Sunday, January 19, 2014

ከመንግስትና ከህግ የበላይ ማነው?

ይህ ትዝብት እንጂ ጥያቄ አይደለም!

በዶ/ር በድሉ ዋቅጅራ

አንዳንድ አንባቢ የመጣጥፌን ርእስ ሲመለከት ጥያቄ ሊመስለው ይችላል፡፡ እኔ ግን አልጠየቅኩም፡፡ መላሽ በሌለበት ለራስ የቀረበ ጥያቄ ትዝብት እንጂ ጥያቄ አይደለም፡፡ የሰለቸው ጠያቂ ታዛቢ ይሆናል ብዬ ታዛቢ ሆኛለሁ፡፡ የትዝብት ዋናው ጥቅም መልስ አለማስናፈቁ ነው፡፡ ከዚህ ዋና ጥቅም የበለጠው ሌላው ዋናው ጥቅም ደግሞ ለህሊና ቁንጥጫ እንጂ ለታጣቂ እርግጫ አሳልፎ አለመስጠቱ ነው፡፡… እና እታዘባለሁ፤ መታዘብ ደልቶኛል፡፡

በጥንቃቄ ነው የምታዘበው፡፡ ከስሜታዊነት የራቀ ትዝብት ቆሽት አያሳርርምና ትዝብቴ ከስሜቴ እንዳይቀየጥ አብዝቼ እጥራለሁ፡፡ እናም መንግስታችንን ባቆመው ሳይሆን በጣሰው ህግ ታዘብኩት፡፡ እውነቴን ነው! መንግስት ህገ-መንግስት አርቅቆና በህዝብ አጸድቆ ሀገር ያስተዳድራል፡፡ በአብዛኛው ግን ህግ የሚጥሰው መንግስት ሆኖ በታየኝ ጊዜ ታዘብኩት፡፡ እዚህ ላይ መንግስት ማለት በየደረጃው የሾማችው ሙያተኞችና ባለስልጣናት ናቸው፡፡ ደግሞ ህግ ቆሞላቸዋል፤ እንዲጠብቁትና እንዲመሩበት፡፡ ብዙዎቹ ግን እኛ መንጋዎቹ የምናከብረውን ህግ፣ ከመጤፍ አይቆጥሩትም፡፡

መገናኛ ላይ አንድ ትራፊክ ፖሊስ ቀኑን ሙሉ ወደ ሲኤምሲ የሚሄድ ሚኒባስ ታክሲ እያስቆመ (አሳቻ ቦታ ተደብቆ) ትርፍ የጫኑትን በወረቀትና በጉቦ ሲቀጣ ውሎ፣ ማታ እራሱ በሞላ ታክሲ ላይ በትርፍነት ተሳፍሮ (ያውም በነፃ) ወደ ቤቱ ይሄዳል፡፡… ትራፊክ በሀሰት ቢከስና ቢያስቀጣ ምስክር አይጠየቅም፡፡ እንግዲህ መንግስትን እንደሰው ብናየው … ትራፊኩ የጣት ያህል ነው፡፡ ግን ቢሆንም ጣትነቱ ህግን የመሻር ‹መብት› ከመጎናፀፍ አላገደውም፡፡ … አንድ ትራፊክ ከፈለገ የተጨናነቀ የመሰለውን መንገድ ዘግቶ፣ ቤታችን መግቢያ ሊያሳጣን፣ ዙሪያ ገባ ሲያሽከረክረን ሊውል ይችላል፡፡ ስድብና ማመናጨቁንማ እዚያው ስልጠናው ላይ የሚማሩት ይመስለኛል፡፡ ህግ ያስከብረው ዘንድ ትራፊክን መንገድ ላይ አቆመ፡፡ መከበርን ያገኘው ግን ህጉ ሳይሆን ትራፊኩ ነው፡፡ አብዛኞቹ ህግ አስከባሪዎቻችን በህግ መከበርን አግኝተው ይኖራሉ፡፡ ግን ይህን በአንድ ሹመኛ ግለሰብ/ህግ አስከባሪ ላይ የሚታይ ከህግ ወጥቶ ህግን መብለጥ ኢህአዴግ አያውቅም? እርግጠኛ ነኝ ያውቃል! ታዲያ ስለምን ሉጋም አያበጁለትም? ብዬ ልጠይቅ አስብና ትውት አድርጌ፣ ‹‹አሁን ይሄ ህዝብ ገና ደጁ ላይ በትራፊክና በህግ አስከባሪ የጀመረው የህግ ጥሰት፣ ቀኑን ሙሉ በየመስሪያቤቱ ባለስልጣን ሲከመርበት አንጎሉ እየዞረ፣ በየመንገዱ ዳር በተዘጋጀለት ጉድጓድ እየተደነጎረ ጎረምሳው/ኮረዳይቱ ቢሰበሩ፣ ሽማግሌው/አሮጊቱ ቢሞቱ፣ ወይም ደግሞ፣ የመንዳት ፈቃድ እንጂ ችሎታ በሌለው ሰው በሚነዳ መኪና ቢዳጥ አያሳዝንም! በማለት ሀሳቤን የነፍስ ሙግት፣ ትዝብት አደርገዋለሁ፡፡ ለምን ቢሉ መልስ ያጣ ጠያቂ ታዛቢ ይሆናል፡፡


