በኣብርሃ ደስታ
በአፅቢ ወንበርታ ወረዳ የህዝብ ዓመፅ መቀስቀሱ ይታወቃል። ለዓመፁ መቀስቀስ ተጠያቂው ህወሓት ነው። ምክንያቱም ህዝባዊ ዓመፁ የተቀሰቀሰው ገዢውን ፓርቲ ህወሓት መንግስታዊ ሐላፊነቱ ስላልተወጣ ነው። ምክንያቱም የአፅቢ ወንበርታ ወረዳ አርሶአደሮች ያመፁበት ምክንያት በመንግስት ለተወሰደባቸው መሬት መንግስት ተገቢውን ካሣ መክፈል ባለመቻሉ ነው። መንግስት ተገቢውን ካሣ አለመክፈሉ የመንግስት ችግር ነው። ስለዚህ ዓመፁ የተቀሰቀሰው በመንግስት ጉድለት እስከሆነ ድረስ ለዓመፁ ተጠያቂ በህወሓት/ኢህአዴግ የሚመራው መንግስት ነው።
ዜጎች አስፈላጊውን ካሳ ሳይከፈላቸው ከቀያቸው ማፈናቀል ሕገ ወጥ ነው። መንግስት ለሁለት ዓስርት ዓመታት ለአርሶአደሮች ካሳ ሳይከፍል መቆየቱ ለህዝቡ ያለው ንቀት የሚያሳይ ነው። ህዝብ ለተወሰደበት መሬት ይሁን ሌላ ንብረት ካሳ የመጠየቅ ሙሉ መብት አለው። የአፅቢ ወንበርታ ህዝብም ለተወሰደበት መሬት ካሳ የመጠየቅ ሕገመንግስታዊ መብት አለው። ህዝቡ ካሳ ጠየቀ፤ መብቱ ጠየቀ። ስለዚህ የአፅቢ ወንበርታ ህዝብ ዓመፅ የመብት ጥያቄ ነው።
መንግስት ለቀረበለት የህዝብ ጥያቄ ተገቢውን መልስ ከመስጠት ይልቅ የሃይል እርምጃ ወሰደ። መንግስት ሐላፊነቱን ባለመወጣቱ ምክንያት የመብት ጥያቄው ወደ ዓመፅ ተሸጋገረ። መንግስት በአግባቡ ካሳ የመክፈል ግዴታው፣ ፍትሕ የማስፈን ሐላፊነቱ፣ ህዝቦችን በእኩልነት የማገልገል ተልእኮው ቢወጣ ኑሮ ዓመፁ አይቀሰቀስም ነበር። ስለዚህ ለዓመፁ መቀስቀስ ገዢው ፓርቲ ህወሓት ሐላፊነት ወስዶ ህዝቡን ይቅርታ መጠየቅ አለበት።
ህዝቡ የካሳ ጥያቄው ሲያነሳ መንግስት ህዝቡን ከማስፈራራት ቢቆጠብ ኑሮ ችግሩ አይፈጠርም ነበር። ህዝብ ጥያቄ ሲያነሳ መንግስት መልስ መስጠት አለበት። መልሱ ደግሞ ጥያቄውን መመለስ እንጂ ማስፈራራት አይደለም። መንግስት የቆመው ህዝብን ለማገልገል እንጂ ህዝብን ለመበደልና ለማስፈራራት አይደለምና።
መንግስት ያጠፋው ጥፋት ምንድነው? ለዓመፁስ እንዴት ህወሓት ተጠያቂ ይሆናል? ህዝቡ ካሳ የማግኘት መብቱ ጠየቀ። ካሳ መጠየቅ ሕጋዊ መብት ነው። ስለዚህ የህዝቡ ጥያቄ ትክክል ነው። መንግስት ካሳ ለመክፈል (የህዝብ ጥያቄ ለመመለስ) ፍቃደኛ አልሆነም። ስለዚህ መንግስት መንግስታዊ ግዴታው አልተወጣም። እዚህ ላይ ገዢው ፓርቲ ህወሓት ተጠያቂ ነው። የካሳው ጉዳይ በግዜውና በአግባቡ መመለስ አልቻለምና።
የህዝቡን ጥያቄ አለመመለስ የህዝቡን መብት መርገጥ ነው። ህዝቡ መብቱን ለማስከበርና የመንግስትን ተግባር ትክክል አለመሆኑ ለማሳየት ተቃውሞ አስነሳ። ህዝብ መብቱ ለማስከበር መንግስትን የመቃወም ሕገመንግስታዊ መብት አለው። ስለዚህ የህዝቡ ተቃወም ትክክል ነበር። ህዝብ መብቱን የማስከበር መብት አለውና።
