Saturday, December 28, 2013

ፖለቲካ ጨለማን ተገን አድርጋ ወንጌል ስትሆን !

በአሌክስ አብረሃም  

ወገኖቸ እሰብካችኋለሁ !!

በደሌ ቢራ አትጠጡ እንደተባለ ሰምታችኋል...... እኔ ግን እላችኋለሁ ባጠቃላይ አልኮል መጠጥ አትጠጡ ! ለጤና ጠንቅ ነውና !! መጠሃፉ ‹‹ደሃ ድህነቱን እንዲረሳ የወይን ጠጅ ስጠው ›› ቢልም እኛ ኢትዮጲያዊያን <አስራ አንድ> በመቶ እያደግን ያለን ሃብታም ህዝቦች ነንና እኛን አይመለከትም ! አዎ ! መጠጥ አገር እያጠፋ ነው ትዳር እየበጠበጠ ነው ይሄ ሁሉ ያማረበት ጠጭ ብርጭቆውን በቄንጥ ይዞ ውሰኪውን የሚከነብል ይሄን ሆንኩ ሳይል ወጋኝ ፈለጠኝ ሳይል ድንገት የሚከነበለው ለምን ይመስላችኋል ......መጠጥ .....መጠጥ ነው ወገኖቸ !!

ህዝቤ ቁሞ ይንከላወሳል እንጅ ጉበቱ እኮ የለም .....ሳንባውኮ በጥቃርሻ ተዥጎርጉሮ የሚያፈስ ኮርኒስ መስሏል ......ነብሱ አድፏል ! ይሄ ሁሉ የሆነው በምንድን ነው በመጠጥ !! መጠጥ እንዝህላል ያደርጋል ግዴለሽ ያደርጋል ዋጋ ቢስ ያደር .... ጋል ወገኖቸ ......ዛሬ እኮ ምፅአት ቀርባለችና ንስሃ ግቡ ሲባል ‹ሎ...ል› የሚል ወጣት ነው እያፈራን ያለነው ....

ትውልዱ በቀቢፀ ተስፋ የሚይዝ የሚጨብጠውን አጥቷል ቤተስኪያኖቻችን ርግብና ዋነስ ሰፍሮባቸው ካለሰው እየዋሉ ቡና ቤቱ በሰው ተጨናንቋል ..... ጭፈራ ቤቱ ካፍ እስከገደፉ ሞልቷል .....ስለሳምሶን ታሪክ ሰምታችኋል (ለነገሩ መቸ መጠሃፉን ታነቡና ፌስ ቡክ ላይ አፍጥጣችሁ እየዋላችሁ ) ሳምሶን ታላቅ የህዝብ ነፃአውጭ ነውና ሲረገዝ እናቱ የአልኮል መጠጥ በአፏ እንዳይዞር እግዜር አዟት ነበር !

ለትውልድ የምታስብ ሴት እንዲያ በክብርና በቅድስና ትኖር ዘንድ መፅሃፉ ያዛል ! ዛሬ ግን ሴቶቻችን በየመሸታው አኮሌ ሙሉ መጠጥ ሲገለብጡና ሲያሽካኩ ያመሻሉ ያድራሉ የረከሰ ትውልድ ከሰካራም እናት ይወለድ ዘንድ ስምንተኛው ሽ ቀርቧል ! ወንዱ መቸስ አንዴውኑ ጠጥቸ ልሙት ብሏል !

ደግሞኮ የድሮ መጠጥ ሲያሰክር ጀግና ያደርጋል የልብን ያናግራል ‹‹በቃኝ ባርነት ...በቃኝ ጭቆና ›› የሚል ሰካራም ዛሬ አይታችሁ ታውቃላችሁ ?.....የለም ! ወንዱ ሰክሮም ፈሪ ባይሰክርም ፈሪ ነው ! ቤቱ ገብቶ ሚስቱና ቤተሰቡ ላይ ነው የሚደነፋው ! ወገኖቸ ስካር ድሮ ቀረ !!


ስለዚህ አልኮል መጠጥ አትጠጡ ! እንደአሸን የሚፈላው የቢራ ፋብሪካና መጠጥ ቤት የዝሙት ቤት ድራሹ ይጥፋ ለአንድ ሽ ሰው የስራ እድል ፈጠረ የምንለው የመጠጥ ስራ ሚሊየኖችን ከሰውነት ክብር ካወረደ አትጠጡ !! ይሄ ውስጡ ኑሮ የሚጮህበት ህዝብ ጩኸቱን በጩኸት ለማጨናበር ዲጀ ማንትስ እከሊት ጭፈራ ቤት እያለ ሲያላዝን ያመሻል የውስጥን ጩኸት በውጭ ጪኸት ለጊዜው ነው ማጥፋት የሚቻለው .....እናም እላለሁ መጠጥ አትጠጡ !! አልኮል በደረሰበት አትድረሱ ! አልፎ አልፎ ምናለበት ለምትሉ ለእናተ እላለሁ መጠጥ ሞት አለበት መርከስ አለበት !!

ወገኖቸ የቴዲ አፍሮን ዘፈን አታዳምጡ እንደተባለ ሰምታችኋል ..... እኔ ግን እላችኋለሁ ባጠቃላይ ዘፈን አታዳምጡ .....መጠሃፉ ዘፋኝነት ዝሙት ሴሰኝነት ሰውን መግደል ..... እኩል ሃጢያት ናቸው ብሏልና ትውልዱን እያዘናጉ ሲያስጨፍሩትና ሲያዘልሉት የሚኖሩትን ስለምን ትከተላላችሁ .....ዘፈን የዝሙት ቀኝ እጅ ነው ! ጥበብ ነው እያሉ ሌላ ነገር እንዳታስቡ የሚያጠቧችሁ ጠላቶቻችሁ ዘፋኞች ናቸው ! ብሶታችሁን ከመናገር ይልቅ ከበሯቸውን እየደለቁ ሴት አሰልፈው ሲያደንዟችሁ የሚውሉት እነሱ አይደሉምን ....