አራት ኪሎ፣ ከዩኒቨርሲቲው ፊትለፊት ጀምሮ እስከ ቅድስት ማርያም… አሁን ስድስት ኪሎም ደርሷል፤ አዲስ አበባ በየመንገዱ ዳር፣ ሲያሻው መንገድ ዘርግቶ፣ ድንኳን ተክሎ ይሸቅጣል- መንግስት፡፡ ለወደዳቸውም ይፈቅዳል፡፡ እዚህ ላይ (ካዛንችስ፣ ያሬድ ፊትለፊት - ወደ ምኒልክ ሆስፒታል በሚወስደው መንገድ ላይ…) የቅዳሜና የእሁድ የሰንበት የጎዳና ገበያዎችን ማለቴ አይደለም፡፡ እኔ የምለው ድርጅቶች የመንግስትን ፈቃድ አግኝተው የሚያደርጉትን የመንገድ ላይ ገበያና ኤግዚቢሽን ነው፡፡ ለምሳሌ የአዲስ አበባ ወጣቶች ሊግ፣ የምርጫ ቦርድ… አይቶቹ መንገዳችንን አጥረው የሃያ ደቂቃውን መንገድ አንድ ሰዓት ሊያስኬዱን ይችላሉ፡፡ የሚገርመው በሚቀጥለው ቀን በዚያው ቦታ ሱቅ በደረቴ አዟሪዎች፣ መንገዱ ዳር ዘርግተው ቀርቶ፣ ቆመው እንኳን መሸጥ አይችሉም፡፡ ፌደራል ፖሊሶች በቆመጥ እየቀለጠሙ ያባርሯቸዋል፡፡ የምርጫ ቦርድና የወጣት ሊግ በድንኳን የዘጋውን አስፋልትና የመንገድ ዳር፣ የትኛውም ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲ፣ ወይም አፍቃሪ ኢህአዴግ ያልሆነ ድርጅት ሊመኘው አይችልም፡፡ መንግስት ያደራጃቸው የጥቃቅንና አነስተኛ ወጣቶች በድንኳን የሚሸቅጡበት ጎዳና አንድና ሁለት ብር አትርፈው በልተው ለማደር ለሚማስኑ ሱቅ በደረቴዎች እርም ነው፡፡… ታዲያ እውነት ኢትዮጵያውያን በህግ ፊት እኩል ነን? ከፊሎች ህጉን ሲሸርፉ፣ ከፊሎቻችን ህጉ ይሸርፈናል፡፡ ከፊሎች በህጉ ስንመጻደቅ፣ ከፊሎቻችን እንሸማቀቅበታለን፡፡ አንድ መንግስት በዜጎቹ ላይ ይህን ለመፈፀም እንደምን ያስችለዋል? በየፍርድ ቤቱ የምንጮህበት የፍትህ መጓደል፣ ጎዳና ላይ ሲሰጣ ከማየት የሚልቅ ምን አለ? ብዬ በቁጭትና ስሜት የታጨቁ፣ የህግ ጥሰት የወለዳቸውን ጥያቄዎች አስብና እተወዋለሁ፡፡ ምክንያቱም እኔ ታዛቢ እንጃ ጠያቂ አይደለሁም፡፡ ግን እውነት፣ ኢህአዴግ ሆይ! የአንድ አባትና እናት ልጆችን ለአንዱ በጥቃቅን በመደራጀቱ መነሻ ገንዘብና መቸርቸሪያ ጎዳና መሰጠት፣ ለሌላው በተማሰለት ቦይ ባለመፍሰሱ፣ መደራጀት ፈቃዱ ባለመሆኑ፣ ወይ እድሉን ባያገኝ የጎዳና ፍሽታ አድርጎ በፖሊስ እያሳደዱ፣ ፈጣሪ የከፈተውን ጉሮሮ እሱ እንዳይዘጋው ማድረግ እውን ለዜጎች ሁሉ እኩልነት ከቆመ፣ ለዚህም ማረጋገጫ ህዳር ሃያ ዘጠኝን ከሚያከብር መንግስት ይጠይቃል!... እታዘባለሁ፡፡ ምክንያቱም እኔ ታዛቢ እንጂ ጠያቂ አይደለሁም፡፡ ብጠይቅ መልሱ አንድም ሰደፍ፣ አንድም እስር ሊሆን ይችላል፡፡ ከዛሬ ሃያ አመት በፊት ጠይቄ የሰደፉንም፣ የእስሩንም መልስ ችየዋለሁ፡፡ ዛሬ ለሰደፉ ትከሻ፣ ለእስር እድሜ የለኝም፡፡… እና አልጠይቅም፤ እታዘባለሁ፡፡