መንግስት ተቃውሞውን ከማብረድ ይልቅ ፖሊሶችን በመላክ የሃይል እርምጃ ወሰደ። ጥያቄ ያነሱ አርሶ አደሮችን አሰረ። ያከባቢው ኗሪዎች የፖሊስን ተግባር በመቃወም ተሰባሰቡ። ፖሊስ ህዝብን ደበደበ፣ አሰረ። ፖሊስ ጥያቄ ያነሱ ዜጎችን የመደብደብ መብት የሰጠው ማነው? መብቱ የጠየቀ ዜጋ መታሰር አለበት ያለው የትኛው አንቀፅ ነው? ስለዚህ የፖሊስ የሃይል እርምጃ ስህተት ነው። አሁንም ለዚህ ጉዳይ ተጠያቂው ፖሊስ የላከ ገዢው ፓርቲ ህወሓት ነው።
ህዝቡ በፖሊስ ተደብድበው የታሰሩ ልጆቹ እንዲፈቱ ጠየቀ። ህዝብ ልጆቹ እንዲፈቱ የመጠየቅ መብት አለው። ስለዚህ የህዝቡ ጥያቄ ትክክል ነበር። ፖሊስ ጥያቄ ላነሳ ህዝብ ለማምበርከክ ተኩስ ከፈተ። በህዝብ ላይ ተኩስ አይከፈትም። ፖሊስ የተሰበሰበውን ህዝብ ለመበተን ተኩስ መክፈቱ አግባብነት የለውም። አሁንም ለተኩሱ ህወሓት ተጠያቂ ነው። ፖሊስ ፀጥታ የማስከበር ሐላፊነቱ በአግባቡ ከመወጣት ይልቅ በህዝብ ላይ ተኩስ በመክፈት ራሱ የፀጥታ ችግር ሁነዋልና።
ህዝብ ተኩስ ሲከፈትበት ራሱን ለመከላከል እርምጃ ወስዷል። አሁንም ህዝቡ ራሱ ከጥቃት የመከላከል መብት አለው። በህዝብ ላይ ተኩስ የከፈቱ ፖሊሶች በህዝብ ትብብር ሲታገቱ ፖሊሶችን ለማስለቀቅ ሲባል የህወሓት ባለስልጣናት ህዝቡን አታለውታል። ባለስልጣናቱ “የታሰሩት ልጆች እንፈታለን፣ አሁን እንለቃቸዋለን። ፖሊሶቹን ልቀቁልን” በሚል ከህዝቡ ጋር ተደራደሩ። ፖሊሶችም ተለቀቁ። ባለስልጣናቱ “የታሰሩት ተለቀው እየመጡ ነው” እያሉ በማጭበርበር ህዝቡ ተሰብስቦ እንዲጠባበቅ አደረጉ። በመጨረሻ ግን የታሰሩትን ከመልቀቅ ይልቅ መከላከያ ሰራዊት ጠርተው ህዝቡን አስከበቡት፣ አስፈራሩት፣ ተኩስ ከፈቱበት። ይህ በራሱ ክህደት ነው። ህዝብን የማታለል ወንጀል ነው። ለህዝብ ያላቸው ንቀት ያሳዩበት አጋጣሚ ነው። ወታደር ማስመጣት በራሱ ዓመፁ ማባባስ ነው። ጠመንጃ ለሌለው ሰለማዊ ህዝብ ወታደር መጥራት በራሱ አግባብነት የለውም።
ህዝብ እስረኞች ተለቀው ከቤተሰቦቻቸው ጋር እንዲቀላቀሉ በመጠባበቅ ላይ እያለ በወታደር እንዲከበብ ተደረገ። ይህ ራሱ የቻለ መንግስታዊ ግዴታን የመዘንጋት ጉድለት ነው። ባለስልጣናቱ በወታደሮች ታጅበው እስረኞቹ በሚቀጥለው ቀን እንደሚፈቱ ቃል ገብተው ህዝቡ እንዲበተን ጠየቁ። ህዝቡ ተበተነ። አከባቢው በወታደሮች ቁጥጥር ስር ሆነ። በነጋታው ህዝብ በተገባለት ቃል መሰረት ልጆቹን ለማስፈታት ተሰባሰበ። አሁንም ባለስልጣናቱ ቃላቸው አጥፈው የታሰሩትን ልጆቹ ለማየት የመጣን ህዝብ የፌደራል ፖሊስ ይዘው ጠበቁት። ልጆቹ ለማየት የተሰባሰበ ህዝብ በፌደራል ፖሊስ ተከቦ አስተዳዳሪዎች አስፈራሩት። የህዝቡ እርምጃ “ስህተት” እንደነበር ህዝቡ እንዲያምን ማስገደድ ያዙ። ይህም ሌላ ክህደት ነው።
ለመሆኑ እንዴት ፌደራል ፖሊስ ገባ? በፌደራል ስርዓት የፌደራል መንግስት ጣልቃ የሚገባበትና የማይገባበት መዋቅር አለ። የፌደራል ፖሊስ በጉዳዩ ላይ ጣልቃ መግባቱ በራሱ ስህተት ነበር። የክልል ፖሊስ፣ የፌደራል ፖሊስና የመከላከያ ሰራዊት አባላት በጉዳዩ ጣልቃ መግባታቸው በራሱ ለዓመፁ ማባባስ የራሱ ሚና ተጫውተዋል። የክልል መንግስት የፌደራል ፖሊስና መከላከያ ሰራዊት አባላትን መጋበዙ ሊጠየቅ ይገባል። እርምጃው ሕገ ወጥ ነውና።
