Saturday, January 25, 2014

ሰማያዊ ፓርቲ በኢትዮ-ሱዳን ድንበር ላይ በጎንደር ሰላማዊ ሰልፍ ሊያደርግ ነው


በመስከረም አያሌው

ሰማያዊ ፓርቲ መንግስት በኢትዮ-ሱዳን ድንበር ላይ ለህዝቡ ግልፅ የሆነ መረጃ እንዲሰጥ ግፊት ለማድረግ በጎንደር ከተማ ሰላማዊ ሰልፍ ለማካሄድ የማሳወቂያ ደብዳቤ ለጎንደር ከተማ ማዘጋጃ ቤት ማስገባቱን ገለፀ።

የፓርቲው የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ብርሃኑ ተ/ያሬድ ትላንት ለሰንደቅ ጋዜጣ እንደገለፁት ሰላማዊ ሰልፉ የሚደረገው ሱዳን ትሪቡዩንን ጨምሮ የተለያዩ የመገናኛ ብዙሃን የኢትዮጵያ መንግስት ለህዝቡ ግልፅ ባልሆነ፣ በታሪክም ሆነ በባህል ከህዝቡ ጋር ባልተገናኛ መልኩ ታሪካዊ የሆኑ ቦታዎችን ጭምር ለሱዳን አሳልፎ ለመስጠት መስማማቱን እየዘገቡ በመሆኑ መንግስት ግልጽ የሆነ መረጃ እንዲሰጥ ግፊት ለማድረግ ነው።

“እነሱ የሚሉት መልሶ መከለል (Re demarcation) ነው። እኛ ደግሞ ከዚህ በፊት የተከለለ ነገር የለም። አሁን ሲከለል 40 ኪ.ሜ ወደ ውስጥ የኢትዮጵያ ግዛት ይነካል። ግዛቱን መንካት ብቻም ሳይሆን፣ የኢትዮጵያን ታሪካዊ እና ከህዝቡ ጋር የተቆራኙ ቋራን የመሳሰሉ ግዛቶችን ወደ ሱዳን እንደሚከለሉ የኛ መረጃ ያመለክታል እያልን ነው” ያሉት አቶ ብርሃኑ፣ ይህን ጉዳይ መንግስት ግልጽ እንዲያደርግ በማሰብ በተለያዩ ክልሎች ሰላማዊ ሰልፍ ለማድረግ ማሰባቸውን ገልጸዋል።

ፓርቲው የመጀመሪያውን ሰላማዊ ሰልፍ የፊታችን ጥር 15 ቀን 2006 ዓ.ም በጎንደር መስቀል አደባባይ ለማድረግ ያቀደ ሲሆን፣ በሰልፉ ላይም የተለያዩ ጥያቄዎች ይነሳሉ። የመጀመሪያውም መንግስት ጉዳዩን ለህዝብ ግልፅ አድርጎ ከህዝቡ ጋር ውይይት እንዲያደርግ ሲሆን፣ ሁለተኛው ደግሞ የኢትዮጵያ ታሪካዊ ግዛቶች ከጫካ ውል ተነስቶ ያለምንም ታሪካዊ መሰረት ለሌላ ሀገር መስጠቱን ፓርቲው እንደሚቃወመው መግለፅ መሆኑን አቶ ብርሃኑ ገልፀዋል።


የሰላማዊ ሰልፉ ዋና ዓላማ ሰማያዊ ፓርቲ የኢትዮጵያን መሬት ቆርሶ መስጠቱን እንደሚቃወም ማሳየት እንደሆነ የገለፁት አቶ ብርሃኑ፤ “መንግስት ከኢትዮጵያ መሆኑ ላይ ቆርሶ የመስጠት ስልጣን (mandate) የለውም። እንደሚባለው በትክክለኛ መንገድ የሱዳኑ መሬት ከሆነ እየተከለለ ያለው ለህዝቡ ግልፅ አድርጎ እና ህዝቡን አወያይቶ መደረግ አለበት ብለን ነው የምናምነው” ብለዋል። ለህዝብ ግልፅ በማድረግ ፈንታ በድብቅ የኢትዮ-ሱዳን ድንበር ኮሚቴ መቋቋሙን ከዚህ በፊት ም/ጠቅላይ ሚኒስትሩን ጨምሮ የተለያዩ ባለስልጣናት መግለፃቸውን የገለፁት አቶ ብርሃኑ፤ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርም በ2002 ዓ.ም ባወጣው መግለጫ ይሄንኑ ያረጋገጠ በመሆኑ ይህ ጉዳይም ግልፅ መደረግ አለበት ብለዋል።

ይህ የተቋቋመው አካል ማን እንደሆነ፣ በየትኛው መስሪያ ቤት ስር እንዳለ እና የመሳሰሉን ጉዳዮች መንግስት ለህዝብ ግልጽ ማድረግ እንዳለበትም በሰላማዊ ሰልፉ ላይ ይነሳል። ይህ መሬትን ቆርሶ መስጠት የሉአላዊነት ጉዳይ በመሆኑ ድርጊቱን ከመቃወም በተጨማሪም የተቻለውን ሁሉ ለማድረግ በዝግጅት ላይ መሆናቸውን ነው አቶ ብርሃኑ የገለፁት።

የመሬት ጉዳይ የአጠቃላይ ህዝብ ጉዳይ ቢሆንም የመጀመሪያውን ሰላማዊ ሰልፍ በጎንደር ማድረግ ያስፈለገው ጎንደር ይከለላል ለተባለው ቦታ ካላት ቅርበት የተነሳ ህዝቡ በወታደር እየደበደበ እንዲነሳ እየተደረገ እንዲሁም ከሱዳን ገበሬዎች መሬት ተከራይቶ እንዲያርስ እየተደረገ መሆኑን ከአካባቢው ካሉ የፓርቲው መዋቅሮችና በተደረገ ጥናት የተረጋገጠ በመሆኑ ህዝቡ ግልፅ መረጃ ኖሮት እንዲታገል ለማድረግ በማሰብ እንደሆነ ተገልጿል። ሰላማዊ ሰልፉ ሲደረግም በአካባቢው ያለውን ህዝብ ለማንቃት እና መረጃውን በተጠናከረ መልኩ ለህዝብ የሚደርስ ስራ ይሰራል። የጎንደር ህዝብ ለጉዳዩ ቅርብ እንደመሆኑ እና ጉዳዩን ስሚያውቀው ወደ ሌሎች ክልሎችም ለመንቀሳቀስ እንደመነሻ እንደሚጠቅም ተገልጿል።

የድንበር ክለላው ጋምቤላ፣ ደቡብ እና ሌሎች ክልሎችንም የሚነካ በመሆኑ በቀጣይም በእነዚህ ክልሎች ተመሳሳይ ስራዎችን በመስራት በፌዴራል ደረጃ ትልቅ የተቃውሞ ፕሮግራም በማዘጋት የፓናል ውይይቶች፣ የፊርማ ማሰባሰብ እና ሰላማዊ ሰልፎችን ለማካሄድ ታቅዷል።

የሰላማዊ ሰልፍ ማሳወቂያ ደብዳቤውን ትናንት ለጎንደር ከተማ ማዘጋጃ ቤት ማስገባታቸውን የገለፁት አቶ ብርሃኑ፣ ሰልፉን
ሊያካሄዱ ባቀዱበት እለት ምንም አይነት አንገብጋቢ ጉዳይ አለመኖሩን ማጣራታቸውንና ቀን ሊያስቀይራቸው የሚችል ምክንያት ይኖራል ብለው እንደማያስቡም አያይዘው ገልፀዋል።

No comments:

Post a Comment