የሰው አገር ዘፋኝ ስለነፃነት ይዘፍናል ስለህዝቡ ሃቂቃውን ይናገራል ያንተ አገር ዘፋኝ በአንድ አይኑ መንግስትን በሌላ አይኑ ብር እየተመለከተ ቀልቡ ሳይሰበሰብ ያላዝናል አንተንም ቀልበ ቢስ ያደርገሃል .....እጀጅ የሚል ዘፈኑን እጅ እጅ በሚል ሬዲዮና ቴሌቪዥን ይለቅና ሲኮፈስ ሲበጠር ይኖራል ፡፡ዘ

ዘፈን እኮ ልመና ሁኗል ወገኖቸ !! ባሳዛኝ ቃልና ዜማ አስተዛዝኖ ገንዘብ ይቀበላችኋል ! ልበቢስና ያልተማረ ቁራ ሁሉ ነው ዘፋኝ ነኝ እያለ የሚያደነቁርህ ! እውነት እውነት እልሃለሁ ዘፈን አታዳምጥ ምንም አይቀርብህም..... እንደውም ሰላም ነው የምትሆነው ! ዘፋኞችህ ድድብናንና መሃይምነትን ነው ለትውልድ የሚረጩት ርኩሰትና ዝሙትን ነው ለወጣቱ የሚያስተላልፉት ! ሲመቻቸው በየጠንቋይና መተታሙ ቤት እየሰገዱ መርገምትን ለትውልድ እንደሚያከፋፍሉ የቅርብ ጊዜ ትዝታህ ነው አሁንም ያው ናቸው !

ትውልዱ ሂሳብ አይወድ ሳይንስ አይወድ አይምሮውን ቤቱ አስቀምጦ ሳይቀመጥ እግሩን ይዘረጋል ..... ሁሉም ዘፋኝ ሁሉም የፊልም ባለሙያ ሁሉም ሞዴል .... በቃ ትውልድ እየከሰረልህ ነው ለዚህ ሁሉ መነሻው አርቲስቶችህ ናቸው እነዚህ አጋሰስ ዘፋኞችህ ትውልድን አንድ እርምጃ እልፍ የሚያደርግ ሃቅ አይነግሩህም ! እልሃለሁ አንተ እና እኔ ዳሽቀናል ልጆቻችን ግን ሲቀለድባቸው መኖር የለባቸውም ዘፈን በቃ የማንም ዱርየ ጫት ቤት በሚፈጥረው ተልካሻ ጩኸት አያደናቁረን ! እደግመዋለሁ ዘፋኞችህ እዚህ ግባ የሚባሉ ፍጥረቶች አይደሉም !! ለማንም አርእያ አይሆኑም !

አንዲት አገር ሰበአዊ ሃብቷ ከዳሸቀ መንገድና ህንፃ የሚቀይራት እንዳይመስልህ .....ዘፋኞችህ ግን ውብ ቪላ ቀለበት መንገድ የሻማ ራት ሳዩሃል እስቲ ድህነትህን ውድቀትህን ያሳየ ዘፋኝ ማነው ....ስራ አጥነትህን ማነው ልሳን ሁኖ የተናገረልህ..... ፍትህ ማጣትህን ማን ዘፈነው .... በሙስና አገርህ ተቦጥቡጣ እርቃኗን መቅረቷን በድፍረት የዘፈነልህ ማነው አየህ ዘፋኝህ ሳንቲም ሰብሳቢ ለማኝ እንጅ የጥበብ ሰው አይደለም !

ቴሌቪዥንህ በዜና ያሳየህን ቀለበት መንገድ ከተሜው ዘፋኝ በክሊፑ ያሳያሃል .....ቴሌቪዥንህ በዜና ያሳየህን የሚዘናፈል አዝመራ የባህል ዘፋኝህ ቁምጣውን ለብሶ እየተወላገደ በክሊፕ ያሳየሃል የተቀናጀ ድንዛዜ ይረጭብሃል !

ዘፋኝህ በዝሙት የሰከረ ሴሰኛ እንጅ የፍቅር ሃዋሪያ አይደለም በየቀኑ ኑሮህን አሰልች ያደረገው ዘፋኝህ ነው ዘፋኝ ከሃኪም ከኢንጅነርና ከጋዜጠኛና ከሌላውም ባለሙያ በላይ ብሶትህን አቤት ሊልልህ ይገባ ነበር ግን ያንተ ዘፋኝ አስመሳይ ሆዳምና ጥገኛ ስለሆነ ሳንቲሙን እንጅ አንተ አራት እግርህን ብትበላ ግድ አይሰጠውም ! እና እልሃለሁ ዘፈን አታዳምጥ !! ካላመንክ ሞክረው አንድ ወር ዘፈን የደረሰበት ባትደርስ ውስጥህ የሚገርም ሰላም ይፈሳል !

ዘመኑ ደርሷል ፌስ ቡክ ላይ እንዳፈጠጣችሁ ምፅኣት ድንገት ከተፍ ብትል ‹‹ሎል›› ብላችሁ የምትተርፉ እንዳይመስላችሁ ወገኖቸ ! አንገት የተሰራው አዙሮ ለማየት ነው ነብሳችሁን ስሙ አለበለዚያ አለም የነፍሳችሁን አንገት በሜንጫ እያበረረች አገር ምድሩን ጭንቅላት አልባ ሰው ይሞላዋል ! ልብ ያለው ልብ ይበል !! ጆሮ ያለው ይስማ !!

No comments:

Post a Comment