Wednesday, April 30, 2014

ለማነው የነጋው?!

በአስራት አብርሃም

አዲስ አበባ በፊት ከየትኛውም የሀገሪቱ ክፍል ለሚመጣ ሰው ገነት ነበረች። አዲስ አበባ የሄደ ሰው ቤት ባይሰራ እንኳ ሆዱ ጠግቦ ይኖራል፤ መኪና ባይኖረውም ባማሩ ታክሲዎች ሽር እልም ማለት ይችላል። ወደ አዲስ አበባ የሄደ ሰው እንደሚያልፍለት ምንም ጥርጥር የለውም እየተባለ ሲነገር ልጅ ሆኘ እሰማ ነበር። እንደ ችግር ከተነሳ አዲስ አበባ የሄደ ሰው ወደ ሀገሩ አይመለስም፤ የሽዋን ውሃ ከቀመሰ ሀገሩን ይረሳል እየተባለ ይወራል። አሁን ያ ሁሉ ተረት ሆኗል። አሁን አዲስ አበባ መምጣት ብቻውን የሚፈይደው ነገር የለም፤ ወይ ደህና ዘመድ ወይም ባለስልጣን ሰው ሊኖርህ የግድ ይላል፤ ምንም ለሌለው ደሀ ሰው ዝም ብሎ እንደ ድሮ ተነስቶ ወደ አዲስ አበባ መምጣት በጣም አስቸጋሪ ነው። ምግብና መኝታ ማግኘት ፂማም ሴት በከተማው የመፈለግ ያህል ከባድ ሊሆንበት ይችላል፤ ጎደና እያደረ ካልለመነ በስተቀር!

እኛ በአዲስ አበባ የምንኖረው ዜጎች በብዙ ነገር ብንማረርም አሁንም ግን መሄጃ ያጡ ብዙ ሰዎች በተለያዩ ምክንያትና ለተለያዩ ዓላማ ከሁሉም ክፍላተ ሀገር ወደ አዲስ አበባ ይጎርፋሉ። ገሚሱ ጫማ ጠራጊ ሲሆን ሌላው ደግሞ መውልዊያ እየዞረ ይሸጣል። ሌላው ቆሎ ሌላው ደግሞ ሎተሪ እያዞረ በመሸጥ የዕለት ምግቡን ያገኛል። ከዚህ ውጪ ለልመናም የሚመጣ አለ፤ ምናልባትም በአዲስ አበባ ቀላሉን ነገር መለመን ሳይሆን አይቀርም፤ ምክንያቱም የአዲስ አበባ ህዝብ አባ መስጠት የሚባል ዓይነት ነው። በየትኛውም ቋንቋ፣ በየትኛውም ኃይማኖት ለምነው ይሰጣል።

የኑሮው ነገርማ እንኳን ምንም ለሌለው አዲስ መጤ ይቅርና እዚሁ የአራዳ ውሀ እየጠጣ ላደገም አስቸጋሪ ሆኗል። በአሁኑ ሰዓት የእግር መኪና ወይም የመስራያቤት ሰርቪስ የሌለን የአዲስ አበባ ነዎሪዎች በቀን ሁለት ጊዜ፣ አንዳንዴም ከዚያ በላይ እንሰለፋለን። ሰልፍ ያማራት እርጉዝ ብትኖር አሁን ብዙም የሚያስቸግር አይደለም፤ ወደ አንዱ የታክሲ ሰልፍ ወስዶ እዚያ እንድትቆም ማድረግ ይቻላል።


የትራንስፖርት ዋጋ ጨመረ ሲባል ያመረርነው ያህል፤ አሁን ታክሲ ለማግኘት ከጦር ሜዳ ውጊያ ያልተናነሰ ግፊያ እየተጋፋን ጉልበት ያለው በጉልበቱ እየተሳፈረ፤ ጉልበት የሌለው ደግሞ እየተዘረፈ ወይም እየተሰበረ ብዙ መከራ ያያል። ለዚህም መላ ተገኘለት ተባለና ሰልፍ ማሰለፍ ተጀመረ። እድሜ ለመንግስታችን ሰዉ ራሱ ማማረርም የተወው ይመስላል። ምክንያቱም ኢህአዴግ አንድን ችግር የሚፈታው ሌላ የከፋ ችግር በመፍጠርና የቀደመውን ችግር እንዲረሳ በማድረግ ነው። ለምሳሌ የዘይትን መወድድ ህዝቡ ሲያማርር ጭራሽ ዘይት የሚባል ነገር እንዲጠፋ ያደረገውና ቀጣዩ ጭንቅ ዘይት የመገኘት ወይም ያለመገኘት ጉዳይ ይሆናል። ከዚያ በኋላ ዘይት ተወደደ ብሎ ማማረር የለም።

