Thursday, December 26, 2013

የቁጫ ህዝብ ጥያቄ የሚፈታው የዜጎች መብት ሲከበር ነው!! ከአንድነት ፓርቲ የተሰጠ ጋዜጣዊ መግለጫ

አንድነት ፓርቲ ልዩ ጠቅላላ ጉባኤውን ታህሳስ 19 እና 20/2006ዓ.ም ያደርጋል 

ኢህአዴግ በሚከተለው የዘረኝነት ፖሊሲና የከፋፍለህ ግዛው አገዛዝ መርህ ዛሬ በሃገራችን የአንድ አካባቢ ህዝብ በሌላው አካባቢ በነፃነት ሰርቶ የመኖር ህገ-መንግስታዊ መብት በገዢው ፓርቲ አመራር አባላት ሴራ ሲጣስ ይታያል፡፡ ባሳለፍናቸው አመታት በማንነታቸውና በእምነታቸው ምክንያት ሰብአዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶቻቸው ተረግጠው በአስርና በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ወገኖቻችን ተወልደው ወልደው ሃብት ንብረት ካፈሩበት መሬት ተፈናቅለውና በዚሁ ሳቢያ ለስደትና ለልመና የመዳረጋቸው ሚስጢር በማናቸውም መልኩ የኢህአዴግ አምባገነናዊ አገዛዝ ድምር ውጤት ነው፡፡

ካለፈው አመት መጨረሻ አካባቢ በደቡብ ክልል በጋሞ ዞን በቁጫ ወረዳ ህዝብና ነዋሪዎች ላይ እየደረሰ ያለውን እስራት፤ ስደት፤ ወከባና እንግልት እንዲሁም ሞት በተለያየ የመገናኛ ብዙሃን ድህረ ገፆች መረጃው በስፋት መቅረቡን ተከትሎ ፓርቲያችን በዚህ ጉዳይ ላይ የፖለቲካ አቅዋም ለመያዝ እንዲያስችለው አንድ በፓርቲው ከፍተኛ አመራር የሚመራ ቡድን ወደ ቦታው በመላክ የተሰበሰበውን መረጃ የፓርቲው ብሄራዊ ምክር ቤት ታህሳስ 13ቀን 2006ዓ.ም በጠራው አስቸካይ ስብሰባ በቁጫ ህዝብ ላይ እየደረሰ ያለውን የፖለቲካ አለመረጋጋት መርምሮ ውሳኔ አስተላልፉዋል፡፡


የቡድኑ የመስክ ጉብኝት መረጃ እንዳመለከተው የቁጫ ህዝብና ነዋሪዎች ጥያቄ ማቅረብና ህዝባዊ የተቃዉሞ እንቅስቃሴ የጀመሩት በወረዳዉ ምንም አይነት ልማትና ህዝቡም በፖለቲካውና በኢኮኖሚው ዘርፍ ለመሳተፍ የተሰጠው እድል ዝቅተኛ ወይም የለም በሚል ቁጭት ደረጃ በደረጃ የመብት ጥያቄ በማንሳት ነው፡፡ በተለይ ከሰኔ ወር 2005ዓ.ም ጀምሮ የህዝቡ ብሶት እየተባባሰ በመምጣቱ መንግስት ተመጣጣኝ ያልሆነ ኃይል እርምጃ መውሰዱ በሪፖርቱ ተመልክቱዋል፡፡ 1015 የሚሆኑ ሰዎች በወረዳው ፖሊስ ጣቢያ፤ በአርባ ምንጭና በጨንቻ ወህኒ ቤቶች መታሰራቸው፤ አቶ ዛራ ዛላ የተባሉ የሁለት ልጆች አባት ህዳር 14ቀን 2006 ኮዶ ኮኖ ቀበሌ ውስጥ በጥይት ተመተው ሞተዋል፤ ሰውየው በጥይት ሲመቱ በቦታው የወረዳው አስተዳዳሪ አቶ ሶጋት ሳንታ፤ አቶ አሸብር ደምሴ የገዢው ፓርቲ የወረዳው ድርጅት ጉዳይ ሃላፊ እና አቶ አያኖ መሰና የወረዳው የፀጥታ ሃላፊ መኖራቸው ደግሞ የመንግስት ኃላፊዎችን ተባባሪ ወይም አስተኩዋሽ ያደርጋቸዋል፡፡ ከዚህም በቀር ህዝቡ በገዢው ፓርቲ ካድሬዎችና ፀጥታ ኃይሎች ማስፈራራት፤ ማዋከብና ሰርቶ የመኖር ነፃነቱ እንደሌለው እንዲሁም ያለመረጋጋትና የፀጥታ ስጋት ስላለ በርካታ ሰዎች ወደ ጎረቤት አካባቢዎች እየተሰደዱ መሆናቸውን ሪፖርቱ ይገልፃል፡፡

