Saturday, January 18, 2014

“የግንቦት 20 ፍሬን የምንለካው ኢህአዴግ በሰላማዊ መንገድ ከሥልጣን ሲወርድ ነው”


ጭቆና ትግልን ያጠነክራል እንጂ አይገድልም...
ኢህአዴግን በምርጫ ለማሸነፍ የአንድ ወር ሥራ በቂ ነው….
ኢህአዴግ ሁልጊዜ የትግራይ ህዝብ በስጋት እንዲኖር ነው የሚፈልገው

 በቅርቡ ለፓርቲዎች የውህደት ጥያቄ አቅርባችኋል፡፡ ለየትኞቹ ፓርቲዎች ነው ጥያቄውን ያቀረባችሁት? መስፈርታችሁስ ምን ነበር? እኛ እንግዲህ ያሰብነው በመድረክ ውስጥ ካሉት ፓርቲዎች ጋር ውህደት ለመፈፀም ነው፡፡ ግን ከመድረክ ውጪም ቢመጣ ችግር የለብንም፡፡ እንግዲህ በጠየቅናቸው ፓርቲዎች ሙሉ ፈቃደኝነት በቅርቡ ከግንባር ወደ ውህደት እንሄዳለን የሚል እምነት ነው ያለኝ። ጥያቄውን ለኦፌኮ፣ ለአንድነት እና ለደቡብ ህብረቶች አቅርበናል፡፡ እነሱም በጐ ምላሽ እየሰጡን ነው፡፡ ውህደት የተጠየቁት ፓርቲዎች የመድረክ አባል ከሆኑ ለምን ራሱን መድረክን አልጠየቃችሁም? ፓርቲዎቹን በተናጠል መጠየቅ ለምን አስፈለገ? ሁለት አቅጣጫ ነው ያለው፡፡ እንዳልከው በቀጥታ መድረክንም መጠየቅ ይቻል ነበር፤ ግን በተናጠል የመጠየቁን መንገድ ነው የመረጥነው፡፡ ይሄን ጥያቄ ያነሳሁት “አረና በመድረክ ላይ እምነት የለውም” የሚሉ አስተያየቶች ስለሚሰነዘሩ ነው… በተናጠል መጠየቁን በመድረክ ህልውና ካለማመን የመጣ ነው የሚሉ ወገኖችም አሉ… እኛ እኮ ሁሉንም ነው የጠየቅነው፡፡ ነጥለን የተውነው ፓርቲ ቢኖር ሊያስብል ይችላል፡፡ ግን የጠየቅናቸው በአጠቃላይ በመድረክ ውስጥ ያሉትን ነው:- አረና፣ ኦፌኮ፣ አንድነት እና የደቡብ ህብረት፡፡ አረና ተነሳሽነቱን ወስዶ ነው የእንዋሃድ ጥያቄውን ያቀረበው፡፡

ስለዚህ መድረኩን አይፈልጉትም የሚያስብል ሁኔታ አይፈጥርም፡፡ ይሄኛውን መንገድ መምረጣችን ብዙም ችግር አለው ብዬ አላስብም፡፡ ለውህደቱ ጥያቄ መነሻችሁ ምንድን ነው? እንዴትስ ይሄኛውን ጊዜ መረጣችሁ? ምናልባት ምርጫውን አስባችሁ ይሆን? እኛ የተቋቋምነው በክልላዊ ፓርቲነት ነበር፡፡ ህወኃት ቅድሚያ ለትግሬነት ስለሚሰጥ ነው እኛም በክልላዊ ፓርቲነት የተቋቋምነው፡፡ በቀላሉ ተቀባይነትን ለማግኘት በመሻት ነው እንጂ የአረና የመጀመሪያ አላማው ሀገራዊ እሳቤን ያዘለ ነው፡፡ ክልላዊነታችን የአጀማመር ጉዳይ ነው እንጂ ለዘለቄታው ያነገብነው አላማ ሀገራዊነትን ነው፡፡ ከሌሎች ፓርቲዎች ጋር ውህደት መፍጠራችንም ሀገራዊ አላማ አንግበው የሚታገሉ ፓርቲዎች፣ በትግራይ ህዝብ በቀላሉ ተሰሚነት እንዲያገኙም አጋዥ ይሆናል የሚል እምነት አለኝ፡፡ ለዚህች ሀገር ሁነኛ መፍትሄ የሚሆነው ትግራይ ለብቻው፣ ኦሮሞው ለብቻው፣ አማራው ለብቻው፣ ሌላውም ለብቻው ሊታገል ሳይሆን ሁሉም በአንድነት ተዋህዶ ተስማምቶ ሲታገል ነው፡፡


