Monday, December 30, 2013

ደም ሰጥቶ ነፃነት የተከለከለው ህዝብ (አብርሃ ደስታ – የሽሬው ስብሰባ ጉዳይ)

(ኢ.ኤም.ኤፍ) ትላንት እሁድ ለት በሽሬ እንዳስላሴ፤ የአረና ፓርቲ ህዝባዊ ስብሰባ የሚያደርግበት ቀን ነበር። ህዝቡ በዚህ ስብሰባ ላይ ለመሳተፍ ግልብጥ ብሎ መጣ። ሁኔታው ያስደነገጣቸው የህወሃት ካድሬዎች ይህ ስብሰባ እንዳይደረግ ከፍተኛ ጥረት አደረጉ። ይህንን ጠቅላላ ሁኔታ፤ የአረና ፓርቲ ህዝብ ግንኙነት የሆነው አብርሃ ደስታ ከስፍራው ዝርዝር ዘገባ አቅርቧል። ሙሉ ዘገባው ከዚህ የሚከተለው ነው፤ ያንብቡት።

ሽሬ ከመቀሌ በስተ ሰሜን ምዕራብ በ320 (?) ኪሎ ሜትር ርቀት የምትገኝ ከተማ ናት። በአውቶቡስ ጉዞ ከሰባት እስከ ስምንት ሰዓት ይወስዳል (እኛ ስምንት ሰዓት ፈጅቶብናል)። ከመቀሌ ማይመኽደን፣ አጉላዕ፣ ዉቅሮ፣ ነጋሽ፣ እንዳተካ ተስፋይ፣ ፍረወይኒ (ስንቃጣ)፣ ማይመገልታ፣ እዳጋሓሙስ፣ ዓዲግራት፣ አሕዘራ፣ ሴሮ፣ እንትጮ፣ ማርያም ሸዊቶ፣ ዓድዋ፣ አክሱም፣ ዉቅሮማራይ፣ ሰለኽለኻ አቋርጠን ሽሬ እንዳስላሴ ገባን።

ሽሬ ለም መሬት ነው። ሰፊና ሜዳማ የእርሻ መሬት አለ። ህዝቡ እንግዳ አክባሪ ነው። ሽሬ የሆነ ደስ የሚል ነገር አለው። ግን ባከባቢው ብዙ ማሕበራዊ፣ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች አሉ። ይሄን ጉዳይ ሌላ ግዜ እመለስበታለሁ። አሁን ግን ወደ የስብሰባው ጉዳይ እንግባ።

ዓረና መድረክ በሽሬ እንዳስላሴ ከተማ ህዝባዊ ስብሰባ ለመጥራት ወሰነ። ስብሰባው የሚያዘጋጅ የዓረና ቡድን ወደ ከተማው ተላከ። በከተማው ስብሰባ ለማድረግ የሚያስችል ፍቃድና መሰብሰብያ አዳራሽ እንዲሰጠን ጠየቅን። ከአንድ ቀን በኋላ ስበሰባ ማድረግ እንደምንችል ፈቅደው አዳራሽ ግን እንደተያዘ ነገሩን። አዳራሽ መከራየት እንደምንችል ካልሆነ ደግሞ በሆነ ሜዳ ማካሄድ እንደምንፈልግ ነገርናቸው። ከአንድ ቀን በኋላ ተነጋግረው አዳራሽ ፈቀዱልን (ሜዳ ላይ ስብሰባ ከተደረገ ለነሱ ጥሩ አለመሆኑ ያውቁታል)።

አዳራሽ ካስፈቀድን በኋላ ሓሙስና ዓርብ ቀሰቀስን። ከአስር ሺ በላይ በራሪ ወረቀት ተበተነ። በማይክሮፎን ተጠቅመን መረጃው ለህዝብ አዳረስን። የከተማው ካድሬዎች በእግርና በመኪኖች እኛን እየተከታተሉና የሽሬ ህዝብ ለኛ ያለው ስሜት ይሰልሉ ነበር። ያኔ ካድሬዎቹና ሰላዮቹ በኛ ላይ ያደረሱት ምንም ተፅዕኖ አልነበረም። የተቀደደብን ወረቀትም ጭራሽ አልነበረም (በሌሎች አከባቢዎች ካድሬዎቹ ወረቀት ተቀብለው የሚቀዱ ነበሩ)። ዓርብ ቤት ለቤት ቀሰቀስን።