በተጨማሪም የወረዳው ህዝብ በሚጠራባቸው ስብሰባዎች ሁሉ የአንድነት ፓርቲ በወረዳው የዘረጋው ጠንካራ መዋቅር እንዲበተን በአንዳንድ የስብሰባው ተካፋዮች “አንድነት ፓርቲ እያለ ልማት አይኖርም፤ እንዴት አንድነትን መንቀል አቃታችሁ፤ የእኛው አካባቢ የፓርቲውን ሰዎች እንዴት ይዛችሁ ማሰር አቃታችሁ” የሚል አስተያየት በተሳታፊዎች የቀረበ በማስመሰል ኢህአዴግ የተለመደውን ድራማ እየሰራ ስለመሆኑ በቡድኑ ሪፖርት ተመልክቱዋል፡፡

እንዲሁም የልዑካኑን መሪ አቶ ትዕግስቱ አወሉ የብሄራዊ ምክር ቤት ዋና ጸሃፊን ጨምሮ ሰባት አባላት “እንዴት መጣችሁ፤ መንግስት በፀጥታ ችግር ላይ ነው፤ ይህንን ለመፍታት በሚደረገው ታላቅ ህዝባዊ ኮንፈረንስ እለት መገኘታችሁ አፋራሽ ተልእኮ ይዛችሁ የመጣችሁ ሰለሚሆን እንጠረጥራችኃለን” በሚል በፖሊስ ቁጥጥር ስር ከአራት ሰዓት በላይ በማዋል በፀጥታ ኃይሎች የማዋከብ ተግባር ተፈፅሞባቸዋል፡፡ የአንድነት ፓርቲ ብሄራዊ ምክር ቤቱ በቀረበው ሰፊ ሪፖርት ላይ ውይይት ካደረገበት በኃላ የሚከተለውን የፖለቲካ ውሳኔ አስተላልፉዋል፡፡

1. በቁጫ ህዝብ ላይ እየደረሰ ያለው የሰብአዊ መብት ረገጣ በአስቸካይ እንዲቆምና ስለደረሰው ሰብአዊና ቁሳዊ ጉዳት የሚያጣራ በገለልተነኛ ወገን እንዲጣራ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲወሰን፤
2. የቁጫ ህዝብ ጥያቄ የስራዓቱ አምባገነናዊነት እንዲቆም በመሆኑ የህገ መንግስታዊ መብቶቻቸው ተከብረው ከዚህ ጉዳይ ጋር በተያዘ የታሰሩት ዜጎች በአስቸካይ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ እንዲፈቱ፤
3. ቁሳዊና ስነልቦናዊ ጉዳት የደረሰባቸው ዜጎች የሞራል ካሳ እንዲሰጣቸው፤
4. በዜጎች ላይ ጉዳት ያአደረሱት ግለሰቦች ለህግ እንዲያቀርቡ፤
5. የገዢው ፓርቲ ካደሬዎች በየስብሰባው ፓርቲያችንን አሉታዊ በሆነ መልኩ ከመፈረጅ ይልቅ የዘጎችን ጥያቄ በህግና በዴሞክራሲያዊ መንገድ ለመፍታት መንግስት ጥረት ያድርግ፤
6. የቁጫ ወረዳ ተወላጅ የሆነው የፓርቲያችን ከፍተኛ አመራር አባላትን ማሳደድና ማወከብ እንዲቆም፤
7. ይህ ሁኔታ የማይሻሻል ከሆነ በመዋቅራችን በመጠቀም በከፍተኛ ሰላማዊ ሰልፍ ህዝባዊ ተቃውሞ ፓርቲው በአካባቢው እንደሚጠራ፤ የፓርቲያችን ብሄራዊ ምክር ቤት ወስናል፡፡