እኛ ኢህአዴግ በህገ መንግሥቱ አንቀፅ 39 ያስቀመጠውን የመገንጠል መብት እንቃወማለን፡፡ መነሻችን ለጊዜው ክልላዊ ይሁን እንጂ ይሄም ያስቀመጥነው አላማ ሀገራዊነት ነው፡፡ አረና በህወሐት ውስጥ የተፈጠረውን አለመግባባት ተከትሎ በተፈጠረ የግለሰቦች ኩርፊያ የተመሰረተ እንጂ ከህወሓት የተለየ አጀንዳ የለውም የሚሉም አሉ፡፡ ይሄን እንዴት ያዩታል? ይሄን የሚለው ፓርቲው ውስጥ ያሉትን አባላት ማየት ያልቻለ ሰው ይመስለኛል፡፡ በሚዲያም ብዙ ጊዜ ወጣቶቹ አይወጡም፡፡ እኔ በፊት የህወሓት አባል አልነበርኩም፡፡ ብዙዎቹም አባል ያልነበሩ ናቸው፡፡ እነ አቶ ገብሩ ደግሞ ከህወሐት ጋር መሰረታዊ ልዩነት አላቸው፡፡ ያንን ልዩነታቸውን በግልፅ አስቀምጠው ነው የወጡት፡፡ ፓርቲ ያቋቋሙት ስላኮረፉ ነው ማለት ከባድ ነው፡፡ ስንት ሰዎች ናቸው ያኮረፉት? አቶ ገብሩ፣ ወ/ሮ አረጋሽና አቶ አውአሎም ናቸው፡፡ ግን እኮ እነዚህ ግለሰቦች ናቸው የፓርቲው ጠንሳሾችና መስራቾች። እነዚህ ሰዎች ደግሞ በኢህአዴግ የብሄር ፌደራሊዝም፣ የመሬት ፖሊሲና በመሳሰሉት የሚያምኑ ናቸው፡፡ በወቅቱ የልዩነታቸው አንዱ መነሻ በኤርትራ ላይ የተያዘው አቋም ነው፡፡

ፓርቲውን ካቋቋሙ በኋላ ከህወሓት ጋር ያላቸውን ልዩነት በነጥብ ማስቀመጥ ይቻላል? በመሰረቱ ከህወሓት ለመለየት ተብሎ የብሄር ፌደራሊዝም ትክክለኛ አይደለም፣ ከህወሐት ለመለየት ተብሎ የብሄር ብሄረሰብ መብት አይከበርም ማለት ተገቢ ነው ብዬ አላምንም፡፡ ለልዩነታችን መነሻ ከሆኑት መካከል ለምሳሌ የአሰብ ወደብ ጉዳይ አለ፡፡ በሰላማዊ መንገድ መንግሥት መቀየር በሚለውና በዲሞክራሲና ሰብአዊ መብቶች ላይ ልዩነት አለን፡፡ ህወሓት ትልቁ የታገልንለት አላማ አንቀፅ 39 ነው ይላል፡፡ እሱ አንቀፅ ይሻሻል ሲባል ግን ህገ መንግሥቱ አይሻሻልም ይላል፡፡ ይሄ በፖለቲካ ስርአት ውስጥ ያልተለመደ ነው፡፡ እኛ ህገ መንግስቱ መሻሻል እንዳለበትና መሻሻልም እንደሚችል እናምናለን። በተቃራኒው ህወሐት ህገ መንግስቱ ፈፅሞ መሻሻል እንደማይችል ያምናል፡፡ በኢኮኖሚው አካሄድ ላይም ልዩነት አለን፡፡ እኛ ቅይጥ የሚለውን የኢኮኖሚ ስልት ሀገሪቱ መጠቀም አለባት እንላለን፡፡ እነሱ አንዱን መስክ መሪ፣ ሌላውን ተመሪ አድርገው ያስቀምጣሉ፡፡ በመሬት ፖሊሲው ላይም ልዩነት አለን፡፡ እኛ መሬት የመንግስት ሆኖ ከግለሰቡ ጋርም የጋራ የሚሆንበት መንገድ አለ ብለን እናምናለን፡፡ በፖለቲካ አካሄዳችን ደግሞ የስልጣን ገደብ ሊኖር ይገባል እንላለን፡፡ አንድ ጠቅላይ ሚኒስትር ሀገር እየመራ የሚሞትበት ስርአት መቀጠል የለበትም ባይ ነን፡፡ በብሄር ፌደራሊዝም ላይ ያላችሁ አቋምስ? እኛ በብሄር ፌደራሊዝም አናምንም፤ ነገር ግን ፌደራሊዝም ለዚህች ሀገር ይጠቅማል የሚል እምነት አለን፡፡