ካድሬዎቹና ሰላዮቹ የህዝቡን ጥሩ አቀባበል ለሚመለከታቸው አካላት ሪፖርት አደረጉ። ዓርብ ከሰዓት የከተማው የካቢኔ አባላት ተሰብስበው በጉዳዩ ተወያዩ። ዓርብ ማታ (ከምሽቱ አንድ ሰዓት) የከተማው ከንቲባ አቶ መረሳ አታክልቲና ምክትል ከንቲባው መምህር ሃይለ አዳነ ወደ ማዘጋጃቤት ጠርተው ቅስቀሳ ማቆም እንዳለብን ነገሩን። ስላደረግነው ቅስቀሳ በቂ መረጃ መሰብሰባቸው፣ በጉዳዩ ካቢኔ መሰብሰቡና እስካሁን የተደረገ ቤት ለቤት ቅስቀሳ በቂ መሆኑ መግባባት ላይ መደረሱ ተነገረን።


እኛም ተቃወምን። አቶ አስገደ ገብረስላሴ ደግሞ ‘ስለ ቅስቀሳው በቂነት የምናውቀውና የምንወሰነው እኛ ራሳችን እንጂ እናንተ አይደላችሁም። ስለዚህ ቅስቀሳችን እንቀጥላለን’ አለ። ምክትል ከንቲባው በጣም ተናዶ ‘አንደኛ ስትቀሰቅሱ መሳደብ አቁሙ’ አለ። ‘መቼ ነው የተሳደብነው’ ስለው ‘ግዕዙይ ምምሕዳር’ ብላችኋል አለኝ። ለካ በማይክሮፎን ስንቀሰቅስ የስብሰባው አጀንዳዎች እንዘረዝር ነበር። ከአጀንዳዎቹ አንድ ስለ ‘መልካም አስተዳደር እጦትና መፍትሔው’ የተመለከተ ነበር። በትግርኛ ‘ግዕዙይ ምምሕዳርን መፍትሒኡን’ ይላል። አስገደም አስከትሎ ‘ግዕዝይናኮ ሙስና ነው። ስለ ሙስና እንነጋገራለን’ አለ (ሙስና በትግርኛ ግዕዝይና ነው)። ምክትል ከንቲባውም ‘ታድያ ሙስናኮ መንግስታችን ህወሓት እየታገለው ነው ያለው፤ እናንተ ምን አገባቹ?’ አለ።

ርእሱ ለመቀየር ሞከርኩ። ‘እስከ ስብሰባው ቀን ድረስ ብንቀሰቅስ ችግሩ ምንድነው?’ ብዬ ጠየቅኩ። ከንቲባው ‘አንደኛ ህዝቡ በቅስቀሳው ደስተኛ አይደለም፤ ሊረብሽ ይችላል። ሁለተኛ ነገ ቅዳሜ ነው፤ የገበያ ቀን ነው። ሦስተኛ እስካሁን በቂ ቅስቀሳ ተደርጓል’ የሚሉ ሦስት ምክንያቶች አቀረበ። እኛም ለሦስቱ ምክንያቶች መልስ ሰጠን። ‘አንደኛ ህዝቡ አይረብሽም፤ በጥሩ ሁኔታ ተቀብሎናል። ሁለተኛ በሕጉ መሰረት ከገበያ ቦታ አምስት መቶ ሜትር ርቀን ነው የምንቀሰቅሰው። ሦስተኛ እኛ በፈለግነው ግዜ ቅስቀሳው እንጀምራለን፣ እናቆማለን’ አልን።

ቅስቀሳው ማቆም እንዳለብን፣ የካቢኔ ዉሳኔና ትእዛዝ መሆኑ ነገሩን። ትእዛዝ ከሆነ በፅሑፍ እንዲያሳውቁን ጠየቅን። በፅሑፍም አሳወቁን። ፅሑፉ ለሚደርስብን ችግር የከተማው አስተዳደር ሐላፊነት እንደማይወስድ ይጠቁማል። ፀጥታ የማስከበር ሐላፊነት የመንግስት ተግባር ነው፤ የኛ ስራ አይደለም ብለን ቅዳሜም ቅስቀሳችን ቀጠልን። ምንም ችግር አልደረሰብንም።