በመጨረሻም ባለስልጣናቱ የህዝቡን ካሳ የመጠየቅ መብት ትክክለኛነት ተቀብሏል፤ ቢዘገይም። የአፅቢ ወንበርታ ህዝብ ተቃውሞ በማስነሳት መብትን ማስከበር እንደሚቻል አረጋግጧል። ለሁለት ዓስርት ዓመታት መፍትሔ ያላገኘ የካሳ ጥያቄ አሁን እንዲመለስ አድርገዋል። ለመብታችን በመታገል መብታችንን ማስከበር እንደምንችል የአፅቢ ወንበርታ ህዝብ አስመስክሯል። በዚሁ መሰረት የአፅቢ ወንበርታ ህዝባዊ ዓመፅ በድል ተጠናቋል ማለት ይቻላል። ጥያቄው ግን አላበቃም፤ የእስረኞቹ ጉዳይ፣ የፍትሕ፣ የልማትና የዴሞክራሲ ጥያቄዎች አሉ። ይቀጥላል።
ባለስልጣናቱ የህዝብን መሬት ካሳ ለመክፈል ተስማምተዋል (ትንሽ ቢያረፍዱም)። ካሳ ለመክፈል መስማማታቸው ጥሩ ቢሆንም የካሳ (የመብት) ጥያቄው ያነሱት ዜጎች ማሰራቸው ግን ስህተት ነው። ላጡትን መሬት ካሳ የመጠየቅ መብት እንዳላቸው ከተስማማን ለምን ጠያቂዎቹን እናስራለን? ስለዚህ ባለስልጣናቱ የካሳ ጥያቄው ትክክለኛነት ከተቀበሉ የካሳ ጥያቄ ያስነሱ አርሶአደሮች ማሰር አልነበረባቸውም፤ አሁንም ከእስር መልቀቅ ነበረባቸው። ካሳ ለመክፈል ተስማምተው ካሳ የጠየቁ ግን አሰሩ። ይህም አንድ የገዢው ፓርቲ ህወሓት በህዝብ ላይ ያለው ንቀት የሚያሳይ ነው።
የካሳ ጥያቄ በማንሳታቸው ምክንያት የታሰሩ ዘጎች በእስርቤት እየተሰቃዩ ይገኛሉ። በቤተሰቦቻቸው እንዲጎበኙ አልተፈቀደም። ዓመፁ የቀረፁ ዜጎችም ታስረው እየተገረፉ የገኛሉ። ለምን እንደቀረፁት፣ ማን እንዳዘዛቸው፣ ለማን ሊሰጡት እንደነበረ … ወዘተ እየተጠየቁ ይደበደባሉ። ዓመፁ ከቀረፁት አንዱ “እኔ የቀረፅኩት ተኩስ የከፈቱትን ሰዎች ለማወቅ ነው። ወላጆቼ በተኩሱ ከተገደሉ የወላጆቼን ገዳዮች እነማን እንደሆኑ ለመለየት ነው የቀረፅኩት” የሚል መልስ ሰጥቷል።
ህወሓት እነኚህ እስረኞች መፍታት አለበት። መብታቸው በመጠየቃቸው ነው የታሰሩት። የትግራይ ህዝብ የነዚህ ዜጎች ጉዳይ ያገባዋል። ዜጎቹን ለማስፈታት ሁላችን የበኩላችን መወጣት አለብን። የታሰሩትን ዜጎች ጉዳይ እንከታተለዋለን። ላደረጉት አስተዋፅዖም ሲታወሱ ይኖራሉ።
ሌላው አንገብጋቢ ጉዳይ የህወሓት ካድሬዎች በፌደራል ፖሊስ ታጅበው ቤትለቤት እየዞሩ ህዝብን እያስፈራሩ ይገኛሉ። ያመፀ ሁሉ እንደሚገደል ይናገራሉ፤ ህዝብን ለማሸበር። በዓረና ፓርቲ አባላት ላይ ጦርነት እንደሚያውጁ ያወራሉ። ህዝብ ከዓረና አባልነቱ እንዲለቅ ለማድረግ ዓረና የሆነ ሁሉ እንደሚገደል ለህዝብ ያውጃሉ። ይህን ሁሉ የሚደረገው ህዝቡን ለማሸበር ተብሎ ነው፤ ደርግ ያደርገው እንደነበረ ሁሉ።
ገዢዎች ዉድቀታቸውን ሲረዱ ህዝብን ማሸበር ይጀምራሉ።
ህወሓት ያሰራቸውን ዜጎች እንዲፈታ እንጠይቃለን!
No comments:
Post a Comment