ምን አይነት ፌደራሊዝም ይሁን በሚለው ጉዳይ አቋም ላይ አልደረስንም፤ ነገር ግን ያለውን ነባራዊ ሁኔታ እያዩ ማስተካከል ይቻላል የሚል እምነት አለን፡፡ በፕሮግራማችን ፌደራሊዝም ለኢትዮጵያ እንደሚጠቅም ያለጥርጥር አስቀምጠነዋል፡፡ የውህደት ጥያቄ ካቀረባችሁላቸው ፓርቲዎች መካከል የፌደራሊዝም አስፈላጊነት ላይ ጥርጣሬ ያላቸው አሉ፡፡ ከነዚህ ፓርቲዎች ጋር ይህን አቋማችሁን እንዴት ነው የምታስታርቁት? በእርግጥ አንዳንዶች የሚያስቀምጧቸው ሃሳቦች አሉ፡፡ ይህን እንግዲህ ወደፊት በውይይት የምንፈታው ነው የሚሆነው፡፡ ለምሳሌ አንድነት የተወሰነ የሄደው ነገር አለ፡፡ የቡድንና የግለሰብ መብትን ሳይነጣጠሉ ማስከበር የሚለውን እንደተቀበሉ አውቃለሁ፡፡ ይህን ሲቀበሉ እስከምን ድረስ ነው የሚለው እንግዲህ ሌላ ውይይት የሚያስፈልገው ነው፡፡ ነገር ግን አንድ ሰው በቋንቋው የመፃፍ፣ የማንበብ፣ የመማር መብቱ ከተረጋገጠለት የቡድን እና የግል መብት የሚባለው ከዚህ በላይ ትርጉም ይኖረዋል ብዬ አላምንም፡፡ እንደ ግለሰብ መብቱ ይከበርለታል፡፡ እንደ ቡድንም እንግዲህ የዘር ልዩነት ሳይሆን የቋንቋ ልዩነት ብቻ ነው ሁላችንም ያለን፡፡ ስለዚህ አንድ ሰው በቋንቋው ከተማረ፣ በቋንቋው መተዳደር ከቻለ፣ መብቱ ከተከበረለት ሌላ ምን ይፈልጋል፡፡ ከዚህ በፊት በመድረክ ስብስብ ውስጥ በመካተታችሁ “የነፍጠኛ ስርአት አቀንቃኞችና ተላላኪዎች” በሚል ስትፈረጁ ነበር፡፡ አሁን ደግሞ ውህደት ካልፈፀምን እያላችሁ ነው፡፡