እሁድ ጠዋት በተፈቀደልን አዳራሽ አከባቢ በማይክሮፎን ህዝቡን ስለ ስብሰባ ማስታወስ ጀመርን። መቀስቀስ እንደሌለብን ፖሊስ ነገረን (ፖሊስ ቅስቀሳው ለማስቆም መታዘዙ ነግሮናል)። መቀስቀሱ አቁመን ወደ አደራሹ ሄድን። ከሁለት ሰዓት ጀምሮ ብዙ ሰዎች ተሰባስበዋል። አደራሹ ግን ዝግ ነው። ዘበኛው እንዲከፍትልን ጠየቅን። ‘አልታዘዝኩም’ አለ። ከድር ወደተባለ አለቃው ደወልኩ። አዳራሹ መክፈት እንዳለበት ነገረው። ባደራሹ በር ሁለት ሰዎች አሉ። ‘ጥብቃ ነን’ አሉ። ግን የህወሓት ካድሬዎች ናቸው።

በሩ ተከፈተ። ህዝብ ለመግባት በር ላይ ሲደርስ ሁለቱ ካድሬዎች ወደ አደራሹ የሚገባ ሰው የቀበሌ መታወቅያ በእጁ የያዘ ብቻ መሆኑን አወጁ። ህዝቡም ‘መታወቂያ አናሳይም’ አለ። ‘መታወቂያ ካላሳያቹ አትገቡም’ ተባለ። ጭቅጭቅ ተጀመረ። ‘በህዝብ ስብሰባ ለመሳተፍ መታወቅያ አያስፈልግም’ ብዬ ለሁለቱም ካድሬዎች ነገርኳቸው። ‘መታወቂያ ያስፈልጋል ተብሏል’ አሉኝ። ‘ህዝቡ መፈተሽ ያለበትኮ ፖሊስ እንጂ እናንተ አይደላችሁም’ አልኳቸው። ካድሬዎቹ የአዳራሹን በር ዘጉት።

ወደ ከንቲባው ደውዬ ህዝብ በፖሊስ ብቻ እየተፈተሸ፣ የቀበሌ መታወቅያ ሳይጠየቅ እንዲገባ ለማድረግ ሕጋዊ ፖሊስ እንዲመደብልን ጠየቅኩት። እሱም ፖሊስ እንደማይመድብ፣ የቀበሌ መታወቂያ ያለው ብቻ መግባት እንዳለበትም ነገረኝ። እኔም እንደዛ ከሆነ ስብሰባው ከአዳራሹ ውጭ እንደምናደርገው ነገርኩት። ‘አይሆንም’ አለኝ።

‘መታወቂያ ያልያዘ አይገባም’ ስለተባለ ስብሰባው ባደራሹ በር ለማድረግ ተስማማን (ልብ በሉ የከተማው አስተዳደር ፖሊስ እንደማይመድብና ለሚፈጠረው ችግር ሐላፊነት እንደማይወስድ ነግሮናል)። አዳራሽ ዉስጥ ገብቶ የነበረ ሰው እንዲወጣ አደረግንና ስብሰባው ባደራሹ በር አከባቢ ባለው ሜዳ ላይ ስብሰባ ጀመርን። በጣም ብዙ ህዝብ ነበር (በሺዎች የሚቆጠር)።

የከተማው አስተዳዳሪዎች መጡ (ከንቲባው፣ ምክትል ከንቲባው፣ የፕሮፓጋንዳ ሐላፊው … እስከ ቀበሌ ተጠሪዎች ተሰባስበው መጡ። ስብሰባው ማቋረጥ እንዳለብን ነገሩን። ከፈለጋቹ እሰሩን እንጂ ህዝብ ጠርተንማ ስብሰባ አናቋርጥም አለን። እኛ ከከተማው አስተዳዳሪዎች ጋር እንጨቃጨቃለን። የዓረና ሊቀመንበር አቶ ብርሃኑ በርሀ ግን ንግግር ማድረግ ጀመረ። አለመግባባቱ ግን እየከረረ መጣ። በአካባቢው ደንብ የለበሰ ፖሊስ አልነበረም። የደህንነት ሰዎች ግን መዓት ነበሩ።