ከዕለታት በአንዱ ቀን ሜክስኮ አደባባይ ወደ አፍሪካ ህብረት በሚወስደው መንገድ ላይ ታክሲ ለመሳፈር ረጅም ሰልፍ ይዘናል፤ ወደ ጆሞ ለመሄድ! በዚህ ቦታ ላይ ተሰላፊ መሆን ብዙ ልብ አድርቅ የሆነ ነገሮች ያጋጥማሉ። ከፀሀዩ እና ከአቧራው ባሻገር ሎተሪ አዟሪዎች፣ ማንኪያና ጭልፋ ሸያጮች እንደዚሁም ለማኞች ተሰላፊውን ህዝብ ይነዘንዙታል።

በዚያ ዕለት አንድ ጠና ያሉ፣ አዳፋ ልብስ የለበሱ ሰውዩ “ስለእግዚሃር” እያሉ ይለምናሉ፤ ሰዉ ብር ሲሰጣቸው ደግሞ በትግርኛ ይመርቃሉ፤ ሰው ደግሞ አንድም በተለየ ቋንቋ ሲመርቁት ደስ እያለው ይሁን ወይም አማርኛ ያለመቻላቸው እያሳዘነው ይሁን ወይም የትግሬ ለማኝ ሲያጋጥመው አንዳች እውነት እየተገለጠለት ይሁን ብቻ ብሩን ወይም ሳንቲሙን መዥረጥ እያደረገ ይሰጣቸዋል። ሰውዬው ግን አጥብቆ ለማኝ ነበሩና አሁንም የሰጣቸውን ሰው በትግርኛ እያመሰገኑ ያልሰጣቸውን ደግሞ በተመሳሳይ እጁን እንዲዘረጋላቸው ስለእግዚሃር ይላሉ።

በዚህ ጊዜ እኔ ነገር ያሳመርኩ መስሎኝ “ተሰጥዎት አይደለ አንዴ ለምን ከዚህ ዞር አይሉም?” አልኳቸው። በዚህ ጊዜ ፈጽሞ ያልጠበኩትን ነገር ተናገሩ። “”ካብቲ ካሊእ እኮ ብኢስኩምና፤ ንስኻትኩም እንተሓለፈልኩም ዘይሓለፈልና ናይ ምልማን መስል የብልናን?” አሉ። “ከሌላው እኮ የእናንተ ባሰብን፤ እናንተ ያለፈላቸሁ እንደሆን እኛ የመለመን መብት የለንም እንዴ!” ብለው ማመረር ጀምሩ። ነገሩ ከረር ያለ መሆኑን ስረዳ በደንብ ላናግራቸው ፈልጌ ከሰልፉ ወጣሁና “ምን ለማለት ፈልገው ነው?” ብዬ አጥብቄ መጠየቅ። በዚህ ጊዜ ለማኙ ሁኔታዬን አይተው ረጋ ባለ ሁኔታ ትህትና ባለው መንገድ ማስረዳት ያዙ። “ንሕና ቸጊሩና እዩ መፂኢና እንልምን ዘለና ኣብዚ ዘለው ሓደ ሓደ ተጋሩ ግና ንምንታይ ዓድኩም አይትኮኑን ይብሉና” (እኛ ቸግሮን ነው የመጣው፣ እየለምንን ያለነውም አማራጭ አጥተን እዚህ ያሉ አንዳንድ ትግራይ ሰዎች ግን ለምን ሀገራችሁ አትሆኑም ለምን እዚህ ትመጣላችሁ እያሉ ይሰድቡናል፤ እኛ ችግር ሆኖብን ነው እንጂ ልመና ጥሩ ነገር እንዳልሆነ እኮ እናቃዋለን) አሉ።

በዚህ ጊዜ እኔ “ግን እኮ መንግስት በሬድዮና በቴሌቭዥን የገጠሩ ህዝብ አልፎለታል ሚሊየነር ሆኖዋል” እያለ እየተናገረ ነው ያለው አልኳቸው። መልስ ለመለስ ችግር እንደሆነባቸው ያሳብቅባቸዋል። ትንሽ ዝም ብለው ከቆዩ በኋላ “እንግዲህ ያለፈላቸው ገበሬዎች ሊኖሩ ይችላሉ፤ እኔ ግን ይሄው እንደምታየኝ የነጣሁ ድሃ ነኝ። ስለሌላው ሰው መመስከር አልችልም” አሉ።