ውህደቱ ለበለጠ ፍረጃ አይዳርጋችሁም፡፡ በፖለቲካ እንቅስቃሴያችሁ ላይስ ተፅእኖ አይፈጥርም? ከነፍጠኛ ስርአት ናፋቂዎች ጋር እየሰራችሁ ነው የሚባለውን እኛ ሚዲያ ባለማግኘታችን ነው እንጂ ማስረዳት እንችላለን፡፡ እኩል የሆነ የኤሌክትሮኒክስ ሚዲያ እድል ቢከፈት፣ በእርግጠኝነት የኛ ሃሳብ የበላይ ይሆን ነበር፡፡ ከአንድነት እና ከሌሎች ጋር መስራታችንን እንደ ነፍጠኛ ስርአት ናፋቂነት እየቆጠረ፣ እራሱ አማራውንና ኦሮሞውን እንወክለዋለን ከሚሉት ጋር እየሰራ፣ ራሱን ለትግራይ ህዝብ ታማኝ እንደሆነ አድርጐ ማቅረቡ ስህተት ነው፡፡ ይህን ስህተቱን ግን ሚዲያ በመከልከላችን ለህዝቡ ማስረዳት አልቻልንም፡፡ እንዲህም ሆኖ ግን ሲመሰረት ቅዠት ነው የተባለው አረና፤ ጫናውን ሁሉ ችሎ ዛሬ ተቀባይነትን በስፋት እያገኘ ነው፡፡ መጀመሪያ በክልሉ ግዙፍ ነኝ ከሚለው ህወሐት ጐን የሚቆም ተገዳዳሪ ፓርቲ ማፍራት መቻሉ ተረጋግጧል፡፡ አሁን ደግሞ ሀገራዊ ሆኖ የበለጠ ተወዳዳሪነቱ የሚጨምር መሆኑን አባሎቻችንን አሳምነን እየተንቀሳቀስን ነው፡፡ እና ለውህደት ከጋበዝናቸው ፓርቲዎች ውስጥ ደግሞ እንዳለፉት ስርአቶች በቋንቋህ መናገር፣ መግባባት፣ መማር አትችልም የሚል አቋም ያላቸው የሉም፡፡ ስለዚህ እነዚህ ሃይላት ለኢትዮጵያ ፖለቲካ አስጊ ናቸው ብዬ አላምንም፡፡ ይልቁኑ አስጊ የሚሆኑት ህወሐት እና ኢህአዴግ ናቸው፡፡ ህወሐት ትግሉ መካን እንዲሆን ጠንክሮ እየሰራ ነው ብዬ አምናለሁ። የትግራይ ህዝብ በሌላው ተገዝቷል፣ በተራውም ገዝቶ ያውቃል፣ አሸንፎ ያውቃል፤ ተሸንፎም ያውቃል፤ ያ እንግዲህ በጦርነት የታየ ነው፡፡

ዛሬ ግን የሚያስፈልገው ሰላማዊ ትግል ነው ተብሎ እስከታመነበት ድረስ ለሰላማዊ ትግሉ በር የመክፈትና ሜዳ የማመቻቸት ተነሳሽነቱን ሊወስድ የሚገባው ህወሐት-ኢህአዴግ ነው፡፡ በሀገር ውስጥም ሆነ በውጭ ካሉት የሰላማዊ ትግል አቀንቃኝ ፓርቲዎች የበለጠ ለዚህች ሀገር ስጋት የሚሆነው ኢህአዴግ ነው፡፡ የዚህች ሀገር ትልቁ ስጋት ኢህአዴግ ነው፡፡ ለትግራይ ህዝብ ይሄን ማስረዳትና ማሳመንም ቀላል ነው፡፡ በየመግለጫዎቻችሁ ኢህአዴግ አላፈናፍን ብሎ መንቀሳቀስ እንዳልቻላችሁ ትናገራላችሁ፡፡ በሌላ በኩል በትግራይ ህዝብ ሰፊ ተቀባይነት አግኝተናል ትላላችሁ፡፡ እንደውም በጥቂት ቀናት ቅስቀሳ ብቻ በምርጫ ኢህአዴግን ከስልጣን ልናወርደው እንችላለን ብላችኋል። እነዚህን ሃሳቦች እንዴት ነው ማስታረቅ የሚቻለው? እንግዲህ ኢህአዴግ ሁልጊዜ የትግራይ ህዝብ በስጋት እንዲኖር ነው የሚፈልገው፡፡ ከሌላው ህዝብ ተነጥሎ ፈርቶ እንዲኖር ነው የሚፈልገው፡፡ ኢህአዴግ ከሌለ የትግራይ ህዝብ እንደማይኖር አድርጐ ነው የሚቀሰቅሰው፡፡ በውስጥ ደግሞ የአረናን አባላት ለማጥላላት “አሸባሪ ናቸው፤ ከነፍጠኛ ጋር ነው የሚሰሩት፤ አኩርፈው ነው እንጂ የተለየ አጀንዳ የላቸውም” የመሳሰሉትን እያለ በፓርቲያችን ላይ ዘመቻውን ያጧጡፋል፡፡ ይህን አላምንም ያለውን ደግሞ በግልፅ ያስራል፡፡ አባሎቻችን በየጊዜው እየተሸበሩ ነው፡፡ ይታሠራሉ፣ ይገረፋሉ፣ አካላቸው ይጐድላል፡፡ ባስ ሲልም በ2002 ምርጫ ያጋጠሙ አይነት የአባላት ግድያ አለ፡፡ እኛ ግን ይህ በደል ስለደረሰብን እጃችንን አጣጥፈን አልተቀመጥንም፡፡

