደ አንድ ሚሊዮን እንደሚጠጋ ምንጮች ገልጸዋል። ዲያስፖራው ይህን ገንዘብ ግማሹን በአንድ ጊዜ ቀሪውን ደግሞ በአንድ ወር ውስጥ እንዲከፍል ይጠበቅበታል። አስገራሚው ነገር ይላሉ ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ምንጮች፣ መንግስት ከሚሰራው ቤት የተሻለ ጥራት ያለው ቤት በ450 ሺ ብር ማግኘት መቻሉ ነው።

ፕሮጀክቶችን ለማስፈጸም ሌላው ችግር የሆነው ተናቦ ለመስራት አለመቻል መሆኑን የውስጥ አዋቂዎች ይገልጻሉ። ለቤቶች ግንባታ ሃላፊነት በተሰጣቸው ሚኒስትር መኩሪያ ሀይሌ፣ በአዲስ አበባው ከንቲና ድሪባ ኩማ፣ በንግድ ባንክ ፕሬዚዳንትና በውጭ ግንኙነት ሚ/ሩ ቴዎድሮስ አዳህኖም መካከል መናበብ በመጥፋቱ ፕሮጀክቱ ባለበት የቆመ ሲሆን፣በተለይም እያንዳንዱ ባለስልጣን ኢህአዴግን ከመውደቅ ያዳንኩት እኔ ነኝ ለማለት ሁሉም የራሱን እቅድ አውጥቶ ሳይናበብ እየሰራ መሆኑን ምንጮች ተናግረዋል።

No comments:

Post a Comment