አንድ የፖሊስ አዛዥ መጣ። ‘ስርዓት ያዙ’ አለን። ‘ስብሰባ እያካሄድን ነን’ አልን። ‘እዚህ ስብሰባ እንድታደርጉ አልተፈቀደላችሁም’ አለ (ትክክል ነበር፤ በሜዳ ስብሰባ ለማድረግ አልተፈቀደልንም)። ‘ግን ህዝቡ በካድሬዎች ወደ አዳራሽ እንዳይገባ እየተከለከለ ነው’ ብለን ለፖሊሱ ነገርነው። ፖሊሱ ‘አሁን ወደ ተፈቀደላቹ አዳራሽ ግቡ’ ሲለን ህዝቡ ለመግባት ሰልፍ ያዘ።

‘ህዝቡ መታወቂያ እየተጠየቀ ነው’ ብለን ለፖሊሱ አሳወቅን። (ከከንቲባውና ጓደኞቹ ጋር የምናደርገው ንትርክ ግን እየከረረ ነው)። ፖሊስ ‘መታወቂያ አያስፈልግም። እየፈተሻቹ አስገቡት’ አለ። ከንቲባው ‘ያለ መታወቂያማ ሰው አይገባም’ አለ። ፖሊሱና ከንቲባው ተጨቃጨቁ። ከንቲባው ተቆጣው። ከዛ ፖሊሱ እኛንና የህወሓት አባላትን መሸምገል ጀመረ። አስገደ ገብረስላሴ ‘አትረብሹን’ አለ (አስገደ ተናዶ ነበር)። መታወቂያ የያዘ ብቻ ሰልፍ ስይዝ መታወቅያ ያልያዘ ጥግ ያዘ። አንድ የደህንነት ሐላፊ ነው የተባለው ሰው መጥቶ ለሚፈት ሹ ካድሬዎች ‘የቀበሌ መታወቂያ ያለው ሳይሆን የዓረና መታወቅያ ያለው ብቻ ነው የምታስገቡ’ የሚል ትእዛዝ አስተላለፈ።

‘ስብሰባው’ኮ የህዝብ እንጂ የዓረና አባላት ብቻ አይደለም’ አልኩና ሁኔታው በፌስቡክ ለመዘገብ ወደ ኢንተርኔት ካፌ ገባሁ። በአደራሹ በር አካባቢ የተሰበሰው የሽሬ ከተማ ህዝብ ለመበተን ጥረት እያደረጉ ነበር እነ አቶ ከንቲባ። ግን በጣም ብዙ ስለነበር በቀላሉ መበተን አልተቻለም። እንዳውም ጭቅጭቁ ለመስማት ይጠጋ ነበር።

ከደቂቃዎች በኋላ ተመለስኩ። አቶ አስገደ ገብረስላሴ ፎቅ ላይ ወጥቶ በማይክሮፎን መናገር ጀመረ። ‘የሽሬ ህዝብ ታፍነሃል…’ ይላል። ከዞኑ ፅሕፈት ቤት ሦስት ሰዎች በፍጥነት ጮክ ብለው እየተናገሩ ወደ ተሰበሰው ህዝብ ተቀላቀሉ። የከተማው አስተዳዳሪዎችና ተጠሪዎች እንዲሁም የደህንነት ሰዎች አሰባስበው አስር ዓመት የማይሞላቸው ህፃናት አስከትለው ‘ሆ’ አሉ። እየጮሁ ዓረናና የዓረና አባላትን መሳደብ ጀመሩ። ‘ዓረና ሻዕቢያ ነው! ዓረና ኪራይ ሰብሳቢ ነው! ዓረና አሸባሪ ነው! እያሉ ይጮኃሉ።