ትግሉን ወደፊት ማስኬድ ይህን መሰሉን ጭቆና ለማስቆም ብቸኛው አማራጫችን እንደሆነም እንገነዘባለን። በዚህ ስሌት ዱላው ሲበረታብን፣ እኛም እየበረታን ትግላችንን እናስቀጥላለን። ደርግም የወደቀው በዚህ መንገድ ነው፡፡ ጭቆና ትግልን ያጠነክራል እንጂ ትግልን አይገድልም፡፡ ህዝቡም ይሄን ያውቃል፡፡ የትግራይ ህዝብ፤ ህወሓት ለትግሉ የተሠው ሠማዕታትን አላማ እንደካደ በሚገባ ተገንዝቧል፡፡ የብሄር ተዋፅኦ ተመጣጣኝ እንዲሆን ተብለው ህወሓትን ባለመደገፋቸው ብቻ ከጦር ሠራዊት እንዲቀነሱ የተደረጉ አሉ፡፡ በመከላከያ ሠራዊት ውስጥ የብሔር ተዋጽኦ ይኑር የሚለውን አትደግፉም ማለት ነው? በሠራዊት ግንባታው ላይ አሁንም የትግራይ ህዝብ ከከፈለው መስዋዕትነት አንፃር ተጠቃሚ አይደለም፡፡ ይሄን የምልህ እንደግለሰብ ባለኝ አቋም ነው እንጂ በፓርቲያችን የተያዘ አቋም አይደለም፡፡ በየግንባሩ ሲዋጉ የወደቁት ወንድሞቻችን አሉ፡፡ ሌላው በገበያ ላይ ተደብድቦ፣ ተገደሎ ህዝቡ የከፈለው መስዋዕትነት አለ፣ እንዲሁም በከተማ የነበረው ትግል አለ፡፡ እነዚህ መስዋዕትነቶች አጉል መቅረት የለባቸውም፤ ወደላቀ ደረጃ መሸጋገር አለባቸው፡፡ በእርግጥም ኢህአዴግ እንደሚለው የተመጣጠነ ሠራዊት ለመገንባት እነዚህን ለትግሉ መስዋዕት የሆኑ ወገኖችን መቀነስ ተገቢ አይደለም፡፡ በቀጥታ ነበር መቀጠል የነበረባቸው፡፡ ቅነሣው ሲካሄድ ደግሞ የእነሱ ታዛዥ ያልሆኑትንና በኤርትራ ላይ ከነሱ የተለየ አቋም ያላቸው ተመርጠው ነው፡፡ ለነገሩ አጠቃላይ የስርአቱ ስትራቴጂ የታዛዥነትን መንፈስ ማስረጽ ነው፡፡ ለነሱ ታዛዥ ያልሆነ ምክንያት ተፈልጐለት ይገለላል፡፡

እኛ እንደ አቋም የግድ ከዚህኛው ብሔር ይሄን ያህል እያልን ቀመር ባናወጣለትም ሠራዊቱ የሁሉም ኢትዮጵያዊ ተዋጽኦ እንዲኖርበት እንፈልጋለን፡፡ የፓርቲያችሁ አንዳንድ አባላት የነበሩ ከሠላማዊ ትግል ወደ ትጥቅ ትግል ለመግባት ኤርትራ ሄደው ስልጠና እየወሰዱ ነው ይባላል? ይሄን መደበቅ አይቻልም፡፡ ከኛ የፓርቲው ማዕከላዊ ኮሚቴ አመራር የነበረ ጐይቶም በርሄ የሚባል ሰው የትኛውን ቡድን እንደተቀላቀለ ባላውቅም ወደ ኤርትራ እንደሄደ ይታወቃል፡፡ እኔ ይሄ አካሄድ ይጠቅማል የሚል እምነት የለኝም፡፡ እዚሁ የኢህአዴግን ጫና ተቋቁሞ ትግል ማድረግ አሁንም ይቻላል፡፡ በኢህአዴግ ውስጥም ሁሉም ክፉዎች ናቸው ብዬ አላምንም፡፡ የዲሞክራሲ ምህዳሩ መጥበብ የሚያሳስባቸው ይኖራሉ የሚል ግምት ነው ያለኝ፡፡ የተከፈለውን መስዋዕትነት እና አሁን እየተደረገ ያለውን እያዩ የሚብከነከኑ የኢህአዴግ አባላት እንደሚኖሩ ጥርጥር የለውም። ስለዚህ መሣሪያ ማንሣትን አማራጭ የሚያደርጉ ወገኖች ተቀባይነት የላቸውም፤ ዞሮ ዞሮ በጠላት ሃይል ነው የሚደገፉት፡፡