“ለምሳሌ እናንት አከባቢ ካሉት ሰዎች እርስዎ ብቻ ኖት ደሀ ማለት ነው” ስላቸው፤
“ሌላውም እንዲሁ ተመሳሳይ ነው፤ ከፈለግህ የመጣሁበት አከባቢ ልንገርህ እና ሄደህ ማረጋገጥ ትችላለህ” አሉ ፈራ ተባ እያሉ።
“ስለዚህ ሬድዮውና ቴሌቭዥኑ ይዋሻል እያሉ ነው?” የሚል ሆነ ቀጣዩ የእኔ ጥያቄ።
“የለም ልጄ እኔ ይዋሻሉ አላልኩም፤ እኔ ለማለት የፈለኩት ምናልባት ሌላ ቦታ ስላሉት ገበሬዎች ይሆናል የተናገሩት ማለቴ ነው። እንግዲህ አንተ እያየክኝ ነው አይቶ መፍረድ ነው” አሉ። በጣም ጥንቃቄ አብዝተዋል። ስንት ነገር ያየ እና ያሳለፈ ህዝብ ሁሉም ነገር መጠርጠሩ ደንብ ነው።

“አሁን እርስዎ ምንም ስለ ሌለዎት ነው እየለመኑ ያሉት?”
“አዎ! በዚህ ላይ የማዳበሪያ ዕዳ አለብኝ።”
“ እዳ ውስጥ የሚከትዎት ከሆነ ለምን ማደበሪያውን ወሰዱ”
“ውሰዱ ብለውን።”
“በግዴታ!”
“አይደለም።”
“ውሰዱ አሉን ወሰድኩ።”
“አልወስድም አይሉም።”
“ለምን እኔ ከሀገር ተለይቼ አልወስድም እላለሁ? ደግሞም መንግስት ለእኛ አስቦ ነው እንጂ ምን እጠቀም ብሎ ነው ውሰዱ የሚለን” አሉ።
“እሺ ከሚለምኑ ለምን ስራ አይሰሩም?” አልኳቸው።
“ምን ስራ አለ! ዘበኛ ለመሆን በራሱ ዋስ ያስፈልጋል። ሸክምም ቢሆን ጎረምሳቹ የሚያሳልፉ አይደሉም” አሉ።
“እሺ ለምን ሎተሪ አያዞሩም?” ስላቸው
“ምን አልከኝ?” አሉኝ የገባቸው አልመሰለኝም። በአጋጣሚ ራቅ ብሎ አንድ ሎተሪ አዟሪ ነበርና “ለምን እንደእርሱ አይሰሩም ማለቴ ነው” ስላቸው “ምኑን አውቄው ነው ልጄ” ብለው ዝም አሉ። በመጨረሻ ከመለየቴ በፊት ብዙ ጊዜ ወስጀባቸው ነበርና ከኪስዬ ብር አውቼ ዘረጋሁላቸው። እንዲያ ሲለምኑ የነበሩት ሰውዬ የእኔን ብር ለመቀበል አንገራገሩ። “ይሄማ ጥሩ አይደለም” ብዬ በግድ ሰጠኋቸው። ብዙ ምርቃቶችን እያሽጎደጎዱ እንድሄድላቸው በዓይናቸው ይለማመጡኛል። ያሳዝናሉ፤ ጥያቸው ሄድኩኝ።
ብዙ ሰዎች ለልመና ወደ አዲስ አበባ የሚመጡት ስለሚቸግራው መሆኑ ምንም ጥርጥር የለውም። አንዳንዱ ደግሞ እንደ ስራ ቆጥሮት ስራዬን ብሎ ለልመና የሚመጣ እንዳለም የሚታወቅ ነው። በእርግጥ በዚህ የሚመደቡት በቁጥር እዚህ ግባ የሚባሉ አይደሉም። የዛሬ ሁለት ዓመት ብሄራዊ ቲያትር አካባቢ ያጋጠመኝ ጉዳይ ለዚህ ጥሩ ምሳሌ የሚሆን ነው። እኔ በተወለድኩበት አከባቢ መካከለኛ እና ደህና የሚባል ኑሮ አላቸው የሚባሉ ቄስ ናቸው፣ ሲለምኑ አይቼ እርሳቸው ናቸው ወይስ አይደሉም ብዬ በደንብ አየኃቸው፤ በእርግጥም ራሳቸው ነበሩ። ድንገት ቢያዩን እንዳያፍሩ በማሰብ እጥፍ ብዬ ሄድኩ። ሌላ ጊዜ የሆነ ዘመዴ እኔን ጥየቃ መጥቶ ስለቄሱ ጉዳይ አነሳሁለት፤ ሲለምኑ እንዳየኃቸውም ነገርኩት። እርሱ ግን እንደ ደህና ነገር እዚህ ሲልምኑ ቆይቶው ወደ ሀገራቸው ሲመለሱ ምን የመሰለ ወይፈን እንደገዙ በኩራት ነገረኝ። እንደዚሁ ዓይነቱ ሳይቸግረው ወይም የሆነ ነገር ለማትፈር ብሎ የሚለምን ቢኖሩም አብዛኛው ግን ቸግሮች እንደሚለምን ከፊታቸው አመድነት፣ ከከንፈራቸው ድርቀት፣ ከገላቸው መራቆትና ከልብሳቸው አዳፋነት መረዳት የሚቻል ነው።