አስገደ ገብረስላሴ ፎቅ ላይ ሁኖ ይናገራል። የሚናገረውን ነገር ህዝቡ እንዳይሰማው ለማድረግ ድምፅ እየጨመሩ ‘አስገደ ሌባ’ እያሉ መጮህ ተያያዙት። ለስብሰባ የመጣ ህዝብ ተበተነ (ጥግ ጥግ ያዘ)። አከባቢውን እነሱ ብቻ ተቆጣጠሩት። ፎቅ ላይ ሆነን ቪድዮ ለማንሳት ሞከርን። መጨረሻ እየጮሁ ወደ ዞን አስተዳደር ህንፃ ገቡ። ስብሰባው ተስተጓጎለ።

ረብሻው ይመሩ የነበሩት ሦስት ሰዎች ሲሆኑ፤ ሁለቱ ተፈናቃይ ኤርትራውያን (ግን በማዘጋጃቤት የተቀጠሩ)ና አንድ የደህንነት ሐላፊ ናቸው። ግን ለምንድነው ኤርትራውያን ለህወሓት የሚደግፉ? የሽሬ ህዝብ ህወሓትን ያልደገፈ ኤርትራውያን ለምን? የሽሬ ህዝብ ግን በሁኔታው እጅግ መገረሙ ከሠዓት በኋላ የደረሰኝ መረጃ ይጠቁማል።

ስብሰባው ተጀምሮ ተስተጓጎለና ወደ ቢሮአችን አመራን። ህዝቡ ‘አይዟቹ’ ይለን ነበር። ከዛ እኔ ወደ ዓድዋ አመራሁ። የማገኛቸው የዓረና አባላት ለማደራጀት ነበር። ከስድስት እስከ ዘጠኝ ሰዓት ዓድዋ ነበርኩ። ዓድዋ ሁኜ ስለ የሽሬ ስብሰባ ለመፃፍ ፈለግኩ። ግን ደክሞኝ ነበር። የተወሰነ መረጃ ለመስጠትና ዓድዋ ከተማ እንደምገኝ ለማሳወቅ ትንሽ ፃፍኩኝ። ግን እንተርኔት ደካማ ስለነበር ፖስት ማድረግ አልቻልኩም። ፅሑፉ ግን በፍላሽ ይዠው ከቀኑ ዘጠኝ ሰዓት አከባቢ ወደ መቀሌ ጉዞ ጀመርኩ። ከምሽቱ ሦስት ሰዓት መቀሌ ገባሁ።

‘የምጥሰጠን መረጃ ታማኝ ከሆነ ለምን በፎቶ ወይም ቪድዮ አታስደግፈውም’ የሚሉ አስተያየቶች ይነሳሉ። ግን ፎቶ ወይም ቪድዮ የማልለጥፍበት ወይ የማላነሳበት ምክንያት አለኝ። በውቅሮ ከተማ ስብሰባ ስናደርግ ካድሬዎች ህዝብ በስብሰባው እንዳይሳተፍ ይመልሱ ነበር። ካድሬዎቹ ህዝብ ሲመልሱ በካሜራ እንቀርፃቸው ነበር። ባጋጣሚ ግን የከተማው ፖሊስ ኮማንደር ሰው ሲመልስ ቀረፅነው (ከሌሎች ካድሬዎች ጋር)። የፖሊስ ኮማንደሩ ‘ያለ ፍላጎቴ ቀርፀውኛል’ ብሎ ፖሊስ ጣብያ ወሰደን። ካሜራው በፖሊስ ተያዘ። አባሎቻችን ተንገላቱ፣ የተቀረፀ ቪድዮ አጠፉት፣ በዛ ሂደት የዉቅሮ ስብሰባችን ሳንቀርፀው ቀረን።

ከዉቅሮ ትምህርት ወስደን ቀረፃ የምናካሂድ በስብሰባው አዳራሽ ዉስጥ ብቻ ነው። በማይጨው ከአዳራሽ ዉጭ አልቀረፅንም። በተምቤን ካድሬዎቹ በአዳራሹ በር አካባቢ ተሰፍስፈው ሲያስቸግሩን በሞባይል የምቀርፃቸው መስዬ በአባቢው አለፍኩ። የተቀረፁ የመሰላቸው የዓብይ ዓዲ ከተማ ፖሊስ ኮማንደር (ክብሮም)ና ሌሎች ባለስልጣናት ወደ ፖሊስ ጣብያ ወሰዱኝ። ‘ያለ ፍቃዳችን ቀረፅከን’ አለኝ። ‘አልቀረፅኩም’ ብዬ ሞባይሌን በባለሙያ ተፈተሸ። ምንም አልቀረፅኩም። ተለቀቅኩ።