የሠላማዊ ትግላችሁ እርምጃ ለውጤት ያበቃናል ብላችሁ ታምናላችሁ? ኢህአዴግ የፖለቲካ ሜዳውን ከከፈተው አሁን ያሉት ተቃዋሚዎች እንደሚያሸንፉት ጥርጥር የለውም፡፡ ህዝቡ ከሚገባው በላይ ኢህአዴግን ጠልቶታል ብዬ ነው የማስበው፡፡ የኢህአዴግ የመከፋፈል፣ አንድን ህዝብ አንዱ በጥርጣሬ አይን እንዲመለከተው የሚያደርገው ሁሉ በህዝቡ ተነቅቶበታል፡፡ በተቃዋሚዎች በኩል ደግሞ ወደ አንድ አቅጣጫ የመምጣት ሂደቱ አሁን ላይ የተሻለ ይመስላል፡፡ ተቃዋሚዎች ያለንን የፖሊሲ ልዩነት እያጠበብን፣ ወደ አንድ አቅጣጫ እየመጣን ነው ብዬ አምናለሁ፡፡ ለውጡ በዚህ ብቻ አይደለም የሚመጣው፡፡ በኢህአዴግ ውስጥም ቅን አሣቢ የሆኑ፣ ለህዝብ የሚቆም ህሊና ያላቸው ወገኖች ይኖራሉ ብዬ እገምታለሁ፡፡ ሸምቀቆው እየበረታ ሲሄድ “ይሄማ ትክክል አይደለም” ብለው የትግሉ አላማ መካዱን የሚያስታውሱ ሰዎች ይፈጠራሉ የሚል እምነት አለኝ፡፡ ኢህአዴግን መቀየር አለበት። ህዝብ እየጠላው ነው ብለው የሚያምኑ ወገኖች በራሱ በኢህአዴግ ውስጥም እንዳሉ ጥርጥር የለኝም፡፡ መሠረታዊ ጥያቄው ኢህአዴግ እንዴት ስልጣን ይልቀቅ የሚለው ነው፡፡ በመሣሪያ ከሆነ ለሃገሪቱም ለሁላችንም ኪሣራ ነው፡፡ በሠላማዊ መንገድ ከሆነ ግን ለኢህአዴግም ወርቃማ ታሪክ፣ ለአገሪቱም ታላቅ ድል ነው፡፡ እኔ አቶ መለስ በስልጣን ላይ እያሉ በመሞታቸው በጣም ነው የማዝነው፡፡ በጣምም ይቆጨኛል፡፡ የትግሉ አላማ ይሄ አልነበረም፡፡ እሣቸው ግን የእነ አፄ ዮሐንስን፣ ሚኒልክን፣ ሃይለስላሴን ታሪክ ነው የደገሙት። አዲስ ነገር አላመጡም፡፡