ከላይ የጻፍኩትን አይነት የጎዳና ህግ የመጣስ ተግባራትን ስለመለከት፣ ጎዳና ትምህርት ቤት መንግስት አስተማሪ ይመስኛል (ይህ ግንዛቤ የመጣው ከሃያ አመት በዘለለ የመምህርነት ሙያዬ የተነሳ ሊሆን ይችላል)፡፡ ጎዳና ትምህርት ቤት ነው፡፡ ድንኳን የሚፈቀድላቸው፣ መንገድ የሚዘጋላቸው ደግሞ፣ ፈቅደው ከጎዳና ትምህርት ቤት የገቡ ተማሪዎች ናቸው፤ መንግስት ነው አስተማሪው፤ ትምህርቱ ደግሞ የህግ ጥሰት ነው፡፡ በዚህ ትምህርት ቤት ጥቂት ተማሪዎች ብዙ ህዝብ የሚተላለፍበትን አስፋልት ዘግተው፣ ፓርኪንጉን ሞልተው የዜጎችን እለታዊ ኑሮ ማወክን ይማራሉ፡፡ የሚገርመው ግን እራሱ መንግስት በተግባር ያስተማረውን የህግ ጥሰት፣ ከተማሪዎቹ በስተቀር ማንም እንዲማረው አይፈቀድም፡፡ ሰኞ መንግስት ድንኳን ባቆመበት ቦታ ማክሰኞ ድንኳን ብንተከል ድንኳኑ ብቻ ሳይሆን እኛም እንነቀላለን፡፡ የመንግስት ህግን መተላለፍ ልማታዊ ዜና፣ የሀገር ኢኮኖሚ እድገት ነው፡፡ የእኛ ተመሳሳይ ተግባር ወንጀል ነው፤ የፖሊስ ኮሚሽነሩ መግለጫ ሊሰጡበት፣ የኮሙኒኬሽን ባለሙያዎች ዘጋቢ ፊልም ሊሰሩበት ይችላሉ፡፡

ግን መንግስት ህግን የመጣስ ‹ማንዴት› ተሰጥቶታል? ዜጎች ለመንግስት የሚሰጡት ተፈጥሯዊ ‹ማንዴት› አለ፤ ይህ ማንዴት ህግን የማስከበር፣ የዜጎችን እኩልነት በህግ ፊት ማረጋገጥ ነው፡፡ ቆይ መንግስት በስራ ደክመን ወደቤታችን ስንሄድ፣ በትራፊኩ መጨናቅ፣ በታክሲ መጠበቅ ያረረ አንጀታችንን ‹ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ አምባሳደሩ፣ ፕሬዚዳንቱ . . . . ሊያልፉ ነው› እያለ ሊበጥሰው ይገባል! (በነገራችን ላይ ይህ ትዝብት ነው)፡፡ አገር ሰላም ብለን፣ የተፈቀደ የመኪና ማቆሚያ ላይ መኪና አቁመን በገባንበት፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዚያ ሲያልፉ ባለመገኘታችን፣ ታርጋ ተፈቶ፣ መኪና ተጎትቶ፣ እንደ ህግ ተላላፊ መቀጮ ሊጣልብን ይገባል! ቆይ እዚች ነጥብ ላይ ህግ ያፈረሰው እኛ ወይንስ ህግ አስከባሪው (መንግስት)?... ይህ ጥያቄ ነውና ትቸዋለሁ፡፡

ለመሆኑ ለአንድ ሀገር ዜጋ ‹መንግስቴ› የሚለው አስተዳዳሪው ባሻው ጊዜ፣ ስለምንም ምክንያት ህግን የሚጥስ ወይም እንዲጣስ የሚፈቅድ መሆኑን አውቆ/አምኖ ከመኖር የበለጠ የሚያሸማቅቅ ነገር አለ? በመንግስቱ ህጋዊነት የማይደሰት ዜጋ እርምጃው የተሰነከለ አይደለምን? ህጉ ኮርኩሞ የሚያስለቅሳቸውና ኮርኩሮ የሚያስቃቸው ዜጎች ያሏት ሀገርስ ልማቷን እንደምን ታሳልጣለች? በህግ ፊት እርኩስና ንጉስ ዜጋ አለን?... የመንግስትን ከህግ በላይ መሆን ሳስብና በስሜት ስብከነከን በርካታ ጥያቄዎች ህሊናዬን ይርመሰመሱበታል፡፡ ይሁን እንጂ ትኩረት ሰጥቼ፣ ለአንደበት አብቅቼ አልጠይቅም፡፡ ምክንያቱም እኔ ታዛቢ እንጂ ጠያቂ አይደለሁም፡፡ የሰለቸሁ ጠያቂ ነኝ፡፡ የሰለቸው… ያልተመለሰለት ጠያቂ ደግሞ ይታዘባል እንጂ አእምሮውን በጥያቄ፣ አንጀቱን ባረቄ እንዳሳረረ አይኖርም፡፡

No comments:

Post a Comment