በዚህ ጋዜጣዊ መግለጫ ማንሳት የምንፈልገው ጉዳይ የኢህአዴግ አምባገነናዊ ስርአት በህዝብ ሙሉ ተሳትፎ በማስወገድ በአገራችን ዴሞክራሲያዊ ስርአት ለመገንባት አንድነት ፓርቲ እንደ አንድ የፖለቲካ አማራጭ ታግሎ ለማታገል ከተደራጀ አምስት አመት አልፎታል፡፡ በዚህ ጊዜ ውስጥ ታህሳስ 19እና20 2006ዓ.ም የሚደረገውን ስትራቴጂካዊ ጠቅላላ ጉባኤን ጨምሮ ሶስት ጠቅላላ ጉባኤዎችን አድርጉዋል፡፡

የአሁኑን ጉባኤ ከአንድ ወር በፊት ለማድረግ ታቅዶ ለስብሰባ የሚሆነንን አዳራሽ ለማግኘት ከፍተኛ ፈተና ገጥሞናል፡፡ የአዳራሾቹ አከራዮች በምንፈልገው ቀን አዳራሹ አለመያዙን ይነግሩንና ለአንድነት ፓርቲ ለስብሰባ ነው የፈለግነው ሲባሉ አንዳንዶቹ እንደውልላችኃለን ሲሉን አንዳንዶቹ ደግሞ በግልጽ “እንስራበት ተውን” ይሉናል፡፡ የምርጫ ቦርድን አዳራሽ እንካን ጠይቀን የተሠጠን ምልሽ “ለስልጠና ፕሮግራም ተይዞበታል” ነው የተባልነው፡፡ በመጨረሻ ፈቅደው ያከራዩን ሰዎችንም ቢሆን ከፍተኛ ጫና ተደርጎባቸዋል፡፡ ከዚህ ሁኔታ መረዳት የሚቻለው ገዢው ፓርቲ ተቃዋሚዎችን ፈርቶ የንግዱን ህብረተሰብ ማሸበር እንደሆነ ነው፡፡

በጉባኤችን እስከ 500 የሚደርሱ የድምፅ ተሳታፊዎች፤ እስከ 150 ሚደርሱ ተጋባዥ የፖለቲካ መሪዎችና እንግዶች እንዲሁም የሚዲያ ባለሞያዎች ይገኙበታል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ ጉባኤው የፓርቲውን ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ፤ የብሄራዊ ምክር ቤት አባላትን፤ የኦዲትና ቁጥጥር ኮሚሽን ሪፖርቶችን ያዳምጣል ውሳኔም ያስተላልፋል፡፡እነዲሁም የፓርቲውን ፐሬዚደንት፤ የብሄራዊ ምክር ቤትና የኦዲትና ቁጥጥር ኮሚሽን አባላትን ይመርጣል፡፡ የፓርቲውን ፕሮግራምና ደንብ የማሻሻያ ረቂቆችን መርምሮ ያፀድቃል፡፡ ሌሎች ከተሰናባቹ ምክር ቤት የሚቀርቡለትን የውሳኔ ሃሳቦችን መርምሮ ያፀድቃል፡፡

አንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ (አንድነት)

ታህሳስ 17ቀን 2006ዓ.ም

አዲስ አበባ

No comments:

Post a Comment