ከስልጣኑ ገለል ብለው ህልፈታቸው ቢሆን ደስታዬ ነበር፡፡ በዚህች ሀገር ታሪክ ውስጥ በጣም የተከበሩ የመሆን እድልም ያገኙ ነበር፡፡ ኢህአዴግ ከአቶ መለስ ተምሮ ታሪኩን ላለማበላሸት መስራት አለበት እላለሁ፡፡ እሱም እንደመሪው ሞቴን በስልጣን ላይ ያድርገው ካለ፣ በገዛ እጁ ታሪኩን እንዳበላሸ እቆጥረዋለሁ። ራሱን ተቃዋሚ ሆኖ ለማየት መጓጓት እንዳለበት ይሠማኛል፡፡ ከኢህአዴግ ውስጥ ለውጥ እንደሚጀምር ያያችሁት ፍንጭ ይኖር ይሆን በተለይ በህወሓት በኩል የመከፋፈል ነገር አለ ማለት ነው? ይፋ የወጣ ነገር ባይኖርም በግሌ ከአንዳንዶች ጋር ስንወያይ “አቶ መለስ በስልጣን ላይ ሙጭጭ እንዳሉ ህይወታቸው ማለፉ የትግሉ አላማን የሣተ ነው፤ በእርግጥም ከስልጣን ወርደው ህይወታቸው ቢያልፍ ለራሳቸውም ለሀገራቸውም ታሪክ ይሆን ነበር፡፡ የትግሉ ፍሬም ውጤቱ ያምር ነበር” እያሉ የሚቆጩ ሰዎች አሉ፡፡ እነዚህ ሰዎች በዚህ የሚቆጩ ከሆነ፣ ህወሓት ኢህአዴግ በስልጣን ላይ እንዳለ እንዲሞት አይፈልጉም ማለት ነው፡፡ እኔ በ2007 ምርጫ ኢህአዴግ በምርጫ ተሸንፎ በሠላም ከስልጣን ይለቃል የሚል ተስፋ አለኝ፡፡ ከለቀቀ በኋላ ደግሞ ሰዶ ማሳደድ ሣይሆን እንደማንኛውም ተቃዋሚ ሆኖ እናየዋለን ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡ እንደምትሉት ግን ኢህአዴግን በምርጫ አሸንፎ ስልጣን መያዝ ቀላል ነው? በሚገባ ማሸነፍ ይቻላል፡፡ ዋናው የሠላማዊ ትግል መንገድ የተደላደለ ይሁን፣ ተቃዋሚዎችም ከልባቸው ከታገሉ በእርግጥም ኢህአዴግን በምርጫ ለማሸነፍ የአንድ ወር ስራ በቂ ነው፡፡ ተቃዋሚዎች ውስጥም ሃገር ለመምራት፣ ሚኒስትር ለመሆን እና ህዝብን ለማስተዳደር አቅም ያላቸው ሰዎች እንዳሉ እንኳን ህዝቡ ኢህአዴግም በሚገባ ይገነዘበዋል፡፡ ኢህአዴግ እኮ ውጤቱን የሚለካው ግሎባላይዜሽን ባመጣቸው ነገሮች ነው፡፡ ሞባይል ለገበሬው አከፋፈልኩ፣ መብራት አስገባሁ ነው የሚለው፡፡ አረና የግንቦት 20 በዓልን ያከብራል? ሠማዕታትንስ እንደ ህወሓት በየአመቱ ይዘክራል? ትግሉ የተጀመረበት የካቲት 11 እና ትግሉ ፍፃሜ ያገኘበት ግንቦት 20 በህወሓት ኢህአዴግ የሚከበሩ ናቸው፡፡ አረና እንደፓርቲ እስካሁን ግንቦት 20ን ለይቶ አክብሮ አያውቅም፡፡ ግን እንደ ግለሰብ የምኮራበት ሊሆን ይችላል፡፡ በግንቦት 20 ምክንያት ቀለበት መንገድ ተሠራ፣ በግንቦት 20 ምክንያት የባቡር ሃዲድ እየተሠራ ነው፣ የአባይ ግድብ የግንቦት 20 ፍሬ ነው ከተባልኩ ግን ፈጽሞ አልቀበለውም። በተለያዩ የቀደሙ መንግስታትም ቢሆን እነዚህን የመሠሉ የልማት አቅጣጫዎች ነበሩ፡፡

አሁን በዚህ ዘመን አፄዎቹ መሪ ቢሆኑም የሚሠሯቸውን ነው ኢህአዴግ እየሠራ ያለው፤ የተለየ ታሪክ አልፈጠረም፡፡ የግንቦት 20 ፍሬን በዚህ አይደለም የምለካው፡፡ ኢህአዴግ በሠላማዊ መንገድ ከስልጣን ሲወገድ ነው ትግሉ ፍሬ አፍርቷል የምለው፡፡ በሠላማዊ መንገድ ስልጣን ማሸጋገር ከተጀመረ የካቲት 11 እና ግንቦት 20 ልዩ ይሆናሉ ብዬ አስባለሁ፡፡ ይህ ካልሆነ ግን ከመስከረም 2 የሚለዩብኝ አይሆንም፡፡ ስለዚህ ግንቦት 20 ፍሬ አፍርቷል ብዬ አላምንም፡፡ ግን ሠላማዊ ሽግግር የሚደረግና የሠማዕታቱ ህልም የሚፈታ ከሆነና ግንቦት 20 ትልቅ በአል ይሆናል ብዬ አምናለሁ፡፡

ምንጭ፡ አዲስ አድማስ

No comments:

Post a Comment