ከዚህ ሁሉ ይልቅ የሚያሳስበውስ እኛ ስላለፈልን ሌላው እየለመነ ክብራችንን ማዋረድ የለበትም ስለሚሉ ዘመናይ ደናቁርት ጉዳይ ነው። እነዚህ የአስራ አምስት ሺህ ዊስኪ በአንድ ሌሊት እየጠጡ “እንደዚህ ዊስኪ ድፍት ያድርገኝ መለስ የመሰለ መሪ፣ እንደ ህወሀት ያለ ድርጅት ከአሁን በፊትም አልነበረም፤ ወደፊትም አይኖርም” እያሉ በየመጠጥ ቤቱ የሚፎክሩት መሀይማን ገበሬው ምን ሆኖ ከቀየው እንደሚሰደድና በየጎደናው ክብሩን አዋርዶ እንደሚለምን ሊገባቸው አይችልም።

ከላይ ሰውዬው ለመናገር ባይደፍሩም ሬድዮውና ቴሌብዥኑ ውሸት እንደሚናገር ይጠፋቸዋል ብዬ አልገምትም፤ ነገር ግን እውነቱን ቢናገሩ ምን እንደሚመጣባቸው ያውቁታል። እንኳን በሰው ሀገር፣ ከማውቁት ሰው ጋር ቀርቶ በራሳቸው ቀየም ቢሆን ደፍረው መንግስት ይዋሻል ብለው የሚናገሩ አይመስለኝም።

አያልነህ ሙላቱ እንዲህ የሚል ግጥም አለው፤

አእዋፍ በጥዋቱ ተነሳ እምትሉኝ ለምን ይሆን ከቶ
ባማረ ድምጻችሁ መስኮቴ ተንኳኩቶ።
በሉ እኔስ ተነሳሁ ነቃሁኝ ታግየ
አዎ በእርግጥ ነግቷል የፀሐይ እግር ታዬ።
ግን ልጠይቃችሁ አዕዋፍ በያይነቱ
ነጋ ጠባ ባዮች ሰርክ በየጠዋቱ።
ያነጋችሁት ቀን በአማረው ዜማችሁ
ለማን እንደጠባ ግን ታውቃላችሁ?!

በደርግ ከነበረው ጊዜ አንፃር አሁን ነግቷል ማለት ይቻል ይሆናል። ለማን እንደነጋ ግን አሁንም ግልፅ አይደለም። ያው እንደተለመደው ለሰፊው ህዝብ እና ለተራው ዜጋ ሳይሆን ጠመንጃ ላነገቱ አዲስ ገዥዎች ነው። አታክልቲ ሀጎስ የተባለ የህወሀት ሰው በውራይና መፅሔት ሚያዝያ 2006 ዓ.ም. 9ኛ ዕትም ላይ እንደፃፈው፤ በ1985 ዓ.ም. ከደራሲ ስብሀት ገብረእግዚአብሄር ጋር በሆነ አጋጣሚ ተገናኝተው ሲያወሩ ስብሀት “በእናንተና በደርግ መሀል ያለውን ልዩነት ልትነግረኝ ትችላለህ?” ብሎ ይጠይቀዋል። አታክልቲም ሰፊ ልዩነት እንዳላቸው ዘርዝሮ አስረዳው። ስብሀት በፅሞና ካዳመጠው በኋላ ቀጥሎ ያለውን እውነት እንደነገረው አስፍሯል፤

“ለእኔ እንኳ በእናንተ እና በደርግ መሀል ያለውን ልዩነት ከምላጭ ስለት በላይ የቀጠነ ሆኖ ነው የሚሰማኝ፤ ሆኖም ግን አንተ እንዳልከው በህዝብ የስልጣን ባለቤትነት የምታምኑ ከሆነ የፓርላማው ወሳኝነት፣ የህግ ፈጻሚና የህግ ተርጓሚ ነጻነት መኖር እንዳለሆኖ ከፍተኛዋን የስልጣን መንበር የያዘው ሰው በእጁ ላይ ያለው ስልጣን የህዝብ መሆኑ አውቆ፣ በታማኝነት ጠብቆ ለሚቀጥለው ሰው በቀናነትና በክብር የሚያስረክብ ሰው እንዲሆን ለማድረግ ፅናቱን ይስጣችሁ።” ጋሽ ስብሀት ይሄን ከተናገረ ሃያ አንድ ዓመት አልፎታል።

No comments:

Post a Comment