ከዚህ በመነሳት በሽሬም እንዳያስተጓጉልን በመስጋት ከአዳራሽ ዉጭ ቪድዮ ለመቅረፅ ይሁን ፎቶ ለማንሳት አልፈለግንም ነበር። ግን ስብሰባው መስተጓጎሉ ከተረዳን በኋላ ግን ሁኔታው በቪድዮ ቀርፀነዋል፣ ፎቶም አንስተናል። የነበረን ሐሳብ ግን ስብሰባው ተጀምሮ የሚካሄደው ውይይት ለመቅረፅ ያለመ ነበር። የተሳታፊዎች ፍቃድ ከሆነ ማቅረብ እችላለሁ። በሚቀጥለው መታወቂያ ያልያዙ ሰዎች ጥግ ይዘው ሲጠባበቁ የሚያሳይ ነው።

ባጠቃላይ በሽሬ ያደረግነው ቅስቀሳ ውጤታማ ነበር። ስብሰባው (ተጀምሮ ሳያልቅ) በድል ተጠናቋል ማለት ይቻላል። ህወሓቶች ግን የህዝቡ የተቃውሞ መንፈስ በጣም አስደንግጧቸዋል። ሁሉም በስብሰባው እንዲሳተፍ ቢፈቀድለት ኑሮ ወደ ሁለት ሺ ሰው ይሳተፍ ነበር የሚል ግምት አለን። ግን ብዙ መስዋእት የከፈለ ህዝብ አማራጭ ሐሳብ እንዳይሰማ ተነፈገ። የፈለገውን ሐሳብ በነፃነት እንዳያራምድ ተደረገ። ህዝብ አማራጭ ሐሳብ እንዳይሰማ መከልከል ህዝብን ማፈን ነው። ታድያ ህዝብ እንዲህ ከታፈነ ለምን ነበር ይህን ሁሉ መስዋእትነት የከፈለው? የሽሬ ህዝብ ደሙ የሰጠ ለነፃነቱ አልነበረም እንዴ? ደም የሰጠ ህዝብ ነፃነት ይከለከላል?

ለማንኛውም የሽሬ ህዝብ የካድሬዎችን ማስፈራርያ ሳይበግረው በስብሰባው ለመሳተፍ መጥቷል። ህዝቡ በስብሰባው እንዳይሳተፍ የተደረገው በማስፈራራት ሳይሆን የአዳራሹን በር በመዝጋትና ስብሰባው እንዳይካሄድ በመረበሽ ነበር። ህዝቡ ግን ለውጥ ይፈልጋል። በቅስቀሳው ወቅት ብዙ አባላት አፍርተናል። ስብሰባው ቢካሄድ ኑሮ ደግሞ የበለጠ ይሆን ነበር። በሐሳብ መከራከር የሰለጠነ መንገድ ነው። ህወሓቶች ዓቅም ካላቸው በህዝብ ፊት ቀርበው ከኛ ጋር ይከራከሩ። ስብሰባ መረበሽ ጀግንነት አይደለም። ጀግንነት ተከራክሮ ማሸነፍ ነው።

በትግራይ ሙሉ በሙሉ አሸንፌያለሁ የሚል መንግስት እንዴት በዓረና ስብሰባ ይደነግጣል? ህወሓት የህዝብ ድጋፍ ካለው ለምን ዓረና ከህዝብ እንዳይገናኝ እንቅፋት ይፈጥራል? ህወሓት ዓቅም እንደሌላቸው አረጋግጠዋል። በሽሬ ከተማ ህወሓት ምንም ድጋፍ እንደሌለውም አረጋግጠናል። የሽሬ ህዝብ በጣም የተበደለ ነው።

ይህን ሁሉ መስዋእትነት በነፃነት የመሰብሰብ መብት ካላስገኘ ታድያ ፋይዳው ምንድነው? ህወሓት የትግራይ ህዝብ ድጋፍ አለኝ ብሎ የሚያምን ቢሆን ኑሮ ይህን ያህን አይፈራም ነበር።

No comments:

Post a Comment